አምላክን በሚያስደስተው መንገድ በማምለክ ኢየሱስን ምሰሉ
አምላክ “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ ሰዎች እንዲያመልኩት ፍቅር የተሞላበት ግብዣ አቅርቧል። (ራእይ 7:9, 10፤ 15:3, 4) ይህን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች ‘የይሖዋን ክብር ውበት ማየት’ ይችላሉ። (መዝ. 27:4፤ 90:17) እነሱም እንደ መዝሙራዊው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “እናምልከው፤ እንስገድለትም፤ በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት እንንበርከክ” በማለት አምላክን ያወድሱታል።—መዝ. 95:6
ይሖዋ ከፍ አድርጎ የተመለከተው አምልኮ
ኢየሱስ፣ የአምላክ አንድያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን የአባቱን አስተሳሰብ እንዲሁም እሱ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና መሥፈርቶች ለማወቅ የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ነበረው። ይህም በመሆኑ ኢየሱስ፣ ይሖዋ ሊመለክበት የሚገባውን ትክክለኛ መንገድ ለሌሎች በእርግጠኝነት መናገር ይችል ነበር። “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል።—ዮሐ. 1:14፤ 14:6
ኢየሱስ ለአባቱ በትሕትና በመገዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። “አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ምንጊዜም የሚያስደስተውን [አደርጋለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 8:28, 29) ኢየሱስ አባቱን ያስደሰተው በየትኞቹ መንገዶች ነበር?
አንደኛው መንገድ፣ ሙሉ በሙሉ ለአባቱ ያደረ በመሆን ነው፤ አምላክን የማምለክ መሠረታዊ ትርጉምም ይኸው ነው። ኢየሱስ ከፍተኛ መሥዋዕትነት መክፈል በሚጠይቅበት ጊዜም እንኳ አባቱን በመታዘዝና ፈቃዱን በማድረግ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ፊልጵ. 2:7, 8) ኢየሱስ ለአምላክ ያቀረበው አምልኮ ሌላው አስፈላጊ ገጽታ ደግሞ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አዘውትሮ መካፈል ነበር፤ ይህን ሥራ ሁልጊዜ ያከናውን ስለነበር በእሱ የሚያምኑት ብቻ ሳይሆን የማያምኑበት ሰዎችም ጭምር መምህር በማለት ይጠሩት ነበር። (ማቴ. 22:23, 24፤ ዮሐ. 3:2) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ጊዜውንና ጉልበቱን ሌሎችን ለመርዳት አውሏል። ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየቱ ለራሱ የሚሆን ጊዜ ቢያሳጣውም ሌሎችን በማገልገሉ ደስተኛ ነበር። (ማቴ. 14:13, 14፤ 20:28) ምንም እንኳ ያለው ጊዜ የተጣበበ ቢሆንም በሰማይ ወደሚኖረው አባቱ አዘውትሮ ለመጸለይ ጊዜ ይመድብ ነበር። (ሉቃስ 6:12) አምላክ፣ ኢየሱስ ያቀረበውን አምልኮ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም!
አምላክን በሚገባ ማስደሰት ጥረት ይጠይቃል
ይሖዋ፣ ልጁ የሚያደርገውን ነገር ይመለከት የነበረ ሲሆን በእሱ መደሰቱንም ገልጿል። (ማቴ. 17:5) ይሁንና ሰይጣን ዲያብሎስም የኢየሱስን የታማኝነት አካሄድ ይመለከት ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ የሰይጣን ዋነኛ የጥቃት ዒላማ ሆነ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ታማኝ በመሆን ይሖዋን በሚፈልገው መንገድ ያመለከው አንድም ሰው አልነበረም። ዲያብሎስ ደግሞ ኢየሱስ ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ እንዳያቀርብ ለማገድ ይፈልግ ነበር።—ራእይ 4:11
ሰይጣን፣ ኢየሱስ ታማኝነቱን እንዲያጎድል ለማድረግ ሲል ፈታኝ የሆነ ግብዣ አቀረበለት። ሰይጣን “ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ [አወጣውና] የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየው።” ከዚያም “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW] ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው። (ማቴ. 4:8-10) ኢየሱስ፣ ለሰይጣን መስገድ ምንም ዓይነት ጥቅም የሚያስገኝ ቢመስልም እንዲህ ማድረግ ጣዖት አምልኮ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ከይሖዋ በቀር ለማንኛውም አካል አንድ ጊዜም እንኳ ቢሆን አምልኮ ለማቅረብ ፈቃደኛ አልነበረም።
በዛሬው ጊዜ ሰይጣን እሱን እንድናመልከው ለማድረግ ሲል የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው ባያቀርብልንም ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች ለአምላክ የሚያቀርቡትን አምልኮ ለማስተጓጎል ጥረት ማድረጉን አላቋረጠም። ዲያብሎስ አንድን አካል ወይም አንድን ነገር እንድናመልክ ሊያደርገን ይፈልጋል።—2 ቆሮ. 4:4
ክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን ጠብቋል። ኢየሱስ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት በመጠበቅ ማንኛውም ሰው አድርጎት በማያውቀው መንገድ ይሖዋን አክብሯል። በዛሬው ጊዜ የምንኖረው እውነተኛ ክርስቲያኖችም ለፈጣሪ የምናቀርበውን አምልኮ ከማንኛውም ነገር በላይ ከፍ አድርገን በመመልከት የኢየሱስን የታማኝነት አካሄድ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። በእርግጥም፣ ካሉን ነገሮች ሁሉ አብልጠን የምንመለከተው ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ነው።
አምላክን በሚያስደስተው መንገድ ማምለክ የሚያስገኛቸው በረከቶች
በአምላክ ፊት “ንጹሕና ነውር የሌለበት” አምልኮ ማቅረብ ብዙ በረከቶችን ያስገኛል። (ያዕ. 1:27) ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ . . . ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች” እንዲሁም “መልካም የሆነውን የማይወዱ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5) በአምላክ ቤት ውስጥ ግን አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማምለክ ከሚጥሩ ንጹሕና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ አለን። ይህ መንፈስን የሚያድስ አይደለም?
ከዚህ ዓለም ነውር ወይም ርኩሰት ራሳችንን መጠበቃችን ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንም ያደርጋል። ለአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመገዛት እንዲሁም ከአምላክ መመሪያ ጋር የማይጋጩትን የቄሳር ሕጎች በመታዘዝ ንጹሕ ሕሊና ይዘን ለመቀጠል ጥረት እናደርጋለን።—ማር. 12:17፤ ሥራ 5:27-29
አምላክን በሙሉ ልብ ማምለክ ሌላም በረከት ያስገኛል። ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ሕይወታችን ትርጉም ያለውና የሚያረካ ይሆናል። “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” ከሚሉት ሰዎች በተቃራኒ እኛ፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስተማማኝ ተስፋ አለን።—1 ቆሮ. 15:32
በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” በሕይወት እንደሚተርፉ የራእይ መጽሐፍ ይጠቁማል። ጥቅሱ “በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል” ይላል። (ራእይ 7:13-15) በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠ የተገለጸው በአጽናፈ ዓለም ላይ ከማንም በላይ ክብር ከተጎናጸፈው ከይሖዋ አምላክ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም። ይሖዋ ምንም ጉዳት እንዳይደርስብህ እየተንከባከበህ ወደ ድንኳኑ በእንግድነት ሲጋብዝህ ምን ያህል እንደምትደሰት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር! በአሁኑ ጊዜም እንኳ በተወሰነ መጠን የእሱን ጥበቃና እንክብካቤ ማግኘት እንችላለን።
ከዚህም በላይ አምላክን በሚያስደስተው መንገድ የሚያመልኩትን ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ “ወደ ሕይወት ውሃ ምንጭ” እንደሚመራቸው ተገልጿል። መንፈስን የሚያድሰው ይህ የውሃ ምንጭ፣ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ይሖዋ ያደረገልንን ዝግጅቶች በሙሉ ያመለክታል። በእርግጥም፣ አምላክ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:17) የሰው ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርስ የሚደረግ ሲሆን ይህም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ሁሉ ወደር የሌለው ደስታ ያስገኝላቸዋል። በአሁኑ ጊዜም እንኳ፣ ደስተኛ የሆኑ የይሖዋ አምላኪዎች ለእሱ ያላቸውን ልባዊ አድናቆት በመግለጽና በሰማይ ካሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ሆነው እሱን በማምለክ ይሖዋን ያወድሱታል። እነዚህ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት ከዘመሩት በሰማይ የሚገኙ ፍጥረታት ጋር በመሆን ይሖዋን በደስታ ያወድሱታል:- “ሁሉን ቻይ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው። የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው። ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና። የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ።”—ራእይ 15:3, 4
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰይጣን እሱን እንድናመልከው ምን ነገሮችን ያቀርብልናል?