የአንባብያን ጥያቄዎች
ዕብራውያን 9፡16 ቃል ኪዳን እንዲጸና ቃል ኪዳን ሰጪው መሞት እንዳለበት ይናገራል። አዲሱን ቃል ኪዳን የሰጠው አምላክ ነው። እሱ ግን አልሞተም። ታዲያ ይህንን ጥቅስ እንዴት እንረዳዋለን?
በዕብራውያን 9:15-17 ላይ “የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ [ክርስቶስ] የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። ቃል ኪዳን ያለ እንደሆነ ቃል ኪዳን የገባውን [ሰው] ሞት ማርዳት የግድ ነውና። ቃል ኪዳን የሚጸናው በሞት ነውና። የቃል ኪዳኑ ተጋቢ [ሰው] በሕይወት በሚኖርበት ጊዜ ግን ምንም ዓይነት ኃይል አይኖረውም”a(አዓት) እንደሚል እናነባለን።
የአዲሱ ቃል ኪዳን አድራጊ ይሖዋ አምላክ ነው። በኤርምያስ 31:31-34 ላይ አምላክ ራሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን እንደሚገባ ተናግሯል። ሐዋርያው ጳውሎስም በዕብራውያን 8:8-13 ላይ ኤርምያስ 31:31-34ን ጠቅሶ የዚህ መለኮታዊ ቃል ኪዳን አመንጪ አምላክ መሆኑን እንደተገነዘበ አሳይቷል።
ይሁን እንጂ ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 9 ላይ ኢየሱስ በአዲሱ ቃል ኪዳን ረገድ የተጫወተውን የተለያየ ሚና በዝርዝር ገልጾአል። ክርስቶስ የመጣው የዚህ ቃል ኪዳን ሊቀ ካህን ለመሆን ነው። በሌላ በኩልም ለአዲሱ ቃል ኪዳን ተሠውቷል። “ሕሊናችንን ከሞተ ሥራ ሊያነፃ” የሚችለው “የክርስቶስ ደም” ብቻ ነው። ሙሴ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ነው።—ዕብራውያን 9:11-15
በአምላክና በሰዎች መሃል የሚገባ ቃል ኪዳን ለማጽናት ሞት አስፈላጊ እንደሚሆን ጳውሎስ ጠቅሶአል። ለዚህም የሕጉ ቃል ኪዳን ምሳሌ ይሆነናል። በአምላክና በሥጋዊ እሥራኤል መሃል የተደረገውን ውል ያዋዋለው ሙሴ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ ነበር። ስለዚህ ሙሴ እሥራኤላውያንን ወደ ቃል ኪዳኑ ለማምጣት ያገለገለና ወሳኝ ሚና የተጫወተ ሰው ነበር። በመሆኑም ሙሴ ከይሖዋ አምላክ ለመነጨው የሕግ ቃል ኪዳን እንደ ሰብአዊ ቃል ኪዳን አድራጊ ሊቆጠር ይችላል። ታዲያ የሕጉ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ እንዲውል ሙሴ ደመ ሕይወቱን ማፍሰስ አስፈልጎታልን? አላስፈለገውም። ለሙሴ ደም ምትክ ሆኖ የቀረበው የእንስሳት ደም ነበር።—ዕብራውያን 9:18-22
በይሖዋና በመንፈሳዊ እሥራኤል መሃል ስለተደረገው አዲስ ቃል ኪዳንስ ምን ሊባል ይችላል? በይሖዋና በመንፈሳዊ እሥራኤል መሃል አስታራቂና መካከለኛ የመሆን ታላቅ ሥራ የተሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ ቃል ኪዳን የመነጨው ከይሖዋ ቢሆንም የቃል ኪዳኑ መጽደቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመካ ነበር። ኢየሱስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ከመሆኑም ሌላ ወደዚህ ቃል ኪዳን ከሚገቡት የመጀመሪያ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ ሥጋዊ ግንኙነት ነበረው። (ሉቃስ 22:20, 28, 29) ከዚህም በላይ አዲሱን ቃል ኪዳን ለማጽደቅ የሚያስፈልገውን መሥዋዕት ለማቅረብ ብቃት ነበረው። ይህም መሥዋዕት የእንስሳት ሥጋ ሳይሆን ፍጹም ሰብአዊ ሕይወት ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ክርስቶስን የአዲሱ ቃል ኪዳን ሰብአዊ ቃልኪዳን አድራጊ ሊለው ችሏል። “ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ” ከገባ በኋላ አዲሱ ቃል ኪዳን ፀደቀ።—ዕብራውያን 9:12-14, 24
ጳውሎስ ሙሴና ኢየሱስ ሰብአዊ ቃል ኪዳን አድራጊዎች መሆናቸው ሲናገር ማንኛቸውም መካከለኛ የሆኑላቸውን ቃል ኪዳኖች ራሳቸው እንዳመነጩአቸው ማመልከቱ አልነበረም። ምክንያቱም እነዚህ ቃል ኪዳኖች የተደረጉት በአምላክ ነበር። እነዚህ ሰዎች ግን መካከለኛ የሆኑላቸውን ቃል ኪዳኖች ለማቋቋም እንደ መካከለኛ በመሆን ቀጥተኛ ድርሻ አበርክተዋል። በሁለቱም ቃል ኪዳኖች ሞት አስፈላጊ ሆኖ ነበር። በአሮጌው ቃል ኪዳን ረገድ እንስሳት የሙሴ ምትክ ሆነው ሲገደሉ ኢየሱስ ደግሞ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለገቡት ሰዎች ሲል የራሱን ደመ ሕይወት ሰጥቶአል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ “የቃል ኪዳኑ ተጋቢ” ተብለው የተተረጎሙት ሁለት የግሪክኛ ቃላት ቃል በቃል “የግል ቃል ኪዳን ያደረገው” ወይም “ቃል ኪዳን አድራጊው” የሚል ትርጉም አላቸው።—በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር በታተመው የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ኢንተርሊኒየር ትርጉምና በዶክተር አልፍሬድ ማርሻል ከግሪክኛ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የታተመው የአዲስ ኪዳን ኢንተርሊኒየር