ምዕራፍ ዘጠኝ
የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተነበዩ በዘመናችን እየተፈጸሙ ያሉ ክንውኖች ምንድን ናቸው?
የአምላክ ቃል “በመጨረሻው ዘመን” ስለሚኖሩ ሰዎች ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻውን ዘመን’ በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጪ ትንቢት ይናገራል?
1. ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ከየት ማወቅ እንችላለን?
በሬዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ዜና ስትሰማ ‘ይህ ዓለም መጨረሻው ምን ይሆን’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች ማንም ባላሰበውና ባልጠበቀው ሰዓት ስለሚከሰቱ ነገ የሚያመጣውን ማንም ሰው አያውቅም። (ያዕቆብ 4:14) ይሁን እንጂ ይሖዋ ወደፊት የሚፈጸመውን ነገር ያውቃል። (ኢሳይያስ 46:10) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን የሚፈጸሙትን አሳዛኝ ክስተቶች ብቻ ሳይሆን በቅርቡ የሚፈጸሙትን አስደሳች ነገሮችም ከረጅም ጊዜ በፊት ተንብዮአል።
2, 3. ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ ምን ጥያቄ አቅርበውለት ነበር? ምን መልስስ ሰጣቸው?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ ክፋትን ስለሚያስወግደውና ምድርን ገነት ስለሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) ሰዎች ይህ መንግሥት መቼ እንደሚመጣ ማወቅ ፈልገው ነበር። እንዲያውም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበትን ጊዜና የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ምልክት እንዲነግራቸው ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስም በምላሹ ይህ ሥርዓት የሚያበቃበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚያውቀው ይሖዋ አምላክ ብቻ መሆኑን ነገራቸው። (ማቴዎስ 24:36) ሆኖም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘሮች እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ከማምጣቱ በፊት በምድር ላይ የሚፈጸሙ ነገሮችን ተንብዮአል። የተናገረው ትንቢት በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ነው!
3 በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚያሳየውን ማስረጃ ከማጤናችን በፊት ማንም ሰው ያላየውን አንድ ጦርነት እስቲ በአጭሩ እንመርምር። ይህ ጦርነት የተከናወነው በማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ሲሆን የዚህ ጦርነት ውጤት በእኛ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አለ።
በሰማይ የተካሄደ ጦርነት
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ከጨበጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሰማይ ምን ተፈጸመ? (ለ) ራእይ 12:12 እንደሚገልጸው በሰማይ የተካሄደው ጦርነት ምን ውጤት ያስከትላል?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ እንደነገሠ ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ ተመልክተናል። (ዳንኤል 7:13, 14) ኢየሱስ የመንግሥቱን ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እርምጃ ወሰደ። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰማይም ጦርነት ሆነ” ሲል ይገልጻል። “ሚካኤልና [የኢየሱስ ሌላ መጠሪያ ነው] መላእክቱ ከዘንዶው [ከሰይጣን ዲያብሎስ] ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው።”a ሰይጣንና ክፉ መላእክቱ ማለትም አጋንንት በውጊያው ድል ተነስተው ከሰማይ ወደ ምድር ተጣሉ። ታማኝ የሆኑት የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሰይጣንና አጋንንቱ በመባረራቸው በጣም ተደሰቱ። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች እንደ መላእክት ሊደሰቱ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለምድር ግን ወዮ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቊጣ ተሞልቶ ወርዶአል’ ሲል ተንብዮአል።—ራእይ 12:7, 9, 12
5 በሰማይ የተካሄደው ጦርነት ምን ውጤት እንደሚያስከትል ልብ በል። ሰይጣን እጅግ በመቆጣት በምድር ባሉት ላይ ወዮታ ወይም መከራ ያስከትላል። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደምትችለው በአሁኑ ጊዜ እየኖርን ያለነው በዚህ የወዮታ ዘመን ነው። ይሁንና ይህ ጊዜ በአንጻራዊ ሁኔታ አጭር ወይም “ጥቂት ዘመን” ነው። ሰይጣን እንኳ ሳይቀር ጊዜው አጭር መሆኑን ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ሲል ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አምላክ በቅርቡ ዲያብሎስ በምድር ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ የሚያስወግደው መሆኑ በእጅጉ የሚያስደስት ነው! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተተነበዩትና በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ካሉት ነገሮች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት። እነዚህ ነገሮች በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እየኖርን እንዳለንና በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ይሖዋን ለሚወዱ ሰዎች ዘላለማዊ በረከቶችን እንደሚያመጣ ያረጋግጡልናል። በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ የዚህ ዘመን መለያ ምልክት አድርጎ ከጠቀሳቸው ገጽታዎች መካከል አራቱን እንመርምር።
በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸሙ ትልልቅ ክስተቶች
6, 7. ኢየሱስ ጦርነትንና ረሃብን አስመልክቶ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን እየተፈጸሙ ያሉት እንዴት ነው?
6 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” (ማቴዎስ 24:7) ባለፈው መቶ ዘመን በተካሄዱ ጦርነቶች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። አንድ ብሪታንያዊ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በታሪክ ውስጥ የ20ኛውን መቶ ዘመን ያህል ብዙ ደም የፈሰሰበት ዘመን የለም። . . . የማያባራ ጦርነት የተካሄደበት ዘመን ነበር ሊባል ይችላል፤ በየትኛውም የምድር ክፍል ምንም ዓይነት የትጥቅ ትግል ሳይካሄድባቸው ያለፉት ወቅቶች በጣም ጥቂትና ለአጭር ጊዜ ብቻ የቆዩ ናቸው።” ወርልድዎች የተባለው ተቋም ያወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “[በ20ኛው] መቶ ዘመን በጦርነት ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ እስከ 1899 ድረስ በተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ሦስት እጥፍ ይበልጣል።” ከ1914 አንስቶ በተካሄዱት ጦርነቶች ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል። በጦርነት ሳቢያ አንድ የምንወደውን ሰው እንኳ ማጣት ምን ያህል ሐዘን እንደሚያስከትል ስለምናውቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ያስከተለው ሐዘንና መከራ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መገመት አያዳግትም።
7 “ራብ . . . ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:7) ባለፉት 30 ዓመታት የእህል ምርት በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና ብዙ ሰዎች እህል ለመሸመት አቅም የላቸውም አሊያም ሰብል ለማምረት የሚያስችል መሬት አያገኙም። በዚህም ምክንያት ዛሬም የምግብ እጥረት አለ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥር በሰደደ ረሃብ ይሠቃያሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚገምተው ከሆነ በየዓመቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት ሞት ዋነኛው መንስኤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው።
8, 9. ኢየሱስ የምድር ነውጥንና ቸነፈርን አስመልክቶ የተናገራቸው ትንቢቶች እንደተፈጸሙ የሚያሳየው ምንድን ነው?
8 “ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው በየዓመቱ በአማካይ 19 ከባድ የመሬት ነውጦች እንደሚከሰቱ ይጠበቃል። እነዚህ ነውጦች በሕንፃዎች ላይ ጉዳት የማድረስና መሬት የመሰነጣጠቅ ኃይል ያላቸው ናቸው። በተጨማሪም በአማካይ ሲታይ ሕንፃዎችን ሙሉ በሙሉ የማውደም ኃይል ያላቸው የምድር ነውጦች በየዓመቱ ተከስተዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ1900 ወዲህ በምድር መናወጥ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። አንድ የመረጃ ምንጭ “በቴክኖሎጂ ረገድ የታየው መሻሻል የሟቾቹን ቁጥር የቀነሰው በጥቂቱ ነው” ሲል ዘግቧል።
9 “ቸነፈር . . . ይከሠታል።” (ሉቃስ 21:11) በሕክምናው መስክ እድገት የታየ ቢሆንም የቆዩትም ሆኑ አዳዲሶቹ በሽታዎች የሰውን ዘር በከፍተኛ ደረጃ በማጥቃት ላይ ናቸው። አንድ ዘገባ እንደገለጸው ሳንባ ነቀርሳን፣ የወባ በሽታንና ኮሌራን ጨምሮ በደንብ የሚታወቁ 20 በሽታዎች ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ይበልጥ እየተስፋፉ ሲሆን አንዳንዶቹን በሽታዎች በመድኃኒት ማዳን በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። እንዲያውም ቢያንስ 30 የሚሆኑ አዳዲስ በሽታዎች ተከስተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ፈውስ ያልተገኘላቸው ከመሆናቸውም በላይ ቀሳፊ ናቸው።
በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች
10. በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ የተተነበዩ በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ የምታያቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
10 መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ የሚታዩትን ትልልቅ ክስተቶች ከመዘርዘሩም በተጨማሪ የመጨረሻው ዘመን በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ በሚታየው ጉልህ ለውጥም ተለይቶ እንደሚታወቅ ተንብዮአል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች በጥቅሉ ምን ባሕርይ እንደሚኖራቸው ገልጿል። 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ” ይገልጽልናል። ጳውሎስ ሰዎች የሚኖራቸውን ባሕርይ አስመልክቶ ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-
ራሳቸውን የሚወዱ
ገንዘብን የሚወዱ
ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ
የማያመሰግኑ
ፍቅር የሌላቸው
ራሳቸውን የማይገዙ
ጨካኞች
ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ
ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል
11. መዝሙር 92:7 ክፉዎች ምን እንደሚደርስባቸው ይገልጻል?
11 በአካባቢህ ያሉት ሰዎች እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያት ያሏቸው ሆነዋል? እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። በየትም ቦታ መጥፎ ባሕርያት ያሏቸው ሰዎች ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት የሚናገር በመሆኑ ይህ ሁኔታ አምላክ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ የሚጠቁም ነው:- “ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣ ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ ለዘላለሙ ይጠፋሉ።”—መዝሙር 92:7
ደስ የሚያሰኙ ክንውኖች!
12, 13. በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ “ዕውቀት” የበዛው እንዴት ነው?
12 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው የመጨረሻው ዘመን በወዮታ የተሞላ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ በይሖዋ አምላኪዎች መካከል ደስ የሚያሰኙ ክንውኖች እየተፈጸሙ ነው።
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ “ዕውቀትም ይበዛል” ሲል ተንብዮአል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ‘በፍጻሜው ዘመን’ ነው። (ዳንኤል 12:4) በተለይ ከ1914 ጀምሮ ይሖዋ እሱን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ግንዛቤያቸው እያደገ እንዲሄድ ረድቷቸዋል። ስለ አምላክ ስምና ዓላማ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት፣ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ የሚገልጹትን ውድ እውነቶች በተመለከተ ያላቸው እውቀት እያደገ ሄዷል። ከዚህም ሌላ የይሖዋ አምላኪዎች እነሱን በሚጠቅምና ለአምላካቸው ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ተምረዋል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት ስለሚጫወተው ሚናና ይህ መንግሥት በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ እንዴት እንደሚያስተካክል ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አግኝተዋል። ይህን እውቀት በመጠቀም ምን ያከናውናሉ? ይህ ጥያቄ በዚህ የመጨረሻ ዘመን እየተፈጸመ ወዳለ ሌላ ትንቢት ይመራናል።
14. በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ ምን ያህል ተስፋፍቷል? ምሥራቹን እየሰበኩ ያሉትስ እነማን ናቸው?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በተናገረው ትንቢት ላይ “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 24:3, 14) በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱ ወንጌል ማለትም የመንግሥቱን ምንነትና የሚያከናውናቸውን ነገሮች እንዲሁም የሚያመጣቸውን በረከቶች ማግኘት ስለምንችልበት መንገድ የሚገልጸው ምሥራች ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው። “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋ” የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት እየሰበኩ ነው። (ራእይ 7:9) ምሥክሮቹ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መማር የሚፈልጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ። ይህ ትንቢት የተፈጸመበት ሁኔታ በተለይ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠሉ’ እንደሚሆኑ የተነበየ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ እጅግ የሚያስደንቅ ነው!—ሉቃስ 21:17
ምን ለማድረግ ታስባለህ?
15. (ሀ) የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደሆነ ታምናለህ? ለምንስ? (ለ) “መጨረሻው” የሚለው አነጋገር ይሖዋን ለሚቃወሙ ሰዎች ምን ትርጉም አለው? ራሳቸውን ለአምላክ መንግሥት ለሚያስገዙ ሰዎችስ?
15 በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ በመሆናቸው የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው ቢባል አትስማማም? ምሥራቹ ይሖዋ በቃ እስከሚል ድረስ ከተሰበከ በኋላ “መጨረሻው” እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 24:14) “መጨረሻው” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው አምላክ ክፋትን ከምድር ላይ የሚያስወግድበትን ጊዜ ነው። ይሖዋ ሆን ብለው የሚቃወሙትን ሁሉ ለማጥፋት ኢየሱስንና ኃያላን መላእክትን ይጠቀማል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-9) ከዚያ በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ሕዝቦችን ማሳት አይችሉም። የአምላክ መንግሥት ራሳቸውን ጻድቅ ለሆነው አገዛዙ በሚያስገዙ ሰዎች ሁሉ ላይ በረከት ያፈስሳል።—ራእይ 20:1-3፤ 21:3-5
16. ምን ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው?
16 የሰይጣን ሥርዓት ፍጻሜ ስለተቃረበ ‘ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል። ስለ ይሖዋና ለእኛ ስላወጣቸው መሥፈርቶች ይበልጥ መማርህን መቀጠልህ በጣም አስፈላጊ ነው። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥና። የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከሚጥሩ ሌሎች ሰዎች ጋር አዘውትረህ የመሰብሰብ ልማድ አዳብር። (ዕብራውያን 10:24, 25) ይሖዋ አምላክ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ያዘጋጀውን የተትረፈረፈ እውቀት ለመቅሰም ጣር፤ እንዲሁም የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንድትችል በሕይወትህ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን አድርግ።—ያዕቆብ 4:8
17. በክፉዎች ላይ የሚመጣው ጥፋት ለአብዛኞቹ ሰዎች ዱብ ዕዳ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?
17 ኢየሱስ አብዛኞቹ ሰዎች በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁመውን ማስረጃ ችላ እንደሚሉት አስቀድሞ ተናግሯል። በክፉዎች ላይ ጥፋት የሚመጣው በድንገትና ባልተጠበቀ ሰዓት ነው። ጥፋቱ ለአብዛኞቹ ሰዎች ልክ በሌሊት እንደሚመጣ ሌባ ዱብ ዕዳ ይሆንባቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:2) ኢየሱስ የሰው ልጅ በሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ወይም በመጨረሻው ዘመን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የሚገዛበት ጊዜ ከኖኅ ዘመን ጋር እንደሚመሳሰል በመግለጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። “ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም [“በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜም፣” NW] እንደዚሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:37-39
18. በቁም ነገር ልንመለከተው የሚገባው ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?
18 በመሆኑም ኢየሱስ አድማጮቹን እንዲህ ብሏቸዋል:- “በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት [ሞገስ አግኝታችሁ] መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።” (ሉቃስ 21:34-36) ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት በቁም ነገር መመልከታችን ጠቃሚ ነው። ለምን? የይሖዋ አምላክንና ‘የሰው ልጅ’ የተባለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ ያገኙ ሰዎች በሰይጣን ዓለም ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ተርፈው በቅርቡ በሚመጣው አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላላቸው ነው!—ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
a ሚካኤል የኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ መጠሪያ መሆኑን የሚገልጽ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 218-219 ላይ ያለውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።