ምዕራፍ አንድ
አምላክ ማን ነው?
1, 2. ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ምን ዓይነት ጥያቄ ያነሳሉ?
ልጆች ብዙ ጥያቄ ይጠይቃሉ። አንድ ነገር ስትነግራቸው አብዛኛውን ጊዜ ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። መልስ ልትሰጣቸው ስትሞክር ደግሞ ‘ግን ለምን?’ ብለው እንደገና ሊጠይቁ ይችላሉ።
2 ልጆችም ሆን አዋቂዎች፣ ሁላችንም ጥያቄ እንጠይቃለን። ለምሳሌ፣ የማናውቀውን ቦታ ሰዎች እንዲያሳዩን ልንጠይቅ እንችላለን፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ስንት ሰዓት እንደሆነ እንጠይቅ ይሆናል። በተጨማሪም ሕይወትንና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ መልስ ያላገኘንላቸው ጥያቄዎች ይኖሩ ይሆናል። ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚያረካ መልስ ካላገኘን ግን መልስ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ልናቆም እንችላለን።
3. ብዙ ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ማግኘት እንደማይችሉ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ለምናነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል? አንዳንድ ሰዎች መልስ እንደሚሰጥ ያምናሉ፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ከባድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ የሚችሉት አስተማሪዎች ወይም የሃይማኖት መሪዎች ብቻ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መልሱን አለማወቃቸው ስለሚያሳፍራቸው መጠየቅ አይፈልጉም። አንተስ ምን ትላለህ?
4, 5. ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ትፈልጋለህ? መልስ ለማግኘት ጥረት ማድረግህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?
4 አንተም ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ትፈልግ ይሆናል፦ ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን? በእርግጥ አምላክ አለ? ካለስ ምን ዓይነት አምላክ ነው?’ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:7) በመሆኑም ትክክለኛ መልስ እስክታገኝ ድረስ ጥረት ማድረግህን ቀጥል።
5 ‘መፈለግህን’ ከቀጠልክ መልሱን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኛለህ። (ምሳሌ 2:1-5) መልሱ ደግሞ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትማረው ነገር፣ በአሁኑ ጊዜ አስደሳች ሕይወት እንድትኖርና የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት እንድትጠብቅ ያስችልሃል። እስቲ ብዙ ሰዎችን ግራ ያጋባ አንድ ጥያቄ እንመልከት።
አምላክ ስለ እኛ ያስባል ወይስ ጨካኝ ነው?
6. አንዳንዶች አምላክ በሰዎች ላይ ስለሚደርሰው መከራ ግድ እንደሌለው የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
6 ብዙ ሰዎች አምላክ ስለ እኛ አያስብም ይላሉ። ‘አምላክ የሚያስብልን ቢሆን ኖሮ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ እንዲህ አይሆንም ነበር’ የሚል አመለካከት አላቸው። በዓለም ላይ ጦርነት፣ ጥላቻና መከራ ተስፋፍቶ ይገኛል። ሰዎች ይታመማሉ፣ ይሠቃያሉ እንዲሁም ይሞታሉ። በመሆኑም አንዳንዶች ‘አምላክ ስለ እኛ የሚያስብ ከሆነ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ ለምን ዝም ብሎ ይመለከታል?’ ብለው ይጠይቃሉ።
7. (ሀ) ሰዎች ‘አምላክ ጨካኝ ነው’ ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ለሚደርስብን መጥፎ ነገር ተጠያቂው አምላክ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
7 አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የሚያስተምሩት ትምህርት ሰዎች፣ ‘አምላክ ጨካኝ ነው’ ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። አንድ መጥፎ ነገር ሲደርስ ‘ይህን ያመጣው አምላክ ነው’ ይላሉ። በሌላ አባባል ‘ተጠያቂው አምላክ ነው’ ማለታቸው ነው። ሆኖም መጥፎ ነገር የሚያመጣብን አምላክ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ያዕቆብ 1:13 አምላክ ማንንም በክፉ ነገር እንደማይፈትን ይናገራል። ጥቅሱ “ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም” ይላል። ስለዚህ አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ ቢፈቅድም እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱብን የሚያደርገው እሱ አይደለም።—ኢዮብ 34:10, 12ን አንብብ።
8, 9. ለሚያጋጥሙን ችግሮች አምላክን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
8 ከወላጆቹ ጋር የሚኖርን አንድ ወጣት እንደ ምሳሌ እንመልከት። አባቱ ልጁን በጣም ይወደዋል፤ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንዲችልም አሠልጥኖታል። ሆኖም ልጁ በአባቱ ላይ ያምፅና ቤቱን ጥሎ ይወጣል። ከዚያም መጥፎ ነገር ይፈጽምና ችግር ላይ ይወድቃል። አባትየው ልጁ ከቤት ሲወጣ ስላልከለከለው፣ ልጁ ለደረሰበት ችግር ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? በፍጹም! (ሉቃስ 15:11-13) ልክ እንደዚህ አባት፣ አምላክም የሰው ልጆች በእሱ ላይ ሲያምፁና መጥፎ ነገር ሲያደርጉ አልከለከላቸውም። ስለዚህ አንድ መጥፎ ነገር ሲደርስ ይህን ያመጣው አምላክ እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን። አምላክን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይሆንም።
9 አምላክ እስካሁን መጥፎ ነገሮችን ያላስወገደበት በቂ ምክንያት አለው። አምላክ ይህን ያላደረገበትን ምክንያት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል፣ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ ተብራርቷል። ሆኖም አምላክ እንደሚወደንና ለሚያጋጥሙን ችግሮች ተጠያቂው እሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እንዲያውም ለችግራችን መፍትሔ ሊሰጠን የሚችለው እሱ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 33:2
10. አምላክ ክፋትን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል የምንለው ለምንድን ነው?
10 አምላክ ቅዱስ ነው። (ኢሳይያስ 6:3) የሚያደርገው ነገር ሁሉ ንጹሕ፣ ከክፋት የጠራና መልካም ነው። በመሆኑም ልንተማመንበት እንችላለን። ሰዎች ግን እንደዚያ አይደሉም። አንዳንዴ ስህተት ይሠራሉ። በጣም ጥሩ የሚባል መሪ እንኳ መጥፎ ሰዎች የሚሠሩትን ክፋት ሁሉ ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል የለውም። የአምላክን ያህል ኃይል ያለው ማንም የለም። አምላክ ክፋትን ለዘላለም ማስወገድ ይችላል፤ ደግሞም ያስወግዳል። በተጨማሪም ክፋት ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።—መዝሙር 37:9-11ን አንብብ።
ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው አምላክ ምን ይሰማዋል?
11. አምላክ መከራ ሲደርስብህ ምን ይሰማዋል?
11 አምላክ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታና በአንተ ላይ የሚደርሰውን ችግር ሲመለከት ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ፍትሕን ይወዳል” ይላል። (መዝሙር 37:28) በመሆኑም አግባብ ያልሆነ ነገር ሲፈጸም ደስ አይለውም። በሰው ልጆች ላይ መከራ ሲደርስ ያዝናል። በጥንት ዘመን ምድር በክፋት ተሞልታ ነበር፤ አምላክ ይህን ሲመለከት ‘ልቡ አዝኖ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:5, 6) አምላክ አሁንም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ስለ አንተ እንደሚያስብ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 5:7ን አንብብ።
12, 13. (ሀ) ለሌሎች ፍቅር ሊኖረን የቻለው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ የሚደርሰውን መከራ ስናይ ምን ይሰማናል? (ለ) አምላክ ማንኛውንም ዓይነት መከራና ግፍ ያስወግዳል የምንለው ለምንድን ነው?
12 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በራሱ መልክ እንደፈጠረን ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:26) ይህ ሲባል የእሱ መልካም ባሕርያት እንዲኖሩን አድርጎ ፈጥሮናል ማለት ነው። በመሆኑም ጥሩ ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው ስታይ የምታዝን ከሆነ አምላክ ደግሞ ከአንተ በላይ እንደሚያዝን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ! ይህን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
13 መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ለሰዎች ፍቅር ሊኖረን የቻለው አምላክ አፍቃሪ ስለሆነ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኃይል ቢኖርህ ኖሮ በዓለም ላይ የምታየውን መከራና ግፍ ታስወግድ ነበር? ሰዎችን ስለምትወድ እንደዚያ እንደምታደርግ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለ አምላክስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ ኃይል አለው፤ እንዲሁም እኛን ስለሚወደን ማንኛውንም ዓይነት መከራና ግፍ ያስወግዳል። በዚህ መጽሐፍ ገጽ 4 እና 5 ላይ የተገለጹት አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ ይፈጸማሉ! ሆኖም እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ መሆን እንድትችል ስለ አምላክ ይበልጥ ማወቅ ያስፈልግሃል።
አምላክ እንድታውቀው ይፈልጋል
14. የአምላክ ስም ማን ነው? በስሙ እንድንጠቀም እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?
14 አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ሰው ጋር ስትተዋወቅ መጀመሪያ ምን ታደርጋለህ? ስምህን ትነግረዋለህ። አምላክ ስም አለው? ብዙ ሃይማኖቶች ስሙ እግዚአብሔር፣ አምላክ ወይም ጌታ እንደሆነ ያስተምራሉ፤ እነዚህ ግን መጠሪያ ስሞች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ “ንጉሥ” ወይም “ፕሬዚዳንት” እንደሚሉት ያሉ የማዕረግ ስሞች ናቸው። አምላክ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ገልጾልናል። መዝሙር 83:18 “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ይህም ይሖዋ ስሙን እንድታውቅና በስሙ እንድትጠቀም እንደሚፈልግ ያሳያል። ስሙን ያሳወቀን ወዳጁ እንድንሆን ስለሚፈልግ ነው።
15. ይሖዋ የሚለው ስም ምን ያመለክታል?
15 ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ትልቅ ትርጉም አለው። አምላክ የገባውን ቃልም ሆነ ዓላማውን መፈጸም እንደሚችል ያመለክታል። እሱ የሚሳነው ነገር የለም። ይሖዋ የሚለው ስም ለሌላ ለማንም ሊሰጥ አይችልም።a
16, 17. (ሀ) “ሁሉን ቻይ” የሚለው የማዕረግ ስም ምን ያመለክታል? (ለ) “የዘላለም ንጉሥ” የሚለው የማዕረግ ስም ምን ያሳያል? (ሐ) “ፈጣሪ” ሊባል የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
16 ቀደም ሲል የተጠቀሰው መዝሙር 83:18 ስለ ይሖዋ ሲናገር ‘አንተ ብቻ ልዑል ነህ’ ይላል። በተጨማሪም ራእይ 15:3 እንዲህ ይላል፦ “ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ሥራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው። የዘላለም ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።” “ሁሉን ቻይ” የሚለው የማዕረግ ስም ምን ያመለክታል? ይሖዋ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከማንም በላይ ኃያል መሆኑን ያመለክታል። “የዘላለም ንጉሥ” የሚለው የማዕረግ ስም ደግሞ ይሖዋ መጀመሪያም መጨረሻም እንደሌለው ያሳያል። መዝሙር 90:2 እሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ እንደሆነ ይናገራል። ይህ የሚያስደንቅ አይደለም?
17 በተጨማሪም ፈጣሪ ሊባል የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ራእይ 4:11 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” አዎ፣ በሰማይ ያሉትን መላእክት፣ ከዋክብትን፣ ፍራፍሬንና የባሕር ዓሣዎችን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ይሖዋ ነው!
የይሖዋ ወዳጅ መሆን ትችላለህ?
18. አንዳንድ ሰዎች ስለ አምላክ ሲማሩ ምን ይሰማቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ምን ይላል?
18 አንዳንድ ሰዎች ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት ሲማሩ የፍርሃት ስሜት ያድርባቸዋል፤ በመሆኑም ‘በላይ በሰማይ የሚኖረው፣ ኃያልና ታላቅ የሆነው አምላክ ስለ እኔ እንዴት ሊያስብ ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ። ሆኖም አምላክ እንዲህ እንዲሰማን ይፈልጋል? በፍጹም። ይሖዋ ወደ እኛ መቅረብ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) አምላክ ወደ እሱ እንድትቀርብ የሚፈልግ ከመሆኑም ሌላ ‘እሱም ወደ አንተ እንደሚቀርብ’ ቃል ገብቷል።—ያዕቆብ 4:8
19. (ሀ) የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ከይሖዋ ባሕርያት መካከል አንተን ይበልጥ የሚማርኩህ የትኞቹ ናቸው?
19 ታዲያ የአምላክ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ከቀጠልክ ይሖዋንና ኢየሱስን ማወቅ ትችላለህ። ይህም የዘላለም ሕይወት ያስገኝልሃል። ለምሳሌ ‘አምላክ ፍቅር እንደሆነ’ ተምረናል። (1 ዮሐንስ 4:16) ይሁንና ሌሎች ግሩም ባሕርያትም አሉት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ ይነግረናል። (ዘፀአት 34:6) ይሖዋ ‘ጥሩና ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው። (መዝሙር 86:5) በተጨማሪም ታጋሽና ታማኝ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9፤ ራእይ 15:4) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ስለ አምላክ ግሩም ባሕርያት ይበልጥ እያወቅክ ትሄዳለህ።
20-22. (ሀ) አምላክን የማናየው ቢሆንም ወደ እሱ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን እንድታቆም ቢገፋፉህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
20 ሆኖም አምላክን የማታየው ከሆነ ወደ እሱ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ይሖዋን በዓይን የምታየው ያህል እንድታውቀው ያስችልሃል። (መዝሙር 27:4፤ ሮም 1:20) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ስታውቅ ደግሞ እየወደድከውና እየቀረብከው ትሄዳለህ።
21 በተጨማሪም ይሖዋ አባታችን እንደሆነ ትገነዘባለህ። (ማቴዎስ 6:9) ይሖዋ ሕይወት የሰጠን ከመሆኑም ሌላ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። አፍቃሪ የሆነ አባት ለልጆቹ የሚመኘው ይህን ነው። (መዝሙር 36:9) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የይሖዋ ወዳጅ መሆን እንደምትችል ይናገራል። (ያዕቆብ 2:23) በእርግጥም የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ የሆነው የይሖዋ ወዳጅ መሆን ትልቅ መብት ነው!
22 አንዳንዶች ሃይማኖትህን ትቀይራለህ ብለው ስለሚፈሩ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና አይፈልጉ ይሆናል። ሆኖም ጥናትህን ካቆምክ የይሖዋ ወዳጅ መሆን አትችልም፤ በመሆኑም ይህ እንዲሆን አትፍቀድ። ከይሖዋ የተሻለ ወዳጅ ፈጽሞ ልታገኝ አትችልም!
23, 24. (ሀ) ጥያቄ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የሌለብህ ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?
23 መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠናበት ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን መረዳት ሊከብድህ ይችላል፤ በመሆኑም ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብህም። ኢየሱስ እንደ ትናንሽ ልጆች ትሑት መሆን እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:2-4) ልጆች ትሑት ስለሆኑ ብዙ ጥያቄዎች ይጠይቃሉ። አምላክ ለጥያቄዎችህ መልስ እንድታገኝ ይፈልጋል። በመሆኑም የምታጠናው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መርምር።—የሐዋርያት ሥራ 17:11ን አንብብ።
24 ስለ ይሖዋ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።
a ይሖዋ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የማይገኝ ከሆነ ወይም ስለዚህ ስም ትርጉምና አጠራር ይበልጥ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግክ ተጨማሪ ሐሳብ 1ን ተመልከት።