አርማጌዶን—አስደሳች ጅማሬ
“አርማጌዶን” ለተሰኘው ስያሜ መገኛ የሆነው “ሃር-ማጌዶን” ወይም “የመጊዶ ተራራ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። ቃሉ የሚገኘው በራእይ 16:16 ላይ ሲሆን እንደሚከተለው ይላል:- “እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ሥፍራ ሰበሰቧቸው።” በአርማጌዶን የተሰበሰቡት እነማን ናቸው? ለምንስ? ሁለት ቁጥሮች ቀደም ብሎ የሚገኘው ራእይ 16:14 ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት’ “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት” እንደሚሰበሰቡ ይናገራል። እነዚህ አባባሎች ደግሞ ትኩረት የሚስቡ ሌሎች ጥያቄዎችን ያስነሳሉ። እነዚህ “ነገሥታት” የሚዋጉት የት ነው? የሚዋጉትስ ለምንድን ነው? ከማንስ ጋር? ብዙዎች እንደሚሉት እነዚህ ነገሥታት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ይጠቀሙ ይሆን? ከአርማጌዶን የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ መልሶቹን ይስጠን።
“የመጊዶ ተራራ” የሚለው አገላለጽ የአርማጌዶን ውጊያ የሚካሄደው በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ አንድ የተወሰነ ተራራ ላይ መሆኑን ያመለክታል? በጭራሽ። በመጀመሪያ ደረጃ የጥንቷ መጊዶ በነበረችበት አካባቢ፣ ሜዳማ ከሆነው ሸለቆ አጠገብ ከሚገኘው 20 ሜትር ከፍታ ካለው ጉብታ በስተቀር እንዲህ ተብሎ የሚጠራ ተራራ የለም። ከዚህም በላይ የመጊዶ አካባቢ ‘የምድር ነገሥታትንና ሰራዊታቸውን’ የመያዝ አቅም የለውም። (ራእይ 19:19) ይሁንና መጊዶ በመካከለኛው ምሥራቅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ከባድና ወሳኝ ውጊያዎች የተካሄዱባት ስፍራ ነች። በመሆኑም አርማጌዶን የሚለው ስያሜ አሸናፊው በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅበትን አንድ ወሳኝ ውጊያ ለማመልከት እንደ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል።—“ተስማሚ ምሳሌ የሆነችው መጊዶ” የሚለውን በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን ተመልከት።
ራእይ 16:14 ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት’ ግንባር ፈጥረው “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት” እንደሚወጡ ስለሚናገር አርማጌዶን ምድራዊ ነገሥታት እርስ በርሳቸው የሚዋጉበት ሊሆን አይችልም። ኤርምያስ በመንፈስ አነሳሽነት በተናገረው ትንቢት ላይ ‘በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር እንደሚረፈረፉ’ ገልጿል። (ኤርምያስ 25:33) በመሆኑም አርማጌዶን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ፣ አንድ የተወሰነ ስፍራ የሚደረግ የሰዎች ውጊያ አይደለም። አርማጌዶን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የይሖዋ ጦርነት ነው።
ይሁንና በራእይ 16:16 ላይ አርማጌዶን “ሥፍራ” ተብሎ መጠራቱን አስተውል። “ሥፍራ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድን ክንውን ወይም ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል። እዚህ ላይ ክንውኑ የሚያመለክተው መላው ዓለም ይሖዋን ለመቃወም ግንባር መፍጠሩን ነው። (ራእይ 12:6, 14) በአርማጌዶን ሁሉም ምድራዊ ነገሥታት “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን ‘የሰማይ ሰራዊት’ ለመቃወም ኅብረት ይፈጥራሉ።—ራእይ 19:14, 16
አርማጌዶን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበት ታላቅ እልቂት አሊያም የምድር ከአንድ የሰማይ አካል ጋር መጋጨት ነው ስለሚሉት አባባሎችስ ምን ለማለት ይቻላል? አፍቃሪው አምላክ በሰው ልጆችና መኖሪያቸው በሆነችው ምድር ላይ እንዲህ ያለ ዘግናኝ እልቂት እንዲደርስ ይፈቅዳል? በፍጹም። አምላክ ምድርን የፈጠራት “ባዶ እንድትሆን” ሳይሆን ‘ለሰው መኖሪያነት’ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 45:18፤ መዝሙር 96:10) ይሖዋ፣ በአርማጌዶን ምድራችንን በእሳት አያጋያትም። ከዚህ ይልቅ “ምድርን ያጠፏትን” ያጠፋቸዋል።—ራእይ 11:18
አርማጌዶን—መቼ?
“አርማጌዶን የሚመጣው መቼ ነው?” ይህ ለብዙ መቶ ዓመታት ማቆሚያ የሌላቸው ግምታዊ መልሶች ሲሰነዘሩበት የኖረ ጥያቄ ነው። የራእይን መጽሐፍ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር እያገናዘብን መመርመራችን ይህ ወሳኝ ጦርነት የሚከናወንበትን ጊዜ እንድናውቅ ይረዳናል። ራእይ 16:15 አርማጌዶንን ኢየሱስ እንደ ሌባ ሆኖ ከሚመጣበት ጊዜ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። ኢየሱስ ራሱም በዚህ ሥርዓት ላይ ለመፍረድ የሚመጣበትን ጊዜ ለማመልከት ተመሳሳይ ምሳሌያዊ መግለጫ ተጠቅሟል።—ማቴዎስ 24:43, 44፤ 1 ተሰሎንቄ 5:2
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜዎች ከ1914 ጀምሮ በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር ያሳያሉ።a ኢየሱስ ‘ታላቁ መከራ’ በማለት የጠራው ጊዜ ለመጨረሻው ዘመን መደምደሚያ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ታላቁ መከራ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይገልጽም። ሆኖም በዚያ ጊዜ የሚከሰተው መከራ በዓለም ላይ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው። ታላቁ መከራም በአርማጌዶን ይደመደማል።—ማቴዎስ 24:21, 29
አርማጌዶን ‘ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በመሆኑ ሰዎች የጦርነቱን ቀን ወደ ሌላ ጊዜ ሊያስተላልፉት አይችሉም። ይሖዋ አርማጌዶን የሚጀምርበትን ‘የተወሰነ ጊዜ’ የቀጠረ ሲሆን ያ ቀን “ከቶም አይዘገይም።”—ዕንባቆም 2:3
ጻድቁ አምላክ ፍትሐዊ ጦርነት ያውጃል
የሆነ ሆኖ አምላክ ለምን ዓለም አቀፋዊ ጦርነት ያውጃል? አርማጌዶን አምላክ ካሉት ታላላቅ ባሕርያት ከአንዱ ማለትም ከፍትሕ ጋር በጥብቅ የሚተሳሰር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 37:28) እርሱ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙትን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በሙሉ ሲመለከት ቆይቷል። እነዚህ ሁኔታዎች ጻድቅ የሆነውን አምላክ እንደሚያሳዝኑት እሙን ነው። በመሆኑም ፍትሐዊ ጦርነት በማወጅ ይህን ክፉ ሥርዓት በአጠቃላይ እንዲደመስስ ልጁን ሾሞታል።
እውነተኛ ፍትሕ የሚንጸባረቅበት፣ ክፉዎችን ለይቶ የሚያስወግድና በየትኛውም የምድር ክፍል ይኑሩ ልበ ቅን ሰዎችን የማይጎዳ ጦርነት ማወጅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:40, 41፤ ራእይ 7:9, 10, 13, 14) ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ ሉዓላዊነቱን የማስከበር መብት ያለው እርሱ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11
ይሖዋ ጠላቶቹን ለማጥፋት በምን ይጠቀማል? ስለዚህ ጉዳይ የምናውቀው ነገር የለም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ክፉ የሆኑትን መንግሥታት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል አቅም እንዳለው ነው። (ኢዮብ 38:22, 23፤ ሶፎንያስ 1:15-18) ይሁንና በምድር ላይ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች በጦርነቱ አይካፈሉም። ራእይ ምዕራፍ 19 ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉት የሰማይ ሠራዊት ብቻ እንደሆኑ ያመለክታል። በምድር ላይ የሚገኝ ማንኛውም የይሖዋ አገልጋይ በጦርነቱ አይካፈልም።—2 ዜና መዋዕል 20:15, 17
ጥበበኛው አምላክ በቂ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል
በሕይወት ስለሚተርፉ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? እውነት ነው፣ አርማጌዶን ሁሉንም ሰው ጠራርጎ አያጠፋም። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው አምላክ “ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ” ይታገሳል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ሐዋሪያው ጳውሎስም የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” እንደሆነ ገልጿል።—1 ጢሞቴዎስ 2:4
ይህንን ለማሳካት ይሖዋ በዓለም ዙሪያ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ‘የመንግሥቱ ወንጌል’ እንዲሰበክ ለማድረግ የጥበብ እርምጃ ወስዷል። በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በሕይወት እንዲተርፉና መዳንን እንዲያገኙ የሚያስችል አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ መዝሙር 37:34፤ ፊልጵስዩስ 2:12) ለመንግሥቱ ወንጌል አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሁሉ ከአርማጌዶን በሕይወት መትረፍና ፍጽምና አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይችላሉ። (ሕዝቅኤል 18:23, 32፤ ሶፎንያስ 2:3፤ ሮሜ 10:13) አንድ ሰው ፍቅር ከሆነው አምላክ የሚጠብቀው ይህን አይደለም?—1 ዮሐንስ 4:8
አፍቃሪው አምላክ ይዋጋል?
ይሁንና ብዙዎች ‘የፍቅር ተምሳሌት የሆነው አምላክ በአብዛኛው የሰው ዘር ላይ ሞትና ጥፋት እንዴት ያመጣል?’ በማለት ይጠይቃሉ። ሁኔታው በተባይ ከተወረረ ቤት ጋር ሊወዳደር ይችላል። አሳቢ የሆነ አባወራ ተባዮቹን በማጥፋት የቤተሰቡን ጤንነትና ደስታ መጠበቅ እንዳለበት አትስማማም?
በተመሳሳይም ይሖዋ በአርማጌዶን ጦርነት የሚዋጋው ለሰዎች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ነው። የአምላክ ዓላማ ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥ፣ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ማድረስና ‘የሚያስፈራቸው ሳይኖር’ በሰላም እንዲኖሩ ማድረግ ነው። (ሚክያስ 4:3, 4፤ ራእይ 21:4) የሰዎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሆን? አምላክ ለጻድቃን ሲል በተባይ የተመሰሉትንና ከስህተታቸው የማይታረሙትን እነዚህን ክፉ ሰዎች ማጥፋት አለበት።—2 ተሰሎንቄ 1:8, 9፤ ራእይ 21:8
ብዙውን ጊዜ አምባጓሮና ደም መፋሰስ የሚከሰተው ፍጹም ባልሆነው የሰው ልጅ አገዛዝና በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስቀደም በሚደረገው ትግል ሳቢያ ነው። (መክብብ 8:9) ሥልጣናቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚጥሩት ሰብዓዊ መንግሥታት የተቋቋመውን የአምላክ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ችላ ብለውታል። ሉዓላዊነታቸውን ለአምላክና ለክርስቶስ አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኞች እንደሆኑ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለም። (መዝሙር 2:1-9) በመሆኑም የአምላክ መንግሥት የጽድቅ አገዛዝ እንዲሰፍን ከተፈለገ እነዚህ መንግሥታት ከቦታቸው መወገድ አለባቸው። (ዳንኤል 2:44) ዓለምንና የሰው ልጆችን የመግዛት መብት ያለው ማን እንደሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ የአርማጌዶን ጦርነት መካሄድ ይኖርበታል።
ይሖዋ በአርማጌዶን አማካኝነት ጣልቃ የሚገባው ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ነው። የዓለም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተባባሱ በሄዱበት በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን ፍላጎት ማርካት የሚችለው የአምላክ እንከን የለሽ አገዛዝ ብቻ ነው። እውነተኛ ሰላምና ብልጽግና ሊሰፍን የሚችለው በመንግሥቱ አማካኝነት ነው። አምላክ ጣልቃ የማይገባ ቢሆን ኖሮ ወደፊት የዓለም ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ሰብዓዊ አገዛዝ ተንሰራፍቶ በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ እንደታየው የሰው ልጅ በጥላቻ፣ በዓመጽና በጦርነት መጎዳቱ አይቀጥልም? በእርግጥም አርማጌዶን ለእኛ ጥቅም ሲባል ከሚደረጉ ግሩም ዝግጅቶች መካከል አንዱ ነው!—ሉቃስ 18:7, 8፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ጦርነቶችን ሁሉ የሚያጠፋ ጦርነት
አርማጌዶን እስከዛሬ ድረስ የተደረጉት ሌሎች ጦርነቶች ሊያከናውኑት ያልቻሉትን ነገር ያከናውናል፤ ይኸውም ጦርነቶችን ሁሉ ያስወግዳል። ጦርነት ጊዜ ያለፈበት ክንውን ሆኖ ለማየት የማይናፍቅ ማን አለ? ይሁንና ሰዎች ጦርነትን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት ሁሉ መና ሆኗል። ሰዎች ጦርነትን ለማስቀረት ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ አለመሳካቱ ኤርምያስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት እውነት እንደሆኑ ያሳያል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤርምያስ 10:23) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚያከናውነውን ነገር አስመልክቶ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:8, 9
ብሔራት በአውዳሚ የጦር መሣሪያዎቻቸው እርስ በርስ በመዋጋት ለምድር ከባቢያዊ ሁኔታ ስጋት መሆን ሲጀምሩ የምድር ፈጣሪ በአርማጌዶን አማካኝነት እርምጃ ይወስዳል! (ራእይ 11:18) በመሆኑም ይህ ጦርነት፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ለዘመናት ሲጠብቁት የኖሩት ተስፋ እንዲፈጸም ያደርጋል። የምድር ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ መላው ፍጥረታቱን የመግዛት መብት እንዳለው ይረጋገጣል።
ስለሆነም አርማጌዶን ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን አያስፈራቸውም። ከዚህ ይልቅ ተስፋ ይፈነጥቅላቸዋል። የአርማጌዶን ጦርነት ከማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ውድቀትና ክፋት ምድርን በማጽዳት በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ሥር ለሚቋቋመው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ሥርዓት መንገድ ይጠርጋል። (ኢሳይያስ 11:4, 5) በምድር ላይ ለዘላለም ለሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች አርማጌዶን አስፈሪ የሆነ የዓለም መጨረሻ ሳይሆን አስደሳች ዘመን መጥባቱን የሚያሳይ ብስራት ነው።—መዝሙር 37:29
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተስማሚ ምሳሌ የሆነችው መጊዶ
የጥንቷ መጊዶ በሰሜን እስራኤል ያለውን የኢይዝራኤል ለምለም ሸለቆ ምዕራባዊ ክፍል ቁልቁል ለማየት በሚያስችል ቦታ ላይ የምትገኝ ምቹ የመሬት አቀማመጥ ያላት ከተማ ነበረች። ከተማይቱ አካባቢውን አቋርጠው የሚያልፉትን ዓለም አቀፍ የንግድ መሥመሮችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ትቆጣጠር ነበር። ስለሆነም መጊዶ ከባድ ውጊያዎች የሚደረጉባት የጦርነት አውድማ ሆነች። ፕሮፌሰር ግራሃም ዴቪስ ሲቲስ ኦቭ ቢብሊካል ዎርልድ—መጊዶ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “መጊዶ . . . ከተለያየ አቅጣጫ የሚጎርፉ ነጋዴዎችና ስደተኞች በቀላሉ የሚገቡባት ከተማ ነበረች፤ ይሁንና አቅሙ ካላት እነዚህኑ መንገዶች ተጠቅማ ንግዱን መቆጣጠርም ሆነ በጦርነት የበላይነቱን መቀዳጀት ትችል ነበር። ስለሆነም . . . ብዙዎች በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ የሚዋደቁባት፣ እጃቸው ከገባችም በኋላ እንዳትወሰድባቸው የሚፋለሙላት ከተማ መሆኗ የሚያስደንቅ አይደለም።”
ረጅሙ የመጊዶ ታሪክ የጀመረው የግብጹ ንጉሥ ሳልሳዊ ቱትሞስ የከነዓን ገዥዎችን መጊዶ ላይ ድል ባደረገበት በሁለተኛው ሺህ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። ይህ ታሪክ፣ የቱርክ ሠራዊት በእንግሊዛዊው ጀኔራል ኤድመንት አለንቢ እጅግ አስከፊ ሽንፈት እስከቀመሰበት እስከ 1918 ድረስ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ዘልቋል። አምላክ፣ መስፍኑ ባርቅ በከነዓናዊው ንጉሥ በኢያቢስ ላይ ታላቅ ድል እንዲቀዳጅ ያደረገው በመጊዶ ነበር። (መሳፍንት 4:12–24፤ 5:19, 20) በዚያው አካባቢ መስፍኑ ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል አድርጓቸዋል። (መሳፍንት 7:1-22) ንጉሥ አካዝያስም ሆነ ንጉሥ ኢዮስያስ የተገደሉት በዚህች ስፍራ ነበር።—2 ነገሥት 9:27፤ 23:29, 30
በመሆኑም አርማጌዶን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወሳኝ ጦርነቶች በተካሄዱባት በዚህች ስፍራ መመሰሉ ተገቢ ነው። መጊዶ አምላክ በተቃዋሚ ኃይሎች ሁሉ ላይ ለሚቀዳጀው የተሟላ ድል ተስማሚ ምሳሌ ናት።
ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አርማጌዶን አስደሳች ዘመን መጥባቱን ያበስራል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለምዙሪያ ያሉ ሰዎች በሕይወት እንዲተርፉ እና መዳንን እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል