የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?
ተፈታታኙ ነገር፦ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎች
ሥር የሰደደ በሽታ ይዞህ ወይም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተፋትተህ አሊያም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ያለህበት ሁኔታ እንዲለወጥ ከመመኘት በቀር ምንም ማድረግ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ሕይወትህን በተቻለ መጠን አንተ በምትፈልገው መንገድ መምራት የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ጳውሎስ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቀናተኛ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዞ ነበር። ይሁን እንጂ ፍትሕ በጎደለው መንገድ ታሰረ፤ ከዚያም ለሁለት ዓመት ያህል አንድ ቤት ውስጥ በወታደር እየተጠበቀ እንዲኖር በመደረጉ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም። ጳውሎስ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከመዋጥ ይልቅ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርጓል። ሊጠይቁት ለመጡት ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ እርዳታና መጽናኛ ይሰጥ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን በርካታ ደብዳቤዎች የጻፈውም በዚያ እያለ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 28:30, 31
አንያ ያደረገችው ነገር
ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንያ ከቤት መውጣት አትችልም። “ካንሰር እንዳለብኝ ማወቄ መላ ሕይወቴን ቀይሮታል። ለተላላፊ በሽታ እንዳልጋለጥ ስለምፈራ ሰብዓዊ ሥራ የማልሠራ ከመሆኑም ሌላ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተገድቧል” ብላለች። ታዲያ አንያ ሊለወጡ የማይችሉ ሁኔታዎችን መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ በማደርጋቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ ማድረጌ በጣም ረድቶኛል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከለየሁ በኋላ አቅሜን ያገናዘበ ፕሮግራም አወጣለሁ። ይህም ሕይወቴን መቆጣጠር እንደቻልኩ እንዲሰማኝ አድርጓል።”
“በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ።”—በፊልጵስዩስ 4:11 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ
ምን ማድረግ ትችላለህ?
በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህን ሁኔታዎች ልትለውጣቸው እንደማትችል ከተሰማህ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር፦
ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። ለምሳሌ ያህል፣ የጤንነትህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአንተ ላይ ባይሆንም አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን በመመገብና በቂ እንቅልፍ በመተኛት ጤንነትህን ተንከባከብ።
በሕይወትህ ውስጥ ምን ማከናወን እንደምትፈልግ በግልጽ አስቀምጥ። ደረጃ በደረጃ ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን መንገዶች ፈልግ። ከዚያም በየቀኑ የተወሰነ ጊዜ መድበህ ወደ ግብህ ለመድረስ የሚረዳህን ነገር አከናውን።
ትናንሽ ቢሆኑም እንኳ ሕይወትህን መቆጣጠር እንደቻልክ እንዲሰማህ የሚያደርጉ ነገሮችን ለማከናወን ሞክር። የመመገቢያ ጠረጴዛ ማጽዳት ወይም ዕቃዎችን ማጠብ ትችላለህ። እንዲሁም ጥሩ አለባበስ ይኑርህ። ጠዋት ላይ ሥራህን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በማከናወን ጀምር።
ያለህበት ሁኔታ ያስገኘልህን ጥቅሞች ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመህ ሁኔታ ችግሮችን መቋቋም የሚቻልባቸውን መንገዶች ይበልጥ እንድትገነዘብ ረድቶሃል? ታዲያ በዚህ ተጠቅመህ ሌሎችን መርዳት ትችል ይሆን?
ዋናው ነጥብ፦ የሚያጋጥሙህን ሁኔታዎች መቆጣጠር ባትችልም ሁኔታዎቹን የምታስተናግድበት መንገድ ግን በአንተ ቁጥጥር ሥር ነው።