ምዕራፍ 30
“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!”
1. ሁለተኛው መልአክ ምን ማስታወቂያ ተናገረ? ታላቂቱ ባቢሎን ማን ነች?
ሰዓቱ የአምላክ ፍርድ የሚፈፀምበት ሰዓት ነው። ስለዚህ መለኮታዊውን መልእክት እናዳምጥ:- “ሌላም ሁለተኛ መልአክ:- አህዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቁጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች እያለ ተከተለው።” (ራእይ 14:8) የራእይ መጽሐፍ ለመጨረሻ ጊዜ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረቱን በታላቂቱ ባቢሎን ላይ አደረገ። ቆየት ብሎ ደግሞ ምዕራፍ 17 በፍትወት የተቃጠለች አመንዝራ እንደሆነች ይገልጻል። ታዲያ እርስዋ ማን ነች? ወደፊት እንደምንመለከተው ምድር አቀፍ፣ ሃይማኖታዊ ድርጅት ነች። ሰይጣን የአምላክን ሴት ዘሮች ለመውጋት የሚጠቀምባት አስመሳይ ድርጅት ነች። (ራእይ 12:17) ታላቂቱ ባቢሎን መላዋ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናት። የጥንትዋን ባቢሎን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ልማዶች የሚከተሉትንና የባቢሎንን መንፈስ የሚያንፀባርቁትን ሃይማኖቶች በሙሉ ታጠቃልላለች።
2. (ሀ) ባቢሎናዊ ሃይማኖት በዓለም በሙሉ የተሰራጨው እንዴት ነው? (ለ) የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የሆነችው ማን ነች? ትልቅ ኃይል ያላት ድርጅት የሆነችውስ ከመቼ ጀምሮ ነው?
2 ይሖዋ ከ4,000 ዓመታት በፊት የባቤልን ግንብ ለመሥራት የተነሱትን ሰዎች ቋንቋ ያዘባረቀው በባቢሎን ነበር። የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ቡድኖች እስከ ዛሬ ድረስ ለአብዛኞቹ የተለያዩ ሃይማኖቶች መሠረት የሆኑትን የክህደት እምነቶችና ልማዶች ይዘው ተበታተኑ። (ዘፍጥረት 11:1-9) ታላቂቱ ባቢሎን የሰይጣን ድርጅት ሃይማኖታዊ ክፍል ነች። (ከዮሐንስ 8:43-47 ጋር አወዳድር።) በዛሬው ጊዜ የዚህች ድርጅት ዋነኛ ክፍል የሆነችው ከክርስቶስ በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን በአብዛኛው ከባቢሎናዊ ሃይማኖት የተገኙ የአምልኮ ሥርዓቶችንና መሠረተ እምነቶችን ይዛ ታላቅ ኃያል ድርጅት የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ናት።—2 ተሰሎንቄ 2:3-12
3. ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃለች ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?
3 ‘ዛሬም ቢሆን በምድር ጉዳዮች ውስጥ ሃይማኖት ይህን የሚያክል ታላቅ ኃይል ያለው ከሆነ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች ብሎ መልአኩ ማስታወቂያ የተናገረው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በ539 ከዘአበ የጥንትዋ ባቢሎን ከወደቀች በኋላ ምን ሆኖ ነበር? እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው እውነተኛ አምልኮ ለማደስና ለማቋቋም ችለው ነበር። ስለዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከ1919 ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ በመስፋፋት ላይ ወደሚገኘው ደማቅ መንፈሳዊ ብልጽግና መመለሳቸው በዚያው ዓመት ታላቂቱ ባቢሎን የወደቀች መሆኑን ያመለክታል። አሁን የአምላክን ሕዝቦች አግዶ ለመያዝ የሚያስችል ኃይል የላትም። ከዚህም በላይ በራስዋ ውስጥ ከባድ ውዝግብ ደርሶባታል። ከ1919 ጀምሮ ምግባረ ብልሹነቷ፣ አጭበርባሪነቷ ሥነ ምግባራዊ እርኩሰትዋ በሰፊው ተጋልጦአል። በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍሎች ቤተ ክርስቲያን የሚሳለሙ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ሆኖአል። በአንዳንድ ሶሺያሊስት አገሮች ደግሞ ሃይማኖት “የሕዝብ ማደንዘዣ መርዝ” እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ታላቂቱ ባቢሎን የአምላክን ቃል እውነት በሚያፈቅሩ ሰዎች ሁሉ ዘንድ የተዋረደች ስለሆነ የይሖዋ የጽድቅ ፍርድ የሚፈጸምባትን ጊዜ እየተጠባበቀች ነው።
የባቢሎን የውርደት ውድቀት
4-6. ታላቂቱ ባቢሎን “የምድርን አሕዛብ በሙሉ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ያጠጣችው” እንዴት ነው?
4 ታላቂቱ ባቢሎን በታላቅ ውርደት የወደቀችበትን ሁኔታ እንመልከት። መልአኩ እዚህ ላይ የሚነግረን “ታላቂቱ ባቢሎን . . . አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ” እንዲጠጡ እንዳደረገች ነው። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? ወረራን ወይም ድል አድራጊነትን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለኤርምያስ “የዚህን ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምሰድድባቸውን አሕዛብን ሁሉም አጠጣቸው ከምሰድድባቸውም ሰይፍ የተነሳ ይጠጣሉ” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 25:15, 16) በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ በጥንትዋ ባቢሎን በመጠቀም ለብዙ አሕዛብ ለከሃዲዋ ይሁዳ ጭምር ምሳሌያዊ የመከራ ጽዋ አጠጥቶ ስለነበር የገዛ ሕዝቦቹ እንኳን ወደ ግዞት ተወስደው ነበር። በኋላ ግን የባቢሎን ንጉሥ “በሰማያት ጌታ” በይሖዋ ላይ ራሱን ከፍ ከፍ ስላደረገ ባቢሎን ራስዋ በተራዋ ወደቀች።—ዳንኤል 5:23
5 ታላቂቱ ባቢሎንም ወረራ አካሂዳ ነበር። የእርስዋ ወረራ ግን በአብዛኛው በግልጽ የሚታይ አልነበረም። “አሕዛብ ሁሉ የቁጣዋን ወይን ጠጅ” እንዲጠጡ ያደረገችው በምንዝር ማታለያዎች ማርካ መንፈሳዊ ምንዝር በመፈጸም ነው። ፖለቲካዊ ገዥዎች ወዳጆችዋና ግብረ አበሮችዋ እንዲሆኑ አድርጋለች። በሃይማኖታዊ ማታለያዎችዋ አማካኝነት የፖለቲካ፣ የንግድና የኤኮኖሚ ጭቆናዎችን አስፋፍታለች። ለፖለቲካና ለንግድ ጉዳዮች ስትል ብቻ ሃይማኖታዊ ስደቶችን፣ ብሔራዊ ጦርነቶችንና የመስቀል ጦርነቶችን አነሳስታለች። እነዚህንም ጦርነቶች በአምላክ ፈቃድ የሚደረጉ ጦርነቶች ናቸው በማለት ቀድሳቸዋለች።
6 በ20ኛው መቶ ዘመን ሃይማኖቶች በጦርነቶችና በፖለቲካ ጉዳዮች መካፈላቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም። በጃፓን አገር ሺንቶዎች፣ በሕንድ ሂንዱዎች፣ በቬትናም ቡዲህስቶች፣ በሰሜን አየርላንድና በላቲን አሜሪካ “ክርስቲያኖች” በሃይማኖት ስም ጦርነት አካሂደዋል። በተጨማሪም በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ጊዜ በሁለቱም ተዋጊ ወገኖች ጎን የተሰለፉ ወጣቶች እርስ በርሳቸው እንዲገዳደሉ ቀሳውስት ማነሳሳታቸው ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ታላቂቱ ባቢሎን በጦርነት ስለመካፈልዋ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ከ1936-1939 በስፓኝ አገር ተደርጎ በነበረው የእርስ በርስ ውጊያ ያደረገችው ተሳትፎ ነው። በዚህ ጦርነት ከ600,000 የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ሁሉ ደም መፋሰስ የተነሳው በአብዛኛው በካቶሊክ ቀሳውስትና በተባባሪዎቻቸው አነሳሽነት ነው። ምክንያቱም የስፓኝ ሕጋዊ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንዋን ሃብትና ሥልጣን ተቃውሞ ስለነበር ነው።
7. የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ዒላማ ሆና የቆየችው ማን ነች? በዚህስ ዒላማዋ ላይ እንዴት ያሉ ዘዴዎችን ተጠቅማለች?
7 ታላቂቱ ባቢሎን የሰይጣን ዘር ሃይማኖታዊ ክፍል ስለሆነች ዋነኛ ዒላማዋ ያደረገችው የይሖዋን “ሴት” ወይም “ላይኛይቱን ኢየሩሳሌም” ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የሴቲቱ ዘር መሆኑ በግልጽ ታውቆ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15፤ ገላትያ 3:29፤ 4:26) ታላቂቱ ባቢሎን ይህችን ንጹህ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ምንዝር በመፈጸም እንድትረክስ ለማድረግ የተቻላትን ሁሉ ሞክራ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ብዙዎች እንደሚታለሉና ታላቅ ክህደት እንደሚኖር አስጠንቅቀው ነበር። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3) ዮሐንስ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ ታላቂቱ ባቢሎን እውነተኛውን ክርስትና ለማበላሸት ባደረገችው ጥረት በመጠኑ ተሳክቶላት እንደነበረ ኢየሱስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የላከው መልእክት ያመለክታል። (ራእይ 2:6, 14, 15, 20-23) ይሁን እንጂ የሚሳካላት ምን ያህል እንደሆነ ኢየሱስ አመልክቶአል።
ስንዴውና እንክርዳዱ
8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የሰጠው ምሳሌ ምን ያመለክታል? (ለ) ‘ሰዎቹ ተኝተው ሳሉ’ ምን ሆነ?
8 ኢየሱስ ስለ ስንዴና ስለ እንክርዳድ በተናገረው ምሳሌ በእርሻው ላይ ንጹሕ ዘር ስለ ዘራ ሰው ተናግሮ ነበር። “ሰዎቹ ተኝተው ሳሉ” ግን ጠላት መጣና እንክርዳድ ዘራበት። በዚህም ምክንያት ስንዴው በእንክርዳዱ ተዋጠ። ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም በሚከተሉት ቃላት ገለጸ:- “መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፣ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው።” ከዚያም በመቀጠል ስንዴውና እንክርዳዱ ‘መላእክት ስንዴውን እስከሚሰበስቡበት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ’ በአንድነት በቅለው እንዲያድጉ እንደሚፈቀድ ተናገረ።—ማቴዎስ 13:24-30, 36-43
9 ኢየሱስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ አስቀድመው ያስጠነቀቁት ነገር ተፈጽሞአል። “ሰዎች ተኝተው ሳሉ” ማለትም ሐዋርያት በሞት ካንቀላፉ በኋላ ወይም ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ፈዛዞች ሆነው የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ ቸልተኞች በሆኑበት ጊዜ ባቢሎናዊ ክህደት በጉባኤው ውስጥ አቆጠቆጠ። (ሥራ 20:31) ብዙም ሳይቆይ እንክርዳዱ በጣም በዛና ስንዴውን ሙሉ በሙሉ ውጦ እንዳይታይ አደረገው። ለብዙ መቶ ዘመናት የሴቲቱ ዘር በታላቂቱ ባቢሎን ዘርፋፋ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ የተዋጠ መስሎ ነበር።
10. በ1870ዎቹ ዓመታት ምን ሆነ? በዚህስ ምክንያት ታላቂቱ ባቢሎን ምን አደረገች?
10 በ1870ዎቹ ዓመታት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን የግልሙትና መንገዶች ራሳቸውን ለመለየት ቁርጠኛ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ሕዝበ ክርስትና ከአረማውያን ያመጣቻቸውን የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች ተዉ። የአሕዛብ ዘመን በ1914 እንደሚፈጸም ከመጽሐፍ ቅዱስ በድፍረት ማስተማር ጀመሩ። የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ መሣሪያ የሆኑት የሕዘበ ክርስትና ቀሳውስት ይህን እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም የተደረገውን እንቅስቃሴ አምርረው ተቃወሙ። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ዓመታት ጦርነቱ የፈጠረውን የተፋፋመ ሁኔታ በመጠቀም ይህን ታማኝ የክርስቲያኖች አነስተኛ ቡድን ፈጽሞ ለማጥፋት ተነሳሱ። እንቅስቃሴአቸው ሙሉ በሙሉ የታገደ በመሰለበት በ1918 ታላቂቱ ባቢሎን ድል ያገኘች መስሎ ነበር።
11. የጥንትዋ ባቢሎን በመውደቅዋ ምክንያት ምን ሊሆን ቻለ?
11 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ትዕቢተኛዋ የባቢሎን ከተማ በ539 ከዘአበ ከከፍተኛ ሥልጣንዋ በክፉ አወዳደቅ ወድቃ ነበረ። በዚያ ጊዜ “ወደቀች፣ ባቢሎን ወደቀች!” የሚል ጩኸት ተሰምቶ ነበር። በዚያ ጊዜ የነበረው የዓለም ኃያል መንግሥት መናገሻ ከተማ በታላቁ ቂሮስ ይመራ በነበረው የሜዶ ፋርስ ጦር እጅ ወደቀች። ከተማዋ ድል በተነሳችበት በዚህ ጊዜ ፈጽሞ ባትጠፋም ከነበራት ታላቅ ሥልጣንና ኃይል ወድቃ ነበር። በዚህም ምክንያት አይሁዳውያን ምርኮኞችዋ ነፃ ለመውጣት ቻሉ። ንጹሑን አምልኮ በኢየሩሳሌም መልሰው ለማቋቋም ወደ አገራቸው ተመለሱ።—ኢሳይያስ 21:9፤ 2 ዜና 36:22, 23፤ ኤርምያስ 51:7, 8
12. (ሀ) በዘመናችን ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃለች ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝበ ክርስትናን ጨርሶ እንደጣላት ምን ማረጋገጫ አለ?
12 በዘመናችንም ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! የሚለው ጩኸት ተሰምቶአል። ሕዝበ ክርስትና በ1918 አግኝታ የነበረው ጊዜያዊና ባቢሎናዊ ድል የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች የሆኑት የዮሐንስ ክፍል አባሎች በ1919 መንፈሳዊ ትንሳኤ ባገኙ ጊዜ ተገለበጠ። ታላቂቱ ባቢሎን በአምላክ ሕዝቦች ላይ በነበራት የአሳሪነት ሥልጣን ረገድ ወደቀች። የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ለሥራ ዝግጁ ሆነው እንደ አንበጣ ሠራዊት እየተመሙ ከጥልቁ ወጡ። (ራእይ 9:1-3፤ 11: 11, 12) የዘመናችን ታማኝና ልባም ባሪያ ሆኑ። ጌታውም በምድር ላይ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ሾማቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) በዚህ መንገድ ማገልገላቸው ይሖዋ ሕዝበ ክርስትና በምድር ላይ የይሖዋ ወኪል እኔ ነኝ ማለትዋን ፈጽሞ እንደማይቀበለው አረጋግጦአል። ንፁሑ አምልኮ ተመልሶ ተቋቋመ። የ144,000ዎቹን ቀሪዎች ማለትም የታላቂቱ ባቢሎን የዘመናት ጠላት የሆነችውን የሴቲቱን ዘር ቀሪ አባሎች የማተም ሥራ የሚፈጸምበት ጥርጊያ መንገድ ተዘጋጀ። ይህ ሁሉ ክንውን ለሰይጣን ሃይማኖታዊ ድርጅት ታላቅ ሽንፈት ሆኖ ነበር።
የቅዱሳን ጽናት
13. (ሀ) ሦስተኛው መልአክ ምን ማስታወቂያ ተናገረ? (ለ) የአውሬውን ምልክት የሚቀበሉ ሰዎች ምን ፍርድ ይደርስባቸዋል?
13 አሁን ሦስተኛው መልአክ መናገር ይጀምራል። እስቲ እናዳምጠው:- “ሦስተኛውም መልአክ ተከተላቸው፣ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ:- ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፣ እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል።” (ራእይ 14:9, 10ሀ) በራእይ 13:16, 17 ላይ በጌታ ቀን የአውሬውን ምስል የማያመልኩ ሁሉ መከራ እንደሚደርስባቸውና እስከ መገደልም እንደሚደርሱ ተገልጾ ነበር። አሁን ደግሞ ይሖዋ “በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል” ማንኛውንም ሰው ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎአል። መራራውን የይሖዋ “የቁጣ ጽዋ” ለመጠጣት ይገደዳሉ። ይህ መሆኑ ምን ነገር ያስከትልባቸዋል? በ607 ከዘአበ ይሖዋ ኢየሩሳሌም “የቁጣውን ጽዋ” እንድትጠጣ ባደረገበት ጊዜ ከተማይቱ ከባቢሎናውያን ሠራዊት “መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ” ደርሶባት ነበር። (ኢሳይያስ 51:17, 19) በተመሳሳይም የምድርን ፖለቲካዊ ኃይሎችና ምስላቸው የሆነውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚያመልኩ ሰዎች የይሖዋን የቁጣ ጽዋ ሲጠጡ ትልቅ እልቂት ይመጣባቸዋል። (ኤርምያስ 25:17, 32, 33) ድምጥማጣቸው ይጠፋል።
14. አውሬውንና ምስሉን የሚያመልኩ ሰዎች ከመጥፋታቸው በፊት እንኳን ቢሆን ምን ይደርስባቸዋል? ዮሐንስ ይህን የገለጸው እንዴት ነው?
14 ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ በፊት እንኳን የአውሬው ምልክት ያላቸው ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ቁጣ የሚያስከተለውን ሥቃይ ይቀምሳሉ። መልአኩ አውሬውንና ምስሉን የሚያመልክ ሰው ስለሚደርስበት ነገር ለዮሐንስ ነግሮት ነበር:- “በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሣቀያል። የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፣ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።”—ራእይ 14:10ለ, 11
15, 16. በራእይ 14:10 ላይ “እሳትና ዲን” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?
15 አንዳንዶች እዚህ ላይ “እሳትና ድኝ” መጠቀሱ የሲኦል እሳት መኖሩን ያረጋግጣል ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ሌላ ትንቢት ብንመለከት የእነዚህን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት እንችላለን። ጥንት በኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ ኤዶማውያንን በእስራኤል ላይ በጠላትነት ስለ ተነሱ ቅጣት እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቆ ነበር። ይሖዋ እንዲህ አለ:- “የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፣ አፈርዋም ዲን ይሆናል፣ መሬትዋም የሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች። በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፣ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፣ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም።”—ኢሳይያስ 34:9, 10
16 ታዲያ ኤዶም ከዘላለም እስከ ዘላለም እንድትቃጠል በአንድ ዓይነት የሲኦል እሳት ውስጥ ተጥላ ነበርን? እንዲህ ያለ ነገር እንዳልደረሰባት ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ይህች ብሔር በእሳትና በዲን እንደ ተቃጠለች ያህል ከዓለም ገጽ ፈጽማ ጠፋች ማለት ነው። የደረሰባት ቅጣት የመጨረሻ ውጤት የዘላለም ሥቃይ ሳይሆን “ባዶነት . . . መፍረስ . . . ምናምንነት” ነበር። (ኢሳይያስ 34:11, 12) ይህ እውነት መሆኑ ‘ጢስዋም ለዘላለም በመውጣቱ’ ግልጽ ሆኖአል። አንድ ቤት ሲቃጠል እሳቱ ከጠፋ በኋላም ቢሆን ከአመዱ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ጢስ መውጣቱ ስለሚቀጥል ተመልካቾች ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶ እንደነበር ለመረዳት ይችላሉ። በዛሬው ጊዜ እንኳን የአምላክ ሕዝቦች ከኤዶም ጥፋት ሊገኝ ስለሚችለው ትምህርት ያስታውሳሉ። በዚህ መንገድ በምሳሌያዊ ሁኔታ ጢስዋ ‘ለዘላለም በመውጣት ላይ ነው’ ሊባል ይችላል።
17, 18. (ሀ) የአውሬውን ምስል የሚቀበሉ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) የአውሬው አምላኪዎች የሚሠቃዩት በምን መንገድ ነው? (ሐ) “የሥቃያቸው ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚወጣው” እንዴት ነው?
17 የአውሬው ምልክት ያላቸው ሁሉ በእሳት እንደተቃጠለ ነገር ለዘላለም ይጠፋሉ። ራእዩ ቆየት ብሎ እንደሚገልጸው አስከሬናቸው በአራዊትና በእንስሳት እንዲበላ በውጭ ሳይቀበር ይጣላል። (ራእይ 19:17, 18) ስለዚህ ቃል በቃል የዘላለም ሥቃይ በመቀበል ላይ አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ታዲያ “በእሳትና በዲን” የሚሠቃዩት እንዴት ነው? የእውነቱ መገለጥና ለሰዎች መታወጅ ስለሚያጋልጣቸውና ስለ መጪው የአምላክ ፍርድ ስለሚያስጠነቅቃቸው ነው። በዚህም ምክንያት የአምላክ ሕዝቦችን ስም ያጠፋሉ። በሚቻላቸው ጊዜም ፓለቲካዊው አውሬ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲያሳድድና እንዲገድል በተንኮል ያነሳሳሉ። እነዚህ ተቃዋሚዎች በመጨረሻ ላይ በእሳትና በዲን እንደተቃጠለ ነገር ፈጽመው ይጠፋሉ። ከዚያ በኋላ በይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ላይ ዳግመኛ ተቀናቃኝ ሆኖ የሚነሳ ቢኖር በእነዚህ ተቃዋሚዎች ላይ የተፈጸመው የይሖዋ ፍርድ እንደ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ስለሚያገለግል “የሥቃያቸው ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።” ይህ ክርክር ለአንዴና ለዘላለም ምላሽ ያገኛል።
18 በአሁኑ ጊዜ ይህን የሚያሠቃይ መልእክት የሚያስተላልፉት እነማን ናቸው? ምሳሌያዊዎቹ አንበጦች የአምላክ ማህተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች እንደሚያሠቃዩ ሥልጣን ተሰጥቶአቸው እንደነበረ ታስታውሳላችሁ። (ራእይ 9:5) ሥቃይ የሚያመጡት እነዚህ በመላእክት የሚመሩት ምሳሌያዊ አንበጦች እንደሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ምሳሌያዊ አንበጦች ከፍተኛ ትጋት ስላላቸው “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፣ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።” በመጨረሻ ሲጠፉ ደግሞ የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ምሳሌ የሆነው “የሥቃያቸው ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል።” ይህ እስኪፈጸም ድረስ ግን የዮሐንስ ክፍል አባሎች መጽናት ይኖርባቸዋል። መልአኩ ቃሉን ሲደመድም እንዲህ አለ:- “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግስታቸው [“ጽናታቸው፣” NW] በዚህ ነው።”—ራእይ 14:12
19. ቅዱሳን መጽናት የሚፈለግባቸው ለምንድን ነው? ዮሐንስ የሚያበረታታቸው ምን ነገር ይናገራል?
19 አዎ፣ ‘የቅዱሳን ትዕግስት’ ወይም ጽናት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ ፍጹም አምልኮ በማቅረባቸው ይገለጣል። የሚያሰሙት መልእክት ተወዳጅነት የለውም። ተቃውሞ፣ ስደትና የሰማዕትነት ሞት የሚያስከትል ነው። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ቀጥሎ የተናገረው ቃል ያጽናናቸዋል:- “ከሰማይም:- ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው። መንፈስ:- አዎን፣ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፣ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።”—ራእይ 14:13
20. (ሀ) ዮሐንስ የተናገረው ተስፋ ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ መገኘት ከተናገረው ትንቢት ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለ ወዲህ የሞቱ ቅቡዓን ምን ልዩ መብት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል?
20 ይህ የተስፋ ቃል ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ መገኘት ከተናገረው ትንቢት ጋር ይስማማል። “እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም። ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላዕክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን።” (1 ተሰሎንቄ 4:15-17) ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለ በኋላ “በክርስቶስ የሞቱ” ሁሉ በመጀመሪያ ተነሱ። (ከራእይ 6:9-11 ጋር አወዳድር።) ከዚያ ጊዜ ወዲህ በጌታ ቀን የሚሞቱ ቅቡዓን ሁሉ ልዩ መብት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል። ወዲያው “በቅጽበት” ተለውጠው መንፈሳዊ ሕይወት ያገኛሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:52) ይህ በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው። የጽድቅ ሥራቸው ወደ ሰማያዊው ዓለም ተከትሎአቸው ይሄዳል።
የምድሩ መከር
21. ዮሐንስ ስለ ምድር “መከር” ምን ይነግረናል?
21 በዚህ የፍርድ ቀን ጥቅም የሚያገኙ ሌሎች ሰዎች እንደሚኖሩም ዮሐንስ ቀጥሎ ይነግረናል:- “አየሁም፣ እነሆም ነጭ ደመና፣ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፣ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ሌላ መልአክም [አራተኛው] ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው:- የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፣ የምድሪቱ መከር ጠውልጐአልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች።”—ራእይ 14:14-16
22. (ሀ) የወርቅ አክሊል ያደረገውና በነጭ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ማን ነው? (ለ) የመከሩ ሥራ የሚደመደመው መቼ ነው? እንዴትስ?
22 በነጩ ደመና ላይ የተቀመጠው ማን እንደሆነ የሚያጠራጥር ነገር የለውም። በነጭ ደመና ላይ የተቀመጠው የሰው ልጅ የሚመስልና የወርቅ አክሊል ያለው ስለሆነ ዳንኤል በራእይ ተመልክቶት የነበረው መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማርቆስ 14:61, 62) ይሁን እንጂ እዚህ ላይ በትንቢት የተነገረው መከር ምንድን ነው? ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በመከር መስሎ ነበር። (ማቴዎስ 9:37, 38፤ ዮሐንስ 4:35, 36) ይህ የመከር ሥራ ድምድማት ላይ የሚደርሰው በዚህ በጌታ ቀን ኢየሱስ የንግሥና ዘውድ ከጫነ በኋላ የአባቱ ወኪል ሆኖ የቅጣት ፍርድ በሚፈጽምበት ጊዜ ነው። ስለዚህ በንግሥና የቆየበት ከ1914 ጀምሮ ያለው ጊዜ መከር የሚሰበሰብበት አስደሳች ጊዜ ሆኖአል።—ከዘዳግም 16:13-15 ጋር አወዳድር።
23. (ሀ) አጨዳ እንዲጀመር የተሰጠው ትዕዛዝ የሚመጣው ከማን ነው? (ለ) ከ1919 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምን የአጨዳ ሥራ ሲከናወን ቆይቶአል?
23 ኢየሱስ ንጉሥና ፈራጅ ቢሆንም አምላኩ ይሖዋ እስኪነግረው ድረስ አጨዳውን አይጀምርም። ይህ የይሖዋ ቃል የሚመጣው ከቤተ መቅደሱ ሲሆን የሚናገረውም በመልአኩ አማካኝነት ነው። ኢየሱስም ወዲያውኑ ትዕዛዙን ተቀበለ። በመጀመሪያ ደረጃ ከ1919 ጀምሮ በነበረው ጊዜ መላእክቱ 144,000ዎቹን የማጨዱን ሥራ እንዲያጠናቅቁ አደረገ። (ማቴዎስ 13:39, 43፤ ዮሐንስ 15:1, 5, 16) ከዚያም የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች የመከር ስብሰባ ሥራ ቀጠለ። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:9) ከ1931 እስከ 1935 በነበሩት ዓመታት በቀላሉ የማይቆጠሩ የሌሎች በጎች ክፍል አባሎች ብቅ ማለት እንደ ጀመሩ ከታሪክ መረዳት እንችላለን። በ1935 ይሖዋ የዮሐንስ ክፍል አባሎችን የማስተዋል ችሎታ በመክፈት በራእይ 7:9-17 ላይ የተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሰዎች እነማን እንደሆኑ እንዲረዱ አስቻላቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ሕዝቦች ለመሰብሰቡ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሲደረግ ቆይቶአል። እስከ 2005 ድረስ የእነዚህ ሕዝቦች ቁጥር ከስድስት ሚልዮን በላይ ደርሶአል። ጭማሪው አሁንም አላቆመም። በእርግጥም የሰውን ልጅ የሚመስለው መልአክ በዚህ የፍጻሜ ዘመን እጅግ የተትረፈረፈና አስደሳች መከር ሰብስቦአል።—ከዘጸአት 23:16ና ከ34:22 ጋር አወዳድር።
የምድሪቱን ወይን መርገጥ
24. በአምስተኛው መልአክ እጅ ውስጥ ምን አለ? ስድስተኛውስ መልአክ ምን አለ?
24 የደህንነቱ መከር ተሰብስቦ ካለቀ በኋላ ሌላ መከር የሚጀምርበት ጊዜ ይመጣል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሌላ መልአክም [አምስተኛው] በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፣ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ [ስድስተኛው] ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን:- ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ።” (ራእይ 14:17, 18) የመላእክት ሠራዊት በጌታ ቀን ብዙ የመከር ስብሰባ ሥራ አከናውነዋል። መልካሙን ከመጥፎው ለይተዋል።
25. (ሀ) አምስተኛው መልአክ ከመቅደሱ ውስጥ መውጣቱ ምን ያመለክታል? (ለ) አጨዳው እንዲጀምር ትዕዛዝ የተሰጠው ከመሰዊያው በመጣው መልአክ መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
25 አምስተኛው መልአክ የመጣው ይሖዋ ከሚገኝበት ከቤተ መቅደሱ ነው። ስለዚህ የመጨረሻውም የመከር ሥራ የሚከናወነው እንደ ይሖዋ ፈቃድ ነው። መልአኩ ‘ከመሰዊያው በወጣ ሌላ መልአክ’ አማካኝነት በሚተላለፍ መልእክት ሥራውን እንዲጀምር ታዝዞአል። ይህ ቁም ነገር ልብ ልንለው የሚገባ ነው። ምክንያቱም ከመሰዊያው ሥር የነበሩ ነፍሳት “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” ሲሉ ጠይቀው ነበር። (ራእይ 6:9, 10) የምድሪቱ ወይን ሲታጨድ ይህ የበቀል ጥያቄ ምላሽ ያገኛል።
26. “የምድሩ የወይን ዘለላ” ምንድን ነው?
26 ይሁን እንጂ “በምድር ያለው የወይን ዛፍ ዘለላ” ምንድን ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የአይሁድ ብሔር የይሖዋ የወይን ዛፍ እንደሆነ ተገልጾአል። (ኢሳይያስ 5:7፤ ኤርምያስ 2:21) በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስና ከእርሱ ጋር በአምላክ መንግሥት የሚያገለግሉት ሰዎች የወይን ዛፍ እንደሆኑ ተነግሮአል። (ዮሐንስ 15:1-8) እዚህ ላይ ትኩረት የተደረገበት የወይን ዛፍ ባሕርይ ፍሬ የሚያፈራ መሆኑ ነው። የእውነተኛው ክርስትና ዛፍ ይሖዋን የሚያስመሰግን ፍሬ አስገኝቶአል። (ማቴዎስ 21:43) ስለዚህ “በምድር ያለው የወይን ዛፍ ዘለላ” ይህ እውነተኛ የወይን ተክል ሊሆን አይችልም። “በምድር ያለው የወይን ዛፍ ዘለላ” የክህደት ክርስትና ግንባር ቀደም አባል የሆነችበት ታላቂቱ ባቢሎን በነገሰችባቸው መቶ ዘመናት በሙሉ ያፈራቻቸው አጋንንታዊ ዘለላዎች የሚገኝበትን የሰይጣን ብልሹ የሚታይ ሥርዓት ያመለክታል።—ከዘዳግም 32:32-35 ጋር አወዳድር።
27. (ሀ) ማጭድ የያዘው መልአክ የምድሩን የወይን ዘለላ ማጨድ ሲጀምር ምን ይሆናል? (ለ) የአጨዳው ስፋት ምን ያህል እንደሚሆን የሚያመለክቱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?
27 የቅጣቱ ፍርድ መፈጸም ይኖርበታል! “መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፣ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቆርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቁጣ መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፣ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ።” (ራእይ 14:19, 20) ይሖዋ በዚህ የወይን ዘለላ ላይ መቆጣቱን ቀደም ሲል አስታውቆአል። (ሶፎንያስ 3:8) በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የተነገረው ትንቢት የወይኑ መጥመቂያ በሚረገጥበት ጊዜ ጠቅላላ ብሔራት እንደሚጠፉ በማያሻማ ሁኔታ ገልጾአል። (ኢሳይያስ 63:3-6) ኢዩኤልም ብዙ “ሕዝቦች” “በፍርድ ሸለቆ” ውስጥ ባለው “መጥመቂያ” ተረግጠው እንደሚጠፉ ተናግሮአል። (ኢዩኤል 3:12-14) በእውነትም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታላቅ መከር ነው። በዮሐንስ ራእይ መሠረት የወይን ፍሬዎቹ ብቻ ሳይሆን መላው የወይን ዛፍ ተቆርጦ በወይኑ መጥመቂያ ውስጥ ይጣልና ይረገጣል። ስለዚህ የምድሩ የወይን ዛፍ ተረግጦ ይጠፋል። ዳግመኛም ሊያቆጠቁጥ አይችልም።
28. የምድሩን ወይን የሚረግጠው ማን ነው? የወይኑ መጥመቂያ የሚረገጠው “ከከተማይቱ ውጪ” መሆኑ ምን ማለት ነው?
28 የወይኑን ዘለላ የረገጡት ፈረሶች ናቸው። ከወይኑ ተረግጦ የወጣው ደም “እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስ” ነበር። “ፈረሶች” የሚለው ቃል የጦርነት ዘመቻን የሚያመለክት ስለሆነ ይህ ጊዜ የጦርነት ጊዜ መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስን ተከትለው በሰይጣን ሥርዓት ላይ ወደሚደረገው የመጨረሻ ዘመቻ የሚከቱት የሰማይ ሠራዊቶች “ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ” እንደሚረግጡ ተነግሮአል። (ራእይ 19:11-16) የምድሪቱን ወይን የሚረግጡት እነዚሁ መላእክት እንደሆኑ ግልጽ ነው። መጥመቂያው የሚረገጠው ከከተማይቱ ውጭ ማለትም ከሰማያዊት ጽዮን ውጭ ነው። በእርግጥም የምድሪቱ ወይን በዚችው ምድር ላይ መረገጡ ተገቢ ነው። በተጨማሪም የሚረገጠው ከከተማው ውጭ ስለሆነ ሰማያዊቱን ጽዮን በምድር ላይ ከሚወክሉት ከሴቲቱ ዘሮች በቀሩት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አይደርስባቸውም። እነዚህም ሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ውስጥ ተሸሽገው ከአደጋው ያመልጣሉ።—ኢሳይያስ 26:20, 21
29. ከመጥመቂያው የሚወጣው ደም ምን ያህል ጥልቀት ይኖረዋል? ይህስ ምን ያመለክታል?
29 ይህ አስደናቂ ራእይ የምድር መንግሥታት በዳንኤል 2:34, 44 ላይ በተገለጸው መንግሥታዊ ዓለት ከመቀጥቀጣቸው ጋር ተመሳሳይነት አለው። ፍጹም የሆነ አጠቃላይ ጥፋት ይኖራል። ከወይኑ መጥመቂያ የሚወጣው የደም ወንዝ ከፍተኛ ጥልቀት ያለው ነው። እስከ ፈረሶቹ ልጓም ድረስ የሚደርስና የ1,600 ምዕራፍ ርዝመት ያለው ነው።a ይህ የአራትን ካሬ በአሥር ካሬ በማባዛት (4 × 4 × 10 × 10) የተገኘው ከፍተኛ ቁጥር የጥፋቱ ውጤት መላዋን ምድር የሚያጠቃልል እንደሚሆን ያመለክታል። (ኢሳይያስ 66:15, 16) ጥፋቱ ተመልሶ ሊጠገን የማይችልና ፍጹም ይሆናል። ከዚያ በኋላ የምድሪቱ የሰይጣን ወይን ግንድ ሥር ሊሰድ ወይም ሊያቆጠቁጥ ፈጽሞ አይችልም።—መዝሙር 83:17, 18
30 በፍጻሜው ዘመን ውስጥ የምንኖር እንደመሆናቸን መጠን የእነዚህ ሁለት መከሮች ራእይ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። የሰይጣንን የወይን ዘለላ ፍሬዎች ለማየት ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። ጽንስ ማስወረድና ሌሎች የነፍስ ግድያ ተግባሮች፣ ግብረ ሰዶም፣ አጭበርባሪነትና የተፈጥሮ ፍቅር መጥፋት ይህንን ዓለም በይሖዋ ፊት በጣም አስጸያፊ አድርጎታል። የሰይጣን የወይን ዘለላ “የመርዛማ ተክል ፍሬና እሬት” አፍርቶአል። የአጥፊነት ባሕርዩና በጣዖት አምልኮ ላይ የተመሠረተው አኗኗሩ የሰው ልጆችን ታላቅ ፈጣሪ የሚያዋርድ ሆኖአል። (ዘዳግም 29:18፤ 32:5፤ ኢሳይያስ 42:5, 8) ለይሖዋ ውዳሴ ኢየሱስ በመሰብሰብ ላይ ባለው የጤናማ ፍሬዎች የመከር ሥራ ከዮሐንስ ክፍል ጋር ለመተባበር መቻል በጣም ትልቅ መብት ነው። (ሉቃስ 10:2) ሁላችንም በዚህ ዓለም የወይን ዘለላ ላለመበከል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የይሖዋ የቁጣ ፍርድ በሚፈጸምበት ጊዜ ከምድሪቱ የወይን ዘለላ ጋር አብረን እንዳንረገጥ እንጠንቀቅ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
30. የሰይጣን የወይን ዘለላ ምን ዓይነት ፍሬዎች አፍርቶአል? ምንስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል?
[በገጽ 208 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘የዝሙትዋ ወይን ጠጅ’
ከታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ አባላት አንዷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነች። ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትገዛው በሮማ ሊቀ ጳጳስ ሲሆን እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስ የሐዋርያው ጴጥሮስ ወራሽ እንደሆነ ታምናለች። ስለእነዚህ የጴጥሮስ ወራሽ ናቸው ስለሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት በጽሑፍ ታትመው ከወጡት መረጃዎች የሚከተሉት ይገኙበታል:-
ፎርሞሰስ (891-96):- “ከሞተ ከዘጠኝ ወር በኋላ የፎርሞሰስ አስከሬን ከጳጳሳት የቀብር ቦታ ወጥቶ አዲስ የተሾመው እስጢፋኖስ የተባለ ጳጳስ ሊቀመንበር በሆነበት ሸንጎ ፊት ለፍርድ ቀረበ። የሞተው ሊቀ ጳጳስ ለጵጵስናው ተገቢ ያልሆነ የስልጣን ምኞት ነበረው የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ የሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ከንቱ ናቸው የሚል ብያኔ ተወስኖበታል። . . . አስከሬኑ ለብሶት የነበረው የጵጵስና ልብስ ከተገፈፈ በኋላ የቀኝ እጁ ጣቶች ተቆርጠውበታል።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ
እስጢፋኖስ 6ኛ (896-97):- “የፍሮሞሰስ አስከሬን ከተፈረደበት ከጥቂት ወራት በኋላ ትልቅ ረብሻ ተነስቶ የሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ ዘመነ ጵጵስና ፍጻሜ ሆነ። በትረ ጵጵስናውን ተነጥቆ በወህኒ ቤት ከቆየ በኋላ ተሰቅሎ ተገደለ።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ
ሰርግዮስ 3ኛ (904-11):- “ከእርሱ በፊት የነበሩት ሁለት ጳጳሳት . . . በወህኒ ቤት እንዳሉ ተሰቅለው ተገደሉ። . . . በሮማ በነበረ ጊዜ የቲዎፊላክተስ ቤተሰቦች ይረዱት ነበር። በዚህ ጊዜ የቲዎፊላክተስ ልጅ ከነበረችው ከማሮዚያ ወንድ ልጅ ወልዶአል ተብሎ ይገመታል። ይህም ልጁ (ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ 11ኛ) ሆነ።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ
እስጢፋኖስ 7ኛ (928-31):- “ዮሐንስ 10ኛ፣ ዘመነ ጵጵስናው ሊፈጸም በተቃረበበት ጊዜ . . . የሮማ ቅድስት እናት ትባል ከነበረችው ከማሮዚያ ጋር ተጣላና ታስሮ ተገደለ። ከዚያ በኋላ ማሮዚያ የጵጵስናውን ሹመት ለሊቀ ጳጳስ ሊዮ 6ኛ ሰጠች። እርሱም ለስድስት ወር ተኩል ብቻ በሹመቱ ላይ ከቆየ በኋላ ሞተ። በእርሱም እግር እስጢፋኖስ 7ኛ ተተካ። ለእርሱም ሹመት ምክንያት የሆነችው ማሮዚያ ሳትሆን አትቀርም። . . . በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ትቆጣጠረው የነበረችው ማሮዚያ ስለነበረች ምንም ዓይነት ሥልጣን አልነበረውም።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ
ዮሐንስ 11ኛ (931-35):- “እስጢፋኖስ 7ኛ ሲሞት . . . የቲዎፊላክተስ ቤተሰብ የሆነችው ማሮዚያ ገና የ20 ዓመት ወጣት የነበረውን ልጅዋን ዮሐንስን ሊቀ ጳጳስ አድርጋ ሾመች። . . . ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ከእናቱ ቁጥጥር ወጥቶ አያውቅም ነበር።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ
ዮሐንስ 12ኛ (955-64):- “የጵጵስና ሹመት በተቀበለ ጊዜ ገና አስራ ስምንት ዓመት አልሞላውም ነበር። ለመንፈሳዊ ነገሮች ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳልነበረውና አስነዋሪ ፈንጠዝያዎችንና ወራዳ ድርጊቶችን በጣም ይወድ እንደነበረ የታወቀ ነበር።”—ዘ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ኦፍ ፖፕስ
ቤኔዲክት 9ኛ (1032-44፤ 1045፤ 1047-48):- “የጵጵስና ሹመቱን ለክርስትና አባቱ ከሸጠለት በኋላ መልሶ ነጥቆ በመውሰዱ የታወቀ ሰው ነበር።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ
ስለዚህ እነዚህም ሆኑ ሌሎቹ ሊቀ ጳጳሳት በታማኝነት ኖሮ የሞተውን የጴጥሮስን አርዓያ ከመከተል ይልቅ የክፋትና የተንኮል አርዓያዎች ሆነዋል። ደም አፍሳሽነትና መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ምንዝር እንዲስፋፋ አድርገዋል። ኤልዛቤልን በመሰለው ጠባያቸው ይገዙት የነበረውን ቤተ ክርስቲያን አርክሰዋል። (ያዕቆብ 4:4) በ1917 የወጣው ያለቀለት ምሥጢር የተባለ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተዘጋጀ መጽሐፍ እነዚህን ታሪካዊ ሐቆች በዝርዝር አውጥቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ‘ምድሪቱን በልዩ ልዩ መቅሰፍት ከመቱባቸው’ መንገዶች አንደኛው ይህ ነበር።—ራእይ 11:6፤ 14:8፤ 17:1, 2, 5
[በገጽ 206 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የነገሠው ክርስቶስ በመላእክት እየታገዘ ፍርዱን ያስፈጽማል
[በገጽ 207 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባቢሎን በ539 ከዘአበ ከወደቀች በኋላ እሥረኞችዋ ነፃ ወጡ