ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ትከተላለህን?
“ጻድቃን . . . እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራሉ።” (ምሳሌ 28:1) ምንም ዓይነት አደጋ ከፊታቸው ቢደቀንም በይሖዋ አገልግሎት በድፍረት ወደፊት ይገፋሉ፤ እምነት አላቸው፤ በአምላክ ቃል ላይም ትምክህት ጥለው ይመሩበታል።
እስራኤላውያን በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከግብፅ ባርነት ነጻ ከወጡ በኋላ በሲና በነበሩበት ወቅት በተለይ ሁለት ሰዎች ልክ እንደ አንበሳ ልበ ሙሉነትን አሳይተዋል። በተጨማሪም በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሥር እያሉ ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት አሳይተዋል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የሙሴ ሎሌ የነበረውና በኋላም ሙሴን እንዲተካ የተሾመው ኤፍሬማዊው ኢያሱ ነው። (ዘጸአት 33:11፤ ዘኁልቁ 13:8, 16፤ ዘዳግም 34:9፤ ኢያሱ 1:1, 2) ሌላው ከይሁዳ ነገድ የሆነው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ነበር።—ዘኁልቁ 13:6፤ 32:12
ካሌብ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት በመቆምና በቅንዓት የይሖዋን ፈቃድ አድርጓል። ለረዥም ዘመን አምላክን ማገልገሉ ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ተከትያለሁ’ ብሎ እንዲናገር አስችሎታል። (ኢያሱ 14:8) ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል “እኔ ግን ለጌታ አምላኬ በፍጹም ታማኝነት ከጎኑ ቆሜአለሁ” ይላል። ካሌብ “በታማኝነት ለይሖዋ ታዟል” ወይም ከይሖዋ አምላክ ‘ጎን በታማኝነት ቆሞ ዓላማውን ፈጽሟል።’ (ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን እና ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) የኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ደግሞ “እኔ . . . ጌታ አምላኬን በሙሉ ልቤ ተከትየዋለሁ” በማለት ካሌብ መግለጹን ይናገራል። አንተስ? ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ትከተላለህን?
ምድሪቱን መሰለል
እስቲ ራስህን ይሖዋ ከግብጽ ባርነት ነፃ ካወጣቸው እስራኤላውያን መካከል እንደ አንዱ አድርገህ አስብ። ነቢዩ ሙሴ አምላክ የሰጠውን መመሪያ እንዴት በታማኝነት እንደተከተለ ተመልከት። ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ስለመሆኑ ካሌብ የነበረውንም ትምክህት ልብ በል።
ጊዜው እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበት ሁለተኛ ዓመት ላይ ነው። እስራኤላውያን በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ በርኔ ሰፍረዋል። በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ቆመዋል። ሙሴ አምላክ ስላዘዘው 12 ሰላዮችን ወደ ከነዓን ሊልክ እየተዘጋጀ ነው። “ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፣ ወደ ተራሮችም ሂዱ፣ ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፣ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፣ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ የሚኖሩባትም ምድር፣ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ፣ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱም ፍሬ አምጡ፤ አይዟችሁ” አላቸው። —ዘኁልቁ 13:17-20
አሥራ ሁለቱ ሰዎች አደገኛውን ጉዟቸውን ጀመሩ። ተልዕኳቸው ለ40 ቀናት ያህል ይቆያል። በኬብሮን ውስጥ ግዙፍ የሆኑ ሰዎችን ተመለከቱ። በኤሽኮል ሸለቆ ውስጥ የምድሪቱን ፍሬያማነት በመመልከት ከፍሬዋ ጥቂት ለመውሰድ ወሰኑ። አንድ የወይን ዘለላ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሁለት ሰዎች በወፍራም ዘንግ መሸከም ነበረባቸው።—ዘኁልቁ 13:21-25
ሰላዮቹ እስራኤላውያን ወደ ሰፈሩበት ተመለሱና እንዲህ ሲሉ ተናገሩ:- “ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፣ እርሷም ወተትና ማር ታፈስሳለች፣ ፍሬዋም ይህ ነው። ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው፣ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባህር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።” (ዘኁልቁ 13:26-29) አሥሩ ሰላዮች የአምላክን ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ ፈቃደኛ አልነበሩም።
‘ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው’
ይሁን እንጂ ፍርሃት የለሹ ሰላይ ካሌብ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነቱን በመጣል “ማሸነፍ እንችላለንና እንውጣ እንውረሰው” በማለት አጥብቆ ተናገረ። ሆኖም አሥሩ ሰላዮች የከነዓን ነዋሪዎች ከእስራኤላውያን ይበረታሉ በማለት ተቃወሙት። የተደናገጡትና እምነት የለሾቹ ሰላዮች ራሳቸውን ከእነርሱ ጋር በማወዳደር የፌንጣ ያህል እንደሆኑ ተሰማቸው። — ዘኁልቁ 13: 30–33
“እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ከእኛ ጋር ነው አትፍሩአቸው” ሲሉ ካሌብና ኢያሱ ሕዝቡን አደፋፈሩ። ሕዝቡ ግን ጆሮውን ደፈነ። ሕዝቡ በድንጋይ እንውገራቸው ብለው ሲናገሩ አምላክ ጣልቃ በመግባት አጉረምራሚዎቹ ላይ እንዲህ የሚል ብያኔ ሰጠ:- “ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። . . . ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፣ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ። . . . በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ . . . ምድሪቱን በሰለላችሁባት ቀን ቁጥር፣ አርባ ቀን፣ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፣ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማለችሁ።”—ዘኁልቁ 14:9, 30-34
ከብዙ ዓመታት በኋላም ታማኞች ነበሩ
የተፈረደባቸው የ40 ዓመት ጊዜ ተፈጸመ። አጉረምራሚው ትውልድ በጠቅላላ ተደመሰሰ። ይሁን እንጂ ካሌብና ኢያሱ አሁንም ለአምላክ ታማኝ ናቸው። በሞዓብ ሜዳ ላይ ሙሴና ሊቀካህኑ አልአዛር ዕድሜአቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ ለውትድርና የደረሱትን ወንዶች ቆጠሩ። አምላክ የተስፋይቱን ምድር የማከፋፈሉን ኃላፊነት የሚሸከሙ ከእያንዳንዱ የእሥራኤል ነገድ አንድ አንድ ሰው መረጠ። ከእነዚህም መካከል ካሌብ፣ ኢያሱና አልአዛር ይገኙ ነበር። (ዘኁልቁ 34: 17–29) ካሌብ ዕድሜው 79 ዓመት ቢሆንም ብርቱ፣ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት የሚቆምና ደፋር ነበር።
ከፍርሃት የተነሳ ወደ ከነዓን ምድር አንገባም ከማለታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ሙሴና አሮን ወደ ከነዓን ምድር በሲና የቆጠሯቸው የእስራኤል ተዋጊዎች 603,550 ያህል ነበሩ። አራት አሥርተ ዓመታት ካለፉ በኋላ የቀሩት ወታደሮች 601,730 ብቻ ነበሩ። (ዘኁልቁ 1:44-46፤ 26:51) ነገር ግን እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነትና በታማኙ ካሌብ አቀናጅነት ከድል ወደ ድል እየተሸጋገሩ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገቡ። ኢያሱና ካሌብ ምን ጊዜም ይጠብቁት እንደነበረው ይሖዋ ለሕዝቡ ጦርነቱን ሁሉ ድል ያደርግላቸው ነበር።
በዕድሜ የገፉት ኢያሱና ካሌብ ከእስራኤል ተዋጊዎች ጋር በመሆን የዮርዳኖስን ወንዝ በማቋረጥ ተዋጊዎቹ በሚገጥሟቸው ችግሮች ሁሉ ይረዷቸው ነበር። ከስደስት የጦርነት ዓመታት በኋላም ገና ያልተያዘ ሠፊ ምድር ቀርቶ ነበር። ይሖዋ የዚያን ምድር ነዋሪዎች ወደፊት ያስወጣቸዋል። አሁን ግን ምድሪቱ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ እንድትከፋፈል ይሖዋ አዘዘ። —ኢያሱ 13:1-7
ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ተከትሏል
ካሌብ በብዙ ጦርነቶች ላይ ስለ ተዋጋ በኢያሱ ፊት ቆሞ እንዲሀ አለ:- “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ባሪያ ሙሴ ምድርን እሰልል ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም በልቤ የነበረውን ቃል መለስሁለት። ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] ፈጽሜ ተከትልሁ።” (ኢያሱ 14:6-8) አዎ፣ ካሌብ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ተከትሏል፣ በታማኝነት ከጎኑ በመቆም የአምላክን ፈቃድ አድርጓል።
ቀጥሎም ካሌብ እንዲህ አለ:- “ሙሴም በዚያ ቀን:- አምላኬ እግዚአብሔርን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም በእርግጥ ርስት ይሆናል ብሎ ማለ። አሁንም፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፣ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፣ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፣ እነሆ፣ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፣ ዛሬ ጉልበታም ነኝ፤ ጉልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፣ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው። አሁን እንግዲህ በዚያን ቀን እግዚአብሔር የተናገረውንም ይህን ተራራማ አገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይሆናል፣ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ አሳድዳቸዋለሁ።” በዚህ ጊዜ ኬብሮን የካሌብ ርስት ሆና ተሰጠችው። — ኢያሱ 14:9-15
በዕድሜ የገፋው ካሌብ ከባድ ሥራ ተቀበለ። እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሰዎች ይኖሩባት የነበረችው ምድር ተሰጠው። ይሁን እንጂ ለዚህ የ85 ዓመት ተዋጊ ይህ ከባድ አልነበረም። ከጊዜ በኋላ ኬብሮንን ይዘዋት የነበሩ ሰዎች ተደመሰሱ። በእስራኤል ፈራጅ የነበረውና የካሌብ ወንድም ልጅ የነበረው ጎቶንያል ዳቤርን ያዘ። ከዚያም ሁለቱ ከተሞች የሌዋውያን መኖሪያ ሆኑ። ኬብሮንም ሳያውቁ ነፍስ ላጠፉ ሰዎች መማጸኛ ከተማ ሆነች። — ኢያሱ 15:13-19፤ 21:3, 11-16፤ መሳፍንት 1:9-15, 20
ምን ጊዜም ቢሆን ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ተከተል
ካሌብና ኢያሱ ፍጽምና ያልነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ሆኖም በታማኝነት የይሖዋን ፈቃድ አድርገዋል። እስራኤላውያን አምላክን ባለመታዘዛቸው ምክንያት ባሳለፏቸው 40 አስቸጋሪ ዓመታት ወቅት እምነታቸው አልቀነሰም። በተመሳሳይም በዘመናችን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋን ለማወደስ በሚያደርጉት አገልግሎታቸው አንዳችም ነገር ጣልቃ እንዲገባባቸው አይፈቅዱም። ውጊያው በአምላክ ድርጅትና በሰይጣን ዲያብሎስ መካከል ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን በማወቅ ምን ጊዜም ሰማያዊ አባታቸውን በሁሉም ነገር ለማስደሰት በመፈለግ ጸንተው ይቆማሉ።
ለምሳሌ ያህል ብዙዎች የይሖዋ ሕዝቦች በጭካኔ መደብደብ ወይም መገደል ሊደርስባቸው እንደሚችል እያወቁ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ወይም የጌታ እራትን ለማክበር ሲሉ የከፋ ተቃውሞ ሞትም እንኳን ሳይቀር ገጥሟቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11: 23-26) ይህን በተመለከተ በ2ኛው የዓለም ጦርነት በናዚ የእሥረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስራ የነበረች አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች:-
“ሁሉም ሰው በልብስ ማጠቢያው ክፍል ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ እንዲገኝ ተነገረው። ልክ ከምሽቱ 5 ሰዓት ሲሆን 105 ሰዎች የምንሆን ተሰበሰብን። ሁላችንም ተጠጋግተን ክብ ሠርተን ቆምን። በመካከላችንም በነጭ ጨርቅ የተሸፈነው ቂጣውና ወይኑ በአጭር በርጩማ ላይ ተቀምጦ ነበር። የኤሌክትሪክ መብራት ያበራን እንደሆን ሊያዩን ስለሚችሉ በክፍሉ ውስጥ ያበራነው ሻማ ነበር። በካታኮምብ እንደነበሩት የጥንት ክርስቲያኖች እንደሆንን ያህል ተሰማን። በታላቅ አክብሮት የተከናወነ በዓል ነበር። ለቲኦክራሲው በታማኝነት እንድንቆምና ባለን ኃይል ሁሉ ቅዱስ ስሙን ለማስከበር ላባታችን የገባነውን ልባዊ ስዕለት እንደገና አደስን።”
ስደት የሚያጋጥመን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን ፈተናዎች ቢደርሱብንም ለቅዱስ ስሙ ክብር ለማምጣት እርሱን በቆራጥነት ለማገልገል አምላክ በሚሰጠን ኃይል ልንቋቋም እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4: 13) ይሖዋን ለማስደሰት በምንጥርበት ጊዜ ካሌብን ማስታወስ ይጠቅመናል። ካሌብ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ በመከተል ያሳየው ምሳሌ በ1921 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረን አንድ ወጣት በኃይል ነካው። እርሱም እንዲህ ሲል ጻፈ:-
“አቅኚ መሆኔ በኮቨንተሪ [ኢንግላንድ] ውስጥ በዘመናዊው የማተሚያ ቤት የነበረኝን ጥሩ ሥራ እንድተው ያደረገኝ ቢሆንም ምንም አልቆጭም። ሕይወቴን የወሰንኩት ለአምላክ ስለሆነ ይህ ውሳኔዬ ለችግሩ መልስ ይሰጣል። ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ተከትሏል’ የተባለለትን ከኢያሱ ጋር ወደ ተስፋይቱ ምድር የገባውን ካሌብን አስታወስኩ። (ኢያሱ 14:8) ትክክለኛው አስተሳሰብ ይህ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። አምላክን ሙሉ በሙሉ ማገልገሉ ለእርሱ የወሰንኩትን ሕይወቴን በብዙ የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚሞላውና በክርስቲያኖች ላይ የሚታየውን ፍሬ ለማፍራት የበለጡ አጋጣሚዎችን እንደሚሰጠኝ አውቅ ነበር።”
ካሌብ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት እየቆመ ሙሉ በሙሉ በመከተሉ እንደተባረከ የተረጋገጠ ነው። ሁልጊዜ መለኮታዊውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ምን ጊዜም መንገድ ይፈልግ ነበር። ልክ እንደ እርሱ ሌሎችም በአምላክ አገልግሎት ታላቅ ደስታ እና ብዙ በረከቶች አግኝተዋል። ሳታቋርጥ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ መከተል ያንተም የግል ተሞክሮ ይሁን።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካሌብ እና ኢያሱ በፈተና ወቅት ለይሖዋ ታማኞች ነበሩ? አንተስ?