የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ መላእክት መንፈሶች ስለሆኑ ሥጋዊ አካል የላቸውም። ታዲያ በሥዕል ላይ ክንፍ እንዳላቸው አድርጋችሁ የምታቀርቧቸው ለምንድን ነው? ሃይማኖታዊ ልማድ ስለሆነ ብቻ ነውን?
ብዙውን ጊዜ መላእክትን ከክንፍ ጋር የምንሥላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ምሳሌያዊ መግለጫዎች ምክንያት ነው።
መላእክት ቃል በቃል ክንፍ ያለው ሥጋዊ አካል የላቸውም ማለትህ ትክክል ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ ፊቶች፣ እጆች፣ እግሮች ወይም ሌላ የሰውነት አካሎች የሏቸውም። ሆኖም አልፎ አልፎ መላእክት ለአምላክ አገልጋዮች በታዩአቸው ወቅቶች ሰዎች መስለዋቸው ስለነበር በሰው ቅርጽ ታይተው መሆን አለበት።—ዘፍጥረት 18:2, 22፤ 19:1፤ ምሳሌ 6:11-22
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መላእክትን በራእይ ወይም በሕልም አይተው ያዩትን ገልጸዋል። ነቢዩ ሕዝቅዔል አራት ሕያዋን ፍጥረታትን ወይም “እንስሳትን” አይቶ ነበር። በኋላም ባየው ራእይ እነዚህ ኪሩቤል በመባል የሚታወቁት መላእክት እንደሆኑ አረጋግጧል። (ሕዝቅኤል 1:5፤ 9:3፤ 10:3) እነዚህ መላእክት እያንዳንዳቸው አራት አራት ክንፎች ነበራቸው። ይህም አምላክ ወደሚያዛቸው ወደ ማንኛውም አቅጣጫ በፍጥነት ለማምራት ያላቸውን ችሎታ ያሳያል። “ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፤ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር። መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር። ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።”—ሕዝቅኤል 1:6, 9, 12
ቢሆንም በራእይ የታዩት መላእክት ሁልጊዜ አንድ ዓይነት መልክ አልነበራቸውም። ኢሳይያስ ያያቸው ሱራፌሎች የተባሉት መላእክታዊ ፍጡራን ስድስት ስድስት ክንፍ ነበራቸው። (ኢሳይያስ 6:1, 2) ሕዝቅኤል ራሱ በተመለከተውም ራእይ ውስጥ ልዩ ልዩ መልክ ነበራቸው። በመጀመሪያው ራእይ መላእክቶቹ ከየአራት ክንፎቻቸው ሥር እግሮች፣ እጆች፣ እንዲሁም አራት አራት (የሰው፣ የአንበሳ፣ የጥጃ ወይም የበሬ የንስር የሚመስሉ) ፊቶች ነበራቸው። በሚቀጥለው ራእይ ከአራቱ ፊቶች አንዱ የጥጃ ሳይሆን የኪሩቤል ፊት የሚመስል ነበረ። ይህም የኪሩቤሎችን ታላቅ ኃይል የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። አሁንም ቆይቶ ስለ ምሳሌያዊዋ ቤተ መቅደስ አሸላለም ባየው ራእይ ሕዝቅኤል ኪሩቤሎች አንዱ የሰው ሌላው ደግሞ የአንበሳ የሚመስሉ ሁለት ሁለት ፊቶች እንደነበራቸው አይቷል። (ሕዝቅኤል 1:5-11፤ 10:7-17፤ 41:18, 19) በቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን እንዲሁም በኢየሩሳሌም በሰለሞን በተሠራው ቤተመቅደስ ውስጥ የነበሩት ኪሩቤሎች ሁለት ሁለት ክንፍ ያላቸው ነበሩ። እነሱም የሚገኙት የቃል ኪዳኑ ታቦት ተብሎ በሚጠራው በጽላቱ የወርቅ ክዳን ላይ ነበር። ሁለቱ የወርቅ ኪሩቤሎች ፊታቸው ትይዩ የነበረ ሲሆን ሁለቱም በታቦቱ ላይ የተዘረጉ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበራቸው። (ዘፀአት 25:10-22፤ 37:6-9) በሰለሞን ቤተመቅደስ በታቦቱና ከክዳኑ በላይ እያንዳንዳቸው የተዘረጉ ሁለት ሁለት ክንፎች ያላቸው ሁለት በወርቅ የተለበጡ ኪሩቦች ተርገው ነበር።—1 ነገሥት 8:6-8፤ 1 ዜና 28:18፤ 2 ዜና 5:7, 8
ጆሴፈስ እንዲህ በማለት ጽፎአል፦ “እነዚያን ኪሩቦች ራሳቸውን በተመለከተ ምን ይመስሉ እንደነበረ ማንም ሊናገር ወይም ሊያስብ አይችልም።” በመሆኑም አንዳንድ ምሁራንና ሰዓሊዎች ለመላእክት (በተለይም ለኪሩቤል) ሥዕሎቻቸው መሠረት የሚያደርጉት ክንፍ ያላቸው የጥንት ቅርብ ምሥራቅ አማልክት ዘመናዊ አምሳያ ናቸው በሚሉት ላይ ነው። አስተማማኙ መመሪያ የሚሆነን ግን ሕዝቅኤል ያያቸው ኪሩቦች “የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበራቸው” በማለት የሰጠው ሐሳብ ነው። (ሕዝቅኤል 1:5) ስለዚህ በመሠረቱ ሰማያዊ መላእክት በጽሑፎቻችን ላይ ለመግለጫ ይሆኑ ዘንድ ስንስላቸው ባጠቃላይ በሰው መልክ ነው። ከክንፍ ጋር የምንስላቸው ደግሞ የተለያዩ ዓይነት መላእክት ክንፍ እንዳላቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ ስላለና መላእክት “እንደሚበሩ” የሚናገሩ ሐሳቦች ስላሉ ነው።—ራእይ 14:6፤ መዝሙር 18:10
ለማጠቃለል ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ቀርቧል! የሚለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 288 ላይ በራሱ ላይ ዘውድ በእጁ ላይ ደግሞ ቁልፍ የያዘ ክንፍ ያለው ፍጡር ያሳያል። እሱም የራእይ 20:1 ሥዕላዊ መግለጫ ነው፦ “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።” ይህ ባለ ቁልፍ መልአክ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አድርገን እንረዳዋለን። ሥዕሉ ከክንፍ ጋር የሚያሳየው አብዛኛውን ጊዜ በራእይ የታዩ መላእክት ክንፍ እንዳላቸው ሆነው ስለሚታዩ ነው።