ይሖዋ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” ይገልጣል
“በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና በእሱ የተገለጠው ራእይ ይህ ነው።”—ራእይ 1:1
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን የሚወክለው የትኛው የግዙፉ ምስል ክፍል ነው?
ዮሐንስ፣ በአንግሎ አሜሪካና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መካከል ያለውን ዝምድና የገለጸው እንዴት ነው?
ዳንኤልና ዮሐንስ የሰብዓዊ አገዛዝ ፍጻሜን የገለጹት እንዴት ነው?
1, 2. (ሀ) ዳንኤልና ዮሐንስ የጻፏቸው ትንቢቶች ስለ ምን ነገር እንድንገነዘብ ይረዱናል? (ለ) የአውሬው የመጀመሪያ ስድስት ራሶች የሚያመለክቱት ማንን ነው?
ዳንኤልና ዮሐንስ የጻፏቸው ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት በዓለም ላይ ስለሚከሰቱ በርካታ ነገሮች እንድንረዳ ያስችሉናል። ዮሐንስ ባየው አውሬ፣ ዳንኤል በተመለከተው አሥር ቀንዶች ያሉት አውሬና ግዙፉን ምስል አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ መካከል ያለውን ተዛምዶ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? እነዚህን ትንቢቶች በደንብ መረዳታችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
2 እስቲ በቅድሚያ ዮሐንስ በራእይ ያየውን አውሬ እንመልከት። (ራእይ, ምዕ. 13) ቀደም ሲል በነበረው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የአውሬው የመጀመሪያዎቹ ስድስት ራሶች የሚያመለክቱት ግብፅን፣ አሦርን፣ ባቢሎንን፣ ሜዶ ፋርስን፣ ግሪክንና ሮምን ነው። ሁሉም ለሴቲቱ ዘር ያላቸውን ጥላቻ አሳይተዋል። (ዘፍ. 3:15) ስድስተኛው ራስ የሆነው ሮም፣ ዮሐንስ ራእዩን ከጻፈ በኋላ ባሉት በርካታ ምዕተ ዓመታት ጭምር የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ቀጥሎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሰባተኛው ራስ ሮምን መተካቱ አይቀርም። ታዲያ ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው ማን ነው? በሴቲቱ ዘር ላይስ ምን ያደርጋል?
ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ኃያላን ሆኑ
3. አሥር ቀንዶች ያሉት አስፈሪው አውሬ ምንን ያመለክታል? አሥሩ ቀንዶችስ?
3 ዮሐንስ የተመለከተውን ራእይ ዳንኤል ካየው አሥር ቀንዶች ካሉት አስፈሪ አውሬ ጋር በማወዳደር በራእይ 13 ላይ የተገለጸውን አውሬ ሰባተኛ ራስ ማንነት ማወቅ እንችላለን።a (ዳን. 7:7, 8, 23, 24ን አንብብ።) ዳንኤል የተመለከተው አውሬ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረውን ሮምን ይወክላል። (ከገጽ 12-13 ላይ የሚገኘውን ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።) በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሮም መንግሥት መፈራረስ ጀመረ። ከሚያስፈራው አውሬ ራስ የወጡት አሥር ቀንዶች ከሮም ግዛቶች የወጡትን መንግሥታት ያመለክታሉ።
4, 5. (ሀ) ትንሹ ቀንድ ምን አደረገ? (ለ) የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማን ነው?
4 በዚህ አስፈሪ አውሬ ራስ ላይ ከወጡት ቀንዶች ወይም መንግሥታት መካከል አራቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። እነሱም ‘ትንሹ ቀንድ’ እና ይህ ቀንድ የነቃቀላቸው ሦስቱ ቀንዶች ናቸው። ብሪታንያን የሚያመለክተው ትንሹ ቀንድ፣ ሦስቱን ቀንዶች የነቃቀለው መቼ ነው? ቀድሞ የሮም ግዛት ክፍል የነበረችው ብሪታንያ ኃያል በመሆን ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ባለችበት ወቅት ነው። ይሁንና እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ድረስ ብሪታንያ ከሌሎቹ አንጻር ስትታይ ያላት ኃይል አነስተኛ ነበር። ከጥንቷ የሮም ግዛት የወጡት ሦስቱ አገሮች ማለትም ስፔን፣ ኔዘርላንድና ፈረንሳይ ከብሪታንያ ይልቅ ኃያላን ነበሩ። ብሪታንያ እነዚህ ኃያላን አገሮች የነበራቸውን ቦታ በመንጠቅ አንድ በአንድ ነቃቅላቸዋለች። በ18ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ብሪታንያ በዓለም መድረክ ላይ ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር ለመሆን በጉዞ ላይ ነበረች። ይሁን እንጂ የአውሬው ሰባተኛ ራስ የምትሆንበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር።
5 ብሪታንያ በዓለም ላይ የበላይነት እያገኘች ብትሄድም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት ቅኝ ግዛቶቿ ተገንጥለው ዩናይትድ ስቴትስ የሚባል መንግሥት መሠረቱ። ያም ሆኖ ዩናይትድ ስቴትስ ኃያል መንግሥት እንዲሆን ብሪታንያ በባሕር ኃይሏ አማካኝነት እገዛ አድርጋለች። የጌታ ቀን በ1914 ሲጀምር ብሪታንያ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሰፊ ግዛት የመሠረተች ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ጠንካራ ኢንዱስትሪ ገንብታ ነበር።b በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከብሪታንያ ጋር ልዩ ጥምረት ፈጠረች። የአውሬው ሰባተኛ ራስ ማለትም አንግሎ አሜሪካ፣ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ ብቅ ያለው በዚህ ጊዜ ነው። ይህ ራስ በሴቲቱ ዘር ላይ ምን ያደርግ ይሆን?
6. ሰባተኛው ራስ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን አደረገ?
6 የጌታ ቀን ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ፣ ሰባተኛው ራስ በአምላክ ሕዝብ ላይ ይኸውም ምድር ላይ በሚገኙት የክርስቶስ ወንድሞች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። (ማቴ. 25:40) ኢየሱስ፣ በእሱ መገኘት ወቅት የዘሩ ክፍል የሆኑት ቀሪ አባላት በምድር ላይ እንደሚኖሩና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት እንደሚወጡ ተናግሯል። (ማቴ. 24:45-47፤ ገላ. 3:26-29) የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በእነዚህ ቅዱሳን ላይ ጦርነት አውጆ ነበር። (ራእይ 13:3, 7) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይህ መንግሥት የአምላክን ሕዝቦች ጨቁኗል፤ አንዳንድ ጽሑፎቻቸውን አግዷል፤ እንዲሁም የታማኝና ልባም ባሪያ ወኪሎችን እስር ቤት ጨምሯቸዋል። በሰባተኛው ራስ ተጽዕኖ ምክንያት የስብከቱ ሥራ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሞተ ያህል ሆኖ ነበር። ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስቀድሞ ለዮሐንስ ገልጦለታል። በተጨማሪም አምላክ፣ የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆኑት ቅቡዓን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን በድጋሚ እንደሚያቀጣጥሉ ነግሮት ነበር። (ራእይ 11:3, 7-11) ይህ ትንቢት በትክክል እንደተፈጸመ ዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ያሳያል።
አንግሎ አሜሪካ እና የብረትና የሸክላ ድብልቅ የሆነው እግር
7. በአውሬው ሰባተኛ ራስና በግዙፉ ምስል መካከል ያለው ተዛማጅነት ምንድን ነው?
7 በአውሬው ሰባተኛ ራስና በግዙፉ ምስል መካከል ያለው ተዛማጅነት ምንድን ነው? ዩናይትድ ስቴትስ የወጣችው ከብሪታንያ ነው፤ ብሪታንያ ደግሞ የወጣችው ከሮም በመሆኑ በተዘዋዋሪ መንገድ ዩናይትድ ስቴትስም የወጣችው ከሮም ግዛት ነው። ስለ ምስሉ እግርስ ምን ማለት ይቻላል? እግሩ የብረትና የሸክላ ድብልቅ እንደሆነ ተገልጿል። (ዳንኤል 2:41-43ን አንብብ።) የምስሉን እግር አስመልክቶ የተነገረው ይህ ሁኔታ የተከሰተው ሰባተኛው ራስ ማለትም አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል በሆነበት ጊዜ ላይ ነው። ሸክላ የተቀላቀለበት ብረት ከንጹሕ ብረት ጋር እኩል ጥንካሬ እንደማይኖረው ሁሉ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትም ከወጣበት ግዛት ይኸውም ከሮም ያነሰ ኃይል ይኖረዋል። ታዲያ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ደካማ የሆነው እንዴት ነው?
8, 9. (ሀ) ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በምስሉ እግር ላይ የሚገኘው ሸክላ የሚያመለክተው ምንድን ነው?
8 የአውሬው ሰባተኛ ራስ እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን ያሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛውን የዓለም ጦርነት በድል በማጠናቀቅ ኃይሉን አሳይቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ሰባተኛው ራስ እንደ ብረት ያለ ኃይል ያለው መሆኑ በግልጽ ታይቷል።c ከዚህ ጦርነት በኋላም ቢሆን ሰባተኛው ራስ እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን ማሳየቱን ቀጥሏል። ይሁንና ሰባተኛ ራስ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ብረቱ ከሸክላ ጋር ተደባልቆ ነበር።
9 የይሖዋ አገልጋዮች የምስሉ እግር ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ለረጅም ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዳንኤል 2:41 የብረቱና የሸክላው ድብልቅ የሚያመለክተው በርካታ መንግሥታትን ሳይሆን አንድን “መንግሥት” ብቻ እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም ሸክላው የሚያመለክተው በንጹሕ ብረት ከተመሰለው ከሮም ግዛት ያነሰ ጥንካሬ ያለው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ተጽዕኖ በሚያሳድርባቸው የምድር ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን የእሱን አቅም የሚያዳክሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው። ሸክላው ‘የሰው ዘርን’ ማለትም ተራውን ሕዝብ እንደሚያመለክት የዳንኤል መጽሐፍ ይገልጻል። (ዳን. 2:43 የ1954 ትርጉም) በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ውስጥ ሰዎች በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ፣ በሠራተኛ ማኅበራትና ነፃነት ለማግኘት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት መብታቸውን ለማስከበር ሞክረዋል። ተራው ሕዝብ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን እንዳያሳይ አዳክሞታል። በተጨማሪም የምርጫ ተወዳዳሪዎች የሚያገኙት ተቀራራቢ ውጤትና ተጻራሪ የሆኑ የፖለቲካ አመለካከቶች መኖራቸው ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ መሪዎችም እንኳ ፖሊሲዎቻቸውን ለማስፈጸም የሚያስችል የተሟላ ሥልጣን እንዳይኖራቸው አድርጓል። ዳንኤል ይህ “መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ” እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል።—ዳን. 2:42፤ 2 ጢሞ. 3:1-3
10, 11. (ሀ) የምስሉ “እግሮች” የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? (ለ) ስለ ጣቶቹ ቁጥር ምን ብለን መደምደም እንችላለን?
10 በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የተመሠረተው ልዩ ዝምድና በ21ኛው መቶ ዘመንም የቀጠለ ሲሆን እነዚህ አገሮች ከዓለም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ተመሳሳይ አቋም ያራምዳሉ። ግዙፉን ምስልና አውሬውን በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች እንደሚያሳዩት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን የሚተካ ሌላ ኃያል መንግሥት ወደፊት አይነሳም። ይህ የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት፣ በብረት እግር ከተመሰለው ከሮም ይልቅ ደካማ ቢሆንም የሚፈራርሰው በራሱ አይደለም።
11 የጣቶቹ ቁጥርስ የሚያመለክተው ነገር አለ? ዳንኤል ባያቸው ሌሎች ራእዮች ላይ ትንቢታዊ ትርጉም ያላቸውን ቁጥሮች ለይቶ ተናግሯል፤ ለምሳሌ በተለያዩ አራዊት ራሶች ላይ የታዩትን ቀንዶች ቁጥር ጠቅሷል። ይሁንና ዳንኤል ስለ ምስሉ ሲናገር የጣቶቹን ቁጥር አልገለጸም። በመሆኑም የምስሉ እጆችና እግሮች እንዲሁም የእጆቹ ጣቶች፣ ቁጥራቸው ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌለው ሁሉ የጣቶቹ ቁጥርም ምንም ትርጉም ያለው አይመስልም። ይሁንና ዳንኤል የምስሉ እግር ጣቶች ከብረትና ከሸክላ እንደተሠሩ ተናግሯል። ዳንኤል ከሰጠው መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክን መንግሥት የሚወክለው “ድንጋይ” ምስሉን በሚመታበት ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆነው አንግሎ አሜሪካ ነው።—ዳን. 2:45
አንግሎ አሜሪካ እና ሁለት ቀንድ ያለው አውሬ
12, 13. ሁለት ቀንድ ያለው አውሬ ምንን ያመለክታል? ምንስ ያደርጋል?
12 የአንግሎ አሜሪካ መንግሥት የብረትና የሸክላ ድብልቅ ቢሆንም ኢየሱስ ለዮሐንስ የሰጠው ራእይ እንደሚጠቁመው ይህ ኃያል መንግሥት በመጨረሻዎቹ ቀኖች ቁልፍ ሚና መጫወቱን ይቀጥላል። እንዴት? ዮሐንስ እንደ ዘንዶ የሚናገር ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ እንግዳ የሆነ አውሬ የሚያመለክተው ምንድን ነው? ሁለት ቀንዶች ያሉት መሆኑ ጥምር መንግሥት እንደሆነ ያሳያል። ዮሐንስ የተመለከተው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን ልዩ ሚና እንደሚጫወት ጠቁሟል።—ራእይ 13:11-15ን አንብብ።
13 ሁለት ቀንድ ባለው በዚህ አውሬ አስተባባሪነት የአውሬው ምስል ይፈጠራል። ዮሐንስ የአውሬው ምስል እንደሚገለጥ ከዚያም እንደሚጠፋና በኋላም እንደገና እንደሚገለጥ ጽፏል። በብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ አስተባባሪነት የዓለምን መንግሥታት አንድ ለማድረግና እነሱን ወክሎ ለመሥራት የተቋቋመው ድርጅት ያጋጠመው ሁኔታ ይኸው ነው።d ይህ ድርጅት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመ ሲሆን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በመባል ይጠራ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር ግን ይህ ድርጅት ጠፋ። ጦርነቱ እየተካሄደ ሳለ የአምላክ ሕዝቦች በራእይ መጽሐፍ ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የአውሬው ምስል ድጋሚ እንደሚገለጥ ተናገሩ። እንደተባለውም የአውሬው ምስል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመባል በድጋሚ ብቅ አለ።—ራእይ 17:8
14. የአውሬው ምስል፣ “ስምንተኛ ንጉሥ” የሆነው እንዴት ነው?
14 ዮሐንስ፣ የአውሬውን ምስል “ስምንተኛ ንጉሥ” በማለት ጠርቶታል። ይሁንና ስምንተኛ ንጉሥ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የአውሬው ስምንተኛ ራስ እንደሆነ ተደርጎ እንዳልተገለጸ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ የዚህ አውሬ ምስል ነው። ይህ የአውሬው ምስል ኃይል ሊያገኝ የቻለው ከአባል አገሮች በተለይም ደግሞ የጀርባ አጥንት ከሆነለት ከአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። (ራእይ 17:10, 11) ይሁን እንጂ ይህ ምስል እንደ ንጉሥ በመሆን አንድ ለየት ያለ ነገር ለማከናወን ሥልጣን ይቀበላል፤ ይህ ክንውን የዓለምን ታሪክ የሚለውጡ ተከታታይ ክስተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል።
የአውሬው ምስል ጋለሞታይቱን ይቦጫጭቃታል
15, 16. ጋለሞታይቱ ማንን ታመለክታለች? ደጋፊዎቿስ ምን እየሆኑ ነው?
15 አንዲት ጋለሞታ፣ የአውሬው ምስል የሆነውን ቀዩን አውሬ እንደፈለገች በመምራት ስትጋልበው ዮሐንስ ተመልክቷል። ይህች ምሳሌያዊ ጋለሞታ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ስም ተሰጥቷታል። (ራእይ 17:1-6) ጋለሞታይቱ፣ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ፣ በዋነኝነት ደግሞ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትን ትወክላለች። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች የአውሬውን ምስል ባርከዋል፤ እንዲሁም በእሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት አድርገዋል።
16 ታላቂቱ ባቢሎን፣ እሷን የሚደግፉ ሰዎችን የሚያመለክቱት ውኃዎቿ በጌታ ቀን ላይ በአስገራሚ ፍጥነት ሲደርቁ ተመልክታለች። (ራእይ 16:12፤ 17:15) ለምሳሌ የአውሬው ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕልውና ሲመጣ በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ የምታሳድረው ሕዝበ ክርስትና የምዕራቡን ዓለም ተቆጣጥራ ነበር። ዛሬ ግን የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትና ቀሳውስቶቻቸው በምዕመኖቻቸው ዘንድ የነበራቸውን አክብሮትና ድጋፍ አጥተዋል። እንዲያውም ብዙ ሰዎች፣ ሃይማኖት ለግጭቶች መንስኤ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲቆም ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ የምዕራቡ ዓለም ምሁራን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
17. የሐሰት ሃይማኖት በቅርቡ ምን ይሆናል? ለምንስ?
17 የሐሰት ሃይማኖት ግን እንዲህ እንደዋዛ የሚጠፋ አይደለም። አምላክ በመንግሥታት ልብ ውስጥ አንድ ሐሳብ እስኪያኖር ድረስ ጋለሞታይቱ ነገሥታትን እሷ በፈለገችው አቅጣጫ በመምራት በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች። (ራእይ 17:16, 17ን አንብብ።) በቅርቡ ይሖዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወከሉትንና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ ኃይሎች ተጠቅሞ በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። እነዚህ መንግሥታት በጋለሞታይቱ ላይ እርምጃ ስለሚወስዱ ተጽዕኖ ማሳደሯ ያከትማል፤ እንዲሁም ሀብቷ ይጠፋል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ይህን ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀየሩ ነው፤ በቀዩ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ጋለሞታ ሚዛኗን መጠበቅ ስላቃታት ልትወድቅ እየተንገዳገደች ነው። ያም ሆኖ ከተቀመጠችበት የምትወድቀው ሸርተት ብላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አወዳደቋ ድንገተኛና አስደንጋጭ ይሆናል።—ራእይ 18:7, 8, 15-19
የአውሬዎቹ መጨረሻ
18. (ሀ) አውሬው ምን ያደርጋል? ውጤቱስ ምን ይሆናል? (ለ) በዳንኤል 2:44 ላይ የአምላክ መንግሥት የትኞቹን መንግሥታት እንደሚያጠፋ ተገልጿል? (ገጽ 17 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
18 በምድር ላይ የሚገኘውና የሰይጣን ፖለቲካዊ መሣሪያ የሆነው አውሬ፣ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ በአምላክ መንግሥት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ይሞክራል። የምድር ነገሥታት ሰማይ በሚኖሩት ላይ ጥቃት መሰንዘር ስለማይችሉ በምድር ላይ በሚገኙና የአምላክን መንግሥት በሚደግፉ ሕዝቦች ላይ ቁጣቸውን ይገልጻሉ። እርግጥ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። (ራእይ 16:13-16፤ 17:12-14) ዳንኤል ይህ የመጨረሻ ጦርነት የሚኖረውን አንድ ገጽታ ይነግረናል። (ዳንኤል 2:44ን አንብብ።) በራእይ 13:1 ላይ የተጠቀሰው አውሬ፣ የዚህ አውሬ ምስልና ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ ድምጥማጣቸው ይጠፋል።
19. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? አሁን ምን የምናደርግበት ጊዜ ነው?
19 የምንኖረው የአውሬው ሰባተኛ ራስ ሥልጣን ላይ ባለበት ወቅት ነው። ይህ አውሬ ከመጥፋቱ በፊት ስምንተኛ ራስ እንደሚኖረው አልተገለጸም። በመሆኑም የሐሰት ሃይማኖቶች በሚጠፉበት ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ የሚቀጥለው አንግሎ አሜሪካ ነው። በዳንኤልና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተመለከትናቸው ትንቢቶች በዝርዝር ተፈጽመዋል። የሐሰት ሃይማኖት ጥፋትም ሆነ የአርማጌዶን ጦርነት በቅርቡ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን አስቀድሞ ገልጦልናል። ታዲያ በትንቢት ለተነገሩት ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን? (2 ጴጥ. 1:19) እንግዲያው ከይሖዋ ጎን ለመቆምና የእሱን መንግሥት ለመደገፍ ጊዜው አሁን ነው።—ራእይ 14:6, 7
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሥር ቁጥር ብዙውን ጊዜ ሙላትን ለማመልከት ይሠራበታል፤ በዚህ አገባቡም ከሮም ግዛቶች የወጡትን መንግሥታት በሙሉ ያመለክታል።
b እርግጥ ነው፣ ጥምር ለሆነው የዓለም ኃያል መንግሥት መገኛ የሆኑት ብሪታንያና አሜሪካ በ18ኛው መቶ ዘመን ላይ በየፊናቸው ኃያል መንግሥት ሆነው ነበር፤ ይሁንና ዮሐንስ ይህ መንግሥት ሰባተኛ ራስ በመሆን ብቅ የሚለው በጌታ ቀን ላይ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት የጀመሩት ‘በጌታ ቀን’ ላይ ነው። (ራእይ 1:10) ሰባተኛው ራስ የሆኑት ብሪታንያና አሜሪካ ግንባር ፈጥረው የዓለም ኃያል መንግሥት የሆኑት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነው።
c ዳንኤል ይህ ንጉሥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሚያስከትለውን ጥፋት አስቀድሞ በራእይ የተመለከተ ሲሆን “አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል” በማለት ጽፏል። (ዳን. 8:24) ለምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአንግሎ አሜሪካ ጠላት በሆነ አገር ላይ ሁለት የአቶሚክ ቦንቦችን በመጣል ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አሰቃቂ ጥፋት አድርሳለች።
d ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 240, 241, 253 ተመልከት።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘እነዚያ መንግሥታት ሁሉ’ የተባሉት እነማን ናቸው?
በዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ትንቢት የአምላክ መንግሥት “እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል” ይላል። እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀሱት መንግሥታት የሚያመለክቱት በምስሉ የተለያዩ ክፍሎች የተመሰሉትን መንግሥታት ብቻ ነው።
ስለ ሌሎቹ ሰብዓዊ መንግሥታትስ ምን ማለት ይቻላል? ተመሳሳይ ስለሆነ ጉዳይ የሚናገረው በራእይ መጽሐፍ ላይ ያለው ትንቢት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠናል። ትንቢቱ መላው ‘የዓለም ነገሥታት’ በይሖዋ ላይ ለመነሳት “ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” እንደሚሰበሰቡ ይገልጻል። (ራእይ 16:14፤ 19:19-21) በመሆኑም በአርማጌዶን የሚጠፉት በምስሉ ላይ የተገለጹት መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ መላው ሰብዓዊ አገዛዝ ነው።