ዘሌዋውያን
26 “‘ትሰግዱላቸው ዘንድ+ ለራሳችሁ ከንቱ አማልክትን አትሥሩ፤+ እንዲሁም ለራሳችሁ የተቀረጸ ምስል+ ወይም የማምለኪያ ዓምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ከድንጋይ የተቀረጸ ምስል አታኑሩ፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 2 ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ ለመቅደሴም አክብሮት* ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።
3 “‘ባወጣኋቸው ደንቦች መሠረት ብትሄዱና ትእዛዛቴን ብትጠብቁ እንዲሁም ብትፈጽሙ+ 4 ዝናብን በወቅቱ አዘንብላችኋለሁ፤+ ምድሪቱም ምርቷን ትሰጣለች፤+ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። 5 ገና እህላችሁን ወቅታችሁ ሳትጨርሱ ወይናችሁን የምትሰበስቡበት ጊዜ ይደርሳል፤ ገና ወይኑን ሰብስባችሁ ሳትጨርሱ ደግሞ ዘር የምትዘሩበት ጊዜ ይመጣል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ያለስጋት ትቀመጣላችሁ።+ 6 በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤+ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤+ እኔም አደገኛ አውሬዎች በምድሪቱ እንዳይኖሩ አደርጋለሁ፤ በምድራችሁም የጦርነት ሰይፍ አያልፍም። 7 እናንተም በእርግጥ ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 8 አምስታችሁ 100 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ መቶዎቻችሁ ደግሞ 10,000 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።+
9 “‘እኔም ሞገስ አሳያችኋለሁ፤* ፍሬያማ እንድትሆኑና እንድትበዙ አደርጋችኋለሁ፤+ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ።+ 10 እናንተም ያለፈውን ዓመት እህል ገና በልታችሁ ሳትጨርሱ ለዘንድሮው እህል ቦታ ለማግኘት ያለፈውን ዓመት እህል ታስለቅቃላችሁ። 11 የማደሪያ ድንኳኔን በመካከላችሁ እተክላለሁ፤+ እኔም አልተዋችሁም።* 12 በመካከላችሁ እሄዳለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ሕዝቦቼ ትሆናላችሁ።+ 13 የግብፃውያን ባሪያዎች ሆናችሁ እንዳትቀሩ ከዚያ ምድር ያወጣኋችሁና ቀንበራችሁን ሰብሬ ራሳችሁን ቀና አድርጋችሁ* እንድትሄዱ ያደረግኳችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።
14 “‘ይሁን እንጂ የማትሰሙኝ ወይም እነዚህን ትእዛዛት በሙሉ የማትፈጽሙ ከሆነ+ 15 እንዲሁም ደንቦቼን ችላ የምትሉና+ ትእዛዛቴን በሙሉ ላለመፈጸም ድንጋጌዎቼን የምትጸየፉ፣* ቃል ኪዳኔንም የምታፈርሱ ከሆነ+ 16 እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፦ ዓይናችሁ እንዲጠፋና ሕይወታችሁ* እንዲመነምን የሚያደርግ የሳንባ ነቀርሳና ኃይለኛ ትኩሳት በእናንተ ላይ በማምጣት በጭንቀት እቀጣችኋለሁ። ዘራችሁን የምትዘሩት እንዲሁ በከንቱ ይሆናል፤ ምክንያቱም የሚበሉት ጠላቶቻችሁ ናቸው።+ 17 እኔም በእርግጥ ፊቴን አጠቁርባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ድል ያደርጓችኋል፤+ የሚጠሏችሁም ሰዎች ይረግጧችኋል፤+ እንዲሁም ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።+
18 “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም የማትሰሙኝ ከሆነ ለሠራችሁት ኃጢአት ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 19 ኃይለኛ የሆነውን ትዕቢታችሁን እሰብረዋለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣+ ምድራችሁን ደግሞ እንደ መዳብ አደርገዋለሁ። 20 ምድራችሁ ምርቷን ስለማትሰጥና የምድርም ዛፍ ፍሬ ስለማያፈራ ኃይላችሁን እንዲሁ በከንቱ ታባክናላችሁ።+
21 “‘ሆኖም እኔን መቃወማችሁን ከቀጠላችሁና እኔን ለመስማት ፈቃደኞች ሳትሆኑ ከቀራችሁ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 22 የዱር አራዊትን እሰድባችኋለሁ፤+ እነሱም ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤+ የቤት እንስሶቻችሁንም ይበሉባችኋል፤ ቁጥራችሁም እንዲመናመን ያደርጋሉ፤ መንገዶቻችሁም ጭር ይላሉ።+
23 “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም እርማቴን ባትቀበሉና+ እኔን መቃወማችሁን ብትገፉበት 24 እኔም እናንተን በመቃወም እመጣባችኋለሁ፤ ለኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25 ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን ስላፈረሳችሁ+ በላያችሁ ላይ የበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ። በከተሞቻችሁ ውስጥ ከተሰበሰባችሁ በመካከላችሁ በሽታ እልክባችኋለሁ፤+ እናንተም ለጠላት እጅ ትሰጣላችሁ።+ 26 የዳቦ እጥረት እንዲከሰትባችሁ+ በማደርግበት ጊዜ* አሥር ሴቶች በአንድ ምድጃ ብቻ ዳቦ ይጋግሩላችኋል፤ ዳቦውንም እየመዘኑ ያከፋፍሏችኋል፤+ እናንተም ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም።+
27 “‘ይሁን እንጂ በዚህም እኔን ለመስማት ፈቃደኛ ካልሆናችሁና እኔን መቃወማችሁን ከገፋችሁበት 28 በኃይል እቃወማችኋለሁ፤+ እኔ ራሴም ለኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29 በመሆኑም የወንድ ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴት ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ።+ 30 በከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉትን ቅዱስ ስፍራዎቻችሁን+ አጠፋለሁ፤ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁንም አስወግዳለሁ፤ በድናችሁንም አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻችሁ* በድን ላይ እከምረዋለሁ፤+ እኔም ተጸይፌያችሁ ከእናንተ ዞር እላለሁ።*+ 31 ከተሞቻችሁን ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፤+ መቅደሶቻችሁንም ባዶ አደርጋቸዋለሁ፤ የመሥዋዕቶቻችሁን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አላሸትም። 32 እኔ ራሴ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤+ በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁም በመደነቅ ይመለከቷታል።+ 33 እናንተንም በብሔራት መካከል እበትናችኋለሁ፤+ ሰይፍም መዝዤ አሳድዳችኋለሁ፤+ ምድራችሁ ባድማ ትሆናለች፤+ ከተሞቻችሁም ይፈራርሳሉ።
34 “‘በጠላቶቻችሁ ምድር ሆናችሁ ምድሪቱ ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች። በዚያን ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን መክፈል ስላለባት ታርፋለች።*+ 35 ምድሪቱ ትኖሩባት በነበረው ጊዜ በሰንበታችሁ ወቅት ስላላረፈች ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ ታርፋለች።
36 “‘ከእናንተ መካከል በሕይወት የሚተርፉትም+ በጠላቶቻቸው ምድር ልባቸው ተስፋ እንዲቆርጥ አደርጋለሁ፤ የቅጠል ኮሽታ እንኳ ያስበረግጋቸዋል፤ ከሰይፍ እንደሚሸሽ ሰው ይፈረጥጣሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ።+ 37 ከሰይፍ እንደሚሸሹ ሰዎች እነሱም ማንም ሳያሳድዳቸው እርስ በርሳቸው እየተደነቃቀፉ ይወድቃሉ። እናንተም ጠላቶቻችሁን መቋቋም ይሳናችኋል።+ 38 በብሔራት መካከል ትጠፋላችሁ፤+ የጠላቶቻችሁም ምድር ትበላችኋለች። 39 ከእናንተ መካከል የሚተርፉትም በሠሩት ስህተት የተነሳ በጠላቶቻችሁ ምድር ይበሰብሳሉ።+ አዎ፣ በአባቶቻቸው ስህተት የተነሳ ይበሰብሳሉ።+ 40 ከዚያም የገዛ ራሳቸውን ስህተት እንዲሁም አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተትና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ይናዘዛሉ፤+ እንዲሁም እኔን በመቃወም ታማኝ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አምነው ይቀበላሉ።+ 41 እኔም እነሱን ወደ ጠላቶቻቸው ምድር በማምጣት+ እቃወማቸዋለሁ።+
“‘ምናልባትም ያልተገረዘው* ልባቸው በዚያ ጊዜ ትሑት ይሆናል፤+ የስህተታቸውንም ዋጋ ይከፍላሉ። 42 እኔም ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳንና ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤+ እንዲሁም ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤+ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43 እነሱም ምድሪቱን ትተዋት በሄዱበት ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች፤+ ያለእነሱም ባድማ ሆና ትቆያለች፤ እነሱም ድንጋጌዎቼን ችላ ስላሉና ደንቦቼን ስለተጸየፉ*+ የስህተታቸውን ዋጋ ይከፍላሉ። 44 ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን በጠላቶቻቸው ምድር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ እርግፍ አድርጌ አልተዋቸውም፤+ ፈጽሜ እስካጠፋቸውም ድረስ አልጥላቸውም፤ እንዲህ ባደርግ ከእነሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ማፍረስ ይሆንብኛል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ። 45 አምላካቸው መሆኔን አስመሠክር ዘንድ ብሔራት በዓይናቸው እያዩ ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው+ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስለ እነሱ ስል አስባለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’”
46 ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካኝነት በራሱና በእስራኤላውያን መካከል ያስቀመጣቸው ሥርዓቶች፣ ድንጋጌዎችና ሕጎች እነዚህ ናቸው።+