የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ሰጥቶኛል
ሄለን ማርክስ እንደተናገረችው
ጊዜው የ1986 በጋ ወቅት ሲሆን ቀኑ በጣም ይወብቃል። በአውሮፓ ከሚገኙት በጣም ጭር ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል በአንዱ ለፍተሻ የምጠባበቀው እኔ ብቻ ነበርኩ። ቦታው ራሷን “ከዓለም የመጀመሪያዋ አምላክ የለሽ አገር” ብላ የሰየመችው የአልባኒያ ዋና ከተማ ቴራን ነበር።
መሣሪያ የታጠቀ አንድ መኮንን ሻንጣዬን መፈተሽ ሲጀምር ጥርጣሬና ፍርሃት በተቀላቀለበት ስሜት ተመለከትኩት። እንዲጠራጠር የሚያደርግ አንድ ነገር አደረግሁ ወይም ተናገርኩ ማለት ለእኔ ከአገሩ መባረር ማለት ሲሆን ከውጭ ሆነው ለሚጠብቁኝ ደግሞ እስር አሊያም የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ካምፕ መግባት ማለት ሊሆን ይችላል። የሚያስደስተው ጥቂት ማስቲካዎችንና ብስኩቶችን በመስጠት መኮንኑ ይበልጥ ወዳጃዊ እንዲሆን ማድረግ ቻልኩ። ይሁን እንጂ በ60ዎቹ እድሜ አጋማሽ ላይ የምገኝ ሴት እዚህ ምን አመጣኝ? ምቾት ያለውን ኑሮ ትቼ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም አራማጅና ዋነኛ ደጋፊ ከነበሩት አገሮች መካከል የመጨረሻዋ ወደሆነችው የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስፋፋት በመሞከር ራሴን ለአደጋ ያጋለጥኩት ለምንድን ነው?
ብዙ ጥያቄዎች ያሏት ታማሚ ልጅ
በ1920 በቀርጤስ ኢራፔትራ ውስጥ ከተወለድኩ ከሁለት ዓመት በኋላ አባቴ በሳምባ ምች ሞተ። እናቴ ድሃና መሀይም ነበረች። እኔ ከአራት ልጆች መካከል የመጨረሻ ስሆን ወይቦ (jaundice) የተባለው በሽታ ሰውነቴን አገርጥቶትና አቅም አሳጥቶኝ ነበር። ጎረቤቶቻችን እሷን ወዲያ ተያትና ትሙት፤ ይልቅ ትኩረትሽን ለሦስቱ ጤናማ ልጆችሽ ብትሰጪና እነሱን ብትንከባከቢ ይሻላል እያሉ እናቴን ይመክሯት ነበር። እናቴ ይህን የጎረቤቶቻችንን ምክር ባለመስማቷ ደስተኛ ነኝ።
እናቴ የአባቴ ነፍስ መንግሥተ ሰማያት እንድትገባ ስትል በየጊዜው አንድ የኦርቶዶክስ ቄስ መካነ መቃብሩ ድረስ ይዛ በመሄድ ታስቆርብ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱን ሥነ ሥርዓት ለማካሄድ የሚከፈለው ገንዘብ እንዲህ የዋዛ አልነበረም። ከጎኗ ጎተት ጎተት እያልኩ ከመካነ መቃብሩ የተመለሰችበት በጣም የሚቀዘቅዝ የገና ዕለት እስከ አሁን ትዝ ይለኛል። ያለችንን ገንዘብ ሁሉ ለቄሱ አስረክበን መምጣታችን ነበር። ጥቂት ጎመን ቀቅላ ካበላችን በኋላ አንጀቷ እንደታጠፈና በተስፋ መቁረጥ ያነባችው እንባ ጉንጯ ላይ እንደደረቀ ወደ መኝታዋ ሄደች። ይሁን እንጂ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቄሱን አባቴ ለምን እንደሞተና ድሃዋ እናቴ ለእርሱ ገንዘብ የምትከፍልበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲነግረኝ በድፍረት ጠየቅሁት። እንደማፈር አለና “አምላክ ወስዶታል። ይህ በሕይወት የሚያጋጥም ነገር ነው። አይዞሽ ከሃዘንሽ ትጽናኛለሽ” በማለት በሹክሹክታ መለሰልኝ።
ቄሱ የሰጠኝ መልስ ትምህርት ቤት ከተማርኩት የጌታ ጸሎት ጋር ሊጣጣምልኝ አልቻለም። “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚሉትን ውብና ትርጉም አዘል የመግቢያ ቃላት አሁን ድረስ አስታውሳቸዋለሁ። (ማቴዎስ 6:9, 10) ታዲያ አምላክ ፈቃዱ በምድር እንዲሆን የሚፈልግ ከሆነ ይሄን ያህል መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው?
በ1929 ኢማንዌል ሊዮኑዳኪስ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ቤታችን ከመጣ በኋላ ይህ ጥያቄ ከሞላ ጎደል ተመልሶልኝ ነበር።a እናቴ ምን እንደፈለገ ስትጠይቀው አንዳችም ቃል ሳይተነፍስ አንድ የመመስከሪያ ካርድ አውጥቶ ሰጣት። ካርዱን እንዳነብበው ሰጠችኝ። ሆኖም ገና የ9 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ የተጻፈውን ብዙም አልተረዳሁትም። እናቴ ሰባኪው ዲዳ ስለመሰላት “ስታሳዝን! አንተ መናገር አትችልም። እኔ ደግሞ ማንበብ አልችልም” አለችውና ደግነት በተሞላበት መንገድ የመውጫውን በር አሳየችው።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጥያቄዎቼ በሙሉ ተመለሱልኝ። ታላቅ ወንድሜ ኢማንዌል ፓተራኪስ ከዚሁ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሙታን የት ናቸው? የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ ቡክሌት አገኘ።b ቡክሌቱን በማንበብ አምላክ አባቴን እንዳልወሰደው ማወቄ እፎይታ አስገኘልኝ። ሞት የኃጢአት ውጤት እንደሆነና አባቴ ትንሣኤ አግኝቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር እየተጠባበቀ እንደሆነ ተረዳሁ።
“ይህ መጽሐፍ በክሏችኋል!”
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዓይናችንን ገለጠልን። የአባቴ የነበረ አንድ አሮጌ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘን ሲሆን በምድጃው ዙሪያ ተሰባስበን መጽሐፉን በሻማ ብርሃን ማጥናት ጀመርን። በአካባቢው ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያሳየሁ ወጣት ሴት እኔ ብቻ ስለነበርኩ አነስተኛ ቁጥር የነበረው የምሥክሮች ቡድን በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳልካፈል ተደረግሁ። በቅንነት ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ ይህ ሃይማኖት የወንዶች ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሼ ነበር።
ወንድሜ ለስብከቱ ሥራ ያለው ቅንዓት እኔንም ለዚህ ሥራ አነሳስቶኛል። ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች ቤተሰባችንን በዓይነ ቁራኛ መከታተል ከመጀመራቸውም በላይ ኢማንዌልንና ጽሑፎችን ለማግኘት ሲሉ ባልታሰበ ሰዓት እየመጡ ቤታችንን ይፈትሹ ነበር። አንድ ቄስ መጥቶ ወደ ቀድሞ ሃይማኖታችን እንድንመለስ ለማሳመን የሞከረበት ቀን ትዝ ይለኛል። ኢማንዌል የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያሳየው መጽሐፍ ቅዱሱን ከእጁ ላይ ነጠቀና ወደ ወንድሜ አፍንጫ በማስጠጋት “ይሄ መጽሐፍ በክሏችኋል!” በማለት ጮኸ።
በ1940 ኢማንዌል በውትድርና እንደማይካፈል በመግለጹ ተይዞ ወደ አልባኒያ የጦር ግንባር ተላከ። ከእርሱ ጋር የነበረን ግንኙነት በመቋረጡ ሞቷል ብለን አሰብን። ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመት በኋላ እስር ቤት ሆኖ የላከው ደብዳቤ ድንገት ደረሰን። በሕይወት ያለ ከመሆኑም በላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር! በደብዳቤው ላይ ከጠቀሳቸው ጥቅሶች መካከል “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” የሚለው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አእምሮዬ ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ ተቀርጿል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ይህ ዓይነቱ ማበረታቻ ምንኛ ያስፈልገን ነበር!
ኢማንዌል እዚያው እስር ቤት ሆኖ የተወሰኑ ወንድሞች መጥተው እንዲጠይቁኝ ማድረግ ችሎ ነበር። ወዲያው ከከተማው ውጪ በሚገኝ የእርሻ ቦታ አካባቢ ባለ አንድ ቤት ውስጥ በድብቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ዝግጅት ተደረገ። ይሁን እንጂ እየተከታተሉን እንዳሉ አልተገነዘብንም ነበር! አንድ እሁድ ቀን መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ከበቡን። ከዚያም በጭነት መኪና ላይ ጭነውን ሰዎች እያዩን በከተማው መሃል እንድናልፍ ተደረገ። ያፌዙብንና ይጮኹብን የነበሩትን ሰዎች ድምፅ አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። ሆኖም ይሖዋ በመንፈሱ አማካይነት ውስጣዊ ሰላም ሰጥቶናል።
ከዚያም ወደ ሌላ ከተማ ካዛወሩን በኋላ ጨለማና ቆሻሻ የሆኑ ክፍሎች ውስጥ ወረወሩን። በእኔ ክፍል ውስጥ ያለው መጸዳጃ ባልዲ ሲሆን በቀን አንድ ጊዜ እየተወሰደ ይደፋ ነበር። የቡድኑ “አስተማሪ” አድርገው ስለቆጠሩኝ የስምንት ወር እስራት ፈረዱብኝ። ይሁን እንጂ እዚያው ታስሮ የነበረ አንድ ወንድም የእሱ ጠበቃ የእኛንም ጉዳይ እንዲይዝ ዝግጅት በማድረጉ በመጨረሻ ተፈታን።
አዲስ ሕይወት
ኢማንዌል ከእስር ሲፈታ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን አቴንስ የሚገኙ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመረ። እኔ ደግሞ በ1947 ወደዚያው የተዛወርኩ ሲሆን በመጨረሻ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችና ልጆችም ከሚገኙበት አንድ ትልቅ የምሥክሮች ቡድን ጋር ተዋወቅሁ። ከዚያም ሐምሌ 1947 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ሚስዮናዊ የመሆን ሕልም ስለነበረኝ እንግሊዝኛ ለመማር ስል የማታ የእንግሊዝኛ ኮርስ መከታተል ጀመርኩ። በ1950 አቅኚ ሆንኩ። እናቴም ከእኔ ጋር መኖር የጀመረች ሲሆን እርሷም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አጥብቃ ያዘች። ከ34 ዓመታት በኋላ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ የይሖዋ ምሥክር ነበረች።
በዚያው ዓመት ጆን ማርክስ (ማርኮፑሎስ) ከተባለና ከዩናይትድ ስቴትስ ከመጣ አንድ የተከበረ መንፈሳዊ ወንድም ጋር ተዋወቅሁ። ጆን የተወለደው ደቡብ አልባኒያ ውስጥ ሲሆን የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተሰደደ በኋላ ነበር። በ1950 ግሪክ በመምጣት በማያፈናፍነው ኮሙኒስታዊ አገዛዝ ሥር ወደነበረችው አልባኒያ ለመግባት የሚያስችለውን ቪዛ ለማግኘት በመሞከር ላይ ነበረ። ከ1936 ጀምሮ ቤተሰቡን ያላያቸው ቢሆንም አልባኒያ ለመግባት የሚያስችል ፈቃድ ሳያገኝ ቀረ። ለይሖዋ አገልግሎት ባለው የጋለ ቅንዓትና ለወንድማማች ማኅበሩ ባለው ጥልቅ ፍቅር ተነካሁ። ሚያዝያ 3, 1953 ተጋባንና ከእርሱ ጋር ኒው ጀርሲ ወደሚገኘው አዲሱ መኖሪያችን ተዛወርኩ።
ጆንና እኔ በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ ስንካፈል ራሳችንን መደገፍ እንድንችል በኒው ጀርሲ የባሕር ዳርቻ ለሚገኙት ዓሣ አጥማጆች ቁርስ በማዘጋጀት አንድ አነስተኛ ንግድ ጀመርን። ሥራችንን ሊነጋጋ ሲል እንጀምርና እስከ 3:00 ሰዓት ድረስ እንቆይ ነበር። አኗኗራችንን ቀላል በማድረግና ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት አብዛኛውን ጊዜያችንን በስብከቱ ሥራ ላይ ማዋል ችለናል። ባለፉት ዓመታት ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው የተለያዩ ከተሞች ተዛውረን እንድናገለግል የተጠየቅን ሲሆን በሄድንበት ቦታ ሁሉ በይሖዋ እርዳታ ፍላጎት ያላቸውን ማስጠናት፣ ጉባኤዎችን ማቋቋምና የመንግሥት አዳራሾች ሲገነቡ እርዳታ ማበርከት ችለናል።
ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችንን መርዳት
ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አንድ አስደሳች የአገልግሎት መስክ ተከፈተልን። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሥራችን በታገደባቸው የባልካን አገሮች ከሚገኙ ወንድሞች ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ፈለጉ። በእነዚህ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከወንድማማች ማኅበሩ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለዓመታት በመቋረጡ ይደርሳቸው የነበረው መንፈሳዊ ምግብ በጣም ጥቂት አንዳንዴም ጭራሽ የሚቋረጥ ሲሆን ኃይለኛ ተቃውሞም ነበረባቸው። ብዙዎቹ ዘወትር በዓይነ ቁራኛ እየተጠበቁ ይኖሩ የነበረ ሲሆን አብዛኞቹ በእስር ላይ አሊያም የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ መመሪያና ማበረታቻ በአስቸኳይ ያስፈልጋቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከአልባኒያ የደረሰን አንድ በምሥጢር የተጻፈ ደብዳቤ የሚከተለውን ትርጉም የያዘ ነበር:- “ለጌታ ጸልዩልን። ፖሊሶች በየቤቱ እየገቡ ያገኙትን ጽሑፍ ይወስዳሉ። እንድናጠና አይፈቅዱልንም። ሦስት ሰዎች ታስረዋል።”
በዚህ ምክንያት ኅዳር 1960 ይህን በመሰለ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን አንዳንድ አገሮች ለመጎብኘት ስድስት ወር የሚፈጅ ረዥም ጉዞ ጀመርን። ተልእኮአችንን ዳር ለማድረስ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል፣” አምላካዊ ድፍረት፣ ልበ ሙሉነትና ብልሃት እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:7 NW ) በመጀመሪያ ለመሄድ ያሰብነው አልባኒያ ስለነበር ፓሪስ ሄደን መኪና ከገዛን በኋላ ጉዟችንን ጀመርን። ይሁን እንጂ ሮም ስንደርስ አልባኒያ ለመግባት የሚያስችለውን ቪዛ ያገኘው ጆን ብቻ ነበር። ስለዚህ ወደ ግሪክ አቴንስ ሄጄ እዚያ ጆንን መጠበቅ ነበረብኝ።
ጆን አልባኒያ የገባው በ1961 የካቲት መጨረሻ ሲሆን እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ ቆይቷል። ጆን 30 ከሚያክሉ ወንድሞች ጋር በግል ተገናኝቷል። በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልጉት የነበረውን ጽሑፍና ማበረታቻ በማግኘታቸው ምንኛ ተደስተዋል! ከውጪ ምንም ዓይነት ጉብኝት ሳይደረግላቸው 24 ዓመታት አሳልፈዋል።
ጆን እነዚህ ወንድሞች ባሳዩት ጽናትና ታማኝነት ተነክቶ ነበር። ብዙዎቹ ኮሚኒስታዊው መንግሥት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አንካፈልም በማለታቸው ብቻ ከሥራ ገበታቸው እንደተፈናቀሉና እንደታሠሩ ተገንዝቧል። በተለይ ግን በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንድሞች ለስብከቱ ሥራ እንዲውል ብለው 100 የአሜሪካ ዶላር ሲሰጡት ልቡ በጣም ተነካ። ይህ ገንዘብ መንግሥት ከሚሰጣቸው አነስተኛ የጡረታ አበል ለዓመታት ያጠራቀሙት ነው።
ጆን በአልባኒያ ያደረገው የመጨረሻ ቆይታ ያበቃው መጋቢት 30, 1961 ማለትም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚውልበት ቀን ነበር። ጆን የመታሰቢያ በዓል ንግግሩን 37 ለሚያክሉ አድማጮች ሰጠ። ይሁን እንጂ ንግግሩ እንዳበቃ ወንድሞች ጆንን ቶሎ ብለው በኋለኛው በር ካስወጡት በኋላ ዱሬስ እስከተባለው ወደብ ድረስ ሸኙት። እዚያም በቱርክ የንግድ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ፕሬቭስ (ፕሪዮስ) ግሪክ አመራ።
ጆን በደህና ተመልሶ ሳየው ተደሰትኩ። አሁን ቀሪዎቹን አደገኛ ጉዞዎች ማድረግ እንችላለን። ቀሪው ጉዞ ሥራችን ወደታገደባቸው ሦስት የባልካን አገሮች ሲሆን ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን፣ ታይፕራይተሮችንና ሌሎች እቃዎችን መያዝ ስለሚጠይቅ አደገኛ ነበር። ለይሖዋ ሲሉ ሥራቸውን፣ ነፃነታቸውንና ሕይወታቸውን እንኳ ሳይቀር ለመሠዋት ፈቃደኛ ከነበሩ በጣም ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመገናኘት መብት አግኝተናል። ቅንዓታቸውና ከልብ የመነጨ ፍቅራቸው የብርታት ምንጭ ሆኖልናል። በተጨማሪም ይሖዋ በሰጠን “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” በጥልቅ ተነክተናል።
ጉዟችን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። በቀጣዮቹ ዓመታት ጽሑፎች ወደ አልባኒያ ለመላክና እዚያ የሚገኙት ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሪፖርት ለመስማት የሚያስችሉንን የተለያዩ ዘዴዎች መጠቀማችንን ቀጥለናል።
ብዙ ጊዜ በፍርሃት መጓዝ
ዓመታት አልፈው ጆን በ76 ዓመት እድሜው በ1981 ሲሞት ብቻዬን ቀረሁ። የታላቅ እህቴ ልጅ የሆነችው ኢቫንጀሊያ እና ባለቤቷ ጆርጅ ኦርፋንዴዝ በደግነት የተቀበሉኝ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚያስፈልገኝን ስሜታዊም ሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጥተውኛል። እነርሱ ራሳቸው በሱዳን በእገዳ ሥር በሚያገለግሉበት ወቅት የይሖዋን ድጋፍ ቀምሰዋል።c
ውሎ አድሮ አልባኒያ ከሚገኙት ወንድሞቻችን ጋር ለመገናኘት የሚያስችል አዲስ ጥረት ማድረግ ተጀመረ። የባለቤቴ ዘመዶች እዚያ ይኖሩ ስለነበር ወደ አልባኒያ ለመሄድ ፈቃደኛ እሆን እንደሆነ ተጠየቅሁ። እንዴታ!
በርካታ ወራትን ካስቆጠረ ጥረት በኋላ ግንቦት 1986 አቴንስ ከሚገኘው የአልባኒያ ኤምባሲ ቪዛ አገኘሁ። የኤምባሲው ሠራተኞች አንድ ችግር ቢደርስብኝ ከውጪው ዓለም ምንም ዓይነት እርዳታ እንደማላገኝ አጥብቀው አሳሰቡኝ። አንድ የጉዞ ወኪል ወደ አልባኒያ ለመሄድ የአውሮፕላን ትኬት ስጠይቀው በመገረም ተመለከተኝ። ፍርሃት ከጉዞዬ እንዲያስቀረኝ ባለመፍቀድ በሳምንት አንዴ ብቻ ከአቴንስ ወደ ቴራን በሚበረው አውሮፕላን ተሳፈርኩ። አውሮፕላኑ ውስጥ ይገኙ የነበሩት ለሕክምና ወደ ግሪክ የመጡ በጣም በዕድሜ የገፉ ሦስት አልባናውያን ብቻ ነበሩ።
ልክ አውሮፕላኑ እንዳረፈ ለጉምሩክ ቢሮነት ወደሚያገለግል አንድ ባዶ ክፍል መሩኝ። የባለቤቴ ታናሽ ወንድምና እህት የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም እንኳ እዚያ ከሚገኙት ጥቂት ወንድሞች ጋር እንድገናኝ በመርዳት ተባበሩኝ። ይሁን እንጂ በሕጉ መሠረት መምጣቴን ለአካባቢው ኃላፊ መንገር ስለነበረባቸው በፖሊሶች ዓይን ውስጥ ገባሁ። በዚህ ምክንያት ዘመዶቼ ቴራን የሚኖሩትን ሁለት ወንድሞች ፈልገው እስኪያመጡልኝ ቤት እንድቆይ ሐሳብ አቀረቡ።
በጊዜው በመላው አልባኒያ አሉ ተብለው የሚታሰቡት ራሳቸውን የወሰኑ ወንድሞች ዘጠኝ ሲሆኑ ለዓመታት የደረሰባቸው እገዳ፣ ስደትና ጥብቅ ክትትል በጣም ጠንቃቆች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የተሸበሸበው ፊታቸው ለዚህ ምሥክር ነበር። ሁለቱ ወንድሞች ትክክለኛ ማንነቴን ከተረዱ በኋላ በመጀመሪያ ያነሱት ጥያቄ “መጠበቂያ ግንቦቹ የት አሉ?” የሚል ነበር። ለዓመታት እጃቸው ላይ የነበሩት ሁለት የቆዩ መጽሐፎች ብቻ ሲሆኑ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳ አልነበራቸውም።
መንግሥት በእነርሱ ላይ የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ለረዥም ሰዓት ተረኩልኝ። በመጪው ምርጫ ወቅት ገለልተኛ አቋም ለመውሰድ ወስኖ ስለነበረ አንድ ውድ ወንድም ሁኔታም ነገሩኝ። ሁሉም ነገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለነበረ እንዲህ ዓይነት አቋም መውሰድ ማለት የወንድም ቤተሰብ የምግብ ራሽን አያገኝም ማለት ሲሆን ያገቡ ልጆቹና ቤተሰቦቻቸው የእርሱን እምነት ባይጋሩም እንኳ እስር ቤት ይገባሉ። ይሁን እንጂ የቤተሰቡ አባላት ሁኔታው ስላስፈራቸው ምርጫው ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ወንድምን ገድለው ሬሳውን ወንዝ ውስጥ ከከተቱት በኋላ ፈርቶ ራሱን ገደለ በማለት ድርጊቱን ማስተባበላቸው ሪፖርት ተደረገ።
እነዚህ ክርስቲያኖች የሚገኙበት የድህነት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል። ይሁን እንጂ ለእያንዳንዳቸው 20 የአሜሪካን ዶላር ልሰጣቸው ስሞክር “የምንፈልገው መንፈሳዊ ምግብ ብቻ ነው” በማለት ሳይቀበሉኝ ቀሩ። እነዚህ ውድ ወንድሞች አብዛኛውን የአገሪቱን ሕዝብ አምላክ የለሽ በማድረግ በተሳካለት አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ብዙ አሥርተ ዓመታትን አሳልፈዋል። ይሁን እንጂ እምነታቸውና ቁርጠኝነታቸው በሌሎች አገሮች እንደሚገኙት ምሥክሮች ሁሉ ጠንካራ ነው። ከሁለት ሳምንታት በኋላ አልባኒያን ስለቅ ይሖዋ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳ ሳይቀር “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ለመስጠት ባለው ችሎታ ተደንቄ ነበር።
በ1989 እና በ1991ም አልባኒያን የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ። በመጨረሻ በዚያች አገር የመናገርና የሃይማኖት ነጻነት ሲገኝ የይሖዋ አምላኪዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አደገ። በ1986 እፍኝ የማይሞሉት ወንድሞች አሁን ቁጥራቸው አድጎ ከ2, 200 በላይ ንቁ አስፋፊዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ሜልፖ የተባለችው የባለቤቴ ታናሽ እህት ትገኝበታለች። የይሖዋ በረከት በዚያ ታማኝ ቡድን ላይ እንደነበረ ማን የሚጠራጠር ይኖራል?
በይሖዋ ኃይል ትርጉም ያለው ሕይወት መርቻለሁ
ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት የጆንና የእኔ ሥራ ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ እርግጠኛ ነኝ። የወጣትነት ጉልበታችንን በጣም ጠቃሚ በሆነ መንገድ ተጠቅመንበታል። የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሥራዬ ብለን መያዛችን ልናደርገው ከምንችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ አስችሎናል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ስለረዳናቸው ብዙ ውድ ግለሰቦች ሳስብ ልቤ በደስታ ይሞላል። አሁን እድሜዬ ቢገፋም ወጣቶች ‘በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ’ ከልቤ ማበረታታት እችላለሁ።—መክብብ 12:1
የ81 ዓመት ሴት ብሆንም አሁንም የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ አስፋፊ ሆኜ አገለግላለሁ። በጠዋት ተነስቼ በአውቶቡስና በመኪና ማቆሚያዎች፣ በመንገድ ላይ አሊያም በመናፈሻ ቦታዎች ለማገኛቸው ሰዎች እመሰክራለሁ። የእድሜ መግፋት የሚያስከትላቸው ችግሮች ሕይወትን አስቸጋሪ ቢያደርጉትም የእህቴን ልጅ ቤተሰብ ጨምሮ መንፈሳዊ ወንድሞቼንና እህቶቼን ያቀፈው ትልቁ አፍቃሪ ቤተሰቤ ከፍተኛ የድጋፍ ምንጭ ሆኖልኛል። ከሁሉም በላይ ግን “የኃይሉ ታላቅነት [“ከወትሮው የበለጠ ኃይል፣” NW ] ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን” ተረድቻለሁ።—2 ቆሮንቶስ 4:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኢማንዌል ሊዮኑዳኪስን የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 25-9 ላይ ተመልከት።
b የኢማንዌል ፓተራኪስን የሕይወት ታሪክ በኀዳር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 22-7 ላይ ተመልከት።
c በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን የ1992 የዓመት መጽሐፍ ከገጽ 91-2 ተመልከት።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- ጆን (በስተ ግራ ዳር)፣ እኔ (መሃል)፣ ከእኔ በስተግራ ኢማንዌል የተባለው ወንድሜና እናታችን ከሌሎች ቤቴላውያን ጋር በ1950 አቴንስ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስተ ግራ:- እኔና ጆን በ1956 ኒው ጀርሲ ባሕር ዳርቻ እናካሂደው በነበረው አነስተኛ ንግድ አጠገብ ቆመን
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1995 አልባኒያ ቴራን ውስጥ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ግንባታው በ1996 የተጠናቀቀው አልባኒያ ቴራን የሚገኘው ቤቴል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከእህቴ ልጅ ከኢቫንጀሊያ ኦርፋኒዲስ (በስተ ቀኝ) እና ጆርጅ ከተባለው ባለቤቷ ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- በ1940 ከወጣ አንድ “የመጠበቂያ ግንብ” እትም ላይ በድብቅ ወደ አልባኒያ ቋንቋ የተተረጎመ ርዕስ