የጥናት ርዕስ 20
የራእይ መጽሐፍ፣ የአምላክን ጠላቶች የሚመለከት ምን ሐሳብ ይዟል?
“እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:16
መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ
ማስተዋወቂያa
1. የራእይ መጽሐፍ ስለ አምላክ ሕዝቦች ምን ይላል?
የራእይ መጽሐፍ የአምላክ መንግሥት በሰማይ እንደተቋቋመና ሰይጣን ከሰማይ እንደተባረረ ይነግረናል። (ራእይ 12:1-9) የሰይጣን መባረር በሰማይ እፎይታ አስገኝቷል፤ ለእኛ ግን ችግሮች አስከትሎብናል። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣን ቁጣ በአሁኑ ወቅት ያነጣጠረው በምድር ላይ ይሖዋን በታማኝነት በሚያገለግሉት ላይ ነው።—ራእይ 12:12, 15, 17
2. በጽናት ለመቀጠል ምን ይረዳናል?
2 የሰይጣንን ጥቃት ተቋቁመን በጽናት ለመቀጠል ምን ይረዳናል? (ራእይ 13:10) የሚረዳን አንዱ ነገር ወደፊት ምን እንደሚከናወን ማወቃችን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በራእይ መጽሐፍ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ በቅርቡ የምናገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች ጠቅሷል። ከእነዚህ በረከቶች አንዱ የአምላክ ጠላቶች መጥፋት ነው። እንግዲያው የራእይ መጽሐፍ እነዚህን ጠላቶች እንዴት እንደሚገልጻቸውና ምን እንደሚደርስባቸው እንመልከት።
“በምልክቶች” የተገለጹት የአምላክ ጠላቶች
3. በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጹት አንዳንድ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
3 የራእይ መጽሐፍ ገና የመጀመሪያ ቁጥሩ ላይ እንደሚነግረን በውስጡ ያሉት ነገሮች የተጻፉት “በምልክቶች” ወይም በምሳሌያዊ ቋንቋ ነው። (ራእይ 1:1) የአምላክን ጠላቶች የሚገልጻቸው በምሳሌ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ አንዳንድ አራዊት እንደተጠቀሱ እናነባለን። ለምሳሌ “ከባሕር ሲወጣ” የታየ አውሬ አለ። ይህ አውሬ “አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች” አሉት። (ራእይ 13:1) ይህን አውሬ ተከትሎ ደግሞ “ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ” ታይቷል። ይሄኛው አውሬ እንደ ዘንዶ የሚናገር ሲሆን “እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።” (ራእይ 13:11-13) በኋላ ላይ ደግሞ ስለ ሌላ አውሬ እናነባለን፤ ይህን “ደማቅ ቀይ አውሬ” አንዲት አመንዝራ እየጋለበችው እንደሆነ ተገልጿል። እነዚህ ሦስት አራዊት የይሖዋንና የመንግሥቱን የረጅም ጊዜ ጠላቶች ይወክላሉ። ስለዚህ ማንነታቸውን ማወቃችን አስፈላጊ ነው።—ራእይ 17:1, 3
4-5. በዳንኤል 7:15-17 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የአራዊቱን ማንነት ለመረዳት የሚያግዘን እንዴት ነው?
4 የእነዚህን ጠላቶች ማንነት ለማወቅ በመጀመሪያ የምልክቶቹን ትርጉም መረዳት ያስፈልገናል። ለዚህ ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ ራሱን እንዲያብራራ መፍቀድ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ ምልክቶች ቀደም ብሎ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ ተብራርተዋል። ለምሳሌ ነቢዩ ዳንኤል ‘አራት ግዙፍ አራዊት ከባሕር ውስጥ ሲወጡ’ በሕልሙ አይቷል። (ዳን. 7:1-3) ዳንኤል እነዚህ አራዊት ምን እንደሚያመለክቱ ገልጿል። ግዙፎቹ አራዊት የሚያመለክቱት አራት ‘ነገሥታትን’ ወይም መንግሥታትን ነው። (ዳንኤል 7:15-17ን አንብብ።) ይህ ግልጽ ማብራሪያ ስላለን በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጹት አራዊትም የፖለቲካ ኃይሎችን ያመለክታሉ ብለን መደምደም እንችላለን።
5 እስቲ አሁን በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተገለጹት ምልክቶች አንዳንዶቹን እንመልከት። እንዲህ ስናደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ የምልክቶቹን ትርጉም ለመረዳት የሚያግዘን እንዴት እንደሆነ እናያለን። የተለያዩ አራዊትን በተከታታይ በማየት እንጀምራለን። በቅድሚያ አራዊቱ ማንን እንደሚያመለክቱ እንመረምራለን። ከዚያም ምን እንደሚደርስባቸው እንመለከታለን። በመጨረሻም እነዚህ ክንውኖች ለእኛ ምን ትርጉም እንዳላቸው እናያለን።
የአምላክ ጠላቶች ማንነት ታወቀ
6. በራእይ 13:1-4 ላይ የተገለጸው ባለ ሰባት ራስ አውሬ ምን ያመለክታል?
6 ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ማን ነው? (ራእይ 13:1-4ን አንብብ።) ይህ አውሬ በጥቅሉ ሲታይ ነብር ይመስላል፤ እግሮቹ ግን የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ነው፤ አሥር ቀንዶችም አሉት። እነዚህን ገጽታዎች በሙሉ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ የተገለጹት አራት አራዊት ላይም እናያቸዋለን። በራእይ መጽሐፍ ላይ ግን እነዚህ ገጽታዎች በሙሉ የሚታዩት በአንድ አውሬ ላይ እንጂ በአራት የተለያዩ አራዊት ላይ አይደለም። ይህ አውሬ አንድን መንግሥት ወይም የዓለም ኃይል ብቻ የሚያመለክት አይደለም። አውሬው “በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ ሥልጣን” እንዳለው ተገልጿል። ስለዚህ አንድን መንግሥት ብቻ ሊያመለክት አይችልም። (ራእይ 13:7) እንግዲያው ይህ አውሬ የሚያመለክተው እስከ ዛሬ የሰው ልጆችን ሲያስተዳድሩ የቆዩ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች መሆን አለበት።b—መክ. 8:9
7. እያንዳንዱ የአውሬው ራስ ምን ያመለክታል?
7 እያንዳንዱ የአውሬው ራስ ምን ያመለክታል? በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ አንድ ፍንጭ እናገኛለን፤ በዚህ ምዕራፍ ላይ የራእይ ምዕራፍ 13ቱ አውሬ ምስል ተገልጿል። ራእይ 17:10 እንዲህ ይላል፦ “ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” ሰይጣን ከተጠቀመባቸው የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ‘ራስ’ የተባሉት ሰባቱ ናቸው። እነዚህ የዓለም ኃይሎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ የጎላ ተጽዕኖ ነበራቸው። በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን አምስቱ አልፈዋል፤ እነሱም ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስና ግሪክ ናቸው። ዮሐንስ ራእዩ በተገለጠለት ጊዜ እየገዛ የነበረው ስድስተኛው የዓለም ኃይል የሆነው የሮም መንግሥት ነው። ታዲያ ሰባተኛውና የመጨረሻው የዓለም ኃይል ወይም ራስ የሚሆነው ማን ነው?
8. የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማን ነው?
8 ቀጥለን እንደምንመለከተው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች ሰባተኛውንና የመጨረሻውን የአውሬውን ራስ ለይተን ለማወቅ ይረዱናል። በፍጻሜው ዘመን ማለትም ‘በጌታ ቀን’ እየገዛ ያለው የዓለም ኃያል መንግሥት ማን ነው? (ራእይ 1:10) የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስ ጥምረት ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። በራእይ 13:1-4 ላይ የተጠቀሰው አውሬ ሰባተኛ ራስም ይህ ጥምር ኃይል ነው ብለን መደምደም እንችላለን።
9. “እንደ በግ ሁለት ቀንዶች” ያሉት አውሬ ማን ነው?
9 ራእይ ምዕራፍ 13 ቀጥሎ እንደሚነግረን ይህ ሰባተኛ ራስ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል በሌላ አውሬ ተመስሏል። ይህ አውሬ “እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ መናገር ጀመረ።” ራእይ ምዕራፍ 16 እና ምዕራፍ 19 ላይ ይህ አውሬ “ሐሰተኛው ነቢይ” ተብሎ ተገልጿል። (ራእይ 16:13፤ 19:20) ይህ አውሬ “[በሰው ልጆች] ፊት ታላላቅ ምልክቶችን ይፈጽማል፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።” (ራእይ 13:11-15) ዳንኤልም ስለ አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ተመሳሳይ ነገር ገልጿል፤ “አሰቃቂ ጥፋት ያደርሳል” ብሏል። (ዳን. 8:19, 23, 24 ግርጌ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሆነውም ይህ ነው። ለዚህ ጦርነት ማብቃት ወሳኝ ሚና የተጫወቱት ሁለቱ የአቶሚክ ቦምቦች የብሪታንያና የአሜሪካ ሳይንቲስቶች የሥራ ውጤት ናቸው። የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ‘እሳት ከሰማይ ወደ ምድር ያወረደ’ ያህል ነበር።
10. “የአውሬው ምስል” ምን ያመለክታል? (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 8, 11)
10 ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ስለ ሌላ አውሬ እንመለከታለን። ይህ አውሬ ሰባት ራሶች ካሉት አውሬ ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ የሚለየው በደማቅ ቀይ ቀለሙ ብቻ ነው። “የአውሬው ምስል” ተብሎ የተጠራ ሲሆን “ስምንተኛ ንጉሥ” ተብሏል።c (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 8, 11ን አንብብ።) ይህ “ንጉሥ” ቀደም ሲል በሕይወት እንደነበረ፣ በኋላ ላይ ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን ከዚያም ዳግም ሕያው እንደሚሆን ተገልጿል። ይህ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በሚገባ ይገልጸዋል። ይህ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታትን ፍላጎት እንደሚያራምድ ይታወቃል። ድርጅቱ መጀመሪያ የተቋቋመው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተብሎ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሕልውና ውጭ ሆነ። በኋላ ላይ ደግሞ ዛሬ ያለውን መልክ ይዞ ብቅ አለ።
11. አራዊቱ ምን ይቀሰቅሳሉ? ልንፈራቸው የማይገባውስ ለምንድን ነው?
11 አራዊቱ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በይሖዋና በሕዝቡ ላይ ተቃውሞ ይቀሰቅሳሉ። በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የዓለምን ነገሥታት ሁሉ’ ወደ አርማጌዶን ጦርነት ይሰበስቧቸዋል፤ ይህ ጦርነት “ሁሉን ቻይ [የሆነው] አምላክ ታላቅ ቀን” ነው። (ራእይ 16:13, 14, 16) ሆኖም የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ታላቁ አምላካችን ይሖዋ የእሱን አገዛዝ የሚደግፉትን ሁሉ ለማዳን አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል።—ሕዝ. 38:21-23
12. አራዊቱ ምን ይደርስባቸዋል?
12 አራዊቱ ምን ይደርስባቸዋል? ራእይ 19:20 መልሱን ይሰጠናል፦ “አውሬውም ተያዘ፤ በፊቱ ተአምራዊ ምልክቶች የፈጸመው ሐሰተኛው ነቢይም ከእሱ ጋር ተያዘ፤ ይህ ነቢይ በእነዚህ ምልክቶች አማካኝነት፣ የአውሬውን ምስል የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አስቷል። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ።” ስለዚህ እነዚህ የአምላክ ጠላቶች ጥፋት የሚደርስባቸው ሥልጣን ላይ እንዳሉ ነው፤ ጥፋታቸውም ዘላለማዊ ነው።
13. የዓለም መንግሥታት በክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
13 ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክና ለመንግሥቱ ታማኞች መሆን አለብን። (ዮሐ. 18:36) ለዚህም ከዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምንጊዜም ገለልተኛ መሆን ያስፈልገናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት አቋም መያዝ ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ምክንያቱም የዓለም መንግሥታት በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ሙሉ ድጋፋችንን እንድንሰጣቸው ይጠብቁብናል። ለሚያሳድሩት ጫና የሚንበረከኩ ሁሉ የአውሬው ምልክት ይደረግባቸዋል። (ራእይ 13:16, 17) ይህ ምልክት የሚደረግበት ማንኛውም ሰው ግን የይሖዋ ቁጣ ይደርስበታል፤ የዘላለም ሕይወትም አያገኝም። (ራእይ 14:9, 10፤ 20:4) እንግዲያው የሚደረግብን ጫና ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ምንጊዜም የገለልተኝነት አቋም መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው።
ታላቋ አመንዝራ የሚደርስባት አሳፋሪ ውድቀት
14. በራእይ 17:3-5 ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ዮሐንስ ቀጥሎ ምን አስገራሚ ነገር ተመለከተ?
14 ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ ያየው ነገር ‘እጅግ እንዳስደነቀው’ ገለጸ፤ ምን ይሆን? አንዲት ሴት ከእነዚያ ጨካኝ አራዊት አንዱን ስትጋልብ ተመለከተ። (ራእይ 17:1, 2, 6) ይህች ሴት “ታላቂቱ አመንዝራ” እንዲሁም “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ ተገልጻለች። ‘ከምድር ነገሥታት ጋር ምንዝር’ ትፈጽማለች።—ራእይ 17:3-5ን አንብብ።
15-16. “ታላቂቱ ባቢሎን” ማን ናት? እንዴትስ እናውቃለን?
15 “ታላቂቱ ባቢሎን” ማን ናት? ይህች ሴት የፖለቲካ ድርጅት ልትሆን አትችልም፤ ምክንያቱም ከዚህ ዓለም የፖለቲካ መሪዎች ጋር ምንዝር እንደምትፈጽም ተገልጿል። (ራእይ 18:9) እንዲያውም እንደምትጋልባቸው ስለተገለጸ እነዚህን መሪዎች ልትቆጣጠራቸው ትሞክራለች። የሰይጣንን ዓለም ስግብግብ የንግድ ሥርዓትም ልታመለክት አትችልም። የንግዱ ሥርዓት “የምድር ነጋዴዎች” በሚለው መግለጫ ለብቻው ተገልጿል።—ራእይ 18:11, 15, 16
16 በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “አመንዝራ” የሚለው ቃል አምላክን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ ሆኖም በሆነ ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚካፈሉ ወይም በሆነ መንገድ ከዓለም ጋር የሚወዳጁ ሰዎችን ያመለክታል። (1 ዜና 5:25፤ ያዕ. 4:4) በአንጻሩ ግን አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎች “ንጽሕት” ወይም “ደናግል” ተብለው ተገልጸዋል። (2 ቆሮ. 11:2፤ ራእይ 14:4) የጥንቷ ባቢሎን የሐሰት አምልኮ ማዕከል ነበረች። ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን የሐሰት አምልኮዎችን በሙሉ የምትወክል መሆን አለባት። እንዲያውም በዓለም ዙሪያ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን ያቀፈች ናት።—ራእይ 17:5, 18፤ jw.org ላይ የሚገኘውን “ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
17. ታላቂቱ ባቢሎን ምን ይደርስባታል?
17 ታላቂቱ ባቢሎን ምን ይደርስባታል? ራእይ 17:16, 17 መልሱን ይሰጠናል፦ “ያየሃቸው አሥሩ ቀንዶችና አውሬውም አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል። አምላክ . . . ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው አኑሯል።” ይሖዋ ብሔራትን በዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ እንዲነሱና ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸው ያነሳሳቸዋል። ብሔራት ይህን የሚያደርጉት ደማቁን ቀይ አውሬ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተጠቅመው ነው።—ራእይ 18:21-24
18. ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
18 ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? አምልኳችን ምንጊዜም “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ” ሊሆን ይገባል። (ያዕ. 1:27) የታላቂቱ ባቢሎን የሐሰት ትምህርቶች፣ አረማዊ በዓላቷ፣ ልል የሆኑት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቿ እንዲሁም መናፍስታዊ ድርጊቶቿ ተጽዕኖ እንዲያደርጉብን ፈጽሞ አንፍቀድ። በተጨማሪም ሰዎች የኃጢአቷ ተካፋይ እንዳይሆኑ “ከእሷ ውጡ” የሚለውን ጥሪ ማሰማታችንን መቀጠል አለብን።—ራእይ 18:4
በአምላክ ቀንደኛ ጠላት ላይ የተላለፈ ፍርድ
19. “ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ታላቅ ዘንዶ” ማን ነው?
19 የራእይ መጽሐፍ “ደማቅ ቀይ ቀለም” ስላለው ‘ታላቅ ዘንዶም’ ይናገራል። (ራእይ 12:3) ይህ ዘንዶ ከኢየሱስና ከመላእክቱ ጋር ይዋጋል። (ራእይ 12:7-9) በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ እንዲሁም ለአራዊቱ ሥልጣን ይሰጣል። (ራእይ 12:17፤ 13:4) ይህ ዘንዶ ማን ነው? “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ” ነው። (ራእይ 12:9፤ 20:2) ሌሎቹን የይሖዋ ጠላቶች በሙሉ የሚቆጣጠራቸው እሱ ነው።
20. ዘንዶው ምን ይደርስበታል?
20 ዘንዶው ምን ይደርስበታል? ራእይ 20:1-3 እንደሚገልጸው አንድ መልአክ ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ይወረውረዋል፤ ይህም እንደ እስር ባለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚሆን ያመለክታል። ሰይጣን በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሚሆንበት ወቅት ለ1,000 ዓመት ‘ሕዝቦችን ማሳሳት’ አይችልም። በመጨረሻም ሰይጣንና አጋንንቱ “ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ” ይጣላሉ፤ ወይም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋሉ። (ራእይ 20:10) ሰይጣንና አጋንንቱ የሌሉበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው። ያ ጊዜ እንዴት አስደናቂ ይሆናል!
21. በራእይ መጽሐፍ ላይ ያነበብነው ነገር የሚያስደስተን ለምንድን ነው?
21 በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ምልክቶች ትርጉም ማወቅ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! የይሖዋ ጠላቶች እነማን እንደሆኑ ለይተን አውቀናል፤ ምን እንደሚደርስባቸውም ተመልክተናል። በእርግጥም “የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙት . . . ደስተኞች ናቸው።” (ራእይ 1:3) ሆኖም የአምላክ ጠላቶች ከጠፉ በኋላ ታማኝ የሰው ልጆች የትኞቹን በረከቶች ያገኛሉ? ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች በመጨረሻው ላይ ይህን እንመለከታለን።
መዝሙር 23 ይሖዋ መግዛት ጀምሯል
a የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ጠላቶችን በምልክቶች ይገልጻቸዋል። የዳንኤል መጽሐፍ ደግሞ የእነዚህን ምልክቶች ትርጉም ለመረዳት ያግዘናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትንቢቶችን በራእይ መጽሐፍ ላይ ከሚገኙ ተመሳሳይ ትንቢቶች ጋር እናነጻጽራለን። ይህም የአምላክን ጠላቶች ለይተን ለማወቅ ይረዳናል። ከዚያም የአምላክ ጠላቶች ምን እንደሚደርስባቸው እናያለን።
b ባለ ሰባት ራሱ አውሬ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች እንደሚያመለክት የሚጠቁመው ሌላው ነገር “አሥር ቀንዶች” ያሉት መሆኑ ነው። አሥር ቁጥር ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙላትን ለማመልከት ይሠራበታል።
c የአውሬው ምስል ከመጀመሪያው አውሬ በተቃራኒ ቀንዶቹ ላይ “ዘውዶች” የሉትም። (ራእይ 13:1) ምክንያቱም ‘የሚወጣው ከሰባቱ’ ነገሥታት ነው፤ ሥልጣኑን የሚያገኘውም ከእነሱ ነው።—jw.org ላይ የሚገኘውን “በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተጠቀሰው ደማቅ ቀይ አውሬ ምን ያመለክታል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።