ከጥቅልል ወደ ኮዴክስ—መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ መልክ የተዘጋጀበት መንገድ
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች መረጃ ለማስቀመጥ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ጸሐፊዎች በሐውልቶች፣ ከድንጋይ ወይም ከእንጨት በተሠሩ ጽላቶች፣ በብራና ጥቅልሎች ወይም በሌሎች ነገሮች ላይ ሐሳባቸውን በጽሑፍ አስፍረዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ሐሳብን በጽሑፍ ለማስፈር የሚያገለግለው ተቀባይነት ያገኘና የታወቀ ዘዴ የፓፒረስና የብራና ጥቅልል ነበረ። ከጊዜ በኋላ ሰዎች በኮዴክስ መጠቀም ጀመሩ፤ ውሎ አድሮም ኮዴክስ ጥቅልልን የተካው ሲሆን ጽሑፎችን ለማስቀመጥ በዚህ መንገድ መጠቀም የተለመደ ሆነ። ኮዴክስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭትም ከፍተኛ እገዛ አበርክቷል። ለመሆኑ ኮዴክስ ምንድን ነው? በጥቅም ላይ የዋለውስ እንዴት ነው?
ኮዴክስ ለአሁኑ ዘመን መጻሕፍት ፈር ቀዳጅ ሆኗል። ኮዴክስ የሚዘጋጀው የታጠፉ ገጾችን አንድ ላይ ሰብስቦ በእጥፋታቸው ላይ በመስፋት ነው። ገጾቹ ከፊትም ከኋላም የሚጻፍባቸው ሲሆን ሽፋንም ይደረግላቸዋል። የጥንቱ ኮዴክስ የዛሬዎቹን መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ ባይመስልም እንደ ሌሎቹ የፈጠራ ውጤቶች ሁሉ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎትና ምርጫ በሚያሟላ መልኩ ይሻሻልና ይለወጥ ነበር።
እንጨት፣ ሰምና ብራና
በመጀመሪያ ኮዴክሶች የሚዘጋጁት ሰም ከተቀቡ የእንጨት ጽላቶች ነበር። በ79 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቬሱቪየስ ከተባለው ተራራ እሳተ ጎሞራ ሲፈነዳ ፖምፔ ከተባለችው ጥንታዊት የጣሊያን ከተማ ጋር በጠፋችው ኸርኩሌኒየም የምትባል ከተማ ውስጥ ሰም ተቀብተው የተጻፈባቸው የእንጨት ጽላቶች በቁመታቸው አንድ ላይ ተያይዘው ተገኝተዋል። የኋላ ኋላ እንደ ልብ መተጣጠፍ የማይችሉት ጽላቶች መተጣጠፍ በሚችሉ ነገሮች ተተኩ። የእነዚህ ኮዴክሶች ወይም መጻሕፍት ገጾች በአብዛኛው የሚዘጋጁት ከቆዳ ስለነበር ኮዴክሶቹ በላቲን ቋንቋ ሜምብራኒ ወይም ብራናዎች ተብለው ይጠሩ ነበር።
በአሁኑ ጊዜ በእጅ የሚገኙ አንዳንድ ኮዴክሶች በፓፒረስ የተዘጋጁ ናቸው። ደረቅ የአየር ጠባይ ባለባቸው አንዳንድ የግብጽ አካባቢዎች ሳይበላሹ የተገኙት አሁን ካሉት ሁሉ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩት የክርስትና ጽሑፎችን የያዙ ኮዴክሶች በፓፒረስ የተዘጋጁ ናቸው።a
ጥቅልል ወይስ ኮዴክስ?
ክርስቲያኖች ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ድረስ በአብዛኛው በጥቅልሎች ይጠቀሙ የነበረ ይመስላል። ከአንደኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን ድረስ ያለው ጊዜ በአንድ በኩል ኮዴክስን በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅልልን በሚደግፉ ሰዎች መካከል ውዝግብ የተካሄደበት ወቅት ነበር። በጥቅልል መጠቀም የለመዱ ወግ አጥባቂዎች ለብዙ ጊዜ ሲሠራበት የቆየውን ልማድ ለመተው እያንገራገሩ ነበር። ይሁን እንጂ አንድን ጽሑፍ ከጥቅልል ላይ ማንበብ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት እንመልከት። ጥቅልል አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የፓፒረስ ወይም የብራና ገጾችን አንድ ላይ በማጣበቅ ሲሆን በዚህ መንገድ የተዘጋጀው ረጅም ገጽ ይጠቀለላል። ጽሑፉ በጥቅልሉ የውስጠኛ ክፍል ላይ የሚሰፍር ሲሆን የሚጻፈውም በዓምድ ተከፋፍሎ ነበር። በጥቅልል የሚጠቀመው ሰው ለማንበብ ሲፈልግ ጥቅልሉን በመተርተር የሚፈልገውን ክፍል ያገኛል። አንብቦ ሲጨርስ ደግሞ እንደገና ይጠቀልለዋል። (ሉቃስ 4:16-20) ብዙውን ጊዜ ለአንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ከአንድ በላይ ጥቅልሎች የሚያስፈልጉ መሆኑ በጥቅልል መጠቀምን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገው ነበር። ከሁለተኛው መቶ ዘመን ወዲህ የነበሩ ክርስቲያኖች ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲገለብጡ በኮዴክስ መልክ ማስቀመጥን ይመርጡ የነበረ ቢሆንም በጥቅልሎች መጠቀም ለብዙ መቶ ዓመታት ቀጥሎ ነበር። ያም ሆኖ ይህን ጉዳይ ያጠኑ ምሁራን እንደሚያምኑት ክርስቲያኖች በኮዴክስ መጠቀማቸው ኮዴክስ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ጽሑፎችን በኮዴክስ መልክ ማዘጋጀት በጉልህ የሚታዩ ጥቅሞች አሉት፤ እነዚህም ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አንድ ላይ ለማሰባሰብ ማስቻሉ፣ ገልጦ ለማንበብ አመቺ መሆኑና ለመሸከም ቀላል መሆኑ ናቸው። በቀድሞ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ጥቅሞች አስተውለዋቸው የነበሩ ቢሆንም እንኳ አብዛኞቹ ሰዎች በጥቅልል መጠቀማቸውን ለመተው ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁን እንጂ አያሌ መቶ ዘመናት ሲያልፉ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ቀስ በቀስ በኮዴክስ መጠቀም ተመራጭ እየሆነ መጣ።
ኮዴክስ ከጥቅልል ጋር ሲወዳደር ቆጣቢ ነው። በአንድ ገጽ ላይ ከፊትና ከኋላ ሊጻፍበት የሚችል ከመሆኑም በላይ በርከት ያሉ መጻሕፍትን በአንድ ላይ መጠረዝ ያስችላል። አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ አንድ ሰው የሚፈልገውን ክፍል ከኮዴክስ ላይ በቀላሉ አውጥቶ ማንበብ መቻሉ፣ ኮዴክስ በክርስቲያኖችና እንደ ጠበቆች በመሳሰሉት ባለሙያዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል። ክርስቲያኖች እጥር ምጥን ባለ መንገድ የተዘጋጁ ጽሑፎች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተጻፈባቸው ዝርዝሮች ማግኘታቸው ለወንጌላዊነት ሥራቸው እጅግ ጠቃሚ ነበር። ከዚህም በላይ ኮዴክስ ብዙውን ጊዜ ከእንጨት የተሠራ ሽፋን ይደረግለት ስለነበር ከጥቅልል ይልቅ ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል።
ኮዴክሶች ለግል ንባብም ተመራጭ ነበሩ። በሦስተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች ዘንድ ከብራና የተሠሩ ትንንሽ ጥራዝ ያላቸው የወንጌል መጻሕፍት ይገኙ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሙሉውን ሆነ ከፊሉን መጽሐፍ ቅዱስ የያዙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅጂዎች በኮዴክስ መልክ ተዘጋጅተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን መለኮታዊ ጥበብ በፍጥነትና በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ። በኮምፒውተሮች፣ በሲዲዎች ወይም በካሴቶችና በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት ይህን ጥበብ ማግኘት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የምትፈልገው በየትኛውም መልክ ይሁን፣ በቃሉ ላይ በየዕለቱ በማሰላሰል ለአምላክ ቃል ያለህን ፍቅር እንዲያድግ አድርግ።—መዝሙር 119:97, 167
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ነሐሴ 15, 1962 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 501-505 (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የጥንቱ የክርስትና ኮዴክስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮዴክስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ከፍተኛ እገዛ አበርክቷል