ረቡዕ፣ ሐምሌ 9
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ አስበኝ፤ . . . ብርታት ስጠኝ።—መሳ. 16:28
ሳምሶን የሚለውን ስም ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አስደናቂ ጥንካሬ የነበረው ሰው መሆኑን ታስታውስ ይሆናል። ደግሞም እውነት ነው። ይሁንና ሳምሶን አስከፊ መዘዝ ያስከተለ መጥፎ ውሳኔም አድርጓል። ያም ቢሆን ይሖዋ ያተኮረው ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ባሳየው ታማኝነት ላይ ነው። ይህ ታሪክ ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተትልን አድርጓል። ይሖዋ የተመረጡ ሕዝቦቹ የሆኑትን እስራኤላውያንን ለመርዳት ሲል አስደናቂ ነገሮችን እንዲፈጽም ሳምሶንን ተጠቅሞበታል። ሳምሶን ከሞተ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሐዋርያው ጳውሎስን በመንፈሱ በመምራት የሳምሶንን ስም አስደናቂ እምነት ባሳዩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲያካትት አድርጓል። (ዕብ. 11:32-34) የሳምሶን ምሳሌ ሊያበረታታን ይችላል። አስቸጋሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ጭምር በይሖዋ ታምኗል። ከሳምሶን ታሪክ ማበረታቻና ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። w23.09 2 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ሐምሌ 10
ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።—ፊልጵ. 4:6
ወደ ይሖዋ አዘውትረን በመጸለይና የልባችንን ጭንቀት በማፍሰስ ጽናት ማዳበር እንችላለን። (1 ተሰ. 5:17) እርግጥ በአሁኑ ወቅት ከባድ መከራ አልደረሰብህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስትበሳጭ፣ ግራ ስትጋባ ወይም ነገሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሲሰማህ የይሖዋን መመሪያ የመፈለግ ልማድ አለህ? ዛሬ በዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ የይሖዋን እርዳታ አዘውትረህ የምትጠይቅ ከሆነ ወደፊት ከበድ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትልም። ይሖዋ እሱ የተሻለ ነው ብሎ በሚያስበው ጊዜና መንገድ እንደሚረዳህ ያለህ እምነትም ጠንካራ ይሆናል። (መዝ. 27:1, 3) በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ መጪውን ታላቅ መከራ በጽናት የማለፍ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። (ሮም 5:3) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ብዙ ወንድሞቻችን ከራሳቸው ተሞክሮ እንደተረዱት በጽናት የተወጡት እያንዳንዱ ፈተና ለቀጣዩ መከራ አዘጋጅቷቸዋል። በፈተና መጽናት ማንነታቸውን እንደሚያጠራው አስተውለዋል። ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ፍላጎቱ እንዳለውና በችግራቸው ፈጥኖ እንደሚደርስላቸው ያላቸው እምነት ተጠናክሯል። ይህ እምነታቸው ደግሞ ቀጣዩን ፈተና በጽናት ለመወጣት ረድቷቸዋል።—ያዕ. 1:2-4፤ w23.07 3 አን. 7-8
ዓርብ፣ ሐምሌ 11
አሳቢነት አሳይሃለሁ።—ዘፍ. 19:21
ይሖዋ ምክንያታዊ እንዲሆን የሚያነሳሳው ትሕትናውና ርኅራኄው ነው። ለምሳሌ፣ ክፉ የሆኑትን የሰዶም ነዋሪዎች ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት ትሕትናው በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ መላእክቱን ልኮ፣ ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሸሽ ለጻድቁ ሎጥ መመሪያ ሰጠው። ሎጥ ግን እዚያ መሄድ ፈራ። በመሆኑም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ዞአር ለመሸሽ እንዲፈቀድለት ለመነ፤ ዞአር ይሖዋ ለጥፋት ካሰባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች። ይሖዋ ሎጥን ‘አንዴ ብያለሁ፣ የተባልከውን አድርግ’ ማለት ይችል ነበር። ሆኖም ልመናውን ሰማው፤ ቀድሞ ያሰበው ባይሆንም ዞአርን ላለማጥፋት ወሰነ። (ዘፍ. 19:18-22) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች ርኅራኄ አሳይቷል። በከተማዋና ክፉ በሆኑት ነዋሪዎቿ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲያውጅ ነቢዩ ዮናስን ላከው። ነዋሪዎቿ ንስሐ ሲገቡ ግን ይሖዋ አዘነላቸው፤ ከተማዋንም ሳያጠፋት ቀረ።—ዮናስ 3:1, 10፤ 4:10, 11፤ w23.07 21 አን. 5