ዘኁልቁ
3 ይሖዋ በሲና ተራራ+ ላይ ከሙሴ ጋር በተነጋገረ ጊዜ የአሮንና የሙሴ የቤተሰብ ሐረግ* ይህ ነበር። 2 የአሮን ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦ የበኩር ልጁ ናዳብ፣ አቢሁ፣+ አልዓዛርና+ ኢታምር።+ 3 የአሮን ወንዶች ልጆች ስም ይኸውም ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት* ቅቡዕ የሆኑት ካህናት ስም ይህ ነበር።+ 4 ይሁንና ናዳብና አቢሁ በሲና ምድረ በዳ በይሖዋ ፊት ያልተፈቀደ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በይሖዋ ፊት ሞቱ፤+ እነሱም ወንዶች ልጆች አልነበሯቸውም። አልዓዛርና+ ኢታምር+ ግን ከአባታቸው ከአሮን ጋር በክህነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ።
5 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 6 “የሌዊን ነገድ+ አምጥተህ በካህኑ በአሮን ፊት አቁመው፤ እነሱም ያገልግሉት።+ 7 ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ የሚያከናውኑትን አገልግሎት በመፈጸም ለእሱም ሆነ ለመላው ማኅበረሰብ ያለባቸውን ኃላፊነት በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ይወጡ። 8 የመገናኛ ድንኳኑን ዕቃዎች በሙሉ በኃላፊነት መቆጣጠርና+ ከማደሪያ ድንኳኑ ጋር የተያያዘውን አገልግሎት በማከናወን ለእስራኤል ልጆች ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል።+ 9 ሌዋውያኑን ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ስጣቸው። እነሱ የተሰጡ ናቸው፤ ከእስራኤላውያን መካከል ለእሱ የተሰጡ ናቸው።+ 10 አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ሹማቸው፤ እነሱም የክህነት ኃላፊነታቸውን ይወጡ፤+ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ወደ መቅደሱ ቢቀርብ ይገደል።”+
11 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “በእስራኤላውያን በኩሮች ሁሉ* ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል እወስዳለሁ፤+ ሌዋውያኑም የእኔ ይሆናሉ። 13 ምክንያቱም በኩር ሁሉ የእኔ ነው።+ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በመታሁበት ቀን+ በእስራኤላውያን መካከል ያለውን የሰውም ሆነ የእንስሳ በኩር ለራሴ ቀድሻለሁ።+ እነሱ የእኔ ይሆናሉ። እኔ ይሖዋ ነኝ።”
14 በተጨማሪም ይሖዋ በሲና ምድረ በዳ+ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 15 “የሌዊን ወንዶች ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶችና በየቤተሰባቸው መዝግብ። አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ መዝግብ።”+ 16 በመሆኑም ሙሴ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ልክ እንደታዘዘው መዘገባቸው። 17 የሌዊ ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦ ጌድሶን፣ ቀአትና ሜራሪ።+
18 የጌድሶን ወንዶች ልጆች ስም በየቤተሰባቸው ይህ ነበር፦ ሊብኒ እና ሺምአይ።+
19 የቀአት ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው አምራም፣ ይጽሃር፣ ኬብሮንና ዑዚኤል ነበሩ።+
20 የሜራሪ ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸው ማህሊ+ እና ሙሺ+ ነበሩ።
የሌዋውያኑ ቤተሰቦች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ነበሩ።
21 የሊብናውያን+ ቤተሰብና የሺምአያውያን ቤተሰብ የተገኘው ከጌድሶን ነበር። የጌድሶናውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ። 22 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 7,500 ነበር።+ 23 የጌድሶናውያን ቤተሰቦች የሰፈሩት ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ+ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ነበር። 24 የጌድሶናውያን የአባቶች ቤት አለቃ የላኤል ልጅ ኤሊያሳፍ ነበር። 25 የጌድሶን ልጆች+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ያለባቸው ኃላፊነት ከማደሪያ ድንኳኑ፣ ከድንኳኑ ጨርቅ፣+ ከመደረቢያው፣+ ከመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ መከለያ፣*+ 26 ከግቢው መጋረጃዎች፣+ በማደሪያ ድንኳኑ ዙሪያ በሚገኘው ግቢ መግቢያ ላይ ካለው መከለያ፣*+ ከመሠዊያው፣ ከድንኳኑ ገመዶችና ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ካለው አገልግሎት ሁሉ ጋር የተያያዘ ነበር።
27 የአምራማውያን ቤተሰብ፣ የይጽሃራውያን ቤተሰብ፣ የኬብሮናውያን ቤተሰብና የዑዚኤላውያን ቤተሰብ የተገኘው ከቀአት ነበር። የቀአታውያን ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+ 28 አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 8,600 ነበር፤ እነሱም ቅዱሱን ስፍራ የመንከባከብ ኃላፊነት ነበረባቸው።+ 29 የቀአት ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ደቡብ በኩል ሰፍረው ነበር።+ 30 የቀአታውያን ቤተሰቦች የአባቶች ቤት አለቃ የዑዚኤል+ ልጅ ኤሊጻፋን ነበር። 31 ኃላፊነታቸውም ከታቦቱ፣+ ከጠረጴዛው፣+ ከመቅረዙ፣+ ከመሠዊያዎቹ፣+ በቅዱሱ ስፍራ ለማገልገል ከሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች፣+ ከመከለያውና*+ ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ካለው አገልግሎት ሁሉ ጋር የተያያዘ ነበር።+
32 የሌዋውያኑ ዋና አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር+ ሲሆን እሱም ከቅዱሱ ስፍራ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የተጣለባቸውን በበላይነት ይከታተል ነበር።
33 የማህላውያን ቤተሰብና የሙሻውያን ቤተሰብ የተገኘው ከሜራሪ ነበር። የሜራሪ ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+ 34 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው 6,200 ነበር።+ 35 የሜራሪ ቤተሰቦች የአባቶች ቤት አለቃ የአቢሃይል ልጅ ጹሪኤል ነበር። እነሱም ከማደሪያ ድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ሰፍረው ነበር።+ 36 የሜራሪ ወንዶች ልጆች የተጣለባቸው ኃላፊነት የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣+ መሰኪያዎቹን፣ ዕቃዎቹን በሙሉ፣+ ከእነዚህ ጋር ግንኙነት ያለውን አገልግሎት ሁሉ+ 37 እንዲሁም በግቢው ዙሪያ ያሉትን ዓምዶች፣ መሰኪያዎቻቸውን፣+ የድንኳን ካስማዎቻቸውንና የድንኳን ገመዶቻቸውን በበላይነት መቆጣጠር ነበር።
38 በማደሪያ ድንኳኑ ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ፀሐይ በምትወጣበት አቅጣጫ የሰፈሩት ሙሴና አሮን እንዲሁም የአሮን ወንዶች ልጆች ነበሩ። እስራኤላውያንን ወክለው እንዲያከናውኑ የተጣለባቸው ግዴታም መቅደሱን የመንከባከብ ኃላፊነት ነበር። ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* ወደዚያ ቢቀርብ ይገደላል።+
39 ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሙሴና አሮን በየቤተሰባቸው የመዘገቧቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሌዋውያን ወንዶች በሙሉ 22,000 ነበሩ።
40 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤላውያን መካከል አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን+ በኩር የሆኑ ወንዶች በሙሉ መዝግብ፤ ከቆጠርካቸውም በኋላ ስማቸውን በዝርዝር ጻፍ። 41 ከእስራኤላውያን መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ለይልኝ፤+ የሌዋውያኑን የቤት እንስሳትም ከእስራኤላውያን የቤት እንስሳት መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ለይልኝ፤+ እኔ ይሖዋ ነኝ።” 42 ከዚያም ሙሴ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ከእስራኤላውያን መካከል በኩር የሆኑትን ሁሉ መዘገበ። 43 አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው በየስማቸው የተመዘገቡት በኩር የሆኑ ወንዶች ብዛታቸው 22,273 ነበር።
44 ይሖዋ እንዲህ በማለት ሙሴን ማነጋገሩን ቀጠለ፦ 45 “ከእስራኤላውያን መካከል በኩር በሆኑት ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ለይ፤ የሌዋውያኑን የቤት እንስሳትም በቤት እንስሶቻቸው ሁሉ ምትክ ለይ፤ ሌዋውያኑ የእኔ ይሆናሉ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 46 ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የበለጠውን 273+ እስራኤላውያን በኩሮች ለመዋጀት+ 47 ለእያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል* መሠረት አምስት ሰቅል* ውሰድ።+ አንድ ሰቅል 20 ጌራ* ነው።+ 48 አንተም ገንዘቡን ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የተረፈውን ሰዎች ለመዋጀት የተከፈለ ዋጋ አድርገህ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ስጥ።” 49 በመሆኑም ሙሴ ቁጥራቸው ከሌዋውያኑ ቁጥር የተረፈውን ሰዎች ለመዋጀት የመዋጃውን ገንዘብ ሰበሰበ። 50 እሱም ገንዘቡን ይኸውም እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት 1,365 ሰቅል ከእስራኤላውያኑ በኩሮች ላይ ወሰደ። 51 ከዚያም ሙሴ በይሖዋ ቃል* መሠረት ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ሰጣቸው።