የዘላለሙን ንጉሥ አወድሱ!
“ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው።”—መዝሙር 10:16 አዓት
1. ዘላለማዊነትን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
ዘላለም ማለት ምን ማለት ነው ትላላችሁ? ጊዜ ለዘላለም የሚቀጥል ይመስላችኋል? ጊዜ መጀመሪያ እንዳልነበረው ምንም አያጠያይቅም። ታዲያ ወደፊት መጨረሻ የሌለው የማይሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚወደስ ይናገራል። (መዝሙር 41:13) ይህ ምን ማለት ነው? ከጊዜ ጋር ስለሚመሳሰለው ስለ ሕዋ ብንመለከት ነገሩን ለመረዳት ይቀለናል።
2, 3. (ሀ) ስለ ሕዋ ያገኘነው እውቀት ዘላለማዊነትን በተመለከተ ግንዛቤ የሚሰጠን እንዴት ነው? (ለ) የዘላለሙን ንጉሥ ለማምለክ መፈለግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
2 ሕዋ ምን ያህል ስፋት አለው? ዳርቻ አለውን? እስከ ዛሬ 400 ዓመት ድረስ ምድራችን የአጽናፈ ዓለሙ እምብርት እንደሆነች ይታሰብ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጋሊሊዮ የሩቁን አቅርቦ የሚያሳይ መነጽር በመሥራቱ ሰማያትን በስፋት መመልከት ተቻለ። ጋሊሊዮ በጣም በርካታ የሆኑ ከዋክብት ለማየት በመቻሉ ምድርና ሌሎቹ ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ መሆናቸውን ለማሳመን ቻለ። ፍኖተ ኀሊብ የተረጨ ወተት መስሎ መታየቱ ቀረ። መቶ ቢልዮን የሚያክሉ ከዋክብት የሚገኙበት ረጨት መሆኑ ተረጋገጠ። እስከ ዕድሜያችን ፍጻሜ ድረስ ብንቆጥር እንኳን እነኚህን የሚያክሉ ከዋክብት ቆጥረን ለመጨረስ አንችልም። ቆየት ብሎ ደግሞ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በቢልዮን የሚቆጠሩ ረጨቶችን አገኙ። እነዚህ የከዋክብት ረጨቶች በጣም ኃይለኛ የሆነው መነጽር እንኳን ሊያይ ከሚችለው የበለጠ ርቀት ባለው ሕዋ ላይ የተናኙ ናቸው። ሕዋ ዳርቻ ያለው አይመስልም። የጊዜም ዘላለማዊነት እንዲሁ ነው። ጊዜ ዳርቻ የለውም።
3 የዘላለማዊነት ሐሳብ ደካማ የሆነው ሰብዓዊ አእምሮአችን ሊረዳው ከሚችለው በላይ የሆነ ይመስላል። ይሁን እንጂ ዘላለማዊነትን በሚገባ ሊረዳ የሚችል አንድ አካል አለ። አዎን፣ ይህ አካል በቢልዮን በሚቆጠሩ ረጨቶች ውስጥ የሚገኙትን በኳድሪልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት ሊቆጥር እንዲያውም በየስማቸው ሊጠራ ይችላል! ይህ አካል እንዲህ ይላል፦ “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” አዓት] የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፣ አይታክትም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም።” (ኢሳይያስ 40:26, 28) እንዴት ያለ አስደናቂ አምላክ ነው! በእርግጥም ልናመልከው የሚገባ አምላክ ነው!
‘የዘላለም ንጉሥ’
4. (ሀ) ዳዊት ለዘላለሙ ንጉሥ ያለውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በታሪክ ዘመናት ከታዩት ታላላቅ ሳይንቲስቶች አንዱ ስለ አጽናፈ ዓለም አመጣጥ የሰጠው መደምደሚያ ምንድን ነው?
4 ዳዊት በመዝሙር 10:16 [አዓት] ላይ ስለዚህ ፈጣሪ አምላክ ሲናገር “ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው።” ብሏል። በመዝሙር 29:10 ላይ ደግሞ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” አዓት] ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል” ብሏል። አዎን፣ ይሖዋ የዘላለም ንጉሥ ነው! በተጨማሪም ዳዊት ይህ ከፍተኛ የሆነ ንጉሥ በሕዋ ላይ የምናያቸው አካላት በሙሉ ሠሪና ፈጣሪ መሆኑን ሲመሠክር በመዝሙር 19:1 ላይ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ይላል። 2,700 ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ሰር አይዛክ ኒውተን የተባለው ዝነኛ የሳይንስ ሊቅ እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ ከዳዊት ጋር የሚስማማ መሆኑን ገልጿል፦ “ይህ እጅግ ውብ የሆነ የፀሐዮች፣ የፕላኔቶችና የኮሜቶች ቅንብር ሊገኝ የሚችለው ዓላማና ሉዓላዊነት ካለው በጣም ኃያልና አዋቂ ከሆነ አካል ብቻ ነው።”
5. ኢሳይያስና ጳውሎስ የጥበብን ምንጭ በተመለከተ የጻፉት ምንድን ነው?
5 እጅግ ሰፊ የሆነው ‘ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዘው ዘንድ’ የማይችለው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ ለዘላለም የሚኖር መሆኑን ማወቃችን ምን ያህል ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል! (1 ነገሥት 8:27) በኢሳይያስ 45:18 ላይ “ሰማያትን የፈጠረ . . . ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም” እንደሆነ የተገለጸው ይሖዋ ሟች የሆነው የሰው ልጅ አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው የበለጠ በጣም ሰፊ የሆነ ጥበብ ምንጭ ነው። በ1 ቆሮንቶስ 1:19 ላይ ጉልህ በሆነ ሁኔታ እንደተገለጸው ይሖዋ “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ” ብሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ላይ በማከል ቁጥር 20 ላይ “ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?” ብሏል። አዎ፣ ጳውሎስ በምዕራፍ 3 ቁጥር 19 ላይ ቀጥሎ እንደተናገረው “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው።”
6. መክብብ 3:11 “ዘላለማዊነትን” በተመለከተ የሚናገረው ምንድን ነው?
6 የጠፈር አካላት ንጉሥ ሰሎሞን እንደሚከተለው በማለት የተናገረላቸው የአምላክ ፍጥረታት ክፍል ናቸው፦ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው።” (መክብብ 3:11) በእርግጥም “ዘላለምነት” ምን እንደሆነ ለማወቅ የመሞከር ፍላጎት በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የተተከለ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ለማወቅ ይችል ይሆን?
አስደናቂ የሕይወት ተስፋ
7, 8. (ሀ) የሰው ልጆች ምን አስደናቂ የሕይወት ተስፋ ይጠብቃቸዋል? ይህን ተስፋ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) መለኮታዊ ትምህርት ለዘላለም የሚቀጥል በመሆኑ መደሰት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ክርስቶስ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎቱ ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ ያለውን እውቀት ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስፈልገናል። ይህን ካደረግን ታላቅ የሆነውን የአምላክ ዓላማ፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል በልጁ በኩል ያዘጋጀውን ዝግጅት ጭምር በትክክል ለማወቅ እንችላለን። በ1 ጢሞቴዎስ 6:19 ላይ “እውነተኛው ሕይወት” የተባለው ይህ ሕይወት ነው። ይህም ኤፌሶን 3:11 [አዓት] “በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በኩል ያወጣው ዘላለማዊ ዓላማ” ከተባለው ዓላማ ጋር የሚስማማ ነው።
8 አዎን፣ እኛ ኃጢአተኛ የሆንን የሰው ልጆች መለኮታዊ ትምህርት በመቀበልና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ለዘላለም ሕይወት ልንበቃ እንችላለን። ይህ መለኮታዊ ትምህርት እስከ መቼ ድረስ የሚቀጥል ነው? የሰው ልጅ የፈጣሪያችንን ጥበብ ደረጃ በደረጃ መማር ስለሚኖርበት እስከ ዘላለም ይቀጥላል። የይሖዋ ጥበብ ዳርቻ የለውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በመገንዘቡ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፤ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። (ሮሜ 11:33) 1 ጢሞቴዎስ 1:17 ይሖዋን “የዘላለም ንጉሥ” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው!
ይሖዋ በፍጥረት ሥራዎቹ ያሳየው ጥበብ
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ምድር ለሰው ልጆች ስጦታ እንድትሆን ሲያዘጋጅ ምን ታላላቅ ሥራዎችን አከናውኗል? (ለ) የይሖዋ የላቀ ጥበብ በፍጥረት ሥራዎቹ የታየው እንዴት ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።)
9 የዘላለሙ ንጉሥ ለእኛ ለሰው ልጆች የሰጠንን አስደናቂ ውርሻ ተመልከቱ። መዝሙር 115:16 እንደሚነግረን “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።” ምድር ዕፁብ ድንቅ ስጦታ እንደሆነች አትስማሙም? እንደምትስማሙ አያጠራጥርም! በተጨማሪም ፈጣሪያችን ምድር መኖሪያችን እንድትሆን ሲያዘጋጅ ያሳየውን የላቀ አርቆ አስተዋይነት በጣም እናደንቃለን።—መዝሙር 107:8
10 እያንዳንዳቸው የሰባት ሺህ ዓመት ርዝመት ባላቸው በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ በተገለጹት ስድስት የፍጥረት “ቀናት” በጣም አስደናቂ ነገሮች ተከናውነዋል። አምላክ የፍጥረት ሥራውን ሲያጠናቅቅ ምድር በለምለም የሣር ምንጣፍ የተሸፈነች፣ በሚያማምሩ ደኖችና የተዋቡ ኅብረ ቀለማት ባላቸው አበቦች ያሸበረቀች ሆነች። እጅግ ብዙ የሆኑ አስገራሚ የባሕር ፍጥረታት የሚርመሰመሱባት፣ የሚያምር ክንፍ ያሏቸው የአእዋፍ መንጋ የሚከንፉባት፣ ‘እንደየወገናቸው’ የተፈጠሩ በጣም በርካታ የሆኑ የቤት እንስሳትና የዱር አራዊት የሚቦርቁባት ቦታ ሆነች። ወንድና ሴት እንደተፈጠሩ ከተሰጠው መግለጫ በኋላ ዘፍጥረት 1:31 “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” በማለት ይነግረናል። ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች በጣም አስደሳች የሆነ አካባቢ ተዘጋጀ። አስደናቂ በሆኑት የምድር ፍጥረታት ሁሉ አፍቃሪ የሆነውን የፈጣሪያችንን ጥበብ፣ አርቆ አስተዋይነትና አሳቢነት ለማየት አንችልምን?—ኢሳይያስ 45:11, 12, 18
11. ሰሎሞን ይሖዋ በፍጥረት ወቅት የተጠቀመበትን ጥበብ ከፍ ከፍ ያደረገው እንዴት ነው?
11 የዘላለሙ ንጉሥ ጥበብ እጅግ ካስደነቃቸው ሰዎች አንዱ ሰሎሞን ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት የፈጣሪን ጥበብ ጠቅሷል። (ምሳሌ 1:1, 2፤ 2:1, 6፤ 3:13-18) ሰሎሞን “ምድር ግን ለዘላለም ነው” በማለት ያረጋግጥልናል። ዝናብ አዘል ደመናዎች የምድራችንን ጥማት በማርካት የሚጫወቱትን ሚና ጨምሮ አስደናቂ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎች እጅግ ተደንቆ ነበር። በዚህም ምክንያት “ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፣ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ” በማለት ጽፏል። (መክብብ 1:4, 7) ስለዚህ ዝናብና ወንዝ ምድርን ካጠጡና ካረኩ በኋላ ውኃዎች ከውቅያኖሶች ላይ ተነሥተው ወደ ደመናነት ይለወጣሉ። ይህን የመሰለ የምድርን ውኃዎች የሚያድስና የሚያጠራ ዑደት ባይኖር ኖሮ ይህች ምድር ምን ትመስል ነበር? እኛስ ምን እንሆን ነበር?
12, 13. ለአምላክ ፍጥረት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
12 ፍጥረት እርስ በርሱ የሚጠባበቅና የሚረዳዳ ስለመሆኑ ያለን አድናቆት ንጉሥ ሰሎሞን የመክብብን መጽሐፍ ሲደመድም በተናገረው ቃል ላይ እንደተገለጸው በተግባር የተደገፈ መሆን ይኖርበታል። “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፣ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።” (መክብብ 12:13, 14) አምላክን የሚያስከፋ አንዳች ነገር እንዳናደርግ መፍራት ይገባናል። ከዚህ ይልቅ ለቅድስናው ባለን አክብሮት ተገፋፍተን ልንታዘዘው ይገባል።
13 አዎን፣ የዘላለሙን ንጉሥ ዕፁብ ድንቅ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ልናወድሰው መፈለግ ይኖርብናል! መዝሙር 104:24 “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች” ይላል። ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች በደስታ “ነፍሴ ሆይ፣ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” አዓት] ባርኪ፣ ሃሌ ሉያ” በማለት ከዚህ መዝሙር የመጨረሻ ቁጥር ጋር የምንስማማ መሆናችንን እናሳይ።
የምድራዊ ፍጥረታት ቁንጮ
14. የሰው ልጆች አፈጣጠር ከእንስሳት አፈጣጠር የላቀ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
14 የይሖዋ ፍጥረት በሙሉ ዕፁብ ድንቅ ችሎታ የሚታይበት ነው። ይሁን እንጂ ከምድር ፍጥረታት በሙሉ የሰውን ያህል አስደናቂ የሆነ ፍጥረት የለም። አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት በስድስተኛው የይሖዋ የፍጥረት ቀን መቋጫ ላይ ነው። የሰው ልጅ ከዓሣዎች፣ ከአእዋፍና ከእንስሳት በጣም የሚበልጥ ፍጡር ነው። ከእነዚህ ፍጥረታት ብዙዎቹ ‘በተፈጥሮ ባሕርይ የወረሱት የየራሳቸው ጥበብ’ ያላቸው ቢሆኑም የሰው ልጅ ግን የማመዛዘን ችሎታ፣ ትክክለኛውን ከስሕተት ለመለየት የሚችል ሕሊና፣ ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ የማውጣት ችሎታና በተፈጥሮው የማምለክ ፍላጎት ተሰጥቶታል። ይህን ሁሉ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? የሰው ልጅ በደመ ነፍስ ከሚመሩት አራዊት ተሻሽሎ የመጣ ሳይሆን በአምላክ መልክና ምሳሌ የተፈጠረ በመሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ ራሱን “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር፣ መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” በማለት የገለጸውን የፈጣሪያችንን ባሕርያት ሊያንጸባርቅ የሚችለው ሰው ብቻ ነው።—ዘጸአት 34:6
15. ራሳችንን ዝቅ አድርገን ይሖዋን ማወደስ ያለብን ለምንድን ነው?
15 ይሖዋን በጣም አስደናቂ ስለሆነው የሰውነታችን አፈጣጠር እናወድሰው፣ እናመስግነው። ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ደማችን በ60 ሰኮንድ ውስጥ በመላ ሰውነታችን አንድ ጊዜ ይዞራል። ዘዳግም 12:23 እንደሚለው ‘ደም ነፍስ ስለሆነ’ ሕይወታችን በአምላክ ዘንድ በጣም ውድ ነው። ጠንካራ በሆኑት አጥንቶቻችን፣ የመተጣጠፍና የመዘረጋጋት ችሎታ ባላቸው ጡንቻዎቻችንና የሰውነታችንን እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሚቆጣጠሩት የነርቭ አውታሮች አናት ላይ የተቀመጠ የማንኛውም እንስሳ አእምሮ ሊተካከለው የማይችልና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ የሚያክል ግዙፍ ኮምፒዩተር እንኳን የማይተካከለው አንጎል አለን። ታዲያ ይህ ሁሉ ራስህን ዝቅ እንድታደርግና እንድታዋርድ አይገፋፋህምን? ሊገፋፋህ ይገባል። (ምሳሌ 22:4) በተጨማሪም አንድ ሌላ ነገር እንመልከት፦ ሳንባችን፣ ላንቃችን፣ ምላሳችን፣ ጥርሳችንና ከንፈራችን ተቀናጅተው በሺህ በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እንድንነጋገር ያስችሉናል። ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች” በማለት ለይሖዋ ተገቢ የሆነ የውዳሴ መዝሙር አቅርቧል። (መዝሙር 139:14) እኛም አስደናቂ የሆነውን ፈጣሪያችንና አምላካችንን ይሖዋን በማመስገንና በማወደስ ከዳዊት ጋር እንተባበር!
16. አንድ ዝነኛ ሙዚቀኛ ለይሖዋ ያቀረበው የውዳሴ መዝሙር ምን ይላል? አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚኖርብን ለየትኛው ትኩረት የሚስብ ግብዣ ነው?
16 ዮሴፍ ሃይደን የደረሰው የ18ኛው መቶ ዘመን የሙዚቃ ድርሰት ስንኝ እንደሚከተለው በማለት ይሖዋን ያወድሳል። “እናንት ድንቅ የሆናችሁ የአምላክ ሥራዎች እርሱን አመስግኑ! ለክብሩ ዘምሩ፣ ለግርማው ዘምሩ፣ ስሙን ባርኩና ከፍ ከፍ አድርጉ። የይሖዋ ውዳሴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፣ አሜን፣ አሜን።” በመዝሙራት ውስጥ በመንፈስ አነሣሽነት በተደጋጋሚ ጊዜያት የተጻፉት አገላለጾች ከዚህ የበለጠ ውበት አላቸው። ከእነዚህም መካከል በ107ኛው መዝሙር (የ1980 ትርጉም) ላይ አራት ጊዜ የቀረበው “ቸር ስለሆነና ፍቅሩም ዘላለማዊ ስለሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚለው ግብዣ ይገኝበታል። በዚህ ውዳሴ ትካፈላላችሁ? መካፈል ይኖርባችኋል፤ ምክንያቱም የማናቸውም አስደሳች የሆኑ ነገሮች ምንጭ የዘላለሙ ንጉሥ የሆነው ይሖዋ ነው።
ሌሎች አስደናቂ ሥራዎች
17. ‘የሙሴና የበጉ ቅኔ’ ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርገው እንዴት ነው?
17 የዘላለሙ ንጉሥ ባለፉት ስድስት ሺህ ዓመታትም በጣም አስደናቂ የሆኑ ሥራዎች አካሂዷል። በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ፣ በራእይ 15:3, 4 ላይ በአጋንንታዊ ጠላቶች ላይ ድል ስለተቀዳጁ ሰማያዊ ፍጥረታት እናነባለን። “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፣ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴንና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።” ይህ መዝሙር ‘የሙሴና የበጉ ቅኔ’ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።
18. በዘጸአት ምዕራፍ 15 ላይ የተዘከረው የትኛው አስደናቂ ሥራ ነው?
18 የዛሬ 3,500 ዓመት ገደማ ኃያል የነበረው የፈርዖን ሠራዊት በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ በጠፋ ጊዜ እስራኤላውያን በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልተው ይሖዋን በመዝሙር አወድሰውት ነበር። ዘጸአት 15:1, 18 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፣ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል።” የዚህ ዘላለማዊ ንጉሥ የጽድቅ ሕግጋት ልዕልናውን የናቁትን ጠላቶች በመፍረዱና በማጥፋቱ ተገልጿል።
19, 20. (ሀ) ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ ያቋቋመው ለምን ነበር? (ለ) በጉና ሌሎች ሰዎች ሰይጣን ላቀረበው ግድድር መልስ የሰጡት እንዴት ነው?
19 ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሸረኛው እባብ የመጀመሪያ ወላጆቻችን ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረገው በኤደን አትክልት ውስጥ ነበር። በዚህም ምክንያት ኃጢአትና አለፍጽምና ወደ ሁሉም የሰው ልጆች ተላለፉ። ሆኖም የዘላለሙ ንጉሥ ከመጀመሪያ ዓላማው ጋር የሚስማማና ጠላቶቹን በሙሉ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ በማጥፋት ገነታዊ ሁኔታዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል እርምጃ ወዲያው ወሰደ። የዘላለሙ ንጉሥ የእስራኤልን ብሔር አቋቋመና ይህን እንዴት እንደሚፈጽም በምሳሌ ለማሳየት ሲል ሕጉን ሰጣቸው።—ገላትያ 3:24
20 ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ብሔር ራሱ በክህደት አዘቅት ውስጥ ወደቀ። በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መጨረሻ ላይ መሪዎቹ የአምላክን አንድያ ልጅ ክፉኛ ተሠቃይቶ እንዲገደል ለሮማውያን አሳልፈው ሰጡ። (ሥራ 10:39፤ ፊልጵስዩስ 2:8) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ” ሆኖ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ፍጹም አቋሙን መጠበቁ የመጀመሪያው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ማንም በምድር ላይ የሚኖር ሰው ከባድ ፈተና ቢያጋጥመው ታማኝ ሆኖ ሊጸና አይችልም በማለት ላቀረበው ግድድር ግንባር ቀደም ምላሽ ሊያስገኝ ቻለ። (ዮሐንስ 1:29, 36፤ ኢዮብ 1:9-12፤ 27:5) ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎችም በአዳም ኃጢአት ምክንያት አለፍጽምና የወረሱ ቢሆንም ያጋጠማቸውን ሰይጣናዊ ጥቃት በሙሉ ተቋቁመው የኢየሱስን ፈለግ ለመከተል ችለዋል።—1 ጴጥሮስ 1:18, 19፤ 2:19, 21
21. ከሥራ 17:29-31 ጋር በተያያዘ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 አሁን ደግሞ ይሖዋ ለእነዚህ ታማኝ ሰዎች ዋጋቸውን የሚከፍልበትና በእውነትና በጽድቅ ጠላቶች ላይ የሚፈርድበት ቀን ደርሷል። (ሥራ 17:29-31) ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።
የክለሣ ሣጥን
◻ ይሖዋ “የዘላለም ንጉሥ” ነው ሊባል የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ የይሖዋ ጥበብ በፍጥረት ሥራዎቹ የታየው እንዴት ነው?
◻ የሰው ልጅ የምድራዊ ፍጥረታት ቁንጮ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
◻ ‘የሙሴና የበጉ ቅኔ’ የሚያስታውሱን የትኞቹን ሥራዎች ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አቻ የማይገኝለት የይሖዋ ጥበብ
የዘላለሙ ንጉሥ ጥበብ በምድር ላይ በሠራቸው ነገሮች በበርካታ መንገዶች ተንጸባርቋል። አጉር “የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው” በማለት የተናገረውን ልብ በሉ። (ምሳሌ 30:5) ከዚያ በኋላ አጉር ስለ አምላክ ሕያዋን ፍጥረታት፣ ስለ ትላልቆቹና ስለ ትናንሾቹ ፍጥረታት ይናገራል። ለምሳሌ ከ24 እስከ 28 ያሉት ቁጥሮች “በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፣ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው” በማለት ይገልጻሉ። እነዚህ ፍጥረታት ጉንዳኖች፣ ሽኮኮዎች፣ አንበጣዎችና እንሽላሊቶች ናቸው።
አዎን፣ እነዚህ እንስሳት ‘ከተፈጥሮ ባሕርያቸው ያገኙት ጥበብ’ አላቸው። ከተፈጥሮ ባገኙት ጥበብ ይመራሉ እንጂ እንደ ሰው ልጆች የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ የላቸውም። ስለነዚህ እንስሳት አስባችሁ ታውቃላችሁ? በጣም አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የተደራጁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ጉንዳኖች ንግሥቲቱን፣ ሠራተኛና ወታደር ጉንዳኖችን ጨምሮ በተለያዩ ቡድኖች የተደራጁ ናቸው። በአንዳንዶቹ የጉንዳን ዝርያዎች ሠራተኛ ጉንዳኖች በሠሩት በረት ውስጥ ጥቃቅን ነፍሳትን ያረባሉ። እነዚህንም ነፍሳት እንደ ላም ያልቧቸዋል። ወታደሮቹ ጉንዳኖች ደግሞ ለወረራ የመጡ ጠላቶችን ያባርራሉ። በምሳሌ 6:6 ላይ “አንተ ታካች፣ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን” የሚል ምክር ተሰጥቷል። ታዲያ እንዲህ ያለው የጥቃቅን ነፍሳት ምሳሌነት እኛ የሰው ልጆች ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ እንድንሆን ሊገፋፋን አይገባምን?—1 ቆሮንቶስ 15:58
የሰው ልጅ በጣም ግዙፍ አውሮፕላኖች ለመሥራት ችሏል። ይሁን እንጂ አእዋፍ፣ ከጥቂት ግራሞች ያልበለጠ ክብደት ያላትን ሐሚንግበርድ የተባለች ድንቢጥ መሳይ ወፍ ጨምሮ፣ እንዴት ያለ የሚያስደንቅ ቅልጥፍና ያላቸው ናቸው! አንድ ቦይንግ 747 ጄት አውሮፕላን ፓስፊክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ 180,000 ሊትር ነዳጅ ተሸክሞ፣ በጣም በተወሳሰቡ የበረራ መሣሪያዎች በሚታገዙና የረዥም ጊዜ ሥልጠና ባገኙ አብራሪዎች መብረር ይኖርበታል። በጣም ትንሽ የሆነችው ሐሚንግበርድ ግን ከሰሜን አሜሪካ ተነሥታ የሜክሲኮን ባሕረ ሰላጤ አቋርጣ ደቡብ አሜሪካ ለመድረስ የሚያስፈልጋት ነዳጅ ከአንድ ግራም ስብ አይበልጥም። ከባድ የነዳጅ ጭነት መሸከም፣ የበረራ ሥልጠና መውሰድ፣ የተወሳሰበ የበረራ ካርታ ወይም ኮምፒዩተር አያስፈልጋትም! ታዲያ ይህን የሚያክል ችሎታ ያገኘችው በአጋጣሚ ከተከሰተ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ነውን? በፍጹም ሊሆን አይችልም! ይህች ትንሽ ወፍ ከፈጣሪዋ ከይሖዋ አምላክ የተሰጣት የተፈጥሮ ጥበብ አላት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልዩ ልዩ የፍጥረት ሥራዎች ‘የዘላለሙን ንጉሥ’ ክብር ያንጸባርቃሉ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴና ሌሎች እስራኤላውያን ይሖዋ በቀይ ባሕር ላይ የተቀዳጀውን ድል እንዳከበሩ ሁሉ ከአርማጌዶን በኋላ ታላቅ ደስታ ይሆናል