ምዕራፍ 23
ሁለተኛው ወዮታ፣ የፈረሰኞች ሠራዊት
1. ቀሳውስት አንበጦቹን ረግጠው ለማጥፋት ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም ምን ነገር ሆኖአል? ሌላ ሁለት ወዮታዎች መከተላቸው ምን ያመለክታል?
ከ1919 ወዲህ የምሳሌያዊዎቹ አንበጦች ወረራ በሕዝበ ክርስትና ላይ ከፍተኛ ሕመምና ሥቃይ አስከትሎአል። አንበጦቹን ረግጠው ለማጥፋት ሞክረው ነበር። ሆኖም አንበጦቹ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ኃይለኛ እየሆኑባቸው መጥተዋል። (ራእይ 9:7) ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፣ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል።” (ራእይ 9:12) ሌላ ተጨማሪ የሚያሠቃይ መቅሠፍት ለሕዝበ ክርስትና ተጠብቆአል።
2. (ሀ) ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ምን ይሆናል? (ለ) ‘ከወርቁ መሰዊያ ቀንዶች የሚወጣው አንድ ድምፅ’ ምን ያመለክታል? (ሐ) አራት መላእክት የተጠቀሱት ለምንድን ነው?
2 ሁለተኛው ወዮታ የመነጨው ከየት ነው? ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፎአል:- “ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፣ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፣ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ:- በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው።” (ራእይ 9:13, 14) መላእክቱ የተፈቱት ከወርቁ መሰዊያ ቀንዶች ለመጣው ድምፅ ምላሽ ለመስጠት ነው። ይህ መሰዊያ የዕጣኑ የወርቅ መሰዊያ ሲሆን ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ከዚህ መሰዊያ የተወሰደው የወርቅ ማእጠንት ዕጣን በቅዱሳን ጸሎት ተመስሎአል። (ራእይ 5:8፤ 8:3, 4) ስለዚህ ይህ አንድ ድምፅ በምድር ላይ የሚገኙት ቅዱሳን የሚያቀርቡትን የተባበረ ጸሎት ያመለክታል። እነዚህ ቅዱሳን የበለጠ ነጻነት አግኝተው በበለጠ ኃይልና ጉልበት የይሖዋ “መልእክተኞች” ሆነው እንዲያገለግሉ ጸልየዋል። እዚህ ላይ “መላእክት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉም “መልእክተኞች” ማለት ነው። ታዲያ አራት መላእክት የነበሩት ለምንድን ነው? ይህ ምሳሌያዊ ቁጥር መላዋን ምድር ለመሸፈን በሚያስችላቸው መንገድ የሚደራጁ መሆናቸውን የሚያመለክት ይመስላል።—ራእይ 7:1፤ 20:8
3. አራቱ መላእክት ‘በታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ የታሰሩት’ እንዴት ነው?
3 እነዚህ መላእክት “በታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ” የታሰሩት እንዴት ነው? በጥንት ዘመን ይሖዋ ለአብርሃም እንደሚሰጠው ቃል የገባለትን ምድር በስተሰሜን ምሥራቅ የሚያዋስነው የኤፍራጥስ ወንዝ ነበር። (ዘፍጥረት 15:18፤ ዘዳግም 11:24) መላእክቱ አምላክ ወደሰጣቸው ምድር ወይም ምድራዊ ሥራቸውን ወደሚያከናውኑበት ክልል እንዳይገቡ ድንበሩ ላይ ታግደው የቆሙ ይመስላል። ይሖዋ ያዘጋጀላቸውን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዳይፈጽሙ ታግደው ነበር። በተጨማሪም የኤፍራጥስ ወንዝ ከባቢሎን ከተማ ጋር የቅርብ ዝምድና ነበረው። ሥጋዊ እስራኤላውያንም ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከጠፋች በኋላ ለ70 ዓመታት ያህል ‘በታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ታስረው’ በግዞት ኖረዋል። (መዝሙር 137:1) በ1919 ዓመትም መንፈሳዊ እስራኤላውያን በተመሳሳይ እሥራት ሥር ይገኙ ስለነበረ በከፍተኛ ሐዘን የይሖዋን መመሪያ በጸሎት ይጠይቁ ነበር።
4. አራቱ መላእክት ምን ሥራ ተሰጥቶአቸዋል? ይህስ ሥራ የተፈጸመው እንዴት ነው?
4 ይሁን እንጂ ዮሐንስ የሚከተለውን ለማለት መቻሉ በጣም ያስደስተናል። “የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ።” (ራእይ 9:15) ይሖዋ ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ የማይል ጊዜ ጠባቂ አምላክ ነው። ለሁሉም ነገር የጊዜ ፕሮግራም ሲኖረው ያወጣውንም ፕሮግራም ይጠብቃል። በዚህም ምክንያት የተነሣ እነዚህ መልእክተኞች በፕሮግራሙ በተወሰነውና መሥራት የሚኖርባቸውን ሥራ ለማከናወን በሚችሉበት ጊዜ ተለቅቀዋል። በ1919 ከእሥራት ወጥተው ለሥራ ዝግጁ ሆነው ሲቀርቡ የተሰማቸውን ደስታ መገመት ይቻላል። ሰዎችን እንዲያሠቃዩ ብቻ ሳይሆን “የሰዎችን ሲሶ እንዲገድሉ” ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል። ይህም የመጀመሪያዎቹ አራት የመለከት ድምፆች ካስታወቁትና በምድር፣ በባሕር፣ በባሕር ፍጥረታት፣ በምንጮች፣ በወንዞችና በሰማይ ብርሃናት ሲሶ ላይ ከሚወርደው መቅሰፍት ጋር ዝምድና አለው። (ራእይ 8:7-12) አራቱ መላእክት ከዚህም የበለጠ ሥራ ይፈጽማሉ። የሕዝበ ክርስትናን መንፈሳዊ በድንነት ሙሉ በሙሉ ስለሚያጋልጡ ‘ይገድላሉ።’ ከ1922 ጀምሮ የተነገሩትና እስከ ጊዜያችን ድረስ ሲነገሩ የቆዩት የመለከት መግለጫዎች ይህን ዓላማ ፈጽመዋል።
5. የስድስተኛው መለከት ድምፅ ሕዝበ ክርስትናን በተመለከተ በ1927 ጎልቶ የተሰማው እንዴት ነው?
5 ሰማያዊው መልአክ ስድስተኛውን መለከት ከነፋ ብዙ ጊዜ እንዳልቆየ ልብ በሉ። ለዚህም መለከት ምላሽ በመስጠት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በተከታታይ ካደረጉአቸው ዓመታዊ ስብሰባዎች ስድስተኛ የሆነውን በቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ ከተማ በካናዳ አደረጉ። ሐምሌ 24 ቀን 1927 እሁድ እለት የቀረበው ፕሮግራም በ53 ሬዲዮ ጣቢያዎች በቀጥታ ተላልፎ ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ይህን የሚያክል የሬዲዮ ስርጭት ኖሮ አያውቅም። ይህን የአፍ መልእክት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ አድማጮች ሳይሰሙት አልቀረም። በመጀመሪያ የቀረበው ጠንካራ ውሳኔ የሕዝበ ክርስትናን መንፈሳዊ ምውትነት ካጋለጠ በኋላ የሚከተለውን ግብዣ አቅርቦአል:- “በዚህ ግራ በተጋባ ዘመን ይሖዋ አምላክ ሰዎች ሁሉ ሕዝበ ክርስትናን ወይም ‘የተደራጀውን ክርስትና’ እንዲተዉና ለዘላለም ጥለው እንዲወጡ ይጠይቃል። . . . ሰዎች ሁሉ ሙሉ ልባቸውንና ታማኝነታቸውን ለይሖዋ አምላክ፣ ለንጉሡና ለመንግሥቱ ይስጡ።” ከዚያ ቀጥሎ የቀረበው የሕዝብ ንግግር ርዕስ “ለሰዎች ሁሉ ነፃነት” የሚል ነበር። ይህንንም ንግግር ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ዮሐንስ ቀጥሎ በራእይ ከተመለከተው ‘እሳት፣ ጢስና ዲን’ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በተለመደው የግለት አቀራረብ ዘዴው አቀረበው።
6. ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተውን የፈረሰኞች ጭፍራ የገለጸው እንዴት ነው?
6 “የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው። የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፣ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ።”—ራእይ 9:16-18
7, 8. (ሀ) ፈረሰኞቹ የሚነጉዱት በማን አመራር ሥር ሆነው ነው? (ለ) ፈረሰኞቹ ከእነርሱ በፊት ከታዩት አንበጦች ጋር የሚመሳሰሉት በምን መንገዶች ነው?
7 ይህ የፈረሰኞች ጭፍራ ወደፊት የሚተምመው በአራቱ መላእክት እየተመራ እንደሆነ ግልጽ ነው። በጣም የሚያስፈራ ትዕይንት ነው! ይህን የሚያክል የፈረሰኞች ጭፍራ አንተን ለማሳደድ ቢመጣ ምን እንደሚሰማህ ገምት። ይህን ማየትህ ብቻውን ልብህ በፍርሐት እንዲሸበር ያደርጋል። ይሁን እንጂ ይህ የፈረሰኞች ጭፍራ ከእርሱ በፊት ከታየው የአንበጣ መንጋ ጋር እንደሚመሳሰል አስተውለሃልን? አንበጦቹ ፈረስ ይመስሉ ነበር። በፈረሰኞቹም ጭፍራ ውስጥ ፈረሶች አሉ። ስለዚህ አንበጦቹም ሆኑ የፈረሰኞቹ ጭፍራ ለቲኦክራቲካዊ ውጊያ የተሰለፉ ናቸው። (ምሳሌ 21:31) አንበጦቹ ጥርሳቸው የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር። የፈረሰኞቹ ፈረሶች ደግሞ ራሳቸው የአንበሳ ራስ ይመስል ነበር። ስለዚህ ሁለቱም መሪያቸው፣ አዛዣቸውና ምሳሌያቸው ከሆነው ከይሁዳ ነገድ አንበሳ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዝምድና አላቸው ማለት ነው።—ራእይ 5:5፤ ምሳሌ 28:1
8 አንበጦቹም ሆኑ ፈረሰኞቹ በይሖዋ የፍርድ ሥራ ይካፈላሉ። አንበጦቹ የወጡት በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው ወዮታና ጥፋት ምሳሌ ከሆነው ጢስ ውስጥ ነው። ከፈረሶቹ አፍ ደግሞ እሳት፣ ጢስና ዲን ይወጣል። አንበጦቹ የብረት ጥሩር ነበራቸው። ይህም ልባቸው በማያወላውል የጽድቅ ፍቅር የተጠበቀ መሆኑን ያመለክታል። ፈረሰኞቹ ደግሞ ቀይ፣ ሰማያዊና ቢጫ ቀለም ያለው የደረት ጥሩር ለብሰዋል። እነዚህ ቀለሞች ከፈረሶቹ አፍ እያፈተለከ የሚወጣው ቀሳፊ የፍርድ መልእክት ምሳሌ የሆኑት የእሳት፣ የጢስና የድኝ ቀለሞች ናቸው። (ከዘፍጥረት 19:24, 28ና ከሉቃስ 17:29, 30 ጋር አወዳድር።) አንበጦቹ ሰዎችን የሚያሰቃዩባቸው ጊንጥ የመሰለ ጅራት ነበራቸው። ፈረሶቹ ደግሞ ሰዎችን የሚገድሉባቸው እንደ እባብ ያሉ ጅራቶች አሉአቸው። አንበጦቹ የጀመሩትን ሥራ ፈረሰኞቹ በበለጠ ኃይልና ጥንካሬ ሰርተው ወደ ፍጻሜው ማድረስ ያለባቸው ይመስላል።
9. ፈረሰኞቹ የምን ምሳሌ ናቸው?
9 ታዲያ ይህ የፈረሰኞች ጭፍራ የምን ምሳሌ ነው? በሕዝበ ክርስትና ላይ የወረደውን መለከት መሰል የይሖዋ የፍርድና የመለኮታዊ በቀል መልእክት ማወጅ የጀመሩትና ‘ለመንደፍና ለመጉዳት’ ሥልጣን የተሰጣቸው የተቀቡት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ስለሆኑ ‘እንዲገድሉ’ ማለትም ሕዝበ ክርስትናና ቀሳውስትዋ በመንፈሳዊ ረገድ ሙሉ በሙሉ በድን መሆናቸውን፣ ይሖዋ ፈጽሞ የጣላቸውና ‘ለእቶን እሳት’ ማለትም ለዘላለም ጥፋት የተጠበቁ መሆናቸውን እንዲያውጁ ይሖዋ የሚጠቀመው በእነዚሁ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መሆን እንደሚኖርበት ለመገመት እንችላለን። በእርግጥም መላው የታላቂቱ ባቢሎን ድርጅት መጥፋት ይኖርበታል። (ራእይ 9:5, 10፤ 18:2, 8፤ ማቴዎስ 13:41-43) ታላቂቱ ባቢሎን ከመጥፋትዋ በፊት ግን የዮሐንስ ክፍል አባሎች የሕዝበ ክርስትናን በድንነት ለማጋለጥ ‘የመንፈስ ሠይፍ በሆነው የአምላክ ቃል’ ይጠቀማሉ። ይህን “በሰዎች ሲሶ” ላይ የሚፈጸመውን ምሳሌያዊ ግድያ የሚመሩት አራቱ መላእክትና ፈረሰኞቹ ናቸው። (ኤፌሶን 6:17፤ ራእይ 9:15, 18) ይህም በጣም ብዙ የሆነው የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሠራዊት ወደ ጦርነቱ በሚዘምትበት ጊዜ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የበላይ ጥበቃ ሥር ሆኖ ተገቢ የሆነ ቲኦክራቲካዊ አመራርና አደረጃጀት እንደሚያገኝ ያመለክታል።
ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ
10. ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ ፈረሰኞች የኖሩት በምን ሁኔታ ነው?
10 እነዚህ ፈረሰኞች እንዴት ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ ሊሆኑ ቻሉ? አንድ እልፍ ቃል በቃል ከተወሰደ 10,000 ነው። ስለዚህ ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ 200 ሚልዮን ይሆናል ማለት ነው።a እርግጥ በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አሉ። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ለመሆን ገና ብዙ ይቀረዋል። ቢሆንም በዘኍልቁ 10:36 ላይ የሚገኘውን የሙሴ ቃል እናስታውሳለን። “አቤቱ፣ [“ይሖዋ፣” NW] ወደ እሥራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ” ብሎ ነበር። (ከዘፍጥረት 24:60 ጋር አወዳድር።) ይህን አነጋገር ቃል በቃል ከተረዳን ‘በአሥር ሚልዮን ወደሚቆጠሩት የእስራኤል ሕዝብ ተመለስ’ ማለት ይሆናል። ይሁን እንጂ በሙሴ ዘመን የእሥራኤላውያን ቁጥር ገና ከሁለት እስከ ሶስት ሚልዮን ብቻ ይደርስ ነበር። ታዲያ ሙሴ ምን ማለቱ ነበር? እስራኤላውያን “እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” ሊቆጠሩ የማይችሉ እንደሚሆኑ አስቦ የተናገረው ቃል እንደሆነ እርግጠኛ ነው። (ዘፍጥረት 22:17፤ 1 ዜና 27:23) ስለዚህ “እልፍ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው የቁጥር ወሰን የሌለውን ብዛት ለማመልከት ነው። በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል “ጌታ ሆይ፣ ሊቆጠሩ የማይችሉትን እስራኤላውያን አሳርፍ” ሲል ተርጉሞአል። ይህም በግሪክኛና በዕብራይስጥ መዝገበ ቃላት “እልፍ” ለሚለው ቃል ከተሰጠው ሁለተኛ ትርጉም ጋር ይስማማል። እልፍ “ሊቆጠር የማይችል ብዙ ሕዝብ፣” “እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ” የሚል ትርጉም አለው።—የኒው ቴየር የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ ወደ እንግሊዝኛ መፍቻ፣ የጀሰንየስ የብሉይ ኪዳን ዕብራይስጥ ወደ እንግሊዝኛ መፍቻ መዝገበ ቃላት በኢድዋርድ ሮቢንሰን የተተረጎመ።
11. የዮሐንስ ክፍል በምሳሌያዊ ሁኔታ እንኳን እልፍ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ያስፈልጋል?
11 ይሁን እንጂ በምድር ላይ የቀሩት የዮሐንስ ክፍል አባሎች ከ10,000 ወይም ከአንድ እልፍ ያነሱ ናቸው። ታዲያ ሊቆጠሩ በማይችሉ እጅግ ብዙ የፈረሰኞች ጭፍራ ሊመሰሉ የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌያዊ አነጋገር እንኳን እልፍ አእላፋት እንዲሆኑ ማጠናከሪያ ኃይል አያስፈልጋቸውምን? አዎ፣ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋም በቸርነቱ ተጨማሪ ኃይል በመስጠት አጠናክሮአቸዋል። እነዚህ ኃይሎች የተገኙት ከየት ነው?
12, 13. የማጠናከሪያ ኃይል የተገኘበትን ምንጭ የሚያመለክቱን ከ1918 እስከ 1935 የተፈጸሙ የትኞቹ የታሪክ ክንውኖች ናቸው?
12 የዮሐንስ ክፍል አባሎች ከ1918 እስከ 1922 ባለው ጊዜ በጭንቅ ለተዋጠው የሰው ልጅ “በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ከሚኖሩት መካከል ሞትን ፈጽሞ የማያዩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖራሉ” የሚል አስደሳች ተስፋ ዘርግተው ነበር። በ1923 ደግሞ በማቴዎስ 25:31-34 ላይ የተጠቀሱት በጎች በአምላክ መንግሥት ሥር ሆነው በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚወርሱ ታወቀ። በ1927 ተደርጎ በነበረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የወጣው የሕዝቦች ነፃነት የተባለው ንዑስ መጽሐፍም ስለ ተመሳሳይ ተስፋ አብራርቶ ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይም ቅን የነበረው የኢዮናዳብ ክፍልም ሆነ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚታየው አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ‘የሚያዝኑትና የሚተክዙት ሰዎች’ የምድራዊ ሕይወት ተስፋ ካላቸው ምሳሌያዊ በጎች ጋር አንድ እንደሆኑ ተገለጸ። (ሕዝቅኤል 9:4፤ 2 ነገሥት 10:15, 16) የነሐሴ 15, 1934 መጠበቂያ ግንብ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ወደ ዘመናዊው “የመማጸኛ ከተማ” በመምራት እንዲህ አለ:- “የኢዮናዳብ ክፍል አባሎች የአምላክን የመለከት ድምፅ ሰምተው ወደ አምላክ ድርጅት በመሸሻቸውና ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመተባበራቸው ማስጠንቀቂያውን የተቀበሉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በዚያም ለዘላለም ይኖራሉ።”—ዘኁልቁ 35:6
13 በ1935 ደግሞ እነዚህ የኢዮናዳብ ክፍል አባሎች በዋሽንግተን፣ ዲ.ሲ፣ ዩ.ኤስ.ኤ በሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ታላቅ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተጋበዙ። በዚያም ግንቦት 31 ቀን ዐርብ ዕለት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባለውን ዝነኛ ንግግር አደረገ። በዚህም ንግግሩ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹት እጅግ ብዙ ሰዎች በማቴዎስ 25:33 ላይ ከተጠቀሱት በጎች ጋር አንድ እንደሆኑና ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ራሳቸውን የወሰኑ ሰዎች እንደሚያመለክቱ በግልጽ አስረዳ። በዚሁ ስብሰባ ላይ ወደፊት በብዛት ለሚፈጸመው ሥራ መንገድ ጠራጊ በመሆን 840 የይሖዋ ምሥክሮች ተጠመቁ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ነበሩ።b
14. እጅግ ብዙ ሰዎች በፈረሰኞቹ ዘመቻ ይካፈላሉን? በ1963 ምን ዓይነት ውሳኔ ተገልጾአል?
14 ታዲያ ይህ ታላቅ ሕዝብ በ1922 በጀመረውና በ1927 በቶሮንቶ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ልዩ ትኩረት በተሰጠው የፈረሰኞች ዘመቻ ተካፍሎአልን? በእርግጥም በአራቱ መላእክት ማለትም በቅቡዓኑ የዮሐንስ ክፍል አባሎች አመራር ሥር ሆኖ በዘመቻው ተካፍሎአል። በ1963 በመላው ዓለም ተደርጎ በነበረው “የዘላለሙ ምሥራች” የወረዳ ስብሰባ ላይ እጅግ ብዙ ሰዎች ከዮሐንስ ክፍል ጋር አንድ ሆነው ቀስቃሽ የሆነ ውሣኔ አስተላልፈዋል። ውሣኔው ዓለም “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የምድር መናወጥ እንደተደቀነበትና የዓለም የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉና ዘመናዊቷ ሃይማኖታዊ ባቢሎን ፈጽመው እንደሚናወጡ” የሚገልጽ ነበር። በተጨማሪም መግለጫው የሚከተለውን አስታውቆ ነበር:- “አለምንም አድልዎና ምርጫ ለሰው ሁሉ የአምላክን መሲሐዊ መንግሥትና፣ ፈጣሪ አምላክን በመንፈስና በእውነት ለማምለክ የሚፈልጉትን ሰዎች ነፃ የሚያወጣውን በአምላክ ጠላቶች ላይ የሚወርድ የቅጣት ፍርድ መናገራችንን እንቀጥላለን።” ይህ ውሣኔ በምድር ዙሪያ በተደረጉ 24 ስብሰባዎች ላይ በተገኙ 454, 977 ተሰብሳቢዎች በጋለ ስሜት ጸደቀ። ከእነዚህ መካከል 95 በመቶ የሚያክሉት የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ነበሩ።
15. (ሀ) በ2005 እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋ በመስክ የሚጠቀምበት ኃይል ስንት መቶኛ ያክሉ ነበር? (ለ) በዮሐንስ 17:20, 21 ላይ የተመዘገበው የኢየሱስ ጸሎት እጅግ ብዙ ሰዎች ከዮሐንስ ክፍል ጋር ያላቸውን አንድነት የገለጸው እንዴት ነው?
15 እጅግ ብዙ ሰዎች በሕዝበ ክርስትና ላይ መቅሰፍት በማውረድ ሥራ ከዮሐንስ ክፍል ጋር ፍጹም አንድነትና ህብረት እንዳላቸው ማሳወቃቸውን ቀጥለዋል። በ2005 እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋ በመስኩ ሥራ ከሚገለገልበት ኃይል 99.8 በመቶ የሚሆነውን ክፍል ይዘው ነበር። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በዮሐንስ 17:20, 21 ላይ የሚከተለውን ጸሎት ካቀረበለት የዮሐንስ ክፍል ጋር ሙሉ ስምምነት አላቸው። “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፣ ከቃላቸው የተነሳ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ አንተ፣ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።” ቅቡዓን የዮሐንስ ክፍል አባሎች የኢየሱስን አመራር በመከተል በግንባር ቀደምትነት ሲሰለፉ ቀናተኞቹ እጅግ ብዙ ሰዎች ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተደረጉት የፈረሰኛ ዘመቻዎች ሁሉ በአጥፊነት ተወዳዳሪ በሌለው ዘመቻ ተካፍለዋል።c
16. (ሀ) ዮሐንስ የምሳሌያዊዎቹን ፈረሶች አፍና ጅራት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች አፍ ለአገልግሎት የተዘጋጀው እንዴት ነው? (ሐ) ‘እባብ የሚመስለው ጅራታቸው’ የምን ምሳሌ ነው?
16 ይህ ፈረሰኛ ሠራዊት በጦርነቱ የሚገለገልበት መሣሪያ ያስፈልገዋል። ይሖዋም ይህንን መሣሪያ በአስደናቂ ሁኔታ ሰጥቶአል። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል:- “የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፣ ራስም አላቸው በእርሱም ይጎዳሉ።” (ራእይ 9:19) ይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑትንና የተጠመቁትን አገልጋዮቹን ለዚህ አገልግሎት ሾሞአቸዋል። ቃሉን እንዲሰብኩና ‘በተማረ አንደበት’ እንደ ባለሥልጣን እንዲናገሩ ለማስቻል በቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት አሰልጥኖአቸዋል። ቃሉን በአፋቸው ላይ አድርጎ ፍርዱን “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” እንዲያስታውቁ ልኮአቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ ኢሳይያስ 50:4፤ 61:2፤ ኤርምያስ 1:9, 10፤ ሥራ 20:20) የዮሐንስ ክፍል አባሎችና እጅግ ብዙ ሰዎች ከጅራት ጋር የሚመሳሰል ነዳፊ መልእክት በየሰዎች ቤት እየተዉ ይሄዳሉ። ባለፉት ዓመታት በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችንና መጽሔቶችን አሰራጭተዋል። ከይሖዋ ስለሚመጣው “ጉዳት” ማስታወቂያ ለተነገራቸው ተቃዋሚዎቻቸው ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ መስለው ይታያሉ።—ከኢዩኤል 2:4-6 ጋር አወዳድር።
17. ሥራው የታገደ በመሆኑ ምክንያት ጽሑፎችን ማሰራጨት በማይቻልባቸው አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በፈረሰኞቹ ግልቢያ ይካፈላሉን? አስረዳ።
17 የዚህ ፈረሰኛ ሠራዊት አካል የሆነ አንድ በጣም ቀናተኛ ክፍለ ጦር የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በታገደባቸው አገሮች ከሚኖሩ ወንድሞች የተውጣጣ ነው። እነዚህ ወንድሞች በተኩላዎች መካከል እንደሚኖር በግ ስለሆኑ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” መሆን ይገባቸዋል። ይሖዋን ስለሚታዘዙ ያዩትንና የሰሙትን ከመናገር ዝም ሊሉ አይችሉም። (ማቴዎስ 10:16፤ ሥራ 4:19, 20፤ 5:28, 29, 32) ለሕዝብ የሚያሰራጩት ጽሑፍ ስለሌላቸው በፈረሰኞቹ ዘመቻ ምንም ተሳትፎ አላደረጉም ለማለት እንችላለንን? በፍጹም አንችልም! የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን የሚናገሩበት አፍና ሥልጣን ከይሖዋ ተሰጥቶአቸዋል። መደበኛ ባልሆኑ ዘዴዎች እየተጠቀሙና ሰዎችን በሚያሳምን ሁኔታ እያነጋገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይጀምሩላቸዋል። በዚህም መንገድ “ብዙዎችን ወደ ጽድቅ መልሰዋል።” (ዳንኤል 12:3) ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፉ ጽሑፎችን በመተው በጅራታቸው ባይናደፉም እንኳን በዘዴና በጥበብ ስለመጪው የይሖዋ የበቀል ቀን ሲመሰክሩ ከአፋቸው ምሳሌያዊ እሳት፣ ጢስና ድኝ ይወጣል።
18. እነዚህ ፈረሰኞች እንደ መቅሰፍት ያሉትን መልእክቶች በታተሙ ጽሑፎች ያሰራጩት በስንት ቋንቋዎችና በምን ያህል ብዛት ነው?
18 በሌሎች አካባቢዎች ግን የመንግሥቱ ጽሑፎች የሕዝበ ክርስትናን ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችና አሠራሮች በማጋለጥ ምሳሌያዊ ጉዳት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ በቁጥር እጅግ ብዙ የሆኑት ፈረሰኞች በጣም ዘመናዊ በሆኑ የማተሚያ መሣሪያዎች በመጠቀም ከ2005 በፊት በነበሩት 68 ዓመታት ከ450 በሚበልጡ የምድር ቋንቋዎች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጽሐፎችን፣ መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን ለማሰራጨት ችለዋል። ይህም ከሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ በጣም የሚበልጥ ታላቅ ቁጥር ነው። በእውነትም እነዚህ ጅራቶች በጣም አሳምመው ነድፈዋቸዋል።
19, 20. (ሀ) የቀሳፊው መልእክት ዋነኛ ዒላማ ሕዝበ ክርስትና ብትሆንም ከሕዝበ ክርስትና ርቀው በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች መልእክቱን እንዴት ተቀብለዋል? (ለ) ዮሐንስ ሰዎች በአጠቃላይ የሚያሳዩትን አቀባበል የገለጸው እንዴት ነው?
19 ይህ ቀሳፊ መልእክት “የሰዎችን ሲሶ” እንዲገድል ይሖዋ አቅዶ ነበር። ስለዚህ መቅሰፍቱ የተሰነዘረው በሕዝበ ክርስትና ላይ ነው። ቢሆንም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ግብዝነት በደንብ በሚታወቅባቸው ከሕዝበ ክርስትና ርቀው በሚገኙ አገሮችም ተዳርሶአል። ታዲያ በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በዚህች ብልሹ ሃይማኖታዊ ድርጅት ላይ የወረደውን መቅሰፍት በመመልከታቸው ምክንያት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ተስበዋልን? አዎ፣ ብዙዎች ተስበዋል! ከሕዝበ ክርስትና ቀጥተኛ ተጽእኖ ውጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የዋህና ቅን ሰዎች መልእክቱን ተቀብለዋል። ስለ አብዛኞቹ ሰዎች ግን ዮሐንስ የሚከተለውን ይነግረናል:- “በእነዚህም መቅሰፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሰሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።” (ራእይ 9:20, 21) እነዚህ ንስሐ ለመግባት እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች አይለወጡም። የዓለም ሕዝብ ሃይማኖት በአጠቃላይ አይለወጥም። በክፋት አኗኗራቸው የሚጸኑ ሁሉ በታላቁ የይሖዋ የበቀል ቀን የቅጣት ፍርድ ይፈጸምባቸዋል። ይሁን እንጂ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—ኢዩኤል 2:32፤ መዝሙር 145:20፤ ሥራ 2:20, 21
20 አሁን የተወያየነው ስለ ሁለተኛው ወዮታ ነው። ይህ ወዮታ ከመፈጸሙ በፊት ግን የሚፈጸም ሌላ ነገር ይኖራል። ይህንንም በሚከተለው ምዕራፍ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በሄንሪ ባርክሌይ የተዘጋጀው የራእይ መጽሐፍ ማብራሪያ “ሁለት እልፍ ጊዜ እልፍ” ስለሚለው ቁጥር ሲያትት “ቁጥሩ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ቃል በቃል ፍጻሜ ይኖረዋል ብለን እንዳናስብ ያግደናል። ከዚህ የሚቀጥለው መግለጫም ቢሆን ይህን ይደግፍልናል” ብሎአል።
b ገጽ 119-126ን፣ በተጨማሪም በ1932 በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን መቀደስ ሦስተኛ መጽሐፍ ገጽ 83-84ን ተመልከት።
c ዮሐንስ የተመለከተው የፈረሰኞች ሠራዊት “የወርቅ አክሊል የሚመስል ዘውድ” ስላልደፋ ከአንበጦቹ የተለየ ሆኖአል። (ራእይ 9:7) ይህም ትልቁን የፈረሰኞች ጭፍራ ክፍል የያዙት እጅግ ብዙ ሰዎች የአምላክን ሰማያዊ መንግሥት የመውረስ ተስፋ የላቸውም ከሚለው ሐቅ ጋር ይስማማል።
[በገጽ 149 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስድስተኛው መለከት መነፋት ሁለተኛውን ወዮታ አስከተለ
[በገጽ 150 እና 151 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አራቱ መላእክት በታሪክ ውስጥ በጣም ታላቅ የሆነውን የፈረሰኞች ዘመቻ ይመራሉ
[በገጽ 153 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ፈረሰኞች በሚልዮን የሚቆጠሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አሰራጭተዋል
[በገጽ 154 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የቀሩት ግን ንስሐ አልገቡም