ኢያሱ
3 ከዚያም ኢያሱ በማለዳ ተነሳ፤ እሱም ሆነ እስራኤላውያን* በሙሉ ከሺቲም+ ተነስተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ። ወደ ማዶም ሳይሻገሩ እዚያው አደሩ።
2 ከሦስት ቀን በኋላም አለቆቹ+ በሰፈሩ ውስጥ በመዘዋወር 3 ሕዝቡን እንዲህ በማለት አዘዙ፦ “ሌዋውያን የሆኑት ካህናት+ የአምላካችሁን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ ከሰፈራችሁበት ቦታ ተነስታችሁ ታቦቱን ተከተሉት። 4 ሆኖም ወደ እሱ አትቅረቡ፤ በእናንተና በታቦቱ መካከል 2,000 ክንድ* ያህል ርቀት ይኑር፤ ከዚህ በፊት በዚህ አቅጣጫ ሄዳችሁ ስለማታውቁ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ።”
5 ኢያሱም ሕዝቡን “ይሖዋ በነገው ዕለት በመካከላችሁ ድንቅ ነገሮችን ስለሚያደርግ+ ራሳችሁን ቀድሱ”+ አላቸው።
6 ከዚያም ኢያሱ ካህናቱን “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንስታችሁ+ ከሕዝቡ ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው። በመሆኑም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት በማንሳት ከሕዝቡ ቀድመው ሄዱ።
7 ይሖዋም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደነበርኩ ሁሉ+ ከአንተም ጋር መሆኔን እንዲያውቁ+ በዛሬው ዕለት አንተን በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።+ 8 አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ‘ዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ እዚያው ዮርዳኖስ ውስጥ ባላችሁበት ቁሙ’ ብለህ እዘዛቸው።”+
9 ኢያሱም እስራኤላውያንን “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ስሙ” አላቸው። 10 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ በመካከላችሁ ሕያው አምላክ እንዳለና+ እሱም ከነአናውያንን፣ ሂታውያንን፣ ሂዋውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ገርጌሻውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን በእርግጥ ከፊታችሁ እንደሚያባርራቸው በዚህ ታውቃላችሁ።+ 11 የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ቀድሟችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል። 12 እናንተም ከእስራኤል ነገዶች 12 ሰዎችን ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ምረጡ፤+ 13 የምድር ሁሉ ጌታ የሆነውን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግር የዮርዳኖስን ውኃ ሲነካ* ከላይ የሚወርደው ውኃ ይቋረጣል፤ ውኃውም ልክ እንደ ግድብ* ቀጥ ብሎ ይቆማል።”+
14 ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ድንኳኑን ነቅሎ ሲነሳ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት+ ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ። 15 ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ዮርዳኖስ ጋ ሲደርሱና እግራቸውን ውኃው ዳር ሲያጠልቁ (ወቅቱ መከር ስለነበር በመከር ጊዜ እንደሚሆነው ሁሉ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ዳርቻውን አጥለቅልቆት ነበር)+ 16 ከላይ ይወርድ የነበረው ውኃ ቆመ። ውኃውም በሩቅ ይኸውም በጻረታን አጠገብ በምትገኘው በአዳም ከተማ እንደ ግድብ* ተቆልሎ ቆመ፤ በአረባ ወደሚገኘው ባሕር ይኸውም ወደ ጨው ባሕር* የሚወርደውም ውኃ ደረቀ። ውኃው ተቋርጦ ስለነበር ሕዝቡ ከኢያሪኮ ማዶ ወዳለው ስፍራ ተሻገረ። 17 እስራኤላውያን በሙሉ በደረቅ መሬት እስኪሻገሩ+ ይኸውም መላው ብሔር ዮርዳኖስን ተሻግሮ እስኪያበቃ ድረስ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ላይ ባሉበት ቆመው ነበር።+