የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የራእይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1
አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ በጳጥሞስ ደሴት ታስሮ ሳለ 16 ራእዮችን ተመለከተ። በእነዚህ ራእዮች ላይ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በጌታ ቀን ውስጥ የሚያከናውኗቸው ነገሮች ለዮሐንስ ተገልጠውለታል፤ የጌታ ቀን፣ የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመበት ከ1914 ጀምሮ የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እስከሚያበቃበት ወቅት ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ዮሐንስ በ96 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የጻፈው የራእይ መጽሐፍ ስለ እነዚህ ራእዮች የሚገልጽ አስደናቂ ዘገባ ይዟል።
ዮሐንስ የተመለከታቸውን የመጀመሪያዎቹን ሰባት ራእዮች የያዘውንና በራእይ 1:1 እስከ 12:17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ዘገባ ጎላ ያሉ ነጥቦች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። እነዚህ ራእዮች በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ከሚታዩት ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ከመሆናቸውም ሌላ ይሖዋ በቅርቡ እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ ስለሚያብራሩ ትኩረታችንን የሚስቡ ናቸው። ስለ እነዚህ ራእዮች የሚገልጸውን ዘገባ በእምነት የሚያነብቡ ሰዎች ማጽናኛና ማበረታቻ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዕብ. 4:12
“በጉ” ከሰባቱ ማኅተሞች ስድስቱን ከፈተ
በመጀመሪያ ዮሐንስ ክብር የተጎናጸፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን የተመለከተ ከመሆኑም ሌላ ‘በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ጽፎ ለሰባቱ ጉባኤዎች የሚልካቸውን’ ተከታታይ መልእክቶች ተቀበለ። (ራእይ 1:10, 11) ቀጥሎም በሰማይ የተቀመጠ ዙፋን በራእይ ተመለከተ። በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በሰባት ማኅተሞች የታሸገ ጥቅልል በቀኝ እጁ ይዞ ነበር። “ጥቅልሉን ሊከፍት የሚገባው” “ከይሁዳ ነገድ [ከሆነው] አንበሳ” ይኸውም “ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች” ካሉት ‘በግ’ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።—ራእይ 4:2፤ 5:1, 2, 5, 6
ሦስተኛው ራእይ “በጉ” የመጀመሪያዎቹን ስድስት ማኅተሞች ተራ በተራ በሚከፍትበት ወቅት የሚከናወኑትን ነገሮች ይገልጻል። ስድስተኛው ማኅተም ሲከፈት ታላቅ የምድር ነውጥ የተከሰተ ከመሆኑም በላይ ታላቁ የቁጣ ቀን መጣ። (ራእይ 6:1, 12, 17) ይሁንና ቀጣዩ ራእይ የ144,000ዎቹ መታተም እስኪያበቃ ድረስ ‘አራት መላእክት አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው እንደያዙ’ ያሳያል። ዮሐንስ፣ ማኅተም ያልተደረገባቸው “እጅግ ብዙ ሕዝብ . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው” ተመለከተ።—ራእይ 7:1, 9
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:4፤ 3:1፤ 4:5፤ 5:6—“ሰባቱ መናፍስት” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ሰባት ቁጥር በአምላክ አመለካከት ሙላትን ያመለክታል። በመሆኑም “ለሰባቱ ጉባኤዎች” የተጻፈው መልእክት በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ ባሉት ከ100,000 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙትን የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ይመለከታል። (ራእይ 1:11, 20) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠው ለማከናወን ከፈለገው ነገር ጋር በሚስማማ ሁኔታ በመሆኑ “ሰባቱ መናፍስት” የሚለው አነጋገር መንፈስ ቅዱስ፣ ለትንቢቱ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች ትንቢቱን መረዳት እንዲሁም በረከት ማግኘት እንዲችሉ በመርዳት ረገድ የሚያከናውነውን ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንደሚፈጽም ያመለክታል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች በሰባት በሰባት ሆነው ተገልጸዋል። በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው ሰባት ቁጥር ሙላትን የሚያመለክት ሲሆን መጽሐፉ የሚናገረውም “የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር” ‘ስለሚፈጸምበት’ ወይም ወደ ሙላት ስለሚደርስበት ሁኔታ ነው።—ራእይ 10:7
1:8, 17—“አልፋና ኦሜጋ” እንዲሁም “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የሚሉት መጠሪያዎች የሚያመለክቱት ማንን ነው? “አልፋና ኦሜጋ” የሚለው መጠሪያ ይሖዋን የሚያመለክት ሲሆን ይህም ከእሱ በፊት ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልነበረና ወደፊትም ቢሆን ፈጽሞ እንደማይኖር ያሳያል። ይሖዋ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” ነው። (ራእይ 21:6፤ 22:13) በራእይ 22:13 ላይ ይሖዋ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የተባለው ከእሱ በፊትም ሆነ ከእሱ በኋላ ማንም ስለሌለ ነው፤ ሆኖም በራእይ 1:17 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው እዚህ ጥቅስ ላይ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ትንሣኤ ሲያገኝ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት የተሰጠው የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ሲሆን ይሖዋ ራሱ ከሞት ያስነሳው እሱን ብቻ በመሆኑ ደግሞ የመጨረሻው ሊባል ይችላል።—ቆላ. 1:18
2:7—‘የአምላክ ገነት’ የተባለው ምንድን ነው? ክርስቶስ ይህን የተናገረው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደመሆኑ መጠን እዚህ ላይ የተገለጸው ገነት የሚያመለክተው በሰማይ ያለውን ገነት መሰል ሁኔታ ማለትም አምላክ ራሱ የሚገኝበትን ስፍራ መሆን ይኖርበታል። ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የሕይወትን ዛፍ’ የመብላት ግሩም አጋጣሚ ያገኛሉ። የማይሞት ሕይወት ይሰጣቸዋል።—1 ቆሮ. 15:53
3:7—ኢየሱስ ‘የዳዊትን ቁልፍ’ የተቀበለው መቼ ነበር? ምንስ ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው? ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተጠመቀበት ወቅት በዳዊት የትውልድ ሐረግ የመጣ ዕጩ ንጉሥ ሆነ። ይሁንና ኢየሱስ ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ እስከተደረገበት እስከ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ የዳዊትን ቁልፍ አልተቀበለም ነበር። በዚህ ወቅት ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ በዳዊት ሥርወ መንግሥት የሚመጡ ነገሥታት የሚያገኟቸውን መብቶች በሙሉ አግኝቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ በተሰጠው ቁልፍ በመጠቀም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ የአገልግሎት አጋጣሚዎችንና መብቶችን ከፍቷል። ኢየሱስ በ1919 ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ “በንብረቱ ሁሉ ላይ” በመሾም “የዳዊትን ቤት መክፈቻ” በባሪያው ጫንቃ ላይ አድርጎታል።—ኢሳ. 22:22፤ ማቴ. 24:45, 47
3:12—ለኢየሱስ የተሰጠው “አዲስ ስም” ምንድን ነው? ይህ ስም ለኢየሱስ ከተሰጠው አዲስ ሹመትና ልዩ መብት ጋር የተያያዘ መሆን ይኖርበታል። (ፊልጵ. 2:9-11) ይህን ስም የኢየሱስን ያህል የሚያውቀው ማንም ባይኖርም ወደ ሰማይ በሄዱት ታማኝ ወንድሞቹ ላይ ስሙን በመጻፍ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲኖራቸው አድርጓል። (ራእይ 19:12) በተጨማሪም ይሖዋ ከሰጠው ልዩ መብቶች አንዳንዶቹን ያካፍላቸዋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:3፦ አምላክ በሰይጣን ዓለም ላይ የፍርድ እርምጃ የሚወስድበት “የተወሰነው ጊዜ [ስለቀረበ]” በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን መልእክት ተረድተን በተግባር ማዋላችን አጣዳፊ ነው።
3:17, 18፦ በመንፈሳዊ ሀብታም ለመሆን ከኢየሱስ “በእሳት የነጠረ ወርቅ” መግዛት ይኖርብናል። ይህም ሲባል በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ ለመሆን መጣር ያስፈልገናል ማለት ነው። (1 ጢሞ. 6:17-19) ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳውቀውን “ነጭ መደረቢያ” መልበስ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ማስተዋል ለማግኘት ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ ላይ እንደሚወጣው ምክር ያለ “ኩል” መጠቀም ይገባናል።—ራእይ 19:8
7:13, 14፦ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በሰማይ ክብር የተጎናጸፉትን 144,000ዎች የሚወክሉ ሲሆን በዚያም ነገሥታት ብቻ ሳይሆን ካህናትም ሆነው ያገለግላሉ። ንጉሥ ዳዊት በ24 ምድቦች ተደራጅተው እንዲያገለግሉ ያደረጋቸው የጥንቶቹ የእስራኤል ካህናት ለ24ቱ ሽማግሌዎች ጥላ ናቸው። ከሽማግሌዎቹ አንዱ የእጅግ ብዙ ሕዝብን ማንነት ለዮሐንስ ነግሮታል። በዚህም ምክንያት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንሣኤ የጀመረው ከ1935 ትንሽ ቀደም ብሎ እንደሆነ ይታሰባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች የእጅግ ብዙ ሕዝብን ማንነት በትክክል የተረዱት በዚህ ዓመት ስለነበር ነው።—ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 4:4፤ 7:9
ሰባተኛው ማኅተም ሲከፈት ሰባት መለከቶች በተከታታይ ተነፉ
በጉ ሰባተኛውን ማኅተም ሲከፍት ለሰባት መላእክት ሰባት መለከቶች ተሰጧቸው። ስድስቱ መላእክት መለከቶቻቸውን በመንፋት በሰው ዘር “አንድ ሦስተኛ” ማለትም በሕዝበ ክርስትና ላይ የፍርድ መልእክት አወጁ። (ራእይ 8:1, 2, 7-12፤ 9:15, 18) ዮሐንስ የተመለከተው አምስተኛው ራእይ ይህ ነው። ዮሐንስ የተሰጠውን ትንሽ ጥቅልል በመብላትና የቤተ መቅደሱን ቅዱስ ስፍራ በመለካት በቀጣዩ ራእይ ላይ ተካፋይ ሆኗል። ሰባተኛው መለከት ከተነፋ በኋላ ታላላቅ ድምፆች እንዲህ ሲሉ ተሰሙ:- “የዓለም መንግሥት የጌታችንና የመሲሑ መንግሥት ሆነ።”—ራእይ 10:10፤ 11:1, 15
ሰባተኛው ራእይ፣ በራእይ 11:15, 17 ላይ ያለውን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። በሰማይ ታላቅ ምልክት ታየ። አንዲት ሴት በሰማይ የታየች ሲሆን እሷም ልጅ፣ ወንድ ልጅ ወለደች። ዲያብሎስ ከሰማይ ተወረወረ። ዲያብሎስ በሰማይ በታየችው ሴት ላይ ተቆጥቶ “ከዘሯ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።”—ራእይ 12:1, 5, 9, 17
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
8:1-5—በሰማይ ጸጥታ የሰፈነው ለምን ነበር? ከዚያ በኋላ ወደ ምድር የተወረወረውስ ምንድን ነው? ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ በሰማይ ጸጥታ የሰፈነው በምድር ላይ ያሉት “የቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት” እንዲሰማ ተብሎ ነው። ይህ የሆነው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ነበር። ብዙዎች እንደጠበቁት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የአሕዛብ ዘመን ሲያበቃ ወደ ሰማይ አልሄዱም። በጦርነቱ ወቅት ሁኔታዎች እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ። በመሆኑም እነዚህ ክርስቲያኖች መመሪያ ለማግኘት አጥብቀው ጸለዩ። መልአኩ ምሳሌያዊውን እሳት ወደ ምድር ሲወረውረው ለጸሎታቸው ምላሽ ያገኙ ሲሆን እሳቱ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቅንዓት እንዲቀጣጠል አድርጓል። እነዚህ ክርስቲያኖች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ የስብከት ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ፤ ይህ ደግሞ የአምላክ መንግሥት አንገብጋቢ ርዕስ እንዲሆን ስላደረገ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እሳት አስነስቷል። እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያ ተሰማ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብርሃን ፈነጠቀ። እንዲሁም በምድር መናወጥ እንደ ተመታ ሕንፃ የሐሰት ሃይማኖት ከመሠረቱ ተናጋ።
8:6-12፤ 9:1, 13፤ 11:15—ሰባቱ መላእክት መለከቶቻቸውን ለመንፋት የተዘጋጁት መቼ ነበር? መለከቶቹ የተነፉትስ መቼና እንዴት ነበር? መላእክቱ ሰባቱን መለከቶች ለመንፋት ያደረጉት ዝግጅት፣ እንደገና ለተነቃቁት በምድር ላይ ያሉት የዮሐንስ ክፍል አባላት ከ1919 እስከ 1922 ባለው ጊዜ ውስጥ መመሪያ መስጠትንም ይጨምራል። በዚህ ጊዜ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሕዝብ የሚሰጠውን ምሥክርነት እንደገና በማደራጀቱና የጽሑፍ ማተሚያዎችን በማዘጋጀቱ ሥራ ተጠምደው ነበር። (ራእይ 12:13, 14) የመለከቶቹ ድምፅ መሰማት ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ የአምላክ ሕዝቦች ከመላእክት ጋር ተባብረው በድፍረት ማወጃቸውን ያመለክታል። ይህ ሥራ የጀመረው በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሲሆን እስከ ታላቁ መከራ ድረስ ይቀጥላል።
8:13፤ 9:12፤ 11:14—የመጨረሻዎቹ ሦስት መለከቶች “ወዮታዎች” ያስከተሉት እንዴት ነው? መጀመሪያ የተነፉት አራት መለከቶች ሕዝበ ክርስትና በመንፈሳዊ በድን መሆኗን የሚያጋልጡ መልእክቶች ሲሆኑ የመጨረሻዎቹ ሦስት መለከቶች ደግሞ ለየት ካሉ ክንውኖች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ወዮታዎች ተብለዋል። የአምስተኛው መለከት መነፋት የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ‘ከጥልቁ’ ማለትም እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አቁመው ከነበሩበት ሁኔታ ከመውጣታቸውና የስብከቱን ሥራ ያለማሰለስ ከማከናወናቸው ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ሥራ ለሕዝበ ክርስትና የሚያሠቃይ መቅሰፍት ሆኖባት ነበር። (ራእይ 9:1) ስድስተኛው መለከት፣ በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የፈረሰኛ ሠራዊትን እንዲሁም በ1922 የጀመረውን ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ የሚመለከት ነው። የመጨረሻው መለከት መነፋት ደግሞ ከመሲሐዊው መንግሥት መወለድ ጋር የተያያዘ ነው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
9:10, 19፦ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ የሚወጡት ኃይል ያላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች የሚናደፍ መልእክት ይዘዋል። (ማቴ. 24:45) ይህ መልእክት “እንደ ጊንጥ ያለ . . . መንደፊያ” ካለው የአንበጣዎቹ ጅራት እንዲሁም ‘ጅራታቸው እባብ ከሚመስለው’ የፈረሰኛ ሠራዊት ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እነዚህ ጽሑፎች ስለ ይሖዋ “የበቀል ቀን” ስለሚያስጠነቅቁ ነው። (ኢሳ. 61:2) እነዚህን ጽሑፎች በድፍረትና በቅንዓት እናሰራጭ።
9:20, 21፦ ክርስቲያን እንዳልሆኑ በሚነገርላቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁንና “የቀሩት” የተባሉት ከሕዝበ ክርስትና ውጪ ያሉ ሰዎች በጅምላ እውነትን ይቀበላሉ ብለን አንጠብቅም። ያም ቢሆን አገልግሎታችንን በጽናት መፈጸማችንን እንቀጥላለን።
12:15, 16፦ “ምድሪቱ” ማለትም በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ ያሉት ነገሮች ወይም በተለያዩ የምድር ክፍሎች የሚገኙ ገዢዎች የአምልኮ ነፃነት እንዲኖር አድርገዋል። ከ1940ዎቹ ዓመታት ወዲህ እነዚህ ገዢዎች “ዘንዶው ከአፉ የለቀቀውን [የስደት] ወንዝ” ውጠውታል። በእርግጥም ይሖዋ ከፈለገ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ከዚህ አንጻር ምሳሌ 21:1 “የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል” ማለቱ የተገባ ነው። ይህን ማወቃችን በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ሊያጠናክረው ይገባል።