ሀ5
መለኮታዊው ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ቴትራግራማተን (יהוה) ተብለው በሚታወቁት ፊደላት የሚወከለው የአምላክ የግል ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በኩረ ጽሑፍ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ እንደሚገኝ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ፣ የአምላክ ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኩረ ጽሑፍ ውስጥ እንደማይገኝ ይሰማቸዋል። በዚህም የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተተረጎሙ በርካታ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲተረጉሙ የአምላክን ስም አልተጠቀሙም። ሌላው ቀርቶ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን፣ ቴትራግራማተን የሚገኝባቸውን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ጥቅሶች ሲተረጉሙ በአምላክ የግል ስም ምትክ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም ተጠቅመዋል።
አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ዓይነቱን የተለመደ የአተረጓጎም ስልት አልተከተለም። ይህ ትርጉም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ የሚለውን ስም 237 ጊዜ ተጠቅሟል። ተርጓሚዎቹ ይህን ለማድረግ የወሰኑት በሚከተሉት ሁለት አበይት ምክንያቶች የተነሳ ነው፦ (1) አሁን በእጃችን ያሉት የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች አይደሉም። በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት በሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል ብዙዎቹ የተዘጋጁት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች ከተጻፉ ቢያንስ ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ነው። (2) በእነዚህ ጊዜያት ቅዱሳን መጻሕፍትን ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች ቴትራግራማተንን “ጌታ” የሚል ትርጉም ባለው ኪርዮስ በሚለው የግሪክኛ ቃል ተክተው አሊያም የአምላክን ስም በዚህ ቃል ከተኩት ቀደም ብለው ከተዘጋጁ ቅጂዎች ላይ ገልብጠው ሊሆን ይችላል።
የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ በመጀመሪያዎቹ የግሪክኛ ጽሑፎች ውስጥ ቴትራግራማተን እንደሚገኝ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ እንዳለ ያምናል። እንዲህ ያለው መደምደሚያ ላይ ሊደርስ የቻለው የሚከተሉትን ማስረጃዎች መሠረት አድርጎ ነው፦
በኢየሱስና በሐዋርያቱ ዘመን ይጠቀሙባቸው የነበሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች በብዙ ቦታዎች ላይ ቴትራግራማተን ይገኝባቸው ነበር። ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዳንዶች ይህን ሐሳብ ይቃወሙ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በኩምራን አቅራቢያ የተገኙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተዘጋጁ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ይህ የተቃውሞ ሐሳብ መሠረት የሌለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢየሱስና በሐዋርያቱ ዘመን ቴትራግራማተን በግሪክኛ በተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኝ ነበር። ምሁራን ለብዙ ዘመናት ቴትራግራማተን፣ ሰብዓ ሊቃናት በግሪክኛ ባዘጋጁት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ አይገኙም ብለው ያስቡ ነበር። ከዚያም በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ እጅግ ጥንታዊ የሆኑ የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁርጥራጮች መገኘታቸው የምሁራንን ትኩረት ሳበ። እነዚህ ቁርጥራጮች በዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈውን የአምላክን የግል ስም ይዘዋል። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን፣ መለኮታዊው ስም በግሪክኛ በተዘጋጁ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደተዘጋጁ በሚታሰቡት እንደ ኮዴክስ ቫቲካነስ እና ኮዴክስ ሳይናይቲከስ ባሉ የሰብዓ ሊቃናት የግሪክኛ ትርጉም ዋና ዋና ቅጂዎች ላይ ከዘፍጥረት እስከ ሚልክያስ ባሉት መጻሕፍት (ቀደም ባሉት ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ መለኮታዊው ስም በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ይገኝ ነበር) ውስጥ መለኮታዊው ስም አይገኝም። በመሆኑም ከዚያን ጊዜ ወዲህ በተዘጋጁትና እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው በቆዩት በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መለኮታዊው ስም አለመገኘቱ ምንም አያስገርምም።
ኢየሱስ “እኔ በአባቴ ስም መጣሁ” ሲል በግልጽ ተናግሯል። እንዲሁም ማንኛውንም ሥራ የሚያከናውነው ‘በአባቱ ስም’ እንደሆነ አበክሮ ገልጿል።
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ራሳቸው ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜ የአምላክን ስም እንደጠቀሰና ይህን ስም ለሌሎች እንዳሳወቀ ይገልጻሉ። (ዮሐንስ 17:6, 11, 12, 26) ኢየሱስ “እኔ በአባቴ ስም መጣሁ” ሲል በግልጽ ተናግሯል። እንዲሁም ማንኛውንም ሥራ የሚያከናውነው ‘በአባቱ ስም’ እንደሆነ አበክሮ ገልጿል።–ዮሐንስ 5:43፤ 10:25
በመንፈስ መሪነት የተጻፉት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀጣይ ክፍል እንደመሆናቸው መጠን የይሖዋ ስም በውስጣቸው አለመኖሩ መጽሐፍ ቅዱስን ወጥነት የጎደለው ያስመስለዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ ገደማ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ሽማግሌዎች “አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ለእነሱ ትኩረት እንደሰጠ ሲምዖን በሚገባ ተርኳል” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የአምላክን ስም የማያውቁ ወይም በስሙ የማይጠቀሙ ቢሆኑ ኖሮ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መናገሩ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር።
የመለኮታዊው ስም አጭር አጠራር በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። በራእይ 19:1, 3, 4, 6 ላይ ባለው “ሃሌሉያህ” በሚለው ቃል ውስጥ የመለኮታዊው ስም አጭር አጠራር ይገኛል። ይህ ቃል የመጣው በቀጥታ ሲተረጎም “ያህን አወድሱ” የሚል ፍቺ ካለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። “ያህ” ደግሞ ይሖዋ የሚለው ስም አጭር አጠራር ነው። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ብዙ ስሞች ከመለኮታዊው ስም ጋር የተያያዙ ናቸው። እንዲያውም አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች የኢየሱስ ስም ራሱ “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም እንዳለው ይገልጻሉ።
የጥንቶቹ የአይሁዳውያን ጽሑፎች፣ ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዳውያን በጽሑፎቻቸው ውስጥ መለኮታዊውን ስም ይጠቀሙ እንደነበር ያሳያሉ። የአይሁዳውያንን የቃል ሕጎች አሰባስቦ የያዘውና በ300 ዓ.ም. ገደማ ተጽፎ የተጠናቀቀው ዘ ቶሴፍታ የተባለው መጽሐፍ በሰንበት ስለተቃጠሉ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የወንጌላውያንና የሚኒም [አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ይታመናል] መጻሕፍትን ከእሳት መታደግ አልተቻለም። መጻሕፍቱ በውስጣቸው ከሰፈረው መለኮታዊ ስም ጋር እንዲቃጠሉ ተደርጎ ነበር።” ይህ ጽሑፍ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ይኖር ስለነበረ ዮሲ የተባለ ረቢ ይጠቅሳል፤ ይህ የገሊላ ሰው በሌሎቹ ቀናት ስለሚደረገው ነገር ሲናገር “አንድ ሰው ከጽሑፎቹ ላይ [እየተናገረ የነበረው ስለ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች መሆኑ ግልጽ ነው] መለኮታዊውን ስም ቆርጦ በማውጣት ካስቀመጠ በኋላ የቀረውን ያቃጥለዋል” ብሏል።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባሉ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተወሰዱ ጥቅሶች ላይ መለኮታዊው ስም ሊገኝ እንደሚችል ያምናሉ። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው ቴትራግራማተን” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሯል፦ “የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ በተጻፉበት ጊዜ፣ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ባሉ ከብሉይ ኪዳን በተወሰዱ በተወሰኑ ወይም በሁሉም ጥቅሶች ላይ ያህዌህ የሚለውን መለኮታዊ ስም የሚወክለው ቴትራግራማተን ይገኝ እንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።” በተጨማሪም ጆርጅ ሃዋርድ የተባሉት ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ቴትራግራም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት በነበረው የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ [ሰብዓ ሊቃናት] ቅጂዎች ላይ ይገኝ ስለነበር የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ከቅዱስ መጽሐፉ ሲጠቅሱ በጥቅሱ ውስጥ የሚገኘውን ቴትራግራም እንዳለ ይገለብጡ ነበር ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።”
የታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የአምላክን ስም ተጠቅመዋል። ከእነዚህ ተርጓሚዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ያደረጉት የአዲስ ዓለም ትርጉም ከመዘጋጀቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ከእነዚህ ተርጓሚዎችና ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ በኸርማን ሃይንፌተር የተዘጋጀው ኤ ሊተራል ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት . . . ፍሮም ዘ ቴክስት ኦቭ ዘ ቫቲካን ማኑስክሪፕት (1863)፣ በቤንጃሚን ዊልሰን የተዘጋጀው ዚ ኢምፋቲክ ዳያግሎት (1864)፣ በጆርጅ ባርከር ስቲቨንስ የተዘጋጀው ዚ ኢፒስልስ ኦቭ ፖል ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ (1898)፣ በዊልያም ራዘርፎርድ የተዘጋጀው ሴይንት ፖልስ ኢፒስል ቱ ዘ ሮማንስ (1900)፣ የለንደን ጳጳስ በነበሩት በዊልያም ዋንድ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ሌተርስ (1946)። በተጨማሪም ፓብሎ ቤሶን የተባለው ተርጓሚ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ባዘጋጀው የስፓንኛ ትርጉም፣ በሉቃስ 2:15 እና በይሁዳ 14 ላይ “ሄኦባ” የሚለውን ስም የተጠቀመ ሲሆን በትርጉሙ ውስጥ ባስገባቸው የግርጌ ማስታወሻዎችም ላይ ከ100 ጊዜ በላይ፣ መለኮታዊው ስም ሊገኝ የሚችልባቸውን ቦታዎች ጠቁሟል። እነዚህ የትርጉም ሥራዎች ከመውጣታቸው ከብዙ ዘመናት በፊት ይኸውም ከ16ኛው መቶ ዘመን ወዲህ ባሉት ጊዜያት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጁ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ብዙ ቦታዎች ላይ ቴትራግራማተንን ተጠቅመዋል። በጀርመንኛ ቋንቋ ብቻ እንኳ ቢያንስ 11 የሚያህሉ ትርጉሞች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ይሖዋ” የሚለውን ስም (ወይም “ያህዌህ” የሚለውን የዕብራይስጡን ቃል) የተጠቀሙ ሲሆን አራት ተርጓሚዎች ደግሞ “ጌታ” ከሚለው የማዕረግ ስም አጠገብ በቅንፍ ውስጥ ስሙን አስገብተዋል። ከ70 የሚበልጡ በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ትርጉሞች መለኮታዊውን ስም በግርጌ ማስታወሻዎች ወይም በተጨማሪ መግለጫዎች ውስጥ አስገብተዋል።
ከአንድ መቶ በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መለኮታዊውን ስም ተጠቅመዋል። በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በፓስፊክ ደሴቶች ውስጥ በሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትርጉሞች መለኮታዊውን ስም ብዙ ጊዜ ተጠቅመዋል። (በገጽ 1678 እና 1679 ላይ የሚገኘውን ዝርዝር ተመልከት።) እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያዘጋጁት ተርጓሚዎች የአምላክን ስም ለመጠቀም የወሰኑት ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ ነው። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል አንዳንዶቹ የተዘጋጁት በቅርብ ዓመታት ነው፤ ለምሳሌ ያህል፣ የሮቱማን መጽሐፍ ቅዱስ (1999) በ48 ጥቅሶች ላይ “ጂሆቫ” የሚለውን ስም 51 ጊዜ ተጠቅሟል፤ በኢንዶኔዥያ የተዘጋጀው የባታክ (ቶባ) ትርጉም (1989) ደግሞ “ጃሆዋ” የሚለውን ስም 110 ጊዜ ተጠቅሟል።
ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክን ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በቀድሞ ቦታው ላይ መልሶ ማስገባቱ ተገቢ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለ። የአዲስ ዓለም ትርጉም ተርጓሚዎችም ያደረጉት ይህንኑ ነው። ለመለኮታዊው ስም ጥልቅ አክብሮት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ምንም ነገር ላለማጉደል ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል።–ራእይ 22:18, 19