ሁለተኛ ዜና መዋዕል
26 ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ የ16 ዓመት ልጅ የነበረውን ዖዝያን*+ ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ምትክ አነገሡት።+ 2 እሱም፣ ንጉሡ* ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤሎትን+ መልሶ በመገንባት ወደ ይሁዳ መለሳት።+ 3 ዖዝያ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 16 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ52 ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+ 4 እሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 5 እውነተኛውን አምላክ መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን አምላክን ይፈልግ ነበር። ይሖዋን ይፈልግ በነበረበት ዘመን እውነተኛው አምላክ አበለጸገው።+
6 እሱም ወጥቶ ከፍልስጤማውያን+ ጋር በመዋጋት የጌትን+ ቅጥር፣ የያብነህን+ ቅጥርና የአሽዶድን ቅጥር አፈረሰ። ከዚያም በአሽዶድና+ በፍልስጤማውያን ክልል ከተሞችን ገነባ። 7 እውነተኛው አምላክ በፍልስጤማውያን ላይ፣ በጉርባዓል በሚኖሩት ዓረቦች+ ላይ እንዲሁም በመኡኒም ላይ ድል እንዲቀዳጅ ረዳው። 8 አሞናውያን+ ለዖዝያ ግብር ይገብሩለት ጀመር። እጅግ እየበረታ ስለሄደም ዝናው እስከ ግብፅ ድረስ ናኘ። 9 በተጨማሪም ዖዝያ በኢየሩሳሌም በማዕዘን በር፣+ በሸለቆ በርና+ የቅጥሩ ማጠናከሪያ በሚገኝበት ስፍራ ጠንካራ ማማዎችን+ ሠራ። 10 ከዚህም ሌላ በምድረ በዳው ማማዎችን ገነባ፤+ ብዙ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችንም ቆፈረ* (ብዙ ከብቶች ነበሩትና)፤ በሸፌላና በሜዳውም* ላይ እንዲሁ አደረገ። ግብርና ይወድ ስለነበር በተራሮቹ ላይና በቀርሜሎስ፣ ገበሬዎችና የወይን አትክልት ሠራተኞች ነበሩት።
11 በተጨማሪም ዖዝያ ለውጊያ ዝግጁ የሆነ ሠራዊት ነበረው። በቡድን በቡድን ተደራጅተው ለጦርነት ይወጡ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከንጉሡ መኳንንት አንዱ በሆነው በሃናንያህ አመራር ሥር ሆነው በሚያገለግሉት በጸሐፊው የኢዔል+ እና በአለቃው ማአሴያህ አማካኝነት ተቆጥረው ተመዘገቡ።+ 12 በእነዚህ ኃያላን ተዋጊዎች ላይ የተሾሙት የአባቶች ቤት መሪዎች አጠቃላይ ቁጥር 2,600 ነበር። 13 በእነሱ አመራር ሥር 307,500 ወታደሮችን ያቀፈ ሠራዊት ነበር፤ ይህም ንጉሡ በጠላት ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ድጋፍ የሚሰጡ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን የያዘ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ነው።+ 14 ዖዝያ መላው ሠራዊት ጋሻ፣ ጦር፣+ የራስ ቁር፣ ጥሩር፣+ ቀስትና የወንጭፍ ድንጋይ+ እንዲታጠቅ አደረገ። 15 በተጨማሪም ባለሙያዎች ባወጡት ንድፍ የተሠሩ የጦር መሣሪያዎችን በኢየሩሳሌም አዘጋጀ፤ መሣሪያዎቹ በየማማውና+ በቅጥሩ ማዕዘናት ላይ የተተከሉ ሲሆን ቀስትና ትላልቅ ድንጋዮች ለማስወንጨፍ ያገለግሉ ነበር። ዖዝያ ከፍተኛ እርዳታ በማግኘቱና እየበረታ በመሄዱ ዝናው በሩቅ ቦታ ሁሉ ተሰማ።
16 ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።+ 17 ወዲያውኑም ካህኑ አዛርያስና ደፋር የሆኑ ሌሎች 80 የይሖዋ ካህናት ተከትለውት ገቡ። 18 ከዚያም ንጉሥ ዖዝያን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እንዲህ አሉት፦ “ዖዝያ ሆይ፣ አንተ ለይሖዋ ዕጣን ማጠንህ ተገቢ አይደለም!+ ዕጣን ማጠን ያለባቸው ካህናቱ ብቻ ናቸው፤ እነሱ የተቀደሱ የአሮን ዘሮች ናቸውና።+ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ስለፈጸምክ ከመቅደሱ ውጣ፤ እንዲህ ማድረግህ በይሖዋ አምላክ ዘንድ ምንም ዓይነት ክብር አያስገኝልህም።”
19 ዕጣን ለማጠን በእጁ ጥና ይዞ የነበረው ዖዝያ ግን እጅግ ተቆጣ፤+ ካህናቱን እየተቆጣ ሳለም በይሖዋ ቤት በዕጣን መሠዊያው አጠገብ ካህናቱ ባሉበት ግንባሩ ላይ የሥጋ ደዌ+ ወጣበት። 20 የካህናቱ አለቃ አዛርያስና ካህናቱ ሁሉ ባዩት ጊዜ ግንባሩ በሥጋ ደዌ ተመቶ ነበር! በመሆኑም ከዚያ አጣድፈው አስወጡት፤ እሱ ራሱም ይሖዋ ስለመታው ለመውጣት ቸኩሎ ነበር።
21 ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ፤ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በመሆኑ በአንድ የተለየ ቤት ውስጥ ተገልሎ ተቀመጠ፤+ ወደ ይሖዋ ቤት እንዳይገባ ታግዶ ነበር። ልጁ ኢዮዓታም በንጉሡ ቤት* ላይ ተሹሞ በምድሪቱ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።+
22 ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለውን የቀረውን የዖዝያ ታሪክ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ+ ጽፎታል። 23 በመጨረሻም ዖዝያ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ቀበሩት፤ ሆኖም “የሥጋ ደዌ አለበት” ብለው ስላሰቡ የቀበሩት ከነገሥታቱ የመቃብር ቦታ ውጭ ባለ መሬት ላይ ነበር። በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮዓታም+ ነገሠ።