እውነተኛ አምላኪዎች የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች የመጡት ከየት ነው?
“እነሆም . . . ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ።”—ራእይ 7:9
1. በራእይ መጽሐፍ ላይ ያሉት ትንቢታዊ ራእዮች በዛሬው ጊዜ ትኩረታችንን በእጅጉ የሚስቡት ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ ላይ ከይሖዋ ዓላማ ጋር የተያያዙ አስደናቂ ክንውኖች የታዩባቸውን ራእዮች ተመለከተ። በራእይ ካያቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ጊዜያቸውን ጠብቀው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈጸማሉ። እነዚህ በሙሉ ይሖዋ በፍጥረታት ሁሉ ፊት ስሙን ለመቀደስ ባለው ታላቅ ዓላማ አስደናቂ ፍጻሜ ላይ ያተኮሩ ናቸው። (ሕዝቅኤል 38:23፤ ራእይ 4:11፤ 5:13) ከዚህም በላይ የእያንዳንዳችንን የሕይወት ተስፋዎች የሚመለከቱ ነገሮች ናቸው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
2. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ በአራተኛው ራእይ ላይ ያየው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ይህን ራእይ በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ዮሐንስ ከተገለጡት ተከታታይ ራእዮች መካከል በአራተኛው ላይ ‘የአምላካችን ባሪያዎች’ ግንባራቸው እስኪታተም ድረስ የጥፋትን ነፋሳት የያዙ መላእክት ተመልክቷል። ከዚያ በኋላ አንድ እጅግ አስደሳች የሆነ ትዕይንት ተመለከተ፤ ይሖዋን በማምለክና ልጁን በማክበር የተባበሩ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ተመልክቷል። ዮሐንስ እነዚህ ሰዎች ከታላቁ መከራ የመጡ ሰዎች እንደሆኑ ተነግሮታል። (ራእይ 7:1–17) ‘የአምላካችን ባሮች’ ተብለው የተገለጹት እነማን ናቸው? ከመከራው በሕይወት የተረፉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚሆኑት እነማን ናቸው? ከእነሱ አንዱ ትሆናለህን?
‘የአምላካችን ባሮች’ እነማን ናቸው?
3. (ሀ) በዮሐንስ 10:1–18 ላይ ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን ዝምድና በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በመሥዋዕታዊ ሞቱ አማካኝነት ለበጎቹ የከፈተላቸው አጋጣሚ ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ከመሞቱ ከአራት ወራት ገደማ በፊት እሱ “መልካም እረኛ” እንደሆነና ተከታዮቹ ደግሞ ሕይወቱን የሚሠዋላቸው “በጎቹ” እንደሆኑ ተናግሯል። በምሳሌያዊ ጉረኖ ውስጥ ያገኛቸውንና በኋላም ልዩ እንክብካቤ ያደረገላቸውን በጎች ለየት ባለ መንገድ ጠቅሷል። (ዮሐንስ 10:1–18)a ኢየሱስ በጎቹን ከኃጢአትና ከሞት ነጻ የሚያወጣቸውን መሥዋዕታዊ ዋጋ በመክፈል በፍቅራዊ መንገድ ነፍሱን ለእነርሱ ሲል አሳልፎ ሰጥቷል።
4. ኢየሱስ እዚህ ላይ ከተናገረው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ በጎች በመሆን በመጀመሪያ የተሰበሰቡት እነማን ናቸው?
4 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ከማድረጉ በፊት መልካም እረኛ በመሆን ራሱ ደቀ መዛሙርትን ሰብስቧል። የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው “በረኛ” የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ ያስረከባቸው ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ ከዚህም ከዚያም የተውጣጣው ‘የአብርሃም ዘር’ አባል መሆን የሚቻልበትን አጋጣሚ የሚቀበሉ ሰዎችን ይፈልግ ነበር። (ዘፍጥረት 22:18 አዓት ፤ ገላትያ 3:16, 29) ለሰማያዊቷ መንግሥት አድናቆትን በልባቸው ውስጥ አሳድሯል፤ በሰማያዊ አባቱ መኖሪያ ቦታ እንደሚያዘጋጅላቸውም አረጋግጦላቸዋል። (ማቴዎስ 13:44–46፤ ዮሐንስ 14:2, 3) ኢየሱስ “ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ሰዎች ለመግባት የሚጋደሉባት ግብ ሆናለች፤ እተየጋደሉ ወደፊት የሚገፉ ሁሉም ያገኟታል” ሲል ተስማሚ በሆነ መንገድ ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:12 አዓት) ይህን ግብ ለመጨበጥ እርሱን የተከተሉት ሰዎች ኢየሱስ በተናገረለት ጉረኖ ውስጥ ይሆናሉ።
5. (ሀ) በራእይ 7:3–8 ላይ የተጠቀሱት ‘የአምላካችን ባሮች’ እነማን ናቸው? (ለ) ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር በአምልኮ የሚተባበሩ ሌሎች ብዙዎች እንደሚኖሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 በራእይ 7:3–8 ላይ ያንን ሰማያዊ ግብ ለመጨበጥ እስከ መጨረሻው በብርቱ የሚጋደሉ ሰዎች ‘የአምላካችን ባሮች’ ተብለውም ተጠርተዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9, 16ን ተመልከት።) እዚያ ላይ የተጠቀሱት 144,000 ሰዎች በተፈጥሯቸው አይሁዳውያን የሆኑ ብቻ ናቸው? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ባለው ምሳሌያዊ ጉረኖ ውስጥ ያሉት አይሁዳውያን ብቻ ናቸው? በፍጹም አይደሉም፤ የአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል አባላት ናቸው፤ ሁሉም በመንፈሳዊው የአብርሃም ዘር ከክርስቶስ ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው። (ገላትያ 3:28, 29፤ 6:16፤ ራእይ 14:1, 3) እርግጥ ውሎ አድሮ የተወሰነው ቁጥር የሚሞላበት ጊዜ መኖር አለበት። ከዚያ በኋላስ? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሌሎች እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር ይቀላቀላሉ።—ዘካርያስ 8:23
“ሌሎች በጎች” ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ናቸውን?
6. ዮሐንስ 10:16 ምን ዓይነት ክስተት እንደሚኖር ይናገራል?
6 ኢየሱስ በዮሐንስ 10:7–15 ላይ አንድ ጉረኖ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ በማለት ስለ ሌላ ቡድን ተናገረ፦ “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ “ሌሎች በጎች” እነማን ናቸው?
7, 8. (ሀ) ሌሎች በጎች ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ናቸው የሚለው ሐሳብ በተሳሳተ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሌሎች በጎች እነማን መሆናቸውን ለመረዳት ስንጥር ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ የሚመለከቱ የትኞቹ እውነታዎች ናቸው?
7 የሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች በጥቅሉ እነዚህ ሌሎች በጎች አሕዛብ ክርስቲያኖች ናቸው፤ ከእነዚህ በፊት የተጠቀሱት በጉረኖ ውስጥ ያሉት ደግሞ በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የነበሩት አይሁዳውያን ናቸው፤ እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተወለደው አይሁዳዊ ሆኖ ነው፤ በትውልዱም የተነሣ በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ነበር። (ገላትያ 4:4) ከዚህም በላይ ሌሎች በጎችን የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት የሚያገኙ ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አንዱን የአምላክ ዓላማ ዐቢይ ክፍል ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ቀርተዋል። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲፈጥርና በኤደን የአትክልት ሥፍራ ሲያስቀምጣቸው ፈጣሪያቸውን እስከታዘዙና እስካከበሩ ድረስ ዓላማው ምድር በሰው እንድትሞላ፣ ሙሉ በሙሉ ገነት እንድትሆንና እንክብካቤ የሚያደርጉላት የሰው ልጆችም እየተደሰቱ ለዘላለም እንዲኖሩ እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ነበር።—ዘፍጥረት 1:26–28፤ 2:15–17፤ ኢሳይያስ 45:18
8 አዳም ኃጢአት ሲሠራ የይሖዋ ዓላማ አልከሸፈም። አምላክ የአዳም ዘሮች አዳም ሳያደንቀው የቀረውን አጋጣሚ እንዲያገኙ ፍቅራዊ ዝግጅት አደረገላቸው። ይሖዋ ሁሉም ሕዝቦች በረከት ሊያገኙ የሚችሉበት አዳኝ ይኸውም አንድ ዘር እንደሚያስነሳ አስቀድሞ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:18 አዓት) ይህ ተስፋ በምድር ላይ የሚገኙ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ ማለት አልነበረም። ኢየሱስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ በዮሐንስ 10:1–16 ላይ የተመዘገበውን ምሳሌ ከመናገሩ ከጥቂት ጊዜ በፊት አባቱ ሰማያዊውን መንግሥት የሚሰጠው ‘ለታናሹ መንጋ’ ብቻ እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 12:32, 33) ስለዚህ ኢየሱስ ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ መልካም እረኛ እንደሆነ አድርጎ ራሱን የገለጸበትን ምሳሌ ስናነብ ኢየሱስ በፍቅራዊ እንክብካቤው የሚያመጣቸውን የሰማያዊ መንግሥቱ ምድራዊ ተገዢ የሚሆኑትን ብዙሃኑን ገሸሽ ማድረግ ስህተት ይሆናል።—ዮሐንስ 3:16
9. ገና በ1884 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሌሎች በጎች እነማን እንደሆኑ ተረድተው ነበር?
9 መጠበቂያ ግንብ ሌሎች በጎች የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሲፈጸም በምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ የሚሰጣቸው ሰዎች እንደሚሆኑ ገና በ1884 ለይቶ ገልጾ ነበር። እነዚህ ቀደምት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከእነዚህ ሌሎች በጎች መካከል አንዳንዶቹ ከኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት በፊት የኖሩና ያንቀላፉ ሰዎች እንደሆኑ ተገንዝበው ነበር። ይሁን እንጂ በትክክል ያልተረዷቸው አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ሌሎች በጎች መሰብሰብ የሚጀምሩት ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን ካገኙ በኋላ ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። ያም ሆኖ ግን ሌሎቹ በጎች ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ብቻ እንዳልሆኑ በእርግጠኝነት ያውቁ ነበር። ከሌሎች በጎች አንዱ የመሆን አጋጣሚ ለአይሁዶችም ሆነ ለአሕዛብ፣ ለሁሉም ሕዝቦችና ዘሮች ክፍት ነው።—ከሥራ 10:34, 35 ጋር አወዳድር።
10. ኢየሱስ ሌሎች በጎቹ አድርጎ ከሚቆጥራቸው መሀል እንድንሆን ምን ነገር የምናደርግ መሆን አለብን?
10 ሌሎች በጎች ኢየሱስ የሰጠውን መግለጫ የሚያሟሉ ሆነው ለመገኘት ከየትኛውም ዓይነት ዘርና ጎሣ የመጡ ቢሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መልካም እረኛ አድርገው ዕውቅና ሊሰጡት ይገባል። ይህ ምንን ይጨምራል? የበጎች ጠባይ የሆኑትን የዋህነትንና ለመመራት ፈቃደኛ የመሆንን ባሕርያት ማሳየት አለባቸው። (መዝሙር 37:11) ልክ እንደ ታናሹ መንጋ እነርሱም ‘የመልካሙን እረኛ ድምፅ ማወቅና’ ሊስቧቸው በሚሞክሩ ሌሎች ሰዎች በመመራት ከመስመር እንዳይወጡ መከላከል አለባቸው። (ዮሐንስ 10:4፤ 2 ዮሐንስ 9, 10) ኢየሱስ ለበጎቹ ሲል ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት ያከናወነውን ነገር ዋጋማነት መገንዘብና በዚያ ዝግጅት ላይ ሙሉ እምነት መጣል አለባቸው። (ሥራ 4:12) መልካሙ እረኛ ለይሖዋ ብቻ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ፣ ዘወትር መንግሥቱን አስቀድመው እንዲፈልጉ፣ ከዓለም ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉና አንዳቸው ለሌላው የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚገለጽ ፍቅር እንዲያሳዩ አጥብቆ ሲያሳስባቸው እነርሱም በእሺታ መንፈስ ‘መስማት’ አለባቸው። (ማቴዎስ 4:10፤ 6:31–33፤ ዮሐንስ 15:12, 13, 19) ኢየሱስ እንደ ሌሎች በጎቹ አድርጎ ስለሚያያቸው ሰዎች የተሰጠውን መግለጫ ታሟላለህን? ለማሟላት ትፈልጋለህን? የኢየሱስ ሌሎች በጎች የሚሆኑ ሁሉ እንዴት ያለ ክቡር ዝምድና ተዘርግቶላቸዋል!
መንግሥቱ ላለው ሥልጣን አክብሮት ማሳየት
11. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መገኘቱ ጊዜ ምልክት ሲናገር ስለ በጎቹና ስለ ፍየሎቹ ምን አለ? (ለ) ኢየሱስ የጠቀሳቸው ወንድሞቹ እነማን ናቸው?
11 ከላይ የተገለጸውን ምሳሌ ከሰጠ በርከት ካሉ ወራት በኋላ ኢየሱስ እንደገና በኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጠው ቤተ መቅደሱ ያለበትን ቦታ እየተመለከቱ ‘የመገኘቱንና የዚህን የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ስለሚጠቁመው ምልክት ዝርዝር መግለጫ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ስለ በጎች መሰብሰብ እንደገና ተናገረ። ከተናገራቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፦ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹንም በግራው ያቆማቸዋል።” በዚህ መንገድ ንጉሡ ትኩረት ያደረገባቸው ሰዎች ‘ለወንድሞቹ’ በሚያደርጉት ነገር ላይ የተመሠረተ ፍርድ እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ አሳይቷል። (ማቴዎስ 25:31–46) እነዚህ ወንድሞቹ እነማን ናቸው? በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች ናቸው፤ ስለዚህ “የእግዚአብሔር ልጆች” ናቸው ማለት ነው። ኢየሱስ የአምላክ የበኩር ልጅ ነው። በመሆኑም የክርስቶስ ወንድሞች ናቸው። ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ እንዲካፈሉ ከሰው ዘር መካከል የተመረጡ በራእይ 7:3 ላይ የተጠቀሱት ‘የአምላካችን ባሮች’ ናቸው።—ሮሜ 8:14–17
12. ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞች የሚይዙበት መንገድ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው ለምንድን ነው?
12 ሌሎች ሰዎች ለእነዚህ የመንግሥቱ ወራሾች የሚያሳዩት ጠባይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ኢየሱስ ክርስቶስና ይሖዋ እነርሱን በሚመለከቱበት መንገድ ትመለከታቸዋለህን? (ማቴዎስ 24:45–47፤ 2 ተሰሎንቄ 2:13) አንድ ሰው ለእነዚህ ቅቡዓን ያለው አመለካከት ለራሱ ለኢየሱስ ክርስቶስና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለሆነው ለአባቱ ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃል።—ማቴዎስ 10:40፤ 25:34–46
13. በ1884 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ እስከ ምን ደረጃ ድረስ መረዳት ችለው ነበር?
13 መጠበቂያ ግንብ በነሐሴ 1884 እትሙ ላይ በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት “በጎች” በምድር ላይ ፍጹም ሕይወት የማግኘት ተስፋ በፊታቸው የተዘረጋላቸው ሰዎች እንደሆኑ በትክክል አመልክቶ ነበር። በተጨማሪም ምሳሌው ክርስቶስ በክብራማው ሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በሚገዛበት ጊዜ የሚፈጸም መሆን እንዳለበት መረዳት ተችሎ ነበር። ሆኖም እዚያ ላይ የተገለጸውን የመለየት ሥራ መቼ እንደሚጀምር ወይም ይህ የመለየት ሥራ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚካሄድ በግልጽ አልተረዱም ነበር።
14. በ1923 በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የተሰጠው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የኢየሱስ ትንቢታዊ ምሳሌ ስለሚፈጸምበት ጊዜ እንዲገነዘቡ የረዳቸው እንዴት ነው?
14 ይሁን እንጂ በ1923 በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ በሰጠው ንግግር የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ስለሚፈጸምበት ጊዜ የማያሻማ ማብራሪያ ሰጠ። ለምን? ከፊሉ ምክንያት ትንቢቱ ሲፈጸም የንጉሡ ወንድሞች፣ ቢያንስ ቢያንስ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ፣ ገና በምድር ላይ እንደሚገኙ ምሳሌው ስለሚገልጽ ነው። ከሰዎች መካከል ወንድሞቹ ተብለው በትክክል ሊጠሩ የሚችሉት በመንፈስ የተወለዱት ተከታዮቹ ብቻ ናቸው። (ዕብራውያን 2:10–12) እነዚህ የኢየሱስ ወንድሞች ኢየሱስ በገለጻቸው መንገዶች ሰዎች ለእነርሱ ጥሩ ማድረግ የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዲያገኙ ሲሉ የሺህ ዓመቱን ዘመን በሙሉ በምድር ላይ አይቆዩም።—ራእይ 20:6
15. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱትን በጎች በትክክል ለይተው ለማወቅ የረዷቸው የትኞቹ ክስተቶች ናቸው? (ለ) በጎቹ ለመንግሥቱ ያላቸውን አድናቆት ያሳዩት እንዴት ነው?
15 በ1923 በተሰጠው በዚያ ንግግር ላይ ጌታ ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች የሰጠው መግለጫ በእነማን ላይ እንደሚሠራ ለይቶ ለማወቅ ጥረት ተደርጎ ነበር፤ ይሁን እንጂ የምሳሌው ትርጉም ሙሉ በሙሉ ግልጽ ከመሆኑ በፊት ሌሎች ጉዳዮችን መረዳት አስፈልጎ ነበር። በተከታዮቹ ዓመታት ይሖዋ ቀስ በቀስ እነዚህን አስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮች አገልጋዮቹ እንዲገነዘቡ አደረጋቸው። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ እንደሆኑ በ1927 በግልጽ መረዳታቸው፣ እንዲሁም በ1932 ኢዮናዳብ ከኢዩ ጋር እንዳደረገው ከይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ጎን በድፍረት የመሰለፍን አስፈላጊነት ማስተዋላቸው ከእነዚህ ግንዛቤዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። (ማቴዎስ 24:45፤ 2 ነገሥት 10:15) በዚያን ጊዜ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች በራእይ 22:17 መሠረት በተለይ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በማድረሱ ሥራ እንዲካፈሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ለመሲሐዊቷ መንግሥት ያላቸው አድናቆት ለጌታ ቅቡዓን ሰብዓዊ ደግነት እንዲያሳዩ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ በኩል ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑና ከቅቡዓኑ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ እንዲሁም ቅቡዓኑ እየሠሩት ባለው ሥራ አብረዋቸው በቅንዓት እንዲካፈሉ ይገፋፋቸዋል። አንተ ይህን እያደረግህ ነውን? ይህን ለሚያደርጉ ንጉሡ “እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ይላቸዋል። በመንግሥቱ ምድራዊ ግዛት ውስጥ ፍጽምናን አግኝቶ ለዘላለም የመኖር ታላቅ ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቷል።—ማቴዎስ 25:34, 46
“እጅግ ብዙ ሰዎች” ወዴት እየተጓዙ ነው?
16. (ሀ) የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በራእይ 7:9 ላይ የተጠቀሱትን እጅግ ብዙ ሰዎች ማንነት በተመለከተ ምን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ነበሯቸው? (ለ) አመለካከታቸው የተስተካከለው መቼና በምን መሠረት ነው?
16 የይሖዋ አገልጋዮች በራእይ 7:9, 10 ላይ የተገለጹት እጅግ ብዙ ሰዎች በዮሐንስ 10:16 ላይ ከተገለጹት ሌሎች በጎችና በማቴዎስ 25:33 ላይ ካሉት በጎች የተለዩ እንደሆኑ አድርገው ረዘም ላለ ጊዜ ያምኑ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዙፋኑ ፊት እንደቆሙ’ ስለሚናገር የክርስቶስ ተባባሪ ወራሾች ሆነው በመግዛት ሳይሆን በዙፋኑ ፊት ሁለተኛ ደረጃ ቦታ ተሰጥቷቸው በሰማይ እንደሚሆኑ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ከልብ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያልነበራቸው፣ የታዘዙትን በማከናወን ረገድ አነስ ያለ ታማኝነት ያሳዩ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። በ1935 ይህ አመለካከት ታረመ።b እንደ ማቴዎስ 25:31, 32 የመሰሉትን ጥቅሶች ግምት ውስጥ በማስገባት በራእይ 7:9 ላይ የተደረገው ምርምር ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ‘በዙፋኑ ፊት’ መሆን እንደሚችሉ በማያሻማ መንገድ ግልጽ አደረገ። በተጨማሪም አምላክ ሁለት ዓይነት የታማኝነት ደረጃዎች እንደማያወጣ ተገልጿል። የእሱን ሞገስ የሚያገኙ ሁሉ ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ መቀጠል አለባቸው።—ማቴዎስ 22:37, 38፤ ሉቃስ 16:10
17, 18. (ሀ) በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉት ሰዎች ቁጥር ከ1935 ጀምሮ ከፍተኛ እድገት እንዲያሳይ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች በቅንዓት እየተካፈሉ ያሉት በምን እጅግ አስፈላጊ ሥራ ነው?
17 ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ሕዝቦች አምላክ ምድርን አስመልክቶ የገባውን ቃል ሲናገሩ ቆይተዋል። ይፈጸማል ብለው በጠበቁት ነገር የተነሣ ከብዙ ጊዜ በፊት በ1920ዎቹ ዓመታት “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞትን ፈጽሞ አያዩም” ብለው ለሕዝብ አውጀዋል። ሆኖም በዚያን ጊዜ አምላክ ለሕይወት ያዘጋጃቸውን ዝግጅቶች የተቀበሉት ሰዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ አልነበሩም። መንፈስ ቅዱስ እውነትን የተቀበሉትን የአብዛኞቹን ሰዎች ልብ ለሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ያነሳሳ ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ ከ1935 በኋላ አንድ ጎላ ያለ ለውጥ ተከሰተ። መጠበቂያ ግንብ በምድር ላይ የሚኖረውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ቸል ብሎት አልነበረም። ለአሥርተ ዓመታት የይሖዋ አገልጋዮች ስለዚህ ተስፋ ሲናገሩና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተስፋው የሚሰጠውን መግለጫ የሚያሟሉ ሰዎችን ሲጠባበቁ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እነዚህ ሰዎች ብቅ አሉ።
18 ለብዙ ዓመታት አብዛኛዎቹ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ ሰዎች ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ ይካፈሉ እንደነበር በእጅ ያለው መዝገብ ያሳያል። ይሁን እንጂ ከ1935 በኋላ በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ በማደግ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ ይካፈሉ የነበሩትን ሰዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ጊዜ እጥፍ በላይ የሚበልጥ ሊሆን ችሏል። እነዚህ ሌሎቹ እነማን ናቸው? እጅግ ብዙ ሰዎች የተባለው ክፍል አባላት የሚሆኑ ናቸው። ይሖዋ እነርሱን የሚሰበስብበትና ከፊታቸው ከሚጠብቃቸው ታላቅ መከራ በሕይወት እንዲተርፉ እነርሱን ማዘጋጀት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶ እንደነበረ ግልጽ ነበር። አስቀድሞ እንደተነገረው “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” የተውጣጡ ናቸው። (ራእይ 7:9) ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ በተነበየለት ሥራ በቅንዓት እየተካፈሉ ነው።—ማቴዎስ 24:14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ስለተገለጹት ጉረኖዎች ወቅታዊ የሆነ የተሟላ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10–20 እና ገጽ 31ን ተመልከት።
b የነሐሴ 1 እና 15, 1935 መጠበቂያ ግንብ
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ያለው ራእይ ልዩ ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
◻ በዮሐንስ 10:16 ላይ የተገለጹት ሌሎች በጎች ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ብቻ ያልሆኑት ለምንድን ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎች በጎች የሚሰጠውን መግለጫ የሚያሟሉ ሰዎች ምን ነገር የሚያደርጉ መሆን አለባቸው?
◻ የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ መንግሥቱ ላለው ሥልጣን አክብሮት የማሳየትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹትን እጅግ ብዙ ሰዎች የሚሰበስብበት ጊዜ እንደደረሰ የጠቆመው ነገር ምን ነበር?