ምዕራፍ ስድስት
የትልቁን ዛፍ ምሥጢር መግለጥ
1. ንጉሥ ናቡከደነፆር ምን ደረሰበት? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?
ንጉሥ ናቡከደነፆር የዓለም ገዥ እንዲሆን ይሖዋ ፈቅዶለት ነበር። የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት እንደመሆኑ መጠን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት፣ የተትረፈረፈ ማዕድና ዕጹብ ድንቅ ቤተ መንግሥት የነበረው፣ ባጭሩ በቁሳዊ ነገሮች በኩል የፈለገውን ማግኘት የሚችል ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ድንገት ውርደት ተከናነበ። ናቡከደነፆር አእምሮውን ስቶ እንደ አውሬ ሆነ! ከቤተ መንግሥት ማዕዱና ከንጉሠ ነገሥታዊ መኖሪያው ተሰድዶ እንደ በሬ ሣር እየበላ በሜዳ ለመኖር ተገደደ። እዚህ ችግር ውስጥ የጣለው ነገር ምን ነበር? ይህ ጉዳይ እኛን ሊያሳስበን የሚገባውስ ለምንድን ነው?—ከኢዮብ 12:17-19፤ መክብብ 6:1, 2 ጋር አወዳድር።
ንጉሡ ልዑሉን ከፍ ከፍ አደረገ
2, 3. የባቢሎን ንጉሥ ተገዥዎቹ ምን እንዲያገኙ ተመኝቶላቸዋል? ልዑሉን አምላክስ በሚመለከት ምን ተሰምቶታል?
2 ናቡከደነፆር ወደ አእምሮው ከተመለሰ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ስለተፈጸመው ነገር የሚገልጽ አስገራሚ ሪፖርት በግዛቱ ሁሉ አሠራጭቷል። ይሖዋ ነቢዩ ዳንኤል እነዚህን ክስተቶች በመንፈስ አነሳሽነት በትክክል መዝግቦ እንዲያስቀምጥ አድርጓል። እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ከንጉሡ ከናቡከደነፆር በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፣ ሰላም ይብዛላችሁ። ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ። ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፣ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።”—ዳንኤል 4:1-3
3 የናቡከደነፆር ግዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ የተካተተውን አብዛኛውን የዓለም ክፍል የሚጠቀልል ስለነበር ተገዥዎቹ ‘በምድር ሁሉ የሚቀመጡ’ ነበሩ። ንጉሡ የዳንኤልን አምላክ በሚመለከት “መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው” ብሏል። እነዚህ ቃላት ይሖዋ በመላው የባቢሎን ግዛት ከፍ ከፍ እንዲል አድርገዋል! ከዚህም በላይ ናቡከደነፆር ‘ለዘላለም’ ጸንቶ የሚቆመው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን እንዲያውቅ ሲደረግ ይህ ሁለተኛ ጊዜ ነው።—ዳንኤል 2:44
4. ከናቡከደነፆር ጋር በተያያዘ መልኩ የይሖዋ ‘ተአምራትና ድንቆች’ መታየት የጀመሩት እንዴት ነው?
4 “ልዑሉ አምላክ” ያደረጋቸው ‘ተዓምራትና ድንቆች’ ምንድን ናቸው? ተዓምራትና ድንቆቹ መታየት የጀመሩት በንጉሡ የግል ገጠመኞች ሲሆን እነዚህም በሚከተለው መንገድ ተገልጸዋል:- “እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ።” (ዳንኤል 4:4, 5) ባቢሎናዊው ንጉሥ ይህንን አስፈሪ ሕልም በሚመለከት ምን አደረገ?
5. ናቡከደነፆር ለዳንኤል ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ለምንስ?
5 ናቡከደነፆር የባቢሎንን ጠቢባን አስጠርቶ ሕልሙን ነገራቸው። ይሁን እንጂ ከአቅማቸው በላይ ነበር! የሕልሙን ትርጓሜ ፈጽሞ ሊነግሩት አልቻሉም። ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት።” (ዳንኤል 4:6-8) የዳንኤል የቤተ መንግሥት ስም ብልጣሶር ሲሆን ንጉሡ “አምላኬ” ሲል የጠራው የሐሰት አምላክ ደግሞ ቤል፣ ነቦ ወይም ማርዱክ ሊሆን ይችላል። ናቡከደነፆር ብዙ አማልክትን የሚያመልክ ሰው ስለነበር ዳንኤልን “የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት” እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። ዳንኤልም የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ አለቃ ስለነበር ንጉሡ “የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ” ሲል ጠርቶታል። (ዳንኤል 2:48፤ 4:9፤ ከዳንኤል 1:20 ጋር አወዳድር።) ይህ ግን የታመነው ዳንኤል የይሖዋን አምልኮ ትቶ አስማተኛ ሆኗል ማለት አይደለም።—ዘሌዋውያን 19:26፤ ዘዳግም 18:10-12
አንድ ትልቅ ዛፍ
6, 7. ናቡከደነፆር ያየውን ሕልም እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
6 የባቢሎኑ ንጉሥ ያየው አስፈሪ ሕልም ምን ነበር? ናቡከደነፆር እንዲህ አለ:- “የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ፤ እነሆ፣ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፣ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። ዛፉም ትልቅ ሆነ፣ በረታም ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፣ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ። ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፣ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፣ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፣ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።” (ዳንኤል 4:10-12) ናቡከደነፆር የሊባኖስን ትላልቅ ዝግባዎች ይወድ እንደነበረና እነዚሁኑ ዛፎች ሊያይ እንደሄደ እንዲሁም የተወሰነ የዝግባ ሣንቃ ይዞ ወደ ባቢሎን እንደተመለሰ አንዳንድ ዘገባዎች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ በሕልሙ የተመለከተውን ዓይነት ዛፍ ፈጽሞ አይቶ አያውቅም። “በምድር መካከል” ጉልህ ሥፍራ የያዘ፣ በምድር ዙሪያ የሚታይ፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈራና ለሥጋ ለባሹ ሁሉ ምግብ የሆነ ዛፍ ነበር።
7 ሕልሙ በዚህ ብቻ አላበቃም። ናቡከደነፆር እንዲህ በማለት ቀጠለ:- “በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፣ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ:- ዛፉን ቁረጡ፣ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፣ ቅጠሎቹንም አራግፉ፣ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ። ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፣ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቆይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን።”—ዳንኤል 4:13-15
8. “ጠባቂ” የተባለው ማን ነው?
8 ባቢሎናውያን በጎና ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታትን በተመለከተ የራሳቸው ሃይማኖታዊ አመለካከት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ከሰማይ የመጣው ይህ “ጠባቂ” ወይም ዘብ ማን ነበር? “ቅዱስ” ተብሎ ስለተጠራ አምላክን የሚወክል ጻድቅ መልአክ ነው። (ከመዝሙር 103:20, 21 ጋር አወዳድር።) በናቡከደነፆር አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉትን ጥያቄዎች እስቲ አስብ! ይህ ዛፍ ለምን ይቆረጣል? ጉቶው በብርና በነሐስ ማሰሪያ ታስሮ እንዳያድግ መከልከሉ ለምንድን ነው? ይህ ቆራጣ ጉቶ ምን ጥቅም ይኖረዋል?
9. ጠባቂው ምን ብሎ ነበር? ምን ጥያቄዎችስ ይነሣሉ?
9 ናቡከደነፆር የሚከተሉትን የጠባቂውን ቃላት ሲሰማ ጭራሹኑ ግራ ተጋብቶ መሆን አለበት:- “ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፣ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት። ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ ለወደደውም እንዲሰጠው፣ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፣ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው።” (ዳንኤል 4:16, 17) አንድ የዛፍ ጉቶ ደም የሚረጭ የሰው ልብ በውስጡ የለውም። ደግሞስ የአውሬ ልብ እንዴት ለዛፍ ጉቶ ሊሰጥ ይችላል? ‘ሰባቱ ዘመናትስ’ ምንድን ናቸው? ይህ ሁሉ ነገርስ ‘ከሰዎች መንግሥት’ አገዛዝ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ናቡከደነፆር እነዚህን ነገሮች ለማወቅ እንደፈለገ ምንም አያጠራጥርም።
ለንጉሡ አሳዛኝ ዜና ነበር
10. (ሀ) ዛፎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምንን ሊያመለክቱ ይችላሉ? (ለ) ትልቁ ዛፍ ምን ያመለክታል?
10 ዳንኤል ሕልሙን ሲሰማ ለጊዜው ቢገረምም ወዲያው በፍርሃት ተዋጠ። ናቡከደነፆር ንገረኝ ብሎ ሲወተውተው ነቢዩ እንዲህ አለ:- “ጌታዬ ሆይ፣ ሕልሙ ለሚጠሉህ፣ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን። ትልቅ የነበረው የበረታውም፣ . . . ያየኸው ዛፍ፤ ንጉሥ ሆይ፣ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቷል፣ እስከ ሰማይም ደርሶአል፣ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው።” (ዳንኤል 4:18-22) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ዛፎች ግለሰቦችን፣ ገዥዎችንና መንግሥታትን ሊያመለክቱ ይችላሉ። (መዝሙር 1:3፤ ኤርምያስ 17:7, 8፤ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 31) በሕልም እንዳየው ትልቅ ዛፍ ናቡከደነፆር ራሱ “ታላቅና ብርቱ” የዓለም ኃይል ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ዛፉ የሚወክለው ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ የመግዛት’ ሥልጣንን ሲሆን ይህም የሰው ልጆችን መንግሥት በሙሉ የሚጠቀልል ነው። በመሆኑም ይህ ዛፍ በተለይ ምድርን በሚመለከት፣ የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚያመለክት ይሆናል።—ዳንኤል 4:17
11. ንጉሡ ያየው ሕልም ውርደት እንደሚከናነብ የሚጠቁመው እንዴት ነው?
11 ናቡከደነፆር ውርደት እንዲከናነብ የሚያደርግ ሁኔታ ይጠብቀው ነበር። ዳንኤል ይህንኑ ሁኔታ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል:- “ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና:- ዛፉን ቁረጡ፣ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቆይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፣ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፈንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፤ ንጉሥ ሆይ፣ ፍቺው ይህ ነው፤ በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው።” (ዳንኤል 4:23, 24) ለዚያ ኃያል ንጉሥ ይህንን መልእክት መንገር ድፍረት የሚጠይቅ እንደነበር ግልጽ ነው!
12. ናቡከደነፆር ምን ነገር ይጠብቀው ነበር?
12 ታዲያ ናቡከደነፆርን የሚጠብቀው ነገር ምን ነበር? ዳንኤል እንደሚከተለው ሲለው ምን እንደተሰማው ገምት:- “ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፣ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፣ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፣ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፣ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል።” (ዳንኤል 4:25) ናቡከደነፆር ‘ከሰዎች ተለይቶ እንዲሰደድ’ የሚያደርጉት የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖቹ ጭምር ይመስላሉ። ይሁን እንጂ በርኅራኄ የሚንከባከቡት ከብት ጠባቂዎች ወይም እረኞች ያገኝ ይሆን? በፍጹም፤ ናቡከደነፆር ‘መኖሪያው ከምድር አራዊት ጋር እንደሚሆንና’ ሣር እንደሚበላ አምላክ ተናግሮ ነበር።
13. ስለ ዛፉ ያየው ሕልም እንደሚጠቁመው የናቡከደነፆር የዓለም ገዥነት መንበር ምን ይሆናል?
13 ዛፉ እንደተቆረጠ ሁሉ ናቡከደነፆርም ከዓለም ገዥነቱ ይቆረጣል። ይሁን እንጂ ይህ ለጊዜው ነው። ዳንኤል እንዲህ ሲል አብራርቷል:- “የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል።” (ዳንኤል 4:26) በናቡከደነፆር ሕልም ውስጥ እንደታየው የወደቀው ዛፍ ጉቶ የሚታሠርና እንዳያድግ የሚታገድ ቢሆንም እንዲቆይ ተፈቅዶለታል። በተመሳሳይም የባቢሎን ንጉሥ “ጉቶ” እንዳያድግ ‘ለሰባት ዘመን’ የሚታሠር ቢሆንም እንዲቆይ ይደረጋል። የዓለም ገዥነት ሥልጣኑ እንደ ታሰረው የዛፉ ጎቶ ይሆናል። ሰባቱ ዘመናት እስኪያልፉ ድረስ ተጠብቆ ይቆያል። ምናልባት ኢቭል ሜሮዳክ የሚባለው ልጁ ምትክ ገዥ ሆኖ ቦታውን ሸፍኖለት ሊሆን ቢችልም ይሖዋ በዚህ መሃል ባለው ጊዜ ማንም ሰው በናቡከደነፆር ፋንታ የባቢሎን ብቸኛ ገዥ እንዲሆን አይፈቅድም ነበር።
14. ዳንኤል ናቡከደነፆርን ምን እንዲያደርግ አጥብቆ አሳስቦታል?
14 ዳንኤል ስለ ናቡከደነፆር ከተነገረው ትንቢት በመነሣት በድፍረት እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጠ:- “ንጉሥ ሆይ፣ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ ኃጢአትህንም በጽድቅ፣ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር።” (ዳንኤል 4:27) ናቡከደነፆር የጭቆና ተግባሩንና ኩራቱን ትቶ ከኃጢአት ጎዳናው ቢመለስ ሁኔታዎች ሊለወጡ ይችሉ ነበር። ለነገሩማ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊትስ ይሖዋ የአሦራውያን መዲና የሆነችን የነነዌ ሰዎች ሊያጠፋ ከወሰነ በኋላ ንጉሡና ተገዥዎቹ ንስሐ በመግባታቸው ሳያጠፋቸው ቀርቶ የለ። (ዮናስ 3:4, 10፤ ሉቃስ 11:32) ኩራተኛው ናቡከደነፆርስ ምን ያደርግ ይሆን? ከመጥፎ ጎዳናው ይመለስ ይሆን?
የሕልሙ የመጀመሪያ ደረጃ ፍጻሜ
15. (ሀ) ናቡከደነፆር ምን ዓይነት ዝንባሌ ማሳየቱን ቀጠለ? (ለ) ተቀርጸው የተገኙ ጽሑፎች ናቡከደነፆር ስላደረገው ነገር ምን ይላሉ?
15 ናቡከደነፆር በኩራቱ ገፋበት። ሕልሙን ካየ ከ12 ወራት በኋላ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ እየተንጎራደደ በጉራ እንዲህ አለ:- “ይህች እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን አይደለችምን?” (ዳንኤል 4:28-30) ባቢሎንን (ባቤልን) የቆረቆረው ናምሩድ ቢሆንም ናቡከደነፆር አስውቧታል። (ዘፍጥረት 10:8-10) የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት ተቀርጸው ከተገኙ ጽሑፎች መካከል በአንዱ ላይ እንደሰፈረው እንዲህ ሲል በጉራ ተናግሯል:- “ኢሳጊላንና ኤዚዳን መልሼ ያቋቋምሁ የባቢሎን ንጉሥ የናቦፖላሳር ልጅ ናቡከደነፆር እኔ ነኝ . . . የኢሳጊላንና የባቢሎንን ቅጥር አቁሜያለሁ የመንግሥቴንም ስም ለዘላለም አጽንቼአለሁ።” (በጆርጅ ኤ ባርተን የተዘጋጀው አርኪኦሎጂ ኤንድ ባይብል የተባለው መጽሐፍ 1949, ገጽ 478-9) ሌላው ተቀርጾ የተገኘ ጽሑፍ ደግሞ እርሱ ስላደሳቸው ወይም በድጋሚ ስላስገነባቸው 20 ቤተ መቅደሶች ይጠቅሳል። ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ እንደሚለው “በናቡከደነፆር ግዛት ባቢሎን ከጥንቱ ዓለም ድንቅ ከተሞች መካከል አንዷ ሆና ነበር። በራሱ መዛግብት ውስጥ ስለ ወታደራዊ እንቅስቃሴው የጠቀሰው ነገር እምብዛም ሆኖ ሳለ ስለ ግንባታ ፕሮጄክቶቹና ለባቢሎኒያ አማልክት ይሰጥ ስለነበረው ትኩረት በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል። ናቡከደነፆር ከጥንቱ ዓለም ሰባት ድንቅ ነገሮች አንዱ የሆነውን በኮረብታ ላይ እንዳለ ሆኖ የተሠራ መናፈሻም ሳያስገነባ አልቀረም።”
16. ናቡከደነፆር የሚዋረደው በምን መልኩ ነበር?
16 ኩሩው ናቡከደነፆር ጉራውን ቢነዛም ውርደት ሊከናነብ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና:- ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ:- መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፣ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፣ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው።”—ዳንኤል 4:31, 32
17. ኩሩው ናቡከደነፆር ምን ደረሰበት? ወዲያውስ ምን ሆነ?
17 ናቡከደነፆር ወዲያውኑ እንደ እብደት አደረገው። ከሰው ልጆችም ተለይቶ በመሰደድ “እንደ በሬ” ሣር በልቷል። በሜዳ ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል ማለት ገነት በመሰለ ሣር ውስጥ ተቀምጦ ቀዝቀዝ ባለ ነፋሻማ አየር ይዝናናል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የባቢሎን ፍርስራሽ በሚገኝባት በዛሬዋ ኢራቅ በበጋ ሙቀቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲደርስ በክረምቱ ወራት ደግሞ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ይወርዳል። ያለ ማንም ተንከባካቢ ለዝናብና ፀሐይ የተጋለጠው የናቡከደነፆር የተፍተለተለ ፀጉር እንደ ንስር ጠጉር ሲሆን ያልተቆረጡት ጥፍሮቹ ደግሞ እንደ ወፎች ጥፍር ሆነው ነበር። (ዳንኤል 4:33) ለዚያ ኩሩ የዓለም ገዥ ይህ እንዴት ያለ ውርደት ነበር!
18. በሰባቱ ዘመናት ወቅት የባቢሎን ዙፋን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነበር?
18 ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ትልቅ ዛፍ ተጥሎና ጉቶውም እንዳያድግ ለሰባት ዘመን ታሥሮ ነበር። በተመሳሳይም ይሖዋ ናቡከደነፆርን አእምሮውን እንዲስት ባደረገው ጊዜ ‘ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋርዷል።’ (ዳንኤል 5:20) በዚህ ጊዜ የንጉሡ ልብ ከሰው ወደ በሬ ልብ የተቀየረ ያህል ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ሰባቱ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስ የንጉሡ ዙፋን ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጎለታል። ኢቭል ሜሮዳክ ጊዜያዊ የመንግሥቱ አስተዳዳሪ ሆኖ አገልግሎ ሊሆን ቢችልም ዳንኤል ‘የባቢሎን አውራጃዎች ሁሉ ሹምና የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ዋነኛ አለቃ’ ነበር። ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹም በባቢሎን አውራጃዎች የአስተዳደር ሥራቸው ቀጥለው ነበር። (ዳንኤል 1:11-19፤ 2:48, 49፤ 3:30) አራቱ ግዞተኞች ‘ልዑሉ የሰዎች መንግሥት ገዥ እንደሆነና ለወደደውም የሚሰጠው መሆኑን’ የተገነዘበው ናቡከደነፆር ወደ አእምሮው ተመልሶ ንግሥናውን የሚጨብጥበትን ጊዜ ተጠባብቀዋል።
የናቡከደነፆር ወደ ሥልጣን መመለስ
19. ይሖዋ የናቡከደነፆርን አእምሮ ከመለሰለት በኋላ የባቢሎኑ ንጉሥ ምን ነገር ተገንዝቧል?
19 ይሖዋ ሰባቱ ዘመናት እንደተፈጸሙ ናቡከደነፆር ወደ አእምሮው እንዲመለስ አደረገ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ የልዑሉን አምላክ ቦታ በመገንዘብ እንዲህ አለ:- “ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፣ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፣ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፣ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቆጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም:- ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።” (ዳንኤል 4:34, 35) አዎን ናቡከደነፆር ልዑሉ በእርግጥም የሰው ልጅ መንግሥት ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር።
20, 21. (ሀ) በሕልም የታየው ዛፍ ጉቶ ላይ የነበረው የብረት ማሠሪያ መፈታት ከናቡከደነፆር ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ናቡከደነፆር ምን ነገር አምኖ ተቀብሏል? ይህስ የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን አድርጎታልን?
20 ናቡከደነፆር ወደ ሥልጣኑ ሲመለስ በሕልም የታየው ዛፍ ጉቶ የታሠረበት የብረት ማሠሪያ የተፈታ ያህል ነበር። ወደ ሥልጣን መመለሱን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፣ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፣ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፣ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ።” (ዳንኤል 4:36) አእምሮውን ስቶ የነበረውን ንጉሥ ንቀውት የነበሩ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣናት እንኳ ቢኖሩ አሁን ግን ከልባቸው ‘ፈልገውታል።’
21 ልዑሉ አምላክ ያከናወነው ‘ተአምርና ድንቅ’ እንዴት ታላቅ ነው! ወደ ሥልጣኑ የተመለሰው የባቢሎን ንጉሥ “አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፣ ታላቅም አደርገዋለሁ፣ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፣ መንገዱም ፍርድ ነውና፣ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና” ማለቱ ምንም አያስገርመንም። (ዳንኤል 4:2, 37) ናቡከደነፆር እንዲህ ብሎ ይናገር እንጂ ከአሕዛብ ወገን የሆነ የይሖዋ አምላኪ አልሆነም።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ማስረጃ ይኖራልን?
22. አንዳንዶች የናቡከደነፆርን እብደት ከየትኛው የጤና መታወክ ጋር አመሳስለውታል? ይሁን እንጂ የእርሱን የአእምሮ መቃወስ በተመለከተ ልንገነዘበው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
22 አንዳንዶች የናቡከደነፆር እብደት ላይካንትረፒ ነው ብለዋል። አንድ የሕክምና መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል:- “ላይካንትረፒ . . . ከ[ላይኮስ]፣ ሉፐስ ወይም ተኩላ እና [አንትሮፖስ]፣ ሆሞ ወይም ሰው ከሚሉት ቃላት የተገኘ ነው። ይህ ወደ እንስሳ ተለውጫለሁ ብለው የሚያምኑና የዚያን እንስሳ ድምፅ ወይም ጩኸት የሚያሰሙ፣ የአካል ቅርጽ ወይም ባሕርይ የሚያሳዩ ሰዎችን ሕመም ለማመልከት የሚያገለግል ስያሜ ነው። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ወደ ተኩላ፣ ውሻ ወይም ድመትነት እንደተለወጡ አድርገው የሚያስቡ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ናቡከደነፆር ወደ በሬነት እንደተለወጡ አድርገው ያስባሉ።” (ዲክስዮኔር ዴ ሲዮንስ ሜዲካል ፓር ኡን ሶሲዬቴ ደ ሜድሰ ኤ ደ ሺሩርዢየ፣ ፓሪስ 1818 ጥራዝ 29 ገጽ 246) የላይካንትረፒ ምልክቶች ናቡከደነፆር በእብደቱ ዘመን ካሳያቸው ሁኔታዎች ጋር ይመሳሰላሉ። ይሁን እንጂ የእርሱ የአእምሮ ሕመም በመለኮታዊ ትእዛዝ የመጣ በመሆኑ ዛሬ ካሉት የሚታወቁ ሕመሞች መካከል አንዱ ነው ለማለት አይቻልም።
23. ናቡከደነፆር አእምሮውን ስቶ እንደነበር የሚያረጋግጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምን ማስረጃ አለ?
23 ምሁሩ ጆን ኢ ጎልዲንጌ ከናቡከደነፆር እብደትና ወደ አእምሮው መመለስ ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ሁኔታዎችን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብለዋል:- “የሽብልቅ ቅርፅ ባላቸው ፊደላት ተጽፎ የተገኘው የአንድ መዝገብ ቁራጭ፣ ናቡከደነፆር አንድ ዓይነት የአእምሮ መታወክ ገጥሞት የነበረ መሆኑንና ምናልባትም ባቢሎንን ትቶ ስለመሄዱ የሚጠቁም ይመስላል።” ጎልዲንጌ “የባቢሎኑ ኢዮብ” የተባለውን አንድ ሰነድ በመጥቀስ እንዲህ ይላሉ:- “ከአምላክ የደረሰበትን ቅጣት፣ ሕመሙንና ውርደቱን፣ የአንድን አስፈሪ ሕልም ትርጓሜ ለማወቅ መጓጓቱን፣ እንደ ዛፍ መቆረጡን፣ ውጭ መጣሉን፣ ሣር መብላቱን፣ ማስተዋል ማጣቱን፣ እንደ በሬ መሆኑን፣ ማርዱክ በጠል እንዳረሰረሰው፣ ጥፍሩና ፀጉሩ እንዳደገ፣ በእግር ብረት እንደታሠረ ከዚያም ወደ ቀድሞው ሥፍራው ተመልሶ አምላክን እንዳወደሰ የሚያረጋግጥ ነው።”
ለእኛም ትርጉም ያላቸው ሰባት ዘመናት
24. (ሀ) በሕልም የታየው ትልቅ ዛፍ ምንን ያመለክታል? (ለ) ለሰባት ዓመታት ታግዶ የቆየው ነገር ምንድን ነው? ይህስ የሆነው እንዴት ነበር?
24 በትልቁ ዛፍ የተመሰለው ናቡከደነፆር የዓለምን አገዛዝ ይወክል ነበር። ይሁን እንጂ ዛፉ ከባቢሎን ንጉሥ የበለጠ አገዛዝንና ሉዓላዊነትን እንደሚወክል አስታውስ። ይህ ዛፍ በተለይ ምድርን በሚመለከት ‘የሰማይ ንጉሥ’ የተባለውን የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚወክል ነው። ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ከመጥፋቷ በፊት ተቀማጭነቱ በዚህች ከተማ በነበረው መንግሥት ሥልጣን የነበራቸውና ‘በይሖዋ ዙፋን’ የተቀመጡት ዳዊትና የእርሱ ወራሾች በምድር ላይ የአምላክን ሉዓላዊነት የሚወክሉ ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 29:23 NW) አምላክ ራሱ በ607 ከዘአበ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋ ባደረገ ጊዜ ይህ ሉዓላዊነት እንዲቆረጥ አድርጓል። በዳዊት የዘር መስመር በሚነሡ ነገሥታት አማካኝነት በምድር ላይ ይገለጽ የነበረው መለኮታዊ ሉዓላዊነት ለሰባት ዘመናት ያህል ታግዷል። የእነዚህ ሰባት ዘመናት ርዝማኔ ምን ያህል ነው? የጀመሩት መቼ ነው? ማብቃታቸውስ የታወቀው እንዴት ነው?
25, 26. (ሀ) በናቡከደነፆር ሁኔታ ‘ሰባቱ ዘመናት’ ምን ያህል ርዝማኔ ነበራቸው? እንደዚያ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው? (ለ) በዋነኛው የትንቢቱ ፍጻሜ ‘ሰባቱ ዘመናት’ የተጀመሩት መቼና እንዴት ነበር?
25 ናቡከደነፆር አእምሮውን ስቶ በነበረበት ዘመን “ጠጉሩም እንደ ንስር፣ ጥፍሩም እንደ ወፎች” ረዝሞ ነበር። (ዳንኤል 4:33) ይህ ከሰባት ቀናት ወይም ሰባት ሳምንታት የበለጠ ጊዜ ወስዶ ነበር። የተለያዩ ትርጉሞች “ሰባት ዘመናት” ብለው ሲያስቀምጡት አማራጮቹ ደግሞ “የተቀጠሩት (የተወሰኑት) ዘመናት” ወይም “ክፍለ ጊዜ” የሚሉት ናቸው። (ዳንኤል 4:16, 23, 25, 32) የጥንቱ ግሪክኛ (ሰፕቱጀንት) ደግሞ ትንሽ ለወጥ በማድረግ “ሰባት ዓመታት” ይላል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስም ‘ሰባቱን ዘመናት’ እንደ “ሰባት ዓመታት” ቆጥሯቸዋል። (አንቲኪውቲስ ኦቭ ዘ ጁዊስ 10ኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 10 አንቀጽ 6) አንዳንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁራንም እነዚህ “ዘመናት” “ዓመታት” እንደሆኑ አድርገው ተረድተዋቸዋል። አን አሜሪካን ትራንስሌሽን፣ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን እና የጄምስ ሞፋት ትርጉም “ሰባት ዓመታት” ብለው አስቀምጠዋቸዋል።
26 የናቡከደነፆር “ሰባት ዘመናት” ሰባት ዓመታት እንደሆኑ መረዳት ይቻላል። በትንቢት ውስጥ አንድ ዓመት በአማካይ 360 ቀናት ወይም እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸውን 12 ወራት ያካተተ ነው። (ከራእይ 12:6, 14 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም የንጉሡ “ሰባት ዘመናት” ወይም ሰባት ዓመታት 360 ቀናት ሲባዛ በ7 ወይም 2,520 ቀናት ነበሩ። ይሁን እንጂ ስለ ሕልሙ ዋነኛ ፍጻሜስ ምን ማለት ይቻላል? ትንቢታዊዎቹ “ሰባት ዘመናት” ከ2,520 ቀናት የሚበልጡ ጊዜያትን የሚያመለክቱ ናቸው። “የተቀጠረው የብሔራት ዘመን እስኪያበቃ ድረስ ኢየሩሳሌም በብሔራት የተረገጠች ትሆናለች” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ይህንኑ የሚጠቁሙ ናቸው። (ሉቃስ 21:24 NW) ይህ ‘መረገጥ’ የጀመረው ኢየሩሳሌም በጠፋችበትና የአምላክ መንግሥት ተምሳሌት የሆነው መንግሥት በይሁዳ መግዛቱ ባከተመበት ዓመት በ607 ከዘአበ ነው። ይህ መረገጥ የሚያበቃው መቼ ነው? ‘ነገር ሁሉ በሚታደስበት ዘመን’ ማለትም በኢየሩሳሌም በተመሰለው በአምላክ መንግሥት አማካኝነት መለኮታዊው ሉዓላዊነት ዳግም በምድር በሚገለጥበት ጊዜ ይሆናል።—ሥራ 3:21
27. በ607 ከዘአበ የጀመሩት “ሰባት ዘመናት” የተፈጸሙት ቃል በቃል ከ2,520 ቀናት በኋላ አይደለም የምትለው ለምንድን ነው?
27 ኢየሩሳሌም ከጠፋችበት ከ607 ከዘአበ አንስተን ቃል በቃል 2,520 ቀናት ብንቆጥር የሚያደርሰን 600 ከዘአበ ላይ ይሆናል። ይህ ደግሞ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ምንም ዓይነት ጉልህ ክንውን የተመዘገበበት ዓመት አይደለም። ነፃ የወጡት አይሁዳውያን ወደ ይሁዳ በተመለሱበት በ537 ከዘአበ እንኳ የይሖዋ ሉዓላዊነት በምድር ላይ አልተገለጠም ነበር። ይህን የምንለው ዘሩባቤል የዳዊት ዙፋን ወራሽ ቢሆንም የፋርስ ግዛት አካል የሆነችው የይሁዳ ገዥ እንጂ ንጉሥ ስላልነበረ ነው።
28. (ሀ) የትንቢታዊዎቹን “ሰባት ዘመናት” 2,520 ቀናት በሚመለከት ሊሠራበት የሚገባው ደንብ የትኛው ነው? (ለ) ትንቢታዊዎቹ “ሰባት ዘመናት” ምን ያህል የጊዜ ርዝማኔ ነበራቸው? የጀመሩትና ያበቁትስ በየትኛው ጊዜ ነው?
28 ‘ሰባቱ ዘመናት’ ትንቢታዊ ስለሆኑ በእነዚህ 2,520 ቀናት ረገድ ‘አንድን ዓመት እንደ አንድ ቀን’ የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ደንብ መጠቀም ይኖርብናል። ይህ ደንብ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንደሚከብቡ በሚናገረው ትንቢት ውስጥም ተጠቅሷል። (ሕዝቅኤል 4:6, 7፤ ከዘኁልቊ 14:34 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም የአሕዛብ ኃይሎች ያላንዳች የአምላክ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ምድርን የሚቆጣጠሩባቸው “ሰባት ዘመናት” 2,520 ዓመታት ናቸው። እነዚህ ዓመታት የጀመሩት ይሁዳና ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ በሰባተኛው የጨረቃ ወር (ቲሽሪ 15) በጠፉ ጊዜ ነው። (2 ነገሥት 25:8, 9, 25, 26) ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 1 ከዘአበ ድረስ 606 ዓመታት አሉ። ከዚያ በኋላ ያሉት 1,914 ዓመታት ደግሞ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 1914 እዘአ ድረስ ይመጣሉ። በመሆኑም ‘ሰባቱ ዘመናት’ ወይም 2,520ዎቹ ዓመታት የተፈጸሙት በቲሽሪ ወር 15ኛ ቀን ወይም ጥቅምት 4/5, 1914 እዘአ ላይ ነው።
29. “‘ከሰው የተዋረደ’ የተባለው ማን ነው? ይሖዋስ ለእርሱ ሥልጣን ለመስጠት ምን አድርጓል?
29 በዚህ ዓመት ‘የተቀጠሩት ዘመናት’ ያበቁ ሲሆን አምላክ ግዛቱን ‘ከሰው ለተዋረደው’ ማለትም በእንጨት ተሰቅሎ እስከመሞት ድረስ በጠላቶቹ ፊት የተናቀ ሆኖ ለታየው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቶታል። (ዳንኤል 4:17) ይሖዋ መሲሐዊ ንጉሡን ለመሾም የሉዓላዊነቱ ጉቶ ታስሮ የነበረበትን ምሳሌያዊ ብረትና ነሐስ ፈትቷል። በዚህ መንገድ ልዑሉ በታላቁ የዳዊት ወራሽ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው ሰማያዊ መንግሥት አማካኝነት በምድር ላይ ሉዓላዊነቱ የሚገለጥበት “ቁጥቋጥ” እንዲያድግ አድርጓል። (ኢሳይያስ 11:1, 2፤ ኢዮብ 14:7-9፤ ሕዝቅኤል 21:27) ስለዚህ አስደሳች ውጤትና የትልቁ ዛፍ ምሥጢር ስለመገለጡ ይሖዋን እንዴት ልናመሰግነው ይገባናል!
ምን አስተውለሃል?
• በናቡከደነፆር ሕልም ውስጥ የታየው ትልቅ ዛፍ የሚያመለክተው ምንን ነው?
• ናቡከደነፆር ስለዛፉ ባየው ሕልም የመጀመሪያ ፍጻሜ መሠረት ምን ነገር ገጥሞታል?
• ሕልሙ ፍጻሜውን ካገኘ በኋላ ናቡከደነፆር ምን ነገር እንደተገነዘበ ተናግሯል?
• ስለዛፉ በታየው ትንቢታዊ ሕልም ዋነኛ ፍጻሜ መሠረት ‘ሰባቱ ዘመናት’ ምን ያህል ርዝማኔ ነበራቸው? የጀመሩትና ያበቁትስ መቼ ነው?
[በገጽ 83 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 91 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]