የጥናት ርዕስ 24
ከሰይጣን ወጥመዶች ማምለጥ ትችላላችሁ!
“[ከዲያብሎስ] ወጥመድ ሊወጡ ይችላሉ።”—2 ጢሞ. 2:26
መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ
ማስተዋወቂያa
1. ሰይጣን ከአዳኝ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
የአዳኞች ዓላማ የሚፈልጉትን እንስሳ መያዝ ወይም መግደል ነው። አንድ አዳኝ የሚፈልገውን እንስሳ ለመያዝ የተለያዩ ወጥመዶችን ሊጠቀም ይችላል፤ ከኢዮብ የውሸት አጽናኞች መካከል አንዱም ይህን ገልጿል። (ኢዮብ 18:8-10) ታዲያ አዳኙ፣ እንስሳው ወደ ወጥመዱ እንዲገባለት የሚያደርገው እንዴት ነው? እንስሳውን በደንብ ያጠናዋል። እንስሳው ብዙ ጊዜ የሚገኘው የት ነው? የሚወደው ነገር ምንድን ነው? ሳያስበው ማጥመድ የሚቻለው እንዴት ነው? ሰይጣንም የሚያደርገው ነገር ከአዳኙ ጋር ይመሳሰላል። በደንብ ያጠናናል። ጊዜ የምናሳልፈው የት እንደሆነ እንዲሁም ምን እንደምንወድ ይከታተላል። ከዚያም ሳናስበው ሊይዘን የሚችል ወጥመድ ይዘረጋል። ሆኖም በሰይጣን ወጥመድ ብንያዝም እንኳ ከወጥመዱ መውጣት እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። እንዲሁም ቀድሞውንም በወጥመዶቹ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንደምንችል ያስተምረናል።
2. በጣም ውጤታማ ከሆኑት የሰይጣን ወጥመዶች መካከል ሁለቱ የትኞቹ ናቸው?
2 በጣም ውጤታማ ከሆኑት የሰይጣን ወጥመዶች መካከል ሁለቱ ኩራት እና ስግብግብነት ናቸው።b ሰይጣን እነዚህን መጥፎ ባሕርያት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፤ ደግሞም ተሳክቶለታል። ሰይጣን፣ ወጥመድ ወይም መረብ ተጠቅሞ እንደሚያጠምድ ወፍ አዳኝ ነው። (መዝ. 91:3) ሆኖም ከሰይጣን ወጥመዶች ማምለጥ አንችልም ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ይሖዋ ስላሳወቀን ነው።—2 ቆሮ. 2:11
3. ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን ያስጻፈልን ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ ከኩራት እና ከስግብግብነት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል፤ እንዲህ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ከእውነተኛ ታሪኮች እንድንማር በመርዳት ነው። ከዚህ ቀጥሎ በምናያቸው ምሳሌዎች ላይ ሰይጣን የጎለመሱ የይሖዋ አገልጋዮችንም ጭምር ማጥመድ እንደቻለ ልብ በል። ታዲያ ይህ ሲባል ከኩራት እና ከስግብግብነት ወጥመድ ማምለጥ አንችልም ማለት ነው? በፍጹም። ይሖዋ እነዚህን ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስጻፈልን “እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።” (1 ቆሮ. 10:11) አምላካችን ከማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ትምህርት በመውሰድ ከዲያብሎስ ወጥመዶች መራቅ ወይም መውጣት እንደምንችል ያውቃል።
ኩራት ወጥመድ ነው
4. ኩራት ምን ያስከትላል?
4 ሰይጣን ተገቢ ያልሆነ ኩራት እንዲያድርብን ይፈልጋል። ተገቢ ያልሆነ ኩራት እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን እንደ እሱ እንደምንሆንና የዘላለም ሕይወት እንደምናጣ ያውቃል። (ምሳሌ 16:18) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አንድ ሰው “በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ” ሊፈረድበት እንደሚችል ያስጠነቀቀው ለዚህ ነው። (1 ጢሞ. 3:6, 7) አዲሶችም ሆንን ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ስናገለግል የቆየን ክርስቲያኖች፣ ማናችንም ይህ ሁኔታ ሊደርስብን ይችላል።
5. በመክብብ 7:16, 20 ላይ እንደተገለጸው አንድ ሰው ኩራተኛ መሆኑ የሚታየው እንዴት ሊሆን ይችላል?
5 ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው። ሰይጣን በተለይ ችግሮች ሲያጋጥሙን ራስ ወዳዶች እንድንሆን ይኸውም በይሖዋ ላይ ሳይሆን በራሳችን ላይ እንድናተኩር ሊገፋፋን ይሞክራል። ለምሳሌ ያህል፣ የሐሰት ውንጀላ ተሰንዝሮብህ ያውቃል? ወይም ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብህ ያውቃል? ሰይጣን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ በይሖዋ ወይም በወንድሞችህ ላይ እንድትበሳጭ ይፈልጋል። እንዲሁም ችግሩን መፍታት የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሰጠህን መመሪያ መከተል ሳይሆን የራስህን እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ሊያሳምንህ ይሞክራል።—መክብብ 7:16, 20ን አንብብ።
6. በኔዘርላንድስ ከምትኖረው እህት ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
6 በኔዘርላንድስ የምትኖርን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች እህት አንዳንድ ሰዎች በሚፈጽሟቸው ስህተቶች ምክንያት በጣም ትበሳጭ ነበር። እነዚህን ሰዎች ጨርሶ ልትታገሣቸው እንደማትችል ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ማንም ከእኔ ጎን እንዳልሆነ ተሰማኝ፤ ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያለኝን አመለካከት መቀየር አልቻልኩም። ስለዚህ ጉባኤ መቀየር እንደምፈልግ ለባለቤቴ ነገርኩት።” ከዚያ ግን የመጋቢት 2016ን JW ብሮድካስቲንግ ተመለከተች። ቪዲዮው የሌሎች ድክመት ሲያስከፋን ምን ማድረግ እንደምንችል ይናገራል። እህታችን እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ለመቀየር ከመሞከር ይልቅ በሐቀኝነትና በትሕትና ስለ ራሴ ስህተቶች ማሰብ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ቪዲዮው በይሖዋ እና በሉዓላዊነቱ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።” ነጥቡ ምንድን ነው? ፈተና ሲያጋጥምህ በይሖዋ ላይ ትኩረት አድርግ። ሌሎችን በእሱ ዓይን ለመመልከት እንዲረዳህ ለምነው። የሰማዩ አባታችን የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ስህተቶች ያያል፤ ሆኖም ይቅር ሊላቸው ፈቃደኛ ነው። አንተም ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ይፈልጋል።—1 ዮሐ. 4:20
7. ንጉሥ ዖዝያ ምን አጋጥሞታል?
7 የይሁዳ ንጉሥ የሆነው ዖዝያ ኩራተኛ መሆኑ የተሰጠውን ምክር እንዳይቀበልና የማይገባውን ድርጊት እንዲፈጽም አድርጎታል። ዖዝያ ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። በወታደራዊ ዘመቻዎች፣ በግንባታ ፕሮጀክቶችና በግብርና ረገድ ብዙ ስኬት ያስመዘገበ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “እውነተኛው አምላክ አበለጸገው” ይላል። (2 ዜና 26:3-7, 10) “ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ።” ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን ማጠን የሚፈቀድላቸው ካህናቱ ብቻ እንደሆኑ ተናግሮ ነበር። ንጉሥ ዖዝያ ግን በእብሪት ስለተሞላ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። ይሖዋ በዚህ በጣም ስላዘነ ይህን ኩራተኛ ሰው በሥጋ ደዌ መታው። ዖዝያ ቀሪ ዕድሜውን በሙሉ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።—2 ዜና 26:16-21
8. በ1 ቆሮንቶስ 4:6, 7 መሠረት ከኩራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
8 እኛስ እንደ ዖዝያ በኩራት ወጥመድ እንያዝ ይሆን? የሆሴን ምሳሌ እንመልከት። ሆሴ በሰብዓዊ ሥራው በጣም የተዋጣለት ሰው ከመሆኑም ሌላ የብዙዎችን አክብሮት ያተረፈ የጉባኤ ሽማግሌ ነበር። በወረዳ እና በክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግር ያቀርብ ነበር፤ እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ምክር ይጠይቁት ነበር። “ሆኖም በራሴ ችሎታና በተሞክሮዬ መተማመን ጀመርኩ” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። “በይሖዋ መታመን አቆምኩ። በመንፈሳዊ ጠንካራ እንደሆንኩ ይሰማኝ ስለነበር የይሖዋን ማስጠንቀቂያዎችና ምክሮች አልተቀበልኩም።” ሆሴ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ከጉባኤ ተወገደ። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሆሴ ወደ ጉባኤ ተመልሷል። ሆሴ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ፣ ዋናው ነገር ያለን መብት ሳይሆን እሱ የሚጠይቀንን ነገር ማድረጋችን እንደሆነ አስተምሮኛል።” ያሉን ተሰጥኦዎችና በጉባኤ ውስጥ የምንቀበላቸው መብቶች በሙሉ ከይሖዋ የተገኙ መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ቆሮንቶስ 4:6, 7ን አንብብ።) ኩራተኛ ከሆንን ይሖዋ አይጠቀምብንም።
ስግብግብነት ወጥመድ ነው
9. ሰይጣንና ሔዋን ስግብግቦች መሆናቸው ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?
9 ስለ ስግብግብነት ስናስብ በመጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ሰይጣን ዲያብሎስ ሳይሆን አይቀርም። ሰይጣን የይሖዋ መልአክ የነበረ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ግሩም መብቶች እንደነበሩት ጥያቄ የለውም። እሱ ግን በዚህ አልረካም። ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ተመኘ። ሰይጣን እኛም እንደ እሱ እንድንሆን ስለሚፈልግ ባለን ነገር እንዳንረካ ለማድረግ ይሞክራል። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረግ የጀመረው ሔዋንን ባነጋገረበት ወቅት ነው። አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ለሔዋንና ለባለቤቷ የተትረፈረፈ ምግብ ሰጥቷቸው ነበር፤ ከአንዱ ዛፍ በቀር “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ” እስኪረኩ ድረስ መብላት ይችሉ ነበር። (ዘፍ. 2:16) ሆኖም ሰይጣን፣ ሔዋንን በማታለል ከተከለከለው ዛፍ መብላት እንደሚያስፈልጋት እንድታስብ አደረጋት። ሔዋን በተሰጣት ነገር አልረካችም፤ ተጨማሪ ነገር ፈለገች። ይህም ምን ውጤት እንዳስከተለ እናውቃለን። ሔዋን ኃጢአት ሠራች፤ ከጊዜ በኋላም ሞተች።—ዘፍ. 3:6, 19
10. ንጉሥ ዳዊት በስግብግብነት ወጥመድ የወደቀው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ ለንጉሥ ዳዊት ብዙ ነገሮች ሰጥቶት ነበር፤ ሀብት፣ ንግሥና እንዲሁም በጠላቶቹ ላይ ድል ሰጥቶታል። ዳዊትም የአምላክን ስጦታዎች ‘ዘርዝሮ ሊጨርሳቸው እንደማይችል’ በአመስጋኝነት ተናግሮ ነበር። (መዝ. 40:5) በአንድ ወቅት ግን ዳዊት ስግብግብነት ስላደረበት ይሖዋ ከሰጠው ተጨማሪ ነገር ፈለገ። ዳዊት ብዙ ሚስቶች የነበሩት ቢሆንም የሌላ ሰው ሚስት ተመኘ። ዳዊት የተመኘው የሂታዊው የኦርዮ ሚስት የሆነችውን ቤርሳቤህን ነው። ዳዊት በራስ ወዳድነት ስለተሸነፈ ከቤርሳቤህ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ምንዝር መፈጸሙ ሳያንስ ኦርዮ እንዲገደል አደረገ። (2 ሳሙ. 11:2-15) ዳዊት እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋል? ይሖዋ የማያየው መስሎት ነው? በአንድ ወቅት ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳዊት ለራስ ወዳድነትና ለስግብግብነት እጅ በመስጠቱ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ደስ የሚለው ግን ዳዊት ከጊዜ በኋላ ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ገብቷል። የይሖዋን ሞገስ መልሶ በማግኘቱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—2 ሳሙ. 12:7-13
11. በኤፌሶን 5:3, 4 መሠረት ስግብግብነትን ለመዋጋት የሚረዳን ምንድን ነው?
11 ከዳዊት ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች በሙሉ ምንጊዜም አመስጋኝ ከሆንን ስግብግብነትን መዋጋት እንደምንችል እንማራለን። (ኤፌሶን 5:3, 4ን አንብብ።) ባለን ነገር መርካት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸውን ሰዎች ይሖዋ ስለሰጣቸው አንድ በረከት እንዲያስቡና ለዚህም ይሖዋን እንዲያመሰግኑት እናበረታታቸው ይሆናል። አንድ ሰው በየቀኑ እንዲህ ካደረገ በሳምንት ውስጥ ስለ ሰባት የተለያዩ ጉዳዮች ይሖዋን አመስግኗል ማለት ነው። (1 ተሰ. 5:18) አንተስ እንደዚህ ታደርጋለህ? ይሖዋ ያደረገልህን ነገሮች ሁሉ እያሰብክ ማሰላሰልህ አመስጋኝ እንድትሆን ይረዳሃል። አመስጋኝ መሆንህ ደግሞ ባለህ ነገር ለመርካት ይረዳሃል። ባለህ ነገር የምትረካ ከሆነ ከስግብግብነት ወጥመድ ማምለጥ ትችላለህ።
12. የአስቆሮቱ ይሁዳ ስግብግብ መሆኑ ወደ ምን መርቶታል?
12 የአስቆሮቱ ይሁዳ ስግብግብ መሆኑ አስከፊ ክህደት እንዲፈጽም አድርጎታል። ሆኖም ይሁዳ ከመነሻው መጥፎ ሰው አልነበረም። (ሉቃስ 6:13, 16) ኢየሱስ ሐዋርያ አድርጎ መርጦት ነበር። የገንዘብ ሣጥኑን እንዲይዝ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑ ጥሩ ችሎታ ያለውና እምነት የሚጣልበት ሰው እንደነበረ ይጠቁማል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያንን ገንዘብ የሚጠቀሙበት በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን ነበር። ይህ ገንዘብ በአሁኑ ወቅት ለዓለም አቀፉ ሥራ ከሚደረገው መዋጮ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሁዳ፣ ኢየሱስ ስለ ስግብግብነት በተደጋጋሚ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ የሰማ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ መስረቅ ጀመረ። (ማር. 7:22, 23፤ ሉቃስ 11:39፤ 12:15) ይሁዳ የኢየሱስን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ብሏቸዋል።
13. የይሁዳ ስግብግብነት በግልጽ መታየት የጀመረው መቼ ነው?
13 ኢየሱስ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት የተፈጸመ አንድ ክንውን የይሁዳ ስግብግብነት በግልጽ እንዲታይ አድርጓል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ማርያምና እህቷ ማርታ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን ቤት ተጋብዘው ነበር። እየተመገቡ ሳሉ ማርያም ተነሳችና በኢየሱስ ራስ ላይ እጅግ ውድ የሆነ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ማፍሰስ ጀመረች። ይሁዳና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በዚህ በጣም ተበሳጩ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እንዲህ የተሰማቸው ገንዘቡን በአገልግሎት ላይ ቢጠቀሙበት እንደሚሻል ስላሰቡ ሊሆን ይችላል። ይሁዳን ያበሳጨው ነገር ግን ሌላ ነበር። ይሁዳ “ሌባ ስለነበረ” ከሣጥኑ ገንዘብ ለመስረቅ ፈልጎ ነበር። ውሎ አድሮ የይሁዳ ስግብግብነት ኢየሱስን በባሪያ ዋጋ አሳልፎ እንዲሰጠው አነሳስቶታል።—ዮሐ. 12:2-6፤ ማቴ. 26:6-16፤ ሉቃስ 22:3-6
14. አንድ ባልና ሚስት በሉቃስ 16:13 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ ያዋሉት እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ለተከታዮቹ አንድ መሠረታዊ እውነታ ነግሯቸዋል፤ “ለአምላክም ለሀብትም በአንድ ጊዜ ባሪያ መሆን አትችሉም” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 16:13ን አንብብ።) ይህ ሐሳብ አሁንም እውነት ነው። በሩማንያ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት የኢየሱስን ምክር የተከተሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት ሀብታም በሆነ አገር ውስጥ ጊዜያዊ ሥራ አግኝተው ነበር። “ብዙ የባንክ ዕዳ ስለነበረብን መጀመሪያ ላይ ይህ ሥራ ከይሖዋ የመጣ በረከት እንደሆነ ተሰምቶን ነበር” በማለት በሐቀኝነት ተናግረዋል። ሆኖም አንድ ችግር ነበር። ሥራው ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ይነካባቸዋል። በነሐሴ 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት” የሚለውን ርዕስ ካነበቡ በኋላ ውሳኔ አደረጉ። እንዲህ ብለዋል፦ “ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ስንል ወደ ሌላ አገር ብንሄድና በዚህ ምክንያት ይሖዋን ማገልገል አስቸጋሪ ቢሆንብን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሁለተኛ ቦታ ላይ እንዳስቀመጥነው ይቆጠራል። እዚያ ብንሄድ መንፈሳዊነታችን እንደሚጎዳ እርግጠኞች ነበርን።” በመሆኑም ሥራውን ላለመቀበል ወሰኑ። ከዚያስ ምን ተፈጠረ? ባልየው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የሚያስችለው ሥራ እዚያው አገሩ ውስጥ አገኘ። ሚስትየዋ “የይሖዋ እጅ ፈጽሞ አጭር አይደለም” ብላለች። እነዚህ ባልና ሚስት ከገንዘብ ይልቅ የይሖዋ ባሪያ ለመሆን በመምረጣቸው በጣም ደስተኞች ናቸው።
የሰይጣን ወጥመዶች እንዳይዟችሁ ተጠንቀቁ
15. ከሰይጣን ወጥመዶች መውጣት እንደሚቻል እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
15 በኩራት ወይም በስግብግብነት ወጥመድ እንደተያዝን ብንገነዘብስ? ከእነዚህ ወጥመዶች መውጣት እንችላለን! ጳውሎስ፣ ዲያብሎስ በሕይወት እንዳሉ አጥምዶ የያዛቸው ሰዎች “ከእሱ ወጥመድ ሊወጡ” እንደሚችሉ ገልጿል። (2 ጢሞ. 2:26) ለምሳሌ ዳዊት፣ ናታን የሰጠውን ጠንከር ያለ ተግሣጽ በመቀበል ንስሐ ገብቶና ስግብግብነቱን አስወግዶ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ወዳጅነት አድሷል። ይሖዋ ከሰይጣን ይበልጥ ኃያል እንደሆነ ፈጽሞ አትርሱ። በመሆኑም የይሖዋን እርዳታ ከተቀበልን ዲያብሎስ ከዘረጋው ከየትኛውም ወጥመድ ማምለጥ እንችላለን።
16. በሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ ምን ይረዳናል?
16 እርግጥ ነው፣ ከሰይጣን ወጥመዶች ለመውጣት ከመሞከር ይልቅ መጀመሪያውኑ በወጥመዱ አለመያዝ የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችለው በአምላክ እርዳታ ብቻ ነው። እርግጥ እኛም መዘናጋት የለብንም! ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ሲያገለግሉ የኖሩ ሰዎችም እንኳ በኩራት ወይም በስግብግብነት ወጥመድ ወድቀዋል። በመሆኑም እነዚህ መጥፎ ባሕርያት በአስተሳሰብህና በድርጊትህ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምረው ከሆነ ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን በየዕለቱ ለምነው። (መዝ. 139:23, 24) እነዚህ ወጥመዶች እንዲይዙህ ፈጽሞ አትፍቀድ!
17. ጠላታችን ዲያብሎስ በቅርቡ ምን ይደርስበታል?
17 ሰይጣን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት አዳኝ ሆኖ ኖሯል። በቅርቡ ግን ይታሰራል፤ በኋላም ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል። (ራእይ 20:1-3, 10) ያንን ቀን በጉጉት እንጠብቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን በሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ ንቁዎች እንሁን። ኩራት ወይም ስግብግብነት እንዳይጠናወተን ከፍተኛ ጥረት እናድርግ። ‘ዲያብሎስን ለመቃወም’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲህ ካደረግን ‘እሱም ከእኛ ይሸሻል!’—ያዕ. 4:7
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
a ሰይጣን የተዋጣለት አዳኝ ነው። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን እኛን ለማጥመድ ከመሞከር ወደኋላ አይልም። ሰይጣን ኩራትን እና ስግብግብነትን ተጠቅሞ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን የሚሞክረው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ በኩራት እና በስግብግብነት ወጥመድ ከወደቁ ሰዎች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንዲሁም ከእነዚህ ወጥመዶች ማምለጥ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ይህ ርዕስ የሚያተኩረው ተገቢ ባልሆነ ኩራት እና በስግብግብነት ላይ ነው። ተገቢ ያልሆነ ኩራት ያለው ሰው ራሱን ከሌሎች እንደሚሻል አድርጎ ይቆጥራል። ስግብግብ የሆነ ሰው ደግሞ ከገንዘብ፣ ከሥልጣን፣ ከፆታ ግንኙነት ወይም ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ የማይረካ ምኞት አለው።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ በኩራት ወጥመድ የወደቀ አንድ ወንድም የተሰጠውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር አልቀበልም ሲል። ብዙ ነገሮች ያሏት አንዲት እህት ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ስትመኝ።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ መልአክ እና ንጉሥ ዖዝያ በኩራት ወጥመድ ወድቀዋል። ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ የበላችው፣ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር የፈጸመው እንዲሁም ይሁዳ ገንዘብ የሰረቀው በስግብግብነት ምክንያት ነው።