ምዕራፍ 20
እጅግ ብዙ ሰዎች
1. ዮሐንስ የ144,000ዎቹን መታተም ከገለጸ በኋላ የትኛውን ሌላ ቡድን ተመለከተ?
ዮሐንስ ስለ 144,000ዎቹ መታተም ከገለጸ በኋላ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት በጣም አስደናቂ ራእዮች አንዱ የሆነውን ራእይ ያቀርብልናል። ይህንን አስደናቂ ትዕይንት በሚተርክልን ጊዜ ልቡ በደስታ ሳይፈነድቅ አልቀረም። “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ።” (ራእይ 7:9) አዎ፣ የአራቱ ነፋሳት መገታት ከ144,000ዎቹ የመንፈሳዊ እስራኤል አባሎች ለተለዩ የሰዎች ክፍል መዳንን አስገኝቶአል። ባለ ብዙ ቋንቋ የሆነ ዓለም አቀፍ የብዙ ሰዎች ጭፍራ ከጥፋት እንዲድን አስችሎአል።a—ራእይ 7:1
2. ዓለማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዴት በማለት ገልጸዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ቢሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህን ሰዎች እንዴት ይመለከቱአቸው ነበር?
2 ዓለማውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ክርስትና የተመለሱ ሥጋዊ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው ወይም ወደ ሰማይ የሚሄዱ ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸው ብለዋል። ቀደም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንኳን እነዚህ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ሰማያዊ ክፍሎች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። ይህም እምነታቸው በ1886 በታተመው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት፣ መለኮታዊው የዘመናት እቅድ በተባለው መጽሐፍ አንደኛ ጥራዝ ላይ ተገልጾአል:- “የዙፋንና መለኮታዊ ባሕርይ የመልበስ ሽልማት ባያገኙም ከመለኮታዊው ባሕርይ ያነሰ መንፈሳዊ ልጅነት ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ቢሆኑም በዓለም መንፈስ ስለሚሸነፉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አልቻሉም።” በ1930 እንኳን ብርሃን በተባለው መጽሐፍ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ተገልጾ ነበር:- “የዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች የጌታ ቀናተኛ ምሥክሮች እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥሪ መቀበል ተስኖአቸዋል።” የእውነት እውቀት ቢኖራቸውም ይህን እውነት ለመስበክ ምንም ጥረት ያላደረጉና ራሳቸውን ያጸደቁ ሰዎች ክፍል እንደሆኑ ተገልጾ ነበር። ከክርስቶስ ጋር አብሮ የመንገሥ መብት የማይሰጣቸው ባለ ሁለተኛ ደረጃ ማዕረግ ሆነው ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ ይታመን ነበር።
3. (ሀ) በኋላ በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ላሳዩ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የነበራቸው ሰዎች ምን ተስፋ ተገልጾላቸው ነበር? (ለ) በ1923 ወጥቶ የነበረው መጠበቂያ ግንብ የኢየሱስን የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ምን በማለት አብራርቶ ነበር?
3 ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ጊዜያት በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ያሳዩ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተባባሪ የሆኑ ሰዎች ብቅ ብለዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የመሄድ ምኞት የላቸውም። ተስፋቸው የይሖዋ ሕዝቦች ከ1918 እስከ 1922 በተከታታይ ያሰሙ ከነበረው የሕዝብ ንግግር ርዕስ ጋር የተስማማ ነበር። በመጀመሪያ ላይ የዚህ ንግግር ርዕስ “የዓለም መጨረሻ ሆኖአል፣ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ነበር።b ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የጥቅምት 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስለ ኢየሱስ የበጎችና የፍየሎች ምሳሌ ትርጉም ሲያብራራ (ማቴዎስ 25:31-46) እንዲህ ብሎአል:- “በጎቹ በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሳይሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት በአእምሮአቸው የሚቀበሉትን እንዲሁም በኢየሱስ ግዛት ሥር የሚገኘውን ጥሩ ኑሮ የሚናፍቁትንና ተስፋ የሚያደርጉትን ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ያመለክታሉ።”
4. ስለ ምድራዊው ክፍል የተገኘው ዕውቀት በ1931 በይበልጥ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው? በ1932 እና በ1934ትስ?
4 ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1931 የወጣው መቀደስ አንደኛ መጽሐፍ የተባለው መጽሐፍ ስለ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ ከጥፋት እንዲተርፉ በግምባራቸው ላይ ምልክት የሚደረግባቸው ሰዎች ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ የተገለጹት በጎች እንደሆኑ ገልጾአል። በ1932 የወጣው መቀደስ ሶስተኛ መጽሐፍ ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ኢዩ የሐሰት ሃይማኖትን ሲያጠፋ የሚኖረውን ቅንዓት ለማየት ተከትሎት ስለሄደው ስለ ኢዮናዳብ ገልጾ ነበር። ኢዮናዳብ እስራኤላዊ ያልነበረና ቅን ልብ የነበረው ሰው ነበር። (2 ነገሥት 10:15-17) መጽሐፉ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ኢዮናዳብ የኢዩ ሥራ [የይሖዋን ፍርድ የማወጅ ሥራ] በሚከናወንበት በዚህ ዘመን በምድር ላይ የሚኖሩትን በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች፣ ከሰይጣን ድርጅት ፈጽሞ የተለዩትን ሰዎች፣ በጽድቅ ጎን የተሰለፉትን ሰዎች ያመለክታል ወይም ይወክላል። ጌታ በአርማጌዶን ጊዜ ከጥፋቱና ከመከራው ጠብቆ በማውጣት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ለእነዚህ ሰዎች ነው። ‘የበጎቹ’ ክፍል የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች ናቸው።” በ1934 መጠበቂያ ግንብ እነዚህ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው መጠመቅ እንደሚኖርባቸው ገለጸ። ይህን ምድራዊ ክፍል በሚመለከት የፈነጠቀው ብርሃን ይበልጥ እየበራ ሄደ።—ምሳሌ 4:18
5. (ሀ) በ1935 እጅግ ብዙ ሰዎች ምን እንደሆኑ ታወቀ? (ለ) በ1935 ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ተሰብሳቢዎች ሁሉ ብድግ እንዲሉ በጠየቀ ጊዜ ምን ሆነ?
5 በራእይ 7:9-17 ላይ የተገኘው ዕውቀት በሙሉ ድምቀቱና ውበቱ ግልጽ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ ደረሰ። (መዝሙር 97:11) የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 3, 1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ ዩ ኤስ ኤ ሊደረግ የታቀደው ስብሰባ በኢዮናዳብ ክፍል ለተመሰሉት ሁሉ ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ እንደሚያስገኝ በተደጋጋሚ ገልጾ ነበር። በእርግጥም ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ አስገኝቶአል። በዚያን ጊዜ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 20,000 ለሚያክሉ ተሰብሳቢዎች “ታላቁ ሕዝብ” በሚል ርዕስ ባደረገው ቀስቃሽ ንግግር የዘመናችን ሌሎች በጎች በራእይ 7:9 ላይ ከተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር አንድ እንደሆኑ የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አቅርቦአል። ተናጋሪው በንግግሩ መጨረሻ ላይ “በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” አለ። ከአድማጮቹ መካከል በጣም ብዙ የሆኑት ብድግ ባሉ ጊዜ ፕሬዚደንቱ “እነሆ፣ ታላቁ ሕዝብ” አለ። ለጥቂት ጊዜ ፍጹም ጸጥታ ከሆነ በኋላ እንደ ነጎድጓድ የሚያስተጋባ የደስታ ጭብጨባ ተሰማ። የዮሐንስ ክፍል የሆኑትም ሆነ የኢዮናዳብ ቡድን ምንኛ ተደስተው ነበር! በሚቀጥለው ቀን 840 የሚያክሉ አዳዲስ ምሥክሮች ተጠመቁ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል እንደሆኑ የሚናገሩ ነበሩ።
የእጅግ ብዙ ሰዎችን ማንነት ማረጋገጥ
6. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ራሳቸውን የወሰኑ ዘመናዊ የክርስቲያኖች ቡድን ናቸው ብለን ለማመን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የእጅግ ብዙ ሰዎች ነጭ ልብስ ምን ያመለክታል?
6 እጅግ ብዙ ሰዎች በአምላክ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ናቸው ብለን በእርግጠኝነት ለመናገር የምንችለው ለምንድን ነው? ቀደም ሲል ዮሐንስ ‘ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ’ ሁሉ ለአምላክ የተዋጁትን የሰማይ ክፍል አባሎች በራእይ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 5:9, 10) እጅግ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ አመጣጥ ቢኖራቸውም የመጨረሻ ዕጣቸው የተለየ ነው። ቁጥራቸውም ቢሆን እንደ አምላክ እስራኤል አባሎች አስቀድሞ የተወሰነ አይደለም። ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን በቅድሚያ ሊያውቅ የሚችል ሰው የለም። ልብሳቸው በበጉ ደም ታጥቦ ነጭ ሆኖአል። ይህም በኢየሱስ መስዋዕት በማመናቸው ምክንያት በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም ማግኘታቸውን ያመለክታል። (ራእይ 7:14) በተጨማሪም የዘንባባ ዝንጣፊ እያወዛወዙ መሲሑ ንጉሣቸው መሆኑን በይፋ በማወጅ ላይ ናቸው።
7, 8. (ሀ) የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዙ ዮሐንስን የትኛውን ጊዜ አስታውሶት ሊሆን ይችላል? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዛቸው ምን ትርጉም አለው?
7 ዮሐንስ ይህን ራእይ በተመለከተበት ጊዜ ሐሳቡ ከ60 ዓመታት በፊት ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት የመጨረሻ ሳምንት ወደ ሆነው ነገር ሳይወስደው አልቀረም። ኒሳን 9 ቀን 33 እዘአ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ሊቀበሉት በተሰበሰቡ ጊዜ “የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና ሆሣዕና በጌታ [“በይሖዋ፣” NW] ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ይጮሁ ነበር። (ዮሐንስ 12:12, 13) እጅግ ብዙ ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የዘንባባ ዝንጣፊ እያወዛወዙ መጮሃቸው ይሖዋ የሾመውን የኢየሱስን ንግሥና ሲቀበሉ የተሰማቸውን ገደብ የለሽ ደስታ ያመለክታል።
8 የዘንባባው ዝንጣፊና የእልልታው ጩኸት ዮሐንስን የጥንቶቹ እስራኤሎች ያከብሩት የነበረውን የዳስ በዓል አስታውሶት እንደነበረ አያጠራጥርም። ይሖዋ ስለዚህ በዓል የሚከተለውን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። “በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የሰሌን ቅርንጫፍ፣ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፣ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ።” የዘንባባ ወይም የሰሌን ዝንጣፊ የደስታ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር። ጊዜያዊ የነበሩት ዳሶች ደግሞ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶ በምድረ በዳ በድንኳን ውስጥ እንዳኖራቸው የሚያሳስቡ ናቸው። በዚህ በዓል “መጻተኛ፣ ድሃ አደግና መበለትም” መካፈል ነበረባቸው። መላው እስራኤል ደስተኛ መሆን ነበረበት።—ዘሌዋውያን 23:40፤ ዘዳግም 16:13-15
9. እጅግ ብዙ ሰዎች በየትኛው የእልልታ ጩኸት ይተባበራሉ?
9 ስለዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች የመንፈሳዊ እስራኤል ክፍል ባይሆኑም እንኳን ድል አድራጊነትና ማዳን የአምላክና የበጉ እንደሆነ በደስታና በአመስጋኝነት ስለሚናገሩ የዘንባባ ዝንጣፊ ማወዛወዛቸው ተገቢ ነው። ይህንንም ዮሐንስ በራእይ ተመልክቶአል:- “በታላቅ ድምፅ እየጮሁ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (ራእይ 7:10) እጅግ ብዙ ሰዎች ከተለያዩ ነገዶችና ጎሣዎች የተውጣጡ ቢሆኑም የሚጮሁት በአንድ “ታላቅ ድምፅ” ብቻ ነው። የተለያየ ቋንቋና ብሔር እያላቸው በአንድ ድምፅ ለመጮህ የቻሉት እንዴት ነው?
10. እጅግ ብዙ ሰዎች በብሔርና በቋንቋ የተለያዩ ቢሆኑም በአንድ ድምፅ ሊጮሁ የቻሉት እንዴት ነው?
10 እጅግ ብዙ ሰዎች በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ሕብረትና አንድነት ያለው ከልዩ ልዩ ብሔራት የተውጣጣ ድርጅት ክፍል ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሚኖሩባቸው አገሮች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓት ይጠብቃሉ እንጂ እንደየአገሩ የሚለያይ የአቋም ደረጃ አያወጡም። በብሔራዊና አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም። ‘ሠይፋቸውን ማረሻ አድርገው ቀጥቅጠዋል።’ (ኢሳይያስ 2:4) በተለያዩ ኑፋቄዎችና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የተከፋፈሉ ስላልሆኑ እንደ ሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች እርስበርሱ የሚቃረን ወይም የተምታታ መልእክት አያሰሙም። ደመወዝተኛ ቀሳውስት እነርሱን ወክለው አምላክን እንዲያወድሱላቸው አያደርጉም። ሦስትነት በአንድነት ያለው የሥላሴ አምላክ ባሪያዎች ስላልሆኑ ማዳን የመንፈስ ቅዱስ ነው ብለው አይጮሁም። በምድር ዙሪያ ከ200 በሚበልጡ ጂኦግራፊያዊ ክልሎች በአንዱ የእውነት ንጹሕ ልሳን እየተናገሩ በአንድ ድምፅ የይሖዋን ስም ይጠራሉ። (ሶፎንያስ 3:9) መዳን የሚመጣላቸው የመዳን አምላክ ከሆነው ከይሖዋና የእርሱ የመዳን ዋና ወኪል ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በሕዝብ ፊት ማሳወቃቸው የተገባ ነው።—መዝሙር 3:8፤ ዕብራውያን 2:10
11. ዘመናዊው ቴክኖሎጂ እጅግ ብዙ ሰዎች ድምፃቸውን በጣም ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ የረዳቸው እንዴት ነው?
11 ዘመናዊው ቴክኖሎጂ በአንድነት እጅግ ብዙ ሰዎች የሚያሰሙት ድምፅ ይበልጥ ጎልቶ እንዲሰማ አስችሎአል። ለሰዎች ሁሉ አንድነት ያለው መልእክት ለማዳረስ ፍላጎት ያለው ሌላ የሃይማኖት ድርጅት ስለሌለ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀት ያስፈለገው አንድም ሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት በምድር ላይ የለም። ለዚህም ሥራ አጋዥ እንዲሆን በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር ክፍል ቅቡዓን አባሎች የበላይ ቁጥጥር ሥር (ሜፕስ) የተባለ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ለኅትመት የሚያስፈልጉ ቅጂዎችን የሚያዘጋጅ የኮምፒተር ፕሮግራም ተዘጋጅቶአል። ይህ መጽሐፍ እስከ ታተመበት ጊዜ ድረስ በምድር ዙሪያ በሚገኙ ከ125 በሚበልጡ ቦታዎች የተለያዩ ዓይነት የሜፕስ ፕሮግራሞች በሥራ ላይ ውለዋል። ይህም መጠበቂያ ግንብ የተባለው በየሁለት ሣምንት የሚወጣ መጽሔት በአንድ ጊዜ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትሞ እንዲወጣ አስችሏል። በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች እንደዚህ መጽሐፍ ያሉትን የተለያዩ መጻሕፍት በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች አዘጋጅተው ያወጣሉ። በዚህ መንገድ በአብዛኛው እጅግ ብዙ ሰዎች የሚገኙበት የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት በየዓመቱ በታወቁት ቋንቋዎች በሙሉ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎችን ለማሰራጨት ችለዋል። ይህም ከነገድና ከቋንቋ የተውጣጡ ተጨማሪ ብዙ ሰዎች የአምላክን ቃል አጥንተው ድምፃቸውን ከእጅግ ብዙ ሰዎች ድምፅ ጋር እንዲያስተባብሩ አስችሎአል።—ኢሳይያስ 42:10, 12
በሰማይ ወይስ በምድር?
12, 13. እጅግ ብዙ ሰዎች ‘በዙፋኑና በበጉ ፊት የቆሙት’ በምን መንገድ ነው?
12 እጅግ ብዙ ሰዎች “በአምላክ ዙፋን ፊት” መቆማቸው ወደ ሰማይ መሄዳቸውን የሚያመለክት አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን? ይህን ጉዳይ ግልጽ የሚያደርግልን ብዙ ማስረጃ አለ። ለምሳሌ ያህል እዚህ ላይ “ፊት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ኤኖፕዮን) ቃል በቃል ትርጉሙ “ትይዩ” ማለት ሲሆን በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በይሖዋ “ፊት” ወይም በይሖዋ “ትይዩ” መቆማቸውን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:21፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:14፤ ሮሜ 14:22፤ ገላትያ 1:20) አንድ ጊዜ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ሙሴ ለአሮን “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ፊት ቅረቡ በል” ብሎት ነበር። (ዘጸአት 16:9) በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ በይሖዋ ፊት እንዲቆሙ ወደ ሰማይ መወሰድ አላስፈለጋቸውም። (ከዘሌዋውያን 24:8 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ እዚያው በምድረ በዳ እንዳሉ በይሖዋ ለመታየት ቆሙ። ይሖዋም ትኩረቱን ወደ እነርሱ አዞረ።
13 በተጨማሪም እንዲህ እናነባለን:- “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ . . . አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ።”c ይህ ትንቢት በሚፈጸምበት ጊዜ መላው የሰው ዘር በሰማይ ይሆናል ማለት አይደለም። “ወደ ዘላለም ቅጣት” የሚሄዱት ሰዎችም ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 25:31-33, 41, 46) ከዚህ ይልቅ መላው የሰው ልጅ በምድር ላይ ሆኖ በኢየሱስ ትይዩ ይቆማል። ኢየሱስም ትኩረቱን ወደ ሰው ልጆች በማዞር ይዳኛቸዋል። እጅግ ብዙ ሰዎችም በተመሳሳይ በይሖዋና በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚታዩበት ቦታ ሆነው ጥሩ ፍርድ ሲፈረድላቸው “በዙፋኑና በበጉ ፊት” ይቆማሉ።
14. (ሀ) ‘በዙፋኑ ዙሪያና’ በሰማያዊቱ ‘የጽዮን ተራራ’ እንዳሉ የተነገረላቸው እነማን ናቸው? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት “በመቅደሱ” መሆኑ እነርሱን የካህናት ክፍል የማያደርጋቸው ለምንድን ነው?
14 24ቱ ሽማግሌዎችና 144,000ዎቹ ቅቡዓን በይሖዋ ዙፋን ዙሪያና በሰማያዊቱ “የጽዮን ተራራ” ላይ እንዳሉ ተገልጾአል። (ራእይ 4:4፤ 14:1) እጅግ ብዙ ሰዎች የክህነት ሹመት ስለሌላቸው ይህን ከፍተኛ ቦታ አያገኙም። እርግጥ ነው በራእይ 7:15 ላይ “በመቅደሱ” እንደሚያገለግሉት ተገልጾአል። ይሁን እንጂ ይህ መቅደስ የውስጠኛውን ቅድስተ ቅዱሳን አያመለክትም። የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ነው። እዚህ ላይ “መቅደስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ናኦስ ሲሆን ለይሖዋ አምልኮ የቆመውን ሕንጻና ቅጥር በሙሉ ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ ይህ መቅደስ ሰማይንና ምድርን የሚያጠቃልል መንፈሳዊ ሕንጻ ነው።—ከማቴዎስ 26:61፤ ከማቴዎስ 27:5, 39, 40፤ ከማርቆስ 15:29, 30ና ከዮሐንስ 2:19-21 ባለማጣቀሻው አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ጋር አወዳድር።
ጽንፈ ዓለማዊ የውዳሴ ጨኸት
15, 16. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች በመታየታቸው በሰማይ ያሉ እንዴት ተሰማቸው? (ለ) የይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረታት እያንዳንዱ የይሖዋ አዲስ ዓላማ በተገለጠበት ጊዜ ሁሉ ምን ተሰምቶአቸው ነበር? (ሐ) እኛ በምድር ላይ የምንኖረው በዚህ የውዳሴ መዝሙር ልንተባበር የምንችለው እንዴት ነው?
15 እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን በማወደስ ላይ ናቸው። ሆኖም የይሖዋን ውዳሴ የሚዘምሩ ሌሎች ፍጥረታትም አሉ። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶች ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፣ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ:- ‘አሜን፣ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን አሜን’ አሉ።”—ራእይ 7:11, 12
16 ይሖዋ ምድርን በፈጠረ ጊዜ ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ “በአንድነት ሲዘምሩ፣ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ” ነበር። (ኢዮብ 38:7) የይሖዋ ዓላማ በሚገለጥበት ጊዜ ሁሉ መላእክት በተመሳሳይ እልል ሳይሉ አልቀሩም። 24ቱ ሽማግሌዎች ማለትም ሰማያዊ ክብራቸውን የተቀዳጁት 144,000 ቅቡዓን ለበጉ ሥልጣን እውቅና በመስጠት እልል ይላሉ። የቀሩትም የአምላክ ሰማያዊ ፍጥረቶች ከእነርሱ ጋር በመተባበር ለኢየሱስና ለይሖዋ የውዳሴ እልልታ ያሰማሉ። (ራእይ 5:9-14) እነዚህ ፍጥረታት ይሖዋ ታማኝ ቅቡዓኖችን ከሙታን አስነስቶ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ትልቅ የክብር ቦታ በመስጠት ዓላማውን ሲያስፈጽም ተመልክተው በጣም ተደስተዋል። አሁን ደግሞ የይሖዋ ታማኝ ሰማያዊ ፍጥረታት እጅግ ብዙ ሰዎችን አንድ ላይ ሆነው ሲመለከቱ የእልልታ መዝሙር ለማሰማት ተቀሰቀሱ። በእውነትም የጌታ ቀን ለይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ጊዜ ነው። (ራእይ 1:10) እኛም በዚህ ምድር ላይ ያለነው ስለ ይሖዋ መንግሥት በመመስከር በውዳሴው መዝሙር ለመካፈል መቻላችን በጣም ታላቅ መብት ነው።
እጅግ ብዙ ሰዎች ብቅ አሉ
17. (ሀ) ከ24ቱ ሽማግሌዎች አንዱ ምን ዓይነት ጥያቄ አነሳ? ሽማግሌው መልሱን ለማግኘት መቻሉ ምን ያመለክታል? (ለ) የሽማግሌው ጥያቄ ምላሽ ያገኘው መቼ ነበር?
17 ከሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ጌታ ቀን ድረስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች ማንነት ግራ ተጋብተው ነበር። ስለዚህ ከ24ቱ ሽማግሌዎች አንዱ የሚከተለውን ተገቢ ጥያቄ በመጠየቅ የዮሐንስን አሳብ መቀስቀሱ ተገቢ ነው። “ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ:- እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም:- ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ አልሁት።” (ራእይ 7:13, 14ሀ) አዎ፣ ይህ ሽማግሌ መልሱን ሊያገኝና ለዮሐንስ ሊነግረው ይችላል። ይህም ከሙታን የተነሱት የ24ቱ ሽማግሌዎች አባላት በዘመናችን መለኮታዊውን እውነት በማስተላለፍ ሥራ እንደሚካፈሉ ያመለክታል። በምድር ያሉት የዮሐንስ ክፍል አባሎችም ቢሆኑ የእጅግ ብዙ ሰዎችን ማንነት ሊያውቁ የቻሉት ይሖዋ በመካከላቸው የሚሠራውን ሥራ በመመልከት ነው። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በ1935 መለኮታዊው ብርሃን በቲኦክራቲካዊው ሰማይ ላይ ብሩሕ ሆኖ እንደፈነጠቀ ወዲያውኑ ተገነዘቡ።
18, 19. (ሀ) በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት የዮሐንስ ክፍል የትኛውን ተስፋ አበክሮ ይገልጽ ነበር? መልእክቱን በብዛት መቀበል የጀመሩት እነማን ነበሩ? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች ማን መሆናቸው በ1935 መታወቁ ስለ 144,000ዎቹ ምን አመለከተ? (ሐ) ስለ መታሰቢያው በዓል የተገለጸው ስታትስቲክስ ምን ያሳያል?
18 የዮሐንስ ክፍል በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በጽሑፎችም ሆነ በስብከቱ ሥራ ጠበቅ አድርጎ ይገልጽ የነበረው ስለ ሰማያዊው ተስፋ ነበር። በዚያ ጊዜ የ144,000ዎቹ ቁጥር ገና አልሞላም ነበር ማለት ነው። ይሁን እንጂ መልእክቱን ከተቀበሉትና በምሥክርነቱ ሥራ ቅንዓት ካሳዩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በገነቲቱ ምድር ውስጥ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። የሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች ስላልሆኑ ወደ ሰማይ የመሄድ ፍላጎት አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች የታናሹ መንጋ ክፍል አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ የሌሎች በጎች አባላት ናቸው። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሰዎች የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች መሆናቸው በ1935 መታወቁ በዚያን ጊዜ የ144,000ዎቹ ቁጥር ሊሞላ መቃረቡን ያመለክት ነበር።
19 ታዲያ ይህ ዓይነቱ ድምዳሜ የስታትስቲክስ ድጋፍ አለውን? አዎ፣ አለው። በ1938 በዓለም በሙሉ 59,047 የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት ተካፍለው ነበር። ከእነዚህ መካከል 36,732ቱ ሰማያዊ ጥሪ እንዳላቸው በማመልከት በዓመታዊው የጌታ እራት መታሰቢያ ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ተካፍለዋል። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ሁሉ ብዙ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ምድራዊ ሕይወታቸውን በሞት ስለ ፈጸሙ የተካፋዮቹ ቁጥር እያነሰ መጥቶአል። በ2005 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን የተካፈሉት 8,524 ብቻ ነበሩ። በበዓሉ ላይ ከተገኙት 16,390,116 ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ 0.05 በመቶ ያህል መሆናቸው ነው።
20. (ሀ) ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች ምን ተናግሮ ነበር? (ለ) በአሁኑ ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች እውነትም ብዙ ሕዝብ መሆናቸውን የሚያሳየን ምንድን ነው?
20 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀመረበት ጊዜ ሰይጣን የእጅግ ብዙ ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። በብዙ አገሮች የይሖዋ ሥራ ታግዶ ነበር። ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በእነዚህ የጨለማ ዓመታትና በጥር ወር 1942 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “እጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥራቸው በጣም ብዙ የሚሆን አይመስልም” ብሎ ሲናገር ተሰምቶ ነበር። ይሁን እንጂ የተገኘው መለኮታዊ በረከት ከዚህ የተለየ ውጤት አስገኝቶአል። በ1946 በዓለም በሙሉ ያገለግሉ የነበሩት አገልጋዮች ቁጥር ከፍተኛ እመርታ በማድረግ 176,456 ደረሰ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ነበሩ። በ2005 በ235 አገሮች ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ 6,390,022 ምሥክሮች ነበሩ። በእውነትም እጅግ ብዙ ሰዎች! ነበሩ። አሁንም ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው።
21. (ሀ) በጌታ ቀን የተፈጸመው የአምላክን ሕዝቦች የመሰብሰብ ሥራ ከዮሐንስ ራእይ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ ትንቢቶች መፈጸም የጀመሩት እንዴት ነው?
21 የአምላክ ሕዝቦች በዚህ የጌታ ቀን መሰብሰባቸው ከዮሐንስ ራእይ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነው። በመጀመሪያ ከ144,000 ክፍል የቀሩት ተሰበሰቡ፣ ከዚያም በኋላ እጅግ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው አሁን “በዘመኑ ፍጻሜ” ብዙ ሰዎች ከአሕዛብ ሁሉ እየወጡ በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ለመካፈል እየጎረፉ ነው። በእርግጥም ይሖዋ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” በመፍጠሩ በጣም ተደስተን እልል እንላለን። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ 65:17, 18) አምላክ “በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ” በመጠቅለል ላይ ነው። (ኤፌሶን 1:10) “በሰማይ ያሉት” የተባሉት ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ ባሉት መቶ ዘመናት ሁሉ ሲመረጡ የቆዩት የመንግሥቱ ቅቡዓን ወራሾች ናቸው። “በምድር ያሉት” የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ደግሞ እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው። ከዚህ ዝግጅት ጋር ተስማምተህ መሥራትህ ዘላለማዊ ደስታ ሊያስገኝልህ ይችላል።
እጅግ ብዙ ሰዎች የሚዘንቡላቸው በረከቶች
22. ዮሐንስ ስለ እጅግ ብዙ ሰዎች ምን ተጨማሪ መረጃ አግኝቶ ነበር?
22 ዮሐንስ በመለኮታዊው የመልእክት ማስተላለፊያ መስመር በኩል ስለዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ተጨማሪ መረጃ አግኝቶአል። “አለኝም [ሽማግሌው]:- እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው። ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፣ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፣ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል።” —ራእይ 7:14ለ, 15
23. እጅግ ብዙ ሰዎች ‘የወጡበት’ ታላቅ መከራ ምንድን ነው?
23 ቀደም ባለው ጊዜ ኢየሱስ በመንግሥት ክብር የሚገኝበት ጊዜ ሲፈጸም “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:21, 22) በዚህ ትንቢት ፍፃሜ መሠረት መላእክቱ መላውን የሰይጣን ዓለማዊ ሥርዓት ለማጥፋት አራቱን የምድር ነፋሳት ይለቃሉ። በመጀመሪያ የምትጠፋው የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን ነች። ከዚያም በኋላ በመከራው ፍጻሜ ላይ ኢየሱስ ከ144, 000ዎቹ ክፍል በምድር ላይ የቀሩትንና እጅግ ብዙ ሰዎችን ነጻ ያወጣቸዋል።—ራእይ 7:1፤ 18:2
24. የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች የሆኑ ግለሰቦች ለመዳን ብቃት የሚያገኙት እንዴት ነው?
24 የእጅግ ብዙ ሰዎች ግለሰብ አባሎች ለመዳን የሚያስችላቸውን ብቃት የሚያገኙት እንዴት ነው? ሽማግሌው “ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው” እንዳነጹ ለዮሐንስ ነግሮታል። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ቤዛቸው መሆኑን አምነዋል፣ ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነዋል፣ ውሳኔያቸውንም በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል፣ በጥሩ ሥነ ምግባር በመመላለስም “በጎ ሕሊና” ይዘዋል። (1 ጴጥሮስ 3:16, 21፤ ማቴዎስ 20:28) ስለዚህ በይሖዋ ፊት ንጹሐንና ጻድቃን ናቸው። ራሳቸውንም “ከዓለም እድፍ” ጠብቀው ይኖራሉ።—ያዕቆብ 1:27
25. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን “ቀንና ሌሊት በመቅደሱ” የሚያመልኩት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በእጅግ ብዙ ሰዎች ላይ ‘ድንኳኑን የሚዘረጋው’ እንዴት ነው?
25 ከዚህም በላይ ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል። “ሌሊትና ቀን በመቅደሱ ያመልኩታል።” አንተስ ከእነዚህ ራሳቸውን ለአምላክ ከወሰኑ እጅግ ብዙ ሰዎች መካከል ነህን? ከሆንክ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ውስጥ ይሖዋን ዘወትር የማገልገል መብት አለህ። በዛሬው ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች በቅቡዓን አመራር ሥር ሆነው አብዛኛውን የስብከት ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው። ሥጋዊ ኃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ጊዜያቸውን አብቃቅተው የሙሉ ጊዜ አቅኚዎች ሆነው ለማገልገል ችለዋል። ከእነዚህ አቅኚዎች መካከል ሆንክም አልሆንክ ራስህን የወሰንክ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ስለሆንክ በእምነትህና በሥራህ ምክንያት የአምላክ ወዳጅ ለመሆን እንደ ጻድቅ ተቆጥረህ በአምላክ ድንኳን ውስጥ እንድታድር ስለ ተጋበዝክ ደስ ሊልህ ይገባል። (መዝሙር 15:1-5፤ ያዕቆብ 2:21-26) ስለዚህ ይሖዋ በሚወዳቸው ሁሉ ላይ ድንኳኑን ይዘረጋል። ጥሩ አስተናጋጅ በመሆኑም እንግዶቹን ይጠብቃል።—ምሳሌ 18:10
26. እጅግ ብዙ ሰዎች ምን ሌላ በረከቶች ያገኛሉ?
26 ሽማግሌው እንደሚከተለው በማለት ይቀጥላል:- “ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፣ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፣ ፀሐይም ትኩሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፣ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:16, 17) አዎ፣ በእርግጥም ይሖዋ ጥሩ አስተናጋጅ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት ምን የጠለቀ ትርጉም አላቸው?
27. (ሀ) ኢሳይያስ ሽማግሌው ከተናገረው ጋር የሚመሳሰል ትንቢት የተናገረው እንዴት ነው? (ለ) የኢሳይያስ ትንቢት መፈጸም የጀመረው በጳውሎስ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ እንደ ነበረ የሚያመለክተን ምንድን ነው?
27 በተመሳሳይ ቃላት የተነገረ ሌላ ትንቢት እንመልከት:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንዲህ ይላል፣ በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፣ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ . . . የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፣ አይጠሙም፣ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጎዳቸውም።” (ኢሳይያስ 49:8, 10፤ በተጨማሪም መዝሙር 121:5, 6 ተመልከት።) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ትንቢት በከፊል ከጠቀሰ በኋላ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ቀን የጀመረውን “የደህንነት ቀን” እንደሚያመለክት ተናግሮአል። እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፣ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና [ይሖዋ]፤ እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።”—2 ቆሮንቶስ 6:2
28, 29. (ሀ) የኢሳይያስ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙት እንዴት ነበር? (ለ) የራእይ 7:16 ቃላት ለእጅግ ብዙ ሰዎች የተፈጸሙት እንዴት ነው? (ሐ) እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ “ሕይወት ውኃ ምንጭ” በመመራታቸው ምን ያገኛሉ? (መ) እጅግ ብዙ ሰዎች ማንም የሰው ልጅ ያላገኘው መብት የሚያገኙት እንዴት ነው?
28 በዚያ የጥንት ዘመን ስላለመራብ ወይም ስላለመጠማት ወይም በፀሐይ ትኩሳት ስላለመመታት የተነገረው ተስፋ ምን ዓይነት ተፈጻሚነት ነበረው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ቃል በቃል የተራቡበትና የተጠሙበት ጊዜ እንደነበረ የታወቀ ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ሁኔታ የተትረፈረፈላቸው ነበሩ። የሚያስፈልጋቸው ሁሉ በብዛት ይቀርብላቸው ስለነበረ መንፈሳዊ ነገሮችን አልተራቡም ወይም አልተጠሙም ነበር። ከዚህም በላይ ይሖዋ የአይሁዳውያንን ሥርዓት በ70 እዘአ ባጠፋ ጊዜ የቁጣው ትኩሳት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ አላደረገም ነበር። ዛሬም ቢሆን የራእይ 7:16 ቃላት ለእጅግ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ መንፈሳዊ ፍጻሜ አላቸው። እጅግ ብዙ ሰዎች ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ሆነው በተትረፈረፈ መንፈሳዊ ዝግጅት ይደሰታሉ።—ኢሳይያስ 65:13፤ ናሆም 1:6, 7
29 አንተም ከእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አንዱ ከሆንክ የዚህ የሰይጣን ሥርዓት ቀን እየጨለመ በሄደበት በዚህ ዘመን ምንም ዓይነት ችግርና ተጽዕኖ ቢደርስብህም ያለህ ጥሩ የልብ ሁኔታ ‘በደስታ እልል ለማለት’ ይገፋፋሃል። (ኢሳይያስ 65:14) በዚህ ረገድ አሁንም እንኳን ቢሆን ይሖዋ ‘ከዓይኖችህ እንባን ሁሉ ሊጠርግልህ’ ይችላል። ከእንግዲህ ወዲያ በጣም የሚያተኩሰው የአምላክ የቁጣ ፍርድ “ፀሐይ” አያስፈራህም። አራቱ የጥፋት ነፋሳት በሚለቀቁበት ጊዜም ከሚያተኩሰው የይሖዋ ቁጣ ትድናለህ። ከዚህ ጥፋት በኋላ በጉ ሕይወት ወደሚያድሰው “የሕይወት ውኃ ምንጭ” ይመራሃል። ይህም ውኃ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ያዘጋጀውን ዝግጅት በሙሉ ያመለክታል። ቀስ በቀስ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ስለምትደርስ በበጉ ደም ያለህ እምነት ይረጋገጣል። እናንተ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች፣ ሞትን ከማይቀምሱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ስለምትሆኑ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መብት ታገኛላችሁ። በእርግጥም ከዓይናችሁ እንባ ሁሉ ይጠረጋል።—ራእይ 21:4
ጥሪውን ማረጋገጥ
30. በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ምን አስደናቂ ትዕይንት ተከፍቶልናል? “ሊቆም” የሚችለውስ ማን ነው?
30 እነዚህ ቃላት በጣም አስደናቂ የሆነ ትዕይንት ይከፍቱልናል። ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል። ሰማያዊም ሆኑ ምድራዊ አገልጋዮቹ በአንድ ድምፅ ያወድሱታል። ምድራዊ አገልጋዮቹ በዚህ ታላቅ የውዳሴ መዝሙር መካፈል እንዴት ያለ ታላቅ መብት እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ የቅጣት ፍርዳቸውን ይፈጽማሉ። “ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና ማንስ ሊቆም ይችላል?” የሚል ጩኸት ይሰማል። (ራእይ 6:17) ታዲያ መልሱ ምንድን ነው? ‘የሚቆሙት’ ወይም ከጥፋቱ የሚተርፉት ጥቂት የሰው ልጆች ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል በወቅቱ በምድር ላይ የሚገኙ የ144,000 አባሎች ካሉ እነርሱና የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ይገኙበታል።—ኤርምያስ 35:19፤ 1 ቆሮንቶስ 16:13
31. የዮሐንስ ራእይ መፈጸሙ ክርስቲያኖችን በሙሉ፣ ቅቡዓንንም ሆነ እጅግ ብዙ ሰዎችን እንዴት ሊነካቸው ይገባል?
31 በዚህ ምክንያት የተነሳ የዮሐንስ ክፍል አባሎች የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ” ለማግኘት ይጋደላሉ። (ፊልጵስዩስ 3:14) በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የሚፈጸሙ ሁኔታዎች ልዩ የሆነ ጽናት እንደሚጠይቅባቸው አሳምረው ያውቃሉ። (ራእይ 13:10) ይሖዋን ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ እምነታቸውን ጠብቀው ይቆማሉ። ‘ስማቸው በሰማይ ስለተጻፈም ይደሰታሉ።’ (ሉቃስ 10:20፤ ራእይ 3:5) እጅግ ብዙ ሰዎችም “እስከ መጨረሻው የሚጸና” ብቻ እንደሚድን ያውቃሉ። (ማቴዎስ 24:13) የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በአጠቃላይ ከታላቁ መከራ እንዲድኑ ምልክት የተደረገባቸው ቢሆኑም በዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ንጹሕና ትጉሕ ሆነው ለመኖር መጋደል ይኖርባቸዋል።
32. በይሖዋ የቁጣ ቀን ሊቆሙ የሚችሉት ሁለት ክፍሎች ብቻ መሆናቸው የትኛውን አጣዳፊ ሁኔታ ያጎላል?
32 ከእነዚህ ሁለት ቡድኖች ሌላ በይሖዋ ቁጣ ቀን “የሚቆም” እንደሚኖር የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። ታዲያ ይህ መሆኑ በየዓመቱ በሚከበረው የጌታ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘት ለኢየሱስ መስዋዕት መጠነኛ አክብሮት የሚያሳዩትና ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው፣ ተጠምቀውና ንቁ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን በኢየሱስ መስዋዕት እምነት እንዳላቸው ያላረጋገጡት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል? “ስለ ትዳር በማሰብ” ወይም “በኑሮ ጭንቀቶች” ልባቸው እንዲከብድባቸው የፈቀዱ ከዚህ በፊት አምላክን ሲያገለግሉ የነበሩ ሰዎችስ? እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ሁሉ “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም [በኢየሱስ ክርስቶስ] ፊት ለመቆም” ይችሉ ዘንድ እንዲነቁና ነቅተውም እንዲኖሩ እንመኛለን። ጊዜው አጭር ነው!—ሉቃስ 21:34-36
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ባለ ማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
b መጠበቂያ ግንብ፣ ሚያዝያ 1, 1918 ገጽ 98
c ቃል በቃል ሲተረጎም “ከእርሱ ፊት ለፊት” ማለት ነው። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ኪንግደም ኢንተርሊኒየር ትርጉም
[በገጽ 119 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሕልምን የሚተረጉም አምላክ ነው
ለብዙ አሥርተ ዓመታት የዮሐንስ ክፍል አባሎች እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም አጥጋቢ መልስ አላገኙም ነበር። ለምን ማግኘት አቃታቸው? ምክንያቱን ታማኙ ዮሴፍ እንደሚከተለው በማለት ከተናገረው ቃል መረዳት እንችላለን:- “ትርጓሜ የአምላክ አይደለምን?” (ዘፍጥረት 40:8 NW) አምላክ የትንቢቶቹን አፈጻጸም የሚተረጉመው እንዴትና መቼ ነው? አብዛኛውን ጊዜ ሊፈጸሙ በተቃረቡበት ወይም በመፈጸም ላይ እንዳሉ ነው። ይህንንም የሚያደርገው ቃሉን የሚመረምሩ አገልጋዮቹ የትንቢቶቹን መልእክት በግልጽ እንዲያስተውሉ ነው። ይህን የመሰለ ማስተዋል የሚሰጠን “በመጽናትና መጽሐፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ . . . ለትምህርታችን” ሲል ነው።—ሮሜ 15:4
[በገጽ 124 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች
▪ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ ሁሉ የተውጣጡ ናቸው
▪ በይሖዋ ዙፋን ፊት ቆመዋል
▪ ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል
▪ ማዳን የይሖዋና የኢየሱስ እንደሆነ ይናገራሉ
▪ ከታላቁ መከራ የወጡ ናቸው
▪ ይሖዋን በመቅደሱ ቀንና ሌሊት ያገለግሉታል
▪ የይሖዋን ፍቅራዊ ጥበቃና እንክብካቤ ያገኛሉ
▪ ኢየሱስ እንደ እረኛቸው ሆኖ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራቸዋል
[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 127 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማዳን የአምላክና የበጉ እንደሆነ እጅግ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ
[በገጽ 128 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉ እጅግ ብዙ ሰዎችን ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራቸዋል