ወደ አምላክ እረፍት ገብተሃል?
“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።”—ዕብ. 4:12
1. በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት መግባት የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንናገረውን ያህል ቀላል የማይሆነው ለምን ሊሆን ይችላል?
ባለፈው የጥናት ርዕስ ላይ ታዛዥ በመሆንና ከአምላክ ዓላማዎች ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ ወደ እረፍቱ መግባት እንደምንችል ተመልክተናል። በእርግጥ ይህን ማድረግ የምንናገረውን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል። አንድ የምንወደውን ነገር ይሖዋ እንደማይቀበለው ስናውቅ መጀመሪያ ላይ የሚቀናን አለመታዘዝ ይሆናል። ይህም “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆንን መማር እንደሚኖርብን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። (ያዕ. 3:17) በዚህ ርዕስ ላይ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ ይኸውም ከልባችን ለመታዘዝ ፈቃደኞች መሆን አለመሆናችን የሚታይባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመለከታለን።
2, 3. በይሖዋ ፊት ምንጊዜም የተመረጠ ዕቃ ሆነን ለመገኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጥህ ለመቀበል ፈቃደኛ ነህ? ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አምላክ ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውን ዕቃ’ ለራሱ እንደሚሰበስብ ይናገራሉ። (ሐጌ 2:7 የ1954 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን መጀመሪያ ላይ እውነትን ስንማር በአምላክ ዘንድ የተመረጠ ዕቃ አልነበርንም። ይሁንና ለአምላክና ለውድ ልጁ ያለን ፍቅር አምላክን ሙሉ በመሉ ለማስደሰት ስንል በአመለካከታችንና በልማዶቻችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንድናደርግ አነሳስቶናል። ይሖዋ እንዲረዳን ደጋግመን ከጸለይንና አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ብዙ ከጣርን በኋላ ራሳችንን ወስነን በመጠመቅ ክርስቲያኖች ስንሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አገኘን።—ቆላስይስ 1:9, 10ን አንብብ።
3 ይሁንና ፍጹማን ባለመሆናችን ካሉብን ድክመቶች ጋር የምናደርገው ትግል ስንጠመቅ አብቅቷል ማለት አይደለም። ይህ ትግል ፍጽምና ላይ እስክንደርስ ድረስ ይቀጥላል። ያም ቢሆን የምናደርገውን ትግል እስከቀጠልንና በአምላክ ፊት እጅግ የተመረጠ ዕቃ ሆነን ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ እስካደረግን ድረስ ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
ምክር ሲያስፈልገን
4. በየትኞቹ ሦስት መንገዶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሊሰጠን ይችላል?
4 ድክመቶቻችንን ለማስተካከል እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ድክመቶቻችንን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ልባችንን እንድንፈትሽ የሚያነሳሳ ንግግር ስናዳምጥ ወይም በጽሑፎቻችን ላይ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርግ ሐሳብ ስናነብ አንድ ከባድ ድክመት እንዳለብን እንገነዘብ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ንግግር ላይ የቀረበውን ሐሳብም ሆነ በጽሑፎች ላይ የወጣውን ነጥብ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው እንደሚገባ ካልተገነዘብን ይሖዋ ያለብንን ድክመት እንድንገነዘብ ለመርዳት በአንድ የእምነት ባልንጀራችን ይጠቀም ይሆናል።—ገላትያ 6:1ን አንብብ።
5. ስለ የትኞቹ ጉዳዮች ምክር ሲሰጠን አሉታዊ ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን? ክርስቲያን ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት መቀጠል ያለባቸው ለምንድን ነው? አብራራ።
5 ምክር የተሰጠን በጥበብና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ቢሆንም እንኳ ፍጹም ያልሆነ ሰው የሚሰጠንን ምክር መቀበል ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሰዎች እኛን “በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት” እንዲያደርጉ ይሖዋ በገላትያ 6:1 ላይ ትእዛዝ እንደሰጣቸው ማስታወስ ያስፈልጋል። የሚሰጠንን ምክር ከተቀበልን በአምላክ ዘንድ እጅግ የተመረጠ ዕቃ እንሆናለን። እርግጥ ነው፣ ወደ አምላክ በምንጸልይበት ጊዜ ፍጹም አለመሆናችንን እንጠቅሳለን። ይሁንና አንድ ግለሰብ፣ የሆነ ድክመት እንዳለብን ሲጠቁመን ሰበብ መፍጠር ወይም ችግሩ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ መናገር ይቀናን ይሆናል፤ አሊያም ምክሩን የሰጠን ግለሰብ ይህን ለማድረግ የተነሳሳበት ዓላማም ሆነ ምክሩን የሰጠበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ መግለጽ ይዳዳን ይሆናል። (2 ነገ. 5:11) በተለይ ደግሞ ምክሩ በቀላሉ የምንከፋበትን ጉዳይ የሚመለከት በሚሆንበት ጊዜ ምክሩን የሰጠንን ግለሰብ የሚያሳዝን መጥፎ ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን፤ ለምሳሌ የአንድ የቤተሰባችንን አባል አካሄድ፣ አለባበሳችንን፣ የግል ንጽሕናችንን ወይም እኛ ብንወደውም ይሖዋ የሚጠላውን መዝናኛ የሚመለከት ምክር ሲቀርብልን እንዲህ እናደርግ ይሆናል። ይሁንና ከተረጋጋን በኋላ ነገሩን ስናስበው፣ የሰጠነው ምላሽ ለራሳችን እንኳ ሊያስገርመን እንዲያውም ምክሩ ተገቢ እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን።
6. የአምላክ ቃል ‘የልብን ሐሳብና ዓላማ’ የሚገልጠው እንዴት ነው?
6 ይህ ጥናት የተመሠረተበት ጥቅስ የአምላክ ቃል “ኃይለኛ” መሆኑን ያስታውሰናል። አዎን፣ የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠመቃችን በፊት የሚያስፈልገንን ለውጥ እንድናደርግ እንደረዳን ሁሉ ከተጠመቅንም በኋላ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ ይረዳናል። በተጨማሪም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የአምላክ ቃል “ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል” ብሏል። (ዕብ. 4:12) በሌላ አባባል የአምላክን ዓላማ በግልጽ ስንረዳ የምንሰጠው ምላሽ ውስጣዊ ማንነታችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ታዲያ ለሰው በሚታየው ማንነታችንና (“ነፍስ”) በእውነተኛ ማንነታችን (“መንፈስ”) መካከል አንዳንድ ጊዜ ልዩነት ይታያል? (ማቴዎስ 23:27, 28ን አንብብ።) አንተ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ ምን ዓይነት እርምጃ እንደምትወስድ እስቲ ለማሰብ ሞክር።
ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ተጓዝ
7, 8. (ሀ) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ የተወሰኑ ክፍሎች መጠበቃቸውን የቀጠሉት ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ይህ አካሄድ ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር የሚስማማ ነበር?
7 አብዛኞቻችን ምሳሌ 4:18 ምን እንደሚል በቃላችን እናውቃለን፤ ጥቅሱ “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው” ይላል። ይህም በጊዜ ሂደት አኗኗራችን እየተለወጠና ስለ አምላክ ዓላማዎች ያለን እውቀት እየጨመረ እንደሚሄድ የሚጠቁም ነው።
8 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በርካታ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ከሙሴ ሕግ መላቀቅ ከብዷቸው ነበር። (ሥራ 21:20) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር እንዳልሆኑ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ቢያቀርብም አንዳንዶች በመንፈስ መሪነት የሰጣቸውን ይህን ሐሳብ አልተቀበሉትም። (ቆላ. 2:13-15) ምናልባትም የሕጉን የተወሰኑ ክፍሎች መጠበቃቸውን ቢቀጥሉ ከሚደርስባቸው ስደት ማምለጥ እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህ ክርስቲያኖች ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ ፈቃደኞች እስካልሆኑ ድረስ ወደ አምላክ እረፍት መግባት እንደማይችሉ በግልጽ ነግሯቸዋል።a (ዕብ. 4:1, 2, 6፤ ዕብራውያን 4:11ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ከፈለጉ አምላክ ሕዝቦቹን በተለየ አቅጣጫ እየመራቸው እንደሆነ መቀበል ነበረባቸው።
9. አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በምንረዳበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
9 በዘመናችን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከምንረዳበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ተደርጓል። ይህ መሆኑ ሊያሳስበን አይገባም፤ እንዲያውም በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ ይበልጥ እንድንተማመን ሊያደርገን ይገባል። ‘ባሪያውን’ የሚወክለው የበላይ አካል ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን ግንዛቤ ይበልጥ መብራራት ወይም መስተካከል እንዳለበት ሲገነዘብ አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ታማኝና ልባም ባሪያ ይበልጥ የሚያሳስበው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ ከሚሄደው የአምላክ ዓላማ ጋር መተባበሩ እንጂ ማስተካከያ በማድረጉ የሚደርስበት ነቀፋ አይደለም። አንተስ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በምንረዳበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ሲደረግ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?—ሉቃስ 5:39ን አንብብ።
10, 11. አንዳንዶች ምሥራቹን ለመስበክ አዳዲስ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ሐሳብ ሲቀርብላቸው ከሰጡት ምላሽ ምን ትምህርት እናገኛለን?
10 እስቲ ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ፣ ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪ የሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከቱን ተልእኮ መወጣት የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው ንግግሮችን አድናቂ ለሆኑ አድማጮች ማቅረብ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። እነዚህ ወንድሞች ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ንግግር መስጠት ይወዱ ነበር፤ አንዳንዶቹም ላቀረቡት ንግግር ከአድማጮች የሚቸራቸው አድናቆት በጣም ያስደስታቸው ነበር። ይሁንና ይሖዋ፣ ከቤት ወደ ቤት መስበክን ጨምሮ ሕዝቦቹ በተለያዩ መንገዶች እንዲያገለግሉ እንደሚፈልግ ከጊዜ በኋላ ግልጽ ሆነ። አንዳንድ የተዋጣላቸው የሕዝብ ተናጋሪዎች ግን ማንኛውንም አዲስ ነገር ለመሞከር አሻፈረን አሉ። እነዚህ ሰዎች ከውጭ ሲታዩ ሙሉ በሙሉ ለጌታ ያደሩ መንፈሳዊ ሰዎች ይመስሉ ነበር። ሆኖም የስብከቱን ሥራ በተመለከተ የአምላክ ዓላማ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ሲቀርብላቸው እውነተኛ ሐሳባቸው፣ ዓላማቸውና ፍላጎታቸው ገሃድ ወጣ። ይሖዋ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ተሰምቶት ነበር? እንዳልባረካቸው በግልጽ ታይቷል። እነዚህ ሰዎች ድርጅቱን ትተው ወጥተዋል።—ማቴ. 10:1-6፤ ሥራ 5:42፤ 20:20
11 ይህ ሲባል ግን ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ ሆነው የቀጠሉት ሁሉ ለሰዎች መስበክ ቀላል ሆኖላቸው ነበር ማለት አይደለም። ብዙዎቹ በተለይ መጀመሪያ ላይ ይህ ሥራ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። ያም ሆኖ ታዛዦች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የፍርሃት ስሜታቸውን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ይሖዋም በእጅጉ ባርኳቸዋል። አንተስ ከለመድከውና ከሚቀልህ በተለየ መንገድ እንድትሰብክ ስትጠየቅ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? አዲስ ነገር ለመሞከር ፈቃደኛ ነህ?
የምንወደው ሰው ይሖዋን ማምለኩን ሲያቆም
12, 13. (ሀ) ይሖዋ፣ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች እንዲወገዱ የሚያደርግበት ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ምን ዓይነት ፈተና ሊያጋጥማቸው ይችላል? ፈተናውን ይበልጥ የሚያከብደው ምንድን ነው?
12 አምላክን ለማስደሰት በአካላዊ፣ በሥነ ምግባራዊና በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ መሆን እንዳለብን የሚገልጸውን መሠረታዊ ሥርዓት ሁላችንም እንደምንስማማበት ምንም ጥርጥር የለውም። (ቲቶ 2:14ን አንብብ።) ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ለይሖዋ ያለን ታማኝነት የሚፈተንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። በጉባኤ ውስጥ አርዓያ የሚሆኑ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እነዚህ ወላጆች ያላቸው አንድ ልጅ ሲሆን እሱም እውነትን ተወ። ይህ ወጣት ከይሖዋና ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ወላጆቹ ጋር ካለው ዝምድና ይልቅ ‘በኃጢአት የሚገኝን ጊዜያዊ ደስታ’ ስለመረጠ ከጉባኤ ተወገደ።—ዕብ. 11:25
13 እነዚህ ወላጆች በከፍተኛ ሐዘን እንደሚዋጡ የታወቀ ነው! እርግጥ ነው፣ ውገዳን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መመሪያ እንደሚሰጥ ያውቃሉ፦ “ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን [ተዉ] አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ [አትብሉ]።” (1 ቆሮ. 5:11, 13) ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ጥቅስ ላይ “ማንኛውም ሰው” የሚለው ሐሳብ አብሯቸው የማይኖር የቤተሰብ አባልንም እንደሚያጠቃልል ይገነዘባሉ። ይሁንና እነዚህ ወላጆች ልጃቸውን በጣም ይወዱታል! ለልጃቸው ያላቸው ጥልቅ ፍቅር እንደሚከተለው ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፦ ‘ከልጃችን ጋር ያለን ግንኙነት ውስን እንዲሆን ካደረግን ወደ ይሖዋ እንዲመለስ እንዴት ልንረዳው እንችላለን? ከእሱ ጋር አዘውትረን ብንገናኝ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ይበልጥ ልንረዳው አንችልም?’b
14, 15. ወላጆች የተወገደ ልጃቸውን ማናገር ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ሲወስኑ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?
14 እነዚህ ወላጆች ያጋጠማቸው ሁኔታ በጣም ያሳዝነናል። ይሁንና ልጃቸው የራሱን ምርጫ ማድረግ የሚችል ሲሆን ከወላጆቹና ከሌሎች የእምነት ባልንጀሮቹ ጋር ካለው የጠበቀ ወዳጅነት ይልቅ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ጎዳና መከተልን መርጧል። በሌላ በኩል ግን ወላጆቹ በምርጫው ጣልቃ መግባት አይችሉም። እነዚህ ወላጆች ሁኔታውን ለማስተካከል ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው በሐዘን ቢዋጡ ምንም አያስገርምም!
15 ታዲያ እነዚህ ወላጆች ምን ያደርጉ ይሆን? የይሖዋን ግልጽ መመሪያዎች ይታዘዙ ይሆን? ወይስ “አስፈላጊ የሆነ የቤተሰብ ጉዳይ አለን” በሚል ሰበብ ከተወገደው ልጃቸው ጋር አዘውትረው ለመገናኘት ይሞክራሉ? ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማው ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ዓላማ የድርጅቱን ንጽሕና መጠበቅና ከተቻለ ደግሞ ኃጢአት የሠሩት ሰዎች ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ማነሳሳት ነው። ክርስቲያን ወላጆች ከዚህ ዓላማ ጋር መተባበር የሚችሉት እንዴት ነው?
16, 17. አሮን በተወው ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 የሙሴ ወንድም አሮን ከሁለት ልጆቹ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ናዳብና አብዩድ የተባሉት ልጆቹ በይሖዋ ፊት ያልተፈቀደ እሳት በማቅረባቸው በተቀሰፉ ጊዜ አሮን ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። እርግጥ ነው፣ የአሮን ልጆች ስለሞቱ ከዚያ በኋላ ከወላጆቻቸው ጋር መነጋገር አይችሉም ነበር። ይሁንና ነገሩ በዚህ አላበቃም። ይሖዋ፣ ለአሮንና ታማኝ ለሆኑት ልጆቹ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ [ሐዘናችሁን ለመግለጽ] ጠጕራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ።” (ዘሌ. 10:1-6) ትምህርቱ ግልጽ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ ታማኝ ላልሆኑ የቤተሰባችን አባላት ካለን ፍቅር መብለጥ ይኖርበታል።
17 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕጎቹን የሚጥሱ ሰዎችን ወዲያውኑ አይቀስፋቸውም። ከዚህ ይልቅ ንስሐ ገብተው ከኃጢአታቸው እንዲመለሱ በፍቅር ተነሳስቶ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ይሁንና ወላጆች፣ ከተወገደ ልጃቸው ጋር ሳያስፈልግ በመገናኘት አምላክን መፈታተናቸውን ቢቀጥሉ ይሖዋ ምን ይሰማዋል?
18, 19. የተወገዱ ግለሰቦችን በተመለከተ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ የሚያከብሩ የቤተሰብ አባላት ምን በረከቶች ያገኛሉ?
18 ከዚህ ቀደም ተወግደው የነበሩ ብዙ ክርስቲያኖች ጓደኞቻቸውና የቤተሰባቸው አባላት ቁርጥ ያለ አቋም መያዛቸው ወደ ልባቸው እንዲመለሱ እንደረዳቸው በግልጽ ይናገራሉ። በአንድ ወቅት ሽማግሌዎች፣ አንዲት የተወገደች ሴት ወደ ጉባኤው እንድትመለስ የድጋፍ ሐሳብ ሲያቀርቡ ሕይወቷን እንድታስተካክል የረዳት “አንዱ ነገር ታላቅ ወንድሟ ለውገዳ ዝግጅት የነበረው አክብሮት” እንደሆነ ገልጸው ነበር። ይህች ሴት “ወንድሟ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን በታማኝነት መከተሉ ወደ ይሖዋ ድርጅት ለመመለስ እንዳነሳሳት” ተናግራለች።
19 ከዚህ በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን፣ የሚሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንዳንቀበል ልባችን ቢያነሳሳንም እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ለማስወገድ መታገል ይኖርብናል። አምላክ ያሉብንን ችግሮች ለማስተካከል የሚወስደው እርምጃ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ከልባችን ልናምን ይገባል።
“የአምላክ ቃል ሕያው” ነው
20. በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ልንረዳው እንችላለን? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
20 ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያው” እንደሆነ ሲጽፍ በዋነኝነት በጽሑፍ ስለሰፈረው የአምላክ ቃል ይኸውም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩ አልነበረም።c በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጳውሎስ፣ አምላክ ስለሰጣቸው ተስፋዎች እየተናገረ እንደነበር ይጠቁማል። ጳውሎስ ሊናገረው የፈለገው ነጥብ፣ አምላክ ቃል የገባውን ነገር ሳይፈጽም የማይቀር መሆኑን ነው። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንደሚከተለው በማለት ይህን ገልጿል፦ “ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ . . . የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።” (ኢሳ. 55:11) እንግዲያው ነገሮች እኛ እንደምንፈልገው ቶሎ ሳይፈጸሙ ሲቀሩ ትዕግሥት ማጣት አይኖርብንም። ይሖዋ ዓላማውን በተሳካ መንገድ ከዳር ለማድረስ ‘መሥራቱን’ ይቀጥላል።—ዮሐ. 5:17
21. በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባል የሆኑ ታማኝ አረጋውያንን የሚያጽናናቸው እንዴት ነው?
21 ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባል የሆኑ ታማኝ አረጋውያን ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ሲያገለግሉት ቆይተዋል። (ራእይ 7:9) ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንደሚያረጁ ፈጽሞ አላሰቡም ነበር። ይሁንና ይህ መሆኑ ተስፋ አላስቆረጣቸውም። (መዝ. 92:14) አምላክ የገባው ቃል የሞተ ወይም ያበቃለት ነገር እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ ሕያው እንደሆነና ይሖዋም ቃሉን ለመፈጸም እየሠራ መሆኑን ይገነዘባሉ። አምላክ፣ ለዓላማው ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው እኛም ዓላማውን ከፍ አድርገን ስንመለከተው ደስ ይለዋል። ይሖዋ፣ ዓላማው እንደሚፈጸምና ሕዝቦቹም በቡድን ደረጃ ዓላማውን እንደሚደግፉ በእርግጠኝነት ስለሚያውቅ አሁን ባለንበት በዚህ በሰባተኛው ቀን እረፍት ላይ ነው ሊባል ይችላል። አንተስ ወደ አምላክ እረፍት ገብተሃል?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በርካታ የአይሁድ መሪዎች የሙሴን ሕግ በጥንቃቄ ይጠብቁ የነበረ ቢሆንም መሲሑ ሲመጣ ግን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ዓላማ ጋር እኩል እየተጓዙ አልነበረም።
c በዛሬው ጊዜ አምላክ የሚያነጋግረን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል። በመሆኑም በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማመልከትም ሊሠራበት ይችላል።
ዓላማው ገብቶሃል?
• በዛሬው ጊዜ ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት ምን ያስፈልገናል?
• ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ የሚሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ከመሆን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
• በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ ሲሰጠን መታዘዝ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው? መታዘዛችን በጣም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
• በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ልንረዳው እንችላለን?
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቹ በጥልቅ ሐዘን ይዋጣሉ!