ምዕራፍ ስምንት
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?
ይህ መንግሥት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው መቼ ነው?
1. አሁን የምንመረምረው የትኛውን የታወቀ ጸሎት ነው?
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ብዙዎች የጌታ ጸሎት ወይም አቡነ ዘበሰማያት ብለው የሚጠሩትን ጸሎት በሚገባ ያውቁታል። ሁለቱም መጠሪያዎች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ናሙና አድርጎ የሰጠውን የታወቀ ጸሎት የሚያመለክቱ ናቸው። ይህ ጸሎት ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሐሳቦችን የያዘ ሲሆን በዚህ ጸሎት ውስጥ የተገለጹትን የመጀመሪያዎቹን ሦስት ልመናዎች መመርመርህ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንድታገኝ ይረዳሃል።
2. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በጸሎታቸው ውስጥ እንዲጠቅሷቸው ካስተማራቸው ነገሮች መካከል ሦስቱ ምንድን ናቸው?
2 ኢየሱስ በዚህ የናሙና ጸሎት መግቢያ ላይ አድማጮቹን “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፤ እንዲሁ በምድር ትሁን’” ሲል አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9-13) እነዚህ ሦስት ልመናዎች ምን ትርጉም አላቸው?
3. ስለ አምላክ መንግሥት ልናውቀው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
3 ይሖዋ ስለተባለው የአምላክ ስም ቀደም ሲል ብዙ ተምረናል። በተጨማሪም ስለ አምላክ ፈቃድ ማለትም ለሰው ዘር እስካሁን ስላከናወናቸውና ወደፊት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች በተወሰነ ደረጃ ተምረናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን ምንን ማመልከቱ ነው? የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ይህ መንግሥት መምጣቱ የአምላክን ስም የሚያስቀድሰው እንዴት ነው? የዚህ መንግሥት መምጣት ከአምላክ ፈቃድ መፈጸም ጋር የሚያያዘውስ እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት ምንነት
4. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ንጉሡስ ማን ነው?
4 የአምላክ መንግሥት በይሖዋ አምላክ የተቋቋመ መስተዳድር ሲሆን በአምላክ የተሾመ ንጉሥ አለው። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ንጉሡ ኢየሱስ ከሰብዓዊ ገዥዎች ሁሉ የሚበልጥ ሲሆን “የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ጢሞቴዎስ 6:15) ከየትኛውም ሰብዓዊ ገዥ፣ ሌላው ቀርቶ በጣም የተሻለ ነው ከሚባለው ሰብዓዊ ገዥም እንኳ የላቀ መልካም ነገር ማከናወን የሚያስችል ኃይል አለው።
5. የአምላክ መንግሥት የሚገዛው የት ሆኖ ነው? የሚገዛውስ ምንን ነው?
5 የአምላክ መንግሥት የሚገዛው የት ሆኖ ነው? ለዚህ መልስ ለማግኘት በቅድሚያ ኢየሱስ የት ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ እንደተሰቀለና በኋላም ከሞት እንደተነሳ ቀደም ሲል ተምረሃል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ አረገ። (የሐዋርያት ሥራ 2:33) በመሆኑም የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በዚያ ማለትም በሰማይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰማያዊ መንግሥት’ በማለት የሚጠራው ለዚህ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:18) የአምላክ መንግሥት ያለው በሰማይ ቢሆንም ምድርን ይገዛል።—ራእይ 11:15
6, 7. ኢየሱስን ከሁሉ የላቀ ንጉሥ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
6 ኢየሱስን ከሁሉ የላቀ ንጉሥ የሚያደርገው ምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት የማይሞት መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ከሰብዓዊ ነገሥታት ጋር በማወዳደር “እርሱ ብቻ ኢመዋቲ [የማይሞት] ነው፤ ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል” ሲል ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 6:16) በመሆኑም ኢየሱስ የሚያከናውናቸው ጠቃሚ ነገሮች ሁሉ ዘላቂነት ይኖራቸዋል ማለት ነው። ለሕዝቡ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን እንደሚያከናውን ደግሞ የተረጋገጠ ነው።
7 ስለ ኢየሱስ የተነገረውን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተመልከት:- “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል።” (ኢሳይያስ 11:2-4) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ጻድቅና ርኅሩኅ ንጉሥ ሆኖ የምድርን ሕዝብ እንደሚገዛ ቃል የተገባ መሆኑን ያሳያሉ። እንዲህ ያለ ገዥ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ?
8. ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት እነማን ናቸው?
8 የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ያለው ሌላው እውነታ ደግሞ ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አለመሆኑ ነው። ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ ሌሎች ነገሥታት ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ብንጸና፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:12) አዎን፣ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስና በአምላክ የተመረጡ ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ። እንዲህ ያለ ልዩ መብት የሚያገኙት ሰዎች ስንት ናቸው?
9. ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት ስንት ናቸው? አምላክ እነዚህን ሰዎች መምረጥ የጀመረውስ መቼ ነው?
9 በዚህ መጽሐፍ ሰባተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው አንድ ራእይ ላይ “በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በጽዮን ተራራ [በሰማይ ባለው ንጉሣዊ ቦታው] ላይ ቆሞ” የተመለከተ ሲሆን “ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ።” እነዚህ 144,000 ሰዎች እነማን ናቸው? ዮሐንስ ራሱ “በጉ ወደ ሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ራእይ 14:1, 4) አዎን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ ተለይተው የተመረጡ ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ናቸው። ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ካገኙ በኋላ ከኢየሱስ ጋር “በምድር ላይ ይነግሣሉ።” (ራእይ 5:10) አምላክ የ144,000ዎቹን ቁጥር ለማሟላት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታማኝ ክርስቲያኖችን ሲመርጥ ቆይቷል።
10. ኢየሱስና 144,000ዎቹ የሰውን ዘር እንዲገዙ መደረጉ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስና 144,000ዎቹ የሰውን ዘር እንዲገዙ መደረጉ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ ሰው መሆንና መሠቃየት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር ‘በድካማችን የማይራራልን አይደለም፤ ነገር ግን እንደ እኛ የተፈተነ ነው፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም’ ብሏል። (ዕብራውያን 4:15፤ 5:8) ተባባሪ ገዥዎቹም ሰው ሆነው ባሳለፉት የሕይወት ዘመናቸው ሥቃይና መከራ ደርሶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የነበሩ ሲሆን የተለያዩ ዓይነት በሽታዎችን ለመቋቋም ተገድደዋል። በእርግጥም የሰው ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በሚገባ ይረዳሉ!
የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?
11. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ፈቃድ በተመለከተ ምን ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል?
11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ ባስተማረበት ወቅት የአምላክ ፈቃድ ‘በምድርም እንዲሆን’ መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። አምላክ ያለው በሰማይ ሲሆን ታማኝ የሆኑት መላእክት ምንጊዜም ፈቃዱን በሰማይ ሲፈጽሙ ኖረዋል። ይሁን እንጂ በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው አንድ ክፉ መልአክ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉን በመተው አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ አደረጋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ በመባል ስለሚታወቀው ስለዚህ ክፉ መልአክ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ ምዕራፍ 10 ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ እናገኛለን። ሰይጣንና እሱን ለመከተል የመረጡ መላእክት የነበሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ማለትም አጋንንት ለተወሰነ ጊዜ በሰማይ እንዲቆዩ ተፈቅዶላቸው ነበር። በመሆኑም በዚያን ጊዜ በሰማይ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ የነበሩት ሁሉም አይደሉም። የአምላክ መንግሥት መግዛት ሲጀምር ግን ይህ ሁኔታ ይለወጣል። የተሾመው አዲሱ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ጦርነት ይከፍታል።—ራእይ 12:7-9
12. በራእይ 12:10 ላይ ምን ሁለት ዋና ዋና ክንውኖች ተገልጸዋል?
12 የሚከተሉት ትንቢታዊ ቃላት የሚፈጸመውን ሁኔታ ይገልጻሉ:- “ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና መንግሥት፣ የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቶአል። ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ [ሰይጣን] ተጥሎአልና።” (ራእይ 12:10) በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ክንውኖች እንደተገለጹ አስተውለሃል? አንደኛ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት መግዛት ይጀምራል። ሁለተኛ ደግሞ ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር ይጣላል።
13. ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ ምን ውጤት አስገኝቷል?
13 ወደፊት እንደምንመለከተው እነዚህ ሁለት ክንውኖች ተፈጽመዋል። ታዲያ ምን ውጤት አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ የተፈጸመውን ሁኔታ ሲገልጽ “ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣ በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ” ይላል። (ራእይ 12:12) አዎን፣ ታማኝ የሆኑት መላእክት ሰይጣንና አጋንንቱ በመባረራቸውና በሰማይ ያለው ፍጡር ሁሉ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ በመሆኑ ይደሰታሉ። በሰማይ የተሟላና የማይደፈርስ ሰላምና ስምምነት ሰፍኗል። የአምላክ ፈቃድ በሰማይ ተፈጽሟል።
14. ሰይጣን ወደ ምድር መጣሉ ምን ሁኔታ አስከትሏል?
14 ስለ ምድርስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል” ሲል ይገልጻል። (ራእይ 12:12) ሰይጣን ከሰማይ ስለተባረረና የቀረው ጊዜ ጥቂት እንደሆነ ስላወቀ ተቆጥቷል። በቁጣ ተሞልቶ በምድር ላይ መከራ ወይም ‘ወዮታ’ አምጥቷል። ይህን ‘ወዮታ’ በተመለከተ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን። ይሁንና ይህ ሁኔታ እያለ የአምላክ መንግሥት የይሖዋን ፈቃድ በምድር ላይ መፈጸም የሚችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን።
15. አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ ምንድን ነው?
15 አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ አስታውስ። ምዕራፍ 3 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተምረህ ነበር። አምላክ በኤደን ውስጥ እንደገለጸው ለዚህች ምድር ያለው ፈቃድ ገነት እንድትሆን እንዲሁም በማይሞቱና ጻድቃን በሆኑ የሰው ዘሮች እንድትሞላ ነው። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ ስላደረገ አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ የሚፈጸምበት ጊዜ ሊዘገይ ችሏል፤ ሆኖም የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። ይሖዋ አሁንም ‘ጻድቃን ምድርን እንዲወርሱና በእርሷም ለዘላለም እንዲኖሩ’ ለማድረግ ዓላማ አለው። (መዝሙር 37:29) የአምላክ መንግሥት ደግሞ ይህን ዓላማ ዳር ያደርሳል። በምን መንገድ?
16, 17. ዳንኤል 2:44 ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
16 ዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ተመልከት። እንዲህ ይላል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ይህ ትንቢት ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
17 በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ መንግሥት “በነዚያ ነገሥታት ዘመን” ወይም ሌሎቹ ሰብዓዊ መንግሥታት ባሉበት ዘመን እንደሚቋቋም ይገልጽልናል። በሁለተኛ ደረጃ መንግሥቱ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ያስገነዝበናል። በሌላ መንግሥት ድል የማይነሳና የማይተካ ይሆናል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ውጊያ እንደሚኖር ይጠቁመናል። የአምላክ መንግሥት በውጊያው ድል ይቀዳጃል። በመጨረሻም የሰውን ዘር የሚገዛ ብቸኛ መስተዳድር ይሆናል። ከዚያ በኋላ የሰው ልጆች አይተውት በማያውቁት ከሁሉ የተሻለ አገዛዝ ሥር ይኖራሉ።
18. በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ውጊያ ምን በመባል ይታወቃል?
18 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ስለሚደረገው የመጨረሻ ጦርነት ብዙ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ክፉ መናፍስት ‘የዓለምን ነገሥታት’ ለማሳት የውሸት ወሬ እንደሚያሰራጩ ያስተምራል። ዓላማቸው ምንድን ነው? ‘ነገሥታቱን ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚሆነው ጦርነት ለመሰብሰብ’ ነው። የምድር ነገሥታት “በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ” ይሰበሰባሉ። (ራእይ 16:14, 16) በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ላይ በተገለጸው ሐሳብ መሠረት በሰብዓዊ መንግሥታትና በአምላክ መንግሥት መካከል የሚካሄደው የመጨረሻው ውጊያ የሐርማጌዶን ወይም የአርማጌዶን ጦርነት በመባል ይታወቃል።
19, 20. የአምላክ ፈቃድ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ እንዳይፈጸም ያገደው ነገር ምንድን ነው?
19 የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን አማካኝነት ምን ነገር ያከናውናል? አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ በድጋሚ አስታውስ። ይሖዋ አምላክ ምድር በገነት ውስጥ ሆነው በሚያገለግሉት ጻድቃንና ፍጹማን የሆኑ የሰው ዘሮች እንድትሞላ ለማድረግ ዓላማ አለው። ይህ ዓላማ አሁን እንዳይፈጸም ያገደው ነገር ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ኃጢአተኞች በመሆናችን እንታመማለን እንዲሁም እንሞታለን። ይሁን እንጂ ለዘላለም መኖር እንድንችል ኢየሱስ እንደሞተልን ምዕራፍ 5 ላይ ተምረናል። በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል” የሚሉትን ቃላት ሳታስታውስ አትቀርም።—ዮሐንስ 3:16
20 ሌላው ችግር ደግሞ ብዙ ሰዎች ክፉ ነገሮች የሚፈጽሙ መሆናቸው ነው። ይዋሻሉ፣ ያጭበረብራሉ እንዲሁም የጾታ ብልግና ይፈጽማሉ። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አይፈልጉም። ክፉ ነገሮችን የሚፈጽሙ ሰዎች በአምላክ የአርማጌዶን ጦርነት ይጠፋሉ። (መዝሙር 37:10) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ያልተፈጸመበት ሌላው ምክንያት መንግሥታት ይህን የአምላክ ፈቃድ እንዲያደርጉ ሰዎችን የሚያበረታቱ አለመሆናቸው ነው። ብዙዎቹ መንግሥታት በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የተሳናቸው ከመሆኑም በላይ ጨካኞች አሊያም ብልሹ ሥነ ምግባር ያላቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ሰውን መግዛቱ ጉዳት’ እንዳስከተለ በግልጽ ይናገራል።—መክብብ 8:9
21. መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት ነው?
21 ከአርማጌዶን በኋላ የሰው ዘር በአንድ መስተዳድር ይኸውም በአምላክ መንግሥት ሥር ብቻ ይሆናል። ይህ መንግሥት የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽም ከመሆኑም በላይ አስደሳች በረከቶች ያመጣል። ለምሳሌ ያህል ሰይጣንንና አጋንንቱን ያስወግዳል። (ራእይ 20:1-3) የኢየሱስ መሥዋዕት ያለው ኃይል ጥቅም ላይ ስለሚውል ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከሕመምና ከሞት ነፃ ይሆናሉ። ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለዘላለም ይኖራሉ። (ራእይ 22:1-3) ምድር ገነት ትሆናለች። በዚህ መንገድ መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸምና የአምላክ ስም እንዲቀደስ ያደርጋል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጨረሻ በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር በሕይወት ያለ ሁሉ የይሖዋን ስም ያከብራል ማለት ነው።
የአምላክ መንግሥት እርምጃ የሚወስደው መቼ ነው?
22. የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜም ሆነ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ እንዳልመጣ እንዴት እናውቃለን?
22 ኢየሱስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምራቸው መንግሥቱ በዚያን ጊዜ እንዳልመጣ ግልጽ ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግስ መንግሥቱ መጥቷል? አልመጣም፤ ምክንያቱም ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “እግዚአብሔር ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው” የሚለው በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘው ትንቢት በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32-35፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ስለዚህ ኢየሱስ የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ አስፈልጎት ነበር።
በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ ይሆናል
23. (ሀ) የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
23 ኢየሱስ ሲጠባበቅ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ዘመን ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ ጊዜ የሚያበቃው በ1914 እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ማስተዋል ችለው ነበር። (ይህን ጊዜ በተመለከተ ከገጽ 215-218 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።) በ1914 በዓለም ላይ መታየት የጀመሩት ክስተቶች እነዚህ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ክርስቶስ በ1914 ንጉሥ እንደሆነና የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መግዛት እንደጀመረ ያመለክታል። በመሆኑም አሁን የምንኖረው ሰይጣን በቀረው “ጥቂት ዘመን” ውስጥ ነው። (ራእይ 12:12፤ መዝሙር 110:2) በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ለማድረግ እርምጃ ይወስዳል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ይህ ትልቅ የምሥራች እንደሆነ ይሰማሃል? እውነት ነው ብለህስ ታምናለህ? የሚቀጥለው ምዕራፍ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል እነዚህን ነገሮች እንደሚያስተምር እንድታስተውል ይረዳሃል።