የራእይን መጽሐፍ በማንበብ ተደሰቱ
“የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW ናቸው።”] —ራእይ 1:3
1. ሐዋርያው ዮሐንስ የራእይን መጽሐፍ የጻፈው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ሆኖ ነበር? እነዚህ ራእይዎችስ በጽሑፍ የሰፈሩበት ዓላማ ምንድን ነው?
“እኔ . . . ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ።” (ራእይ 1:9) ዮሐንስ አፖካሊፕስን ወይም ራእይን የጻፈው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር። በፍጥሞ ታስሮ የነበረው ንጉሠ ነገሥታዊ አምልኮን ባጠናከረውና ቀንደኛ የክርስቲያኖች አሳዳጅ በነበረው በንጉሠ ነገሥት ዶሚሺያን የግዛት ዘመን (81-96 እዘአ) እንደሆነ ይታሰባል። ዮሐንስ በፍጥሞ ሳለ ተከታታይ ራእዮችን የተቀበለ ሲሆን እነዚህንም በጽሑፍ አስፍሯቸዋል። ዮሐንስ ያያቸውን ራእዮች ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች ያካፈላቸው እየደረሰባቸው ከነበረውና ከፊታቸውም ከሚጠብቃቸው ፈተና አንጻር ጥንካሬ፣ መጽናኛና ማበረታቻ እንዲያገኙ በማሰብ እንጂ እነርሱን ለማስፈራራት አልነበረም።—ሥራ 28:22፤ ራእይ 1:4፤ 2:3, 9, 10, 13
2. ዮሐንስና ክርስቲያን ጓደኞቹ የነበሩበት ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ክርስቲያኖች ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈባቸው ሁኔታዎች ዛሬ ለምንኖረው ክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም አላቸው። ዮሐንስ የይሖዋና የልጁ የክርስቶስ ኢየሱስ ምሥክር በመሆኑ ስደት ይደርስበት ነበር። እርሱም ሆነ ክርስቲያን አጋሮቹ ጥሩ ዜጎች ለመሆን የሚጥሩ ሰዎች ቢሆኑም ንጉሠ ነገሥታዊ አምልኮ ባለማቅረባቸው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ። (ሉቃስ 4:8) ዛሬም “በሃይማኖት ረገድ ትክክለኛው ነገር” ምን እንደሆነ እናውቃለን የሚሉ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ ከዮሐንስ ጊዜ የተለየ አይደለም። እንግዲያውስ በራእይ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ያሉት ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው:- “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፣ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን [“ደስተኛ፣” NW] ናቸው።” (ራእይ 1:3) አዎን፣ የራእይን መጽሐፍ በትኩረት የሚከታተሉና የሚታዘዙ አንባቢዎች እውነተኛ ደስታና ብዙ በረከት ሊያገኙ ይችላሉ።
3. ለዮሐንስ የተሰጠው ራእይ ምንጭ ማን ነው?
3 የራእይ መጽሐፍ ምንጭ ማን ነው? መልእክቱንስ ለማስተላለፍ የተጠቀመበት መስመር ምንድን ነው? የመክፈቻው ቁጥር እንዲህ ይላል:- “ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፣ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ።” (ራእይ 1:1) በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል የራእይው ዋነኛ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ሲሆን እርሱ ለኢየሱስ፣ ኢየሱስ ደግሞ በአንድ መልአክ አማካኝነት ለዮሐንስ አስተላልፎታል። ጉዳዩን ተጨማሪ ትኩረት ሰጥተን ከመረመርነው ኢየሱስ መልእክቱን ወደ ጉባኤዎች ለማስተላለፍም ሆነ ራእይውን ለዮሐንስ ለመግለጥ በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠቀመ እናስተውላለን።—ራእይ 2:7, 11, 17, 29፤ 3:6, 13, 22፤ 4:2፤ 17:3፤ 21:10፤ ከሥራ 2:33 ጋር አወዳድር።
4. ዛሬም ቢሆን ይሖዋ በምድር ያለውን ሕዝቡን ለመምራት በምን ይጠቀማል?
4 ዛሬም ቢሆን ይሖዋ በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ለማስተማር ‘የጉባኤ ራስ’ በሆነው ልጁ ይጠቀማል። (ኤፌሶን 5:23፤ ኢሳይያስ 54:13፤ ዮሐንስ 6:45) ለሕዝቡ መመሪያ ለመስጠት መንፈሱንም ይጠቀማል። (ዮሐንስ 15:26፤ 1 ቆሮንቶስ 2:10) ኢየሱስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የሚያበረታ መንፈሳዊ ምግብ ለማስተላለፍ ‘በባሪያው በዮሐንስ’ እንደተጠቀመ ሁሉ ዛሬም ለቤተሰቡ እና የእነርሱ ተባባሪ ለሆኑት ሰዎች ‘በጊዜው ምግብ ለማቅረብ’ ምድር ካሉት ቅቡዓን ‘ወንድሞቹ’ በተውጣጣው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይጠቀማል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ 25:40) በመንፈሳዊ ምግብ መልክ የምናገኘው ‘በጎ ስጦታ’ ምንጭ ማን እንደሆነና የሚተላለፍበት መስመር የትኛው እንደሆነ የሚገነዘቡ ሰዎች ደስተኞች ናቸው።—ያዕቆብ 1:17
በክርስቶስ የሚመሩ ጉባኤዎች
5. (ሀ) ክርስቲያን ጉባኤዎችና የበላይ ተመልካቾቻቸው በምን ተመስለዋል? (ለ) ሰብዓዊ አለፍጽምና ቢኖርም ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርግ ምን ነገር አለ?
5 በራእይ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤዎች በመቅረዝ ተመስለዋል። የበላይ ተመልካቾቻቸው ደግሞ በመላእክት (መልእክተኞች) እና በከዋክብት ተመስለዋል። (ራእይ 1:20)a ክርስቶስ ስለ ራሱ ሲናገር ዮሐንስ እንደሚከተለው ብሎ እንዲጽፍ ነግሮታል:- “በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል።” (ራእይ 2:1) በእስያ ለነበሩት ሰባት ጉባኤዎች የተላኩት ሰባት መልእክቶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ጉባኤዎችና ሽማግሌዎቻቸው የራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎን እንደነበራቸው ይጠቁማሉ። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም የጉባኤያችን ራስ የሆነው ክርስቶስ በመካከላችን እንዳለ ዘወትር ካስታወስን ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ምን እየተሠራ እንዳለ አሳምሮ ያውቃል። የበላይ ተመልካቾቹ ‘በቀኝ እጁ’ ውስጥ እንዳሉ ተደርገው በምሳሌያዊ መንገድ የተገለጹ ሲሆን ይህም በእርሱ ቁጥጥርና መመሪያ ሥር መሆናቸውንና ጉባኤውን በእረኝነት ስለሚመሩበት መንገድ ለእርሱ መልስ እንደሚሰጡ የሚያመለክት ነው።—ሥራ 20:28፤ ዕብራውያን 13:17
6. ለክርስቶስ መልስ መስጠት የሚጠበቅባቸው የበላይ ተመልካቾች ብቻ እንዳልሆኑ የሚያሳየው ምንድን ነው?
6 ይሁንና ለክርስቶስ መልስ የሚሰጡት የበላይ ተመልካቾች ብቻ ናቸው ብለን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው። ክርስቶስ ከመልእክቶቹ በአንዱ ውስጥ እንዲህ ብሏል:- “አብያተ ክርስቲያናትም [“ጉባኤዎች፣” NW] ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፣ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።” (ራእይ 2:23) ይህ ራሱ ማስጠንቀቂያም ማበረታቻም ነበር። ኢየሱስ ልባችን ውስጥ ያለውን ውስጣዊ ዝንባሌ ሳይቀር የሚያውቅ መሆኑ ማስጠንቀቂያ ሲሆን የምናደርገውን ጥረት ማወቁና የምንችለውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ደግሞ እንደሚባርከን ማወቃችን የሚያበረታታ ነው።—ማርቆስ 14:6-9፤ ሉቃስ 21:3, 4
7. በፊልድልፍያ ያሉ ክርስቲያኖች ‘ስለ ኢየሱስ ጽናት የሚናገሩትን ቃላት’ የጠበቁት እንዴት ነበር?
7 ክርስቶስ በልድያዋ ከተማ በፊልድልፍያ ላለው ጉባኤ የላከው መልእክት ምንም ዓይነት ወቀሳ አልነበረበትም። ይሁን እንጂ የሁላችንንም ትኩረት የሚስብ አንድ ተስፋ ይዟል። “የትዕግሥቴን [“የጽናቴን፣” NW] ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።” (ራእይ 3:10) “የጽናቴን ቃል ስለ ጠበቅህ” የሚለው ግሪክኛ “ስለ ጽናት የተናገርኩትን ቃል ስለጠበቅህ” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቁጥር 8 በፊልድልፍያ የነበሩት ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትእዛዛት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በታማኝነት እንዲጸኑ የሰጣቸውን ምክርም ተከትለዋል።—ማቴዎስ 10:22፤ ሉቃስ 21:19
8. (ሀ) ኢየሱስ በፊልድልፍያ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ምን ቃል ገብቶላቸዋል? (ለ) ዛሬ ‘በፈተናው ሰዓት’ የሚነኩት እነማን ናቸው?
8 በተጨማሪም ኢየሱስ “ከፈተናው ሰዓት” እንደሚጠብቃቸው ተናግሯል። እነዚህ ቃላት በዚያን ወቅት ለነበሩት ክርስቲያኖች በትክክል ምን ትርጉም እንደነበራቸው አናውቅም። ዶሚሺያን በ96 እዘአ ከሞተ በኋላ ስደቱ ትንሽ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም በትራጃን (98-117 እዘአ) ግዛት አዲስ የስደት ማዕበል እንደጀመረ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ዋነኛው ‘የፈተና ሰዓት’ የመጣው ‘በጌታ ቀን’ ማለትም ዛሬ ባለንበት ‘የፍጻሜ ዘመን’ ነው። (ራእይ 1:10፤ ዳንኤል 12:4) በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜ በተወሰነ የፈተና ወቅት ውስጥ አልፈዋል። ይሁንና ‘የፈተናው ሰዓት’ ገና አላበቃም። ከታላቁ መከራ በሕይወት የማለፍ ተስፋ ያላቸውን በሚልዮን የሚቆጠሩ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ጨምሮ ‘መላውን የምድር ነዋሪ’ የሚነካ ነው። (ራእይ 3:10፤ 7:9, 14) ‘ኢየሱስ ስለ ጽናት የተናገረውን ነገር ብንጠብቅ’ ደስተኞች እንሆናለን። “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:13
ለይሖዋ ሉዓላዊነት በደስታ መገዛት
9, 10. (ሀ) ስለ ይሖዋ ዙፋን የታየው ራእይ እንዴት ሊነካን ይገባል? (ለ) የራእይን መጽሐፍ ማንበባችን ለደስታችን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው?
9 ስለ ይሖዋ ዙፋንና ሰማያዊ መቀመጫ በራእይ ምዕራፍ 4 እና 5 ላይ የተገለጸው ራእይ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይገባዋል። ኃያላን ሰማያዊ ፍጥረታት ለይሖዋ ጽድቅ የተላበሰ ሉዓላዊነት በደስታ ራሳቸውን በማስገዛት የሚያሰሙት ልባዊ ውዳሴ ሊነካን ይገባል። (ራእይ 4:8-11) እኛም ድምፃችንን እንደሚከተለው ከሚሉት ወገኖች ጋር ማሰማት አለብን:- “በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ:- በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፣ ለበጉም ይሁን።”—ራእይ 5:13
10 ወደ ተግባራዊነቱ ከመጣን ይህ በማንኛውም ነገር ለይሖዋ ፈቃድ በደስተኛነት መገዛት ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፣ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።” (ቆላስይስ 3:17) በአእምሯችንና በልባችን ጓዳ ሳይቀር የይሖዋን ሉዓላዊነት የምንቀበል ከሆነና በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ የእርሱን ፈቃድ ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ የራእይን መጽሐፍ ማንበባችን እውነተኛ ደስታ ይሰጠናል።
11, 12. (ሀ) የሰይጣን ምድራዊ ሥርዓት የሚናወጠውና የሚጠፋው እንዴት ነው? (ለ) በራእይ ምዕራፍ 7 መሠረት በዚያ ጊዜ ‘ሊቆም የሚችለው’ ማን ነው?
11 በግለሰብ ደረጃም ይሁን በአጽናፈ ዓለም ደረጃ ደስታ ለማግኘት ቁልፍ የሆነው ነገር ለይሖዋ ሉዓላዊነት በደስታ መገዛት ነው። በቅርቡ የሰይጣንን ዓለም ሥርዓት ከሥሩ የሚያናጋና የሚያወድም ታላቅ ምሳሌያዊ መሬት መንቀጥቀጥ ይመጣል። የማያጠያይቀውን የአምላክ ሉዓላዊነት ለሚወክለው ለሰማያዊው የክርስቶስ ንጉሣዊ መስተዳድር ራሳቸውን ለማስገዛት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚሸሸጉበት ስፍራ አይኖራቸውም። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፣ ተራራዎችንና ዓለቶችንም:- በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቊጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቊጣው ቀን መጥቶአልና፣ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።”—ራእይ 6:12, 15-17
12 ሐዋርያው ዮሐንስ ከዚሁ ጥያቄ ጋር በሚዛመድ መልኩ በቀጣዩ ምዕራፍ ውስጥ ከታላቁ መከራ የመጡትን የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ‘በዙፋኑና በበጉ ፊት እንደቆሙ’ አድርጎ ገልጿቸዋል። (ራእይ 7:9, 14, 15) በአምላክ ዙፋን ፊት መቆማቸው ሥልጣኑን አምነው የሚቀበሉና ለይሖዋ ሉዓላዊነትም የሚገዙ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። በመሆኑም በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም አግኝተዋል።
13. (ሀ) አብዛኛው የምድር ነዋሪ አምልኮ የሚሰጠው ለማን ነው? በግንባራቸው ወይም በእጆቻቸው ላይ ያለው ምልክት የምን ምሳሌ ነው? (ለ) ታዲያ ጽናት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
13 በሌላ በኩል ግን ምዕራፍ 13 የቀሩት የምድር ነዋሪዎች በአውሬ የተመሰለውን የሰይጣን የፖለቲካ ሥርዓት እንደሚያመልኩ ይገልጻል። ‘በግምባራቸውና’ ‘በእጃቸው’ ምልክቱን የተቀበሉ ሲሆን ይህም ሥርዓቱን በሐሳብም ሆነ በድርጊት እንደሚደግፉ የሚያሳይ ነው። (ራእይ 13:1-8, 16, 17) ከዚያም ምዕራፍ 14 እንዲህ ሲል አክሎ ይናገራል:- “እርሱ ደግሞ በቊጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቊጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፣ . . . የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው።” (ራእይ 14:9, 10, 12) ጊዜው ወደ ፊት በገሰገሰ መጠን ይበልጥ እያስተጋባ የሚሄደው ጥያቄ:- የምትደግፈው ማንን ነው? ይሖዋንና ሉዓላዊነቱን ወይስ በአውሬ የተመሰለውን አምላካዊ አክብሮት የሌለው የፖለቲካ ሥርዓት? የሚል ይሆናል። የአውሬውን ምስል ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉና ለይሖዋ ሉዓላዊነት በታማኝነት በመገዛት የሚጸኑ ሰዎች ደስተኞች ናቸው።
14, 15. በራእይ ውስጥ ስለ አርማጌዶን በሚሰጠው መግለጫ ጣልቃ ምን መልእክት ገብቶአል? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
14 ‘የዓለም ሁሉ’ ነገሥታት በሉዓላዊነት ጥያቄ ላይ ከይሖዋ ጋር ፊት ለፊት የሚያፋጥጣቸውን አደገኛ ጎዳና እየተከተሉ ነው። አውደ ግንባሩ ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ አርማጌዶን ይሆናል። (ራእይ 16:14, 16) የምድር ነገሥታት ከይሖዋ ጋር ጦርነት ለመግጠም ስለመሰብሰባቸው በተሰጠው መግለጫ መሃል አንድ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ገብቶ እናገኛለን። ኢየሱስ ራሱ በራእይ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ “እነሆ፣ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው” ብሏል። (ራእይ 16:15) ይህ በጥበቃ ሥራቸው ላይ እያሉ ተኝተው ከተገኙ ልብሳቸውን ስለሚገፈፉትና በአደባባይ ስለሚዋረዱት ሌዋውያን የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቅስ ሊሆን ይችላል።
15 መልእክቱ ግልጽ ነው። ከአርማጌዶን መትረፍ ከፈለግን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖርና የይሖዋ አምላክ የታመንን ምሥክሮች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቀውን ምሳሌያዊ ልብሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ድካምን አስወግደን ስለ ተቋቋመው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን “የዘላለም ወንጌል” እያወጅን ያለመታከት ወደ ፊት ከገፋን ደስተኞች እንሆናለን።—ራእይ 14:6
‘እነዚያን ቃላት የሚጠብቅ ደስተኛ ነው’
16. የዮሐንስ ራእይ የመደምደሚያ ምዕራፎች የተለየ የደስታ ምክንያት የሚሆኑን ለምንድን ነው?
16 የራእይን መጽሐፍ በደስታ የሚያነብቡ ሰዎች የሚፈነድቁት ስለ ክብራማው የአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ተስፋችን የሚናገሩትን የመደምደሚያ ምዕራፎች ሲያነብቡ ብቻ ነው። ይህ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ጽድቅ የሰፈነበት ንጉሣዊ የሰማይ መስተዳደርና በዚያ ሥር የሚተዳደር አዲስ ንጹሕ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ማለት ነው። ይህም ‘ሁሉን ለሚገዛው አምላክ’ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ነው። (ራእይ 21:22) እነዚህ ድንቅ ተከታታይ ራእይዎች ሲደመደሙ መልእክተኛው መልአክ ለዮሐንስ እንደሚከተለው ብሎታል:- “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፣ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፣ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”—ራእይ 22:6, 7
17. (ሀ) በራእይ 22:6 ላይ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል? (ለ) ከምን ነገር ለመራቅ ንቁዎች መሆን አለብን?
17 ደስተኛ የሆኑት የራእይ አንባቢዎች ‘በጥቅልሉ’ መግቢያ ላይም ተመሳሳይ ቃላት እንደሚገኙ ያስታውሳሉ። (ራእይ 1:1, 3) እነዚህ ቃላት በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ የተተነበዩት ‘ነገሮች’ በሙሉ ‘በቅርቡ’ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ይሰጡናል። ዛሬ ወደ ፍጻሜው ዘመን ጠልቀን ስለገባን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት የተነገሩ ተስማሚ ነገሮች በቅርቡ አንድ በአንድ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ሊታይ የሚችል ማንኛውም ዓይነት መረጋጋት እንድናንቀላፋ ሊያዘናጋን አይገባም። ንቁ የሆነ አንባቢ ለሰባቱ የእስያ ጉባኤዎች በተላከው መልእክት ውስጥ ያለውን ማስጠንቀቂያ በማስታወስ ከፍቅረ ነዋይ፣ ከጣዖት አምልኮ፣ ከሥነ ምግባር ብልግና፣ ለብ ያለ ከመሆንና ከክህደት ኑፋቄዎች ራሱን ይጠብቃል።
18, 19. (ሀ) ኢየሱስ ገና መምጣት የሚኖርበት ለምንድን ነው? ዮሐንስ የተናገረው የየትኛው ተስፋ ተካፋዮች እንሆናለን? (ለ) ይሖዋስ ገና ወደፊት ‘የሚመጣው’ ለምን ዓላማ ነው?
18 ኢየሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “ቶሎ ብዬ እመጣለሁ” እያለ ደጋግሞ ተናግሯል። (ራእይ 2:16፤ 3:11፤ 22:7, 20ሀ) በታላቂቱ ባቢሎን፣ በሰይጣን የፖለቲካ ሥርዓትና ዛሬ በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ለተገለጠው የይሖዋ ሉዓላዊነት ለመገዛት አሻፈረኝ በሚሉ ሰዎች ሁሉ ላይ ፍርዱን ለማስፈጸም ገና ይመጣል። እኛም ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ድምፃችንን በማስተባበር “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” እንላለን።—ራእይ 22:20ለ
19 ይሖዋ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፣ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።” (ራእይ 22:12) ‘የአዲስ ሰማይም’ ይሁን ‘የአዲስ ምድር’ ክፍል ሆነን እንደምናገኘው ቃል የተገባልንን ክብራማ የሕይወት ሽልማት እየተጠባበቅን “ና . . . የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን ጥሪ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ማዳረሳችንን እንቀጥል። (ራእይ 22:17) እነርሱም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውና ቀስቃሽ የሆነው የራእይ መጽሐፍ አንባቢዎች እንዲሆኑ ምኞታችን ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! ገጽ 28-9, 136 (የግርጌ ማስታወሻ) ተመልከት።
የክለሳ ነጥቦች
◻ ይሖዋ የራእይውን መልእክት ለማስተላለፍ የተጠቀመበት መስመር ምን ነበር? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
◻ በእስያ ለሚገኙት ሰባት ጉባኤዎች የተላኩትን መልእክቶች በማንበብ ደስ ሊለን የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ ‘በፈተናው ሰዓት’ ጥበቃ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ የራእይን መልእክት በያዘው ጥቅልል ውስጥ ያሉትን ቃላት ብንጠብቅ ምን ደስታ እናገኛለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምሥራቹ ምንጭ ማን እንደሆነ የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነቅቶ የሚጠብቅ ደስተኛ ነው