መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ በሁሉም ቦታ ይገኛል?
በርካታ ሰዎች አምላክ ቃል በቃል በሁሉም ቦታና በሁሉም ነገሮች ውስጥ ይገኛል ብለው ያምናሉ። ይሁንና ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (1 ነገሥት 8:30, 39) አምላክ ማደሪያ ወይም መኖሪያ ስፍራ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰለሞን ይህንን ቦታ “ሰማይ” ሲል ጠርቶታል። ይሁን እንጂ ሰማይ የሚያመለክተው ምንን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ በምድር ዙሪያ ያለውን ግዑዝ ጽንፈ ዓለም ለማመልከት “ሰማይ” እና “ሰማያት” የሚሉትን ቃላት ይጠቀማል። (ዘፍጥረት 2:1, 4) ይሁንና አምላክ ሁሉን ነገር የፈጠረ እንደመሆኑ መጠን የእሱ መኖሪያ ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ከመፍጠሩ በፊት የነበረ መሆን አለበት። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ የሚኖረው ከቁስ አካል በተሠራ ነገር ውስጥ አይደለም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይ የአምላክ መኖሪያ እንደሆነ ሲናገር ከምድር ከባቢ አየር ውጭ ያለውን ቦታ ወይም ሕዋ እየጠቀሰ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ መንፈሳዊ ዓለም መናገሩ ነበር።
እጅግ አስደናቂ የሆነ ራእይ
ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ይሖዋ የሚኖርበትን እጅግ ማራኪ ስፍራ በራእይ እንደተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዮሐንስ በራእዩ ላይ በሰማይ አንድ የተከፈተ በር ከተመለከተ በኋላ አንድ ድምፅ “ና ወደዚህ ውጣ” ሲለው ሰማ።—ራእይ 4:1
ቀጥሎም ዮሐንስ እጅግ አስደናቂ በሆነ ራእይ ይሖዋ አምላክን ተመለከተ። ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ በከፊል ይህን ይመስላል፦ “በሰማይ ዙፋን ተቀምጦ ነበር፤ . . . በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ገጽታው እንደ ኢያስጲድና ቀይ ቀለም እንዳለው የከበረ ድንጋይ ነበር፤ በዙፋኑም ዙሪያ መረግድ የሚመስል ቀስተ ደመና ነበር። . . . ከዙፋኑም መብረቅ፣ ድምፅና ነጎድጓድ ይወጣ ነበር፤ . . . በዙፋኑም ፊት ክሪስታል የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ያለ ይመስል ነበር።”—ራእይ 4:2-6
ዕጹብ ድንቅና ተወዳዳሪ የሌለውን የይሖዋን ግርማና ውበት የሚያሳይ እንዴት ያለ መግለጫ ነው! እስቲ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ያሉትን ነገሮች እንመልከት። ቀስተ ደመናው የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታን ያመለክታል። መብረቁ፣ ድምፁና ነጎድጓዱ የአምላክ ኃይል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳያል። የብርጭቆው ባሕር በአምላክ ፊት የሚቆሙት ሁሉ ያላቸውን ንጹሕ የሆነ አቋም ያሳያል።
የራእዩ መግለጫ ምሳሌያዊ ቢሆንም ስለ አምላክ የመኖሪያ ስፍራ ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል። ይሖዋ በሰማይ ፍጹም ሥርዓት እንዲሰፍን አድርጓል። በመኖሪያ ስፍራው ከሥርዓት ውጪ የሆነ ምንም ነገር የለም።
በሁሉም ቦታ በማንኛውም ጊዜ ይገኛል?
ይሖዋ የመኖሪያ ስፍራ ያለው መሆኑ በሁሉም ቦታ በማንኛውም ጊዜ እንደማይገኝ ይጠቁማል። ታዲያ ነገሮች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚያውቀው እንዴት ነው? (2 ዜና መዋዕል 6:39) አንዱ መንገድ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ።”—መዝሙር 139:7-10
መንፈስ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ በሚገኙ ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚችል ለማስረዳት ፀሐይን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ፀሐይ ቋሚ የሆነ አንድ ቦታ ቢኖራትም ሰፊ ለሆነው የምድር ክፍል ኃይል ትሰጣለች። በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ አንድ የመኖሪያ ስፍራ አለው። ይሁንና በጽንፈ ዓለም ውስጥ በየትኛውም ቦታ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በሁሉም ቦታ በማንኛውም ጊዜ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ቅዱስ መንፈሱን ሊጠቀም ይችላል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:9 “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” በማለት የሚናገረው ከዚህ አንጻር ነው።
በተጨማሪም አምላክ፣ መላእክት የሚባሉ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈ ድርጅት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት በመቶ ሚሊዮን ምናልባትም በቢሊዮን ሊቆጠሩ ወይም ከዚያ በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማል።a (ዳንኤል 7:10) መላእክት አምላክን ወክለው ወደ ምድር እንደሚመጡና ሰዎችን እንደሚያነጋግሩ ከዚያም ያገኙትን መረጃ ለአምላክ እንደሚነግሩ የሚገልጹ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአብርሃም ዘመን መላእክት በሰዶምና በገሞራ የሚሰማውን ጩኸት ለማየት ወርደው ነበር። አምላክ ከተሞቹን ለማጥፋት የወሰነው እነዚህ መላእክት ያመጡትን መረጃ ከተቀበለ በኋላ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው።—ዘፍጥረት 18:20, 21, 33፤ 19:1, 13
በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው ይሖዋ በሁሉም ቦታዎች ቃል በቃል በአካል መገኘት አያስፈልገውም። ቅዱስ መንፈሱንና መላእክታዊ ሠራዊቱን በመጠቀም የፍጥረታቱን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ማወቅ ይችላል።
በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችንን በደንብ እንድናውቀው ሊረዳን ይችላል። አምላክ የሚኖረው ከግዑዙ ጽንፈ ዓለም ውጪ ባለ “ሰማይ” በተባለ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። እልፍ አእላፋት የሆኑ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራንም ከእሱ ጋር በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ይኖራሉ። በተጨማሪም ሰላም፣ ንጽሕናና ኃይል የአምላክ መኖሪያ ስፍራ ልዩ ገጽታዎች ናቸው። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ አሁን በሰማይ ላይ ያለው ዓይነት ሰላም በምድር ላይ እንደሚሰፍንና የሰው ልጆችም በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጣል።—ማቴዎስ 6:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ራእይ 5:11 (የ1954 ትርጉም) በአምላክ ዙፋን ዙሪያ “አእላፋት ጊዜ አእላፋት” መላእክት እንደነበሩ ይገልጻል። እልፍ ሲባል 10,000 ማለት ነው። አንድ እልፍ ሲባዛ አንድ እልፍ (10,000 x 10,000) 100 ሚሊዮን ይሆናል ማለት ነው። ይሁንና ይህ ጥቅስ “አእላፋት ጊዜ አእላፋት” የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል።
ይህን አስተውለኸዋል?
● አምላክ በሁሉም ቦታ ይገኛል?—1 ነገሥት 8:30, 39
● የአምላክ መንፈስ የማይደርስበት ቦታ አለ?—መዝሙር 139:7-10
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ፀሐይ ቋሚ የሆነ አንድ ቦታ ቢኖራትም በጣም ሰፊ ለሆነ ቦታ ኃይል ትሰጣለች። በተመሳሳይም አምላክ አንድ የመኖሪያ ስፍራ አለው፤ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ በጽንፈ ዓለም ውስጥ አምላክ የፈለገው ቦታ ሁሉ መገኘት ይችላል