-
ስንሞት ምን እንሆናለን?መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
-
-
ምዕራፍ ስድስት
ስንሞት ምን እንሆናለን?
1-3. ሰዎች ሞትን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ይጠይቃሉ? አንዳንድ ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ‘ሞት የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ራእይ 21:4) በምዕራፍ 5 ላይ፣ ኢየሱስ የከፈለልን ቤዛ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ እንደከፈተልን ተምረናል። ይሁንና አሁንም ሰዎች ይሞታሉ። (መክብብ 9:5) በመሆኑም ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው።
2 በተለይ ደግሞ የምንወደውን ሰው በሞት በምናጣበት ወቅት የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ እንፈልጋለን። ‘የት ሄዶ ይሆን? እኛን እያየን ይሆን? ሊረዳን ይችላል? እንደገና እናገኘው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል።
3 ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች ‘ጥሩ ሰው ከሆንክ ወደ ሰማይ ትሄዳለህ’፤ ‘መጥፎ ሰው ከሆንክ ደግሞ ገሃነም ገብተህ ትቃጠላለህ’ ብለው ያስተምራሉ። ሌሎች ሃይማኖቶች ‘ስትሞት መንፈስ ትሆንና ከሞቱ ዘመዶችህ ጋር አብረህ ትኖራለህ’ ብለው ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሰዎች ከሞቱና ፍርድ ከተሰጣቸው በኋላ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ሆነው እንደገና ይወለዳሉ ብለው ያምናሉ።
4. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ሞትን በተመለከተ የሚያስተምሩት ትምህርት አንድ ዓይነት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት እንዲሁ ሲታይ የተለያየ ሊመስል ይችላል። ሆኖም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት ዞሮ ዞሮ አንድ ዓይነት ነው። ‘አንድ ሰው ሲሞት ከእሱ ተለይታ የምትኖር ነገር አለች’ ብለው ያስተምራሉ። ይሁንና ይህ እውነት ነው?
ስንሞት ምን እንሆናለን?
5, 6. ስንሞት ምን እንሆናለን?
5 ይሖዋ ስንሞት ምን እንደምንሆን ያውቃል፤ አንድ ሰው ሲሞት ሕይወቱ እንደሚያበቃ ገልጾልናል። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። አንድ ሰው ሲሞት ከእሱ ተለይታ በሌላ ስፍራ የምትኖር ረቂቅ ነገር የለችም።a በመሆኑም ስንሞት ስሜታችንም ሆነ ትዝታችን ሁሉ ይጠፋል፤ ማየትና መስማት እንዲሁም ማሰብ አንችልም።
6 ንጉሥ ሰለሞን “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት ጽፏል። የሞቱ ሰዎች መውደድም ሆነ መጥላት አይችሉም፤ “በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።” (መክብብ 9:5, 6, 10ን አንብብ።) በተጨማሪም መዝሙር 146:4 ሰው ሲሞት ‘ሐሳቡ ሁሉ እንደሚጠፋ’ ይናገራል።
ኢየሱስ ስለ ሞት ምን ብሏል?
7. ኢየሱስ ሞትን የገለጸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ የቅርብ ጓደኛው አልዓዛር በሞተ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል” ብሏቸው ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ቃል በቃል አልዓዛር ተኝቷል ማለቱ አልነበረም። ምክንያቱም ኢየሱስ “አልዓዛር ሞቷል” ሲል በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:11-14) ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። ኢየሱስ፣ አልዓዛር ወደ ሰማይ እንደሄደም ሆነ ከሞቱ ቤተሰቦቹ ጋር እንደተገናኘ አልተናገረም። በተጨማሪም ‘አልዓዛር በገሃነም እየተሠቃየ ነው’ አላለም፤ ሌላ ሰው ወይም እንስሳ ሆኖ ዳግመኛ እንደሚወለድም አልነገራቸውም። ከዚህ ይልቅ አልዓዛር ከባድ እንቅልፍ የወሰደው ያህል ነበር። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር ያመሳስሉታል። መጽሐፍ ቅዱስ እስጢፋኖስ እንደተገደለ ሲገልጽ “በሞት አንቀላፋ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 7:60) ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘በሞት እንዳንቀላፉ’ ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 15:6
8. አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው እንዲሞቱ እንዳልሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
8 አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ለተወሰኑ ዓመታት ኖረው እንዲሞቱ ነው? በፍጹም! ይሖዋ የፈጠራቸው ሙሉ ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነው። የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ለዘላለም የመኖር ፍላጎት አላቸው፤ ይሖዋ ሰዎችን የፈጠረው በዚህ መንገድ ነው። (መክብብ 3:11) ወላጆች፣ ልጆቻቸው እንዲታመሙና እንዲሞቱ አይፈልጉም፤ ይሖዋም ለእኛ ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው። ታዲያ አምላክ የፈጠረን ለዘላለም እንድንኖር ከሆነ የምንሞተው ለምንድን ነው?
የምንሞተው ለምንድን ነው?
9. ይሖዋ፣ ለአዳምና ለሔዋን የሰጣቸው ትእዛዝ ተገቢ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
9 በኤደን የአትክልት ስፍራ ይሖዋ አዳምን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ። ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:9, 16, 17) ይህን ግልጽ የሆነ መመሪያ መታዘዝ ከባድ አልነበረም። አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው ይሖዋ በመሆኑ ለእነሱ የሚጠቅመውን ነገር የሚያውቀው እሱ ነው፤ ደግሞም ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለአዳምና ለሔዋን የመንገር መብት አለው። አዳምና ሔዋን ይሖዋን በመታዘዝ የእሱን ሥልጣን እንደሚያከብሩና እሱ ለሰጣቸው ነገሮች ሁሉ አመስጋኝ እንደሆኑ ማሳየት ይችሉ ነበር።
10, 11. (ሀ) ሰይጣን፣ አዳምንና ሔዋንን የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ ያደረጋቸው እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ያደረጉት ነገር ይቅር ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው?
10 የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን ይሖዋን አልታዘዙም። ሰይጣን ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት። ሔዋንም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን። ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”—ዘፍጥረት 3:1-3
11 ከዚያም ሰይጣን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍጥረት 3:4-6) ሰይጣን እንዲህ ያለው፣ ሔዋን መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በራሷ መወሰን እንደምትችል አድርጋ እንድታስብ ስለፈለገ ነው። በተጨማሪም የይሖዋን ትእዛዝ ብትጥስ እንደማትሞት በመንገር አታለላት። ሔዋን፣ ሰይጣን የነገራትን በማመን ፍሬውን በላች፤ ከዚያም ለባሏ ሰጠችው። አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋ ፍሬውን እንዳይበሉ እንዳዘዛቸው ያውቃሉ። ፍሬውን መብላታቸው የተሰጣቸውን ግልጽና ቀላል ትእዛዝ ሆን ብለው እንደጣሱ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታቸው አክብሮት እንደሌላቸው ይጠቁማል። በእርግጥም አዳምና ሔዋን ያደረጉት ነገር ይቅር ሊባል የማይችል ነው!
12. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ በጣም አዝኖ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው?
12 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለፈጣሪያቸው አክብሮት አለማሳየታቸው በጣም ያሳዝናል! አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አሉህ እንበል፤ እነሱን ለማሳደግ ብዙ የለፋህ ቢሆንም ካደጉ በኋላ አንተን መታዘዝ ትተው የፈለጉትን ቢያደርጉ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምታዝን የታወቀ ነው!
13. ይሖዋ “ወደ አፈር ትመለሳለህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
13 አዳምና ሔዋን ይሖዋን ባለመታዘዛቸው ለዘላለም የመኖር መብታቸውን አጥተዋል። ይሖዋ አዳምን “አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:19ን አንብብ።) አዳም ከመፈጠሩ በፊት አፈር ነበር፤ ሲሞትም ተመልሶ አፈር ይሆናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 2:7) አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ሞተ፤ በመሆኑም ሕይወት የሌለው ወይም በድን ሆኗል።
14. የምንሞተው ለምንድን ነው?
14 አዳምና ሔዋን አምላክን ታዘው ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በሕይወት ይኖሩ ነበር። ሆኖም የእሱን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት ስለሠሩ ለተወሰኑ ዓመታት ከኖሩ በኋላ ሞቱ። ኃጢአት ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የወረስነው ከባድ በሽታ ነው ሊባል ይችላል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ስለምንወለድ እንሞታለን። (ሮም 5:12) ይሁንና አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ይህ አልነበረም። አምላክ የሰው ልጆች እንዲሞቱ አይፈልግም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “ጠላት” በማለት ይጠራዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:26
እውነት ነፃ ያወጣናል
15. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው?
15 ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ያወጣናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሞቱ ሰዎች ሥቃይም ሆነ ሐዘን እንደማይሰማቸው ይናገራል። የሞቱ ሰዎችን ልናናግራቸው አንችልም፤ እነሱም ቢሆኑ እኛን ሊያናግሩን አይችሉም። በተጨማሪም ልንረዳቸው አንችልም፤ እነሱም ሊረዱን አይችሉም። የሞቱ ሰዎች ሊጎዱን ስለማይችሉ እነሱን መፍራት አይገባንም። ይሁንና አንዳንድ ሃይማኖቶች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ከእሱ ተለይታ ስለምትኖር ለቄሶች ወይም ለሃይማኖት መሪዎች ገንዘብ በመክፈል የሞተውን ሰው መርዳት እንደምንችል ያስተምራሉ። ስለ ሞት እውነቱን ስናውቅ ግን እነዚህ ሰዎች በሚናገሩት ውሸት አንታለልም።
16. አንዳንድ ሃይማኖቶች ስለ ሞቱ ሰዎች ምን የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ?
16 ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት በመጠቀም እኛን ለማታለል ይሞክራል። ለምሳሌ አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ስንሞት ከእኛ ተለይታ በሌላ ስፍራ የምትኖር ነገር እንዳለች ያስተምራሉ። የአንተም ሃይማኖት የሚያስተምረው እንዲህ ነው? ወይስ የሚያስተምረው ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው? ሰይጣን እንዲህ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ተጠቅሞ ሰዎች ከይሖዋ እንዲርቁ እያደረገ ነው።
17. ይሖዋ ሰዎችን በገሃነም ያቃጥላል ብሎ ማሰብ እሱን እንደመሳደብ ይቆጠራል የምንለው ለምንድን ነው?
17 ብዙ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት ትምህርት ዘግናኝ ነው። ለምሳሌ አንዳንዶች፣ ክፉ ሰዎች በገሃነም ለዘላለም እንደሚቃጠሉ ያስተምራሉ። ይህ ይሖዋን እንደመሳደብ ይቆጠራል። ይሖዋ፣ ሰዎችን እንዲህ ባለ መንገድ ፈጽሞ አያሠቃይም! (1 ዮሐንስ 4:8ን አንብብ።) አንድ ወላጅ የልጁን እጅ በእሳት በማቃጠል ቢቀጣው ምን ይሰማሃል? ‘በጣም ጨካኝ ነው’ ብለህ ማሰብህ አይቀርም። እንዲህ ዓይነቱን ሰው እንደምትጠላው የታወቀ ነው። ሰይጣንም ስለ ይሖዋ እንዲህ እንዲሰማን ይፈልጋል!
18. የሞቱ ሰዎችን ልንፈራ የማይገባው ለምንድን ነው?
18 አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ሲሞቱ መንፈስ እንደሚሆኑ ይናገራሉ። እነዚህ መናፍስት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ወዳጆች ወይም ጨካኝ ጠላቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ልናከብራቸው እንዲሁም ልንፈራቸው እንደሚገባ ያስተምራሉ። ብዙ ሰዎች ይህን የሐሰት ትምህርት አምነው ተቀብለዋል። የሞቱ ሰዎችን ስለሚፈሩ ይሖዋን ማምለክ ሲገባቸው የሙታን መናፍስትን ያመልካሉ። የሞቱ ሰዎች ምንም ስሜት እንደሌላቸውና ምንም እንደማያውቁ አስታውስ፤ በመሆኑም ልንፈራቸው አይገባም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ፈጣሪያችን ነው። እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ስለሆነ ሊመለክ የሚገባው እሱ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11
19. ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
19 ስለ ሞት እውነቱን ማወቃችን የተለያዩ ሃይማኖቶች ከሚያስተምሩት የሐሰት ትምህርት ነፃ ያወጣናል። ይህን እውነት መገንዘባችን ይሖዋ ሕይወታችንንና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ቃል የገባቸውን አስደሳች ተስፋዎች ለመረዳት ያስችለናል።
20. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንማራለን?
20 ኢዮብ የተባለ በጥንት ዘመን የኖረ የአምላክ አገልጋይ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። (ኢዮብ 14:14) በእርግጥ የሞተ ሰው እንደገና በሕይወት ሊኖር ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም አስደሳች ነው። የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ያብራራል።
a አንዳንድ ሰዎች፣ ‘ሰው ከሞተ በኋላ ከእሱ ተለይታ የምትኖር ነፍስ ወይም መንፈስ አለች’ ብለው ያምናሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። ይህን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት ተጨማሪ ሐሳብ 17ን እና 18ን ተመልከት።
-
-
የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
-
-
ምዕራፍ ሰባት
የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!
1-3. ሁላችንም የምን እስረኞች ነን? ይሖዋስ እኛን ከዚህ እስራት ነፃ ለማውጣት ምን ያደርጋል?
አንተ ባልፈጸምከው ወንጀል ተከሰህ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደብህ እንበል። ከእስር ልትለቀቅ የምትችልበት ምንም መንገድ የለም። ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ ምንም ነገር ልታደርግ አትችልም። በጣም ተስፋ ቆርጠህ ሳለ ከእስር ቤት ሊያስወጣህ የሚችል ሰው እንዳለ ሰማህ፤ ሰውየውም እንደሚረዳህ ቃል ገባልህ! በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል?
2 ሁላችንም የሞት እስረኞች ነን ሊባል ይችላል። ምንም ነገር ብናደርግ ከሞት ማምለጥ አንችልም። ይሖዋ ግን እኛን ከሞት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ኃይል አለው። ደግሞም ይሖዋ “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል” በማለት ቃል ገብቶልናል።—1 ቆሮንቶስ 15:26
3 ወደፊት ስለ ሞት የማንጨነቅበት ዘመን ይመጣል፤ ያ ጊዜ ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ይሖዋ ሞትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የሞቱ ሰዎችም እንደገና በሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህ እንደሚያጽናናህ ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ፣ “በሞት የተረቱት” ዳግመኛ በሕይወት እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 26:19) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትንሣኤ በማለት ይጠራዋል።
የምንወደው ሰው ሲሞት
4. (ሀ) የቤተሰባችን አባል ወይም ጓደኛችን ሲሞት መጽናኛ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? (ለ) ከኢየሱስ የቅርብ ጓደኞች መካከል እነማን ይገኙበታል?
4 የቤተሰባችን አባል ወይም የቅርብ ጓደኛችን ሲሞት በጣም እናዝናለን፤ ስሜታችን በጣም ይጎዳል። ምንም አቅም እንደሌለን ይሰማናል። በሞት ያጣነው ሰው ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖር ማድረግ አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ያጽናናናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) ይሖዋና ኢየሱስ፣ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ከሞት ማስነሳት ይፈልጋሉ፤ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም የተባሉ የቅርብ ጓደኞች ነበሩት። ኢየሱስ አዘውትሮ ወደ እነሱ ቤት ይሄድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር” ይላል።—ዮሐንስ 11:3-5
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ፣ የአልዓዛር ቤተሰቦችና ወዳጆች ሲያለቅሱ ሲያይ ምን ተሰማው? (ለ) ኢየሱስ ሞትን በተመለከተ ያለውን ስሜት ማወቃችን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል?
5 አንድ ቀን አልዓዛር ሞተ። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ማርታንና ማርያምን ሊያጽናና ሄደ። ማርታ፣ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች። ኢየሱስን በማግኘቷ የተደሰተች ቢሆንም “አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ማርታ፣ ኢየሱስ የደረሰው ዘግይቶ ስለነበር ምንም ማድረግ እንደማይችል ተሰምቷት ነበር። ኢየሱስ፣ የማርታ እህት ማርያምና አብረዋት የነበሩት ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ ስሜቱ ስለተረበሸ አለቀሰ። (ዮሐንስ 11:21, 33, 35) እኛ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ በጣም እንደምናዝን ሁሉ ኢየሱስም ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶታል።
6 ኢየሱስ ሞትን በተመለከተ እኛ የሚሰማን ዓይነት ስሜት እንዳለው ማወቃችን በጣም ያጽናናናል። ኢየሱስ ደግሞ የአባቱ ዓይነት ባሕርይና ስሜት ያለው በመሆኑ ይሖዋም ስሜታችንን እንደሚረዳ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 14:9) ይሖዋ ሞትን ለዘላለም ማስወገድ ይችላል፤ ደግሞም በቅርቡ ይህን ያደርጋል።
“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”
7, 8. ማርታ ድንጋዩ እንዲነሳ ያልፈለገችው ለምን ነበር? ሆኖም ኢየሱስ ምን አደረገ?
7 ኢየሱስ አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ሲደርስ መቃብሩ በትልቅ ድንጋይ ተዘግቶ ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። ማርታ ግን ድንጋዩን እንዲያነሱት አልፈለገችም። ምክንያቱም አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። (ዮሐንስ 11:39) ማርታ፣ ኢየሱስ ቀጥሎ ምን ለማድረግ እንዳሰበ የምታውቀው ነገር አልነበረም።
8 ከዚያም ኢየሱስ አልዓዛርን “ና ውጣ!” አለው። በዚህ ጊዜ ማርታና ማርያም ያዩት ነገር በጣም የሚያስገርም ነበር። “የሞተው ሰው እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ” ወይም በጨርቅ እንደተጠቀለሉ ወጣ። (ዮሐንስ 11:43, 44) አልዓዛር እንደገና በሕይወት መኖር ጀመረ! ከቤተሰቡና ከወዳጆቹ ጋር ዳግመኛ ተገናኘ። እነዚህ ሰዎች አልዓዛርን ሊጨብጡት፣ ሊያቅፉትና ሊያናግሩት ይችሉ ነበር። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ማስነሳቱ በጣም የሚያስደንቅ ተአምር ነው!
“አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!”
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ያገኘው ከማን ነው? (ለ) ስለ ትንሣኤ የሚናገሩት ታሪኮች ጠቃሚ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
9 ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ያስነሳው በራሱ ኃይል ነው? አይደለም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል፤ ይሖዋም አልዓዛርን ማስነሳት እንዲችል ኃይል ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 11:41, 42ን አንብብ።) ከሞት የተነሳው አልዓዛር ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ በጣም ታማ እንደነበረ ይገልጻል። ኢያኢሮስ የተባለው የልጅቷ አባት በጣም ስለተጨነቀ ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው። ይህ ሰው ከእሷ በስተቀር ሌላ ልጅ አልነበረውም። ኢያኢሮስ ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የተወሰኑ ሰዎች መጥተው “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ኢያኢሮስን “አትፍራ፤ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። ከዚያም አብረው ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሄዱ። እዚያ ሲደርሱ የሚያለቅሱ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስም የሚያለቅሱትን ሰዎች “በቃ አታልቅሱ፤ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። የልጅቷ አባትና እናት ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ግራ ሳያጋባቸው አይቀርም። ኢየሱስ ቤት ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ ካስወጣ በኋላ ከልጅቷ አባትና እናት ጋር ሆኖ ትንሿ ልጅ ተኝታ ወደነበረችበት ክፍል ገባ። ከዚያም እጇን በመያዝ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አላት። ልጅቷ ወዲያውኑ ተነስታ መራመድ ስትጀምር ወላጆቿ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ኢየሱስ ልጃቸውን ከሞት አስነሳላቸው። (ማርቆስ 5:22-24, 35-42፤ ሉቃስ 8:49-56) ከዚያ ቀን ጀምሮ ልጃቸውን ባዩ ቁጥር ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ያደረገላቸውን ታላቅ ነገር እንደሚያስታውሱ ጥርጥር የለውም።a
10 ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ ሞተዋል። ይሁንና የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ማንበባችን ጠቃሚ ነው፤ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ይረዳናል። ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ከሞት ማስነሳት ይፈልጋል፤ ደግሞም ያስነሳቸዋል።
ስለ ትንሣኤ ከሚናገሩት ታሪኮች ምን ትምህርት እናገኛለን?
11. መክብብ 9:5 ከሚገልጸው ሐሳብ አንጻር አልዓዛር ስለነበረበት ሁኔታ ምን ማለት እንችላለን?
11 መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ይናገራል። አልዓዛር የነበረበት ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። (መክብብ 9:5) ኢየሱስ እንደተናገረው አልዓዛር የተኛ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 11:11) አልዓዛር መቃብር ውስጥ በነበረበት ጊዜ ‘ምንም አያውቅም’ ነበር።
12. አልዓዛር ከሞት እንደተነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ብዙ ሰዎች ተመልክተዋል። የኢየሱስ ጠላቶችም እንኳ ይህን ተአምር እንደፈጸመ ያውቁ ነበር። አልዓዛር ዳግመኛ በሕይወት መኖሩ ለዚህ ማስረጃ ነው። (ዮሐንስ 11:47) በተጨማሪም ብዙ ሰዎች አልዓዛርን ለማየት የሄዱ ሲሆን በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ እንደሆነ አምነዋል። የኢየሱስ ጠላቶች በዚህ ስላልተደሰቱ ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል አስበው ነበር።—ዮሐንስ 11:53፤ 12:9-11
13. ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
13 ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ከሞት እንደሚነሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28) በመሆኑም ይሖዋ ከሞት የሚያስነሳቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው። ሆኖም ይሖዋ አንድን ሰው ከሞት ለማስነሳት ስለዚያ ሰው ሁሉንም ነገር ማስታወስ ይኖርበታል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ማድረግ ይችላል? እስቲ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስለሚገኙት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት አስብ። ይሖዋ የእያንዳንዱን ኮከብ ስም እንደሚያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:26ን አንብብ።) ይሖዋ የእያንዳንዱን ኮከብ ስም ማስታወስ ከቻለ፣ ከሞት የሚያስነሳቸውን ሰዎች የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን ማስታወስ እንደማይከብደው ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ይሖዋ በመሆኑ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
14, 15. ኢዮብ የተናገረው ሐሳብ ምን ያስገነዝበናል?
14 ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ በትንሣኤ ያምን ነበር። “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም ይሖዋን “አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሎታል። አዎ፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቀ እንዳለ ኢዮብ ተገንዝቦ ነበር።—ኢዮብ 14:13-15
15 ስለ ትንሣኤ ተስፋ ስታውቅ ምን ተሰማህ? ‘በሞት የተለዩኝ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼስ ይነሱ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት እንደሚጓጓ ማወቃችን ያጽናናናል። ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እስቲ እንመልከት።
‘ድምፁን ሰምተው ይወጣሉ’
16. ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራቸዋል?
16 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ከሞት የተነሱ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ዳግመኛ የኖሩት እዚሁ ምድር ላይ ነው። ወደፊትም ከሞት የሚነሱት ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ይኖራሉ፤ በዚያን ጊዜ ግን በምድር ላይ የሚኖረው ሁኔታ በጣም የተሻለ ይሆናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከሞት የሚነሱት ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይችላሉ። በተጨማሪም ያን ጊዜ የሚኖረው ዓለም አሁን ከምንኖርበት ዓለም በጣም የተለየ ነው። ጦርነት፣ ወንጀልና ሕመም አይኖርም።
17. ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?
17 ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው ይወጣሉ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ራእይ 20:13 “ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና መቃብርም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ” ይላል። አዎ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት ይኖራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?
18. ከሞት የሚነሱት “ጻድቃን” እነማን ናቸው?
18 “ጻድቃን” ከተባሉት መካከል ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይገኙበታል። እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩትና አስቴር ያሉ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ተጠቅሰዋል። ይሁንና በዘመናችን ስለሞቱት የአምላክ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም ቢሆኑ “ጻድቃን” ስለሆኑ ከሞት ይነሳሉ።
19. “ዓመፀኞች” የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋስ ምን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል?
19 “ዓመፀኞች” የተባሉት ስለ ይሖዋ የመማር አጋጣሚ ያላገኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ ይሖዋ አይረሳቸውም። ከሞት ያስነሳቸዋል፤ በመሆኑም ስለ እሱ የመማርና እሱን የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ።
20. ትንሣኤ የሚያገኙት ሁሉም አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?
20 እንዲህ ሲባል ታዲያ የሞቱ ሰዎች ሁሉ ትንሣኤ ያገኛሉ ማለት ነው? በፍጹም። ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች ከሞት እንደማይነሱ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:5) አንድ ሰው ከሞት ይነሳል ወይስ አይነሳም የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው ማን ነው? የመጨረሻው ፈራጅ ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስን “በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ” ሾሞታል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42) ክፉ ተብሎ የተፈረደበትና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው ከሞት አይነሳም።—ተጨማሪ ሐሳብ 19ን ተመልከት።
ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?
21, 22. (ሀ) ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ምን ዓይነት አካል ይኖራቸዋል? (ለ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሄደው ማን ነው?
21 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉም ይናገራል። ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ የሚሄድ ሰው ከሞት የሚነሳው የሰው አካል ይዞ አይደለም። ወደ ሰማይ የሚሄደው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ነው።
22 ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ያለውን ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 3:13) ኢየሱስ ከተገደለ ከሦስት ቀን በኋላ ይሖዋ ከሞት አስነስቶታል። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 13:34, 35) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው የሰው አካል ይዞ አልነበረም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ “ሥጋዊ አካል ለብሶ እያለ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈሳዊ አካል ይዞ ሕያው ሆነ” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ነው! (1 ቆሮንቶስ 15:3-6) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ትንሣኤ የሚያገኙ ሌሎች ሰዎችም እንዳሉ ይናገራል።
23, 24. ኢየሱስ “ትንሽ መንጋ” በማለት የጠራቸው እነማንን ነው? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው?
23 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት፣ ታማኝ ለሆኑት ደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2) ስለዚህ ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹ ትንሣኤ አግኝተው ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ይኖራሉ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ትንሽ መንጋ” በማለት መጥራቱ ቁጥራቸው ጥቂት እንደሆነ ያመለክታል። (ሉቃስ 12:32) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስን በጽዮን ተራራ (በሰማይ) ላይ ቆሞ ባየው ጊዜ “ከእሱም ጋር . . . 144,000 ነበሩ” በማለት ቁጥራቸውን በቀጥታ ለይቶ ጠቅሷል።—ራእይ 14:1
24 ታዲያ 144,000ዎቹ ክርስቲያኖች ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? ይህ የሚሆነው ክርስቶስ በሰማይ መግዛት ከጀመረ በኋላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:23) በዛሬው ጊዜ የምንኖረው ክርስቶስ እየገዛ ባለበት ወቅት ላይ ሲሆን ከ144,000ዎቹ መካከል አብዛኞቹ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ሄደዋል። አሁን በምድር ላይ የሚገኙት ደግሞ ሲሞቱ ወዲያውኑ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ በሞት ያንቀላፉ አብዛኞቹ ሰዎች ያላቸው ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ነው።
25. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንማራለን?
25 በቅርቡ ይሖዋ የሰው ልጆችን በሙሉ ከሞት እስራት ነፃ የሚያወጣቸው ከመሆኑም ሌላ ሞትን ለዘላለም ያስወግዳል! (ኢሳይያስ 25:8ን አንብብ።) ይሁንና ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች እዚያ ምን ያከናውናሉ? መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በተቋቋመው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር እንደሚገዙ ይናገራል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለዚህ መንግሥት እንማራለን።
a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ታሪኮች ላይ ወጣቶችና አረጋውያን፣ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም እስራኤላውያንና የሌላ አገር ሰዎች ከሞት እንደተነሱ እናነባለን። እነዚህ ዘገባዎች በ1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:20, 21፤ ማቴዎስ 28:5-7፤ ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-42፤ 20:7-12 ላይ ይገኛሉ።
-