ዕዝራ
10 ዕዝራ በእውነተኛው አምላክ ቤት ፊት ተደፍቶ እያለቀሰ፣ እየጸለየና+ እየተናዘዘ ሳለ በርካታ ቁጥር ያላቸው እስራኤላውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ምርር ብሎ ያለቅስ ነበር። 2 ከዚያም ከኤላም+ ልጆች መካከል የየሂኤል+ ልጅ ሸካንያህ ዕዝራን እንዲህ አለው፦ “በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦች መካከል ባዕዳን ሴቶችን በማግባት* በአምላካችን ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመናል።+ ያም ሆኖ እስራኤል አሁንም ተስፋ አለው። 3 እንግዲህ ይሖዋም ሆነ ለአምላካችን ትእዛዝ አክብሮት ያላቸው* ሰዎች+ በሰጡት መመሪያ መሠረት ሚስቶቻችንን በሙሉና ከእነሱ የተወለዱትን ልጆች ለማሰናበት ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እንጋባ።+ ሕጉንም ተግባራዊ እናድርግ። 4 ይህ የአንተ ኃላፊነት ስለሆነ ተነስ፤ እኛም ከጎንህ ነን። አይዞህ፣ እርምጃ ውሰድ።”
5 በዚህ ጊዜ ዕዝራ ተነስቶ የቀረበውን ሐሳብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የካህናቱን፣ የሌዋውያኑንና የመላው እስራኤልን አለቆች አስማላቸው፤+ እነሱም ማሉ። 6 ከዚያም ዕዝራ ከእውነተኛው አምላክ ቤት ፊት ተነስቶ የኤልያሺብ ልጅ ወደሆነው ወደ የሆሃናን ክፍል* ሄደ። ሆኖም በግዞት የተወሰደው ሕዝብ በፈጸመው ታማኝነት የጎደለው ድርጊት+ አዝኖ ስለነበር ወደዚያ ቢሄድም እንኳ እህል አልቀመሰም፤ ውኃም አልጠጣም።
7 ከዚያም በግዞት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የሚያዝዝ አዋጅ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አወጁ፤ 8 መኳንንቱና ሽማግሌዎቹ ባስተላለፉት ውሳኔ መሠረት በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንኛውም ሰው ንብረቱ በሙሉ እንዲወረስና* በግዞት ከተወሰደው ሕዝብ ጉባኤ እንዲባረር ይደረጋል።+ 9 በመሆኑም ከይሁዳና ከቢንያም ነገድ የሆኑ ወንዶች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ ማለትም በዘጠነኛው ወር ከወሩም በ20ኛው ቀን በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ በእውነተኛው አምላክ ቤት ግቢ ውስጥ ተቀምጠው ነበር፤ ከጉዳዩ ክብደትና ከሚዘንበው ኃይለኛ ዝናብ የተነሳም ይንቀጠቀጡ ነበር።
10 ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነስቶ እንዲህ አላቸው፦ “ባዕዳን ሚስቶችን በማግባት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽማችኋል፤+ በዚህም የተነሳ የእስራኤል በደል እንዲበዛ አድርጋችኋል። 11 እንግዲህ አሁን ለአባቶቻችሁ አምላክ ለይሖዋ ተናዘዙ፤ ፈቃዱንም ፈጽሙ። በምድሪቱ ከሚኖሩት ሕዝቦችና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ራሳችሁን ለዩ።”+ 12 በዚህ ጊዜ መላው ጉባኤ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ልክ እንደተናገርከው ማድረግ ግዴታችን ነው። 13 ይሁንና ሕዝቡ ብዙ ነው፤ የዝናብ ወቅት ስለሆነ ውጭ መቆም አስቸጋሪ ነው። ደግሞም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የፈጸምነው ዓመፅ እጅግ ከባድ በመሆኑ ጉዳዩ በአንድ ወይም በሁለት ቀን የሚቋጭ አይደለም። 14 ስለዚህ እባክህ መኳንንታችን ለመላው ጉባኤ ተወካይ ሆነው ያገልግሉ፤+ ባዕዳን ሴቶችን ያገቡ በከተሞቻችን በሙሉ የሚገኙ ሰዎችም ከእያንዳንዱ ከተማ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ጋር በተወሰነው ጊዜ ይምጡ፤ በዚህ ጉዳይ የተነሳ የመጣብን የአምላካችን የሚነድ ቁጣ እስኪመለስ ድረስ እንዲህ ብናደርግ የተሻለ ነው።”
15 ይሁን እንጂ የአሳሄል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ያህዘያህ ይህን ሐሳብ ተቃወሙ፤ ሌዋውያኑ መሹላምና ሻበታይም+ ተባበሯቸው። 16 ሆኖም በግዞት የነበሩት ሰዎች በስምምነቱ መሠረት እርምጃ ወሰዱ፤ ከዚያም በአሥረኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ካህኑ ዕዝራና በየስማቸው የተመዘገቡት የአባቶቻቸው ቤት የቤተሰብ መሪዎች ሁሉ ጉዳዩን ለመመርመር ብቻቸውን ተሰበሰቡ። 17 እነሱም ባዕዳን ሴቶችን ያገቡትን ሰዎች ጉዳይ በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ መርምረው ጨረሱ። 18 ባዕዳን ሴቶችን ካገቡት ሰዎችም መካከል አንዳንድ የካህናት ልጆች መኖራቸው ታወቀ፤+ እነሱም የየሆጼዴቅ ልጅ የየሆሹዋ+ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች የሆኑት ማአሴያህ፣ ኤሊዔዘር፣ ያሪብ እና ጎዶልያስ ናቸው። 19 እነዚህ ሰዎች ሚስቶቻቸውን ለማሰናበት ቃል ገቡ፤* በደለኞች ስለሆኑም ለበደላቸው ከመንጋው መካከል አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ።+
20 ከኢሜር+ ወንዶች ልጆች ሃናኒ እና ዘባድያህ፤ 21 ከሃሪም+ ወንዶች ልጆች ማአሴያህ፣ ኤልያስ፣ ሸማያህ፣ የሂኤል እና ዖዝያ፤ 22 ከጳስኮር+ ወንዶች ልጆች ኤሊዮዔናይ፣ ማአሴያህ፣ እስማኤል፣ ናትናኤል፣ ዮዛባድ እና ኤልዓሳ። 23 ከሌዋውያኑ መካከል ዮዛባድ፣ ሺምአይ፣ ቄላያህ (ማለትም ቀሊጣ)፣ ፐታያህ፣ ይሁዳ እና ኤሊዔዘር፤ 24 ከዘማሪዎቹ መካከል ኤልያሺብ፤ ከበር ጠባቂዎቹ መካከል ሻሉም፣ ተሌም እና ዖሪ።
25 ከእስራኤል መካከል የፓሮሽ+ ወንዶች ልጆች የሆኑት ራምያህ፣ ይዝዚያህ፣ ማልኪያህ፣ ሚያሚን፣ አልዓዛር፣ ማልኪያህ እና በናያህ ነበሩ፤ 26 ከኤላም+ ወንዶች ልጆች ማታንያህ፣ ዘካርያስ፣ የሂኤል፣+ አብዲ፣ የሬሞት እና ኤልያስ፤ 27 ከዛቱ+ ወንዶች ልጆች ኤሊዮዔናይ፣ ኤልያሺብ፣ ማታንያህ፣ የሬሞት፣ ዛባድ እና አዚዛ፤ 28 ከቤባይ+ ወንዶች ልጆች የሆሃናን፣ ሃናንያህ፣ ዛባይ እና አትላይ፤ 29 ከባኒ ወንዶች ልጆች መሹላም፣ ማሉክ፣ አዳያህ፣ ያሹብ፣ ሸአል እና የሬሞት፤ 30 ከፓሃትሞአብ+ ወንዶች ልጆች አድና፣ ከላል፣ በናያህ፣ ማአሴያህ፣ ማታንያህ፣ ባስልኤል፣ ቢኑይ እና ምናሴ፤ 31 ከሃሪም+ ወንዶች ልጆች ኤሊዔዘር፣ ይሽሺያህ፣ ማልኪያህ፣+ ሸማያህ፣ ሺምኦን፣ 32 ቢንያም፣ ማሉክ እና ሸማርያህ፤ 33 ከሃሹም+ ወንዶች ልጆች ማቴናይ፣ ማታታ፣ ዛባድ፣ ኤሊፌሌት፣ የሬማይ፣ ምናሴ እና ሺምአይ፤ 34 ከባኒ ወንዶች ልጆች ማአዳይ፣ አምራም፣ ዑኤል፣ 35 በናያህ፣ ቤድያህ፣ ከሉሂ፣ 36 ዋንያህ፣ መሬሞት፣ ኤልያሺብ፣ 37 ማታንያህ፣ ማቴናይ እና ያአሱ፤ 38 ከቢኑይ ወንዶች ልጆች ሺምአይ፣ 39 ሸሌምያህ፣ ናታን፣ አዳያህ፣ 40 ማክናደባይ፣ ሻሻይ፣ ሻራይ፣ 41 አዛርዔል፣ ሸሌምያህ፣ ሸማርያህ፣ 42 ሻሉም፣ አማርያህ እና ዮሴፍ፤ 43 ከነቦ ወንዶች ልጆች የኢዔል፣ ማቲትያህ፣ ዛባድ፣ ዘቢና፣ ያዳይ፣ ኢዩኤል እና በናያህ። 44 እነዚህ ሁሉ ባዕዳን ሚስቶችን ያገቡ ናቸው፤+ እነሱም ሚስቶቻቸውን ከነልጆቻቸው አሰናበቱ።+