ምዕራፍ 32
የአምላክ ቁጣ ወደ ፍጻሜ ደረሰ
1. ሰባቱ ጽዋዎች ፈስሰው ከማለቃቸው በፊት ምን ይፈጸማል? ታዲያ አሁን ስለ ጽዋዎቹ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
ዮሐንስ ቀደም ሲል ሰባቱን ጽዋዎች ለማፍሰስ የተመደቡትን መላእክት አስተዋውቆ ነበር። እነዚህ “የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት” እንደሆኑ ገልጾአል። (ራእይ 15:1፤ 16:1) እነዚህ ይሖዋ በምድር ላይ ለሚታየው ክፋት ያለውን ጥላቻ የሚገልጹ መቅሰፍቶች እስከመጨረሻ ድረስ መፍሰስ ይኖርባቸዋል። ፈስሰው በሚያልቁበት ጊዜ የአምላክ የቅጣት ፍርድ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። ከዚያ በኋላ የሰይጣን ዓለም ፈጽሞ አይኖርም! እነዚህ መቅሰፍቶች ለመላው የሰው ዘርና ለዚህ ክፉ ሥርዓት ገዥዎች ምን ትርጉም ይኖራቸዋል? ክርስቲያኖች ከዚህ ለጥፋት ከተወሰነው ዓለም ጋር በመቅሰፍቶቹ ከመጎዳት እንዴት ሊድኑ ይችላሉ? እነዚህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ሲሆኑ አሁን መልሳቸውን ያገኛሉ። የጽድቅን ድል አድራጊነት የሚናፍቁ ሁሉ ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተውን ነገር ለማወቅ ብርቱ ፍላጎት ይኖራቸዋል።
ይሖዋ “በምድሪቱ” ላይ የገለጸው ቁጣ
2. የመጀመሪያው መልአክ ጽዋውን በምድር ላይ በማፍሰሱ ምክንያት ምን ነገር ይፈጸማል? “ምድር” የምን ምሳሌ ነው?
2 የመጀመሪያው መልአክ ሥራውን ጀመረ:- “ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው።” (ራእይ 16:2) እንደ መጀመሪያው የመለከት ድምፅ ሁሉ እዚህም ላይ “ምድር” ሰይጣን ከ4,000 ዓመታት በፊት በናምሩድ ዘመን መገንባት የጀመረውን የማይናወጥ የሚመስል የፖለቲካ ሥርዓት ያመለክታል።—ራእይ 8:7
3. (ሀ) ብዙ መንግሥታት ከተገዥዎቻቸው ከአምልኮ የማይተናነስ ነገር የጠየቁት እንዴት ነው? (ለ) ብሔራት ለአምላክ መንግሥት ምትክ የሚሆን ምን ነገር አቋቁመዋል? እርሱንስ በሚያመልኩ ሰዎች ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?
3 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ብዙ መንግሥታት አገራቸው ከአምላክም ሆነ ታማኝነትን ከሚጠይቅ ከማንኛውም ነገር ሁሉ በላይ መሆን አለበት ስለሚሉ ከዜጎቻቸው ከአምልኮ ጋር የሚመጣጠን ተገዥነት ጠይቀዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ከሉቃስ 20:25ና ከዮሐንስ 19:15 ጋር አወዳድር።) ከ1914 ጀምሮ ብሔራት ወጣቶቻቸው ዘመናዊውን የዓለም ታሪክ ገጾች በደም ባጥለቀለቁት አጠቃላይ ጦርነቶች እንዲካፈሉ ወይም ለመካፈል ዝግጁ ሆነው እንዲጠባበቁ ለውትድርና መመልመላቸው የተለመደ ነገር ሆኖአል። በተጨማሪም ብሔራት በዚህ በጌታ ቀን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ምትክ በማድረግ የአውሬው ምስል የሆነውን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና በእርሱ ቦታ የተተካውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቋቁመዋል። የቅርብ ዓመታት ጳጳሳት እንደሚያደርጉት ይህን ሰው ሠራሽ ድርጅት ብቸኛው የሰው ልጅ ተስፋ ነው ብሎ መናገር ታላቅ ስድብ ነው። የአምላክን መንግሥት በጥብቅ የሚቃወም ድርጊት ነው። ይህን ምስል የሚያመልኩ ሁሉ በሙሴ ዘመን ይሖዋን የተቃወሙት ግብጻውያን በአካላዊ ቁስልና እባጭ እንደተመቱ ሁሉ መንፈሳዊ እርኩሰትና እባጭ ይዞአቸዋል።—ዘጸአት 9:10, 11
4. (ሀ) የመጀመሪያው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ምን ነገር አጉልቶ የሚገልጽ ነበር? (ለ) ይሖዋ የአውሬውን ምልክት የሚቀበሉ ሰዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል?
4 የዚህ ጽዋ መልእክት በሰው ልጆች ፊት የተደቀነውን ምርጫ ጉልህ በሆነ መንገድ አቅርቦአል። በሰው ልጆች ፊት የዓለምን ጥላቻ ከመቋቋምና የይሖዋን ቁጣ ከመጋፈጥ መካከል አንዱን የመምረጥ ግዴታ ተደቅኖባቸዋል። መላው የሰው ዘር “የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል” በመደረጉ የአውሬውን ምልክት እንዲቀበል ግዳጅ ተደርጎበታል። (ራእይ 13:16, 17) ይሁን እንጂ ለዚህ ድርጊታቸው የሚከፍሉት ኪሣራ አለ። ይሖዋ ምልክቱን የተቀበሉ ሁሉ ‘በጎጂ ቁስልና በመርዛማ እባጭ’ እንደተመቱ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ከ1922 ጀምሮ ሕያውን አምላክ የካዱ ሰዎች መሆናቸው ግልጽ ሆኖአል። የፖለቲካ እቅዳቸው ስለማይሳካ ብስጭት ይደርስባቸዋል። በመንፈሳዊ ሁኔታ የረከሱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ የፍርድ ቀን ስለ ቀረበ ንስሐ ገብተው ካልተመለሱ የያዛቸው በሽታ ይገድላቸዋል። የዚህ ዓለም ሥርዓት ክፍል በመሆንና ከክርስቶስ ጎን ተሰልፎ ይሖዋን በማገልገል መካከል ገለልተኛ አቋም መያዝ አይቻልም።—ሉቃስ 11:23፤ ከያዕቆብ 4:4 ጋር አወዳድር።
ባሕሩ ደም ሆነ
5. (ሀ) ሁለተኛው ጽዋ ሲፈስ ምን ይሆናል? (ለ) ይሖዋ በምሳሌያዊው ባሕር ውስጥ የሚኖሩትን እንዴት ይመለከታቸዋል?
5 አሁን ደግሞ ሁለተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ መፍሰስ ይኖርበታል። የዚህ ጽዋ መፍሰስ ለሰው ልጅ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፣ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።” (ራእይ 16:3) እንደ ሁለተኛው የመለከት ድምፅ ሁሉ ይህም ጽዋ የታለመው “በባሕር” ማለትም ከይሖዋ በራቀው ተነዋዋጭና ዓመፀኛ የሰው ልጅ ክፍል ላይ እንዲፈስ የተዘጋጀ ነው። (ኢሳይያስ 57:20, 21፤ ራእይ 8:8, 9) ይህ “ባሕር” በይሖዋ ዓይን ሲታይ ሕያዋን ፍጥረታት ሊኖሩ የማይችሉበት ደም ሆኖአል። ክርስቲያኖች የዚህ ዓለም ክፍል መሆን የማይገባቸውም በዚህ ምክንያት ነው። (ዮሐንስ 17:14) ሁለተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ መፍሰሱ በባሕሩ ውስጥ የሚኖሩ የሰው ልጆች በሙሉ በይሖዋ ፊት በድኖች መሆናቸውን ያጋልጣል። የሰው ልጅ በሙሉ ንጹሕ ደም የማፍሰስ ማኅበረሰብአዊ ተጠያቂነት አለበት። የይሖዋ የቁጣ ቀን ሲመጣ በይሖዋ የቅጣት አስፈጻሚ ሠራዊት በሞት ይቀጣሉ።—ራእይ 19:17, 18፤ ከኤፌሶን 2:1ና ከቆላስይስ 2:13 ጋር አወዳድር።
ደም ማጠጣት
6. ሶስተኛው ጽዋ ሲፈስስ ምን ይሆናል? ከመልአኩና ከመሠዊያው ምን የሚሉ ቃላት ተሰምተዋል?
6 ሦስተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ እንደ ሦስተኛው የመለከት ድምፅ በውኃ ምንጮች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነው። “ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። የውኃውም መልአክ:- ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፣ ቅዱስ ሆይ፣ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፣ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። ከመሠዊያውም:- አዎን፣ ሁሉን የምትገዛ ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ ሆይ፣ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 16:4-7
7. “ወንዞችና የውኃ ምንጮች” ምን ያመለክታሉ?
7 እነዚህ “ወንዞችና የውኃ ምንጮች” ይህ ዓለም ጥበብና መመሪያ ሰጪዎች ናቸው በማለት የሚቀበላቸውንና የሚመራባቸውን ማለትም የሰው ልጆችን ውሳኔዎችና ድርጊቶች የሚመሩትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስ፣ የትምህርት፣ የማኅበረሰብና የሃይማኖት ፍልስፍናዎችን ያመለክታሉ። ሰዎች የሕይወት ምንጭ ከሆነው አምላክ ሕይወት ሰጪ የሆነውን እውነት ለማግኘት ከመፈለግ ይልቅ ‘በአምላክ ፊት ሞኝነት የሆነውን የዚህን ዓለም ጥበብ’ ለመጠጣት “የተቀደዱትንም ጉድጓዶች ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች፣ ለራሳቸው ቆፍረዋል።”—ኤርምያስ 2:13፤ 1 ቆሮንቶስ 1:19፤ 2:6፤ 3:19፤ መዝሙር 36:9
8. የሰው ልጅ የደም ባለዕዳ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
8 እንደነዚህ ያሉት የተበከሉ ‘ውኃዎች’ ሰዎችን የደም አፍሳሽነት ወንጀል እንዲሠሩ አድርገዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል ባለፈው መቶ ዘመን በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በነጠቁት ታላላቅ ጦርነቶች እንዲካፈሉ በመምራት የደም ጎርፍ እንዲያፈስሱ አድርገዋቸዋል። በተለይም ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በተነሱባት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ተጣድፈዋል። በተለይ የአምላክ ምሥክሮችን ደም ለማፍሰስ ተቻኩለዋል። (ኢሳይያስ 59:7፤ ኤርምያስ 2:34) በተጨማሪም የሰው ልጅ የይሖዋን የጽድቅ ሕግ በመተላለፍ በጣም ብዙ ደም በሕክምና ሰበብ በደም ሥር እንዲሰጥ በማድረጉ የደም ወንጀለኛ ሆኖአል። (ዘፍጥረት 9:3-5፤ ዘሌዋውያን 17:14፤ ሥራ 15:28, 29) በዚህም የተነሣ በደም ሥር በሚሰጠው ደም አማካኝነት ኤድስ፣ ሄፓታይትስና ሌሎች በሽታዎች በመዛመታቸው ትልቅ ሐዘንና መከራ አጭደዋል። በቅርቡ እነዚህ ወንጀለኞች ‘በታላቁ የአምላክ ቁጣ የወይን መጥመቂያ’ ተረግጠው የመጨረሻውን ቅጣት ሲቀበሉ የወንጀላቸውን ሙሉ ብድራት ይቀበላሉ።—ራእይ 14:19, 20
9. የሦስተኛው ጽዋ መፍሰስ ምን ማድረግን የሚጠይቅ ነበር?
9 በሙሴ ዘመን የአባይ ወንዝ ወደ ደም በተለወጠበት ጊዜ ግብጻውያን ከሌሎች የውኃ ምንጮች ውኃ በመቅዳት ሕይወታቸውን ለማቆየት ችለው ነበር። (ዘጸአት 7:24) መንፈሳዊ መቅሰፍት በወረደበት በአሁኑ ጊዜ ግን ሰዎች ከሰይጣን ዓለም ምንም ዓይነት ሕይወት ሰጪ የሆነ ውኃ ሊያገኙ አልቻሉም። ሦስተኛው ጽዋ መፍሰሱ “የወንዞችና የውኃ ምንጮች” ጠጪውን ሁሉ በመንፈሳዊ የሚገድል ደም መሆኑን ማሳወቅን የሚጨምር ነበር። ሰዎች ወደ ይሖዋ ካልተመለሱ የቅጣት ፍርዱን መቀበላቸው አይቀርም።—ከሕዝቅኤል 33:11 ጋር አወዳድር።
10. “የውኃዎቹ መልአክ” ምን ነገር አሳውቆአል? መሰውያውስ ምን ተጨማሪ ምስክርነት ሰጠ?
10 ይህን ጽዋ ወደ ውኃው የሚያፈስሰው “የውኃው መልአክ” ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ፈራጅና የጽድቅ ፍርዶቹ ፍጹም የሆኑ አምላክ መሆኑን አሳውቆአል። በዚህም ምክንያት ስለሰጠው ፍርድ ሲናገር “የሚገባቸው ነውና” ብሎአል። መልአኩ በዚህ ክፉ ዓለም ለብዙ ሺህ ዓመታት በሐሰት ትምህርቶችና ፍልስፍናዎች ምክንያት የተስፋፋውን ጭካኔና ደም መፋሰስ ተመልክቶ እንደነበረ አያጠራጥርም። ስለዚህ የይሖዋ የፍርድ ውሣኔ ትክክል መሆኑን ያውቅ ነበር። የአምላክ መሰዊያ እንኳን ይህ ትክክል መሆኑን ይናገራል። በራእይ 6:9, 10 ላይ በሰማዕትነት የተገደሉት ሰዎች ነፍሳት በዚህ መሠዊያ ሥር እንዳሉ ተነግሮአል። ስለዚህ የይሖዋ ውሣኔ ፍትሐዊና ጽድቅ ስለመሆኑ መሰዊያው ተጨማሪ ምስክርነት ሰጥቶአል።a በእርግጥም ይህን የሚያክል ብዙ ደም አለአግባብ የተጠቀሙና ያፈሰሱ ሰዎች ተገድደው ደም መጠጣታቸው ተገቢ ነው። ይህም ይሖዋ የሞት ፍርድ የፈረደባቸው መሆኑን ያመለክታል።
ሰዎችን በእሳት ማቃጠል
11. አራተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ዒላማ የሆነው ምንድን ነው? ጽዋውስ በፈሰሰ ጊዜ ምን ሆነ?
11 የአራተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ዒላማ ፀሐይ ነች። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፣ በእነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፣ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም።”—ራእይ 16:8, 9
12. የዚህ ዓለም “ፀሐይ” ምንድን ነው? ለዚህስ ምሳሌያዊ ፀሐይ ምን የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል?
12 ዛሬ፣ በዚህ የሥርዓቱ ፍጻሜ ዘመን የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች “በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ” በማብራት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 13:40, 43) ኢየሱስ ራሱ “የጽድቅ ፀሐይ” ነው። (ሚልክያስ 4:2) የሰው ልጅ ግን የራሱ “ፀሐይ” ማለትም የአምላክን መንግሥት በመቃወም ለማብራት የሚሞክሩ የራሱ ገዥዎች አሉት። አራተኛው የመለከት ድምፅ በሕዝበ ክርስትና ሰማይ ውስጥ ያሉት ‘ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት’ የጨለማ እንጂ የብርሃናት ምንጮች አለመሆናቸውን አሳውቆአል። (ራእይ 8:12) አሁን ደግሞ አራተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ የዓለም “ፀሐይ” መቋቋም የማይቻል ትኩሳት እንደሚኖረው ያሳውቃል። እንደ “ፀሐይ” የሚታዩት መሪዎች የሰው ልጆችን በትኩሳታቸው “ያቃጥላሉ”። ይህን የማድረግ ሥልጣን ለምሳሌያዊው ፀሐይ ይሰጠዋል። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ይህን ሁኔታ በሰው ልጆች ላይ የሚያወርደው እሳታማ ፍርድ ክፍል እንዲሆን ይፈቅዳል። ይህ በትኩሳት መመታት ወይም መቃጠል የተፈጸመው በምን መንገድ ነው?
13. ፀሐይ መሰሎቹ የዚህ ዓለም ገዥዎች የሰው ልጆችን በትኩሳት ‘ያቃጠሉት’ እንዴት ነው?
13 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዚህ ዓለም ገዥዎች የዓለምን የሰላምና የደኅንነት ችግር ለመፍታት በማሰብ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን አቋቋሙ። ሆኖም ጥረታቸው አልተሳካም። በዚህም ምክንያት እንደ ፋሽዝምና ናዚዝም የመሰሉ የአገዛዝ ዓይነቶች ተሞከሩ። ኮምኒዝምም መስፋፋት ጀመረ። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙት ፀሐይ መሰል ገዥዎች የሰው ልጆችን ችግር ከማቃለል ይልቅ ‘በታላቅ ትኩሳት ማቃጠል’ ጀመሩ። በስፓኝ፣ በኢትዮጵያና በማንቹሪያ የተደረጉት ጦርነቶች ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት አስነስተዋል። አምባገነኖቹ ሂትለር፣ ሙሶሎኒና ስታሊን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች፣ በጣም ብዙ ለሆኑ ለራሳቸው ዜጎች ጭምር መሞት ምክንያት መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቦአል። በቅርቡ ደግሞ እንደ ቬትናም፣ ካምፑቺያ፣ ኢራን፣ ሊባኖስ፣ አየርላንድ ባሉትና በሌሎች የላቲን አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች የተደረጉት የእርስበርስና በብሔራት መካከል የተደረጉ ጦርነቶች ሕዝቦችን በታላቅ ትኩሳት አቃጥለዋል። በእነዚህ ግጭቶች ላይ የሰው ልጆችን በሙሉ ለመፍጀት የሚችሉ የኑክሌር መሣሪያዎች ቁልል ባላቸው ልዕለ ኃያላን መካከል የሚደረገው ፉክክርና ፍጭት ተጨምሮአል። በእርግጥም በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት መላው የሰው ልጅ ጻድቃን ላልሆኑት ገዥዎቹ ወይም ለምሳሌያዊው “ፀሐይ” ትኩሳት ተጋልጦአል። የአራተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ መፍሰስ እነዚህን ታሪካዊ ሐቆች በግልጽ አመልክቶአል። የአምላክ ሕዝቦችም እነዚህን ሐቆች በምድር በሙሉ አውጀዋል።
14. የይሖዋ ምሥክሮች ለሰው ልጅ ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ምን መሆኑን ሲያስተምሩ ቆይተዋል? ለዚህስ ስብከታቸው የሰው ልጅ በአጠቃላይ እንዴት ያለ አቀባበል አሳይቶአል?
14 የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጅ ለተደቀኑበት ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ይሖዋ ስሙን የሚቀድስበት የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን በማያወላውል ሁኔታ አስተምረዋል። (መዝሙር 83:4, 17, 18፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በአጠቃላይ ለዚህ መፍትሔ ጆሮውን አልሰጠም። መንግሥቱን ለመቀበል እምቢተኞች ከሆኑት ብዙዎቹ ፈርኦን የአምላክን ሉዓላዊነት ለመቀበል እምቢተኛ በሆነ ጊዜ እንዳደረገው የአምላክን ስም ተሳድበዋል። (ዘጸአት 1:8-10፤ 5:2) እነዚህ ተቃዋሚዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምንም ዓይነት ፍላጎት ስለሌላቸው በሚያተኩሰው “ፀሐይ” ሥር ማለትም በጨቋኝ ሰብዓዊ ገዥዎቻቸው ሥር ለመቃጠል መርጠዋል።
የአውሬው ዙፋን
15. (ሀ) አምስተኛው ጽዋ የፈሰሰው በምን ላይ ነው? (ለ) “የአውሬው ዙፋን” ምንድን ነው? ጽዋውስ በእርሱ ላይ መፍሰሱ ምንን ያመለክታል?
15 የሚቀጥለው መልአክ ጽዋውን የሚያፈስሰው በምን ላይ ነው? “አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ።” (ራእይ 16:10ሀ) “አውሬው” የሰይጣን መንግሥታዊ ሥርዓት ነው። አውሬው ራሱ ምሳሌያዊ በመሆኑ ዙፋኑም እውነተኛ ዙፋን አይደለም። ይሁን እንጂ ዙፋን መጠቀሱ አውሬው በሰው ልጆች ላይ ንጉሣዊ ስልጣን እንደነበረው ያመለክታል። ይህም እያንዳንዱ የአውሬው ራስ አክሊል የደፋ ከመሆኑ ጋር ይስማማል። እንዲያውም “የአውሬው ዙፋን” የዚህ ሥልጣን መሠረት ወይም ምንጭ ነው።b መጽሐፍ ቅዱስ “ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው” በማለት የአውሬውን ትክክለኛ የሥልጣን ምንጭ ይገልጻል። (ራእይ 13:1, 2፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ጽዋው በአውሬው ዙፋን ላይ መፍሰሱ ሰይጣን አውሬውን በመደገፍና በማቋቋም ረገድ የነበረውን እውነተኛ ሚና የሚያጋልጥ መግለጫ እንደሚወጣ ያመለክታል።
16. (ሀ) ብሔራት አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚያገለግሉት ማንን ነው? አስረዳ። (ለ) ዓለም የሰይጣንን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? (ሐ) የአውሬው ዙፋን የሚገለበጠው መቼ ነው?
16 ይህ በሰይጣንና በብሔራት መካከል ያለው ዝምድና የተጠበቀው እንዴት ነው? ሰይጣን ኢየሱስን በፈተነበት ጊዜ የዚህን ዓለም መንግሥታት በሙሉ በራእይ ካሳየው በኋላ ያንን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ሊሰጠው እንደሚችል ነግሮት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ስጦታ ለማግኘት መፈጸም የሚኖርበት ግዴታ ነበር። በሰይጣን ፊት ወድቆ በመስገድ እርሱን ማምለክ ነበረበት። (ሉቃስ 4:5-7) ታዲያ የዓለም መንግሥታት ሥልጣን የተቀበሉት ከዚህ ያነሰ ግዳጅ ፈጽመው ነው ብለን ለማሰብ እንችላለንን? በፍጹም አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሰይጣን የዚህ ሥርዓት አምላክ በመሆኑ ብሔራት አወቁትም አላወቁት ሰይጣንን ያገለግሉታል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4)c ይህ ሁኔታ በጠባብ ብሔረተኛነት፣ በጥላቻና የራስን ጥቅም በማሳደድ ላይ በተገነባው በዚህ በዛሬው ሥርዓት አደረጃጀት ውስጥ ግልጽ ሆኖ ታይቶአል። ይህ ሥርዓት የተደራጀው ሰይጣን በሚፈልገው መንገድ ማለትም የሰው ልጆችን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በሚያስችለው መንገድ ነው። በዛሬው ጊዜ ተስፋፍቶ የሚታየው የመንግሥታት አድሎአዊነት፣ ለሥልጣን መስገብገብ፣ የውሸት ዲፕሎማሲ፣ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም ሁሉ የሰይጣንን ወራዳ ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ዓለም የሰይጣንን ከጽድቅ የራቀ የአቋም ደረጃ ተቀብሎአል። ይህን በማድረጉም ሰይጣንን አምላኩ አድርጎታል። አውሬው በሚጠፋበትና የአምላክ ሴት ዘር ሰይጣንን ወደ ጥልቁ በሚከትበት ጊዜ የአውሬው ዙፋን ይገለበጣል።—ዘፍጥረት 3:15፤ ራእይ 19:20, 21፤ 20:1-3
ጨለማና የሚያሠቃይ ሕመም
17. (ሀ) የአምስተኛው ጽዋ መፍሰስ የአውሬውን መንግሥት ከዋጠው መንፈሣዊ ጨለማ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? (ለ) አምስተኛው የአምላክ ቁጣ ሲፈስስ ሰዎች ምን ተሰማቸው?
17 የዚህ አውሬ መንግሥት ገና ከመጀመሪያው አንስቶ በመንፈሣዊ ጨለማ ውስጥ የሚገኝ ነው። (ከማቴዎስ 8:12ና ከኤፌሶን 6:11, 12 ጋር አወዳድር።) አምስተኛው ጽዋ ይህን ጨለማ በተጠናከረ ሁኔታ የሚያጋልጥ ሕዝባዊ ማስታወቂያ ነበር። እንዲያውም ይህ የአምላክ የቁጣ ጽዋ በምሳሌያዊው አውሬ ዙፋን ላይ መፍሰሱ በትዕይንታዊ ሁኔታ ተገልጾአል። “መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፣ ከሥቃይም የተነሣ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር። ከሥቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፣ ከሥራቸውም ንስሐ አልገቡም።”—ራእይ 16:10ለ, 11
18. በአምስተኛው የመለከት ድምፅና በአምስተኛው የአምላክ የቁጣ ጽዋ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
18 አምስተኛው የመለከት ድምፅና አምስተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት አይደሉም። ምክንያቱም የመለከቱ ድምፅ የሚያስታውቀው የአንበጦቹን መቅሰፍት ነው። ይሁን እንጂ ይህ የአንበጦች መቅሰፍት በተለቀቀበት ጊዜ ፀሐይና አየር ጨልሞ እንደነበረ ማስተዋል ይቻላል። (ራእይ 9:2-5) በዘጸአት 10:14, 15 ላይ ደግሞ ይሖዋ ግብጻውያንን ስለመታበት የአንበጦች መቅሰፍት የሚከተለውን እናነባለን:- “አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፣ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፣ እጅግም ብዙ ነበሩ። ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፣ ወደ ፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም። የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት አገሪቱም ጨለመች።” አዎ፣ ፍጹም ጨለማ ሆነ! ዛሬም ቢሆን የዓለም መንፈሳዊ ጨለማ በአምስተኛው መለከት መነፋትና በአምስተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ መፍሰስ ምክንያት ግልጽ ሆኖ ታይቶአል። በዘመናዊዎቹ የአንበጦች ሠራዊት የሚነገረው የሚቆጠቁጥ መልእክት ‘ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ለወደዱት’ ክፉ ሰዎች ከፍተኛ ሥቃይና ሕመም አስከትሎባቸዋል።—ዮሐንስ 3:19
19. በራእይ 16:10, 11 መሠረት ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክ እንደሆነ መጋለጡ ምን ውጤት አስከተለ?
19 ሰይጣን የዓለም ገዥ በመሆኑ ብዙ ችግርና መከራ አምጥቶአል። ረሐብ፣ ጦርነት፣ ዓመፅ፣ ወንጀል፣ የዕፅ ሱሰኝነት፣ ዝሙት፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ አጭበርባሪነት፣ ሃይማኖታዊ ግብዝነትና ሌሎች እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች የሰይጣን ሥርዓት መለያ ባሕርያት ሆነዋል። (ከገላትያ 5:19-21 ጋር አወዳድር።) ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክ እንደሆነ መጋለጡ የእርሱን የአቋም ደረጃ ተከትለው ለሚኖሩ ሰዎች እፍረትና ሥቃይ አስከትሎባቸዋል። በተለይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ሰዎች “ከሥቃይ የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር።” ብዙ ሰዎች እውነት አኗኗራቸውን ስለሚያጋልጥባቸው ይጠሉታል። አንዳንዶች ደግሞ የእውነት መልእክት ስለሚያስፈራቸው መልእክቱን የሚያስፋፉትን ሰዎች ያሳድዳሉ። የአምላክን መንግሥት አይቀበሉም፣ የይሖዋንም ቅዱስ ስም ይነቅፋሉ። ሃይማኖታዊ በሽተኞችና ቁስለኞች መሆናቸው ግልጽ ሆኖ ስለታየባቸው የሰማይን አምላክ ይሳደባሉ። ይሁን እንጂ “ከሥራቸው ንስሐ” አይገቡም። ስለዚህ ይህ ሥርዓት ከመፈጸሙ በፊት የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ወደ ክርስትና ይለወጣሉ ብለን ልንጠባበቅ አንችልም።—ኢሳይያስ 32:6
የኤፍራጥስ ወንዝ ደረቀ
20. ስድስተኛው የመለከት ድምፅም ሆነ የስድስተኛው ጽዋ መፍሰስ የኤፍራጥስን ወንዝ የሚመለከት የሆነው እንዴት ነው?
20 ስድስተኛው የመለከት ድምፅ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት” መፈታት የሚያበስር ነበር። (ራእይ 9:14) በታሪክ እንደሚታወቀው ባቢሎን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተቀመጠች ታላቅ ከተማ ነበረች። ምሳሌያዊዎቹ አራት መላእክት በ1919 መፈታታቸው የታላቂቱን ባቢሎን መውደቅ በጉልህ የሚያሳይ ነበር። (ራእይ 14:8) ስለዚህ ስድስተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ የኤፍራጥስን ወንዝ የሚመለከት መሆኑ ተገቢ ነው። “ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።” (ራእይ 16:12) ይህም ቢሆን ለታላቂቱ ባቢሎን ክፉ መርዶ ነበር።
21, 22. (ሀ) በ539 ከዘአበ ለባቢሎን በመከላከያነት ያገለግል የነበረው የኤፍራጥስ ወንዝ የደረቀው እንዴት ነው? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን የተቀመጠችባቸው “ውኃዎች” ምንድን ናቸው? እነዚህ ምሳሌያዊ ውኃዎች አሁንም እንኳን በመድረቅ ላይ የሆኑት እንዴት ነው?
21 የጥንትዋ ባቢሎን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረችበት ዘመን ከመከላከያ ዝግጅቶችዋ ዋነኛው እስከጫፍ ሞልቶ ይፈስስ የነበረው የኤፍራጥስ ወንዝ ነበር። በ539 ከዘአበ ግን የፋርስ መሪ ቂሮስ የዚህን ወንዝ አቅጣጫ ባስቀየረው ጊዜ ወንዙ ደረቀ። በዚህም ምክንያት “ከፀሐይ መውጫ” (ከምሥራቅ) ለመጡት ነገሥታት ለፋርሳዊው ቂሮስና ለሜዶናዊው ዳርዮስ ወደ ባቢሎን እንዲገቡና ከተማዋን እንዲወርሩአት መንገዱ ክፍት ሆነ። በዚህ የችግር ሰዓት የኤፍራጥስ ወንዝ ለባቢሎን ከተማ መከላከያ ሊሆን አልቻለም። (ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:7፤ ኤርምያስ 51:36) ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት በሆነችው በዘመናዊቷ ባቢሎን ላይም ተመሳሳይ ነገር ሊፈጸም ነው።
22 ታላቂቱ ባቢሎን “በብዙ ውኃዎች” ላይ ተቀምጣለች። እነዚህ ውኃዎች በራእይ 17:1, 15 መሠረት “ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም” ማለትም ታላቂቱ ባቢሎን እንደ መከላከያ ይሆኑኛል ብላ የምትተማመንባቸው ደጋፊዎችዋ ናቸው። ይሁን እንጂ “ውኃዎቹ” በመድረቅ ላይ ናቸው። ታላቂቱ ባቢሎን ከፍተኛ ተጽዕኖ ታደርግባቸው በነበሩት የአውሮፓ አገሮች በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በግልጽ በሃይማኖት ላይ ጀርባቸውን አዙረዋል። በአንዳንድ አገሮች የሃይማኖትን ተጽዕኖ ፈጽሞ የማጥፋት መርሕ እንዳለ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ በይፋ ታውቋል። በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች ለታላቂቱ ባቢሎን መከታ ሆነው አልተነሱም። ታላቂቱ ባቢሎን የምትጠፋበት ጊዜ ሲደርስ በተመሳሳይ በቁጥር የተመናመኑት ደጋፊዎችዋ ሊያድኑአት የማይችሉ እንደሆነ ይረጋገጣል። (ራእይ 17:16) ታላቂቱ ባቢሎን በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ አባሎች እንዳሉአት ብትናገርም እንኳን “ከፀሐይ መውጫ” የሚመጡትን ነገሥታት ለመቋቋም ፈጽሞ አትችልም።
23. (ሀ) በ539 ከዘአበ “ከፀሐይ መውጫ” የመጡት ነገሥታት እነማን ነበሩ? (ለ) በጌታ ቀንስ ‘ከፀሐይ መውጫ የሚመጡት ነገሥታት’ እነማን ናቸው? ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፉትስ እንዴት ነው?
23 እነዚህ ነገሥታት እነማን ናቸው? በ539 ከዘአበ ይሖዋ የጥንትዋን የባቢሎን ከተማ ድል አድርጎ እንዲይዝ የተጠቀመው በሜዶናዊው ዳርዮስና በፋርሳዊው ቂሮስ ነበር። በዚህ የጌታ ቀንም ቢሆን የሐሰት ሃይማኖት ሥርዓት የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን በሰብዓዊ ገዥዎች ትጠፋለች። ይህም ጥፋት ቢሆን መለኮታዊ ፍርድ ነው። “ከፀሐይ መውጫ” የሚመጡት ነገሥታት፣ ማለትም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዓዊ ገዥዎች በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲነሱና ፈጽመው እንዲያጠፉአት በልባቸው ውስጥ “አሳብ” ያስገቡባቸዋል። (ራእይ 17:16, 17) ስድስተኛው ጽዋ መፍሰሱ ይህ ፍርድ ሊፈጸም የተቃረበ መሆኑን ያሳውቃል።
24. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ስድስት የይሖዋ ቁጣ ጽዋዎች የያዙአቸው መልእክቶች ለሕዝብ የተገለጹት እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) የራእይ መጽሐፍ ስለቀረው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ከመናገሩ በፊት ምን ይገልጽልናል?
24 እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ስድስት የአምላክ ቁጣ ጽዋዎች አሳሳቢ መልእክት የያዙ ናቸው። የአምላክ ምድራዊ አገልጋዮች በመላእክት እየታገዙ መልእክቱ የያዛቸውን ነገሮች በምድር በሙሉ በትጋት ሲያስፋፉ ቆይተዋል። በዚህ መንገድ በሰይጣን ዓለም የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ ላይ ተገቢ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ይሖዋም ግለሰቦች ወደ ጽድቅ ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩበትን አጋጣሚ ሁሉ ሰጥቶአቸዋል። (ሕዝቅኤል 33:14-16) ይሁን እንጂ አሁንም አንድ የቀረ የአምላክ ቁጣ ጽዋ አለ። ቢሆንም የራእይ መጽሐፍ ስለዚህ ጽዋ ከመናገሩ በፊት ሰይጣንና ምድራዊ ወኪሎች ስለ ይሖዋ ፍርዶች የተነገሩትን መልእክቶች ለመቋቋም እንዴት እንደሚሞክሩ ይገልጽልናል።
ወደ አርማጌዶን መሰብሰብ
25. (ሀ) ዮሐንስ “እርኩስ” ስለሆነና እንቁራሪት ስለሚመስል ንግግር ምን ይነግረናል? (ለ) በጌታ ቀን እንደ እንቁራሪት “አስጸያፊ የሆነ ንግግር” የተሰማው እንዴት ነው? ምንስ ውጤት አስከተለ?
25 ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፣ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ።” (ራእይ 16:13, 14) በሙሴ ዘመን ይሖዋ በፈርኦን ትገዛ በነበረችው በግብጽ ምድር ላይ የእንቁራሪት ወይም የጓጉንቸር መቅሰፍት አውርዶ ስለነበረ ‘ምድሪቱ ከመቅሰፍቱ የተነሣ መሽተት ጀምራ ነበር።’ (ዘጸአት 8:5-15) በዚህ የጌታ ቀንም ቢሆን ከተለየ አቅጣጫ ይሁን እንጂ እንደ እንቁራሪት የመሰሉ አስጸያፊ ነገሮች ታይተዋል። እነዚህም ሰብአዊ ገዥዎችንና ነገሥታትን በይሖዋ አምላክ ላይ ለማነሳሳት ታስበው ለሚሰራጩት ፕሮፓጋንዳዎች ምሳሌ የሆኑት ከሰይጣን አፍ የሚወጡ ጸያፍ መናፍስታዊ ንግግሮች ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ገዥዎችና ነገሥታት ከአምላክ የቁጣ ጽዋዎች በሚፈስሱት መልእክቶች እንዳይወሰዱና “ሁሉን የሚችለው አምላክ የጦርነት ቀን” በሚጀምርበት ጊዜ ንቅንቅ ሳይሉ ከእርሱ ጎን እንዲሰለፉ ሰይጣን የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
26. (ሀ) ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ የሚመጣው ከየትኞቹ ሦስት ምንጮች ነው? (ለ) “ሐሰተኛው ነቢይ” ምንድን ነው? እንዴትስ እናውቃለን?
26 ፕሮፓጋንዳው የሚመነጨው ቀደም ስንል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከተመለከትናቸው ፍጥረታት ማለትም ‘ከዘንዶው’ (ከሰይጣን) እና ከአውሬው (የሰይጣን ምድራዊ የፖለቲካ ተቋም) ነው። “ሐሰተኛውስ ነቢይ” ምንድን ነው? ይህ አዲስ የሆነው በስሙ ብቻ ነው። ቀደም ስንል ሰባት ራሶች ባሉት አውሬ ፊት ብዙ ድንቅ ነገሮችን ይፈጽም የነበረ ሁለት ቀንዶች ያሉት በግ የመሰለ አውሬ ተመልክተን ነበር። ይህ አታላይ ፍጥረት ለአውሬው እንደ ነቢይ ሆኖ አገልግሎአል። እንዲያውም ለአውሬው ምስል እንዲሠራለት በማድረግ የአውሬውን አምልኮ አስፋፍቶአል። (ራእይ 13:11-14) ይህ የበግ የመሰሉ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ እዚህ ላይ ከተጠቀሰው “ሐሰተኛ ነቢይ” ጋር አንድ መሆን ይኖርበታል። ቆየት ብለን ሐሰተኛው ነቢይ ሁለት ቀንዶች እንዳሉት ምሳሌያዊ አውሬ “በእርሱም [በባለ ሰባት ራሱ አውሬ] ፊት ተዓምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር” እንደተያዘ ስለምናነብ የዚህን ትክክለኛነት ያረጋግጥልናል።—ራእይ 19:20
27. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ምን ዓይነት ወቅታዊ የሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል? (ለ) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? (ሐ) ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ያስተጋባው እንዴት ነው?
27 ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳዎች በተስፋፉበት በዚህ ዘመን ዮሐንስ ቀጥሎ የመዘገባቸው ቃላት በእርግጥም ወቅታዊ ናቸው:- “እነሆ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” (ራእይ 16:15) “እንደ ሌባ” ሆኖ የሚመጣው ማን ነው? ኢየሱስ ራሱ ባልታወቀ ጊዜ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ ይመጣል። (ራእይ 3:3፤ 2 ጴጥሮስ 3:10) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜም እንዲህ በማለት የራሱን አመጣጥ ከሌባ አመጣጥ ጋር አመሳስሎ ነበር። “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:42, 44፤ ሉቃስ 12:37, 40) ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንኑ ማስጠንቀቂያ ሲያስተጋባ የሚከተለውን ጽፎአል:- “የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም።”“ሰላምና ደህንነት” ሆኗል የሚለውን የውሸት አዋጅ የሚያስነግረው ሰይጣን ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3
28. ኢየሱስ ዓለማዊ ተጽዕኖዎችን ስለመቃወም ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል? ክርስቲያኖች “እንደ ወጥመድ” እንዳይደርስባቸው የሚፈልጉት “ያ ቀን” ምንድን ነው?
28 በተጨማሪም ኢየሱስ ይህ በፕሮፓጋንዳ የተጥለቀለቀ ዓለም በክርስቲያኖች ላይ ስለሚያመጣቸው የተጽዕኖ ዓይነቶች አስጠንቅቆአል። እንዲህ አለ:- “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። . . . እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ።” (ሉቃስ 21:34-36) “ያ ቀን” “ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን” ነው። (ራእይ 16:14) ይህ የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት “ቀን” በቀረበ መጠን የኑሮን ችግሮች ለመቋቋም ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ ይሄዳል። ክርስቲያኖች ይህ ቀን እስኪመጣ ድረስ ንቁዎችና ትጉዎች ሆነው ለመቆየት መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
29, 30. (ሀ) ኢየሱስ ተኝተው የተገኙት “መጎናጸፊያቸው” ተወስዶባቸው እንደሚያፍሩ ማስጠንቀቁ ምን ያመለክታል? (ለ) የተለበሰው መጎናጸፊያ ለባሹ ምን መሆኑን ያመለክታል? (ሐ) አንድ ሰው ምሳሌያዊ መጎናጸፊያውን ሊያጣ የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስከትልበታል?
29 ይሁን እንጂ እንቅልፍ ተኝተው የሚገኙት ልብሳቸውን ተነጥቀው እፍረት እንደሚደርስባቸው የተነገረው ማስጠንቀቂያ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በጥንት እስራኤላውያን ዘመን በቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሥራ የተመደበ ማንኛውም ካህን ወይም ሌዋዊ ከፍተኛ ኃላፊነት ነበረበት። በዚህ ሥራ ላይ ተመድቦ እያለ አንቀላፍቶ የተገኘ ማንኛውም ሰው በሕዝብ ሁሉ ፊት ውርደት እንዲደርስበት ሲባል ልብሱ ይወልቅና ይቃጠል እንደነበረ አይሁዳውያን ሊቃውንት ይነግሩናል።
30 ዛሬም ቢሆን ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ሊኖር እንደሚችል ኢየሱስ አስጠንቅቆአል። ካህናቱና ሌዋውያኑ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ጥላ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይሁን እንጂ የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ለእጅግ ብዙ ሰዎችም ተፈጻሚነት አለው። እዚህ ላይ የተጠቀሰው መጎናጸፊያ አንድ ሰው ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ የሚያሳውቀውን መለያ ያመለክታል። (ከራእይ 3:18ና ከራእይ 7:14 ጋር አወዳድር።) ማንም ሰው የሰይጣን ዓለም በሚያመጣበት ተጽዕኖ ተሸንፎ ቢያንቀላፋ ወይም ቢቀዘቅዝ ይህን መጎናጸፊያውን ማለትም የክርስቲያንነት መታወቂያውን ያጣል። እንዲህ ያለው ሁኔታ በጣም የሚያሳፍር ነው። አንድን ሰው ሁሉንም ነገር በማጣት አደጋ ላይ ይጥለዋል።
31. (ሀ) ክርስቲያኖች ነቅተው መኖር እንደሚያስፈልጋቸው ራእይ 16:16 ጠበቅ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ስለ አርማጌዶን ምን ግምታዊ አስተያየት ሰጥተዋል?
31 በተለይ የሚቀጥለው የራእይ ቁጥር ሊፈጸም በሚቃረብበት ጊዜ ክርስቲያኖች ንቁ ሆነው መጠባበቅ በጣም ያስፈልጋቸዋል። በአጋንንት መንፈስ የተነገሩት ቃላት ምድራዊ ነገሥታትን ወይም ገዥዎችን “በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ሥፍራ አስከተቱአቸው።” (ራእይ 16:16) ይህ አርማጌዶን የተባለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ቢሆንም የሰው ልጆችን ግምታዊ አስተሳሰብ ያነሳሳ ቃል ነው። የዓለም መሪዎች የኑክሌር አርማጌዶን ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በተጨማሪም አርማጌዶን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ብዙ ጦርነቶች ተደርገውበት ከነበረው ከጥንቱ የመጊዶ ከተማ ጋር ዝምድና እንዳለው ስለተገለጸ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በምድር ላይ የሚደረገው የመጨረሻ ጦርነት በዚህ ውስን ቦታ እንደሚደረግ ገምተዋል። በዚህም ግምታቸው ከእውነቱ በጣም ርቀው ሄደዋል።
32, 33. (ሀ) ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን ቃል በቃል አንድን የተወሰነ ቦታ ሳይሆን ምን የሚያመለክት ቃል ነው? (ለ) ከ“አርማጌዶን” ጋር የሚዛመዱ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምንድን ናቸው? (ሐ) ሰባተኛው መልአክ የመጨረሻውን የአምላክ ቁጣ ጽዋ የሚያፈስበት ጊዜ የሚደርሰው መቼ ነው?
32 አርማጌዶን ወይም ሐርማጌዶን የሚለው ቃል “የመጊዶ ተራራ” ማለት ነው። ይሁን እንጂ ቃሉ የሚያመለክተው አንድን የተወሰነ ቦታ ሳይሆን ብሔራት በሙሉ ይሖዋን ተቃውመው የሚሰበሰቡበትንና ፈጽመው የሚጠፉበትን የዓለም ሁኔታ ነው። ይህም ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ስፋት ያለው ነው። (ኤርምያስ 25:31-33፤ ዳንኤል 2:44) ብሔራት በይሖዋ እጅ ለመጥፋት ከሚሰበሰቡበት “ከአምላክ የቁጣ ወይን መጥመቂያ” እና “ከውሳኔ ሸለቆ” ወይም “ከኢዮሳፍጥ ሸለቆ” ጋር አንድ ነው። (ራእይ 14:19፤ ኢዩኤል 3:12, 14) በተጨማሪም የማጎጉ ጎግ ሰይጣናዊ ጭፍሮች ከሚጠፉበት “ከእስራኤል ምድር” እንዲሁም “የሰሜኑ ንጉሥ” በታላቁ መስፍን በሚካኤል እጅ “ወደ ፍጻሜው” ከሚመጣበት “በባሕርና በከበረው በቅዱሱ ተራራ መካከል” ካለው ቦታ ጋር ይዛመዳል።—ሕዝቅኤል 38:16-18, 22, 23፤ ዳንኤል 11:45 እስከ 12:1
33 ብሔራት በሙሉ ከሰይጣንና ከምድራዊ ወኪሎቹ በሚወጣው የእንቁራሪት ድምፅ የሚመስል ፕሮፓጋንዳ አማካኝነት ወደዚህ ሁኔታ ከተሰበሰቡ በኋላ ሰባተኛው መልአክ የመጨረሻውን የአምላክ ቁጣ ጽዋ የሚያፈስበት ጊዜ ይሆናል።
“ተፈጽሞአል!”
34. ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን ያፈሰሰው በምን ላይ ነው? ‘ከመቅደሱና ከዙፋኑ’ ምን ዓይነት መግለጫ ወጥቶአል?
34 “ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፣ ከመቅደሱም ውስጥ:- ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ።”—ራእይ 16:17
35. (ሀ) በራእይ 16:17 ላይ የተጠቀሰው “አየር” ምንድን ነው? (ለ) ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን በአየሩ ላይ ሲያፈስስ ምን ነገር ገልጾአል?
35 የመጨረሻው መቅሰፍት የሚደርሰው ሕይወትን ጠብቆ በሚያቆየው “አየር” ላይ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አየር ቃል በቃል እውነተኛ አየር አይደለም። እውነተኛው አየር የይሖዋን የቁጣ ፍርድ እንዲቀበል የሚያደርገው ምንም ዓይነት በደል አልሠራም። ግዑዙ ምድር፣ እውነተኛው ባሕርና የውኃዎች ምንጮችም ሆኑ ግዑዝዋ ፀሐይ የይሖዋን የቅጣት ፍርድ የሚቀበሉበት ምንም ዓይነት በደል የለባቸውም። ይህ “አየር” ጳውሎስ ሰይጣንን “በአየር ላይ ሥልጣን ያለው አለቃ” ብሎ በጠራው ጊዜ የገለጸውን ዓይነት አየር ያመለክታል። (ኤፌሶን 2:2) ይህ “አየር” የዛሬው ዓለም የሚተነፍሰው ሰይጣናዊ “አየር” ወይም የመላው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት መለያ ባሕርይ የሆነው መንፈስ ወይም አጠቃላይ ዝንባሌ ወይም ከይሖዋ ድርጅት ውጭ በሆነው የሕይወት መስክ ሁሉ ሰፍኖ የሚገኘው ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ነው። ስለዚህ ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ ሲያፈስስ አምላክ በሰይጣን፣ በሰይጣን ድርጅትና የሰው ልጅ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንዲቃወምና የሰይጣን ደጋፊ ሆኖ እንዲቆም ባነሳሳው ነገር ሁሉ ላይ የሚገልጸውን ቁጣ መግለጹ ነው።
36. (ሀ) ሰባቱ መቅሰፍቶች በአጠቃላይ ምንድን ናቸው? (ለ) ይሖዋ “ተፈጽሞአል!” ማለቱ ምን ያመለክታል?
36 ይሖዋ በሰይጣንና በሰይጣን ሥርዓት ላይ የሚያስተላልፋቸው ፍርዶች በዚህኛውና ቀደም ባሉት ስድስት መቅሰፍቶች ተጠቃልለዋል። እነዚህም ለሰይጣንና ለዘሩ የጥፋት መልእክቶች ሆነዋል። ይኸኛው የመጨረሻ ጽዋ ከፈሰሰ በኋላ ይሖዋ ራሱ “ተፈጽሞአል!” አለ። ከዚህ ሌላ የሚባል ነገር አይኖርም። የአምላክ ቁጣ ጽዋዎች ይሖዋ በቃ እስኪል ድረስ ከተነገሩና ከታወጁ በኋላ በእነዚህ መልእክቶች የተገለጹትን ፍርዶች ፈጥኖ ይፈጽማል።
37. ሰባተኛው የአምላክ ቁጣ ጽዋ ከፈሰሰ በኋላ የሆነውን ነገር ዮሐንስ የገለጸው እንዴት ነው?
37 ዮሐንስ የሚከተለውን በማለት ይቀጥላል:- “መብረቅና ድምፅም ነጎድጓድም ሆኑ፣ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ። ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፣ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቁጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች። ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም። በሚዛንም አንድ ታላንት የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሠፍት የተነሣ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፣ መቅሠፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና።”—ራእይ 16:18-21
38. (ሀ) የ“ምድሩ መናወጥ” (ለ) “ታላቂቱ ከተማ” የተባለችው ታላቂቱ ባቢሎን በሦስት መከፈልዋ (ሐ) እያንዳንዱ ደሴት መሸሹና ተራሮች አለመገኘታቸው (መ) ‘የበረዶው መቅሰፍት’ ምን ያመለክታል?
38 አሁንም እንደገና ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ ትክክለኛ እርምጃ ወሰደ። ይህን እርምጃውን እንደ ጀመረ ምልክት የሚሆነው “መብረቅና ድምፅ ነጎድጓድ” ነው። (ከራእይ 4:5ና ከ8:5 ጋር አወዳድር።) የሰው ልጅ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን በከፍተኛ የምድር መናወጥ እንደተናወጠ ያህል ከመሠረቱ ይናጋል። (ከኢሳይያስ 13:13ና ከኢዩኤል 3:16 ጋር አወዳድር።) ይህ ከፍተኛ ነውጥ “ታላቂቱን ከተማ” ባቢሎንን ስለሚያነቃንቃት “በሦስት” ትከፋፈላለች። ይህም ተመልሳ ልትጠገን በማትችልበት ሁኔታ እንደምትፈራርስ ያመለክታል። በተጨማሪም “የአሕዛብም ከተማዎች” ይወድቃሉ። “ደሴቶችም ሁሉ” “ተራራዎችም” ማለትም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጽኑ ወይም ቋሚ የሚመስሉት ተቋሞችና ድርጅቶች ይጠፋሉ። “ታላቅ በረዶ፣” ግብጽን በሰባተኛው መቅሰፍት ጊዜ መትቶአት ከነበረው እጅግ በጣም የሚበልጥ በረዶ የሰው ልጆችን ይደበድባል። እያንዳንዱ በረዶ አንድ ታላንት ያህል የሚመዝን ይሆናል።d (ዘጸአት 9:22-26) ይህ ዓይነቱ የጠጠረ ውኃ ውርጅብኝ የይሖዋ የቁጣ ፍርድ በከባድ ሁኔታ መነገሩን ያመለክታል። ይህም መግለጫ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ሊመጣ መሆኑን የሚያመለክት ማስታወቂያ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ በሚፈጽመው የማጥፋት ሥራ ላይ ቃል በቃል በበረዶ ሊጠቀም ይችላል።—ኢዮብ 38:22, 23
39. ሰባቱ መቅሰፍቶች ቢፈስሱም አብዛኞቹ የሰው ልጆች እንዴት ያለ አካሄድ መርጠዋል?
39 በዚህ መንገድ የይሖዋ የጽድቅ ፍርድ በሰይጣን ዓለም ላይ ይፈጸማል። አብዛኛው የሰው ልጅ ክፍል አምላክን ማዋረዱንና መስደቡን እስከ መጨረሻው ይቀጥላል። እንደ ጥንቱ ፈርኦን ሁሉ እነርሱም በተደጋጋሚ በወረዱባቸው መቅሰፍቶች ወይም ለመጨረሻ ጊዜ በሚወርድባቸው ገዳይ መቅሰፍት ልባቸው አይለሰልስም። (ዘጸአት 11:9, 10) በመጨረሻው ሰዓት ላይ በብዛት ተለውጠው ልባቸውን ወደ አምላክ አይመልሱም። በመጨረሻው ትንፋሻቸው እንኳን “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደሆንሁ ያውቃሉ” የሚለውን አምላክ በመቃወም ይሳደባሉ። (ሕዝቅኤል 38:23) ይሁን እንጂ ሁሉን የሚችለው አምላክ የይሖዋ ሉዓላዊነት ይረጋገጣል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሕይወት የሌላቸው ነገሮች ምስክር ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምሳሌ ከተፈለገ ዘፍጥረት 4:10፤ 31:44-53፤ ዕብራውያን 12:24 መመልከት ይቻላል።
b “ዙፋን” የሚለው ቃል ስለ ኢየሱስ በተነገረው “እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ዙፋንህ ነው” በሚለው ትንቢት በተመሳሳይ ሁኔታ ተሠርቶበታል። (መዝሙር 45:6 NW) የኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣን ምንጩ ወይም መሠረቱ ይሖዋ ነው።
c በተጨማሪም ኢዮብ 1:6, 12፤ 2:1, 2፤ ማቴዎስ 4:8-10፤ 13:19፤ ሉቃስ 8:12፤ ዮሐንስ 8:44፤ 12:31፤ 14:30፤ ዕብራውያን 2:14፤ 1 ጴጥሮስ 5:8ን ተመልከት።
d ዮሐንስ የተናገረው ስለ ግሪክ ታላንት ከነበረ እያንዳንዱ በረዶ 20 ኪሎ ግራም ይመዝናል ማለት ነው። ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል በረዶ ነው ማለት ነው።
[በገጽ 221 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በምድር ውስጥ”
የዮሐንስ ክፍል ይሖዋ “በምድሪቱ” ላይ ያለውን ቁጣ እንደ ሚከተሉት ባሉ መግለጫዎች አስታውቆአል:-
“የፖለቲካ ፓርቲዎች ከብዙ መቶ ዓመታት ሙከራ በኋላ በዘመናችን የሚታየውን ሁኔታ ለመቋቋምና በጣም አሳዛኝ ለሆኑት ችግሮች መፍትሔ ማስገኘት አቅቶአቸዋል። ይህንን ጥያቄ በጥሞና የሚያጠኑ የኢኮኖሚ ጠበብትና ርዕሳነ ብሔራት ምንም ነገር ለማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን ተገንዝበዋል።”—በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በፍጹም ሞትን አያዩም፣ 1920, ገጽ 61
“በዛሬው ጊዜ የዓለምን ክፍል ያረካ አንድም መንግሥት በምድር ላይ አይገኝም። አብዛኞቹ ብሔራት የሚገዙት በአምባገነን መሪዎች ነው። መላው ዓለም የኢኮኖሚ ክስረት ደርሶበታል።”—ተፈላጊ መንግሥት፣ 1924፣ ገጽ 5
“ይህን የክፋት ዓለም ለማስወገድና ሰላምና ጽድቅ የሚያብበትን ጥርጊያ ለማዘጋጀት የሚቻለው ይህንን ሥርዓት በማጥፋት ብቻ ነው።”—“ይህ የመንግሥት ምሥራች”፣ 1954፣ ገጽ 25
“የዛሬው ዓለም አደረጃጀት ተለይቶ የሚታወቅበት ባሕርይ የኃጢአት መስፋፋት፣ ከጽድቅ መራቅ፣ በአምላክና በአምላክ ፈቃድ ላይ ማመጽ ነው። . . . ፈጽሞ ሊሻሻል የማይችል ዓለም ነው። ስለዚህ ፈጽሞ መጥፋት ይኖርበታል!” መጠበቂያ ግንብ፣ ህዳር 15, 1981፣ ገጽ 6
[በገጽ 223 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በባሕር ውስጥ”
የዮሐንስ ክፍል ባለፉት ዓመታት አምላክ በዚህ እረፍት የለሽና ዓመፀኛ በሆነው “ባሕር” ላይ ማለትም አምላክ የለሽ በሆነውና ከአምላክ በራቀው የሰው ልጅ ላይ የተሰማውን ቁጣ ለማስታወቅ ካወጣው መግለጫዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው:-
“በመደቦች መካከል ትግል እንደነበረ የእያንዳንዱ ብሔር ታሪክ ያመለክታል። ጥቂቶቹ በብዙሃኑ ላይ ተነስተዋል። . . . እነዚህ ትግሎች ብዙ አብዮቶችን፣ ብዙ ሥቃይና ብዙ ደም መፋሰስ አስከትለዋል።”—መንግሥት፣ 1928፣ ገጽ 244
በአዲሱ ዓለም ውስጥ “እረፍት የለሽ፣ ዓመፀኛና አምላክ የለሽ ከሆኑ ሕዝቦች ምሳሌያዊ “ባሕር” ውስጥ ለዲያብሎስ አገልግሎት የወጣው ምሳሌያዊ አውሬ ይጠፋል።”—መጠበቂያ ግንብ፣ መስከረም 15, 1967፣ ገጽ 567
“ይህ የአሁኑ ሰብአዊ ኅብረተሰብ መንፈሳዊ ሕመምና በሽታ ያለበት ነው። በሽታው ለሞት የሚያደርሰው እንደሆነ የአምላክ ቃል ስለሚያመለክት ማናችንም ልናድነው አንችልም።”—እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት—ከየት ይገኛል?፣ 1973፣ ገጽ 131
[በገጽ 224 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በወንዞችና በውኃ ምንጮች ላይ”
ሦስተኛው መቅሰፍት እንደሚከተሉት ባሉ መግለጫዎች አማካኝነት “ወንዞችንና የውኃ ምንጮችን” አጋልጦ ነበር:-
“የክርስቶስን መሠረተ ትምህርቶች እናስተምራለን የሚሉት ቀሳውስት ጦርነትን ቀድሰዋል። እንደ ቅዱስ ነገርም እንዲቆጠር አድርገዋል። ሥዕሎቻቸውና ሐውልቶቻቸው ከደም አፍሳሽ ጦረኞች ጎን ሆኖ በመታየቱ ተደስተዋል።”—መጠበቂያ ግንብ፣ መስከረም 15, 1924፣ ገጽ 275
“መናፍስትነት የሰው ነፍስ አትሞትም፣ ሰው ከሞተ በኋላ ተለይታው ለዘላለም ትኖራለች በሚለው የሐሰት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ሐሰት ነው።”—“ከሞት በኋላ በሕይወት ስለመኖር” ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?፣ 1955፣ ገጽ 51
“ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች፣ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ አውጪዎች፣ የማኅበረሰብ አደራጆች፣ የምጣኔ ሀብት አማካሪዎችና የሃይማኖታዊ ወግ ጠበቆች ሕይወት ሰጪና የሚያረካ ውኃ ሊሰጡ አልቻሉም። . . . እንዲያውም እነዚህን የመሰሉት ውኃዎች ጠጪዎቻቸው ፈጣሪ ስለ ደም ቅድስና የሰጠውን ሕግ እንዲተላለፉና ሃይማኖታዊ አሳዳጆች እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።”—በ“ዘላለሙ ወንጌል” ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የተላለፈ ውሣኔ፣ 1963
“ከሰው ልጅ የሚጠበቀው ሳይንሳዊ መዳንን ሳይሆን የመላው ሰው ዘር ጥፋት ነው። . . . የሰው ልጆችን አስተሳሰብ ይለውጡልናል ብለን በዓለም የሳይኮሎጂ ጠበብትና የሥነ አእምሮ ሐኪሞች ላይ ተስፋ ልንጥል አንችልም። . . . ይህችን ምድር ለመኖሪያ የምትመችና ሰላም የሰፈነባት ዓለም ለማድረግ በሚመሠርት ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል ልንተማመን አንችልም።”—የሰው ልጆችን በመንግሥቱ መንገድ ማዳን፣ 1970፣ ገጽ 5
[በገጽ 225 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በፀሐይ ላይ”
የሰው ልጅ የአገዛዝ “ፀሐይ” የሰውን ልጅ በትኩሳት ባነደደበት በዚህ የጌታ ቀን የዮሐንስ ክፍል እንደሚከተሉት ባሉት መግለጫዎች አማካኝነት በመፈጸም ላይ ያሉት ነገሮች ትኩረት እንዲያገኙ አድርጎአል:-
“ዛሬ ጭፍን አምባገነን ገዥዎች የሆኑት ሂትለርና ሙሶሎኒ የመላውን ዓለም ሰላም ስጋት ላይ ጥለዋል። ነፃነትን ለማጥፋት በሚያደርጉት ጥረት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ድጋፍ አላቸው።”—ፋሽዝም ወይስ ነፃነት፣ 1939፣ ገጽ 12
“በታሪክ ዘመናት ሁሉ አምባገነን ገዥዎች ሲከተሉ የቆዩት መርሕ ግዛ ወይም አጥፋ! የሚል ነበር። አምላክ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በምድር በሙሉ የሚያስፈጽመው ደንብ “መገዛት ወይም መጥፋት” የሚል ነው።”—የሰው ልጆች በሙሉ በአምላክ መንግሥት ሥር አንድነት በሚያገኙበት ጊዜ፣ 1961 ገጽ 23
“ከ1945 ጀምሮ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች በተደረጉ ከ150 በሚበልጡ ጦርነቶች ከ25 ሚልዮን በላይ ሰዎች ተገድለዋል።”—መጠበቂያ ግንብ፣ ጥር 15, 1980፣ ገጽ 6
“በዓለም በሙሉ የሚገኙ ብሔራት ስለ ዓለም አቀፋዊ ግዴታቸው ወይም ስለ ሥነ ምግባር ግዴታቸው ደንታ የላቸውም። አንዳንድ ብሔራት ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚጠቅማቸው ከሆነ አስፈላጊ ሆኖ የተሰማቸውን ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ወደ ኋላ አይሉም። ይገድላሉ፣ ሰዎችን ያስጠልፋሉ፣ በቦምብ ያስደበድባሉ፣ ወዘተ። . . . ብሔራት እንደዚህ ያለውን ትርጉም የለሽና ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት እየፈጸሙ እርስ በርሳቸው ተቻችለው የሚኖሩት እስከ መቼ ድረስ ነው?”—መጠበቂያ ግንብ፣ የካቲት 15, 1985፣ ገጽ 4
[በገጽ 227 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በአውሬው ዙፋን ላይ”
የይሖዋ ምሥክሮች የአውሬውን ዙፋን አጋልጠዋል። እንደሚከተሉት ባሉት መግለጫዎች አማካኝነትም ይሖዋ እንደሚያወግዘው ለሕዝብ አሳውቀዋል:-
“የብሔራት ገዥዎችና ፖለቲካዊ መሪዎች የሚመሩት በጠላትነት በተነሳሱ ከሰው በላይ በሆኑ ኃይላት ነው። እነዚህም ኃይላት ወሳኝ ወደሆነው የአርማጌዶን ጦርነት እያስከተቱአቸው ስለሆነ ወደ ከፍተኛ እልቂት እየነዱአቸው ነው።”—ከአርማጌዶን በኋላ የሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም፣ 1953፣ ገጽ 8
“አውሬው ጸረ ቲኦክራቲካዊ አቋም ያለው ሰብአዊ አገዛዝ ሲሆን ሥልጣኑን፣ ኃይሉንና ዙፋኑን የተቀበለው ከዘንዶው ነው። ስለዚህም በዘንዶው ላይ ከሚደርሰው ዕጣ ተካፋይ መሆን ይኖርበታል።”—ከአርማጌዶን በኋላ የሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም፣ 1953፣ ገጽ 15
“የአሕዛብ ብሔራት የተሰለፉት የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጎን ብቻ ነው።”—“በመለኮታዊ ድል” ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የተላለፈ ውሣኔ፣ 1973
[በገጽ 229 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ውኃው ደረቀ”
በአሁኑ ጊዜ እንኳን ለባቢሎናዊ ሃይማኖቶች የሚሰጠው ድጋፍ በብዙ አካባቢዎች እየደረቀ ነው። ይህም “ከፀሐይ መውጫ የሚመጡት ነገሥታት” ጥቃታቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ የሚሆነውን ነገር ይጠቁማል።
“በታይላንድ ተደርጎ በነበረ አገር አቀፍ ጥናት እንደታወቀው በከተሞች አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚያክሉት ስብከት ለማዳመጥ ወደ ቡድሂስት መቅደሶች ፈጽሞ አይሄዱም። በገጠር አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ደግሞ ወደ መቅደሶች የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በጣም እያነሰ መጥቶ ሃምሳ በመቶ ደርሶአል።”—ባንኮክ ፖስት፣ መስከረም 7, 1987፣ ገጽ 4
“በታኦይዝም የነበረው ምትሐታዊ ኃይል ሃይማኖቱ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ከተመሠረተበት ከቻይና አገር ጠፍቶአል። . . . ካህናቱ ራሳቸውም ሆኑ ከእነርሱ በፊት የነበሩት ብዙ ተከታዮችን ይስቡበት የነበረውን ምትሐታዊ ኃይል ስለተነጠቁ በእግራቸው የሚተኩ ካህናት አጥተዋል። በዚህም ምክንያት ታኦይዝም የተደራጀ ሃይማኖት መሆኑ ቀርቶ ፈጽሞ ወደ መጥፋት ተቃርቦአል።”—ዘ አትላንታ ጆርናል ኤንድ ኮንስቲትዩሽን፣ መስከረም 12, 1982፣ ገጽ 36–A
“ጃፓን . . . ብዙ የባዕድ አገር ሚስዮናውያን ከሚኖሩባቸው አገሮች አንዱዋ ነች። 5,200 የሚያክሉ ሚስዮናውያን ይገኙባታል። . . . ሆኖም ግን ወደ ክርስትና የተለወጡት ሰዎች ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ ከ1% ያነሰ ነው። . . . በዚህ አገር ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ሲሠሩ የቆዩ አንድ ፍራንቼስካዊ ቄስ ባዕዳን ሚስዮኖች በጃፓን አገር ያላቸው ተፈላጊነት እንዳከተመለት አምነዋል።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ሐምሌ 9, 1986፣ ገጽ 1
በእንግሊዝ አገር ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት “16,000 ከሚያክሉ የአንግሊካን አብያት ክርስቲያናት መካከል 2,000 የሚያክሉት ተገልጋይ በማጣታቸው ምክንያት ተዘግተዋል። የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቁጥር በጣም አንሶ ክርስቲያን ነን ከሚሉ አገሮች በሙሉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሶአል። . . . ‘አሁን እንግሊዝ የክርስቲያን አገር ነች ለማለት አይቻልም’ ሲሉ የዱርሃም ጳጳስ ተናግረዋል።”—ዘ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ግንቦት 11, 1987፣ ገጽ A4
“የግሪክ ፓርላማ ብዙ ሰዓቶች የፈጀ ክርክር ካደረገ በኋላ ሶሻሊስታዊው መንግሥት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የያዘችውን ሰፊ ርስት እንዲወርስ የሚያስችለው ሕግ አጽድቆአል። . . . ከዚህም በላይ ሕጉ የክህነት ሹመት የሌላቸው ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ገቢ የምታገኝባቸውን ሆቴሎች የዕብነበረድ ማዕድናትንና የሚከራዩ ሕንፃዎችንና የመሳሰሉትን የሚያስተዳድሩ ኮሚቴዎችንና ጉባኤዎችን እንዲቆጣጠሩ ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ሚያዝያ 4, 1987፣ ገጽ 3
[በገጽ 222 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የመጀመሪያዎቹ አራት የአምላክ ቁጣ ጽዋዎች መፍሰስ የመጀመሪያዎቹ አራት መለከቶች በመነፋታቸው ምክንያት የመጡትን የመሰሉ መቅሠፍቶች ያመጣል
[በገጽ 226 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለአውሬው ዙፋኑን የሰጠው ሰይጣን መሆኑን አምስተኛው ጽዋ አጋለጠ
[በገጽ 231 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳ የምድርን ገዥዎች የይሖዋ ፍርድ በላያቸው ላይ ወደሚፈስበት ወደ ሐርማጌዶን በመሰብሰብ ላይ ነው
[በገጽ 233 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተበከለው የሰይጣን “አየር” ሲመሩ የነበሩ ሁሉ በይሖዋ የጽድቅ ፍርድ ይገደላሉ