ረቡዕ፣ ሚያዝያ 22
ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21
የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ከሚቻልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ በቤተሰቡም ሆነ በሌሎች ሰዎች ብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል። አማኝ ያልሆኑት ዘመዶቹ አእምሮውን እንደሳተ ተናግረዋል፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ሥራውን የሚያከናውነው በአጋንንት ኃይል እንደሆነ በመግለጽ ወንጅለውታል፤ ሮማውያን ወታደሮች ደግሞ አፊዘውበታል፤ አንገላተውታል፤ በስተ መጨረሻም ገድለውታል። (ማር. 3:21, 22፤ 14:55፤ 15:16-20, 35-37) ያም ቢሆን ኢየሱስ ምንም አጸፋ ሳይመልስ ይህን ሁሉ ግፍ ተቋቁሟል። ከእሱ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (1 ጴጥ. 2:21-23) የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ማድረግ ያለብንን ነገር በተመለከተ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ መቼ ዝም ማለት፣ መቼ ደግሞ መናገር እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ማቴ. 26:62-64) የሐሰት ክስ በተሰነዘረበት ቁጥር ምላሽ አልሰጠም። (ማቴ. 11:19) በተናገረባቸው ጊዜያትም አሳዳጆቹን አልሰደባቸውም ወይም አልዛተባቸውም። w24.11 4-5 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23
ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ።—1 ጢሞ. 1:15
ለአንድ ለምትወደው ሰው ውብና ጠቃሚ የሆነ ልዩ ስጦታ ሰጠኸው እንበል። ግለሰቡ ስጦታውን ሣጥን ውስጥ ቢያስቀምጠውና ከዚያ በኋላ ጨርሶ ባያስታውሰው ምን ይሰማሃል? እንደምታዝን የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ግን ግለሰቡ ስጦታውን በሚገባ ሲጠቀምበትና አድናቆቱን ሲገልጽልህ እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ ልጁን ሰጥቶናል። ለዚህ ውድ ስጦታና ቤዛውን በማዘጋጀት ላሳየን ፍቅር አመስጋኝነታችንን ስናሳይ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:7, 8) ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቤዛውን ስጦታ አቅልለን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክን ስጦታ ሣጥን ውስጥ እንዳስቀመጥነው ሊቆጠር ይችላል። ስጦታው ስለተሰጠን ደስተኞች ነን፤ ሆኖም ስጦታውን መለስ ብለን አናየውም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳያጋጥመን፣ አምላክና ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር ያለንን አመስጋኝነት በየጊዜው ማደስ ይኖርብናል። w25.01 26 አን. 1-2
ዓርብ፣ ሚያዝያ 24
እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።—1 ጢሞ. 4:15
የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚሾም ወንድም አዲስ ክርስቲያን ሊሆን አይገባም። ከተጠመቅክ ብዙ ዓመት መቆጠር ባያስፈልገውም የጎለመስክ ክርስቲያን እንድትሆን የተወሰነ ጊዜ ሊያልፍ ይገባል። ሽማግሌ ሆነህ ከመሾምህ በፊት ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት እንደሆንክና ይሖዋ ኃላፊነት እስኪሰጥህ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆንክ ማሳየት አለብህ። (ማቴ. 20:23፤ ፊልጵ. 2:5-8) ይሖዋን የሙጥኝ በማለትና የጽድቅ መሥፈርቶቹን በጥብቅ በመከተል እንዲሁም በድርጅቱ በኩል የምታገኘውን መመሪያ በመታዘዝ ታማኝ መሆንህን ታሳያለህ። ቅዱሳን መጻሕፍት የበላይ ተመልካች የሚሆን ሰው የማስተማር ብቃት ያለው ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ሲባል ከመድረክ ስታስተምር አንደበተ ርቱዕ መሆን አለብህ ማለት ነው? አይደለም። ብቃት ያላቸው በርካታ ሽማግሌዎች ከመድረክ ሲያስተምሩ አንደበተ ርቱዕ ባይሆኑም እንኳ በአገልግሎትና በእረኝነት ጉብኝት ወቅት ውጤታማ በሆነ መንገድ ያስተምራሉ። w24.11 23 አን. 14-15