“በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ”
“የኋለኛው አዳም ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።”—1 ቆሮ. 15:45
1-3. (ሀ) የምናምንባቸውን መሠረታዊ ነገሮች ስንጠቅስ ልናካትተው የሚገባው ትምህርት የትኛው ነው? (ለ) ትንሣኤ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
‘የሃይማኖታችሁ መሠረታዊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን ትመልሳለህ? ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ይሖዋ መሆኑን እንደምናምን ጎላ አድርገህ ትናገር ይሆናል። ቤዛ ሆኖ በሞተልን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነትም መጥቀስህ አይቀርም። በተጨማሪም ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆንና የአምላክ ሕዝቦችም በዚያ ለዘላለም እንደሚኖሩ ያለንን አስደሳች ተስፋ ትናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ትልቅ ቦታ ከምትሰጣቸው ትምህርቶች መካከል የትንሣኤ ተስፋን እንደ አንዱ አድርገህ ትገልጸዋለህ?
2 ከታላቁ መከራ በሕይወት አልፈን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርግ ቢሆንም፣ ቁልፍ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች አንዱ የትንሣኤ ተስፋ እንደሆነ ለማመን የሚያበቁ ምክንያቶች አሉን። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የትንሣኤ ተስፋ ለእምነታችን መሠረት የሆነው ለምን እንደሆነ ሲያስረዳ “የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነዋ!” ብሏል። ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ ንጉሣችን ሆኖ እየገዛ አይደለም እንዲሁም ስለ ክርስቶስ አገዛዝ የምናስተምረው ትምህርት ከንቱ ነው ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:12-19ን አንብብ።) እኛ ግን ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኞች ነን። እንዲህ ብለን ማመናችን ደግሞ የሞቱ ሰዎች መነሳታቸውን ጨርሶ ከማይቀበሉት ሰዱቃውያን የተለየን እንድንሆን አድርጎናል። አንዳንዶች ቢያሾፉብንም እኛ በትንሣኤ ላይ ያለን እምነት ጠንካራ ነው።—ማር. 12:18፤ ሥራ 4:2, 3፤ 17:32፤ 23:6-8
3 ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ [የተማርነው] መሠረታዊ ትምህርት” ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል ‘ስለ ሙታን ትንሣኤ የሚገልጸው ትምህርት’ እንደሚገኝበት ጽፏል። (ዕብ. 6:1, 2) በተጨማሪም በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው ተናግሯል። (ሥራ 24:10, 15, 24, 25) የትንሣኤ ተስፋ ከመሠረታዊ ትምህርቶች ይኸውም ‘ከአምላክ ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች’ አንዱ ቢሆንም እንኳ ይህን ተስፋ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ያስፈልገናል። (ዕብ. 5:12) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
4. ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
4 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መማር ሲጀምሩ ቀደም ባሉት ዘመናት ስለተከናወኑ ትንሣኤዎች የሚገልጹ ዘገባዎችን፣ ለምሳሌ የአልዓዛርን ታሪክ ማንበባቸው አይቀርም። በተጨማሪም እነዚህ ግለሰቦች አብርሃም፣ ኢዮብና ዳንኤል ሙታን ወደፊት እንደሚነሱ ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው ይማራሉ። ያም ቢሆን ‘ትንሣኤ እንደሚኖር የተሰጠ ተስፋ፣ ከበርካታ ዓመታት ምናልባትም ከዘመናት በኋላ ሊፈጸም እንደሚችል ለመተማመን የሚያበቃ ማስረጃ አለ?’ ተብለህ ብትጠየቅ መልስህ ምን ይሆናል? ደግሞስ መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እምነታችንን ለማጠናከር አስፈላጊ ነው፤ እስቲ ቅዱሳን መጻሕፍት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚሉ እንመርምር።
ተስፋ ከተሰጠ ከረጅም ዘመን በኋላ የተከናወነ ትንሣኤ
5. ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ ምን እንመረምራለን?
5 ከሞተ ብዙም ያልቆየ ሰው ትንሣኤ እንዳገኘ መቀበል አይከብደን ይሆናል። (ዮሐ. 11:11፤ ሥራ 20:9, 10) ይሁንና ከብዙ ዓመታት ምናልባትም ከዘመናት በኋላ እንደሚፈጸም ስለተነገረ የትንሣኤ ተስፋስ ምን ማለት ይቻላል? ምናልባትም እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ የተሰጠው ከሞተ ብዙም ያልቆየን አሊያም ከዘመናት በፊት የሞተን ሰው አስመልክቶ ሊሆን ይችላል፤ ታዲያ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም መተማመን ትችላለህ? በመሠረቱ፣ ተስፋ ከተሰጠ ከብዙ ዘመናት በኋላ የተከናወነ አንድ ትንሣኤ አለ፤ አንተም ይህ ትንሣኤ መፈጸሙን አምነህ ተቀብለሃል። ለመሆኑ የምንናገረው ስለ የትኛው ትንሣኤ ነው? ይህ ክንውን ትንሣኤን በተመለከተ ካለህ ተስፋ ጋር የሚገናኘውስ እንዴት ነው?
6. በመዝሙር 118 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በኢየሱስ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
6 ከብዙ ዘመናት በፊት የተሰጠ የትንሣኤ ተስፋን በተመለከተ መዝሙር 118 ምን ፍንጭ እንደሚሰጠን እንመልከት፤ አንዳንዶች ይህን መዝሙር ያቀናበረው ዳዊት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህ መዝሙር ላይ “ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ እንድታድነን እንለምንሃለን! . . . በይሖዋ ስም የሚመጣው የተባረከ ነው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ኒሳን 9 ላይ በአህያ ውርንጭላ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ፣ ሕዝቡ ከመሲሑ ጋር የተያያዘውን ይህን ሐሳብ እንደጠቀሱ እናስታውስ ይሆናል። (መዝ. 118:25, 26፤ ማቴ. 21:7-9) ይሁን እንጂ መዝሙር 118 ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚከናወን ትንሣኤ እንደሚኖር የሚጠቁመው እንዴት ነው? ትንቢታዊ ይዘት ያለው ይህ መዝሙር “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ” የሚል ሐሳብም እንደያዘ ልብ እንበል።—መዝ. 118:22
7. አይሁዳውያኑ ኢየሱስን ምን ያህል እንደሚንቁት ያሳዩት እንዴት ነው?
7 መዝሙሩ ላይ “ግንበኞች” የተባሉት የአይሁድ መሪዎች መሲሑን እንደናቁት አሳይተዋል። ይህን ያደረጉት፣ ኢየሱስን ለመስማት ወይም ደግሞ ክርስቶስ መሆኑን ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ብቻ አይደለም። በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ እንዲገደል ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ንቀታቸውን ገልጸዋል። (ሉቃስ 23:18-23) በእርግጥም እነዚህ አይሁዳውያን በኢየሱስ ሞት እጃቸው አለበት።
8. ኢየሱስ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” የሆነው እንዴት ነው?
8 ይሁንና ኢየሱስ ከተናቀና ከተገደለ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” እንደሚሆን የተነገረው ትንቢት የሚፈጸመው እንዴት ነው? ትንቢቱ ሊፈጸም የሚችለው ኢየሱስ ከሞት የሚነሳ ከሆነ ብቻ ነው። ኢየሱስ ራሱ ይህን ግልጽ የሚያደርግ ምሳሌ ተናግሯል። ምሳሌው አንድ የወይን እርሻ ባለቤት በተለያየ ጊዜ ወደ እርሻው የላካቸውን ሰዎች ገበሬዎቹ እንዳንገላቷቸው ይገልጻል፤ ይህም እስራኤላውያን፣ አምላክ ወደ እነሱ የላካቸውን ነቢያት ከያዙበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል። በምሳሌው ላይ የእርሻው ባለቤት የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ወደ ገበሬዎቹ የላከው የሚወደውንና ወራሹ የሆነውን ልጁን እንደሆነ ተገልጿል። ታዲያ ገበሬዎቹ ልጁን ተቀበሉት? በጭራሽ። እንዲያውም ልጁን ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት። ኢየሱስ ምሳሌውን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በመዝሙር 118:22 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ጠቅሷል። (ሉቃስ 20:9-17) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡት የሕዝቡ ገዢዎች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት’ ጋር ሲነጋገር ይህን ትንቢት ጠቅሷል። ጴጥሮስ እነዚህ ሰዎች ‘በእንጨት ላይ ስለሰቀሉት ሆኖም አምላክ ከሞት ስላስነሳው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ’ ከተናገረ በኋላ “‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ እሱ ነው” በማለት ነጥቡን በግልጽ አስቀምጦታል።—ሥራ 3:15፤ 4:5-11፤ 1 ጴጥ. 2:5-7
9. በመዝሙር 118:22 ላይ ምን ትኩረት የሚስብ ክንውን ተገልጿል?
9 በእርግጥም በመዝሙር 118:22 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ ትንሣኤ እንደሚኖር ከዘመናት በፊት ጠቁሟል። መሲሑ በሰዎች ይናቃል እንዲሁም ይገደላል፤ ይሁን እንጂ ከሞት ተነስቶ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ይሆናል። ይህ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ማለትም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች መዳን የሚያገኙበት ብቸኛው መንገድ ሆኗል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም” የሚለው ለዚህ ነው።—ሥራ 4:12፤ ኤፌ. 1:20
10. (ሀ) መዝሙር 16:10 ምን ትንቢታዊ ሐሳብ ይዟል? (ለ) መዝሙር 16:10 በዳዊት ላይ እንዳልተፈጸመ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
10 ስለ ትንሣኤ የተነገረ ትንቢት የያዘ ሌላም ጥቅስ እንመልከት። ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው ተስፋው ከተሰጠ ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በኋላ ነው፤ ይህ ደግሞ ትንሣኤ እንደሚኖር የተሰጠ ተስፋ፣ ከበርካታ ዓመታት በኋላም ሊፈጸም እንደሚችል ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። ዳዊት በመዝሙር 16 ላይ “መቃብር ውስጥ አትተወኝምና። ታማኝ አገልጋይህ ጉድጓድ እንዲያይ አትፈቅድም” ብሏል። (መዝ. 16:10) ዳዊት ይህን ያለው፣ እሱ ራሱ ፈጽሞ እንደማይሞት ወይም ወደ መቃብር እንደማይወርድ ለመግለጽ አስቦ አይደለም። ምክንያቱም የአምላክ ቃል፣ ዳዊት በዕድሜ ገፍቶ እንደሞተና ‘በዳዊት ከተማ እንደተቀበረ’ በግልጽ ይናገራል። (1 ነገ. 2:1, 10) ታዲያ መዝሙር 16:10 ስለ ማን እየተናገረ ነው?
11. ጴጥሮስ መዝሙር 16:10ን ያብራራው መቼ ነው?
11 ትንቢቱ ስለ ማን እንደሚናገር መገመት አያስፈልገንም። ይህ መዝሙር ከተጻፈ አንድ ሺህ ዓመታት ካለፉ ይኸውም ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ጴጥሮስ በመዝሙር 16:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ማን እንደሚናገር አብራርቷል። (የሐዋርያት ሥራ 2:29-32ን አንብብ።) ጴጥሮስ በሺዎች ለሚቆጠሩ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ባቀረበው በዚህ ንግግር ላይ ዳዊት እንደሞተና እንደተቀበረ ጠቅሷል። ንግግሩን የሚያዳምጡት ሰዎችም ይህን ያውቁ ነበር። “አምላክ ክርስቶስን በመቃብር እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ” ዳዊት “አስቀድሞ ተረድቶ ስለ [መሲሑ ትንሣኤ]” እንደተናገረ ሐዋርያው አብራርቷል፤ በዚህ ወቅት ከአድማጮቹ መካከል የተቃውሞ ሐሳብ ያነሳ እንደነበረ ዘገባው አይገልጽም።
12. መዝሙር 16:10 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ይህስ የትንሣኤ ተስፋን በተመለከተ ምን ያረጋግጥልናል?
12 ጴጥሮስ ይህን ነጥብ ለማጠናከር በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘውን የዳዊትን ሐሳብ ጠቅሷል። (የሐዋርያት ሥራ 2:33-36ን አንብብ።) ጴጥሮስ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ማስረጃ ስላቀረበ፣ የተሰበሰበው ሕዝብ ኢየሱስ “ጌታም ክርስቶስም” መሆኑን አምኖ ተቀብሏል። ከዚህም ባሻገር፣ ሕዝቡ መዝሙር 16:10 ፍጻሜውን ያገኘው ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ እንደሆነ ተገንዝቧል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ ለሚኖሩ አይሁዳውያን ሲሰብክ ይህንኑ አሳማኝ ማስረጃ ተጠቅሟል። ሰዎቹ፣ ጳውሎስ ያቀረበውን ማስረጃ አሳማኝ ሆኖ ስላገኙት፣ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ መስማት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:32-37, 42ን አንብብ።) እኛም፣ ቀደም ሲል የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተነገሩት ከበርካታ ዘመናት በፊት ቢሆንም እንኳ በትክክል ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ መተማመን እንችላለን።
ትንሣኤ—መቼ?
13. አንዳንዶች ትንሣኤን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ሊያነሱ ይችላሉ?
13 ትንሣኤ እንደሚኖር የተሰጠ ተስፋ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ፍጻሜውን ሊያገኝ እንደሚችል ማወቃችን እንደሚያበረታታን ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ አንዳንዶች ‘ታዲያ በሞት የተለየኝን ሰው ዳግም ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ አለብኝ ማለት ነው? የምጓጓለት ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ፣ የማያውቋቸውና ሊያውቋቸው የማይችሉ ነገሮች እንዳሉ ገልጾላቸዋል። አንዳንድ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ‘ጊዜና ወቅት’ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም። (ሥራ 1:6, 7፤ ዮሐ. 16:12) ይህ ሲባል ግን ትንሣኤ የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ ምንም የምናውቀው ነገር የለም ማለት አይደለም።
14. የኢየሱስ ትንሣኤ ከእሱ በፊት ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የተለየ የሆነው እንዴት ነው?
14 ይህን መረዳት እንድንችል፣ ስለ ትንሣኤ የሚገልጹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶችን መለስ ብለን ለማሰብ እንሞክር። ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የኢየሱስ ትንሣኤ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ከሞት ባይነሳ ኖሮ ማናችንም በሞት ያጣናቸውን ሰዎች እንደገና የማየት ተስፋ አይኖረንም ነበር። ከኢየሱስ በፊት ከሞት የተነሱት ሰዎች፣ ለምሳሌ ኤልያስና ኤልሳዕ ያስነሷቸው ሰዎች ለዘላለም አልኖሩም። እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ ሞተው ወደ መቃብር ወርደዋል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ “ከሞት እንደተነሳና ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ሞት በእሱ ላይ እንደ ጌታ ሊሠለጥን አይችልም።” በሰማይ “ለዘላለም” የሚኖር ሲሆን መበስበስን ጨርሶ አያይም።—ሮም 6:9፤ ራእይ 1:5, 18፤ ቆላ. 1:18፤ 1 ጴጥ. 3:18
15. ኢየሱስ “በኩራት” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?
15 መንፈሳዊ አካል ይዞ መጀመሪያ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነው፤ የእሱ ትንሣኤ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሥራ 26:23) ይሁን እንጂ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ፣ ለታማኝ ሐዋርያቱ በሰማይ ከእሱ ጋር እንደሚገዙ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30) ይህን ሽልማት የሚያገኙት ግን ከሞቱ በኋላ ነው። ከዚያም ልክ እንደ ክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ይነሳሉ። ጳውሎስ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሌሎችም እንዳሉ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።”—1 ቆሮ. 15:20, 23
16. ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ከሞት የሚነሱበትን ጊዜ ለማወቅ የሚረዳን ምንድን ነው?
16 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ከሞት ስለሚነሱበት ጊዜ የሚጠቁመን ነገር አለ። ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው ክርስቶስ “በሚገኝበት ጊዜ” ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ባደረጉት ምርምር፣ ኢየሱስ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ የጀመረው በ1914 እንደሆነ ተገንዝበዋል። አሁንም የምንኖረው በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲሆን የዚህ ክፉ ሥርዓት ማብቂያ ደግሞ በጣም ተቃርቧል።
17, 18. በክርስቶስ መገኘት ወቅት አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ይሆናሉ?
17 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከተለውን ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል፦ “በሞት አንቀላፍተው ስላሉት ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም። ኢየሱስ እንደሞተና ከሞት እንደተነሳ የምናምን ከሆነ . . . በሞት ያንቀላፉትንም አምላክ ሕይወት ሰጥቶ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ያደርጋል። . . . ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የምንኖር በሞት አንቀላፍተው ያሉትን በምንም መንገድ አንቀድምም፤ ምክንያቱም ጌታ ራሱ በትእዛዝ ድምፅ . . . ከሰማይ ይወርዳል፤ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው የሞቱትም ቀድመው ይነሳሉ። ከዚያም በሕይወት ቆይተን የምንተርፈው እኛ በአየር ላይ ከጌታ ጋር ለመገናኘት ከእነሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መንገድ ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።”—1 ተሰ. 4:13-17
18 ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከናወነው፣ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በደመና ይነጠቃሉ።’ ‘በደመና የሚነጠቁት’ ቅቡዓን፣ ሞተው ረጅም ጊዜ ስለማይቆዩ ‘በሞት አያንቀላፉም’ ሊባል ይችላል። እነዚህ ቅቡዓን “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [ይለወጣሉ]።”—1 ቆሮ. 15:51, 52፤ ማቴ. 24:31
19. ወደፊት የሚከናወነው ትንሣኤ “የተሻለ ትንሣኤ” የተባለው ለምንድን ነው?
19 በአሁኑ ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ታማኝ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አልተቀቡም፤ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋም የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ክፉ ሥርዓት ‘በይሖዋ ቀን’ የሚደመደምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ይህ ቀን መቼ እንደሆነ ማናችንም ብንሆን ማወቅ አንችልም፤ ይሁንና ቀኑ በጣም እንደቀረበ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። (1 ተሰ. 5:1-3) ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ፣ ሌላ ዓይነት ትንሣኤ ይከናወናል፤ የሞቱ ሰዎች፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። ከሞት የተነሱት ሰዎች፣ ወደ ፍጽምና ደረጃ የመድረስና የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። ቀደም ባሉት ዘመናት “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀብለዋል”፤ ሆኖም ትንሣኤ ያገኙት እነዚህ ሰዎች እንደገና በሞት አንቀላፍተዋል፤ በመሆኑም ወደፊት የሚከናወነው ትንሣኤ “የተሻለ ትንሣኤ” እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዕብ. 11:35
20. የወደፊቱ ትንሣኤ በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
20 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰማያዊው ትንሣኤ ስለሚከናወንበት መንገድ ሲናገር “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል” ይላል። (1 ቆሮ. 15:23) በምድር ላይ ለመኖር ከሞት የሚነሱት ሰዎች ትንሣኤም በተደራጀ መልኩ እንደሚከናወን መተማመን እንችላለን። ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ክንውን ነው። የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በዘመናችን የሞቱ ሰዎች በቅድሚያ ከሞት ተነስተው ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ይገናኙ ይሆን? አመራር የመስጠት ችሎታ ያላቸው በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ አገልጋዮች፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የአምላክን ሕዝቦች በማደራጀቱ ሥራ እንዲካፈሉ ሲባል በቅድሚያ ከሞት ይነሱ ይሆን? ፈጽሞ ይሖዋን አገልግለው ስለማያውቁ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የሚነሱት መቼ እና የት ነው? ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ነገሮች አሁን መጨነቅ ያስፈልገናል? እዚያው ደርሰን የሚሆነውን እስክናይ መጠበቁ የተሻለ አይሆንም? ይሖዋ እነዚህን ነገሮች እንዴት እንደሚያከናውን ስንመለከት እንደምንደነቅ ጥርጥር የለውም።
21. የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ ምን ተስፋ አለን?
21 እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ በመታሰቢያ መቃብር ያሉትን ሙታን እንደሚያስነሳቸው ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል፤ ይሖዋ ይህን እንደሚያደርግ በኢየሱስ በኩል አረጋግጦልናል። (ዮሐ. 5:28, 29፤ 11:23) በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ይሖዋ ሙታንን ማስነሳት እንደሚችል ሲያስረዳ አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን ጠቅሶ “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 20:37, 38) እንግዲያው እኛም እንደ ጳውሎስ “[ሙታን] እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።—ሥራ 24:15