ምዕራፍ 22
የመጀመሪያው ወዮታ፣ አንበጦች
1. መላእክት የመለከት ድምፅ ሲያሰሙ ምን ነገሮች ተፈጸሙ? የአምስተኛው መለከት መነፋት ምን ነገር አስተዋወቀ?
አምስተኛው መልአክ መለከቱን ለመንፋት ተዘጋጀ። ከዚህ ቀደም ሲል አራት ሰማያዊ መለከቶች ተነፍተው አራት መቅሰፍቶች ወርደዋል። እነዚህም መቅሰፍቶች ይሖዋ ከማንኛውም የዓለም ክፍል ይበልጥ ነውረኛ አድርጎ በሚመለከተው የሕዝበ ክርስትና የምድር ሲሶ ላይ ወርደዋል። ሕዝበ ክርስትና ለሞት በሚያደርስ በሽታ መያዝዋ እርቃኑን ወጥቶ ተጋልጦአል። መላእክት የመለከቱን ድምፅ በሚያሰሙበት ጊዜ ሰብአዊ አዋጅ ነጋሪዎችም ከእነርሱ ጋር ሆነው በምድር ላይ መልእክቱን አሰምተዋል። አሁን ደግሞ አምስተኛው መላእክታዊ መለከት ከቀደሙት ወዮታዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈሪ የሆነውን ወዮታ ሊያስተዋውቅ ተዘጋጅቶአል። ወዮታው አስፈሪ የሆነ የአንበጦችን መቅሰፍት የሚመለከት ነው። በመጀመሪያ ግን ይህን መቅሰፍት በይበልጥ እንድንረዳ የሚያስችሉንን ሌሎች ጥቅሶች እንመልከት።
2. ዮሐንስ ከተመለከተው ጋር በሚመሳሰል መንገድ ስለ አንበጦች መቅሰፍት የሚገልጸው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው? ይህስ በጥንት እሥራኤል ላይ ምን ውጤት የሚያስከትል ነበር?
2 በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈው የኢዩኤል መጽሐፍ ዮሐንስ ከተመለከተው መቅሰፍት ጋር የሚመሳሰል የአንበጦችና የሌሎች በራሪ ነፍሳት መቅሰፍት እንደሚመጣ ይናገራል። (ኢዩኤል 2:1-11, 25)a ይህ መቅሰፍት ከሐዲዋን የእስራኤል ብሔር የሚያስጨንቅና ግለሰብ አይሁዶች ንሥሐ ገብተው ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ የሚያደርግ ነበር። (ኢዩኤል 2:6, 12-14) ይህ የሚሆንበት ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ መንፈሱን “ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ” ያፈስሳል። “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን” ከመምጣቱ በፊት አስፈሪና አስደንጋጭ ምልክቶች ይታያሉ።—ኢዩኤል 2:11, 28-32
የመጀመሪያው መቶ ዘመን መቅሰፍት
3, 4. (ሀ) የኢዩኤል ምዕራፍ 2 ትንቢት የተፈጸመው መቼ ነበር? እንዴትስ? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ እንደ አንበጦች መንጋ ያለ መቅሰፍት የደረሰው እንዴት ነበር? መቅሰፍቱስ ለምን ያህል ጊዜ ቆይቶ ነበር?
3 የኢዩኤል ምዕራፍ 2 ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተፈጽሞ ነበር። ይህ ትንቢት የተፈጸመው በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ለመቀባትና “የእግዚአብሔርን ድንቅ ነገሮች” በተለያዩ ልሳኖች እንዲናገሩ ሥልጣን ለመስጠት በፈሰሰ ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት በጣም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በተመለከቱት ነገር በጣም ለተደነቁት ሰዎች የኢዩኤል 2:28, 29 ትንቢት ሲፈጸም መመልከታቸው እንደሆነ ገለጸላቸው። (ሥራ 2:1-21) ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ በአንዳንዶች ላይ ሥቃይ ያስከተለና ሌሎችን ደግሞ ወደ ንሥሐ የመራ ቃል በቃል የአንበጦችና የበራሪ ፍጥረታት መቅሰፍት ወርዶ እንደነበረ የሚገልጽ ታሪክ የለም።
4 በዚያ ዘመን የደረሰ ምሳሌያዊ መቅሰፍት ነበርን? አዎ፣ በእርግጥም ነበር። አዲሶቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አለፋታ በመስበካቸው ምክንያት የመጣ መቅሰፍት ነበር።b በእነዚህ ክርስቲያኖች አማካኝነት ይሖዋ አድማጭ ጆሮ ያላቸውንና ንሥሐ ለመግባት ፈቃደኛ የሆኑትን አይሁዳውያን ከእርሱ ዘንድ የዘላለም በረከት እንዲቀበሉ ጋብዞአል። (ሥራ 2:38-40፤ 3:19) ግብዣውን የተቀበሉ ግለሰቦች ሁሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሞገሱን ተቀብለዋል። አንቀበልም ላሉት ሰዎች ግን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንደ አጥፊ የአንበጣ ሠራዊት ሆነውባቸው ነበር። ከኢየሩሳሌም ጀምረው በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ ተሰራጩ። ብዙ ጊዜ ሳይቆይ በሁሉም ሥፍራ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱንና የእርሱም መነሳት የሚያስገኘውን ውጤት ለሰው ሁሉ በመስበክ የማያምኑትን አይሁዶች አሰቃዩአቸው። (ሥራ 1:8፤ 4:18-20፤ 5:17-21, 28, 29, 40-42፤ 17:5, 6፤ 21:27-30) ይህ መቅሰፍት ይሖዋ የሮማውያን ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከተማይቱን እንዲያጠፋ እስካደረገበት እስከ 70 እዘአ ‘አስፈሪ ቀን’ ድረስ አላቆመም። የዳኑት በእምነት የይሖዋን ስም የጠሩ ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ።—ኢዩኤል 2:32፣ ሥራ 2:20, 21፣ ምሳሌ 18:10
በዛሬው ጊዜ ያለው የአንበጣ መቅሰፍት
5. የኢዩኤል ትንቢት ከ1919 ጀምሮ የተፈጸመው እንዴት ነበር?
5 የኢዩኤል ትንቢት በዚህ የፍጻሜ ዘመን የመጨረሻ ፍጻሜ ይኖረዋል ብለን ብናስብ ምክንያታዊ ነው። ይህ ነገር በእርግጥም እውነት ሆኖ ተገኝቶአል። ከመስከረም 1-8, 1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩ.ኤስ.ኤ በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባ ላይ የፈሰሰው የይሖዋ መንፈስ የይሖዋ ሕዝቦች ምድር አቀፍ የስብከት ዘመቻ እንዲያደራጁ አነሳስቶአቸዋል። ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሕዝቦች ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በዙፋን ላይ መቀመጡን የተገነዘቡት እነርሱ ብቻ እንደመሆናቸው መጠን ይህንኑ ምሥራች ለሕዝብ ሁሉ ከማወጅ ወደኋላ አላሉም። በትንቢቱ ፍጻሜ መሠረት አለአንዳች ፋታ መስበካቸው ለከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና የሚያሰቃይ መቅሰፍት ሆኖባት ነበር።—ማቴዎስ 24:3-8, 14፤ ሥራ 1:8
6. (ሀ) አምስተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ዮሐንስ ምን ተመለከተ? (ለ) ይህ “ኮከብ” ማንን ያመለክታል? ለምንስ?
6 ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከ26 ዓመታት በኋላ የተጻፈው የራእይ መጽሐፍም ስለዚሁ መቅሰፍት ይገልጻል። ይሁን እንጂ በኢዩኤል ትንቢት ላይ ምን የሚጨምረው ነገር አለ? ዮሐንስ ያቆየልንን የጽሑፍ መዝገብ እንመልከት:- “አምስተኛውም መልአክ ነፋ፣ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፣ የጥልቁም ጉድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።” (ራእይ 9:1) ይህ “ኮከብ” ዮሐንስ ከሰማይ ሲወድቅ ከተመለከተው ከራእይ 8:10 ኮከብ የተለየ ነው። አሁን የተመለከተው “ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ” ሲሆን አሁን ደግሞ በምድር ላይ የሚፈጽመው ሥራ ተሰጥቶታል። ታዲያ ይህ ኮከብ መንፈሳዊ አካል ነው ወይስ ሥጋዊ አካል? “የጥልቁ ጉድጓድ መክፈቻ” የተሰጠው መልአክ ሰይጣንን ወደ “ጥልቁ” እንደጣለው ተነግሮአል። (ራእይ 20:1-3) ስለዚህ ከፍተኛ ኃይል ያለው መንፈሳዊ አካል መሆን ይኖርበታል። ዮሐንስ በራእይ 9:11 ላይ የአንበጦቹ ንጉሥ “የጥልቁ መልአክ” እንደሆነ ተናግሮአል። የጥልቁን መክፈቻ የያዘው መልአክ የጥልቁ መልአክ መሆን ስለሚኖርበት ሁለቱም ጥቅሶች የሚያመለክቱት አንዱን መልአክ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚቀበሉት አንዱን መልአካዊ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ስለሆነ ኮከቡም ይሖዋ የሾመውን ንጉሥ ማመልከት ይኖርበታል።—ቆላስይስ 1:13፤ 1 ቆሮንቶስ 15:25
7. (ሀ) “የጥልቁ ጉድጓድ” ሲከፈት ምን ሆነ? (ለ) “ጥልቁ” ምንድን ነው? በዚህ ውስጥ ለአጭር ጊዜ የቆዩት እነማን ናቸው?
7 ታሪኩ እንደሚከተለው በማለት ይቀጥላል:- “የጥልቁንም ጉድጓድ ከፈተው፣ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጉድጓዱ ወጣ። ፀሐይና አየርም በጉድጓዱ ጢስ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፣ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው።” (ራእይ 9:2, 3) በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት “ጉድጓድ” ምንም እንቅስቃሴ የማይደረግበት፣ እንዲያውም የሞት ሥፍራ ነው። (ከሮሜ 10:7፤ ራእይ 17:8፤ 20:1, 3 ጋር አወዳድር።) በቁጥር አነስተኛ የነበሩት የኢየሱስ ወንድሞች የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ባለቀበት ጊዜ (1918-19) እንዲህ ወዳለው የሥራ እንቅስቃሴ ወደ ሌለው “ጉድጓድ” ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ገብተው ነበር። በ1919 ይሖዋ ንሥሐ በገቡት አገልጋዮቹ ላይ መንፈሱን ባፈሰሰ ጊዜ ግን በፊታቸው ላይ የተደቀነውን የሥራ ጫና ለመወጣት በአንድ ላይ ተነሳሱ።
8. አንበጦቹ ሲለቀቁ ብዙ “ጢስ” የወጣው እንዴት ነው?
8 ዮሐንስ እንደተመለከተው አንበጦቹ በተለቀቁ ጊዜ “ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ያለ” ጢስ ታይቶ ነበር።c በ1919 የተፈጸመው ልክ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ነበር። ሁኔታው ለሕዝበ ክርስትናና ለአጠቃላዩ ዓለም ጨለማ ሆኖ ነበር። (ከኢዩኤል 2:30, 31 ጋር አወዳድር።) እነዚህ የዮሐንስ ክፍል የሆኑት አንበጦች መለቀቃቸው የአምላክን መንግሥት ሥራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመግደል አሲረው ለነበሩትና አሁን ደግሞ የአምላክን መንግሥት ለካዱት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ትልቅ ሽንፈት ነበር። የአንበጦቹ ጭፍራ መለኮታዊ ሥልጣን በተሰጠው ጊዜና በዚህም ሥልጣን ለመጠቀም ጠንካራ የፍርድ መልእክቶችን ማሰማት በጀመረበት ጊዜ ከሃዲዋን ሕዝበ ክርስትና እንደ ጢስ ያለ መጋረጃ ሊሸፍናት ጀምሮ ነበር። የሕዝበ ክርስትና “ፀሐይ”፣ ማለትም ብርሃን ሰጪ መስላ መታየትዋ ከባድ ግርዶሽ ወደቀበት። “አየሩም” በመለኮታዊ ፍርድ መግለጫዎች ተሞላ። ምክንያቱም የሕዝበ ክርስትና አምላክ “የአየሩ ባለሥልጣን ገዥ” መሆኑ በግልጽ ተብራራ።—ኤፌሶን 2:2፤ ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19
የሚያሰቃዩት አንበጦች
9. አንበጦቹ ምን የውጊያ መመሪያ ተሰጥቶአቸዋል?
9 እነዚህ አንበጦች የተሰጣቸው የጦርነት መመሪያ ምን ነበር? ዮሐንስ ይነግረናል። “የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆን ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጎዱ ተባለላቸው። አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም። እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው። በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፣ አያገኙትምም። ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል።”—ራእይ 9:4-6
10. (ሀ) መቅሰፍቱ በተለይ የተላከው በእነማን ላይ ነው? በእነርሱስ ላይ ምን ውጤት ያስከትላል? (ለ) ምን ዓይነት ሥቃይን ይጨምራል? (በተጨማሪ የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
10 ይህ መቅሰፍት በመጀመሪያ ደረጃ የወረደው ‘በምድር ሣርና ዛፎች ላይ’ ማለትም በምድር ሕዝቦችና በሕዝቦች መካከል ዋነኛ ሆነው በሚታዩት ሰዎች ላይ አለመሆኑን አስተውል። (ከራእይ 8:7 ጋር አወዳድር።) አንበጦቹ የሚጎዱት በግምባራቸው ላይ ማኅተም የሌላቸውንና ታትመናል ቢሉም ውሸታሞች መሆናቸውን የገዛ ሥራቸው የሚመሰክርባቸውን የሕዝበ ክርስትናን አባሎች ነው። (ኤፌሶን 1:13, 14) ስለዚህ የእነዚህ ዘመናዊ አንበጦች የሚያሠቃይ መልእክት በመጀመሪያ ደረጃ የተሰነዘረው በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ላይ ነው። እነዚህ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ትዕቢተኞች መንጎቻቸውን ወደ ሰማያት ማስገባት አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ቢሆኑ ሊገቡ እንደማይችሉ በአደባባይ በይፋ ሲነገር ሲሰሙ በጣም ተሰቃይተዋል።d የእነርሱ ሁኔታ ‘ዕውር ዕውርን እንደሚመራው’ ነው።—ማቴዎስ 15:14
11. (ሀ) አንበጦቹ የአምላክን ጠላቶች ለምን ያህል ጊዜ እንዲጎዱ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል? ይህስ አጭር ጊዜ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሥቃዩ ምን ያህል ከባድ ነው?
11 ሥቃዩ የሚቆየው ለአምስት ወራት ነው። ታዲያ ይህ አጭር ጊዜ አይደለምን? ቃል በቃል ለአንበጣ አጭር ጊዜ አይደለም። አምስት ወር የአንድ አንበጣ አማካይ ዕድሜ ነው። ስለዚህ ዘመናዊዎቹ አንበጦች የአምላክን ጠላቶች የሚነድፉት በሕይወት በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ ነው። ከዚህም በላይ ሥቃዩ በጣም ከባድ ስለሆነ ሰዎች ሞትን እስከመምረጥ ይደርሳሉ። እውነት ነው፣ አንበጦቹ ከነደፉአቸው ሰዎች መካከል ራሳቸውን ለመግደል የሞከሩ እንዳሉ የሚያረጋገጥ ማስረጃ የለንም። ቢሆንም የአነጋገሩ ዘይቤ እንደ ጊንጥ ንክሻ የሚያሳምመው ሥቃይ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል። ይህም ሁኔታ ኤርምያስ አስቀድሞ ከተመለከተው ባቢሎናውያን ወራሪዎች በሚበታትኑአቸው ከሃዲ እሥራኤላውያን ላይ ካደረሱት ሥቃይ ጋር የሚመሳሰል ነው። እነዚህ እስራኤላውያን ከመኖር ሞትን መርጠው ነበር።—ኤርምያስ 8:3፤ በተጨማሪም መክብብ 4:2, 3ን ተመልከት።
12. አንበጦቹ የሕዝበ ክርስትናን ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንፈሣዊ መንገድ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዳይገድሏቸው ሥልጣን የተሰጣቸው ለምንድን ነው?
12 እነዚህን ሰዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዳይገድሉአቸው ሥልጣን የተሰጣቸው ለምንድን ነው? ይህ መቅሰፍት የሕዝበ ክርስትናን ውሸታምነትና ውድቀትዋን የሚያጋልጥ የመጀመሪያ ወዮታ ነው። መንፈሳዊው በድንነትዋ ግን የሚጋለጠው ቆየት ብሎ ማለትም የጌታ ቀን እየገፋ ሲሄድና ሞት መሰሉ መንፈሳዊ ሁኔታዋ ሙሉ በሙሉ ሲታወቅ ነው። ይህም የሚፈጸመው ከሰዎች ሲሶው በሚገደሉበት በሁለተኛው ወዮታ ጊዜ ነው።—ራእይ 1:10፤ 9:12, 18፤ 11:14
ለጦርነት የታጠቁ አንበጦች
13. አንበጦቹ ምን ዓይነት መልክ ነበራቸው?
13 እነዚህ አንበጦች በጣም አስደናቂ መልክ አላቸው። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል:- “የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደተዘጋጁ ፈረሶች ነው፣ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፣ የሴቶችን ጠጉር የሚመስል ጠጉር ነበራቸው፣ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ። የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው። የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ።”—ራእይ 9:7-9
14. ዮሐንስ ስለ አንበጦቹ የሰጠው መግለጫ በ1919 እንደገና ሕያው ለሆኑት የክርስቲያኖች ቡድን ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ይህ ሥዕላዊ መግለጫ በ1919 እንደገና ሕያው ሆነው ለተነሳሱት ክርስቲያኖች የሚስማማ መግለጫ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በገለጸበት መንገድ ለእውነት ለመዋጋት እንደ ፈረስ ለጦርነት ተዘጋጅተዋል። (ኤፌሶን 6:11-13፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4) ዮሐንስ በራሳቸው ላይ የወርቅ ዘውድ የሚመስል ነገር ተደፍቶባቸው ተመልክቶአል። በምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ የንግሥና ሥልጣን ስለማይኖራቸው እውነተኛ ዘውድ ቢደፉ ትክክል አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 4:8፤ ራእይ 20:4) ይሁን እንጂ በ1919ም ቢሆን ነገሥታት መስለው ታይተው ነበር። የንጉሡ ወንድሞች በመሆናቸው እስከ መጨረሻው ጸንተው ከተገኙ ሰማያዊ ዘውድ ወይም አክሊል ተጠብቆ ይቆያቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 1 ጴጥሮስ 5:4
15. የአንበጦቹ (ሀ) የብረት ጥሩር (ለ) እንደ ሰው ያለ ፊት (ሐ) እንደ ሴቶች ያለ ጠጉር (መ) እንደ አንበሳ ያለ ጥርስ (ሠ) የሚያሰሙት ከፍተኛ ድምፅ ምን ትርጉም አለው?
15 በራእዩ ውስጥ አንበጦቹ የብረት ጥሩር እንዳላቸው ተገልጾአል። ይህም በምንም ነገር የማይፈርስ የጽድቅ አቋም እንዳላቸው ያመለክታል። (ኤፌሶን 6:14-18) በተጨማሪም የሰው ፊት አላቸው። ይህ ደግሞ ሰው የተፈጠረው ፍቅር በሆነው አምላክ ምሳሌ ስለሆነ የፍቅርን ባሕርይ ያመለክታል። (ዘፍጥረት 1:26፤ 1 ዮሐንስ 4:16) ፀጉራቸው እንደ ሴት ፀጉር ረዥም ነው። ይህም ንጉሣቸው ለሆነው ለጥልቁ መልአክ የሚገዙ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው። ጥርሳቸውም የአንበሳ ጥርስ ይመስላል። አንበሳ ጥርሱን የሚጠቀመው ሥጋ ለመቦጨቅ ነው። የዮሐንስ ክፍል ከ1919 ጀምሮ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ችሎአል። ይህ በተለይ “ከይሁዳ ነገድ የሆነውን አንበሳ” የኢየሱስ ክርስቶስን መንግሥት እውነቶች መመገብን ያመለክታል። አንበሳ ድፍረትን እንደሚያመለክት ሁሉ ይህን የሚያሳምም መልእክት አኝኮ ለማዋሃድ፣ በጽሑፎች ላይ ለማውጣትና በምድር ሁሉ ለማሰራጨት ከፍተኛ ድፍረት ጠይቆአል። እነዚህ ምሳሌያዊ አንበጦች ከፍተኛ ድምፅ እንዲሰማ አድርገው ነበር። ይህም ድምፅ “ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ።” የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አርዓያ ስለሚከተሉ ዝም ለማለት አይፈልጉም።—1 ቆሮንቶስ 11:7-15፤ ራእይ 5:5
16. አንበጦቹ “እንደ ጊንጥ ጅራት ያለ ጅራት” ያላቸው መሆኑ ምን ትርጉም አለው?
16 ይህ ስብከት በቃል በሚነገሩ ቃላት ብቻ የተወሰነ አይደለም። “እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፣ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፣ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጎዱ ሥልጣን አላቸው።” (ራእይ 9:10) ታዲያ ይህ ነገር ምን ትርጉም ይኖረዋል? የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት ሥራቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በቃላቸውና በጽሑፎች አማካኝነት በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ ኃይለኛ መግለጫዎችን ያስተላልፋሉ። ስለ መጪው የይሖዋ የበቀል ቀን ማስጠንቀቂያ ስለሚሰጡ መልእክታቸው እንደ ጊንጥ ይናደፋል። (ኢሳይያስ 61:2) የዚህ ትውልድ መንፈሳዊ አንበጦች የሕይወት ዘመናቸውን ከመፈጸማቸው በፊት የተሰጣቸውን የይሖዋን ፍርድ የማሰማትና አንገተ ደንዳና ተሳዳቢዎችን የመጉዳት መለኮታዊ ሥራ ይፈጽማሉ።
17. (ሀ) በ1919 በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ስብሰባ ላይ የሚሰጡትን ምስክርነት የመንደፍ ኃይል የሚጨምር ምን ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር? (ለ) ቄሶች የተሠቃዩት እንዴት ነበር? የዚህንስ አጸፋ ለመመለስ ምን አድርገዋል?
17 ይህ የአንበጦች ጭፍራ በ1919 በተደረገው ስብሰባ ላይ ወርቃማው ዘመን የተባለ አዲስ መጽሔት እንደሚወጣ ማስታወቂያ በተነገረ ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት ነበር። ይህ መጽሔት ምሥክርነት የመስጠት ሥራቸውን የመናደፍ ኃይል ለመጨመር ታስቦ በየሁለት ሣምንት ተዘጋጅቶ የሚወጣ መጽሔት ነበር።e መስከረም 29 ቀን 1920 ታትሞ የወጣው የቁጥር 27 እትም ቀሳውስት ከ1918-19 በነበረው ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በማሳደድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊት አጋልጦ ነበር። በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት ሁሉ ወርቃማው ዘመን ቀሳውስት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ስለሚሠሩት የመሰሪነት ሥራና በተለይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከናዚና ከፋሽስት አምባገነኖች ጋር ሽርክና በመፍጠር ስለፈጸሙት ተንኮል የሚያጋልጡና እንደ ጊንጥ ንክሻ የሚያሳምሙ ርዕሰ ትምህርቶችንና የካርቱን ሥዕላዊ መግለጫዎችን አውጥቶአል። ቀሳውስት ይህን ለመቋቋም ሲሉ ‘በሕግ ተጠቅመው ተንኮል’ በመሥራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ሁከት በማነሳሳት ምላሽ ሰጥተዋል።—መዝሙር 94:20
የዓለም መሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው
18. አንበጦቹ ምን የሚያከናውኑት ሥራ ነበራቸው? አምስተኛው መለከት ሲነፋ ምን ነገር ተፈጸመ?
18 ዘመናዊዎቹ አንበጦች ሊያከናውኑት የሚገባ ሥራ ነበራቸው። የመንግሥቱ ምሥራች መሰበክ ነበረበት። ማንኛውም ስህተትና በደል መጋለጥ ነበረበት። የጠፉ በጎች ተፈልገው መገኘት ነበረባቸው። አንበጦቹ ይህን ሁሉ ሥራ ለመፈጸም በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ዓለም ዝም ብሎ ለመመልከት ተገድዶ ነበር። የዮሐንስ ክፍል አባሎች ለመላእክቱ የመለከት ድምፆች ታዛዦች በመሆን ሕዝበ ክርስትና የይሖዋን ኃይለኛ የቅጣት ፍርዶች መቀበል የሚገባት መሆኗን ማጋለጣቸውን ቀጥለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምስተኛውን መለከት ድምፅ በመታዘዝ ከግንቦት 25-31, 1926 በለንደን ከተማ በእንግሊዝ አገር ባደረጉት ከፍተኛ ስብሰባ ላይ ከእነዚህ የፍርድ ገጽታዎች በአንደኛው ላይ ልዩ ትኩረት አድርገዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ “ለዓለም ገዥዎች የተሰጠ ምሥክርነት” የሚል ውሳኔና መግለጫ እንዲሁም በሮያል አልበርት አዳራሽ “የዓለም ኃያላን የሚናወጡት ለምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው?” የሚል የሕዝብ ንግግር ቀርቦ ነበር። የውሳኔውና የሕዝብ ንግግሩ ሙሉ ቃል በሚቀጥለው ቀን በአንድ እውቅ የለንደን ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቶ ነበር። ከዚያም በኋላ አንበጦቹ የውሳኔውን ቃል በዓለም በሙሉ በ50 ሚልዮን ትራክቶች አሰራጭተዋል። እውነትም ቀሳውስቱን የሚያሰቃይ ድርጊት ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላም እንኳ ሳይቀር በእንግሊዝ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ስለዚህ ነዳፊ መግለጫ በማስታወስ ይናገሩ ነበር።
19. ምሳሌያዊዎቹ አንበጦች ምን ተጨማሪ የውጊያ መሣሪያ አገኙ? ይህስ ስለ ለንደን መግለጫ ምን አለ?
19 ምሳሌያዊዎቹ አንበጦች በዚህ ስብሰባ ላይ ተጨማሪ የውጊያ መሣሪያ አግኝተው ነበር። ይህም መሣሪያ ነፃ መውጣት የተባለው አዲስ መጽሐፍ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ላይ ‘የወንዱ ልጅ’ መንግሥት ማለትም የክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥት በ1914 መወለዱን የሚያረጋግጠውን ምልክት የሚያብራራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ወጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 24:3-14፤ ራእይ 12:1-10) በተጨማሪም በለንደን ከተማ በ1917 የታተመውንና “በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ሰባኪዎች መካከል የሚቆጠሩ” ስምንት ቀሳውስት የፈረሙበትን መግለጫ ጠቅሶ ነበር። እነዚህ ቀሳውስት ዋና ዋናዎቹን የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የባፕቲስት፣ የኮንግሪጌሽናል፣ የፕርስቢተሪያን፣ የኤጲስቆጶሳውያንና የሜቶዲስት አብያተ ክርስቲያናትን የሚወክሉ ነበሩ። መግለጫው የሚከተለውን ቃል አስፍሮ ነበር። “የጊዜያችን ችግር የአሕዛብ ዘመን የተፈጸመ መሆኑን ስለሚያመለክት ከእንግዲህ ወዲህ ጌታ በማንኛውም ጊዜ እንደሚገለጥ መጠባበቅ ይቻላል።” አዎ፣ እነዚህ ቀሳውስት የኢየሱስ መገኘት ምልክቶች መፈጸማቸውን ተገንዝበው ነበር። ይሁን እንጂ አንዳች ነገር ለማድረግ ፈልገው ነበርን? ነፃ መውጣት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጽልን “በጣም የሚያስደንቀው ነገር መግለጫውን የፈረሙት ቀሳውስት ራሳቸው ከጊዜ በኋላ የራሳቸውን መግለጫ ክደው ወደ ዓለም ፍጻሜ እንደተቃረብንና በጌታ ሁለተኛ መገኘት ዘመን እንደምንኖር የሚያሳየውን ማስረጃ አለመቀበላቸው ነው።”
20. (ሀ) ቀሳውስት በአንበጦቹ ሠራዊትና በንጉሣቸው ረገድ ምን ምርጫ አድርገዋል? (ለ) የአንበጦቹ የበላይ ማን እንደሆነ ዮሐንስ ተናገረ? ስሙስ ማን ነው?
20 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት መጪውን የአምላክ መንግሥት ከማስታወቅ ይልቅ ከሰይጣን ዓለም ጋር ጸንተው ለመቆየት መርጠዋል። ከአንበጦቹ ጭፍራና ከንጉሣቸው ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት እንዲኖራቸው አልፈለጉም። ዮሐንስ ቀጥሎ ስለ አንበጦቹ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው፣ እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው። ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን [“ጥፋት” ማለት ነው] በግሪክም አጶልዮን [“አጥፊ” ማለት ነው] ይባላል።” (ራእይ 9:11) በእርግጥም ኢየሱስ “የጥልቁ መልአክ” እና “አጥፊ” እንደመሆኑ መጠን በሕዝበ ክርስትና ላይ የመቅሰፍት ወዮታ ለቆባታል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም፣ ሌላም ነገር ሊቀጥል ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኢዩኤል 2:4, 5, 7ን (በዚህ ላይ አንበጦቹ ፈረስና ሰው እንደሚመስሉና እንደሠረገላ ያለ ድምፅ እንደሚያሰሙ ተገልጾአል) ከራእይ 9:7-9 እና ከኢዩኤል 2:6, 10 ጋር (የአንበጦቹ መቅሰፍት የሚያስከትለውን ሕመምና ሥቃይ የሚገልጽ ነው) እንዲሁም ከራእይ 9:2, 5 ጋር አወዳድር።
b በታኅሣሥ 1, 1961 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “በፍርድ ሸለቆ በብሔራት ላይ በአንድነት መቆም” የሚለውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከት።
c ይህ ጥቅስ በጥልቁ ውስጥ የሲኦል እሳት እንዳለ ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል አለመቻሉን አስተውሉ። ዮሐንስ የተናገረው ብዙ ጢስ ከእቶን እሳት እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ሲወጣ መመልከቱን ነው። (ራእይ 9:2) በጥልቁ ውስጥ እሳት እንደተመለከተ አልተናገረም።
d እዚህ ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል ባሳኒዞ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል አካላዊ ሥቃይ መቀበልን ያመለክታል። ይሁን እንጂ የአእምሮ ሥቃይንም ሊያመለክት የሚችልበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል በ2 ጴጥሮስ 2:8 ላይ ሎጥ በሰዶም ይመለከት በነበረው ሁኔታ ምክንያት “ጻድቅ ነፍሱን ሲያስጨንቅ” (ሲያሠቃይ) እንደነበረ እናነባለን። በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎችም ከሎጥ በተለየ ምክንያት የአእምሮ ሥቃይ ደርሶባቸው ነበር።
e ይህ መጽሔት በ1937 ኮንሶሌሽን፣ በ1946 ደግሞ ንቁ! የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር።
[በገጽ 143 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምስተኛው መለከት መነፋት የመጀመሪያዎቹን ሦስት መቅሰፍቶች አስከተለ
[በገጽ 146 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ። (መዝሙር 45:5) በ1930ዎቹ ዓመታት ይህንን የሥዕል መግለጫ ሐሳብ በመያዝ “የአምላክ ማኅተም የሌለባቸውን” ይነድፉ የነበሩ ከላይ ያለውን የካርቱን ሥዕል የመሰሉ ሥዕሎች ታትመው ይወጡ ነበር
[በገጽ 147 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሮያል አልበርት አዳራሽ፣ ዴሊቨራንስ (ነፃ መውጣት) የተሰኘው መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ የወጣበትና “ለዓለም ገዥዎች የተሰጠ ምስክርነት” የሚለው የአቋም መግለጫ ውሳኔ የተላለፈበት አዳራሽ