ሞትን እፈራ ነበር—አሁን ግን ‘ሕይወት እንደሚትረፈረፍልኝ’ ተስፋ አለኝ
ፕዬሮ ጋቲ እንደተናገሩት
ዝግ ብሎ ይሰማ የነበረው ድምፅ ቀስ በቀስ እየጨመረ መጣ። ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ወደ መጠለያ እንዲገቡ የሚያስጠነቅቅ የአደጋ ጊዜ ደወል ተሰማ። ከዚያም አካባቢው በቦምብ የተደበደበ ሲሆን ጆሮ የሚያደነቁር ኃይለኛ ፍንዳታ ተሰማ።
ይህ ሁኔታ የተከሰተው በሚላን፣ ጣሊያን ሲሆን ጊዜው 1943/1944 ነበር። በወቅቱ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የነበርኩ ወታደር ስሆን በቦምብ ድብደባው የተነሳ ማንነታቸውን መለየት እስከሚያቅት ድረስ አካላቸው የተቆራረጠ ሰዎችን አስከሬን እንድሰበስብ ብዙ ጊዜ መመሪያ ይሰጠኝ ነበር። የሞቱ ሰዎችን በቅርብ ከመመልከቴም ባሻገር አንዳንድ ጊዜ እኔው ራሴ ከሞት የማመልጠው ለጥቂት ነበር። በዚያ ወቅት አምላክ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ካተረፈኝ ፈቃዱን እንደማደርግ ቃል ገባሁ።
የሞት ፍርሃትን ማስወገድ
ያደግሁት በስዊስ ድንበር አቅራቢያ ካለች ኮሞ የተባለች የጣሊያን ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ነው። ገና በልጅነቴ ከባድ ሐዘን የደረሰብኝ ከመሆኑም ሌላ ሞትን መፍራት ጀመርኩ። በኅዳር በሽታ ምክንያት ሁለቱን እህቶቼን አጥቼ ነበር። ከዚያም በ1930 ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለሁ እናቴ ሉዊጃ ሞተች። ያደግሁት በካቶሊክ እምነት ውስጥ ሲሆን ሃይማኖታዊ መመሪያዎችን እጠብቅና በየሳምንቱ እቆርብ ነበር። ይሁንና የሞት ፍርሃቴን ለማስወገድ የሚያስችል እርዳታ ያገኘሁት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳይሆን ከዓመታት በኋላ በአንድ የወንዶች ፀጉር ቤት ውስጥ ነው።
በ1944 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ብዙ ሰዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል። የጦርነት ቀጠና ከነበረችው ከጣሊያን፣ ገለልተኛ ወደሆነችው ወደ ስዊዘርላንድ ከሸሹ በአሥር ሺዎች ከሚቆጠሩ የጣሊያን ወታደሮች መካከል አንዱ ነበርኩ። እዚያ እንደደረስን ወደተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ተወሰድን። እኔም በሰሜናዊ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘው በሽታይናክ አቅራቢያ ወዳለ አንድ የመጠለያ ካምፕ ተላክሁ። በዚህ ቦታ የተወሰነ ነፃነት ይሰጠን ነበር። በሽታይናክ ያለ አንድ ፀጉር አስተካካይ፣ በፀጉር ቤቱ ውስጥ የሚያግዘው ጊዜያዊ ሠራተኛ ይፈልግ ነበር። ከፀጉር አስተካካዩ ጋር እየሠራሁ የኖርኩት ለአንድ ወር ብቻ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ያወቅሁት ሰው የነገረኝ ነገር ግን ሕይወቴን ለውጦታል።
ከፀጉር ቤቱ ደንበኞች መካከል አንዱ በስዊዘርላንድ የሚኖር አዶልፎ ቴሊኒ የተባለ ጣሊያናዊ ነበር። ይህ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ነው። ስለ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት ሰምቼ አላውቅም፤ በእርግጥ በወቅቱ በመላው ጣሊያን የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ከ150 ብዙም የማይበልጡ ከመሆናቸው አንጻር ይህ አያስገርምም። አዶልፎ ወደፊት ሰላምና ‘የተትረፈረፈ ሕይወት’ እንደሚኖር የሚናገረውን ተስፋ ጨምሮ ግሩም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ነገረኝ። (ዮሐ. 10:10፤ ራእይ 21:3, 4) ወደፊት ጦርነትና ሞት የሌለበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገረውን መልእክት ስሰማ በጣም ተደስቼ ነበር። ወደ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ስመለስ ጁዜፔ ቱቢኒ ለተባለ ጣሊያናዊ ወጣት ይህን ተስፋ ነገርኩት፤ እሱም ልክ እንደ እኔው በጣም ተደሰተ። አዶልፎና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች በየጊዜው ወደ ካምፑ እየመጡ ይጠይቁን ነበር።
አዶልፎ፣ ከሽታይናክ 10 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አርቦ ወደተባለ ከተማ ወሰደኝ፤ በዚያም ጥቂት ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በጣሊያንኛ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። የሰማሁት ነገር በጣም ስለማረከኝ በቀጣዩ ሳምንትም በእግሬ ወደ አርቦ ሄድኩ። ከጊዜ በኋላ በዙሪክ የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በጅምላ ጭፍጨፋው ያለቁ የበርካታ ሰዎች አስከሬን ተቆልሎ የሚያሳይ የስላይድ ፊልም ስመለከት በጣም አዘንኩ። በጀርመን ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ለእምነታቸው ሲሉ ሰማዕት እንደሆኑ ከፊልሙ መገንዘብ ቻልኩ። በስብሰባው ላይ ማሪያ ፒትሳቶ ከተባለች እህት ጋር ተዋወቅሁ። ማሪያ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በመካፈሏ የጣሊያን ፋሽስት ባለሥልጣናት የ11 ዓመት እስር ፈርደውባት ነበር።
ጦርነቱ ሲያበቃ ወደ ጣሊያን ተመልሼ በኮሞ ከሚገኘው ትንሽ ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ባላጠናም መሠረታዊ እውነቶችን በደንብ ተረድቼ ነበር። ማሪያ ፒትሳቶም የዚህ ጉባኤ አባል ነበረች። ማሪያ የመጠመቅን አስፈላጊነት የነገረችኝ ከመሆኑም በላይ በሶንድሪዮ ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው ካስትዮኔ አንዴቬኖ የተባለች ከተማ ሄጄ ማርቼሎ ማርቲኔሊን እንዳነጋግር ሐሳብ አቀረበችልኝ። ማርቼሎ ታማኝ የሆነ ቅቡዕ ወንድም ሲሆን በአምባገነናዊው አገዛዝ ሥር የ11 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር። እሱ ጋ ለመሄድ በብስክሌት 80 ኪሎ ሜትር መጓዝ ነበረብኝ።
ማርቼሎ ለመጠመቅ የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካብራራልኝ በኋላ አብረን ጸለይን፤ ከዚያም ወደ አዳ ወንዝ ሄደን ተጠመቅኩ። ይህ የሆነው መስከረም 1946 ነበር። ይህ ለእኔ ልዩ ቀን ነበር! ይሖዋን ለማገልገል በመወሰኔና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጠንካራ ተስፋ በማግኘቴ በጣም ስለተደሰትኩ በዚያን ቀን 160 ኪሎ ሜትር በብስክሌት እንደተጓዝኩ አልታወቀኝም ነበር!
ከጦርነቱ በኋላ በጣሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ስብሰባ የተደረገው ግንቦት 1947 ሲሆን ስብሰባው የተከናወነው በሚላን ነበር። በፋሽስት አገዛዝ ሥር ስደት የደረሰባቸውን በርካታ ሰዎች ጨምሮ 700 የሚያህሉ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከናወነ። በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የመሠከርኩለት ጁዜፔ ቱቢኒ፣ የጥምቀት ንግግሩን ካቀረበ በኋላ እሱ ራሱ በዚህ ስብሰባ ላይ ተጠመቀ።
በዚህ ስብሰባ ላይ ከብሩክሊን ቤቴል ከመጣው ከወንድም ናታን ኖር ጋር የመተዋወቅ መብት አግኝቼ ነበር። ወንድም ናታን፣ እኔና ጁዜፔ ሕይወታችንን አምላክን ለማገልገል እንድንጠቀምበት አበረታታን። እኔም በአንድ ወር ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ። ቤት እንደደረስኩ ያደረግኩትን ውሳኔ ለቤተሰቤ ነገርኳቸው። ሁሉም ሐሳቤን ለማስለወጥ የሞከሩ ቢሆንም በውሳኔዬ መጽናት ችዬ ነበር። በመሆኑም ከወር በኋላ ሚላን በሚገኘው ቤቴል ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ። በወቅቱ የቤቴል ቤተሰብ አባላት አራት ሚስዮናውያን ሲሆኑ እነሱም ጁዜፔ (ጆሴፍ) ሮማኖ እና ባለቤቱ አንጀሊና እንዲሁም ካርሎ ቤናንቲ እና ባለቤቱ ኮስታንሳ ነበሩ። አምስተኛው የቤቴል ቤተሰብ አባል በቅርቡ የገባው ጁዜፔ ቱቢኒ ሲሆን እኔም ስድስተኛ የቤተሰቡ አባል ሆንኩ።
ቤቴል ከገባሁ ከአንድ ወር በኋላ የመጀመሪያው ጣሊያናዊ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። በ1946 የመጀመሪያው ሚስዮናዊ ሆኖ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ጣሊያን የመጣው ጆርጅ ፍሬድያኔሊ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል ነበር። ለጥቂት ሳምንታት ካሠለጠነኝ በኋላ ይህን ሥራ ለብቻዬ ማከናወን ጀመርኩ። መጀመሪያ የጎበኘሁትን የፋኤንዛ ጉባኤን አልረሳውም። እስቲ አስቡት! ከዚያ በፊት በጉባኤ ውስጥ እንኳ ንግግር ሰጥቼ አላውቅም! እንደዚያም ሆኖ በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሰዎች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ አበረታታኋቸው። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ በጣሊያን ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ተቀብለው ይሠሩ ነበር።
አስደሳች በሆነው የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ስካፈል በሕይወቴ ውስጥ አስገራሚ ሁኔታዎችን የተመለከትሁ ሲሆን ማስተካከያ ማድረግም አስፈልጎኝ ነበር። ተፈታታኝም ሆነ አስደሳች በሆኑ ሁኔታዎች ሥር አልፌያለሁ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑት ወንድሞችና እህቶች ጥልቅ ፍቅር አሳይተውኛል።
ከጦርነቱ በኋላ በጣሊያን የነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ
በዚያን ጊዜ በጣሊያን ስለነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ እስቲ ላውጋችሁ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራት። በ1948 አዲስ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም እስከ 1956 ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት እንዳይሰብኩ የሚያግደው የፋሽስት ሕግ በይፋ አልተሻረም ነበር። ቀሳውስቱ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ የተነሳ ብዙ ጊዜ የወረዳ ስብሰባዎች ይስተጓጎሉ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ቀሳውስቱ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ፍሬ ቢስ ይሆኑ ነበር፤ በ1948 በማዕከላዊ ጣሊያን በምትገኘው ሱልሞና የተባለች ትንሽ ከተማ የተከናወነውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።
በዚያ ወቅት በቲያትር ቤት ውስጥ አንድ ትልቅ ስብሰባ እየተከናወነ ነበር። እሁድ ጠዋት፣ ጁዜፔ ሮማኖ የሕዝብ ንግግር እየሰጠ ነበር፤ የስብሰባው ሊቀ መንበርም እኔ ነበርኩ። በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንጻር በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች ብዙ ነበሩ። በመላው አገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች 500 የማይሞሉ ቢሆንም 2,000 የሚያህሉ ሰዎች ቲያትር ቤቱን ሞልተውት ነበር። በንግግሩ መገባደጃ ላይ አንድ ወጣት በተሰብሳቢዎች መካከል በነበሩት ሁለት ቄሶች ገፋፊነት መድረኩ ላይ ዘሎ ወጣ። ይህ ወጣት ግርግር ለመፍጠር አስቦ ድምፁን ከፍ አድርጎ መጮህ ጀመረ። ወዲያውኑ እንዲህ አልሁት፦ “የምትናገረው ነገር ካለህ መጀመሪያ አዳራሽ ተከራይ፤ ከዚያም የፈለግኸውን መናገር ትችላለህ።” ተሰብሳቢዎቹ ያሰሙት የተቃውሞ ጩኸት የወጣቱን ንግግር ዋጠው። በዚህ ጊዜ ይህ ወጣት ከመድረኩ ወርዶ ከአካባቢው ተሰወረ።
በዚያን ጊዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ የምጓዘው በእግሬ፣ በብስክሌት ወይም ባረጁና በተጨናነቁ አውቶቡሶች አሊያም በባቡር ነበር። በፈረስ ጋጣ ወይም በመጋዘን ውስጥ ያደርኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ጦርነቱ ካበቃ ብዙም ስላልቆየ አብዛኞቹ ጣሊያኖች ድሆች ነበሩ። በወቅቱ የወንድሞች ቁጥር ጥቂት ከመሆኑም ሌላ ኑሯቸው ዝቅተኛ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋን ማገልገል አስደሳች ነበር።
በጊልያድ ያገኘሁት ሥልጠና
በ1950 እኔና ጁዜፔ ቱቢኒ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ16ኛው ክፍል እንድንሠለጥን ተጋበዝን። ገና ከጅምሩ እንግሊዝኛ መማር አስቸጋሪ ሊሆንብኝ እንደሚችል ተሰምቶኝ ነበር። የምችለውን ሁሉ ጥረት ባደርግም ቋንቋውን መልመድ በጣም ከብዶኝ ነበር። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ ማንበብ ነበረብን። ይህን ለማድረግ ስል አንዳንድ ጊዜ ምሳዬን በመተው ድምፄን ከፍ አድርጌ ማንበብ እለማመድ ነበር። በመጨረሻም ንግግር የምሰጥበት ተራ ደረሰ። አስተማሪው ያለኝን ነገር ትላንት የተናገረኝ ያህል በደንብ አስታውሰዋለሁ፤ “አካላዊ መግለጫህና ግለትህ ግሩም ነበር፤ እንግሊዝኛህን ግን ማንም ሊረዳው አይችልም!” ያም ቢሆን ሥልጠናውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ችያለሁ። እኔና ጁዜፔ ሥልጠናውን እንዳጠናቀቅን በድጋሚ በጣሊያን እንድናገለግል ተመደብን። ያገኘነው ተጨማሪ ሥልጠና ወንድሞቻችንን በተሻለ ሁኔታ እንድናገለግል አስችሎናል።
በ1955 ሊድያ ከተባለች እህት ጋር ተጋባን፤ ከሰባት ዓመት በፊት ሊድያ ስትጠመቅ የጥምቀት ንግግሩን የሰጠሁት እኔ ነበርሁ። አባቷ ዶሜኒኮ በፋሽስት አገዛዝ ወቅት ስደት የደረሰበት ከመሆኑም ሌላ ለሦስት ዓመታት በግዞት እንዲኖር ቢፈረድበትም ሰባት ልጆቹን በእውነት ቤት ውስጥ ለማሳደግ የተቻለውን ጥረት አድርጓል። ሊድያም ብትሆን ከእውነት ጎን ለመቆም ብዙ ታግላለች። ከቤት ወደ ቤት የመስበክ ሕጋዊ መብታችን በይፋ ከመታወቁ በፊት ሦስት ጊዜ ፍርድ ቤት ቆማለች። በትዳር ውስጥ ስድስት ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ቤንያሚኖ የተባለው የመጀመሪያ ልጃችን ተወለደ። በ1972 ደግሞ ማርኮ የተባለው ሁለተኛ ልጃችን ተወለደ። ሁለቱም ልጆቻችን ከነቤተሰቦቻቸው ይሖዋን በቅንዓት እያገለገሉ መሆኑን መመልከቴ በጣም ያስደስተኛል።
በይሖዋ አገልግሎት ቀናተኛ ሆኖ መቀጠል
ሌሎችን በማገልገል ባሳለፍኳቸው አስደሳች ዓመታት ያገኘኋቸው በርካታ የማይረሱ ትዝታዎች አሉኝ። ለምሳሌ ያህል፣ በ1980ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አማቴ በዚያን ጊዜ የጣሊያን ፕሬዚዳንት ለነበሩት ለሳንድሮ ፐርቲኒ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። ወንድም ዶሜኒኮና ሳንድሮ ፐርቲኒ በፋሽስት አገዛዝ ወቅት የመንግሥት ጠላቶች እንደሆኑ የሚታሰቡ ሰዎች ወደሚታሰሩበት ወደ ቬንቶቴኔ ደሴት በግዞት ተወስደው ነበር። ወንድም ዶሜኒኮ ለፕሬዚዳንቱ ለመመሥከር በማሰብ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመወያየት እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄው ተቀባይነት ሲያገኝ አብረን ሄድን፤ እዚያም ስንደርስ ከጠበቅነው በላይ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገልን። ፕሬዚዳንቱም ወንድም ዶሜኒኮን እቅፍ በማድረግ የሞቀ ሰላምታ ሰጡት። ከዚያም እምነታችንን በተመለከተ የተነጋገርን ሲሆን አንዳንድ ጽሑፎችንም ሰጠናቸው።
ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ በመላው ጣሊያን የሚገኙ ጉባኤዎችን ለ44 ዓመታት ከጎበኘሁ በኋላ በ1991 የወረዳ ሥራዬን አቆምኩ። በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ፤ ከዚያም ባጋጠመኝ ከባድ የጤና እክል ምክንያት ኃላፊነቴን ለመቀነስ ተገደድኩ። ያም ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ይሖዋ በጸጋው አማካኝነት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ መቀጠል እንድችል ስለረዳኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ምሥራቹን ለመስበክና ለማስተማር የተቻለኝን ጥረት እያደረግሁ ሲሆን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አሉኝ። አሁንም ድረስ ንግግር ሳቀርብ በከፍተኛ ግለት እንደምናገር ወንድሞች ይነግሩኛል። ዕድሜዬ እየገፋ ሲሄድ ግለቴ እየቀነሰ ባለመሄዱ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።
ልጅ እያለሁ ሞትን በጣም እፈራ ነበር፤ ሆኖም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘቴ ኢየሱስ ‘የተትረፈረፈ ሕይወት’ ብሎ የጠራውን የዘላለም ሕይወት እንደማገኝ እርግጠኛ እንድሆን አስችሎኛል። (ዮሐ. 10:10) ወደፊት ሰላም፣ ደኅንነትና ደስታ የሞላበት ሕይወትን ጨምሮ የተትረፈረፈ በረከት ከይሖዋ ለማግኘት እየተጠባበቅሁ ነው። ስሙን የመሸከም መብት የሰጠን አፍቃሪው ፈጣሪያችን ምስጋና ይድረሰው።—መዝ. 83:18 NW
[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ስዊዘርላንድ
በርን
ዙሪክ
አርቦ
ሽታይናክ
ጣሊያን
ሮም
ኮሞ
ሚላን
የአዳ ወንዝ
ካስትዮኔ አንዴቬኖ
ፋኤንዛ
ሱልሞና
ቬንቶቴኔ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ጊልያድ ስንሄድ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጁዜፔ ጋር በጊልያድ ሳለን
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሠርጋችን ዕለት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውዷ ባለቤቴ ከ55 ለሚበልጡ ዓመታት ከጎኔ ሆና ደግፋኛለች