ምዕራፍ 3
በቅርቡ መፈጸም ያለባቸው ነገሮች
1. አምላክ በዚህ ዓለም ላይ ከሚያመጣው ፍርድ ልታመልጥ የምትችለው እንዴት ነው?
በዘመናችን ያለው ዓለም ሁኔታ በጣም ሊያሳስብህ ይገባል። ለምን ቢባል ይህ ዓለም ከአምላክ የቅጣት ፍርድ ሊያመልጥ ስለማይችል ነው። አንተ ግን ልታመልጥ ትችላለህ። ጥፋት የተወሰነበት የዚህ ዓለም ክፍል ካልሆንክ ከጥፋቱ ልትድን ትችላለህ። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ችግርና ጉስቁልና የበዛበት የገዳም ኑሮ መኖር አለብህ ማለት አይደለም። ጤናማና ትርጉም ያለው ኑሮ እየኖርክ ራስህን ከፖለቲካ ውዝግብ፣ ከስግብግብ ንግድ፣ አምላክን ከሚያዋርድ የሐሰት ሃይማኖትና ከሥነ ምግባር ውጭ ከሆነ ቅጥ የለሽ አኗኗር መጠበቅ ይኖርብሃል ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክን የአቋም ደረጃዎች መጠበቅና ፈቃዱን ለማድረግ መፈለግ ይገባሃል። (ዮሐንስ 17:14-16፤ ሶፎንያስ 2:2, 3፤ ራእይ 21:8) በእነዚህ መስኮች ምን ያህል ትጋት ማሳየት እንደሚገባህና በአኗኗርህ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ያመለክታል።
2. ሐዋርያው ዮሐንስ ታላቁን የራእይ ትንቢት ያስተዋወቀው እንዴት ነው? አምላክስ ይህንን ከባድ መልእክት የሰጠው ለማን ነው?
2 ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ታላቅ ትንቢት ሲከፍት “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው” ራእይ እንደሆነ ገልጾአል። (ራእይ 1:1ሀ) ይህንን ክብደት ያለው መልእክት ከአምላክ የተቀበለው ከሙታን የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ የምሥጢራዊ ሥላሴ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ሳይሆን የአባቱ ተገዥ እንደሆነ ተገልጾአል። የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች የሆኑትም “ባሮች” በተመሳሳይ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስ ተገዥዎች ስለሆኑ ‘በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።’ (ራእይ 14:4፤ ኤፌሶን 5:24) ይሁን እንጂ በዛሬው ዘመን የአምላክ “ባሮች” እነማን ናቸው? የራእይስ መጽሐፍ የሚጠቅማቸው በምን መንገድ ነው?
3. (ሀ) ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገዙት “ባሮች” እነማን ናቸው? (ለ) ታማኞቹ “ባሮች” በመላእክት አመራር ሥር ሆነው ምን ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው?
3 የራእይን መጽሐፍ የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ራሱ ከእነዚህ ባሮች አንዱ እንደሆነ ተናግሮአል። በሕይወት የቀረ የመጨረሻው ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን በሰማያት የማይሞት ሕይወት ከሚቀበሉት ምርጥ በመንፈስ የተቀቡ “ባሮች” መካከል አንዱ ነበር። በዛሬው ዘመን በምድር ላይ የቀሩት የዚህ ክፍል አባሎች በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው። በተጨማሪም አምላክ ሌሎች አገልጋዮች አሉት። እነዚህም በአሁኑ ጊዜ ብዛታቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ የሆኑት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናት የሚገኙበት እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በመላእክት እየተመሩ የዘላለሙን ወንጌል ለሰው ልጆች በሙሉ በማወጁ ሥራ ከቅቡዓን “ባሮች” ጋር ይካፈላሉ። እነዚህ ባሮች በሙሉ፣ የምድር የዋሆች መዳንን እንዲያገኙ ለመርዳት ራሳቸውን ሳይቆጥቡ በትጋት ይሠራሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 7:9, 14፤ 14:6) ከዚህ አስደሳች ምሥራች ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚኖርብህ የራእይ መጽሐፍ ያመለክትሃል።
4. (ሀ) ዮሐንስ የራእይን መጽሐፍ ከጻፈ 1,900 ዓመት ስላለፈው “በቅርቡ ይሆን ዘንድ ያለውን” ነገር ተናግሯል ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ማስረጃ በትንቢት ስለተነገሩት ነገሮች ምን ያረጋግጣል?
4 ይሁን እንጂ ዮሐንስ “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባው ነገር” “ለባሪያዎቹ” ይገለጻል ሊል የቻለው እንዴት ነው? እነዚህ ቃላት የተነገሩት ከ1,900 ዓመታት በፊት አይደለምን? አንዱን ሺህ ዓመት “እንደ ትናንት ቀን” ለሚመለከተው ለይሖዋ አምላክ ምድርን ሲፈጥርና ለሰው ልጅ መኖሪያ እንድትሆን ሲያዘጋጅ ካሳለፈው ቁጥር ሥፍር ከሌለው ዘመን ጋር 1,900 ዓመት ሲወዳደር በጣም አጭር ጊዜ ነው። (መዝሙር 90:4) ሐዋርያው ጳውሎስ የተዘጋጀለት ሽልማት በጣም ቅርብና እርግጠኛ እንደሆነ ይሰማው ስለነበረ “ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነው” ሲል ጽፎአል። (ፊልጵስዩስ 1:20) ይሁን እንጂ ዛሬ በትንቢት የተነገረው ሁሉ በተመደበለት ቅደም ተከተልና ጊዜ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሞልቶአል። የሰው ልጅ ሕልውና እንደዛሬው በአደገኛ ሁኔታ ላይ የወደቀበት የታሪክ ዘመን የለም። ለዚህ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 45:21
የሐሳብ መገናኛ መስመር
5. ራእዩ በመጀመሪያ ለዮሐንስ ከዚያም ለጉባኤዎች የደረሰው እንዴት ነው?
5 ራእይ 1:1ለ, 2 እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ። እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ።” ስለዚህ ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረውን መልእክት የተቀበለው መልእክተኛ ሆኖ በተላከ አንድ መልአክ አማካኝነት ነበረ። ከዚያም በመጽሐፍ ጥቅልል ጽፎ በዘመኑ ለነበሩት ጉባኤዎች አስተላለፈው። ይህን መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት 100,000 ገደማ ለሚሆኑ የተባበሩ የአምላክ አገልጋዮች ጉባኤዎች ማበረታቻ እንዲሆን አምላክ ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረጉ ልንደሰት ይገባናል።
6. ኢየሱስ በዛሬው ዘመን ለባሮቹ መንፈሣዊ ምግብ የሚያቀርብበትን መስመር ለይቶ ያሳወቀው እንዴት ነው?
6 አምላክ በዮሐንስ ዘመን የራእይን መልእክት ያስተላለፈበት መገናኛ መስመር ነበረው። ዮሐንስም የዚህ መስመር ምድራዊ ክፍል ነበር። ዛሬም ቢሆን አምላክ ‘ለባሪያዎቹ’ መንፈሣዊ ምግብ የሚሰጥበት መስመር አለው። ኢየሱስ ስለ ሥርዓቱ የፍፃሜ ዘመን በተናገረው ታላቅ ትንቢት ላይ የዚህ መስመር ምድራዊ ክፍል “ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጥ ጌታው በቤተሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆነ ገልጾአል። (ማቴዎስ 24:3, 45-47) ይህንን የዮሐንስ ክፍል የትንቢቱን ትርጉም ለመፍታት አምላክ ይጠቀምበታል።
7. (ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ምልክቶች እንዴት ሊነኩን ይገባል? (ለ) ከዮሐንስ ክፍል አባሎች መካከል አንዳንዶቹ በራእይ ትንቢቶች ፍጻሜ ለምን ያህል ጊዜ ተካፍለዋል?
7 ኢየሱስ ራእዩን ያሳየው ‘በምልክቶች’ ወይም በምሳሌዎች እንደሆነ ዮሐንስ ጽፎአል። ምልክቶቹ አስደናቂዎች ሲሆኑ ለመመርመርም የሚያጓጉ ናቸው። ታላላቅ ድርጊቶችን የሚያመለክቱ ስለሆኑ ትንቢቱንና ትርጉሙን ለሰዎች እንድናሳውቅ ሊቀሰቅሱንና ቅንዓታችንን ሊያነሳሱ ይገባል። የራእይ መጽሐፍ ልብን የሚመስጡ ብዙ ትዕይንቶችን ይገልጽልናል። በእነዚህ ትዕይንቶች በሙሉ ዮሐንስ በተመልካችነት ወይም በተሳታፊነት ተካፍሎአል። እነዚህን ራእዮች በመፈጸሙ ሥራ ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተካፈሉት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ለሌሎች ለማብራራት እንዲችሉ የአምላክ መንፈስ የራእዮቹን ትርጉም ስለፈታላቸው በጣም ተደስተዋል።
8. (ሀ) እያንዳንዱ ራእይ ምን የተለየ ባሕርይ አለው? (ለ) የዳንኤል ትንቢት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱትን አራዊት ምንነት እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
8 በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ራእዮች በአፈጻጸም ቅደም ተከተል የቀረቡ አይደሉም። እያንዳንዱ ራእይ የሚፈጸምበት የራሱ ጊዜ አለው። ብዙዎቹ ራእዮች ቀደም ሲል የተነገሩ ትንቢቶች ቃላት ይገኙባቸዋል። ይህም ትርጉማቸውን የምንረዳበትን ፍንጭ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል የዳንኤል ትንቢት አስፈሪ ስለሆኑ አራት አራዊት ከተናገረ በኋላ እነዚህ አራዊት ምድርን ለመግዛት የሚነሱ ኃይሎችን እንደሚያመለክቱ ይገልጻል። ስለዚህ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት አራዊት የፖለቲካ ገዥዎችን፣ በዘመናችን የሚገኙትን ጭምር እንደሚያመለክቱ ለመረዳት እንችላለን።—ዳንኤል 7:1-8, 17፤ ራእይ 13:2, 11-13፤ 17:3
9. (ሀ) የዮሐንስ ክፍል እንደ ዮሐንስ ያለ ምን ዝንባሌ አሳይቶአል? (ለ) ዮሐንስ ደስተኛ ለመሆን የምንችልበትን መንገድ ያመለከተን እንዴት ነው?
9 አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጠውን መልእክት ዮሐንስ በታማኝነት መስክሮአል። ‘ያየውን ሁሉ’ በዝርዝር ገልጾአል። የዮሐንስ ክፍልም ትንቢቱን ሙሉ በሙሉ ለመረዳትና አስፈላጊዎቹን ነጥቦች ለአምላክ ሕዝቦች ለማሳወቅ እንዲችል የአምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን እርዳታና አመራር ከልብ ፈልጎአል። ዮሐንስ ለቅቡዓን ጉባኤዎች ጥቅም (አምላክ ከታላቁ መከራ በሕይወት ጠብቆ ለሚያሳልፋቸው ብሔራት አቀፍ እጅግ ብዙ ሰዎች ጭምር) የሚከተለውን ጽፎአል:- “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው።”—ራእይ 1:3
10. ደስታ ለማግኘት ከፈለግን በራእይ መጽሐፍ ረገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
10 የራእይን መጽሐፍ ብታነብ፣ በተለይ ደግሞ በውስጡ የተጻፈውን ብትጠብቅ ብዙ ጥቅም ታገኛለህ። ዮሐንስ ከመልእክቶቹ በአንዱ እንዲህ ብሎአል:- “ትዕዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና። ትዕዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፣ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።” (1 ዮሐንስ 5:3, 4) እንዲህ ያለውን እምነት ብትገነባ እጅግ በጣም ደስተኛ ልትሆን ትችላለህ።
11. (ሀ) የትንቢቱን ቃል መጠበቅ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ በአደገኛ ሁኔታ እየቀረበ የመጣው የትኛው ጊዜ ነው?
11 “ዘመኑ ቀርቦአልና” የትንቢቱን ቃል መጠበቃችን በጣም አጣዳፊ ነው። የቀረበው ምን የሚሆንበት ዘመን ነው? የራእይ ትንቢቶች፣ የአምላክ ፍርድ ጭምር የሚፈጸምበት ዘመን ነው። አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን በሚገዛው ዓለማዊ ሥርዓት ላይ የመጨረሻውን ፍርድ የሚያወርዱበት ጊዜ ቀርቦአል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “ቀኑን ወይም ሰዓቱን” የሚያውቀው አባቱ ብቻ እንደሆነ ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ በዘመናችን በጣም የበዛውን መከራ አስቀድሞ በመመልከት “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሎአል። ስለዚህ አምላክ ፍርዱን የሚፈጽምበት ጊዜ በአደገኛ ሁኔታ ቀርቦአል ማለት ነው። (ማርቆስ 13:8, 30-32) ዕንባቆም 2:3 እንደሚለው “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፣ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም።” ከታላቁ መከራ መዳናችን የአምላክን የትንቢት ቃል በመጠበቃችን ላይ የተመካ ነው።—ማቴዎስ 24:20-22
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የራእይን መጽሐፍ ለመረዳት የሚያስፈልጉን ነገሮች
● የይሖዋን መንፈስ እርዳታ ማግኘት
● የጌታ ቀን የጀመረበትን ጊዜ ማስተዋል
● በዘመናችን ያለውን ታማኝና ልባም ባሪያ ማወቅ