የዘመናት ስሌት
ፍቺ:- አንዳንድ ነገሮች የተፈጸሙበትን ወይም የተከናወኑበትን ጊዜ ማስላት ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናትን የሚቆጥረው ከግለሰቦች የሕይወት ዘመን፣ አንዳንድ ገዥዎች በሥልጣን ከቆዩበት ጊዜና የታወቁ ድርጊቶች ከተፈጸሙበት ጊዜ ጋር በማዛመድ ነው። አዳም እስከ ተፈጠረበት ዘመን የሚዘልቅ የተሟላ የዘመናት ስሌት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት የአምላክን ዓላማ የሚያሟሉ አንዳንድ ትላልቅ ድርጊቶች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በቅድሚያ አሳውቋል። ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሚሠራበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር እስከ 1582 ድረስ አይሠራበትም ነበር። ዓለማዊ የታሪክ መረጃዎች አንዳንድ የታሪክ ክንውኖች ስለተፈጸሙበት ዘመን እርስ በርሳቸው አይስማሙም። ይሁን እንጂ የተረጋገጡ ቁልፍ ዓመታት አሉ። ከእነዚህም መካከል ባቢሎን የወደቀችበት 539 ከዘአበ እና አይሁዳውያን ከግዞት የተመለሱበት 537 ከዘአበ በሚገባ የተረጋገጡ ዓመታት ናቸው። (ዕዝራ 1:1–3) እነዚህን ዓመታት እንደ መነሻ አድርጎ በመጠቀም በጥንት ዘመን የተከናወኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ከአሁኑ የዘመናት አቆጣጠር አንፃር ማስላት ይቻላል።
ሳይንቲስቶች ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት እንዳለፉና መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ጥቂት ሺ ዓመታት ብቻ እንዳልሆነ አረጋግጠዋልን?
ሳይንቲስቶች አንዳንድ ነገሮች የተፈጸሙበትን ዘመን ለማስላት የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ቢችሉም በግምት ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ውጤቶችን ያስገኛሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል የሚባሉትን ዓመታት በየጊዜው ሲለዋውጡና ሲያሻሽሉ ይታያሉ።
በመጋቢት 18, 1982 ኒው ሳይንቲስት የተባለ መጽሔት ላይ የቀረበ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “‘ከዚህ በፊት ሰጥቼ የነበረውን መግለጫ የሰጠሁት ከአንድ ዓመት በፊት ብቻ መሆኑን ማመን ይቸግረኛል።’ ይህን ቃል ባለፈው ዓርብ ምሽት በሮያል ኢንስቲትዩሽን ተሰብስበው ለነበሩት አድማጮች የተናገሩት ሪቻርድ ሊኬ ናቸው። በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት ዘ ሜኪንግ ኦቭ ማንካይንድ (የሰው ዘር አፈጣጠር) በሚል ርዕስ በተከታታይ በቢቢሲ ቴሌቪዥን ቀርቦ በነበረው ፕሮግራም ላይ የሰጡት መግለጫ ‘በአንዳንድ ዐበይት ነጥቦች ላይ ስህተት ያለበት ሊሆን እንደሚችል’ ለመግለጽ ነበር። በተለይ በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያው ሰው መኖር የጀመረው በቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ከ15–20 ሚልዮን ዓመታት በፊት ሳይሆን ከዚህ በጣም ካነሰ ጊዜ በፊት እንደሆነ ተገንዝበዋል።”—ገጽ 695
በየጊዜው ዘመናትን ለማስላት አዳዲስ ዘዴዎች ይፈለሰፋሉ። እነዚህስ ዘዴዎች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1976፣ ማክሮፔድያ፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 509) ተርሞሉሚኒሰንስ ስለሚባል የዘመናት መለኪያ ሲናገር:- “በዛሬው ጊዜ ለተርሞሉሚኒሰንስ የዘመናት ማስያ ዘዴ ትልቅ ግምት ያሰጠው ተስፋ እንጂ የማስያው ትክክለኛነት አይደለም” ብሏል። በተጨማሪም ሳይንስ የተሰኘው ጽሑፍ (ነሐሴ 28, 1981፣ ገጽ 1003) የአሚኖ አሲድ ራሲማይዜሺን የዕድሜ መለኪያ 70,000 ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ያሳየው አጥንት በራዲዮ አክቲቭ የዕድሜ መለኪያ ሲለካ 8,300 ወይም 9,000 ዓመታት ዕድሜ ብቻ ሊኖረው እንደሚችል ማሳየቱን ሪፖርት አድርጓል።
የፊዚክስ ምሁር የሆኑት ሮበርት ጄንትሪ “በራዲዮ አክቲቭ ብስባሽ የሚሰሉ ዘመናት በጥቂት ዓመታት ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ በሆኑ ዓመታት ሊሳሳቱ እንደሚችሉ የሚያምኑ መሆናቸውን” ፖፑላር ሳይንስ (ኅዳር 1979፣ ገጽ 81) ዘግቧል። ይኸው ጽሑፍ የሮበርት ጄንትሪ ምርምር “ሰው በምድር ላይ መኖር የጀመረው ከ3.6 ሚልዮን ዓመታት በፊት ሳይሆን ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት ብቻ ሊሆን ይችላል” ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል በማለት ገልጿል።
ሳይንቲስቶች የመሬት ዕድሜ ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ዘመን በጣም ይበልጣል ብለው እንደሚያምኑ ልብ ማለት ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህንን አባባል አይቃወምም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩት ሰዎች ዕድሜ የተቆጠረው ዛሬ እኛ በምንጠቀምበት ዓመት ነውን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት “ዓመታት” ከእኛ ወሮች ጋር የሚተካከሉ ናቸው ቢባል ሄኖስ ልጅ የወለደው በሰባት ዓመቱ ሲሆን ቃይናንም ልጅ የወለደው በአምስት ዓመቱ ነበር ማለት ነው። (ዘፍ. 5:9, 12 የ1980 ትርጉም ) ይህ ደግሞ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው።
ስለጥፋት ውኃ የተሰጠው የዘመናት ስሌት በዚያ ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የወሮችና የዓመታት ርዝመት ይጠቁማል። ዘፍጥረት 7:11, 24ን ከ8:3, 4 ጋር ብናወዳድር አምስት ወር የተባለው (ከ2ኛው ወር 17ኛ ቀን እስከ 7ኛው ወር 17ኛ ቀን ድረስ) 150 ቀን ወይም እያንዳንዳቸው 30 ቀኖች ያሏቸው አምስት ወራት መሆናቸውን እንረዳለን። “አሥረኛው ወር” ተለይቶ የተገለጸ ሲሆን የሚቀጥለው ዓመት ከመግባቱ በፊትና ከአሥረኛው ወር በኋላ የነበሩ ሌሎች ጊዜያትም ተገልጸዋል። (ዘፍ. 8:5, 6, 8, 10, 12–14) በግልጽ እንደሚታየው አንድ ዓመት ይባል የነበረው እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው የአሥራ ሁለት ወራት ርዝመት ያለው ጊዜ ነበር። እስራኤላውያን ቀደም ካሉት ዘመናት ጀምረው በጨረቃ ላይ የተመሠረተውን የዘመን አቆጣጠራቸውን ከፀሐይ ዓመት ጋር ለማስተካከል በተወሰኑ ጊዜያት ማስተካከያ ያደርጉ ነበር። ወቅቶችን ጠብቀው ያከብሯቸው የነበሩትን ዓመታዊ በዓሎቻቸውን ተለይተው በተጠቀሱ ቀናት ለማክበር የቻሉት በዚህ ምክንያት ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ በዓላቱ መከበር በሚገባቸው ወቅት ላይ አይውሉም ነበር።—ዘሌ. 23:39
አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው ለዘላለም እንዲኖሩ እንደሆነ አንርሳ። ሞትን ያመጣው የአዳም ኃጢአት ነው። (ዘፍ. 2:17፤ 3:17–19፤ ሮሜ 5:12) ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩት ሰዎች ከእኛ ይበልጥ ለፍጽምና የቀረቡ ስለነበሩ ረጅም ዘመን ኖረዋል። ቢሆንም ሁሉም የሞቱት አንድ ሺህ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት የተቋቋመችው በ1914 ነው የሚሉት ለምንድን ነው?
ወደዚህ ዓመት የሚጠቁሙ ሁለት ማስረጃዎች አሉ:- (1) የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት እና (2) ከ1914 ጀምሮ በመፈጸም ላይ የሚገኙት ትንቢቶች ናቸው። እዚህ ላይ የምንመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስን የዘመናት ስሌት ነው። ስለ ትንቢቶቹ መፈጸም “የመጨረሻ ቀኖች” የሚለውን ዋና ርዕስ ተመልከት።
ዳንኤል 4:1–17ን አንብብ። ይህ ትንቢት በናቡከደነፆር ላይ እንደተፈጸመ ቁጥር 20–37 ያሳያል። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ ፍጻሜ አለው። ይህ መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ቁጥር 3 እና 17 አምላክ ለናቡከደነፆር ያሳየው ሕልም ስለ አምላክ መንግሥትና አምላክ መንግሥቱን ‘እርሱ ለፈለገው . . . ከሰዎችም ለተዋረደው’ እንደሚሰጠው ስለገባው ቃል የሚናገር መሆኑን ያሳያሉ። ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው የይሖዋ ዓላማ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወኪሉ ሆኖ የሰው ልጆችን እንዲገዛ መሆኑን ነው። (መዝ. 2:1–8፤ ዳን. 7:13, 14፤ 1 ቆሮ. 15:23–25፤ ራእይ 11:15፤ 12:10) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው መግለጫ በእርግጥ እርሱ ‘ከሰዎች ሁሉ የተዋረደ’ ወይም ዝቅ ያለ እንደነበረ ያሳያል። (ፊልጵ. 2:7, 8፤ ማቴ. 11:28–30) ስለዚህ ትንቢታዊው ራእይ የሚያመለክተው ይሖዋ መንግሥቱን ለልጁ የሚሰጥበትን ጊዜ ነው።
ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ምን ምን ነገሮች መፈጸም ነበረባቸው? በዛፉና በጉቶው የተመሰለው በሰዎች ላይ የሚሰለጥን አገዛዝ “የአውሬ ልብ” ይኖረዋል። (ዳን. 4:16) በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የአውሬነት ጠባይ ያላቸው መንግሥታት ሰውን ይገዛሉ። በአሁኑ ጊዜ ድብ ሩሲያን፣ ንሥር አሜሪካን፣ አንበሳ እንግሊዝን፣ ዘንዶ ቻይናን የሚያመለክቱ ዓርማዎች ናቸው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አራዊትን ለዓለም መንግሥታትና በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ላለው አጠቃላይ የሰዎች ምድራዊ አገዛዝ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። (ዳን. 7:2–8, 17, 23፤ 8:20–22፤ ራእይ 13:1, 2) ኢየሱስ ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን በተናገረው ትንቢት ላይ እንዳመለከተው “[የተወሰነው] የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።” (ሉቃስ 21:24) የኢየሩሳሌም ነገሥታት “በይሖዋ ንጉሣዊ ዙፋን” ላይ እንደተቀመጡ ይነገርላቸው ስለነበር “ኢየሩሳሌም” የአምላክን መንግሥት ትወክላለች። (1 ዜና 28:4, 5 አዓት ፤ ማቴ. 5:34, 35) ስለዚህ በአውሬ የተመሰሉት የአሕዛብ መንግሥታት የአምላክ መንግሥት የሰዎችን ጉዳይ ለመምራት ያላትን መብት ‘ይረግጣሉ።’ ራሳቸውንም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር አድርገዋል።—ከሉቃስ 4:5, 6 ጋር አወዳድር።
ይሖዋ መንግሥቱን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከመስጠቱ በፊት እነዚህ መንግሥታት በሥልጣናቸው እንዲጠቀሙ የሚፈቀድላቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ዳንኤል 4:16 “ሰባት ዘመናት” ይላል። (“ሰባት ዓመታት” አት እና ሞፋት፤ እንዲሁም ጀባ በቁጥር 13 የግርጌ ማስታወሻ) ትንቢታዊ ዘመናት ሲሰሉ አንድ ቀን እንደ አንድ ዓመት ተደርጎ እንደሚቆጠር መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (ሕዝ. 4:6፤ ዘኍ. 14:34) ታዲያ ሰባቱ ዘመናት ምን ያህል “ቀኖች” ይሆናሉ? በራእይ 11:2, 3 በሚገኘው ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱት 42 ወሮች (3 1/2 ዓመታት) 1,260 ቀኖች እንደሚሆኑ ተገልጿል። በዚህም መሠረት ሰባት ዓመታት የዚህ እጥፍ ወይም 2,520 ቀን ይሆናል። ‘አንድን ቀን ለአንድ ዓመት’ የሚለውን ደንብ ብንጠቀም 2,520 ዓመታት ይሆናል።
“ሰባቱ ዘመናት” ከመቼ ጀምሮ ይቆጠራሉ? የአምላክን መንግሥት ይወክል በነበረው መንግሥት ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ነግሦ የነበረውን ሴዴቅያስን ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ከነበረው ዙፋን ካስወገዱት በኋላ ነበር። (ሕዝ. 21:25–27) በ607 ከዘአበ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የአይሁድ ሉዓላዊ መንግሥት የመጨረሻ ቅሪት ተወገደ። በዚያ ዘመን በባቢሎናውያን ተሹሞ የነበረው የአይሁድ ገዥ ጎዶልያስ ተገደለና ቀሪዎቹ አይሁዶች ወደ ግብፅ ሸሹ። (ኤርምያስ ምዕራፍ 40–43) አስተማማኝ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት ይህ የተፈጸመው አይሁዳውያን ከምርኮ ከተመለሱበት ዓመት ከ537 ከዘአበ 70 ዓመት ቀደም ብሎ እንደነበር ይገልጻል። ይህ የሆነው በጥቅምት ወር መጀመሪያ በ607 ከዘአበ ነበር። (ኤር. 29:10፤ ዳን. 9:2፤ ለተጨማሪ ማብራሪያ “መንግሥትህ ትምጣ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 186–189ን ተመልከት።)
ታዲያ እስከ 1914 ድረስ ያለው ዘመን የተሰላው እንዴት ነው? ከላይ ባለው ቻርት እንደተመለከተው ከ607 ከዘአበ የጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምረን 2,520 ዓመታት ብንቆጥር 1914 እዘአ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ያደርሰናል።
“ሰባቱን ዘመናት” ማስላት
“ሰባት ዘመናት” = 7 × 360 = 2,520 ዓመታት
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ “ዘመን” ወይም ዓመት = 12 × 30 ቀኖች = 360 (ራእይ 11:2, 3፤ 12:6,14)
“በሰባቱ ዘመናት” አፈጻጸም እያንዳንዱ ቀን የአንድ ዓመት ርዝመት ይኖረዋል። (ሕዝ. 4:6፤ ዘኍ. 14:34)
ከጥቅምት መጀመሪያ 607 ከዘአበ እስከ ታኅሣሥ 31, 607 ከዘአበ= 1/4 ዓመት
ከጥር 1, 606 ከዘአበ እስከ ታኅሣሥ 31, 1 ከዘአበ = 606 ዓመታት
ከጥር 1, 1 እዘአ እስከ ታኅሣሥ 31, 1913 = 1,913 ዓመታት
ከጥር 1, 1914 እስከ ጥቅምት መጀመሪያ 1914 = 3/4 ዓመት
ጠቅላላ:- 2,520 ዓመታት
በዚያን ጊዜ ምን ነገር ተፈጸመ? ይሖዋ በሰማይ ከፍ ያለ ክብር ለተቀዳጀው ልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን የመግዛት ሥልጣን ሰጠው።—ዳን. 7:13, 14
ታዲያ ዛሬም በምድር ላይ ይህን ያህል ክፋት ያለው ለምንድን ነው? ክርስቶስ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ወደ ምድር ስለተጣሉ ነው። (ራእይ 12:12) ክርስቶስ እንደነገሠ የይሖዋን የበላይነትና የእርሱን መሲሕነት ያልተቀበሉትን ሰዎች ወዲያውኑ አላጠፋቸውም። ከዚያ ይልቅ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ መካሄድ ነበረበት። (ማቴ. 24:14) ንጉሥ ሆኖ የዓለም ሕዝቦች በሁለት ወገን እንዲከፈል የሚያደርግ ሥራ በመምራት ላይ ነው። ጻድቃን ተብለው የተቆጠሩት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሲያገኙ ክፉዎች ደግሞ በዘላለም ሞት ይቀጣሉ። (ማቴ. 25:31–46) በዚህ ጊዜ ውስጥ ስለ ‘መጨረሻ ቀኖች’ የተተነበዩት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይከሰታሉ። “የመጨረሻ ቀኖች” በሚለው ርዕስ ሥር እንደተገለጸው እነዚህ ሁኔታዎች ከ1914 ጀምሮ በግልጽ ሲታዩ ቆይተዋል። በ1914 በሕይወት ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ትውልድ የመጨረሻ አባላት ሞተው ከማለቃቸው በፊት የአሁኑ ክፉ ዓለም የሚጠፋበትን “ታላቅ መከራ” ጨምሮ አስቀድሞ በትንቢት የተነገሩት ነገሮች ሁሉ ይፈጸማሉ።—ማቴ. 24:21, 22, 34
የዚህ ክፉ ዓለም ፍጻሜ የሚመጣው መቼ ነው?
ኢየሱስ ስለዚህ ሲመልስ:- “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሏል። ይሁን እንጂ በተጨማሪም እንዲህ ብሏል:- “እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ [‘የመጨረሻ ቀኖች’ “ምልክት” መታየት ሲጀምር በሕይወት የነበረው ትውልድ] አያልፍም።”—ማቴ. 24:36, 34
ራእይ 12:12 በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራዋ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመች በኋላ በተከታታይ የሚፈጸሙትን ድርጊቶች ከገለጸ በኋላ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።