ኢየሱስ የተናገረው ስለ ገሃነመ እሳት ነበር?
በገሃነመ እሳት መሠረተ ትምህርት የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች በማርቆስ 9:48 (ወይም ቁጥር 44 እና 46) ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ አባባል ይጠቅሳሉ። ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ ስለማይሞት ትልና ስለማይጠፋ እሳት ተናግሮ ነበር። አንድ ሰው ይህ ጥቅስ ምን ትርጉም እንዳለው ቢጠይቅህ ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ግለሰቡ በሚጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ቁጥር 44ን, 46ን ወይም 48ን ሊያነብልህ ይችላል፤ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ እነዚህ ጥቅሶች ተመሳሳይ ሐሳቦች ይዘዋል።a የአዲስ ዓለም ትርጉም እንዲህ ይላል:- “ዓይንህም ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከምትጣል አንድ ዓይን ኖሮህ ወደ አምላክ መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፤ በገሃነም ትላቸው አይሞትም፤ እሳቱም አይጠፋም።”—ማር. 9:47, 48
ያም ሆነ ይህ አንዳንዶች፣ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ክፉ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነፍሳቸው ለዘላለም እንደሚሠቃይ ይጠቁማል የሚል አመለካከት አላቸው። ለአብነት ያህል፣ በነቫር ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ሳግራታ ቢብሊያ የተባለው የስፓንኛ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ጌታችን [በእነዚህ ቃላት] የተጠቀመው በገሃነም የሚኖረውን ሥቃይ ለማመልከት ነው። ‘የማይሞተው ትል’ በገሃነም የሚገኙ ሰዎች የሚሰማቸውን ዘላለማዊ ጸጸት እንደሚያመለክት እንዲሁም ‘የማይጠፋው እሳት’ የሚደርስባቸውን አካላዊ ሥቃይ እንደሚያመለክት ብዙውን ጊዜ ይገለጻል።”
ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር በኢሳይያስ ትንቢት የመጨረሻ ቁጥር ላይ ካለው ሐሳብ ጋር እስቲ እናወዳድር።b ኢየሱስ፣ በኢሳይያስ ምዕራፍ 66 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መጥቀሱ እንደነበር ግልጽ ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ ነቢዩ፣ “በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደነበረው የሄኖም ሸለቆ (ገሃነም)” ስለመውጣት መግለጹ ሳይሆን አይቀርም፤ “በዚህ ቦታ በአንድ ወቅት ሰዎች መሥዋዕት ይደረጉ የነበረ ሲሆን (ኤር. 7:31) ከጊዜ በኋላ ቦታው የከተማዋ ቆሻሻ መጣያ ሆኗል።” (ዘ ጄሮም ቢብሊካል ኮሜንታሪ) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢሳይያስ 66:24 የሚናገረው ስለሚሠቃዩ ሰዎች ሳይሆን ስለ ሬሳ ነው። እንደማይሞቱ የተገለጹትም ትሎቹ እንጂ በሕይወት ያሉ ሰዎች ወይም የማይሞቱ ነፍሳት አይደሉም። ታዲያ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው?
ኤል ኤቫንሄልዮ ደ ማርኮስ፣ አናሊሲስ ሊንግዊስቲኮ ኢ ኮሜንታርዮ ኤክሴሄቲኮ በተባለው የካቶሊክ ጽሑፍ ጥራዝ ሁለት ላይ ስለ ማርቆስ 9:48 የተሰጠውን ሐሳብ እንመልከት:- “ይህ ሐረግ የተወሰደው ከኢሳይያስ (66,24) ነው። እዚህ ላይ ነቢዩ የገለጸው ብዙውን ጊዜ አስከሬን የሚወገድባቸውን ሁለት መንገዶች ይኸውም መበስበስንና መቃጠልን ነበር፤ . . . ትልና እሳት አንድ ላይ መጠቀሳቸው መጥፋት የሚለውን ሐሳብ ለማጠናከር ይረዳል። . . . ሁለቱም የጥፋት ኃይሎች ቀጣይ እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል (‘አይጠፋም፣ አይሞትም’)፤ ከእነዚህ ነገሮች በምንም መንገድ ማምለጥ አይቻልም። በዚህ ማብራሪያ ላይ እንደማይጠፉ ተደርገው የተጠቀሱት ሰዎቹ ሳይሆኑ ትሎቹና እሳቱ ብቻ ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ ያገኙትን ሁሉ ድምጥማጡን ያጠፉታል። በመሆኑም ይህ ጥቅስ ዘላለማዊ ሥቃይን የሚያብራራ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክት ነው፤ ይህ ዓይነቱ ጥፋት ትንሣኤ የሌለው በመሆኑ ዘላለማዊ ነው። ስለዚህ [እሳት] ሙሉ በሙሉ የመጥፋት ምሳሌ ነው።”
እውነተኛው አምላክ አፍቃሪና ፍትሐዊ እንደሆነ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ በዚህ መንገድ መረዳት ምክንያታዊ መሆኑን ይገነዘባል። እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ክፉዎች ለዘላለም እንደሚሠቃዩ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የትንሣኤ ተስፋ የሌለው ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው መግለጹ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አስተማማኝ በሆኑት ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ቁጥር 44 እና 46 አይገኙም። ምሑራን፣ ሁለቱ ቁጥሮች ከጊዜ በኋላ የተጨመሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ፕሮፌሰር አርኪባልድ ቶማስ ሮበርትሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ጥንታዊ በሆኑትና ከሁሉ በተሻሉት ቅጂዎች ላይ እነዚህ ሁለት ቁጥሮች አይገኙም። እነዚህ ቁጥሮች የተጨመሩት ከምዕራብና ከሶርያ (ባይዛንታይን) የጥንታዊ ጽሑፎች ቅጂዎች ነው። በቁጥር 48 ላይ ያለውን ሐሳብ የሚደግሙ ናቸው። በመሆኑም ቁጥር 44 እና 46 ትክክለኛ ባለመሆናቸው [አውጥተናቸዋል]።”