28 ክፉዎች ማንም ሳያሳድዳቸው ይሸሻሉ፤
ጻድቃን ግን እንደ አንበሳ ልበ ሙሉ ናቸው።+
2 በአንድ አገር ውስጥ ሕግ ተላላፊነት ሲነግሥ ብዙ ገዢዎች ይፈራረቁበታል፤+
ይሁንና ጥልቅ ግንዛቤና እውቀት ያለው ሰው በሚያበረክተው እርዳታ ገዢ ለረጅም ዘመን ይቆያል።+
3 ችግረኞችን የሚበዘብዝ ድሃ፣+
እህሉን ሁሉ ጠራርጎ እንደሚወስድ ዝናብ ነው።
4 ሕግን የሚተዉ ሰዎች ክፉዎችን ያወድሳሉ፤
ሕግን የሚጠብቁ ሰዎች ግን በእነሱ ላይ ይቆጣሉ።+
5 ክፉዎች ፍትሕን መረዳት አይችሉም፤
ይሖዋን የሚፈልጉ ግን ሁሉን ነገር መረዳት ይችላሉ።+
6 መንገዱ ብልሹ ከሆነ ሀብታም ይልቅ
ንጹሕ አቋም ይዞ የሚመላለስ ድሃ ይሻላል።+
7 አስተዋይ ልጅ ሕግን ይጠብቃል፤
ከሆዳሞች ጋር የሚወዳጅ ግን አባቱን ያዋርዳል።+
8 ወለድና+ አራጣ በማስከፈል ሀብት የሚያካብት፣
ለድሆች ሞገስ ለሚያሳይ ሰው ያከማችለታል።+
9 ሕግን ለመስማት አሻፈረኝ የሚል ሰው፣
ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው።+
10 ቅኖችን አሳስቶ ወደ መጥፎ መንገድ የሚመራ፣ እሱ ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ይገባል፤+
ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።+
11 ሀብታም ሰው በገዛ ዓይኖቹ ፊት ጥበበኛ ነው፤+
ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ድሃ ግን ማንነቱን ይደርስበታል።+
12 ጻድቃን ድል ሲያደርጉ ታላቅ ክብር ይሆናል፤
ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ግን ሰዎች ይሸሸጋሉ።+
13 የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤+
የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።+
14 ምንጊዜም ተጠንቅቆ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤
ልቡን የሚያደነድን ሁሉ ግን ለጥፋት ይዳረጋል።+
15 ምስኪን በሆነ ሕዝብ ላይ የተሾመ ክፉ ገዢ፣
እንደሚያገሳ አንበሳና ተንደርድሮ እንደሚመጣ ድብ ነው።+
16 ጥልቅ ግንዛቤ የሌለው መሪ ሥልጣኑን አላግባብ ይጠቀማል፤+
በማጭበርበር የሚገኝን ትርፍ የሚጠላ ግን ዕድሜውን ያራዝማል።+
17 የሰው ሕይወት በማጥፋቱ የደም ባለ ዕዳ የሆነ ሰው መቃብር እስኪገባ ድረስ ሲሸሽ ይኖራል።+
እንዲህ ያለውን ሰው ማንም አይርዳው።
18 እንከን የለሽ በሆነ መንገድ የሚመላለስ ሰው ይድናል፤+
መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ድንገት ይወድቃል።+
19 መሬቱን የሚያርስ ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤
ከንቱ የሆኑ ነገሮችን የሚያሳድድ ግን እጅግ ይደኸያል።+
20 ታማኝ ሰው ብዙ በረከት ያገኛል፤+
ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ ግን ንጽሕናውን ማጉደፉ አይቀርም።+
21 አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፤+
ሆኖም ሰው ለቁራሽ ዳቦ ብሎ ስህተት ሊፈጽም ይችላል።
22 ቀናተኛ ሰው ሀብት ለማግኘት ይጓጓል፤
ድህነት ላይ እንደሚወድቅ አያውቅም።
23 በምላሱ ከሚሸነግል ይልቅ
ሰውን የሚወቅስ+ የኋላ ኋላ ይበልጥ ሞገስ ያገኛል።+
24 አባቱንና እናቱን እየዘረፈ “ምንም ጥፋት የለበትም” የሚል ሁሉ+
የአጥፊ ተባባሪ ነው።+
25 ስግብግብ ሰው ጠብ ያነሳሳል፤
በይሖዋ የሚታመን ግን ይበለጽጋል።+
26 በገዛ ልቡ የሚታመን ሁሉ ሞኝ ነው፤+
በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም።+
27 ለድሃ የሚሰጥ ሁሉ አይቸገርም፤+
እነሱን ላለማየት ዓይኖቹን የሚከድን ግን ብዙ እርግማን ይደርስበታል።
28 ክፉዎች ሥልጣን ሲይዙ ሰው ራሱን ይሸሽጋል፤
ክፉዎች ሲጠፉ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።+