ምዕራፍ 37
ባቢሎን ስትጠፋ የሚኖረው ልቅሶና ደስታ
1. ታላቂቱ ባቢሎን በድንገት ስትጠፋ “የምድር ነገሥታት” እንዴት ይሰማቸዋል?
የባቢሎን መጥፋት ለይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ የምሥራች ነው። ይሁን እንጂ ብሔራት እንዴት ይሰማቸው ይሆን? ዮሐንስ ይነግረናል:- “ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው:- አንቺ ታላቂቱ ከተማ፣ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፣ ወዮልሽ፣ ወዮልሽ፣ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ።”—ራእይ 18:9, 10
2. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፉት የቀዩ አውሬ ምሳሌያዊ አሥር ቀንዶች ከሆኑ “የምድር ነገሥታት” በመጥፋትዋ ምክንያት የሚያዝኑት ለምንድን ነው? (ለ) በጣም ያዘኑት ነገሥታት ከጠፋችው ከተማ ራቅ ብለው የሚቆሙት ለምንድን ነው?
2 ባቢሎንን ያጠፉት የቀዩ አውሬ ምሳሌያዊ አሥር ቀንዶች መሆናቸውን ስንመለከት ብሔራት በጥፋትዋ ምክንያት ማዘናቸው ሊያስገርመን ይችላል። (ራእይ 17:16) ባቢሎን ከጠፋች በኋላ “የምድር ነገሥታት” ታላቂቱ ባቢሎን ሕዝቦቻቸውን በማረጋጋትና በማስገዛት ረገድ በጣም ትጠቅማቸው እንደነበረ ይገነዘባሉ። ቀሳውስት ጦርነት ቅዱስ ነው ብለዋል። ወታደሮችን ለመመልመል መሣሪያ ሆነዋል። ወጣቶች በጦር ሜዳ እንዲሰለፉ ሰብከዋል። ምግባረ ብልሹ ገዥዎች ሃይማኖት በሰጣቸው የቅድስና መጋረጃ ተሸፍነው ተራውን ሕዝብ ጨቁነዋል። (ከኤርምያስ 5:30, 31ና ከማቴዎስ 23:27, 28 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እነዚህ በሐዘን የተመቱ ነገሥታት ከጠፋችው ከተማ ራቅ ብለው እንደቆሙ እናስተውል። ወደ እርስዋ ተጠግተው አይረዱአትም። በመጥፋትዋ ምክንያት ቢያዝኑም ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው ሊረዱአት አልፈለጉም።
ነጋዴዎች ያለቅሳሉ፣ ያዝናሉ
3. በታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት ምክንያት የሚያዝኑት ሌሎች እነማን ናቸው? ለዚህስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ዮሐንስ ተናግሮአል?
3 በታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት የሚያዝኑት የምድር ነገሥታት ብቻ አይደሉም። “የመርከባቸውን ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር [“ተጓዥ፣” NW] ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፣ ቀጭንም የተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣ ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፣ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፣ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።”—ራእይ 18:11-14
4. ‘ተጓዥ ነጋዴዎች’ ታላቂቱ ባቢሎን በመጥፋትዋ የሚያለቅሱትና የሚያዝኑት ለምንድን ነው?
4 አዎ፣ ታላቂቱ ባቢሎን የባለጠጋ ነጋዴዎች የቅርብ ወዳጅና ጥሩ ደንበኛ ነበረች። ለምሳሌ ያህል አድባራት፣ ገዳማትና የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ በርካታ ወርቅ፣ ብር፣ ዕንቁ፣ ውድ እንጨቶችና ብዙ ዓይነት ሌላ ሀብት አከማችተዋል። ከዚህም በላይ ክርስቶስን በሚያዋርደው የገና በዓልና በሌሎች ዓመት በዓላት የሚታየው የሸመታ ትርምስና ፈንጠዝያ የሃይማኖትን ድጋፍና ቡራኬ ያገኘ ነው። የሕዝበ ክርስትና ሚሲዮኖች ራቅ ወዳሉ አገሮች ጠልቀው እየገቡ ለዚህ ዓለም ነጋዴዎች ሸቀጥ ማራገፊያ የሚሆኑ አዳዲስ ገበያዎችን ከፍተዋል። በጃፓን አገር በ17ኛው መቶ ዘመን ከነጋዴዎች ጋር አብሮ የገባው የካቶሊክ እምነት በባላባታዊ ግጭቶች እንኳን ይካፈል ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ በኦሳካ ቤተ መንግሥት ውስጥ ስለተፈጸመ ወሳኝ ውጊያ ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል:- “የቶኩጋዋ ሠራዊት መስቀል የተሳለበት አርማና የመድኃኒታችንንና የስፓኝ ባለአደራ የሆነውን የቅዱስ ያዕቆብን ምስል ከያዙ ጠላቶች ጋር ተጋጠመ።” ድል አድራጊው ወገን ከፍተኛ ስደት አካሂዶ ከዚያች አገር የካቶሊክን እምነት ጨርሶ አጥፍቶአል። ዛሬም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን በዓለማዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትዋ ምንም ዓይነት በረከት አያስገኝላትም።
5. (ሀ) ከሰማይ የተሰማው ድምፅ ‘ተጓዥ ነጋዴዎች’ የተሰማቸውን ሐዘን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ነጋዴዎቹም ‘ራቅ ብለው’ የቆሙት ለምንድን ነው?
5 ከሰማይ የተሰማው ድምፅ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ:- በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጎናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፣ ወዮላት፣ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ሥቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ።” (ራእይ 18:15-17ሀ) “ነጋዴዎቹ” ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ የንግድ ሸሪካቸውን ስለሚያጡ ያዝናሉ። በእውነትም “ወዮ፣ ወዮ” የሚያሰኝ ነው። ይሁን እንጂ ሐዘናቸው ከራስ ወዳድነት የመነጨ እንደሆነ እናስተውል። ምክንያቱም እነርሱም እንደ ነገሥታቱ “ከሩቅ ቆመዋል።” ታላቂቱ ባቢሎንን ለመርዳት ጠጋ አላሉም።
6. ከሰማይ የተሰማው ድምፅ የመርከብ አለቆችና ባሕረኞች የተሰማቸውን ሐዘን የገለጸው እንዴት ነው? የሚያለቅሱትስ ለምንድን ነው?
6 ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ሥፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፣ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ:- ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፣ ወዮላት፣ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።” (ራእይ 18:17ለ-19) የጥንትዋ ባቢሎን የንግድ ከተማ ስለነበረች ብዙ መርከቦች ነበሩአት። ታላቂቱ ባቢሎንም በተመሳሳይ ሕዝቦችዋ በሆኑት “ብዙ ውኃዎች” አማካኝነት ብዙ ትነግዳለች። ይህም ንግድዋ ለብዙ ሃይማኖታዊ ተገዥዎችዋ የሥራ ዕድል ከፍቶላቸዋል። የታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት ለእነዚህ ሰዎች ትልቅ የኢኮኖሚ ውድቀት ይሆንባቸዋል። እርስዋ ከጠፋች ሌላ መተዳደሪያ ሊያገኙ አይችሉም።
በመጥፋትዋ መደሰት
7, 8. ከሰማይ የተሰማው ድምፅ ስለ ታላቂቱ ባቢሎን የተናገረውን መልእክት ያጠቃለለው እንዴት ነው? እነዚህንስ ቃላት በደስታ የሚቀበሉት እነማን ናቸው?
7 የጥንትዋ ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን በተገለበጠች ጊዜ ኤርምያስ “አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን እልል ይላሉ” ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 51:48) ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ ከሰማይ ይሰማ የነበረው ድምፅ:- “ሰማይ ሆይ፣ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፣ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፣ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና” በማለት መልእክቱን አጠቃልሎአል። (ራእይ 18:20) ይሖዋና መላእክት እንዲሁም አሁን ከሙታን ተነስተው ለ24ቱ ሽማግሌዎች በተዘጋጀው ሰማያዊ ቦታ የተቀመጡት የጥንት ክርስቲያን ነቢያትና ሐዋርያት ለረዥም ዘመን የአምላክ ጠላት ሆና የቆየችው ድርጅት ድምጥማጥዋ ሲጠፋ በጣም ይደሰታሉ።—ከመዝሙር 97:8-12 ጋር አወዳድር።
8 በእርግጥም ከሙታን የተነሱትም ሆኑ ገና ከምድር ያልተወሰዱት “ቅዱሳን” የሌሎች በጎች ክፍል ከሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ጋር ሆነው በደስታ እልል ይላሉ። ጊዜው ሲደርስ ደግሞ የጥንት ታማኝ ሰዎች ከሙታን ተነስተው በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ሲኖሩ ከዚህ ታላቅ ደስታ ይካፈላሉ። የአምላክ ሕዝቦች ያሳደዱአቸውን የሐሰት ሃይማኖተኞች ለመበቀል አልሞከሩም። “በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ [“ይሖዋ፣” NW]” የሚለውን የይሖዋን ቃል ያስታውሳሉ። (ሮሜ 12:19፤ ዘዳግም 32:35, 41-43) አሁን ይሖዋ ብድራቱን ይመልስላቸዋል። ታላቂቱ ባቢሎን ያፈሰሰችውን ደም በሙሉ ትከፍላለች።
አንድን ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ መወርወር
9, 10. (ሀ) አሁን ብርቱው መልአክ ምን አደረገ? ምንስ ተናገረ? (ለ) በራእይ 18:21 ላይ የተጠቀሰው ብርቱ መልአክ የፈጸመው የትኛው ድርጊት በኤርምያስ ዘመን ተፈጽሞ ነበር? ይህስ ለምን ነገር ዋስትና ሆኖ ነበር? (ሐ) ዮሐንስ የተመለከተው ብርቱ መልአክ የፈጸመው ድርጊት ለምን ነገር ማረጋገጫ ነው?
9 ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ነገር ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጽመው ፍርድ የመጨረሻ መሆኑን ያረጋግጣል። “አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል:- ‘ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም።’” (ራእይ 18:21) በኤርምያስ ዘመንም ጠንካራ ትንቢታዊ መልእክት ያለው ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሞ ነበር። ኤርምያስ “በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ” በመጽሐፍ እንዲጽፍ በመንፈስ ተመርቶ ነበር። የጻፈውንም መጽሐፍ ለሠራያ ሰጠውና ይዞት ወደ ባቢሎን እንዲሄድ አዘዘው። ባቢሎን እንደደረሰም ኤርምያስ እንዳዘዘው በከተማይቱ ላይ የተነገረውን የጥፋት መልእክት አነበበ። “አቤቱ [“ይሖዋ፣” NW] ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት ለዘላለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚህች ሥፍራ ተናግረሃል።” ከዚያም በኋላ ሠራያ በመጽሐፉ ላይ ድንጋይ አሠረና “እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች፣ አትነሣምም” ብሎ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወረወረው።—ኤርምያስ 51:59-64
10 መጽሐፉ ድንጋይ ታስሮበት ወደ ወንዝ መጣሉ ባቢሎን ተመልሳ ልታንሰራራ በማትችልበት ሁኔታ እንደምትጣል ያረጋግጣል። ሐዋርያው ዮሐንስም አንድ ብርቱ መልአክ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም መመልከቱ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመው የይሖዋ ዓላማ ሳይፈጸም እንደማይቀር ጠንካራ ዋስትና ይሰጣል። የጥንትዋ ባቢሎን ፈራርሳና ባድማ ሆና መታየትዋ በቅርቡ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ለሚፈጸመው ነገር ማረጋገጫ ነው።
11, 12. (ሀ) አሁን ብርቱው መልአክ ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ምን ተናገረ? (ለ) ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር? ይህስ ለዘመናችን ምን ያመለክታል?
11 አሁን ብርቱው መልአክ እንደሚከተለው በማለት ለታላቂቱ ባቢሎን ይናገራል:- “በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እምቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፣ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፣ የወፍጮ ድምፅም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፣ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፣ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፣ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።”—ራእይ 18:22, 23
12 ኤርምያስም ከዚህ ጋር በሚመሳሰሉ ቃላት ስለ ከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ትንቢት ተናግሮአል:- “ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ፣ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች።” (ኤርምያስ 25:10, 11) ሕዝበ ክርስትና የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል እንደመሆንዋ መጠን ኢየሩሳሌም ከ607 ከዘአ ባድማ ከሆነች በኋላ በነበሩት ዓመታት እንደታየው ባለ ሁኔታ ሕይወት የማይኖርባት ፍርስራሽ ትሆናለች። አንድ ዘመን የደስታ ውካታና እንቅስቃሴ ይታይባት የነበረችው ሕዝበ ክርስትና የተወረረችና ወና ትሆናለች።
13. በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ምን ዓይነት ድንገተኛ ለውጥ ይመጣባታል? ‘በተጓዥ ነጋዴዎችዋ’ ላይስ ምን ዓይነት ውጤት ይመጣባቸዋል?
13 በእርግጥም መልአኩ ለዮሐንስ እንደተናገረው ታላቂቱ ባቢሎን ዓለም አቀፋዊ ኃያል ግዛት ከመሆንዋ ወርዳ ደረቅና ጠፍ ምድር ትሆናለች። “ነጋዴዎችዋ”፣ በጣም ከበርቴ የሆኑትም ጭምር የታላቂቱ ባቢሎንን ሃይማኖት የግል ጥቅማቸው ማራመጃ በማድረግ ወይም በሽፋንነት ተጠቅመውበታል። ቀሳውስቱም ከእነዚህ ከበርቴዎች ጋር ሆነው ጋዜጣ ላይ መታየታቸው ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ አግኝተውታል። ከዚያ በኋላ ግን የምድር ነጋዴዎች የታላቂቱ ባቢሎንን ሽርክና አያገኙም። ከዚያ በኋላ የምድርን አሕዛብ በምስጢራዊ የሃይማኖት ሥርዓቶችዋና ምትሐቶችዋ አታደናግራቸውም።
በጣም አስደንጋጭ የሆነ የደም ወንጀል
14. ብርቱው መልአክ የይሖዋ ፍርድ ከባድ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ ምን ብሎአል? ኢየሱስም በምድር ሳለ ምን ተመሳሳይ ነገር ተናግሮ ነበር?
14 ብርቱው መልአክ መልእክቱን ሲያጠቃልል ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲህ ያለ የጭካኔ ፍርድ የፈረደበትን ምክንያት ይነግረናል:- “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።” (ራእይ 18:24) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ‘ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በምድር ላይ ለፈሰሰው ደም ሁሉ’ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ተናግሮ ነበር። በዚህም ምክንያት ያ ጠማማ ትውልድ በ70 እዘአ ጠፋ። (ማቴዎስ 23:35-38) ዛሬ ደግሞ ሌላ የሃይማኖታዊያን ትውልድ የአምላክን አገልጋዮች በማሳደዱ ምክንያት የደም ዕዳ ተከምሮበታል።
15. በናዚ ጀርመን የነበረችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሁለት መንገዶች የደም ወንጀለኛ የሆነችው እንዴት ነው?
15 ጉንተር ሌዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የናዚዋ ጀርመን በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 13 ቀን [1933] በባቫሪያ በታገዱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ይህን የተከለከለ ሃይማኖት የሚከተል ማንኛውንም ሰው እንድትጠቁም የትምህርትና የሃይማኖት ሚኒስቴር የሰጣትን የሥራ ድርሻ እንኳን ተቀብላ ነበር።” ስለዚህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በመታጎራቸው በኃላፊነት ትጠየቃለች። እጆችዋም በተገደሉት በመቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደም ተጨማልቀዋል። እንደ ቪልኸልም ኩሴሮቭ የመሰሉት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አለምንም ፍርሐት በጥይት ተደብድበው ለመሞት ፈቃደኞች እንደሆኑ በታየ ጊዜ ሂትለር በሕሊና ምክንያት አንዋጋም የሚሉ ሁሉ በጥይት ተረሽነው መገደል የለባቸውም ብሎ ወሰነ። በዚህም ምክንያት ይበልጥ አሰቃቂ የሆነ አገዳደል ተመረጠና የቪልኸልም ወንድም የነበረው ቮልፍጋንግ በ20 ዓመት ዕድሜው ጊሎቲን በተባለው ስለት አንገቱ ተቆርጦ ሞተ። በዚህ ጊዜ ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወጣት ጀርመናውያን ካቶሊኮች ከአባት አገራቸው ሠራዊት ጋር ተሰልፈው እንዲሞቱ ታበረታታ ነበር። የቤተ ክርስቲያን የደም አፍሳሽነት ወንጀል በግልጽ ሊታይ የሚችል ነው።
16, 17. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን ለየትኛው የደም ወንጀል መጠየቅ ይኖርባታል? ናዚዎች ለፈጸሙት የአይሁዳውያን እልቂት ቫቲካን በወንጀለኛነት መጠየቅ የሚኖርባት ለምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን በተደረጉት በመቶ የሚቆጠሩ ጦርነቶች ለሞቱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት በኃላፊነት ከምትጠየቅባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
16 ይሁን እንጂ “በምድር ለታረዱ ሁሉ ደም” በወንጀለኛነት የምትጠየቀው ታላቂቱ ባቢሎን እንደሆነች ትንቢቱ ይናገራል። የዘመናችንም ታሪክ ይህን ያረጋግጣል። ለምሳሌ ያህል ሂትለርን በጀርመን አገር ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ያስቻለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ደባ ነው። በዚህም ምክንያት ቫቲካን በናዚዎች የእልቂት ዘመቻ ለተገደሉት ስድስት ሚልዮን አይሁዶች ሕይወት ተጠያቂ ነች። ከዚህም በላይ በዚህ ዘመን ከመቶ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በመቶ በሚቆጠሩ ጦርነቶች ተገድለዋል። በዚህስ ረገድ የሐሰት ሃይማኖት ተጠያቂ ትሆናለችን? አዎ፣ በሁለት መንገዶች ተጠያቂ ነች።
17 አንደኛው መንገድ ብዙዎቹ ጦርነቶች የተደረጉት በሃይማኖታዊ ልዩነቶች ምክንያት መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል ከ1946-48 በሕንድ አገር በሂንዱዎችና በእስላሞች መካከል ተደርጎ የነበረው ግጭት መነሻ ምክንያቱ ሃይማኖት ነበር። በዚህም ግጭት ምክንያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶአል። በ1980ዎቹ ዓመታት በኢራቅና በኢራን መካከል የተደረገው ጦርነት ምክንያቱ ሃይማኖታዊ ልዩነት ነበር። በዚህም ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሰሜን አየርላንድ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል የሚካሄደው አምባጓሮ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኖአል። የርዕሰ አንቀጽ ጸሐፊ የሆኑት ሲ ኤል ሱልዝበርገር በ1976 ስለዚህ ጉዳይ ጥናት ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከሚደረጉት ጦርነቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑ በጣም የሚያሳዝን ሐቅ ነው።” እርግጥ ነው ጦርነትና ግጭት የተበጠበጠ ታሪክ ባላት ታላቂቱ ባቢሎን በኖረችበት ዘመን ሁሉ የነበረ ነው።
18. የዓለም ሃይማኖቶች የደም ወንጀለኞች የሚሆኑበት ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?
18 ሁለተኛውስ መንገድ ምንድን ነው? ዓለማዊ ሃይማኖቶች በሙሉ በይሖዋ ዓይን የደም ወንጀለኞች ናቸው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ስለሚፈልገው ብቃት የሚገልጸውን እውነት በሚያሳምን መንገድ ለተከታዮቻቸው አላስተማሩም። የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ኢየሱስ ክርስቶስን መምስል እንደሚኖርባቸውና የማንኛውንም ብሔርና ጎሣ አባላት ማፍቀር እንደሚኖርባቸው በሚያሳምን ሁኔታ አላስተማሩም። (ሚክያስ 4:3, 5፤ ዮሐንስ 13:34, 35፤ ሥራ 10:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) የታላቂቱ ባቢሎን አባላት የሆኑት ሃይማኖቶች እነዚህን ነገሮች ስለማያስተምሩ ተከታዮቻቸው በዓለም አቀፋዊ ግጭቶችና ጦርነቶች ተላልቀዋል። ለዚህም በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተፈጸሙት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በቂ መረጃ ናቸው። እነዚህ ሁለት ጦርነቶች ተቀስቅሰው ሃይማኖት አለን የሚሉ ሰዎችን እርስበርሳቸው ያጨራረሱት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ እነዚህ ጦርነቶች ሊጀመሩ አይችሉም ነበር።
19. ታላቂቱ ባቢሎን እንዴት ያለ አስደንጋጭ የደም ወንጀል ተሸክማለች?
19 ይሖዋ ለዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ ተወቃሽ የሚያደርገው ታላቂቱ ባቢሎንን ነው። ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ በተለይም የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ለሕዝቦቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ቢያስተምሩ ኖሮ ይህን የሚያክል የደም ጎርፍ አይፈስም ነበር። ስለዚህ ታላቂቱ አመንዝራና ታላቂቱ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት፣ ታላቂቱ ባቢሎን ራስዋ ላሳደደቻቸውና ለገደለቻቸው “ነቢያትና ቅዱሳን ደም” ብቻ ሳይሆን “በምድር ለታረዱ ሁሉ ደም” ጭምር ለይሖዋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልስ መስጠት ይኖርባታል። በእርግጥም ታላቂቱ ባቢሎን በጣም ከባድ የደም ዕዳ በጫንቃዋ ላይ ተሸክማለች። ፍጻሜዋ በሚደርስበት ጊዜ ድምጥማጥዋ መጥፋቱ እንዴት ያለ ጥሩ ነገር ይሆናል!
[በገጽ 270 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጽኑ አቋም ይዞ አለመቆም የሚያስከትለው ኪሣራ
ጉንተር ሌዊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የናዚዋ ጀርመን በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “የጀርመን ካቶሊክ ሃይማኖት ከመጀመሪያው አንስቶ የናዚን መንግሥት ቢቃወም ኖሮ የዓለም ታሪክ ከአሁኑ የተለየ አቅጣጫ ይከተል ነበር። የቤተ ክርስቲያን ጥረት ሂትለርን ለማሸነፍና ብዙዎቹ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ለመከልከል ባይችልም እንኳን የቤተ ክርስቲያንን ሞራልና ክብር በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን ከፍ ሊያደርገው ይችል ነበር። እንዲህ ያለ ተቃውሞ ማቅረብ በሰዎች ላይ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መሥዋዕትነት በጣም ከፍተኛ ለሆነ ዓላማ ይውል ነበር። ሂትለር የገዛ አገሩ ሁኔታ እንደማያስተማምን ሲመለከት ሌሎች አገሮችን ለመውረር አይደፍርም ነበር። በዚህም መንገድ በሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት ከሞት ይተርፍ ነበር። . . . በሺህ የሚቆጠሩ ፀረ ናዚ ጀርመኖች በሂትለር ኮንሴንትሬሽን ካምፖች ውስጥ በሥቃይ ሲሞቱ፣ በሺህ የሚቆጠሩ የፖላንድ ምሁራን ሲጨፈጨፉ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሩስያውያን ኡንተርሜንሸን [ከሰው በታች የሆኑ ፍጥረታት] ናቸው ተብለው ሲገደሉ፣ 6, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች በዘራችሁ አርያውያን አይደላችሁም ተብለው ሲታረዱ በጀርመን አገር የነበሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች የመንግሥቱን አቋም እያጠነከሩ ለእነዚህ ወንጀሎች ተባባሪ ሆነው ነበር። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ራስና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አስተማሪ የሆኑት የሮማው ፓፓም ይህ ሁሉ ሲፈጸም ጸጥ ብለው ነበር።”—ገጽ 320, 341
[በገጽ 268 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገዥዎች “ወዮላት፣ ወዮላት” ይላሉ
[በገጽ 268 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጋዴዎች “ወዮላት፣ ወዮላት ይላሉ”