የጥናት ርዕስ 40
“የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን” መርዳት
“የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን [የሚረዱ] ለዘላለም እንደ ከዋክብት ያበራሉ።”—ዳን. 12:3
መዝሙር 151 አምላክ ይጣራል
ማስተዋወቂያa
1. በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የትኞቹ አስደሳች ክንውኖች ይጠብቁናል?
በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በምድር ላይ ትንሣኤ መከናወን የሚጀምርበት ዕለት ምንኛ አስደሳች ይሆናል! የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ በሙሉ ዳግመኛ ሊያዩአቸው ይናፍቃሉ። ይሖዋም የሚሰማው እንዲህ ነው። (ኢዮብ 14:15) በመላው ምድር የተነፋፈቁ ሰዎች ሲገናኙ ምንኛ ደስታ እንደሚሰፍን እስቲ አስቡት! ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ “ጻድቃን” “ለሕይወት ትንሣኤ” ይወጣሉ። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:29) ምናልባትም በሞት ካጣናቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በምድራዊው ትንሣኤ ወቅት መጀመሪያ ከሚነሱት መካከል ሊሆኑ ይችላሉ።b በተጨማሪም “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ለምሳሌ ከመሞታቸው በፊት ይሖዋን ለማወቅ ወይም እሱን በታማኝነት ለማገልገል በቂ አጋጣሚ ያላገኙ ሰዎች “ለፍርድ ትንሣኤ” ይወጣሉ።
2-3. (ሀ) ኢሳይያስ 11:9, 10 እንደሚጠቁመው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር የትኛው ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች በሙሉ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። (ኢሳ. 26:9፤ 61:11) በመሆኑም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር መዘርጋት አለበት። (ኢሳይያስ 11:9, 10ን አንብብ።) ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ ትንሣኤ ያገኙ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ስለ ቤዛው እንዲሁም ከይሖዋ ስምና ከሉዓላዊነቱ ጋር በተያያዘ ስለተነሳው ወሳኝ ጥያቄ መማር ይኖርባቸዋል። ጻድቃንም ቢሆኑ እነሱ ከሞቱ በኋላ ይሖዋ ለምድር ካለው ዓላማ ጋር በተያያዘ ደረጃ በደረጃ የገለጻቸውን ነገሮች መማር ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ ታማኝ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የሞቱት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከመጠናቀቁ በፊት ነው። በመሆኑም ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች የሚማሩት ብዙ ነገር አለ።
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ይህ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር የሚካሄደው እንዴት ነው? ሰዎች ለዚህ ትምህርት የሚሰጡት ምላሽ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ በቋሚነት ከመጻፉ ጋር በተያያዘ ምን ለውጥ ያመጣል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ በዛሬው ጊዜ ያለነውን እኛን ሊያሳስበን ይገባል። በዳንኤል እና በራእይ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አስደናቂ ትንቢቶች ሙታን በሚነሱበት ጊዜ የሚሆነውን ነገር በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ የሚያጠሩልን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን በዳንኤል 12:1, 2 ላይ በሚገኘው ትንቢት ውስጥ የተገለጹትን አስደሳች ክንውኖች እንመልከት።
‘በምድር አፈር ውስጥ ያንቀላፉት ይነሳሉ’
4-5. ዳንኤል 12:1 ስለ ፍጻሜው ዘመን ምን ይናገራል?
4 ዳንኤል 12:1ን አንብብ። የዳንኤል መጽሐፍ በፍጻሜው ዘመን አንዳንድ አስደናቂ ክንውኖች የሚከሰቱበትን ቅደም ተከተል ይነግረናል። ለምሳሌ ዳንኤል 12:1 ሚካኤል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ለአምላክ ሕዝብ እንደቆመ’ ይነግረናል። ይህ የትንቢቱ ክፍል መፈጸም የጀመረው ኢየሱስ በ1914 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ጊዜ ነው።
5 ሆኖም ዳንኤል ኢየሱስ ‘እንደሚነሳም’ ተነግሮታል። ይህ የሚሆነው “ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ” በሚመጣበት ወቅት ነው። ይህ የጭንቀት ጊዜ በማቴዎስ 24:21 ላይ ከተገለጸው “ታላቅ መከራ” ጋር አንድ ዓይነት ነው። ኢየሱስ በዚህ የጭንቀት ጊዜ መጨረሻ ማለትም በአርማጌዶን ወቅት የአምላክን ሕዝቦች ለመታደግ ይነሳል ወይም እርምጃ ይወስዳል። የራእይ መጽሐፍ እነዚህን የአምላክ ሕዝቦች “ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ [እጅግ ብዙ ሕዝብ]” በማለት ይጠራቸዋል።—ራእይ 7:9, 14
6. እጅግ ብዙ ሕዝብ ታላቁን መከራ ካለፉ በኋላ ምን ይከናወናል? አብራራ። (በተጨማሪም በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን ስለ ምድራዊ ትንሣኤ የሚገልጸውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።)
6 ዳንኤል 12:2ን አንብብ። እጅግ ብዙ ሕዝብ ይህን የጭንቀት ጊዜ ካለፉ በኋላ ምን ይከናወናል? ይህ ትንቢት ቀደም ሲል እናስብ እንደነበረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የሚከናወነውን ምሳሌያዊ ትንሣኤ ማለትም የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ማንሰራራታቸውን የሚያመለክት አይደለም።c ከዚህ ይልቅ ይህ ሐሳብ የሚናገረው በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚከናወነው የሙታን ትንሣኤ ነው። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደረገን ምንድን ነው? “አፈር” የሚለው ቃል በኢዮብ 17:16 ላይ ‘መቃብርን’ ለማመልከት ተሠርቶበታል። በመሆኑም ዳንኤል 12:2 የሚናገረው የመጨረሻዎቹ ቀናት ካበቁና የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ስለሚኖረው የሙታን ትንሣኤ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።
7. (ሀ) አንዳንዶች “ለዘላለም ሕይወት” ይነሳሉ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ይህ ትንሣኤ “የተሻለ ትንሣኤ” የሆነው በምን መንገድ ነው?
7 ይሁንና ዳንኤል 12:2 አንዳንዶች “ለዘላለም ሕይወት” እንደሚነሱ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል ይሖዋንና ኢየሱስን የሚያውቁ ወይም ማወቃቸውን የሚቀጥሉ እንዲሁም በ1,000 ዓመቱ ወቅት እነሱን የሚታዘዙ ሰዎች በመጨረሻ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። (ዮሐ. 17:3) ይህ በጥንት ጊዜ ከሞት የተነሱ አንዳንድ ሰዎች ካገኙት ትንሣኤ “የተሻለ ትንሣኤ” ይሆናል። (ዕብ. 11:35) ለምን? ምክንያቱም ከሞት የተነሱት እነዚያ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በድጋሚ ሞተዋል።
8. ሌሎች “ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት” ይነሳሉ ሲባል ምን ማለት ነው?
8 ሆኖም ከሞት ከተነሱት ሰዎች መካከል ይሖዋ ያዘጋጀውን የትምህርት መርሐ ግብር የማይቀበሉ ይኖራሉ። የዳንኤል ትንቢት አንዳንዶች “ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት” እንደሚነሱ ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች የዓመፀኝነት መንፈስ ስለሚያሳዩ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ አይጻፍም፤ የዘላለም ሕይወትም አያገኙም። ከዚህ ይልቅ “ዘላለማዊ ውርደት” ወይም ጥፋት ይደርስባቸዋል። ስለዚህ ዳንኤል 12:2 የሚናገረው ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች በሙሉ ከሞት ከተነሱ በኋላ በሚያደርጉት ነገር መሠረት የሚጠብቃቸውን የመጨረሻ ዕጣ ነው።d (ራእይ 20:12) አንዳንዶች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ፤ ሌሎች ደግሞ አያገኙም።
“የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን” መርዳት
9-10. ከታላቁ መከራ በኋላ ሌላስ ምን ይከናወናል? “እንደ ሰማይ ጸዳል [የሚያበሩትስ]” እነማን ናቸው?
9 ዳንኤል 12:3ን አንብብ። ከመጪው “የጭንቀት ጊዜ” በኋላ ሌላስ ምን ይከናወናል? ከዳንኤል 12:2 በተጨማሪ ቁጥር 3ም ከታላቁ መከራ በኋላ ምን እንደሚከናወን ይናገራል።
10 “እንደ ሰማይ ጸዳል [የሚያበሩት]” እነማን ናቸው? ኢየሱስ በማቴዎስ 13:43 ላይ የተናገረው ሐሳብ ፍንጭ ይሰጠናል። ኢየሱስ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” ብሏል። ኢየሱስ በዚህ ወቅት እየተናገረ የነበረው ስለ “መንግሥቱ ልጆች” ማለትም በሰማያዊ መንግሥቱ አብረውት ስለሚያገለግሉት ቅቡዓን ወንድሞቹ ነው። (ማቴ. 13:38) ስለዚህ ዳንኤል 12:3 የሚናገረው ስለ ቅቡዓኑና እነሱ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ስለሚያከናውኑት ሥራ መሆን አለበት።
11-12. መቶ አርባ አራት ሺዎቹ በ1,000 ዓመቱ ወቅት ምን ሥራ ያከናውናሉ?
11 ቅቡዓኑ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ “ብዙ ሰዎችን” የሚረዱት እንዴት ነው? ቅቡዓኑ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመተባበር በ1,000 ዓመቱ ወቅት በምድር ላይ የሚካሄደውን የትምህርት መርሐ ግብር ይመራሉ። መቶ አርባ አራት ሺዎቹ፣ ነገሥታት ሆነው ከመግዛት በተጨማሪ ካህናት ሆነውም ያገለግላሉ። (ራእይ 1:6፤ 5:10፤ 20:6) በዚህ መንገድ “ሕዝቦችን [በመፈወሱ]” ማለትም የሰው ልጆች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ በመርዳቱ ሥራ ይካፈላሉ። (ራእይ 22:1, 2፤ ሕዝ. 47:12) ቅቡዓኑ በዚህ ሥራ ሲካፈሉ ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!
12 የጽድቅን ጎዳና ከሚከተሉት “ብዙ ሰዎች” መካከል እነማን ይገኙበታል? ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች፣ አርማጌዶንን የሚያልፉት ሰዎች እንዲሁም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚወለዱት ልጆች ይገኙበታል። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በሙሉ ፍጹማን ይሆናሉ። ታዲያ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ በእርሳስ ሳይሆን በብዕር በቋሚነት የሚጻፈው መቼ ነው?
የመጨረሻው ፈተና
13-14. በምድር ላይ ያሉ ፍጹማን ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ከማግኘታቸው በፊት ምን ማስመሥከር ይኖርባቸዋል?
13 አንድ ሰው ፍጹም ስለሆነ ብቻ የዘላለም ሕይወት ያገኛል ማለት እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ለምሳሌ አዳምና ሔዋን ፍጹማን ቢሆኑም እንኳ የዘላለም ሕይወት ከማግኘታቸው በፊት ለይሖዋ አምላክ ያላቸውን ታዛዥነት ማስመሥከር እንደነበረባቸው አስታውሱ። የሚያሳዝነው ደግሞ ይሖዋን ሳይታዘዙ ቀርተዋል።—ሮም 5:12
14 በ1,000 ዓመቱ መጨረሻ ላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታስ ምን ይመስላል? ሁሉም ፍጽምና ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ይሁንና እነዚህ ፍጹማን ሰዎች ለዘላለም የይሖዋን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ? ወይስ እንደ አዳምና እንደ ሔዋን ፍጹማን ቢሆኑም እንኳ ታማኝነታቸውን ያጓድላሉ? እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል፤ ግን እንዴት?
15-16. (ሀ) ሁሉም የሰው ልጆች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩበት አጋጣሚ የሚያገኙት መቼ ነው? (ለ) የዚህ ፈተና የመጨረሻ ውጤት ምን ይሆናል?
15 በ1,000 ዓመቱ ወቅት ሰይጣን ይታሰራል። በዚያ ወቅት ማንንም ማሳሳት አይችልም። ሆኖም በ1,000 ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል። ከዚያም ፍጹም የሆኑ ሰዎችን ለማሳሳት ይሞክራል። በዚያ የፈተና ወቅት በምድር ላይ ያሉ ፍጹም የሰው ልጆች በሙሉ ከአምላክ ስምና ከሉዓላዊነቱ ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄ ላይ ከየትኛው ወገን እንደሚሰለፉ በግልጽ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ራእይ 20:7-10) ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ በቋሚነት መጻፍ አለመጻፉ የተመካው ለሰይጣን ፈተና በግለሰብ ደረጃ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ነው።
16 ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ሰዎች እንደ አዳምና እንደ ሔዋን የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? ራእይ 20:15 መልሱን ይሰጠናል፦ “በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ።” አዎ፣ እነዚህ ዓመፀኞች ለዘላለም ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ፍጹም ሰዎች ይህን የመጨረሻ ፈተና ያልፋሉ። ከዚያ በኋላ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ በቋሚነት ይጻፋል።
‘በፍጻሜው ዘመን’
17. ዳንኤል ስለ ዘመናችን ምን ተነግሮታል? (ዳንኤል 12:4, 8-10)
17 ወደፊት ስለሚከናወኑት ነገሮች ማሰብ ምንኛ ያስደስታል! ይሁንና መልአኩ ለዳንኤል ስለ “ፍጻሜው ዘመን” ማለትም ስለ ዘመናችንም አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎች ሰጥቶታል። (ዳንኤል 12:4, 8-10ን አንብብ፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) መልአኩ ለዳንኤል “እውነተኛው እውቀት [እንደሚበዛ]” ነግሮታል። አዎ፣ የአምላክ ሕዝቦች በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ይረዷቸዋል። አክሎም መልአኩ በዚያ ወቅት “ክፉዎች . . . ክፉ ድርጊት [እንደሚፈጽሙና] ከክፉዎች መካከል አንዳቸውም [እንደማይረዱት]” ተናግሯል።
18. ክፉዎች በቅርቡ ምን ይደርስባቸዋል?
18 በዛሬው ጊዜ ክፉዎች ለክፋታቸው የሚገባቸውን ቅጣት የማያገኙ ሊመስል ይችላል። (ሚል. 3:14, 15) ሆኖም ኢየሱስ በቅርቡ በፍየል በተመሰሉት ሰዎች ላይ ይፈርድባቸዋል፤ እንዲሁም በበግ ከተመሰሉት ሰዎች ይለያቸዋል። (ማቴ. 25:31-33) እነዚህ ክፉዎች ከታላቁ መከራ አይተርፉም፤ ትንሣኤ አግኝተውም በአዲሱ ዓለም ውስጥ አይኖሩም። ስማቸው በሚልክያስ 3:16 ላይ በተጠቀሰው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ውስጥ አይገኝም።
19. አሁን ምን የምናደርግበት ጊዜ ነው? ለምንስ? (ሚልክያስ 3:16-18)
19 ከክፉዎች መካከል እንደማንመደብ የምናስመሠክርበት ጊዜ አሁን ነው። (ሚልክያስ 3:16-18ን አንብብ።) ይሖዋ እንደ “ልዩ ንብረት” ወይም እንደ ውድ ሀብት የሚመለከታቸውን ሰዎች እየሰበሰበ ነው። እኛም ከእነሱ መካከል መገኘት እንደምንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም።
20. ዳንኤል ምን የሚል ቃል ተገብቶለታል? ይህ ቃል የሚፈጸምበትን ቀን የምትናፍቁትስ ለምንድን ነው?
20 በእርግጥም የምንኖረው እጅግ አስደናቂ ጊዜ ላይ ነው። በቅርቡ ደግሞ ይበልጥ አስደናቂ የሆኑ ክንውኖች ይጠብቁናል። ክፋት ሁሉ ሲጠፋ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ከዚያ በኋላ፣ ይሖዋ ለዳንኤል “በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ” በማለት የገባለት ቃል ሲፈጸም እንመለከታለን። (ዳን. 12:13) ዳንኤል እና በሞት ያጣችኋቸው የምትወዷቸው ሰዎች የሚነሱበትን ቀን አትናፍቁም? ከሆነ፣ ከአሁኑ ታማኝ ለመሆን አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ስማችሁ በይሖዋ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሳይጠፋ እንደሚኖር እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ!
መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”
a ይህ ርዕስ በዳንኤል 12:2, 3 ላይ ከተጠቀሰው መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ ባለን ግንዛቤ ላይ የተደረገውን ማስተካከያ ይዟል። ይህ የትምህርት መርሐ ግብር የሚከናወነው መቼ እንደሆነና በሥራው የሚካፈሉት እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን። በተጨማሪም ይህ የትምህርት መርሐ ግብር በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን በክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ለሚኖረው ፈተና የሚያዘጋጃቸው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
b ትንሣኤ በመጨረሻዎቹ ቀናት ታማኝነታቸውን ጠብቀው ከሞቱ ሰዎች ጀምሮ ወደ ኋለኞቹ ትውልዶች ሊቀጥል ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ ያሉ ሰዎች በግል የሚያውቋቸውን ሰዎች የመቀበል አጋጣሚ ያገኛሉ። ያም ሆነ ይህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከናወነው “ተራ” ጠብቆ እንደሆነ ይናገራል፤ ስለዚህ ምድራዊው ትንሣኤም በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን እንጠብቃለን።—1 ቆሮ. 14:33፤ 15:23
c ይህ ማብራሪያ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 17 እና በሐምሌ 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 21-25 ላይ የወጣውን ትምህርት የሚያስተካክል ነው።
d በአንጻሩ ግን በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ያሉት “ጻድቃን” እና “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” የሚሉት ቃላት እንዲሁም ዮሐንስ 5:29 ላይ ያሉት “መልካም የሠሩ” እና “ክፉ የሠሩ” የሚሉት አገላለጾች የሚያተኩሩት ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ባከናወኑት ነገር ላይ ነው።