ሲኦል ዘላለማዊ መሠቃያ ነው ወይስ ተራ መቃብር?
የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመካከለኛው ዘመን የሃይማኖት ሊቃውንትና የሃይማኖታዊ ተሐድሶ መሪዎች የሲኦል ሥቃይ ዘላለማዊ ነው ብለው እንደተከራከሩ ተነግሮሃልን? ተነግሮህ ከነበረ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህንን አባባል አንደማይቀበሉ ስታውቅ ትደነቅ ይሆናል። ከእነዚህ ምሁራን አንዱ የሆኑት የብሪታንያው ጆን አር ስቶት “ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያመለክቱት መጥፋትን ነው። እየሰሙ ለዘላለም መሠቃየት ከፍተኛ በሆነው የቅዱሳን ጽሑፎች ሥልጣን መሸነፍ ያለበት ወግ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። — Essentials—A Liberal-Evangelical Dialogue
እኚህ ሰው የዘላለም ሥቃይ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም ብለው እንዲደመድሙ ያስቻላቸው ምንድን ነው?
የቋንቋ ትምህርት
የመጀመሪያ ክርክራቸው በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው የኩነኔ ፍርድ ሲናገር (“ጌሄና”፣ ሣጥኑን በገጽ 8 ላይ ተመልከት) አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀመው “ጥፋትን” በሚያመለክቱ የግሪክኛ ቃላት ማለትም “አፖሉሚ (ማጥፋት) አፖሌያ (ጥፋት) በሚሉት ቃላት ነው” በማለት ያስረዳሉ። እነዚህ ቃላት ሥቃይን ያመለክታሉን? ግሱ አድራጊ በሚሆንበት ጊዜ አፖሉሚ “መግደል” ማለት እንደሆነ ስቶት ገልጸዋል። (ማቴዎስ 2:13፤ 12:14፤ 21:41) ስለዚህ ማቴዎስ 10:28 በኪንግ ጀምስ ትርጉም መሠረት አምላክ “ነፍስንና ሥጋን በሲኦል” እንደሚያጠፋ ሲናገር የሚገልጸው በሞት መጥፋትን እንጂ የዘላለም ሥቃይ መቀበልን አይደለም። ኢየሱስ በማቴዎስ 7:13, 14 ላይ ወደ ሕይወት የሚወስደውን “ጠባብ መንገድ” ወደ ጥፋት ከሚወስደው “ሠፊ መንገድ” ጋር አነጻጽሮአል። ስቶት “ስለዚህ ጥፋት ይደርስባቸዋል የተባሉ ሰዎች ሳይጠፉ ቢቀሩ እንግዳ ነገር ይሆናል” በማለት ተችተዋል። “መግደል ማለት ሥጋን ሕይወት ማሳጣት ከሆነ ሲኦልም አካላዊና መንፈሳዊ ሕይወት ማጣትንና ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ማመልከት የሚኖርበት ይመስላል” የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱት አለበቂ ምክንያት አይደለም። — Essentials pages 315–16.
ስለ ሲኦል የተነገሩትን ምሳሌያዊ መግለጫዎች መተርጎም
እንዲህም ሆኖ ብዙ ሃይማኖታዊ ሰዎች የደቡብ ባፕቲስት ኮንቬንሽን ፕሬዘዳንት ከሆኑት ከሞሪስ ኤች ቻፕማን ጋር ይስማማሉ። እኚህ ሰው “እኔ የምሰብከው ሲኦል ቃል በቃል ሲኦል ነው” ብለዋል። ቀጥለውም:- “ይህን ሲኦል መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእሳት ባሕር’ ይለዋል። ይህን አተረጓጎም ለማሻሻል የሚቻል አይመስለኝም” ብለዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እሳት የሚናገሩት ምሳሌያዊ መግለጫዎች በአእምሮ ውስጥ የሥቃይን ሥዕል የሚስሉ እንደሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ኢሰንሽያልስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እሳትን እየሰሙ ከመሠቃየት ጋር በአእምሮአችን የምናዛምደው ሁላችንም መቃጠል የሚያስከትለውን ከባድ ሕመም ስለቀመስን እንደሆነ አይጠረጠርም። ይሁን እንጂ ዋነኛው የእሳት ተግባር ማጥፋት እንጂ ማሳመም አይደለም። ለዚህም በዓለም ዙሪያ ያሉት የቆሻሻ አቃጣዮች ምሥክሮች ናቸው።” (ገጽ 316) ይህን ልዩነት መገንዘብ ለአንዳንድ ጥቅሶች የሌለ ትርጉም እንዳትሰጥ ይረዳሃል። አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት:-
ኢየሱስ ወደ ገሃነም ስለሚጣሉ ሰዎች ሲናገር ‘ትላቸው እንደማይሞትና እሳቱም እንደማይጠፋ’ ተናግሮአል። (ማርቆስ 9:47, 48) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች መጽሐፈ ዮዲት በሚባለው አዋልድ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ቃል በማመን (“በሥጋቸው ላይ እሳትና ትል ይልክባቸዋል። ለዘላለምም በሥቃይ ያለቅሳሉ” ዮዲት 16:17) ኢየሱስ የተናገረው ስለዘላለማዊ ሥቃይ ነው ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፈ ዮዲት አዋልድ መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የማርቆስን ጽሑፍ ለመተርጎም መሠረት ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። ኢየሱስ ይህን ቃል ሲናገር በአእምሮው ይዞት የነበረው የኢሳይያስ 66:24 ጥቅስ የአምላክ ጠላቶች ሬሣ በትሎችና በእሳት እንደሚጠፋ ያመለክታል። ኢየሱስም ሆነ ኢሳይያስ የተናገሩአቸው ቃላት እየሰሙ ለዘላለም መሠቃየትን የሚያመለክት መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ የለም። እሳቱ ፍጹም መጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌ ነው።
ራእይ 14:9–11 አንዳንዶች ‘በእሳትና በዲን እንደሚሠቃዩና የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ እንደሚወጣ’ ይናገራል።a ታዲያ ይህ እየሰሙ ለዘላለም መሠቃየት መኖሩን ያረጋግጣልን? ይህ ጥቅስ የሚናገረው ክፉዎች እንደሚሠቃዩ እንጂ ለዘላለም እንደሚሠቃዩ አይደለም። ለዘላለም የሚኖረው ጭሱ ማለትም እሳቱ የማጥፋት ሥራውን እንደፈጸመ የሚያመለክተው ማስረጃ እንጂ አሳታማው ሥቃይ እንዳልሆነ ጥቅሱ ያመለክታል።
ራእይ 20:10–15 ደግሞ “ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ” ይላል። ይህ ጥቅስ ላይ ላዩን ሲነበብ እየሰሙ ለዘላለም መሠቃየት መኖሩን የሚያረጋግጥ ይመስላል። ግን ፈጽሞ አያረጋግጥም። ለምን? ከሌሎች ምክንያቶች በተጨማሪ እዚህ ላይ “የእሳት ባሕር” በተባለው ውስጥ የሚጣሉት “አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ” እንዲሁም “ሞትና ሲኦል” ስለሆኑ ነው። በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው አውሬው፣ ሐሰተኛው ነቢይ፣ ሞትና ሲኦል ቃል በቃል ሰዎች አይደሉም። በዚህም ምክንያት የሥቃይ ስሜት ሊሰማቸው አይችልም። ከዚህ ይልቅ ጂ ቢ ካርድ የተባሉት ፀሐፊ ኤ ኮመንተሪ ኦን ዘ ሬቬለሽን ኦቭ ሴይንት ጆን ዘ ዲቫይን በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደጻፉት “የእሳት ባሕር ፍጹም ጥፋትና ከሕልውና ውጭ መሆን ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ስለዚህ የእሳት ባሕር ሲናገር “ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” ስለሚል እዚህ ግንዛቤ ላይ መድረስ አስቸጋሪ አይሆንም። — ራእይ 20:14
ሃይማኖታዊ መንትዮችን መነጠል
አንዳንድ አማኞች እነዚህን ሁሉ ማሳመኛ ነጥቦች እያሉ “ጥፋት” የተባለው ቃሉ እንደሚያመለክተው ጥፋት ሳይሆን የዘላለም ሥቃይ ማለት ነው ይላሉ። ለምን? አስተሳሰባቸው የሲኦል እሳት መንትያ በሆነው የሰው ነፍስ አትሞትም በሚለው ለሚለው መሠረተ ትምህርት ስለተጣመመ ነው። ቤተ ክርስቲያናቸው እነዚህን መንትያ መሠረተ ትምህርቶች ለብዙ መቶ ዘመናት ጠብቆ ስላቆየ ስለጥፋት የሚናገሩት ጥቅሶች የዘላለም ሥቃይ ትርጉም ያላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም የማትሞተው ሰብአዊ ነፍስ ከሕልውና ውጭ ልትሆን አትችልም ብለው ይከራከራሉ።
ይሁን እንጂ የአንግሊካን ቄስ የሆኑት ፊሊፕ ኢ ሂውዝ የተናገሩትን ልብ በል:- “የዘላለማዊነት ባሕርይ ያለው የሰው ነፍስ ብቻ ነው ብሎ መከራከር በቅዱሳን ጽሑፎች ትምህርት ውስጥ በየትም ሥፍራ ያልተደገፈ እምነት መያዝ ነው። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ልጅ ባሕርይ የመንፈስና የአካል ውህደት እንደሆነ ተገልጾአል። . . . አምላክ ‘ከእርስዋ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ’ በማለት ስለተከለከለው ዛፍ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የተነገረው የሥጋና የመንፈስ ጥምር ለሆነ ፍጥረት ነበር። ከፍሬው ቢበላ የሚሞተው ይኸው የሥጋና የመንፈስ ጥምር የሆነው ሰው ነው። የማይሞት ሌላ ክፍል እንዳለውና የሚሞተው በከፊል ብቻ እንደሆነ የሚያመለክት ነገር የለም።” — The True Image—The Origin and Destiny of Man in Christ
የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ክላርክ ፒኖክም በተመሳሳይ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ [የሰው ነፍስ ዘላለማዊት ናት የሚለው] ጽንሰ ሐሳብ በጣም ብዙ ለሆኑ ዘመናት በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር የኖረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ የዘላለማዊነት ባሕርይ እንዳላት አያስተምርም።” ሕዝቅኤል 18:4, 20 እንዲሁም ማቴዎስ 10:28 ይህንን ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ወዳጁ የሆነው አልዓዛር በሞተ ጊዜ እንደተኛ ተናግሮአል። በተጨማሪም “ከእንቅልፉ ላስነሳው እሄዳለሁ” ብሎአል። (ዮሐንስ 11:11–14) ስለዚህ አልዓዛር የተባለው ሰብአዊ አካል ወይም ሰብዓዊ ነፍስ ሞቶ ነበር። ከሞተ ጥቂት ጊዜ ያለፈው ቢሆንም ከሞት ሊነሳና ወደ ሕይወት ሊመለስ ይችል ነበር። ይህም ትክክል መሆኑ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት በማስነሳቱ ታይቶአል። — ዮሐንስ 11:17–44
እነዚህ ነጥቦች በዘላለም ሥቃይ መሠረተ ትምህርት ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይኖራቸዋል? ዊልያም ቴምፕል የተባሉት ጸሐፊ በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን እንዲህ ብለው ነበር:- “በማይጠፋ እሳት ውስጥ ስለመጣል የሚናገሩ ጥቅሶች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ጥቅሶች በዚያ የሚጣለው ነገር ሊጠፋ የማይችል ነው የሚለውን እምነት ይዘን ካላነበብን በስተቀር በእሳቱ ውስጥ የሚጣለው ነገር እንደሚጠፋ እንጂ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንደሚቃጠል ለመረዳት አንችልም።” ይህ ትክክለኛ ትንታኔ አሁንም እውነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስም የሚያስተምረው ይህንን ነው።
በሲኦል ውስጥ እየሰሙ ለዘላለም የመሠቃየት ጽንሰ ሐሳብ ትክክል መሆኑን እንድትጠራጠር የሚያስገድዱ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ሊካድ አይችልም። ይሁን እንጂ በጥርጣሬ ብቻ ተወስነህ ሳትቀር የሚከተለውን የተናገሩትን የፕሮፌሰር ፒኖክን ምክር ለመከተል ትፈልግ ይሆናል። “በሲኦል ዙሪያ ያሉት እምነቶች በሙሉ፣ ፍጻሜ ስለሌለው ሥቃይ የሚገልጸው እምነት ጭምር ፈጽመው መጣልና ጠንካራ መሠረት ባላቸው መሠረተ ትምህርቶች መተካት አለባቸው።” አዎ፣ ትክክለኛ ሥነ ምግባር፣ ፍትሕና ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንድታደርግ ያሳስቡሃል።
ይህን ብታደርግ ትክክለኛው የሲኦል ምንነት ለማመን የሚያዳግት እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። ስለዚህ ጉዳይ ለመረዳት ከፈለግህ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ጠቃሚ መረጃ ለማግኘት ትችላለህ።b ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምትገናኝበት ጊዜ ይህን መጽሐፍ እንዲሰጡህ ጠይቅ። “ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?”፣ “ሲኦል ምን ዓይነት ቦታ ነው?”፣ “ትንሣኤ — ለማንና የት?” የሚሉትን ምዕራፎች አንብብ። ትክክለኛው የሲኦል ምንነት ለማመን የማያዳግት ብቻ ሳይሆን ብሩሕ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ጭምር ለመገንዘብ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ውስጥ ‘በእሳት መሠቃየት’ የሚያመለክተው ፍጻሜ ያለውን መንፈሣዊ ሥቃይ ነው። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ራእይ፣ ታላቁ መደምደሚው ደርሷል! የተባለውን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመ መጽሐፍ ተመልከት።
b በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ መጽሐፍ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቃሎቹን ትርጉም መረዳት
በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተገለጹትና የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሊቃውንት የሚጠቀሙባቸው “ሲኦል” እና “የሲኦል እሳት” የተባሉት ቃላት (በእንግሊዝኛ “ሄል”) የሚያመለክቱት “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ 12 ጊዜ የሚገኘውን ጌኢና የተባለ የግሪክኛ ቃል ነው። (ማቴዎስ 5:22, 29, 30፤ 10:28፤ 18:9፤ 23:15, 33፤ ማርቆስ 9:43, 45, 47፤ ሉቃስ 12:5፤ ያዕቆብ 3:6) የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን የግሪክኛ ቃል “ሲኦል” ወይም “ሄል” እያሉ ቢተረጉሙትም “ገሃነም” ብለው የተረጎሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ይህም በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የዘላለም ጥፋት ምሳሌ ሆኖ ከተጠቀሰው “ሁለተኛ ሞት፣ የእሳት ባሕር” ጋር ተመሳሳይ ነው። — ራእይ 20:14
አንዳንድ ጊዜ “ሲኦል” ተብለው ስለሚተረጎሙ ሌሎች ሁለት ቃላት በዊልያም ስሚዝ የተዘጋጀው ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (1914) እንዲህ ይላል:- “ተርጓሚዎቻችን ሺኦል የተባለውን የዕብራይስጥ ቃል ሲኦል ወይም ሄል ብለው መተርጎማቸው ያሳዝናል። የዕብራይስጡን ቃል እንዳለ ትቶ ሺኦል ማለት አለበለዚያም ‘መቃብር’ ወይም ‘ጉድጓድ’ ብሎ መተርጎም ሳይሻል አይቀርም ነበር። . . . በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሔድስ የተባለው ቃል ልክ እንደ ሺኦል አንዳንድ ጊዜ ‘መቃብር’ የሚል ትርጉም አለው። . . . የሃይማኖታችን ቀኖና ጌታችን ወደ ሲኦል እንደወረደ የሚናገረው በዚህ ትርጉም መሠረት ነው። ይህም ማለት ሙታን ወዳሉበት ሁኔታ ሄደ ማለት ነው።”
ሺኦልና ሔድስ የሚያመለክቱት ወደ ሕይወት የመመለስ ተስፋ ያለበትን የሰው ልጆች ተራ መቃብር እንጂ ጌሄና እንደሚለው ቃል የመጨረሻውን ጥፋት አይደለም። — ራእይ 20:13
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንቅልፍ አስነሳው