የጥናት ርዕስ 19
የራእይ መጽሐፍ፣ ዛሬ አንተን የሚመለከትህ እንዴት ነው?
“የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው።”—ራእይ 1:3
መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!
ማስተዋወቂያa
1-2. ለራእይ መጽሐፍ ትኩረት እንድንሰጥ የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?
አንድ ሰው የፎቶ አልበሙን እንድታይ ጋበዘህ እንበል። አልበሙን ገለጥ ገለጥ እያደረግህ ስታይ ብዙ የማታውቃቸው ሰዎች አየህ። አንደኛው ፎቶ ግን ትኩረትህን ሳበው፤ እዚያ ፎቶ ላይ አንተም አለህበት። ፎቶውን ትኩር ብለህ እያየህ የትና መቼ እንደተነሳ ለማስታወስ ትሞክራለህ። ፎቶው ላይ ያሉት ሌሎች ሰዎች እነማን እንደሆኑም ታስባለህ። ከሌሎቹ ፎቶዎች ይልቅ ይህ ፎቶ ለአንተ ልዩ ትርጉም አለው።
2 የራእይ መጽሐፍ ከዚህ ፎቶግራፍ ጋር ይመሳሰላል። እንዴት? ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛ፣ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈው ለእኛ ነው። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቁጥር እንዲህ ይለናል፦ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው።” (ራእይ 1:1) ስለዚህ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በአጠቃላይ ለዓለም ሕዝብ ሳይሆን ለእኛ ማለትም ራሳችንን ለወሰንን የአምላክ አገልጋዮች ነው። የአምላክ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በዚህ አስደናቂ መጽሐፍ ውስጥ ባሉት ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ የእኛም ድርሻ እንዳለበት ብናውቅ ልንገረም አይገባም። በሌላ አባባል፣ እኛም ፎቶው ላይ አለንበት።
3-4. የራእይ መጽሐፍ እንደሚናገረው ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው? ይህስ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
3 ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙበት ጊዜ ጋር የተያያዘ ነው። አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ “በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ” በማለት ጊዜውን ነግሮናል። (ራእይ 1:10) ሐዋርያው ዮሐንስ በ96 ዓ.ም. ይህን ሐሳብ በጻፈበት ወቅት ‘የጌታ ቀን’ ሊጀምር ገና ብዙ ዘመናት ይቀሩት ነበር። (ማቴ. 25:14, 19፤ ሉቃስ 19:12) ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው በ1914 ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት ይህ ቀን ጀመረ። ከዚህ ዓመት አንስቶ በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት የአምላክን ሕዝቦች የሚመለከቱ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀመሩ። አዎ፣ ዛሬ የምንኖረው ‘በጌታ ቀን’ ነው!
4 የምንኖረው በዚህ አስደናቂ ጊዜ ውስጥ ስለሆነ በራእይ 1:3 ላይ ለሚገኘው ፍቅራዊ ማሳሰቢያ የተለየ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። ማሳሰቢያው እንዲህ ይላል፦ “የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ናቸው፤ የተወሰነው ጊዜ ቀርቧልና።” አዎ፣ የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብለን ‘ማንበብ፣ መስማትና መጠበቅ’ ይኖርብናል። ለምሳሌ የትኞቹን የትንቢቱን ቃላት መጠበቅ ያስፈልገናል?
አምልኮህ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አረጋግጥ
5. አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጣችን አስፈላጊ እንደሆነ የራእይ መጽሐፍ የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 ከራእይ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ አንስቶ እንደምንረዳው ኢየሱስ በጉባኤው ውስጥ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል። (ራእይ 1:12-16, 20፤ 2:1) ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለሚገኙ ሰባት ጉባኤዎች የላከው መልእክት ይህን ያሳያል። በመልእክቶቹ ላይ፣ እነዚያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አምልኳቸው ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ደግሞም እነዚያ መልእክቶች ዛሬ ላሉ የአምላክ ሕዝቦችም ይሠራሉ። ታዲያ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? መሪያችን ክርስቶስ ኢየሱስ ስላለንበት መንፈሳዊ ሁኔታ በሚገባ ያውቃል። ኢየሱስ ይመራናል እንዲሁም ይጠብቀናል፤ ከእሱ እይታ የሚያመልጥ አንዳች ነገር የለም። የይሖዋን ሞገስ ሳናጣ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ያውቃል። ታዲያ ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ልንጠብቀው የሚገባ ምን መመሪያ ሰጥቷል?
6. (ሀ) ራእይ 2:3, 4 እንደሚጠቁመው ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤ በላከው መልእክት ላይ ምን መሠረታዊ ችግር አንስቷል? (ለ) ከዚህ የምናገኘው ትምህርትስ ምንድን ነው?
6 ራእይ 2:3, 4ን አንብብ። ለይሖዋ ያለንን የመጀመሪያ ፍቅር መተው የለብንም። ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤ የጻፈው መልእክት እንደሚያሳየው እነዚህ ክርስቲያኖች የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ጸንተዋል፤ እንዲሁም ሳይታክቱ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሁንና መጀመሪያ ላይ የነበራቸውን ፍቅር ትተው ነበር። ይህን ፍቅራቸውን መልሰው ማቀጣጠል ያስፈልጋቸው ነበር፤ አለዚያ አምልኳቸው ተቀባይነት አይኖረውም። በዛሬው ጊዜም መጽናታችን ብቻውን በቂ አይደለም። እንድንጸና የሚያነሳሳን ምክንያትም ትክክለኛ መሆን ይኖርበታል። አምላካችን ምን እናደርጋለን የሚለው ብቻ ሳይሆን ለምን እናደርጋለን የሚለውም ያሳስበዋል። አንድን ነገር ለማድረግ ለተነሳሳንበት ዝንባሌ ትኩረት ይሰጣል፤ ምክንያቱም እንድናመልከው የሚፈልገው ለእሱ ባለን ጥልቅ ፍቅርና አድናቆት ተነሳስተን ነው።—ምሳሌ 16:2፤ ማር. 12:29, 30
7. (ሀ) ራእይ 3:1-3 እንደሚያሳየው ኢየሱስ በሰርዴስ ክርስቲያኖች ላይ ምን ችግር አስተውሎ ነበር? (ለ) እኛስ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
7 ራእይ 3:1-3ን አንብብ። ምንጊዜም ንቁ መሆን ይኖርብናል። የሰርዴስ ጉባኤ ክርስቲያኖች የነበረባቸው ችግር ደግሞ የተለየ ነው። ቀደም ሲል በመንፈሳዊ ሥራ የተጠመዱ ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ለአምላክ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ቸልተኞች መሆን ጀምረው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “ንቃ” ብሏቸዋል። ታዲያ ይህ ለእኛ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት ይዟል? እውነት ነው፣ ይሖዋ ያከናወንነውን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም። (ዕብ. 6:10) ያም ቢሆን ቀደም ሲል በይሖዋ አገልግሎት ባከናወንነው ነገር ብቻ ረክተን ልንቀመጥ አይገባም። እርግጥ ነው፣ አሁን የአቅም ገደቦች ይኖሩብን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ‘በጌታ ሥራ’ በመጠመድ እስከ መጨረሻው ንቁ መሆን ያስፈልገናል።—1 ቆሮ. 15:58፤ ማቴ. 24:13፤ ማር. 13:33
8. የሎዶቅያ ክርስቲያኖች በራእይ 3:15-17 ላይ የተባሉት ነገር ለእኛ ምን ትምህርት ይዞልናል?
8 ራእይ 3:15-17ን አንብብ። አምልኳችንን በቅንዓትና በሙሉ ልብ ማከናወን አለብን። ኢየሱስ ለሎዶቅያ ጉባኤ በላከው መልእክት ላይ እነዚህ ክርስቲያኖች የነበረባቸውን የተለየ ችግር አንስቷል። ከአምልኳቸው ጋር በተያያዘ “ለብ” ያሉ ነበሩ። በግድ የለሽነታቸው የተነሳ ኢየሱስ “ጎስቋላ” እና “ምስኪን” እንደሆኑ ነግሯቸዋል። ለይሖዋና ለአምልኮው እንደ እሳት የሚነድ ቅንዓት ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። (ራእይ 3:19) ይህ ለእኛ ምን ትምህርት ይዞልናል? ቅንዓታችን በተወሰነ መጠንም ቢሆን ቀዝቅዞ ከሆነ ለመንፈሳዊ ሀብታችን ያለንን አድናቆት ማቀጣጠል አለብን። (ራእይ 3:18) የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት የምናደርገው ጥረት ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው አንፍቀድ፤ ይህ አካሄድ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁለተኛ ቦታ እንድንሰጥ ስለሚያደርገን ልንጠነቀቅ ይገባል።
9. ኢየሱስ ለጴርጋሞንና ለትያጥሮን ክርስቲያኖች የላከው መልእክት እንደሚያሳየው ከየትኛው አደጋ ልንጠነቀቅ ይገባል?
9 ከከሃዲዎች ትምህርት መራቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ በጴርጋሞን ጉባኤ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ክፍፍልና ኑፋቄ እንዲኖር በማድረጋቸው ወቅሷቸዋል። (ራእይ 2:14-16) በትያጥሮን ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ደግሞ ‘ከሰይጣን ጥልቅ ነገሮች’ በመራቃቸው አመስግኗቸዋል፤ እንዲሁም እውነትን ‘አጥብቀው እንዲይዙ’ አሳስቧቸዋል። (ራእይ 2:24-26) በዚህ ጉባኤ ያሉ በሐሰት ትምህርት የተታለሉ አንዳንድ ደካማ ክርስቲያኖች ንስሐ መግባት ያስፈልጋቸው ነበር። በዛሬው ጊዜስ? ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ከሚጻረር ማንኛውም ትምህርት መራቅ አለብን። ከሃዲዎች “ለአምላክ ያደሩ መስለው” ይታዩ ይሆናል፤ “በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ።” (2 ጢሞ. 3:5) የአምላክን ቃል በትጋት የምናጠና ከሆነ የሐሰት ትምህርቶችን መለየትና ከዚያ መራቅ ቀላል ይሆንልናል።—2 ጢሞ. 3:14-17፤ ይሁዳ 3, 4
10. ኢየሱስ ለጴርጋሞንና ለትያጥሮን ጉባኤዎች ከተናገረው ነገር ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን?
10 ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም የለብንም፤ እንዲህ ዓይነቱን ምግባር በቸልታ ማለፍም ሆነ ማበረታታትም አይኖርብንም። የጴርጋሞንና የትያጥሮን ክርስቲያኖች የነበረባቸው ሌላም ችግር ነበር። ኢየሱስ በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ አንዳንዶች የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸማቸው አውግዟቸዋል። (ራእይ 2:14, 20) እኛ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ብናገለግልም ወይም የተለያዩ የአገልግሎት መብቶች ቢኖሩንም እንኳ የሥነ ምግባር ብልግና ፈጽመን ይሖዋ ጉዳዩን በቸልታ እንደሚያልፈው ልንጠብቅ አይገባም። (1 ሳሙ. 15:22፤ 1 ጴጥ. 2:16) በዙሪያችን ያለው ዓለም በሥነ ምግባር እያዘቀጠ ቢሄድም እንኳ እኛ ምንጊዜም የእሱን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንድናከብር ይጠብቅብናል።—ኤፌ. 6:11-13
11. እስካሁን ምን ትምህርት አግኝተናል? (“ምን ትምህርት ይዞልናል?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
11 እስካሁን ያገኘነውን ትምህርት እስቲ እናጠቃልለው፦ የምናቀርበው አምልኮ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጣችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አይተናል። አምልኳችን ተቀባይነት እንዲያጣ የሚያደርግ ነገር እያደረግን ከሆነ ሁኔታውን ለማስተካከል በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን። (ራእይ 2:5, 16፤ 3:3, 16) ኢየሱስ ለጉባኤዎቹ በላካቸው መልእክቶች ላይ ያጎላው ሌላም ነገር አለ። ምን ይሆን?
ስደትን በጽናት ለመቋቋም ዝግጁ ሁን
12. ኢየሱስ ለሰምርኔስና ለፊላደልፊያ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ ዛሬ ያለነውን ክርስቲያኖች ትኩረት የሚስብ ምን ነገር ተናግሯል? (ራእይ 2:10)
12 አሁን ደግሞ ኢየሱስ ለሰምርኔስና ለፊላደልፊያ ጉባኤዎች የላከውን መልእክት እንመልከት። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ስደትን መፍራት እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል፤ ምክንያቱም ለታማኝነታቸው ወሮታ ይከፈላቸዋል። (ራእይ 2:10ን አንብብ፤ 3:10) እኛ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ስደት እንደሚደርስብን መጠበቅና በጽናት ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለብን። (ማቴ. 24:9, 13፤ 2 ቆሮ. 12:10) ይህ አስፈላጊ ማሳሰቢያ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
13-14. በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ የተጠቀሰው ክንውን የአምላክን ሕዝቦች የሚነካው እንዴት ነው?
13 የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ‘በጌታ ቀን’ ማለትም በዘመናችን ስደት እንደሚደርስባቸው መረጃ ይሰጠናል። ራእይ ምዕራፍ 12 የአምላክ መንግሥት መወለዱን ተከትሎ በሰማይ ጦርነት እንደተነሳ ይነግረናል። ሚካኤል ማለትም ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስና ሠራዊቱ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ተዋጉ። (ራእይ 12:7, 8) በውጤቱም እነዚያ የአምላክ ጠላቶች ተሸንፈው ወደ ምድር ተጣሉ፤ ይህም በምድርና በነዋሪዎቿ ላይ ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ አስከትሏል። (ራእይ 12:9, 12) ሆኖም ይህ ክንውን የአምላክን ሕዝቦች የሚነካው እንዴት ነው?
14 በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ቀጥሎ ሰይጣን ምን እንዳደረገ ይነግረናል። ወደ ሰማይ የሚሄድበት መንገድ እንደተዘጋ ስላወቀ ቁጣውን ምድር ላይ ወዳሉት ቅቡዓን ቀሪዎች አዞረ፤ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ የአምላክ መንግሥት ወኪሎች ሲሆኑ “ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ” ተሰጥቷቸዋል። (ራእይ 12:17፤ 2 ቆሮ. 5:20፤ ኤፌ. 6:19, 20) ታዲያ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
15. በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት ‘ሁለት ምሥክሮች’ እነማንን ይወክላሉ? ምንስ አጋጥሟቸዋል?
15 ሰይጣን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በሚመሩት ቅቡዓን ወንድሞች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገደሉት ‘ሁለቱ ምሥክሮች’ ሥራውን የሚመሩትን እነዚህን ወንድሞች ያመለክታሉ።b (ራእይ 11:3, 7-11) በ1918 ኃላፊነት ያላቸው ስምንት ወንድሞች በሐሰት ተከሰሱ፤ እያንዳንዳቸውም የረጅም ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሥራ ‘የሞተ’ ያህል ነበር።
16. በ1919 ምን ያልተጠበቀ ነገር ተከናወነ? ሆኖም ሰይጣን ከዚያ ጊዜ አንስቶ ምን ሲያደርግ ቆይቷል?
16 በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ትንቢት ‘ሁለቱ ምሥክሮች’ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ዳግም ሕያው እንደሚሆኑም ይናገራል። በትንቢቱ ፍጻሜ መሠረት ወንድሞች ከታሰሩ ዓመት እንኳ ሳይሞላ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተፈጸመ። በ1919 መጀመሪያ ላይ እነዚያ ቅቡዓን ወንድሞች ከእስር ተፈቱ፤ በኋላም ከተወነጀሉበት ክስ ነፃ ተደረጉ። ወንድሞች ወዲያውኑ ወደ ሥራ ገቡ፤ ወደ መንግሥቱ ሥራ። ሆኖም ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት በዚህ አላቆመም። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰይጣን በሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ላይ የስደት “ወንዝ” እየለቀቀ ነው። (ራእይ 12:15) በእርግጥም እያንዳንዳችን “ጽናትና እምነት ማሳየት [የሚያስፈልገን] እዚህ ላይ ነው።”—ራእይ 13:10
ይሖዋ በሰጠን ሥራ የቻልከውን ያህል ተሳትፎ አድርግ
17. የአምላክ ሕዝቦች የሰይጣን ጥቃት ዒላማ ቢሆኑም ምን ያልተጠበቀ እርዳታ አግኝተዋል?
17 ራእይ ምዕራፍ 12 ቀጥሎ እንደሚጠቁመው የአምላክ ሕዝቦች ካልተጠበቀ ምንጭ የተወሰነ እርዳታ ያገኛሉ። ጥቅሱ እንደሚለው “ምድሪቱ” የተለቀቀውን የስደት “ወንዝ” ትውጣለች። (ራእይ 12:16) የሆነውም ይህ ነው። በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚገኙ የተሻለ ምክንያታዊነት ያላቸው ተቋማት ለምሳሌ አንዳንድ የፍትሕ አካላት፣ ለአምላክ ሕዝቦች የደረሱላቸው ጊዜ አለ። የይሖዋ አገልጋዮች በተደጋጋሚ ያገኟቸው የፍርድ ቤት ድሎች የተወሰነ ነፃነት እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል። ይህን ነፃነታቸውን የተጠቀሙበት እንዴት ነው? ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በሚገባ በመጠቀም ነው። (1 ቆሮ. 16:9) ይህ ሥራ ምንን ይጨምራል?
18. በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት የተሰጠን ዋነኛ ሥራ ምንድን ነው?
18 የአምላክ ሕዝቦች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች’ በመላው ምድር እንደሚሰብኩ ኢየሱስ ተንብዮአል። (ማቴ. 24:14) በራእይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው አንድ መልአክ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች [ይዟል]።” በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራ ሲያከናውኑ ከአንድ መልአክ ወይም ከመላእክት ቡድን ድጋፍ ያገኛሉ።—ራእይ 14:6
19. ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ሌላ ምን ዓይነት መልእክት መስበክ አለባቸው?
19 የአምላክ ሕዝቦች እንዲያውጁ የተነገራቸው መልእክት የመንግሥቱ ምሥራች ብቻ አይደለም። በራእይ ምዕራፍ 8 እስከ 10 ላይ መላእክት እንደሚያከናውኑት የተገለጸ ሥራ አለ፤ የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራም መደገፍ አለባቸው። እነዚህ መላእክት የአምላክን መንግሥት በማይቀበሉት ሁሉ ላይ ተከታታይ ወዮታዎችን አስተላልፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ‘በበረዶና በእሳት’ የተመሰለ የፍርድ መልእክት ሲያውጁ ቆይተዋል፤ ይህ መልእክት አምላክ ክፉ በሆነው የሰይጣን ዓለም የተለያዩ ክፍሎች ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ የሚገልጽ ነው። (ራእይ 8:7, 13) ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ አድርገው ከይሖዋ የቁጣ ቀን እንዲተርፉ መጨረሻው በጣም መቅረቡን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። (ሶፎ. 2:2, 3) ሆኖም ይህ መልእክት በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ አይደለም። መልእክቱን ማወጅ ድፍረት ይጠይቅብናል። በታላቁ መከራ ወቅት የምናውጀው የመጨረሻ የፍርድ መልእክት ደግሞ ይበልጥ የሚያም ይሆናል።—ራእይ 16:21
የትንቢቱን ቃል ጠብቅ
20. በቀጣዮቹ ሁለት ርዕሶች ላይ ምን እንመለከታለን?
20 አዎ፣ “የዚህን ትንቢት ቃል” መጠበቅ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም በራእይ መጽሐፍ ላይ በምናነባቸው ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ እኛም አለንበት። (ራእይ 1:3) ሆኖም የሚደርስብንን ስደት በጽናት ተቋቁመን እነዚህን መልእክቶች በድፍረት ማወጃችንን ለመቀጠል ምን ይረዳናል? ሁለት ነገሮች ብርታት ይሰጡናል፦ አንደኛው፣ የራእይ መጽሐፍ ስለ አምላክ ጠላቶች የሚናገረው ነገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በታማኝነት ከጸናን ወደፊት የምናገኛቸው በረከቶች ናቸው። በቀጣዮቹ ሁለት ርዕሶች ላይ እነዚህን ሐሳቦች እንመለከታለን።
መዝሙር 32 ከይሖዋ ጎን ቁም!
a የምንኖረው አስደናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው! በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው። እነዚህ ትንቢቶች እኛን የሚመለከቱን እንዴት ነው? በዚህና በቀጣዮቹ ሁለት ርዕሶች ላይ በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ነጥቦችን እንመረምራለን። በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጻፉትን ነገሮች መታዘዛችን በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እናያለን።
b በኅዳር 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።