የኤደን ገነት ጉዳይ አንተንም ይነካል
አንዳንድ ምሑራን ስለ ኤደን በሚናገረው ዘገባ ላይ ካነሷቸው በጣም አስገራሚ ተቃውሞዎች መካከል አንዱ በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አልተጠቀሰም የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ሞሪስ “የኤደን ገነት ታሪክ በኋላ ላይ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ በቀጥታ አልተጠቀሰም” በማለት ጽፈዋል። የእሳቸው የግምገማ ውጤት በተለያዩ “ምሑራን” ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ ቢችልም ከእውነታው ግን በቀጥታ የሚቃረን ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ፣ ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ እባቡ ይናገራል።a ይሁንና ጥቂት ምሑራን የሚሠሩት ስህተት የሃይማኖት መሪዎች ከሚፈጽሙት መጠነ ሰፊ ስህተት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሃይማኖት መሪዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚናገረውን የዘፍጥረት ዘገባ ሲያጣጥሉ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የጥቃት ዘመቻ መክፈታቸው ነው። እንዴት?
በኤደን የተከሰተውን ነገር መረዳት ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት በጣም ወሳኝ ነው። ለአብነት ያህል፣ የአምላክ ቃል የተዘጋጀው ሰዎች ለሚያነሷቸው እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ በአብዛኛው በኤደን የአትክልት ስፍራ ከተፈጸሙ ክስተቶች ጋር ተዛማጅነት አለው። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
● የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? አዳምና ሔዋን ለአምላክ ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ይኖሩ ነበር። የሚሞቱት ካመፁ ብቻ ነበር። ባመፁበት ዕለት ወደ ሞት ማምራት ጀመሩ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:19) በዚህ ጊዜ ፍጽምናቸውን ያጡ ሲሆን ለዘሮቻቸውም ማውረስ የሚችሉት ኃጢአትንና አለፍጽምናን ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” በማለት ሁኔታውን ይገልጻል።—ሮም 5:12
● አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? በኤደን ገነት ሰይጣን፣ አምላክ ለፍጡራኑ መልካም ነገርን የሚነፍግ ውሸታም እንደሆነ በመግለጽ ሰድቦታል። (ዘፍጥረት 3:3-5) በዚህ በመንገድ ሰይጣን የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ ስለመሆኑ ጥያቄ አስነስቷል። አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጎን ለመሰለፍ በመምረጥ እነሱም የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል፤ በሌላ አባባል ሰዎች መልካም ወይም ክፉ የሚባለው ምን እንደሆነ በራሳቸው መወሰን ይችላሉ ብለው የተናገሩ ያህል ነበር። ፍጹም ፍትሐዊና ጥበበኛ የሆነው ይሖዋ ለተነሳው ክርክር ተገቢ መልስ ለመስጠት ብቸኛው አማራጭ ሰዎች በፈለጉት መንገድ ራሳቸውን የሚገዙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ጊዜ መስጠት መሆኑን ያውቅ ነበር። ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መምረጣቸው ያስከተለው ክፋት፣ በከፊል የሰይጣን እጅ ያለበት ሲሆን በጊዜ ሂደት አንድ ትልቅ እውነታ እንዲገለጥ አድርጓል፦ ሰው ከአምላክ ተነጥሎ ራሱን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር አይችልም።—ኤርምያስ 10:23
● አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ይሖዋ በኤደን የአትክልት ስፍራ በማዘጋጀት ምድር ሊኖራት የሚገባውን ውበት በተመለከተ መሥፈርት አውጥቶ ነበር። አዳምና ሔዋን ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉና ‘እንዲገዟት’ ተልእኮ የሰጣቸው ሲሆን ይህም በመላዋ ፕላኔት ወጥነት ያለው ውበት እንዲኖርና ሁሉ ነገር ስምም እንዲሆን ያስችላል። (ዘፍጥረት 1:28) ስለዚህ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ፍጹም የሆኑና አንድነት ያላቸው የአዳምና ሔዋን ዘሮች የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያተኩረው አምላክ ይህን የመጀመሪያ ዓላማውን ስለሚፈጽምበት መንገድ ነው።
● ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለምን ነበር? በኤደን ገነት የተነሳው ዓመፅ በአዳምና በሔዋን ብሎም በዘሮቻቸው ላይ የሞት ቅጣት ያስከተለ ቢሆንም አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አዘጋጀ። አምላክ ቤዛ ለማዘጋጀት ልጁን ወደ ምድር ላከ። (ማቴዎስ 20:28) ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ “ኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራ ሲሆን በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ ለይሖዋ ታዛዥ ሆኖ ፍጽምናውን በመጠበቅ አዳም ያላደረገውን ነገር ፈጽሟል። ከዚያም ሕይወቱን መሥዋዕት ወይም ቤዛ አድርጎ በነፃ በመስጠት ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸውና ወደፊት ደግሞ አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ ይኸውም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በኤደን ውስጥ የነበራቸውን ዓይነት ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፈተላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:22, 45፤ ዮሐንስ 3:16) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ፣ ይሖዋ ይህችን ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት የማድረግ ዓላማውን ከግብ እንደሚያደርስ ዋስትና ሰጥቷል።b
የአምላክ ዓላማ ለመረዳት የሚያስቸግር ወይም የማይጨበጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውን የሆነ ነገር ነው። በዚህች ምድር ላይ የነበረችው ኤደን ገነት በእውን የነበሩ እንስሳትና ሰዎች የሚኖሩባት እውን ቦታ እንደሆነች ሁሉ አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የገባው ቃልም በቅርቡ የሚፈጸም እውንና የተረጋገጠ ተስፋ ነው። አንተስ ይህን ተስፋ መጨበጥ ትችል ይሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው በአንተ ላይ ነው። አምላክ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በተሳሳተ የሕይወት ጎዳና ላይ የሚገኙትም ጭምር ይህን የወደፊት ተስፋ እንዲያገኙ ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
ኢየሱስ ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ መጥፎ የሕይወት ጎዳና ይከተል ከነበረ አንድ ሰው ጋር ተነጋግሮ ነበር። ሰውየው ወንጀለኛ ሲሆን የሞት ቅጣት እንደሚገባውም ያውቅ ነበር። ያም ሆኖ ከኢየሱስ መጽናኛና ተስፋ ለማግኘት ፈልጎ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠው? “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ ይህ ወንጀለኛ ወደፊት ከሞት ተነስቶ ልክ እንደ ኤደን ገነት ውብ በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ሲያገኝ መመልከት የሚፈልግ ከሆነ ለአንተስ ይህንኑ አይመኝልህም? በእርግጥ ይመኝልሃል! አባቱም ቢሆን የሚመኝልህ ይህንኑ ነው! ይህንን የወደፊት ተስፋ መጨበጥ የምትፈልግ ከሆነ የኤደንን የአትክልት ስፍራ ስላዘጋጀው አምላክ ለማወቅ የተቻለህን ጥረት አድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 13:10ን፤ ዘዳግም 32:8ን የ1954 ትርጉም፤ 2 ሳሙኤል 7:14ን NW፤ 1 ዜና መዋዕል 1:1ን፤ ኢሳይያስ 51:3ን፤ ሕዝቅኤል 28:13ንና 31:8, 9ን፤ ሉቃስ 3:38ን፤ ሮም 5:12-14ን፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22, 45ን፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3ን፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14ን፤ ይሁዳ 14ን እና ራእይ 12:9ን ተመልከት።
b ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 5ን ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተሳስር ትንቢት
“በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 3:15
ይህ ትንቢት፣ አምላክ በኤደን ገነት የተናገረው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ነው። ለመሆኑ በትንቢቱ ላይ የተጠቀሱት ማለትም ሴቲቱና ዘሯ እንዲሁም እባቡና ዘሩ እነማን ናቸው? በመካከላቸው “ጠላትነት” የተፈጠረውስ እንዴት ነው?
እባቡ
ሰይጣን ዲያብሎስ።—ራእይ 12:9
ሴቲቱ
በሰማይ ያሉ ፍጥረታትን ያቀፈው የይሖዋ ድርጅት። (ገላትያ 4:26, 27) ኢሳይያስ “ሴቲቱ” መንፈሳዊ ሕዝብ እንደምትወልድ ትንቢት ተናግሮ ነበር።—ኢሳይያስ 54:1፤ 66:8
የእባቡ ዘር
የሰይጣንን ፈቃድ ለማድረግ የመረጡ።—ዮሐንስ 8:44
የሴቲቱ ዘር
በዋነኝነት የሚያመለክተው ከይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ወጥቶ የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት የእሱ መንፈሳዊ ወንድሞችም ‘በዘሩ’ ውስጥ ተካተዋል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአንድነት መንፈሳዊ ብሔር የሚያስገኙ ሲሆን ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብለው ተጠርተዋል።—ገላትያ 3:16, 29፤ 6:16፤ ዘፍጥረት 22:18
የተረከዙ መቀጥቀጥ
በመሲሑ ላይ የሚደርስ ዘላቂ ያልሆነ ጉዳት። ሰይጣን ኢየሱስን በምድር ሳለ እንዲገደል በማድረግ ተሳክቶለት የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል።
የራሱ መቀጥቀጥ
በሰይጣን ላይ የሚደርስ ዘላቂ ጉዳት። ኢየሱስ ሰይጣንን ለዘላለም ከሕልውና ውጪ ያደርገዋል። ከዚያ በፊትም እንኳ ኢየሱስ፣ ሰይጣን በኤደን የጀመረውን ክፋት ያስወግዳል።—1 ዮሐንስ 3:8፤ ራእይ 20:10
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ አጭርና ግልጽ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳምና ሔዋን ኃጢአት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ደርሶባቸዋል