ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ከመከራ መዳን
“ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፣ . . . ደስ ይበላችሁ።”—1 ጴጥሮስ 4:13
1. ይሖዋ አገልጋዮቹን ያበለጸጋቸው እንዴት ነው?
ይሖዋ ምስክሮቹን በብዙ ስጦታዎች አበልጽጓቸዋል። ታላቁ አስተማሪያችን እንደመሆኑ መጠን የፈቃዱና የዓላማውን ሙሉ እውቀት ሰጥቶናል። በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነትም ብርሃኑን በድፍረት የማብራት ችሎታ በውስጣችን እንዲያድግ አድርጓል። በመንፈስ ተነሳስቶ የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 1:5-7 ላይ እንዲህ ይለናል፦ “ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና . . . እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጐድልባችሁም።”
2. “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ” ምን አስደሳች ተስፋ ይዞልናል?
2 “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ” ተብሎ የተጠቀሰው ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ባለግርማ ንጉሥ ሆኖ ለታማኝ ተከታዮቹ ዋጋቸውን ለመስጠትና አምላካዊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የበቀል ቅጣቱን በመፈጸም እርምጃ ለመውሰድ የሚገለጥበትን ጊዜ ያመለክታል። ይህ እርምጃ የሰይጣንን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የሚያበስር በመሆኑ ፍጹም አቋም ጠባቂ የሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችና ከጎናቸው በታማኝነት የሚቆሙት ባልንጀሮቻቸው የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ሐሴት የሚያደርጉበትና የሚደሰቱበት’ ጊዜ እንደሚሆን 1 ጴጥሮስ 4:13 ያመለክታል።
3. በተሰሎንቄ እንደነበሩት ወንድሞቻችን ጸንተን መቆም ያለብን እንዴት ነው?
3 ይህ የሚሆንበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ ሰይጣን በጣም ስለሚቆጣ በእኛ ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ያጠነክራል። እንደሚያገሣ አንበሳ ሆኖ ሊውጠን ይፈልጋል። ጸንተን መቆም አለብን! (1 ጴጥሮስ 5:8-10) በጥንቷ ተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩት ወንድሞቻችን በእውነት ውስጥ አዲሶች በነበሩበት ጊዜ ብዙ የይሖዋ ምስክሮች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የመሰለ መከራ አጋጥሟቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የጻፈላቸው ቃላት ለእኛ በጣም ትርጉም ያላቸው ናቸው፦ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፣ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።” (2 ተሰሎንቄ 1:6-8) አዎ፤ ከመከራ የምናርፍበት ጊዜ ይመጣል!
4. በኢየሱስ መገለጥ ጊዜ ቀሳውስት የጥፋት ፍርድ የሚገባቸው ለምንድን ነው?
4 በጳውሎስ ዘመን ብዙ መከራ ይመጣ የነበረው ከአይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ሰላም ወዳድ በሆኑት የይሖዋ ምስክሮች ላይ ተቃውሞ የሚደርሰው በአብዛኛው አምላክን እንወክላለን ከሚሉ ሰዎችና በተለይም ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ነው። እነዚህ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት አምላክን እናውቃለን ቢሉም አንዱን አምላክ ይሖዋን ትተው በእርሱ ቦታ ምሥጢራዊ የሆነ ሥላሴ ተክተዋል። (ማርቆስ 12:29) ከመከራ ዕረፍት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉት በሰው አገዛዝ ስለሆነና መጪውን የክርስቶስ የጽድቅ መንግሥት ምሥራች ስለማይቀበሉ ለጌታችን ለኢየሱስ ወንጌል አልታዘዙም። እነዚህ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች በሙሉ ‘ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ በሚገለጥበት’ ጊዜ መደምሰስ አለባቸው።
የኢየሱስ ክርስቶስ “መምጣት”
5. የኢየሱስ መገለጥ በማቴዎስ 24:29, 30 ላይ ጉልህ በሆነ መንገድ የተገለጸው እንዴት ነው?
5 ይህ መገለጥ በማቴዎስ 24:29, 30 ላይ በሥዕላዊ መንገድ ሕያው ተደርጎ ተገልጿል። ኢየሱስ የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ ምልክቶች የተለያዩ ገጽታዎች ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም [የአምላክ መሲሃዊ ንጉሥ የሆነው] በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።” ይህ መምጣት በግሪክኛ ኤርኮሜኖን የሚያመለክተው ኢየሱስ የይሖዋን ስም ከነቀፌታ የሚነፃ በመሆን መገለጡን ነው።
6, 7. “ዓይን ሁሉ [የሚያየው]” እንዴት ነው? ከሚያዩት ውስጥስ እነማን ይገኙበታል?
6 ይህን “መምጣት” ሐዋርያው ዮሐንስም በራእይ 1:7 ላይ “እነሆ፣ ከደመና ጋር ይመጣል” በማለት ገልጾታል። እነዚህ ጠላቶች ኢየሱስን በሥጋዊ ዓይናቸው አያዩትም፤ ምክንያቱም “ከደመና ጋር” መምጣቱ በማይታይ ሁኔታ መጥቶ የቅጣት ፍርዱን እንደሚፈጽም ያመለክታል። ተራ የሆኑ ሰዎች የኢየሱስን ሰማያዊ ክብር በሥጋዊ ዓይናቸው ቢመለከቱ ልክ ሳውል ወደ ደማስቆ በሚሄድበት ጊዜ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ በብርሃን ነጸብራቅ ታይቶት እንደታወረ ሁሉ እነሱም ይታወራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 9:3-8፤ 22:6-11
7 የራእይ መጽሐፍ በመቀጠል “ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፣ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ” ይላል። ይህ ማለት በምድር ላይ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች በጥፋቱ ጊዜ ኢየሱስ የይሖዋ ቅጣት አስፈጻሚ በመሆን በላያቸው ላይ በታላቅ ኃይልና ግርማ እንደመጣባቸው ያስተውላሉ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች “የወጉት” የተባሉት ለምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ የሚያሳዩት መራራ ጥላቻ የኢየሱስ አሳዳጆች ካሳዩት ጥላቻ ያልተለየ በመሆኑ ነው። በእርግጥም “ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ።”
8. ኢየሱስና ጳውሎስ ድንገተኛ ጥፋትን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ተናግረዋል?
8 ይህ የይሖዋ የበቀል ቀን የሚመጣው እንዴት ነው? ኢየሱስ በሉቃስ ምዕራፍ 21 በተመዘገበው ትንቢቱ ላይ ከ1914 ወዲህ ላለው መገኘቱ ምልክት የሚሆኑትን አስፈሪ ሁኔታዎች ገልጿል። ከዚያም በቁጥር 34 እና 35 ላይ ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።” አዎ፤ ይህ የይሖዋ የበቀል ቀን የሚመጣው በድንገት ሳይታሰብ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በ1 ተሰሎንቄ 5:2, 3 ላይ እንዲህ በማለት አረጋግጧል፦ “የጌታ [የይሖዋ አዓት] ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ . . . ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ . . . በድንገት ይመጣባቸዋል።” መንግሥታት በአሁኑ ጊዜም እንኳን ስለ ሰላምና ደኅንነት መናገርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ችግር ያለባቸውን ቦታዎች በወታደራዊ ኃይል አማካኝነት እንዲቆጣጠር ለማጠናከር ሐሳብ እያቀረቡ ነው።
9. ‘ብርሃን የሚበራላቸው’ ለእነማን ነው?
9 ሐዋርያው በቁጥር 4 እና 5 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “እናንተ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፣ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም።” የብርሃን ልጆች ስለሆንን አዎ፤ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ለማግኘት ለሚናፍቁ ሁሉ ብርሃን አብሪዎች ስለሆንን በጣም እንደሰታለን። መዝሙር 97:10, 11 “እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር [ይሖዋን አዓት] የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፣ ከኀጥአንም እጅ ያድናቸዋል። ብርሃን ለጻድቃን፣ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።”
የነገሮች ቅደም ተከተል
10. ስለ አምላክ የበቀል ቀን ምን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መቀበል ይኖርብናል? (ራእይ 16:15)
10 ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ የሚፈጸሙት ነገሮች ቅደም ተከተል ምን ይሆናል? ራእይ ምዕራፍ 16ን እናውጣ። ከቁጥር 13 እስከ 16 ላይ እንደተገለጸው እርኩሳን አጋንንታዊ መናፍስት የመላውን ምድር ብሔራት ሁሉን ወደሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን ወደ ሐርማጌዶን ይሰበስቧቸዋል። የበቀሉ ቀን አመጣጥ እንደ ሌባ መሆኑ አሁንም በድጋሚ ተገልጿል። ንቁ ሆነን እንድንኖርና መዳን የሚገባን ሰዎች መሆናችንን የሚያሳየውን መንፈሳዊ ልብስ ለብሰን እንድንቆይ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። የምድር ሕዝቦች በሙሉና አንድ ሌላ አካል ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ጊዜ ደርሷል። ይህች ሌላ አካል ማን ትሆን?
11. በራእይ 17:5 ላይ የተገለጸችው ሴት ማንነቷን የምታሳውቀው እንዴት ነው?
11 ራስዋን ትልቅ ለማድረግ የሞከረች ምሳሌያዊት ሴት ነች። ይህቺ ሴት በራእይ 17:5 ላይ ምሥጢር በሆነ ስም “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት” በመባል ተገልጻለች። አሁን ግን ለይሖዋ ምስክሮች ምሥጢር አይደለችም። የሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች ዋነኛ ክፍል የሆኑባት የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት መሆኗ በግልጽ ታይቷል። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ገብታ መዘባረቋ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በማሳደድ “በቅዱሳን ደም መስከሯ” እና በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች ብቻ የተገደሉትን ከመቶ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ጨምሮ “በምድር ሁሉ ለታረዱት ሰዎች ደም” በኃላፊነት የምትጠየቅ መሆኗ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ አድርጓታል።—ራእይ 17:2, 6፤ 18:24
12. የሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች የሚወገዙት ለምንድን ነው?
12 ከሁሉ የከፋው ደግሞ የሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች በግብዝነት እንወክለዋለን በሚሉት አምላክ ስም ላይ ስድብና ነቀፌታ ማምጣታቸው ነው። ንጹሕ በሆነው የአምላክ ቃል ምትክ ባቢሎናዊና ግሪካዊ ፍልስፍናዎችን አስተምረዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረኑ ልቅ ምግባሮችን በመደገፍና በመፍቀድ ብሔራት ሁሉ በሥነ ምግባር ዕድፍ እንዲበከሉ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በመካከላቸው የሚገኙ ስግብግብ ሸቃጮች በያዕቆብ 5:1, 5 ላይ በሚገኙት በሚቀጥሉት ቃላት እንደሚከተለው ተወግዘዋል፦ “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፣ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል።”
ታላቂቱ ባቢሎን ትወድማለች!
13. ታላቁ መከራ የሚጀምረው እንዴት ነው? በራእይ 18:4, 5 ላይ አጥብቆ የተገለጸው ምን አስቸኳይ ጉዳይ ነው?
13 ታላቁ መከራ የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የይሖዋን ፍርድ በማስፈጸም ነው። ራእይ 17:15-18 አምላክ ታላቂቱ ባቢሎንን ለማጥፋት “አሥሩን ቀንዶች” ማለትም ሕብረ ብሔራዊ በሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “አውሬ” ውስጥ የሚገኙትን ጠንካራ ኃይሎች ለማነሳሳት ያለውን “አሳብ” ጉልህ በሆነ መንገድ ይገልጻል። “ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል። እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ . . . በልባቸው አግብቶአልና።” በራእይ 18:4, 5 ላይ አንድ ሰማያዊ ድምፅ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ” የሚለውን አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ ማሰማቱ አያስደንቅም። አሁንም ጊዜው ከማለቁ በፊት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያላችሁን ማንኛውንም ግንኙነት አቋርጡ! የሚለው ጥሪ ማስተጋባቱን ይቀጥላል።
14. በታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት የሚያለቅሱት እነማን ናቸው? ለምንስ?
14 የታላቂቱ ባቢሎንን ውድመት ዓለም እንዴት ይመለከተዋል? ምግባረ ብልሹ የሆኑ ፖለቲከኞች ይኸውም “የምድር ነገሥታት” ለብዙ መቶ ዘመናት ከእርስዋ ጋር በነበራቸው መንፈሳዊ ግልሙትና ይደሰቱ ስለነበር ከሩቅ ቆመው ያዝኑላታል። በተጨማሪም የሚያለቅሱላትና የሚያዝኑላት ስግብግብ የሆኑ የንግድ ሰዎች ማለትም በእርሷ ባለ ጠጎች የሆኑት ታላላቅ “የምድር ነጋዴዎች” ናቸው። እነዚህም ከሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፦ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቊም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፣ ወዮላት፣ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና።” የተንቆጠቆጡት የክህነት አልባሳትና የዓለም ታላላቅ ካቴድራሎች ግርማ ለዘላለም ይጠፋል! (ራእይ 18:9-17) ይሁን እንጂ ለታላቂቱ ባቢሎን ሁሉም ሰው ያለቅስላታል?
15, 16. የአምላክ ሕዝቦች ምን የሚደሰቱበት ምክንያት ይኖራቸዋል?
15 ራእይ 18:20, 21 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ሰማይ ሆይ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፣ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፣ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን ወደ ባሕር እንደተጣለ የወፍጮ ድንጋይ “ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም።”
16 እንዴት ያለ አስደሳች ነገር ነው! ራእይ 19:1-8 ይህን ይገልጽልናል። አራት ጊዜ “ሃሌ ሉያ” የሚል ውዳሴ ከሰማይ ያስተጋባል። ሦስቱ የሃሌ ሉያ ውዳሴዎች የተሰሙት ይሖዋ በስመ ጥፉዋ አመንዝራ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የጥፋት ፍርድ ስለፈጸመባት ይሖዋን ለማወደስ ነበር። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጠፍታለች። ከአምላክ ዙፋን የወጣ ድምፅ “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱን የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፣ አምላካችንን አመስግኑ” ብሏል። በዚህ የውዳሴ መዝሙር ለመካፈል መቻላችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!
የበጉ ሠርግ
17. ራእይ 11:17ን እና 19:6ን በማነጻጸር ይሖዋ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምረው ከምን ሁለት ሁኔታዎች አንፃር ነው?
17 አራተኛው ሃሌ ሉያ አንድ ሌላ መልዕክት የሚያስተዋውቅ ነው። “ሁሉን የሚገዛ ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላካችን ነግሦአልናል።” ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ ዝማሬ በራእይ 11:17 ላይ ተሰምቶ አልነበረም? እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ያለህና የነበርክ፣ ሁሉን የምትገዛ [የምትችል አዓት] ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ሆይ፣ ትልቁን ኃይልህን ስለያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን።” ይሁን እንጂ ከራእይ 11:17 ዙሪያ ያለው ሐሳብ የሚናገረው ይሖዋ “አሕዛብን በሙሉ በብረት በትር” እንደ እረኛ ሆኖ የሚጠብቀውን መሲሐዊ መንግሥት በ1914 ስለ ማምጣቱ ነው። (ራእይ 12:5) ራእይ 19:6 ግን የሚገልጸው ከታላቂቱ ባቢሎን ውድመት ጋር ስለተያያዘ ጉዳይ ነው። ጋለሞታ መሰል የሆነ ሃይማኖት በመወገዱ የይሖዋ አምላክነት ለዘላለም ይረጋገጣል። ከዚያ በኋላ የይሖዋ ሉዓላዊነትና ንግሥና ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሰፍናል!
18. የታላቂቱ ባቢሎን መወገድ ለምን አስደሳች ማስታወቂያ ነው መንገድ የሚከፍተው?
18 በዚህ ምክንያት የሚከተለው የደስታ ማስታወቂያ ሊነገር ይችላል፦ “የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራሷን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሴትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ [ለይሖዋ] እናቅርብ። ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቷታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።” (ራእይ 19:7, 8) በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ሰማያዊ ትንሣኤያቸውን የሚያገኙት መቼ እንደሆነ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው በበጉ በክርስቶስ ጋብቻ የሚካፈሉበት ጊዜ የደስታ ጊዜ እንደሚሆን ተረጋግጧል። በጋብቻው የሚካፈሉት ስመ ጥፉዋ ጋለሞታ ታላቂቱ ባቢሎን ስትዋረድ በአካል ተገኝተው ካዩ በኋላ ሲሆን ደግሞ ደስታቸው የበለጠ ይሆናል።
የሰይጣን ዓለም ይጠፋል
19. በራእይ 19:11-21 ላይ ምን ሌሎች ሁኔታዎች ተገልጸዋል?
19 በራእይ 6:2 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ነጭ ፈረስ አሁንም እንደገና ብቅ አለ። በራእይ 19:11 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “የተቀመጠበትም [ በነጩ ፈረስ ላይ] የታመነና እውነተኛ ይባላል፣ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም።” በዚህ መንገድ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ብሔራትን ለመቀጥቀጥና “ሁሉን የሚችለውን አምላክ ቁጣ ወይን መጥመቂያ” ለመርገጥ ወደፊት ይጋልባል። “የምድር ነገሥታትና ጭፍራዎቻቸው” በአርማጌዶን ጦርነት ተሰብስበው እርሱን ለመውጋት የሚያደርጉት ሙከራ ከንቱ ይሆናል። የነጩ ፈረስ ጋላቢ ፍጹም ድል ይቀዳጃል። ከሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ምንም የሚቀር ነገር አይኖርም።—ራእይ 19:12-21
20. ዲያብሎስ ራሱ ምን ይደርስበታል?
20 ይሁን እንጂ ዲያብሎስ ራሱስ ምን ይሆናል? በራእይ 20:1-6 ላይ ክርስቶስ ኢየሱስ “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ” እንደሆነና ከሰማይ እንደሚወርድ ተገልጿል። ታላቁን ዘንዶና የቀደመውን እባብ ሰይጣን ዲያብሎስን ይዞ ያስረዋል። በጥልቅ ውስጥም ጥሎ ይዘጋበትና ያትምበታል። ሰይጣን ቦታ ከለቀቀና ሰዎችን ሊያስት በማይችልበት ሁኔታ እንዲገታ ከተደረገ በኋላ የበጉና የሙሽራይቱ ክብራማ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል። ከዚያ በኋላ እንባና ሐዘን አይኖርም! አዳማዊው ሞት አይኖርም! ልቅሶ፣ ጩኸት፣ ሥቃይ አይኖርም! ‘የቀደሙት ነገሮች አልፈዋልና።’—ራእይ 21:4
21. የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት እየጠበቅን ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
21 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት እየተጠባበቅን ስለ አምላክ ፍቅራዊ የመንግሥት ተስፋዎች ለሌሎች በቅንዓት እንናገር። ከመከራ የምንገላገልበት ጊዜ ቀርቧል! ብርሃን የበራልን የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ልጆች በመሆን ወደፊት፣ ምን ጊዜም ወደፊት እንራመድ!
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንደቀረበ የሚያመለክተው ምንድን ነው?
◻ የይሖዋ የበቀል ቀን የሚመጣው እንዴት ነው?
◻ ‘ይሖዋን የሚወዱ’ ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የዓለም ሁኔታ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?
◻ ታላቁ መከራ ሲጀምር የነገሮች አፈጻጸም ቅደም ተከተል ምን ይሆናል?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ፍርዱን ለማስፈጸም ለዓይን በማይታይ ሁኔታ ‘ከደመናት ጋር ይመጣል’
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ የሐሰት ሃይማኖት፣ የሰይጣን ክፉ ሥርዓትና ሰይጣን ራሱ ግብዓተ መሬታቸው ይፈጸማል