ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
2 “በኤፌሶን ላለው ጉባኤ+ መልአክ+ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው+ እንዲህ ይላል፦ 2 ‘ሥራህን፣ ድካምህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም መጥፎ ሰዎችን መታገሥ እንደማትችል እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን+ ፈትነህ ውሸታሞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ። 3 በተጨማሪም በአቋምህ ጸንተሃል፤ ስለ ስሜም ስትል ብዙ ችግሮችን ተቋቁመሃል፤+ ደግሞም አልታከትክም።+ 4 ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል።
5 “‘ስለዚህ ከየት እንደወደቅክ አስታውስ፤ ንስሐም ግባ፤+ ቀድሞ ታደርገው የነበረውንም ነገር አድርግ። አለዚያ እመጣብሃለሁ፤ ንስሐ ካልገባህ+ መቅረዝህን+ ከስፍራው አነሳዋለሁ። 6 ያም ሆኖ አንድ የሚያስመሰግንህ ነገር አለ፦ እኔም የምጠላውን የኒቆላውያንን+ ሥራ* ትጠላለህ። 7 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል ለሚነሳ+ በአምላክ ገነት ውስጥ ካለው የሕይወት ዛፍ እንዲበላ እፈቅድለታለሁ።’+
8 “በሰምርኔስ ላለው ጉባኤ መልአክም እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ‘የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣’+ ሞቶ የነበረውና ዳግም ሕያው የሆነው+ እንዲህ ይላል፦ 9 ‘መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ይሁንና ሀብታም ነህ፤+ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይሁዳውያን ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ፤ እነሱ የሰይጣን ምኩራብ ናቸው።+ 10 ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ።+ እነሆ፣ ሙሉ በሙሉ እንድትፈተኑና ለአሥር ቀን መከራ እንድትቀበሉ ዲያብሎስ አንዳንዶቻችሁን እስር ቤት ይከታል። እስከ ሞት ድረስ ታማኝነትህን አስመሥክር፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።+ 11 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል የሚነሳ+ በሁለተኛው ሞት+ ከቶ አይጎዳም።’
12 “በጴርጋሞን ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ረጅም ሰይፍ+ የያዘው እንዲህ ይላል፦ 13 ‘የምትኖረው የሰይጣን ዙፋን ባለበት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ያም ሆኖ ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል፤+ ሰይጣን በሚኖርበት፣ እናንተ ባላችሁበት ቦታ በተገደለው+ በታማኙ ምሥክሬ+ በአንቲጳስ ዘመን እንኳ በእኔ ላይ ያለህን እምነት አልካድክም።+
14 “‘ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገሮች አሉኝ፤ የእስራኤል ልጆች ለጣዖት የተሠዉ ነገሮችን እንዲበሉና የፆታ ብልግና* እንዲፈጽሙ+ በፊታቸው ማሰናከያ እንዲያስቀምጥ ባላቅን+ ያስተማረውን የበለዓምን ትምህርት+ አጥብቀው የሚከተሉ በመካከልህ አሉ። 15 እንደዚሁም የኒቆላዎስን የኑፋቄ ትምህርት+ አጥብቀው የሚከተሉ ሰዎች በመካከልህ አሉ። 16 ስለዚህ ንስሐ ግባ። አለዚያ በፍጥነት ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በአፌም ረጅም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።+
17 “‘መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፦+ ድል ለሚነሳ+ ከተሰወረው መና ላይ እሰጠዋለሁ፤+ እንዲሁም ነጭ ጠጠር እሰጠዋለሁ፤ በጠጠሩም ላይ ከሚቀበለው ሰው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም ተጽፎበታል።’
18 “በትያጥሮን+ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖችና+ እንደጠራ መዳብ ያሉ እግሮች+ ያሉት የአምላክ ልጅ እንዲህ ይላል፦ 19 ‘ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ።
20 “‘ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ራሷን ነቢዪት ብላ የምትጠራውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን+ ችላ ብለሃታል፤ እሷም የፆታ ብልግና* እንዲፈጽሙና+ ለጣዖት የተሠዉ ነገሮችን እንዲበሉ ባሪያዎቼን ታስተምራለች እንዲሁም ታሳስታለች። 21 እኔም ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ እሷ ግን ለፈጸመችው የፆታ ብልግና* ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ አይደለችም። 22 እነሆ፣ የአልጋ ቁራኛ ላደርጋት ነው፤ ከእሷ ጋር ምንዝር የሚፈጽሙትም ከሥራዋ ንስሐ ካልገቡ ታላቅ መከራ አመጣባቸዋለሁ። 23 እንዲሁም እኔ የውስጥ ሐሳብንና* ልብን የምመረምር እንደሆንኩ ጉባኤዎቹ ሁሉ እንዲያውቁ ልጆቿን በገዳይ መቅሰፍት እፈጃለሁ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።+
24 “‘ነገር ግን ይህን ትምህርት ለማትከተሉ ሁሉና “የሰይጣን ጥልቅ ነገሮች”+ የሚባሉትን ለማታውቁ፣ በትያጥሮን ለምትገኙ ለቀራችሁት ይህን እላለሁ፦ በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሸክም አልጭንባችሁም። 25 ብቻ እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።+ 26 ደግሞም ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በብሔራት ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤+ 27 ይህም ከአባቴ የተቀበልኩት ዓይነት ሥልጣን ነው። ድል የነሳውም ሕዝቦችን እንደ ሸክላ ዕቃ እንዲደቅቁ በብረት በትር ይገዛቸዋል።*+ 28 እኔም አጥቢያ ኮከብ+ እሰጠዋለሁ። 29 መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’