የአፖካሊፕስ ‘ብስራት’
“በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብና ለነገድ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ ለማብሠር ዘላለማዊውን የምሥራች ቃል የያዘ ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበርር አየሁ።”—ራእይ 14:6 የ1980 ትርጉም
1. የይሖዋ ምሥክሮች የአፖካሊፕስ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያምኑ ቢሆንም “አፖካሊፕሳዊ ቡድን” አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንዶች እንደሚወነጅሏቸው “አፖካሊፕሳዊ ቡድን” ወይም “መዓት ይመጣል የሚል ኑፋቄ” አይደሉም። ይሁን እንጂ አፖካሊፕስ ወይም የራእይ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል እንደሆነ ያምናሉ። የራእይ መጽሐፍ በክፉዎች ላይ ስለሚመጣው ፍርድ የሚናገር መልእክት እንዳለው አይካድም። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች ለሕዝብ የሚሰጡት ምሥክርነት በዋነኛነት ያተኮረው አፖካሊፕስን ወይም ራእይን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጹት ግሩም ተስፋዎች ላይ ነው። በመሆኑም በዚያ ውስጥ በሚገኘው ትንቢታዊ ቃል ላይ አንዳች አይጨምሩም አንዳችም አይቀንሱም።—ራእይ 22:18, 19
ብስራት ነጋሪዎች
2. የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ በስብከት ሥራቸው የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
2 ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት ሕዝባዊ አገልግሎት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሆኖ የሚጠቀሰው የሚከተለው ኢየሱስ የተናገረው ነገር ነው:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል [“ምሥራች፣” NW] በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ታዲያ ይህ “የመንግሥት ምሥራች” ምንድን ነው? ብዙ ምሥክሮች ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጡት ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛትና ስለ ንጉሣዊ መስተዳድሩ እንዲሁም ሞት፣ ሐዘንና ስቃይ ‘ስለማይኖርበት’ የሰው ዘር ማኅበረሰብ የሚናገሩትን የራእይ ምዕራፍ 20 እና 21 ቁጥሮች በመጥቀስ ነው።—ራእይ 20:6፤ 21:1, 4
3. የይሖዋ ምሥክሮች ሕዝባዊ አገልግሎት ከምን ተልዕኮ ጋር ተመሳሳይነት አለው?
3 የይሖዋ ምሥክሮች የዚህ ብስራት ነጋሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ተልዕኮው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በምሳሌያዊ መንገድ የተገለጸው ሰማያዊ መልእክተኛ ቃል አቀባዮች ናቸው ለማለት ይቻላል። “በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብና ለነገድ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ ለማብሠር ዘላለማዊውን የምሥራች ቃል የያዘ ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበርር አየሁ።” (ራእይ 14:6 የ1980 ትርጉም) ይህ ‘ዘላለማዊ ምሥራች’ “የዓለም መንግሥት [አገዛዝ] ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ” ሆናለች፤ ‘ምድርን የሚያጠፏትንም ያጠፋ ዘንድ የቀጠረው ዘመን’ መጥቷል የሚለውን አዋጅ ይጨምራል። (ራእይ 11:15, 17, 18) ይህ በእርግጥ ምሥራች አይደለምን?
የራእይ መጽሐፍ ምን ይዞልናል?
4. (ሀ) በራእይ ምዕራፍ አንድ ላይ የተገለጸው መሠረታዊ እውነት ምንድን ነው? (ለ) ከሚነገረው ምሥራች ለመጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
4 የራእይ መጽሐፍ የመክፈቻ ምዕራፍ ይሖዋ ‘ያለና የነበረ የሚመጣም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ’ እንደሆነ ይገልጻል። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ‘የታመነ ምሥክር፣ የሙታን በኩር’ እንዲሁም ‘የምድር ነገሥታት ገዥ’ እንደሆነ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ‘እንደወደደንና በደሙም እንዳጠበን’ ይናገራል። (ራእይ 1:5, 8) በዚህ መልኩ የራእይ መጽሐፍ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ መሠረታዊ ስለሆነው ሕይወት ሰጭ እውነት ያብራራል። ‘በምድር የሚኖሩ’ የተባሉት ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት አምነው ካልተቀበሉ፣ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት ከሌላቸውና ይሖዋ ከሙታን እንዳስነሳው እንዲሁም ዛሬ በምድር ላይ አምላክ የሾመው ገዥ እርሱ መሆኑን የማያምኑ ከሆነ ከሚነገረው ምሥራች ተጠቃሚ አይሆኑም።—መዝሙር 2:6-8
5. በራእይ ምዕራፍ 2 እና 3 ላይ ኢየሱስ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል?
5 ቀጣዮቹ ሁለት ምዕራፎች ክርስቶስ ኢየሱስ በምድር ያሉት ደቀ መዛሙርቱ የተሰባሰቡባቸውን ጉባኤዎች በፍቅራዊ መንገድ የሚመራ ሰማያዊ የበላይ ተመልካች መሆኑን ይገልጻሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በትንሿ እስያ ለነበሩ የተመረጡ ሰባት ጉባኤዎች የተላከው ጥቅልል ዛሬም ጭምር የሚሠራ ማበረታቻና ጠበቅ ያለ ምክር ይዟል። ለጉባኤዎቹ የተላከው መልእክት በአብዛኛው የሚጀምረው ‘ሥራህን አውቃለሁ’ ወይም ‘መከራህን አውቃለሁ’ የሚሉትን በመሰሉ ቃላት ነው። (ራእይ 2:2, 9) አዎን፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ምን ነገር እየተከናወነ እንዳለ በትክክል ያውቅ ነበር። አንዳንዶቹን ስላሳዩት ፍቅርና እምነት፣ በአገልግሎቱ ስለመድከማቸው፣ ስለ ጽናታቸው እንዲሁም ለስሙና ለቃሉ ስላሳዩት ታማኝነት አመስግኗቸዋል። ሌሎችን ደግሞ ለይሖዋና ለልጁ የነበራቸው ፍቅር ስለቀዘቀዘ አሊያም ደግሞ ወደ ጾታ ብልግና፣ ጣዖት አምልኮ ወይም የክህደት ኑፋቄ በመመለሳቸው ወቅሷቸዋል።
6. በምዕራፍ 4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ራእይ ሰዎች ምን ነገር እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል?
6 ምዕራፍ 4 የይሖዋ አምላክን ሰማያዊ ዙፋን የሚመለከት አስገራሚ ራእይ ይዟል። ይሖዋ ያለው ክብር እንዲሁም እርሱ የሚጠቀምበት የሰማያዊ አገዛዝ መዋቅር ምን ሊመስል እንደሚችል ይጠቁመናል። በአጽናፈ ዓለሙ ማዕከላዊ ዙፋን ዙሪያ ባለው መንበራቸው ዘውድ ጭነው የተቀመጡት ገዥዎች በግንባራቸው ተደፍተው ለይሖዋ እየሰገዱ እንዲህ ይላሉ:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11
7. (ሀ) መልአኩ የምድር ነዋሪዎች ምን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል? (ለ) የማስተማር ሥራችን ጉልህ ገጽታ ምንድን ነው?
7 ይህ ዛሬ ላሉት ሰዎች የሚያስተላልፈው መልእክት አለ? አዎ አለ። በሺህ ዓመቱ መስተዳድር ሥር ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ‘በሰማይ መካከል የሚበርረው’ መልአክ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” ሲል የሚያሰማውን አዋጅ ማዳመጥ ይኖርባቸዋል። (ራእይ 14:6, 7) የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ዘመቻ ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ‘በምድር የሚኖሩ ሰዎች’ ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲያመልኩት፣ ፈጣሪነቱን አምነው እንዲቀበሉ እንዲሁም ጽድቅ ለተላበሰው ሉዓላዊነቱ ራሳቸውን እንዲያስገዙ መርዳት ነው።
ክብር ሊሰጠው የሚገባ በግ
8. (ሀ) በምዕራፍ 5 እና 6 ላይ ኢየሱስ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል? (ለ) ምሥራቹን የሚያዳምጡ ሁሉ ከዚህ ራእይ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
8 ቀጣዮቹ ምዕራፍ 5 እና 6 ኢየሱስ ክርስቶስ የሰባቱን ማኅተም ጥቅልል ይፈታ ዘንድ በሌላ አባባል በዘመናችን የሚከናወኑትን ነገሮች በምሳሌያዊ መግለጫ ያሳየን ዘንድ የተገባው በግ እንደሆነ ይገልጻሉ። (ከዮሐንስ 1:29 ጋር አወዳድር።) ይህን ምሳሌያዊ በግ በሚመለከት ከሰማይ የወጣ ድምፅ እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፣ ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ።” (ራእይ 5:9, 10) ከዚህ ራእይ እንደምንማረው በፈሰሰው የክርስቶስ ደም መሠረት ከየወገኑ የተውጣጡ የተወሰኑ ሰዎች በሰማይ ከእርሱ ጋር ሆነው ‘በምድር ላይ እንዲነግሡ’ ተጠርተዋል። (ከራእይ 1:5, 6 ጋር አወዳድር።) የእነዚህ ሰዎች የተወሰነ ቁጥር በዚህ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ትንሽ እልፍ ብሎ ተገልጿል።
9. ምዕራፍ 6 ውስጥ ክርስቶስ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል?
9 በዚሁ ራእይ ውስጥ ክርስቶስ ዘውድ ጭኖ ‘ድል እየነሳ ድል ለመንሳት’ እንደወጣ ነጭ ፈረስ ጋላቢ ሆኖ ተገልጿል። የተቀሩት ሦስት የአፖካሊፕስ ጋላቢዎች የሚወክሉትን ክፉ ነገር ሁሉ ድል የሚያደርግ መሆኑ ያስደስታል። የእነዚህ ፈረሰኞች ሽምጥ ግልቢያ ወሳኝ ከሆነው ዓመት ከ1914 አንስቶ በሰው ልጅ ላይ ጦርነት፣ ረሃብና ሞት አምጥቷል። (ራእይ 6:1-8) የአምላክ በግ የሆነው ክርስቶስ በሰው ልጆች መዳንና ድንቅ በሆነው የይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚና የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ዘመቻ ዋና ጭብጥ ነው።
10. (ሀ) በምዕራፍ 7 ላይ ምን ጠቃሚ መረጃ ቀርቧል? (ለ) ክርስቶስ መንግሥቱን ስለሚያገኙ ሰዎች ምን ብሏል?
10 ምዕራፍ 7 በእርግጥም ምሥራች ያዘለ ምዕራፍ ነው። የበጉ አባት መንግሥትን የሚሰጣቸውና ኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” ሲል የጠራቸው ሰዎች ቁጥር ስንት እንደሆነ ተጠቅሶ የምናገኘው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ነው። (ሉቃስ 12:32፤ 22:28-30) እነዚህን ሰዎች ይሖዋ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት አትሟቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) ራእይውን የተቀበለው ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ያረጋግጣል:- “የታተሙትንም ቊጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።” (ራእይ 7:4) ይህ በግልጽ የተቀመጠ አኃዝ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ከበጉ ጋር ለመግዛት ‘ከሰዎች የተዋጁትን’ ጠቅላላ ቁጥር የሚያመለክት መሆኑ ወደኋላ በሌላ ምዕራፍ ውስጥ ተረጋግጧል። (ራእይ 14:1-4) የሚያስገርመው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይህን ቁጥር በተመለከተ የተድበሰበሰና አሳማኝ ያልሆነ ማብራሪያ የሚሰጡ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኢ ደብልዩ ቡሊንገር ይህን በተመለከት እንዲህ ብለዋል:- “እዚሁ ምዕራፍ ላይ ከተገለጸው ያልተወሰነ ቁጥር ጋር ተነጻጽሮ የተገለጸ የተወሰነ ቁጥር በመሆኑ ሐሳቡ ግልጽና የማያሻማ ነው።”
11. (ሀ) በምዕራፍ 7 ውስጥ የሚገኙት መልካም ወሬዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባላት ከፊታቸው ምን ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል?
11 ቡሊንገር የጠቀሱት ያልተወሰነ ቁጥር የትኛው ነው? ቁጥር 9 ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ።” (ራእይ 7:9) የእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አባላት እነማን ናቸው? በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ፊት ያላቸው አቋም ምንድን ነው? ወደ ፊትስ ምን ተስፋ አላቸው? አፖካሊፕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ለምድር ነዋሪዎች ሁሉ ምሥራች ነው። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ጥበቃ ያገኛሉ። ክርስቶስ “ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” (ራእይ 7:14-17) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ያሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ከሚተርፉት ከእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል መሆን ይችላሉ። በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ መስተዳድር ሥር ስለሚኖሩ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ይመራቸዋል። ይህ ምሥራች አይደለምን?
‘ፍርዱ እውነትና ጽድቅ ነው’
12, 13. (ሀ) ከ8 እስከ 19 ያሉት ምዕራፎች ምን ቁም ነገር ይዘዋል? (ለ) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ባሉት ትንቢቶች መሸበር የማይገባቸው ለምንድን ነው?
12 አፖካሊፕስ ወይም የራእይ መጽሐፍ ስለ አስፈሪ መዓት የሚያወራ መጽሐፍ ነው የሚል ስም እንዲያተርፍ ያደረጉት ከ8 እስከ 19 ያሉት ምዕራፎች ናቸው። በተለያዩ የሰይጣን ዓለም ክፍሎች ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ የሚገልጹ (በመለከት መነፋት፣ በመቅሰፍትና በመለኮታዊው የቁጣ ጽዋ የተመሰሉ) ጠንካራ የፍርድ መልእክቶችን ይዘዋል። እነዚህ ፍርዶች የሚፈጸሙት በመጀመሪያ በሐሰት ሃይማኖት (“ታላቂቱ ባቢሎን”) ከዚያም በአውሬ በተመሰሉትና አምላካዊ አክብሮት በሌላቸው የፖለቲካ ሥርዓቶች ላይ ይሆናል።—ራእይ 13:1, 2፤ 17:5-7, 15, 16a
13 እነዚህ ምዕራፎች ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ወደ ምድር አቅራቢያ ተጥለው ሰማይ እንደፀዳ ይነግሩናል። ይህም ከ1914 ወዲህ በምድር ላይ የሚታየው ይህ ነው የማይባል አስጨናቂ ሁኔታ የመጣበትን ምክንያት እንድንረዳ የሚያስችለን ብቸኛ ምክንያታዊ መልስ ነው። (ራእይ 12:7-12) በተጨማሪም በምድር ላይ ባለው የሰይጣን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚመጣውን ጥፋት በምሳሌያዊ መንገድ ይገልጻሉ። (ራእይ 19:19-21) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዚህ ታላቅ ክንውን ሊደናገጡ ይገባልን? በፍጹም አይገባም። ምክንያቱም አምላክ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ከሰማይ “ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው” የሚል ድምፅ ተሰምቷል።—ራእይ 19:1, 2
14, 15. (ሀ) የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በጽድቅ የሚደመደመው እንዴት ነው? (ለ) ይህ የአፖካሊፕስ ክፍል ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች የደስታ ምክንያት ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ምድርን የሚያጠፏትን ሰዎች ከምድር ላይ ሳያስወግድ ጽድቅ የሰፈነበት የነገሮች ሥርዓት አያመጣም። (ራእይ 11:17, 18፤ 19:11-16፤ 20:1, 2) ይሁን እንጂ ይህንን ማድረግ የሚያስችል አቅምም ሆነ ሥልጣን ያለው አንድም ሰው ወይም ፖለቲካዊ መንግሥት አይኖርም። ይህንን በጽድቅ ማድረግ የሚችሉት ይሖዋና እርሱ ንጉሥና ዳኛ አድርጎ የሾመው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ናቸው።—2 ተሰሎንቄ 1:6-9
15 አፖካሊፕስ በግልጽ እንደሚያስረዳው ይሖዋ ዛሬ ያለውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው የማምጣት ዓላማ አለው። ይህም ‘በሚሠራው ርኩሰት ለሚያዝኑና ለሚተክዙት’ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ የደስታ ምክንያት ሊሆንላቸው ይገባል። (ሕዝቅኤል 9:4) ይህም ምሥራቹን ሲያበስር የነበረው መልአክ ያሰማቸውን የሚከተሉትን ቃላት የመጠበቁን አጣዳፊነት እንድናስተውል ሊረዳን ይገባል:- “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ . . . ሰማይንና ምድርንም . . . ለሠራው ስገዱለት።” (ራእይ 14:7) እንዲህ ያሉት ሰዎች ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከሚጠብቁትና የኢየሱስም ምስክር’ ካላቸው አገልጋዮቹ ጎን ተሰልፈው ይሖዋን እንዲያመልኩና እንዲያገለግሉት ምኞታችን ነው።—ራእይ 12:17
ክብራማው የሺህ ዓመት ግዛት
16. (ሀ) የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚናገረውን ተስፋ ገሸሽ ያደረጉት ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የናሙናው ጸሎት መልስ ያገኛል ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
16 ከ20 እስከ 22 ያሉት የራእይ መጽሐፍ ምዕራፎች ለሺህ ዓመቱ ተስፋ መሠረት የሚሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ይዘዋል። በሰማይና በምድር ዘላለማዊ ደስታ ከመስፈኑ በፊት እንደ መቅድም ሆኖ ስለሚመጣው የሺህ ዓመት ግዛት የሚጠቅሰው ብቸኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይህ ነው። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚናገረውን ተስፋ ገሸሽ አድርገዋል። የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጻድቃን ወደ ሰማያዊ ሕይወት ክፉዎች ደግሞ ወደ ሲኦል ይሄዳሉ የሚል ስለሆነ ምድራዊ ገነት ይኖራል ለሚለው እምነት ቦታ የለውም። “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚል ልመና ያዘለው የናሙና ጸሎት በብዙ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት ዘንድ ትርጉም አጥቷል። (ማቴዎስ 6:10) ይሁን እንጂ ይህ አባባል በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አይሠራም። ይሖዋ አምላክ ‘ምድርን መኖሪያ ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንዳልሠራት’ አጥብቀው ያምናሉ። (ኢሳይያስ 45:12, 18) በዚህ መንገድ ጥንታዊ ትንቢቶች፣ የናሙናው ጸሎትና የአፖላኪፕሱ የሺህ ዓመት ተስፋ እርስ በርሳቸው ይስማማሉ። ክርስቶስ በሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም እንዲሆን ያደርጋል።
17. “ሺህ ዓመት” የሚለው መግለጫ ቃል በቃል የሚወሰድ እንደሆነ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
17 “ሺህ ዓመት” የሚለው መግለጫ በራእይ መጽሐፍ 20ኛ ምዕራፍ የመጀመሪያ ሰባት ቁጥሮች ውስጥ ስድስት ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ሦስት ጊዜ “ም” የሚል ጠቃሽ አመልካች ያለው መሆኑ ሊጤን ይገባል። ይህም ብዙ የሕዝበ ክርስትና ተንታኞች ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት ሺህ ዓመት የሚለው መግለጫ በውል የማይታወቅን ረጅም ጊዜ የሚያመለክት ሳይሆን ቃል በቃል አንድን ሺህ ዓመት እንደሚያመለክት የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። በዚህ ሺህ ዓመት ውስጥ ምን ነገሮች ይከናወናሉ? በመጀመሪያ ይህ ጊዜ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሰይጣን እንቅስቃሴ አልባ ይደረጋል። (ራእይ 20:1-3፤ ከዕብራውያን 2:14 ጋር አወዳድር።) ይህ እንዴት ያለ ምሥራች ነው!
18. (ሀ) አንድ ሺው ዓመት አንድ የፍርድ “ቀን” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ምን ነገር ይከናወናል?
18 ‘ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ለሚነግሡት’ ሰዎች “ዳኝነት” ስለተሰጣቸው ይህ ጊዜ በእርግጥም የአንድ ሺህ ዓመት ርዝማኔ ያለው የፍርድ “ቀን” ነው። (ራእይ 20:4, 6፤ ከሥራ 17:31፤ 2 ጴጥሮስ 3:8 ጋር አወዳድር።) ሙታን ተነሥተው ‘ከታላቁ መከራ’ በሕይወት ከተረፉት ሰዎች ጋር በዚያ ወቅት በሚያደርጉት ነገር ወይም በሥራቸው ላይ የተመሠረተ አግባብነት ያለው ፍርድ ይሰጣቸዋል። (ራእይ 20:12, 13) በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ሰይጣን ለሰው ዘር የመጨረሻ ፈተና እንዲያቀርብ ለጥቂት ጊዜ የሚፈታ ሲሆን ከዚህ በኋላ እርሱ፣ አጋንንቱና በምድር ላይ ያለ እርሱን የሚከተሉ ዓመፀኞች በሙሉ ለዘላለም ይጠፋሉ። (ራእይ 20:7-10) ይህንን ፈተና የሚያልፉ ሰዎች ስማቸው በማይፋቅ መንገድ ‘በሕይወት መጽሐፍ’ ውስጥ ይሰፍርና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ደስታ በሰፈነበት ሁኔታ ይሖዋን እያገለገሉና እያመለኩ ለዘላለም ይኖራሉ።—ራእይ 20:14, 15፤ መዝሙር 37:9, 29፤ ኢሳይያስ 66:22, 23
19. (ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ግሩም ተስፋ ያለ ምንም ችግር ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ነገር እንወያያለን?
19 በአፖካሊፕስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህን የመሳሰሉ ምሥራቾች ናቸው። እነዚህ እንዲሁ ከንቱ ሰው ሠራሽ ወሬዎች አይደሉም። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።” (ራእይ 21:5) እነዚህ አስደሳች ነገሮች ፍጻሜያቸውን በሚያገኙበት ጊዜ ተካፋይ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? የራእይ መጽሐፍ አምላክን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች ብዙ ምክር ይዟል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምናየው እንዲህ ያለውን ምክር መከተላችን አሁንም ሆነ ወደፊት ወሰን የሌለው ደስታ ያስገኝልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ ራእይ መጽሐፍ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ያዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።
የክለሳ ነጥቦች
◻ የብስራቱ ዋነኛ ክፍል የሆኑት ከራእይ ምዕራፍ 4 እስከ 6 ላይ የሚገኙት መሠረታዊ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?
◻ በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘው ምሥራች ምንድን ነው?
◻ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በራእይ ውስጥ በሚገኘው የፍርድ መልእክት ሊሸበሩ የማይገባው ለምንድን ነው?
◻ የሺህ ዓመት ግዛቱ አንድ የፍርድ “ቀን” ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ መላዋን ምድር ከጦርነት ከረሃብና ሞት ነፃ ያደርጋል