የአንባብያን ጥያቄዎች
“ሌሎች በጎች” እና “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መካከል ልዩነት አለ ለማለት ይቻላልን?
አዎን፣ ልዩነት አላቸው፤ ይሁን እንጂ ስለ ቃላት አጠቃቀም ከመጠን በላይ ጥንቁቆች መሆን ወይም አንድ ሰው አንድን ነገር ለመግለጽ ሁለቱን ቃላት እያቀያየረ ቢጠቀምባቸው በነገሩ ቅር መሰኘት አይኖርብንም።
ብዙ ክርስቲያኖች እነዚህ ቃላት የሚገኙባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሳምረው ያውቋቸዋል። አንደኛው የሚገኘው ዮሐንስ 10:16 ላይ ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” ብሏል። “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚለው ሌላው ቃል ደግሞ ራእይ 7:9 ላይ ይገኛል። እንዲህ እናነባለን፦ “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ።”
በመጀመሪያ ዮሐንስ 10:16ን እንመልከት። በጎቹ እነማን ናቸው? ሁሉም የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች በጎች ተብለው እንደሚጠሩ መገንዘብ ይገባናል። በሉቃስ 12:32 ላይ ሰማያዊ ውርሻ ያላቸውን ደቀ መዛሙርቱን “ታናሽ መንጋ” ሲል ጠርቷል። የምን መንጋ ናቸው? የበጎች መንጋ ናቸው። “የታናሹ መንጋ” “በጎች” በሰማይ የመንግሥቱ ክፍል ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደ በግ የሚቆጥራቸው ከዚህ የተለየ ተስፋ ያላቸው ሌሎች ሰዎች አሉ።
ይህንንም በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ማየት እንችላለን። ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ሕይወት ስለሚጠራቸው እንደ ሐዋርያት ያሉ በጎች ከተናገረ በኋላ በቁጥር 16 ላይ “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል” ብሏል። በዚህ ቁጥር ላይ ኢየሱስ ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስለሚኖራቸው ሰዎች መናገሩ እንደነበረ የይሖዋ ምሥክሮች ከረዥም ጊዜ በፊት ተረድተውታል። እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ኖኅ እና ሚልክያስ ያሉት ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖሩ የነበሩ ብዙ ታማኝ ሰዎች የነበራቸው ተስፋ ምድራዊ ነው። በዚህም ምክንያት በዮሐንስ 10:16 ላይ ከተጠቀሱት “ሌሎች በጎች” ጋር ብንመድባቸው ትክክል ነው። እንደነዚህ ያሉት የቅድመ ክርስትና ዘመን ምሥክሮች በሺህ ዓመቱ ግዛት ከሙታን ተነስተው ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከተማሩና እርሱን ከተቀበሉ በኋላ የመልካሙ እረኛ “ሌሎች በጎች” ይሆናሉ።
በተጨማሪም የሰማያዊው ክፍል አጠቃላይ ጥሪ ካበቃ ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነዋል። እነዚህም የ“ታናሹ መንጋ” ክፍል ባለመሆናቸው “ሌሎች በጎች” ተብለው መጠራታቸው ተገቢ ነው። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሌሎች በጎች በምድራዊ ገነት የሚኖሩበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃሉ።
በራእይ 7:9 ላይ ስለተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ማንነትስ ምን ለመናገር እንችላለን? ቁጥር 13ን ብንመለከት “እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” የሚል ጥያቄ እንደቀረበ እናነባለን። መልሱን ራእይ 7:14 ላይ እናገኛለን። ጥቅሱ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” ይላል። ስለዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከታላቁ መከራ በሕይወት የተረፉ ወይም የወጡ ሰዎች ናቸው። ቁጥር 17 በምድር ላይ ‘ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ እንደሚመሩ’ ይናገራል።
እነዚህ ሰዎች እየቀረበ ካለው ታላቅ መከራ ለመትረፍ ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው እውነተኛ አምላኪዎች መሆን እንደሚያስፈልጋቸው ለመገንዘብ እንችላለን። ስለዚህም ራእይ 7:9 እነዚህን ሰዎች “እጅግ ብዙ ሰዎች” ብሎ ሲጠራቸው ከመከራው በኋላ ስለሚኖራቸው ሁኔታ በመግለጽ ቢሆንም “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚለው ቃል መንግሥታት በሐሰት ሃይማኖት ላይ በሚያደርሱት ጥቃት የሚጀምረው ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ባለው በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት ልንጠቀምበት እንችላለን።
ለማጠቃለል ያህል “ሌሎች በጎች” የሚለው ቃል በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ የሚያጠቃልል ሰፋ ያለ ቃል ነው ለማለት እንችላለን። በዛሬው ጊዜ የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ክፍል ለመሆን በመሰብሰብ ላይ የሚገኙትንና በጣም እየቀረበ ካለው ታላቅ መከራ በሕይወት የማለፍ ተስፋ ያላቸውን የተወሰነ የበጎች ክፍል የሚያካትት ቃል ነው። በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኙት አብዛኞቹ ታማኝ ክርስቲያኖች ‘የሌሎች በጎችም’ ‘የእጅግ ብዙ ሰዎችም’ ክፍል ናቸው።
ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ስያሜዎች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ማግኘታችን ጥሩ ነገር ቢሆንም ከሚገባው በላይ ቃል ሰንጣቂዎች በመሆን ስለ ቃላት መጨነቅ የማይገባን መሆኑንም ደግመን ለማሳሰብ እንወዳለን። ጳውሎስ ‘በትዕቢት ተነፍተው በቃል ይዋጉ’ ስለ ነበሩ አንዳንድ ሰዎች በመጥቀስ አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5) በቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ተገንዝበን ከሆነ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትን በትክክል የማይጠቀሙ ቢኖሩ በግልጽም ሆነ በውስጣችን ልንተቻቸው አይገባንም።